Back to Front Page


Share This Article!
Share
ሃቅ የያዘው ማነው፣ የትክክለኛነት መመዘኛውስ ምንድነው?

ሃቅ የያዘው ማነው፣ የትክክለኛነት መመዘኛውስ ምንድነው?

ዶር. ዮሃንስ አበራ አየለ 12-28-18

ባለፈው ሰሞን ሁለት ቢድዮዎች አየሁ። እጅግ በተራራቀ ቦታ የተፈፀሙ ቢሆኑም መልእክታቸው ግን አንድ አይነት ነው። አንደኛው መቐለ ላይ የአቶ ዓምዶም ንግግር በጭብጨባ የተቋረጠበት ሲሆን ሌላኛው ደግሞ በአሜሪካ ንግግራቸው በጭብጨባና በግርግር የተቋረጠባቸው ወይዘሮ ጉዳይ ነው። ሦስተኛውና ከዚች አጭር ገለፃ አልፌ የማልሄድበት የኤል ቲቪ ጋዜጠኛ ቃለ መጠይቅ ነው።

በህወሓት ላይ ያላትን የከረረ አመለካከት የኢትዮጵያ ህዝብን "ወክላ" አቶ ሠራዊት ፍቅሬ አፍ ውስጥ ለመክተት በስሜት ተውጣ ስትታገል የነበረችው የኤል ቲቪ ጋዜጠኛ አርቲስቱ የኢትዮጵያ ህዝብ እዚያው ስቱድዮ ውስጥ እያለ መጥቶ የሚፋረደው እስኪመስለው ድረስ ስለወጠረችው አንዴ "ሌሎቹ ናቸው ያደረጉት" ይላል አንዴ ደግሞ የምትለው ነገር ልክ እንደሆነ ለመግለፅ የቃላት መረጣ ጭንቀት ውስጥ የገባበት አሳዛኝ ፍፃሜ ነው።  

Videos From Around The World

አፍ ያለው፣ ወይንም ሚድያውን የተቆጣጠረ፣ ወይንም ጉልበተኛ ሆኖ እንደልቡ ቢሰራ አሞጋሽ እንጂ ጠያቂ የሌለው ግለሰብ ወይንም ቡድን ራሱን የዩኒቨርሳል ሃቅ አራማጅ አድርጎ ከመቁጠሩ የተነሳ ከሱ የሚለየውን አመለካከት እንደ ዩኒቨርሳል ውሸት አድርጎ ይወስዳል። በተቃራኒው ላይ የሚወስዳቸው እርምጃዎችም የህግና ስርአት መስመራቸውን የሳቱ የሰውን ዲሞክራሲያዊ መብት የሚረግጡ ይሆናሉ።

አቶ ዓምዶም ሲናገር የነበረው የራሱ የግል ስሜት ይሁን፣ የፓርቲው አቋም ይሁን፣ የዶር. አብይ አመለካከትን ወገን ይዞ እያንፀባረቀ ይሁን ባይታወቅም ማወቁ ግን ለዛ ስብሰባና ዋና አላማው አስፈላጊ አልነበረም። ስብሰባው የተጠራው በኔ ግምት ሩቅ ለሩቅ ሆነን በማህበራዊ ሚድያ ከምንራኮት ተቀራርበን እስቲ በሰከነ መንፈስ እንደ ኢትዮጵያውያን እንከራከር፣ እንግባባም እንለያይም፤ ከዛም ሄደን ወገናችንን ሰለውይይትና መግባባት እናስተምር ተብሎ ነው። እንዲያውም በዚህ አጋጣሚ ፕሮፌሰር ህንደያን መመረቅ እፈልጋለሁ፦ "ብሩክ ኩን"!  

አቶ ዓምዶም ንግግሩን አራዝሞ ከሆነ ሰብሳቢ አለ፤ መድረክ ላይ የተቀመጠው ሰዓትና አጀንዳ ለመቆጣጠር ነው። የስብሰባው ዋናው አላማ የማይመቸንም ቢሆን ሃሳቡን በትእግስት አዳምጠን የራሳችን የመናገር እድል ሲደርስ ነጥብ በነጥብ ግን በአክብሮትና በስርአት ሃሳብ እንድናንሸራሽር ነው። እዛ የተሰበሰበው በእውቀትና በልምዱ ቀላል ሰው መስሎ አልታየኝም እዛው ባልኖርም። በጭብጨባ ሰው ሃሳቡን እንዳይጨርስ ካሰናከልን የሚሰጠው ግልፅ ትርጉም ተናጋሪ ለተናገረውና ሊናገር ነበር ተብሎ የተገመተውን ሃሳብ በሃሳብ ለመምታት አቅሙ አለመኖሩ ነው።  ስለዚህ ሃሳቡን በሃሳብ መምታት የማይቻል ከሆነ ሰው እንዳይሰማው ማድረግ ነው የወሰኑት ባለጭብጨባዎቹ። የምሁራን አንዱ ዋናው መገለጫቸው እየመረራቸውም ቢሆን የስብሰባ ስርአት ማክበር ነው።

ተሰብሳቢው የሰብሳቢውን ስራ የሚወስድበት ከሆነ አስተባባሪ የሌለውና የተለየ መፈክር የሚያሰማ ሰው የሚደበደብበት የአውራጎዳና ላይ ሰልፍ ከመሆን አይዘልም። የአማራ ክልል መሪዎች የአማራ ዳያስፓራውን በይፋዊው መግለጫቸው  እንዳሉት የልማት ድጋፍ ለመጠየቅ አሜሪካ ተገኝተዋል። መልካም ነው። ሁሉም ወደዛ ብቻ ቢያተኩር የምንቆራቆስበት ሳይሆን የምንግባባበት፣ የምንጋራውና የምንደጋገፍበት በቂ እድል ይኖረን ነበር። ልማት እኮ እንኳና ያንዲት የኢትዮጵያ ልጆች ቀርቶ አህጉር ተሻግረው ጠላት የነበሩትም አብረው እየሠሩ ነው።

የአማራ ክልል መሪዎች ያለባቸው ትልቅ ሃላፊነት አማራው ብዛት ስላለው በቁጥር ያነሱትን ግን በመብት ደረጃ ከአማራው እኩል የሆኑትን የራሳቸው ማንነት ያላቸውን ማህበረሰቦች ከማእከላዊ መንግስት በአደራ ተቀብሎ እያስተዳደረ መሆኑን ነው። ህምራ፣ አዊ፣ ኦሮሞ፣ ወዘተ ክልል መሆን ባለመቻላቸው እንጂ  እንደ ህዝብ ያላቸው መብት ግን ከማንኛውም ክልል ያነሰ አይደለም። ትግራይ ውስጥ ያሉት ኩናማና ሳሆዎችንም ይመለከታል። ልዩ ዞን ብለው ባለመጠየቃቸው ልዩ ዞን አልሆኑም። ከጠየቁ ግን "እናንተ ትግራዮች አይደላችሁም እንዴ? አብራችሁ ከኛ ጋር በአንድ ገበታ በልተን፣ ትግርኛ እንዲያውም ከኛ የበለጠ እየተናገራችሁ!" ተብለው አይወቀሱም፣ አይነቀሱም፣አይገሰሱም! የራስን የኖረ ጥቅም ለመጠበቅ የሌላውን መርገጥ ህጋዊም ሞራላዊም አይደለም።

የአማራ ክልል መሪዎች ስብሰባ እየመሩ እያለ በሰብሳቢው እንድትናገር እድል የተሰጣት አንዲት ወይዘሮ "እንኳን የትግሬን መንግስት ድራሹን አጠፋችሁልን፣ አሁንም ቀጥሉ፣ እንዳትለቋቸው፣ መሬታችንን አስመልሱልን፣ ከጉያችን ያሉትን የነሱ መልክተኞች ንብረታቸውን እያስቀራችሁ ወደዛ ድንጋይ መሬታቸው መልሳችሁ አባሩልን፣ ከመሃል አገር ምንም ነገር ወደ እነሱ እንዳያልፍ መንገድ በመዝጋትና በመውረስ በችጋር አምበርክኳቸው፣ ከህግደፍ ጋር ውል አስራችሁ ዙሪያቸውን ከባችሁ አስጨንቋቸው" ብላ ሰአታት ወስዳ ብትናገር ኖሮ አዳራሹን የሚያናውጥ ንግግሯን የሚያስቆም ሳይሆን የሚያስቀጠል ጭብጨባ ይደረግላት ነበር። የአርበኞች ናቸው የተባሉ አንድ አዛውንት፣ አርፈው ወጣቶችን ለሰላም እንዲቆሙ እንደመምከር "ትግሬን እንውጋ፣ እዚህ ያሉትን እናባርር" እያሉ ሲፎክሩ በወንጀል መክሰስ ቀረና በጭብጨባ ሲታጀቡ በቪድዮ በማየቴ ነበር ከላይ ላሰፈርኩት ግምት መነሻ የሆነኝ። ጊዜው በጣም ተቀይሯል ሳይሆን ቀይሯል። አርበኛ ሲባል ወገኑን ከውጭ ጠላት ለመከላከል የሚዋደቅ ይመስለኝ ነበር። አሁን አርበኛ የሚባለው ለካ "ወገን ገዳይ" እያለ የሚያቅራራውንም ያካትታል። ይህ በጊነስ ቡክ ያስመዘግባል።

ወይዘሮዋ የተናገረችው ነገር ግን ከተያዘው "መደበኛ እውነት" ያፈነገጠ ሆኖ ተገኘ። "ህዝቤ አለቀ" አለች እንባ እየተናነቃት። መቸም የሆረር ልብወለድ ፊልም ስክሪፕት ያጠናች ተዋናይ አትመስለኝ። እንኳንና ህዝብ አለቀ እየተባለ አንድ ሰው ሞተ ሲባል እንኳ ያስደነግጣል። "ህዝብ አላለቀም፣ የሞተ የለም" ብሎ መከራከር ያባት ነው። ህዝብ ማለቁ ሆድ እያወቀ አለቀ እያለ የተናገረውን ቢያልቅስ ለምን ትናገራለህ ብሎ ማፈን በመዝገበ ቃላት ውስጥ በትክክል የሚገልፀው ቃል የለም።

ቅማንቶችን በመፅሃፍ አንብቤ ወይንም ወሬ ሰምቼ አይደለም የማውቃቸው። በቅርበት የማውቅበትና የምተዋወቅበት በርካታ አጋጣሚዎች ነበሩኝ። አብረው ከሚኖሩት የአማራ ህዝብ ጋር የሚለያቸውም የሚያመሳስሏቸውም ነገሮች እንዳሉ ተገንዝቤአለሁ። የቅማንቱን ማህበረሰብ ስሜት የሚጎዱ በግዴለሽነት ሲነገሩ የኖሩ አባባሎች አሉ። እንግዲህ አንድ መሆን ጥሩ ነው። ካልተመቸ ሁለትም ሶስትም መሆንም ጥሩ ነው፤ ሰው መብቱና ክብሩ በሚገባ መጠበቁን እርግጠኛ መሆን እስከሚችልበት ድረስ። ቅማንቶች ራሳችንን እናስተዳድር፣ አብረን ስንሆን እየተናናቅና እየተጎረባበጥን ነው ሲሉ "አይ እናንተ እንዲህ አትሉም፤ ትግሬዎች እኛን እንድታዳክሙላቸው መክረዋችሁ ነው፤ የወልቃይትና ራያ ጥያቄ ስላነሳንባቸው እናንተን እንደ መቀልበሻ እየተጠቀሙባችሁ ነው" ብሎ በክልል ደረጃ አቋም መውሰድ አይጠበቅም አይመጥንምም።

ለአቅመ ሄዋን የደረሰች ልጃቸው መኝታ ለብቻየ ይዘጋጅልኝ፣ እቃዎቼንም ለብቻየ የምቆልፍበት ቁም ሳጥን ይሰጠኝ ብላ ስትጠይቅ ወላጆቿ እንኳን ደረስሺልን ብለው እንደመደሰት በንዴት ተነሳስተው "እነዚህ ባለጌ ጓደኞችሽ እየመከሩሽ ነው" ብለው ለራሱ እንደማያውቅ ህፃን ቢናገሯት የሚያተርፉት ነገር ቢኖር ቃላት መለዋወጥ፣ መደፋፈር፣ መደባደብ፣ ቤት ጥሎ መሄድና ሌላ ጣጣ መጎተት ነው። "እሰይ" ብለው ቢፈቅዱላት ግን የወላጅ ፍቅርና የራስ መተማመን ይኖራታል።

የወያኔ ፅሁፍ ነው የምታነቢው ብሎ ከእጇ ለመቀማት መታገልና፣ አንዱ "ተዋት" እያለ ይጮሃል ሌላዋ ባልቴት ከወንበርዋ ተነስታ "ወግድ በሏት" እያለች እጇን ታወራጫለች፤ በአለም በዴሞክራሲያዊነት ከኔ የሚልቅ የለም ከምትባለው አሜሪካ ውስጥ የኖሩ ተሰብሳቢዎች በመብት ጠያቂ ላይ እንዲህ ቅጥ ሲይጡ ማየት አስደማሚ ነው። ለካ "ድንጋይ አርባ አመት ዉሃ ውስጥ ቢቀመጥ አይርስም አይለሰልስም" የሚባለው ለዚህ ነው።

ህወሓት ናት የቅማንትን ህዝብ የምታነሳሳብን የሚለው እንደ እውነት ወስደን እንኳ ብናየው ቅንነት ሊኖር የሚገባው ከሁለት ወገን ነው። ሁለት ወገኖች፣ መነሻው ምን ይሁን ምን፣ ሽኩቻ ሲጀምሩ አንዱ ጨዋታውን ቅንነት በጎደለው አካሄድ መጫወት ከመረጠ ሌላኛው ወገን ጨዋታውን በቅንነት መስመር ያከናውነዋል ብሎ መጠበቅ የዋህነት ነው። በወልቃይትና ራያ ላይ ህዝቡ "ትግርኛ ቢናገሩም አማሮች ናቸው" እየተባለ በአገር ደረጃ ነውጥ ሲፈጠር "እሾህን በእሾህ" ብላ ህወሓት ተመሳሳይ ስራ ብትሰራ ተወቃሹ ማን ሊሆን ነው? የሚመረጠው በዛም "ቱታ" በዛም "ዘራፍ" ሳይሆን በሰከነ መንፈስ መነጋገርና መደጋገፍ ነው። ቅማንትና አማራው የየራሱ አስተዳደር ይዞ፣ የትግራይና አማራው የድንበር ላይ ህዝቦችን ከማባላት ይልቅ በጋራ ልማት ላይ ቢሰማሩ አይሻልም? በዚህ ህዝብን የሚጎዳ ግርግር ወንበሩን የሚያደላድል ጥቅመኛ ከሌለ ማለቴ ነው። ህዝብን በማዋጋት ስልጣኑን የሚያደላድል ግለሰብ ሆነ ቡድን የህዝብ መተባበር የሚያስፈራው ደካማ ፍጡር ነው።

በአቶ አምዶምና በወይዘሮዋ ላይ የደረሰው አንዲት የትግራይ ሴት  ጥያቄና አስተያየት  "ይህ አስተያየት ያንቺ አይደለም" ከተባለው ጋር ተመሳሳይነት አለው፤ ንግግሯ በጭብጨባ ወይንም በሰብሳቢው አለመቋረጡ በጎ ነገር ሆኖ። ህወሃት የሰጠቻት ማህተሙ የሚታይ የአቋም መግለጫስ ቢሆን የሆድን በሆድ ይዞ ለጥያቄው መልስ በመስጠት ብስለትን ማስመሰክር ይቻል ነበር። ህወሓት ከሆነችና እንዲህ እንደሚባል ገምታ ኖራ ከሆነ ሙሉ ስኮር አገኘች ማለት ነው።

"እኔ እንደምለው ካላልክ አላናግርህም፣ እንዲያውም ጠላቴ ነህ" አይነት አምባገነንነት ረዘም ያለ እድሜ አለው። የደርግና የኢህአፓ ካድሬዎች የሚያጣላ ነገር በሌለው አንድ ወጥ በሆነው ማርክሲዝም-ሌኒኒዝም አተረጓጎም ላይ ሲጠፋፉ እስከ የአማርኛ ቋንቋ ቀበሌኛ ዘየ ድረስ ወርደው ነበር። ኢህአፓዎች "የደርግ ካድሬዎች 'ወዛደር' የሚሉት ቅቤ እየበላ ፊቱ የወዛ ነው ብለው ሠራተኛው ላይ እያሻፉበት ነው" ብለው ያስቡ ነበር። በዚህም የተነሳ ማንም ግለሰብ ኢትዮጵያዊ "ወዛደር" ብሎ ከተናገረ የደርግ ደጋፊ ነህ ተብሎ የትም ቦታ በማንም የኢህአፓ አባል እርምጃ ይወሰድበታል። በኢህአፓ በኩል ትክክለኛ ስም ነው ብለው ያመኑት "ላብ አደር" ነበር። "ላብ አደር" ያለ ሁሉ ወገን ሆነ። "አቸናፊ" ያለ በኢህአፓ በኩል የህዝብ ወገን ሆኖ ሲመደብ "አሸናፊ" ካለ ግን የደርግ ደጋፊና የህዝብ ጠላት ሆኖ ይቆጠር ነበር።

አሁንም "ወያኔዎች" ያለ ሁሉ ሰይጣንም ቢሆን ወገን ሆኗል። ለረዥም ጊዜ በኢትዮጵያና በዳያስፓራው ውስጥ ወደተቃዋሚነት ጎራ በክብር ለመቀላቀልና ለመወደስ ብቸኛ ይለፍ ሆኖ የቆየው በሳይንሳዊ ትንተና ላይ የተመሰረተ ግምገማ ሳይሆን "ወያኔን እጠላለሁ" ማለት በቂ ሆኖ ቆይቷል። በአኒማል ፋርም የእንሰሳቱ ታማኝነት የሚመዘነው "ሁለት እግር መጥፎ፣ አራት እግር ጥሩ" የሚለውን መዝሙር በስሜት ከዘመሩ ነው።

ማንንም ሳትጎዳና ወንጀል ሳትሠራ ማንኛውንም የፓለቲካ ድርጅት አባል ወይንም ደጋፊ መሆን ችግር የለውም መብትም ነው። በንጉሱ ዘመን ተስቶህም ቢሆን "ንጉሱ ጥሩ ናቸው" ብትል የሪቮዎች እራት መሆን ነው፤ "ሞናርኪስት ሪአክሽነሪ" ተብለህ እንደ ስጋ ደዌ በሽተኛ ትገለል ነበር። በደርግ ጊዜ ወያኔ መሆን ጀግንነት ነበር፣ ደርግ መሆን ጭራቅ መሆን ነበር። አሁን ደግሞ "ደርጊስት" ወይንም  "ሞናርኪስት" መሆን አስሞጋሽ ሆኗል። መቼ አደብ ገዝተን የሁሉንም ሃሳብ በእኩልነት የምናንሸራሽርበት ጊዜ እንደሚመጣ ግራ ያጋባል።

 

Back to Front Page