Back to Front Page


Share This Article!
Share
ሕዝብን ማጥላላት፤ ማንቋሸሽና መግደል የተገባ ነውን?

ሕዝብን ማጥላላት፤ ማንቋሸሽና መግደል የተገባ ነውን?

ይዲድያ ብፁእ 08-03-18

ዛሬ ዛሬ አረማዊ ድርጊት ወይም ተግባር በአዋጅ እየተነገረ፤ በይፋ እየተለፈፈና አየተፈጸመ፤ ታላቅና አቻ በሌለው በፍቅር ካባ አጊጦ በመድረክ ላይ ተሽሞንሙኖና ተውረግርጎ የሚታይ የተለመደ አሳዛኝ የመድረክ ትእይንት ወይም ድራማ ሆኖ እየተመለከትን ነው።

የእግዚአብሔር ቃል፤ እግዚአብሔርን መፍራት የጥበብ ሁሉ መጀመሪያ እንደ ሆነ ያስተምራል። ይህን ትልቅና ግንበር ቀደም ጥበብ የሆነውን እግዚአብሔርን መፍራት በሚገባ ከተገነዘብነው፤ ሕዝብንና ግለ ሰብን ማክበር እንዳለብን የሚያሳስበን ነው። ትራሱን በእንባው ያርስና ያረጥብ የነበረው ስመ-ጥር የእግዚአብሔር አገልጋይ፤ ንጉሱና መዝሙረኛው ዳዊት፤ ሰውን ስበደል አንተን እበድላለሁ በማለት በቁጭት የጨኾውን ማንሣት ያስፈልጋል። በሰው ላይ የሚደረግ ትልቅ ይሁን ትንሽ በደል በእግዚአብሔር ላይ የሚደረግ በደል እንደ ሆነ ማወቅ አስፈላጊ ነው። ባንድም ሆነ በሌላ መንገድ በሰው ላይ የሚደረግ በደል በእግዚአብሔር ላይ የተደረገ በደልና ጥፋት ነው።

ለመሆኑ ሕዝብንና ሰውን ስንበድል፤ በተለይም ልባችን ለመጥላትና አልፎም ለመግደል ሲነሣሣ፤ በማን ላይ አመጻ ወይም ክፉ ነገር እያደርግን እንደሆነ እናውቀው እንሆንን? ቀዳሚ ጥበብ የሆነው እግዚአብሔርን መፍራት በዚህ ምግባራችን እያጨናገፍነው እንደ ሆነስ እንገነዘባለንን? ሕዝብንና ግለሰቦችን እየጠሉ፤ አብሶም ከምድር ገጽ ለማጥፋት እየከጀሉ፤ እግዚአብሔርን እፈራለሁ ማለት በእውን ይቻል ይሆን ወይ? በምሬትና በጥላቻ ከተሞላ ልብ የሚቀርብ ጸሎትስ ተሰሚነት ይኖሮዋልን? እግዚአብሔርስ ከእንዲህ ዓይነቱ ጥመት ከሞላበት ልብ የሚቀርብለት ጸሎት የሚያዳምጠው ይሆንን?

Videos From Around The World

ትናንት በፈሪሃ እግዚአብሔር የተሞላ የአገራችን ምድርና ሕዝብ፤ዛሬ ወንድም ወንዱሙን በሚያሳቅቅ ሁኔታ የሚያጠምድበትና የሚገድልበት ሆኖ ማየቱ ልብን የሚሰብርና የሚያሳዝን ከመሆኑ ባሻገር፤ እግዚአብሔር ይህን ዓለም በጽድቅ የሚፈርድ አምላክ አይደለምን? በተባለው ጻድቅ ፈራጅ አምላክ ዘንድም ጽኑ ቅጣት የሚያከናንብ ነው።

ማንም ይሁን ምን ሕዝብ ከእግዚአብሔር ቀጥሎ ክቡር ነው። የተከበረው ሁሉም ሕዝብ እንጂ የእኔ የምለው ሕዝብ ብቻ አይደለም። ይህ መሰረታዊ እውነት ለኔ ብቻ ሳይሆን በማሕበረ ሰብ ሳይንስ ሕግጋትም የተረጋገጠ ነው። በሰለጠነ ማሕበረሰብ የህዝብ ክቡሩነትና አይነኬነት በደማቅ ቀለም የተጻፈ ነው። ስለሆነም ሕዝብን የሚጠላና የሚያጥላላ፤ የሚንቅና የሚያናንቅ፤የሚገድልና የሚያስገድል በእግዚአብሔርም ሆነ በሰው ዘንድ የተወገዘና ፍርድም የሚጠብቀው ነው።

የትግራይ ሕዝብ እንደ ማንኛውም ሕዝብ ሊከበር የሚገባው እንጂ ልትጠላውና ልታጠፋው መነሳትና መከጀል ከጌታ ቃልና ከማሕበረ ሰብ ሕግ አንጻር ተቀባይነት የሌለው ነው። ይህ ሕገ ወጥነት ብቻ ሳይሆን ሕግ አልበኛነት ነው። ሕግ ወጥነት ሕግ እያለ ሕግን መጣስ ሲሆን፤ ሕግ አልበኛነት ግን ሕግ ከናካቴው ያለመኖር ነው። ሕግ አልበኞች በዚህ ተግባራቸውና ባህሪያቸው ከአራዊት ተርታ የሚያሰልፋቸው ነው። ሕግ ወጥነት፤ ሕግ ኖሮ ሕግን መተላለፍ ነው፤ ሊጣስ የማይገባው የተሰመረ ምልክት አለ፤ መስመሩን ወይም ምልክቱን ረግጦ ማለፍ ሕግ ወጥነት (transgression) ነው። ሕግ አልበኛነት ግን ሕግ የሚባል ጭራሽኑ የሌለውና እንዲሁ በደመ ነፍስ መኖርን የሚያሳይ ነው። በዚህም ሕግ አልበኛነት ከሕግ ወጥነት በእጅጉ የወረደና የዘቀጠ ነው።

ሕዝቦች በተገቢው ዓይን ከታዩ አንድ ናቸው። ይህ ከእግዚአብሔርና ከማሕበረሰብ ሳይንስ አኳያ ለሚያየው ሰው ብዥታ የሌለው እውነት ነው። ሃቁ በሕይወት ዘመኔ በተግባር ቀምሼዋለሁና፤ ሳልሳቀቅና ሳላመነታ መናገር እችላለሁ። በወጣነት እድሜዩ አስተማሪ ሆኜ በተመደክበት ቦታ የተለማመድኩትን ቀጥሎ በአጭሩ ለማቅረብ እሞክራለሁ።

ትምህርቴን ጨርሼ ወደ ተመደብኩበት ከተማ አስተማሪ ሆኜ ከመሄዴ በፊት ተማሪ ቤት እያለን ጥናት ሲበዛብን ፤ እንቶኔ ወደሚባል ቦታ ለምትሄድ ይህ ሁሉ ልፋት ለምን? የሚል ተስፋ አስቆራጭ ቃል ይሰነዘር ነበር። በወቅቱ የሥራ ምደባ ወይም ድልድል በመንግስት ድርጅት በእጣ ይካሄድ ስለ ነበረ፤ እንደ እድል ሆኖ እንቶኔ በተባለው ሩቅና ሕዝቡም ክፉ ነው ወደተባለው ከተማ ደረሰኝ ። እዚያስ አልሄድም ብዩ ጥቂት ካንገራገርኩና ካቅማማሁ በሃላ፤ ዘወትር ምክሩ መሬት ላይ ጠብ የምትለው ወዳጄና የልብ ጓደኛዩ፤ ሰማህ ወንድሜ፦ ሕዝብ ክፉና እብድ አይደለም፤ የሰው ወሬ መስማቱ አቁምና ሄዴህ እየው ፤ ነገሩ እንደሚወራው ሆኖ ካገኘኸው ሌላ አማራጭ እናፈላልጋለን፤ ሕዝብን ግን አክብረው እንጂ አታናንቀው፤ የሞያ ግዴታህም ብፍቅር ግለጽ፤ ሳይቆይ አጸፋው ከሕዝቡ ታገኘዋለሁ አለኝ። የወዳጄ ምክር ሰምቼ ወደ ምድብ ሥራዩ አቀናሁ፤ እንደ ደርስኩ ጥርጣሬዩ ሁሉ ወዲያውኑ ባነነ። ሕዝቡ በሚገባ ተቀብሎ አስተናገደኝ እንጂ አንድም ክፉ ነገር

አላጋጠመኝም። ከተማሪዎቼና ከሕዝቡም ጋር ጨውና ድልህ ሆንን፤ በሥራዬም ጓደኛዬ እንደ መከረኝ ተጋሁ እንጂ አልለገምኩም፤ የሕዝቡም እንክብካቤ በቃላት ልገልጸው አልችልም።

ያች የጓደኛዬ ምክር እስከ አሁን ድረስና ለወደፊቱ ስንቅ ሆናኝ እነሆ በሕዝብ ምንነትና ባሕሪ ምንም ግርታና ብዥታ እንዳይኖረኝ ከማድረግ ባለፈ፤ የተሟላ ስዕል እንዲኖረኝ አድርጋልኛለች፤ በዚህ አጋጣሚም ለቅንና ውጤታማ ምክር ለጋሹ ጓደኛዬ ባለበት ለትልቅ ውለታው ምስጋና ሳልገልጽ ለማለፍ አልፈልግም።

ወደ ፍሬ ጉዳዩ መለስ ስንል፤ መንግሥት በተለይም በህዝብ ላይ በሚነጣጠር በማንኛውም ድርጊት፤ እንቅስቃሴ፤ ዛቻና ወከባ፤ እንዲሁም በንግግርና በጽሑፍ በሚሰራጩ ሕገ ወጥ መልእክቶች በወንጀለኛ መቅጫው አካትቶ ተገቢው ቅጣት መውሰድ ይኖርበታል። ይህ ግን ወደ አንዱ ጫፍ ተለጥጦ የዜጎች ሃሳብን በነጻነት የማቅረብ፤ የመናገር፤ የመጻፍ፤ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብት እንዳይነካና እንዳይገድብ ልዩ ጥንቃቄ ማድረግ የተገባ ነው።

ወደ ተጨባጩ የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ዞር ስንል፤ ዘርን ወይም ማንነትንና ብሔርን መሠረት ያደረገ ጥቃት፤ ግድያ፤ ዘረፋ፤ ወከባና ማስፈራሪያ ማየት የየቀኑ ትእይንት ሆኗል። ይህ ለምን ሆነ? ለሚል ተገቢ ጥያቄ የተለያዩ መልሶች መስጠት ቢቻልም፤ ዋናዎቹ በሁለት ማቅረብ ይቻላል የሚል አሰተያየት አለኝ።

የመጀመሪያው ያለማወቅ (Ignorance) ሲሆን፤ በጠንካራና ተከታታይ ትምሕርት ሊቋቋሙት የሚቻል ነው፤ የዜግነት ትምሕርት በሚገባ በስርዓተ ትምህርት ተዘጋጅቶና ተቀርጾ ዜጎች መብታቸውና ግዴታቸው እንዲያውቁ ማድረግና ከዚያ አልፎ ወንጀል ከተፈጸመ ግን የሚያሰከትለው ቅጣት መግለጽና ማስተማር ያስፈልጋል።

ሁለተኛው ጥፋተኝነት የሚጥማቸውና የሚጣፍጣቸው በጣም ጥቂት ሰዎች፤ በተናጠል ይሁን ተደራጅተው የሚፈጹሙት ክፉ ድርጊት ነው። እንዲህ ዓይነት ዝንባሌ ያላቸው ግለ ሰዎች በእያንዳንዱ ሕዝብ መካከል የሚኖሩ ሲሆን፤ በቁጥራቸው፤ በቅርጻቸውና ይዘውት በሚወጡት ሰበብ ከሕዝብ ወደ ሕዝብ የሚለያይ ነው። እነዚህ በቁጥር ጥቂት፤ ነገር ግን በጥንቃቄ ሊታዩ የሚገባቸው ጽንፈኞች ናቸው። ለሁሉም ዜጋ የስነ ዜግነት ትምህርት መሰጠት የተገባ ሲሆን፤ በተገኘ አጋጣሚ ሁሉ ለእነዚህም ሳይሰለቹና ሳያቋርጡ የዜግነት ትምህርት መስጠት የተገባ ነው። ነገር ግን አፈንግጠው ሕግ አልባኛነታቸው በአደባባይ የሚገለጥ ከሆነ ጠንከር ያለ እርምጃ መውሰድ አስፈላጊ ነው።

መንግሥት፤ ማሕበረ ሰቡ፤ የሃይማኖት ተቋማትና የሲቪክ ማሕበራት አደጋው ከመድረሱ በፊት ተቀናጅተው መስራት አዳጋው እንዲቀንስ ሊያደርገው ይችላል። ከላይ ወይም ከውጭ ሲታይ ሕዝብን የሚያጥላሉት ቡድኖች ወይም ማሕበራት፤ ጥላቻውና ሁከቱን የሚያነሣሱት የራሳቸው ሕዝብ ሰበብ አድርገው ነው። አንድን ሕዝብ የሚጠሉበት ምክንያት በጅምላ ሕዝባችንን በድሏል በሚል ሰንካላ ምክንያት ነው። ዳሩ ግን እንወደዋለንና እንቆረቆርለታለን የሚሉት ሕዝብ ወደውት ሳይሆን፤ በራሳቸው የተሳሳተ አመለካከትና ስሜት ጠንቅና፤ ከዚያም ከዘለለ ለራስ ጥቅምና ዝና ለማግኘትና ለማትረፍ ነው።

እንወደዋለን ከሚሉት ሕዝብ ተነስቶ ገመዱን ወይም ክሩን ይዞ ወደ ታች ከሄዱ ወይም ከወረዱ፤ ሕዝቤ ከሚሉት ወደ ወረዳቸው፤ ከወረዳው ወደ ቀበሌአቸው፤ ከቀበሌአቸው ወደ መንደራቸው፤ ከመንደራቸው ወደ ቤታቸው በመጨረሻም ወደ ራሳቸው የሚደርስ ነው። ሕዝብ የሚጠላበትና የሚገደልበት የተበላሸውና የቆሸሸው ምንጭና ጥንስስ ይኼው ነው። አደጋው ለማንጠፍ ሆነ ለመቀነስ ይህ የተመረዘ ምንጭ የደም ጎርፍ ሆኖ ከመጉረፉ በፊት መከታተልና ተገቢ እርምጃ መውሰድ የሚጠይቅ ነው።

ሕዝብ ሕዝብን በምንም ተአምር ሊጠላና ሊያጠፋ አይነሣም፤ ይህ ከሕዝብ አጠቃላይ ባሕሪ ጋር የሚጻረር ነው። ዳሩ ግን ሕዝባቸውን አመካኝተው ሌላውን በሚጠሉ ሰዎች ተነሳስተው በርካታ ሰዎች በስሜት ሊያነሳሱና እንዲከተልዋቸውም ማድረግ ይችላሉ። አደጋው ተገቢ መረጃና እውነቱንም በማሳወቅና በማቅረብ፤ ወደ ህዝቡ በመሄድ ገና ከእንጭጩ ማስወገድና መቅጨት የሚቻል ነው። በሕዝብና በሕዝብ መካከል ብጥብጥና ሁከት ለሚፈጥሩት፤ መንግሥት፤ የሃይማኖት ተቋማትና ሲቪክ ማሕበራት በቃችሁ፤ አቁሙ ሊልዋቸው የተገባ ነው።

በአማራ ክልል አሁን አሁን ምንም ባላጠፉ ትግራዎት ኢትዮጵያዊያን ላይ በዘራቸው ብቻ ሲዋረዱ፤ ንብረታቸው ሲዘረፍ፤ ከዚህ ተርፎም በአሰቃቂ ሁኔታ በጠራራ ፀሐይ ሲገደሉ ማየትና መስማት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ዓይንና ጆሮ እንግዳ ከቶ አይደለም። ተቀባይነት የሌለው እንዲህ ዓይነቱ ሕገ ወጥ ተግባር የሚፈጸመው በአማራ ሕዝብ ስም በጥቂት ሕግ አልበኛ ፋኖዎች ነው። የእነዚህ ሕግ የለሽ ፋኖች ድርጊት የአማራ ሕዝብ እርምጃ እንዳይደለ ማወቅ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ የአማራ ሕዝብ በተለይም የአስተዳደር መዋቅሩ፤ በቃላት ከመቃወም አልፎ በተግባር ሊታገለው የተገባ ነው።

ምንም እንኳን የአማራ ክልል መሰተዳድር በሚያስተዳድረው ክልል ስር በትግራዎት ላይ ተደጋጋሚ የዘር ማጥቃት እርምጆች የተፈጸመ መሆኑ የሚያወቅ ቢሆንም፤ ከቃላት ማስጠንቀቂያ የዘለለ ተጨባጭ እርምጃ ሲወስድ ባለ መታየቱ በአሰተዳደሩ ባለሰልጣናት አሜኔታ እያጣንና እየተጠራጠርናቸው ነን። ከዚህ ተነሥቶ አንዱ ምናልባትኮ ከባለስልጣናቱም በዚህ ክፉ ተግባር የተሰለፉ ይኖራሉ፤ አይዞአችሁ በርቱ ግፉበት እያሉ እንቅስቃሴውን በድብቅ የሚመሩ ባለስልጣናትም ከትእይንቱ ጀርባ ይኖራሉ ቢል አይፈረድበትም። እጃቸው ጥፋተኛን ሲኮረክም ስለማይታይ፤ ሁላችንም እንዲህ ልናስብ እየተገደድን ያለንበት ወቅት ደርሰናል።

ተጠቂና የግድያው ሰለባ የሆነው የትግራይ ሕዝብ ለኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነት ባለው ጽኑ ፍቅር ምክንያት የሚያሳየው ትእግስት የሚደነቅ ሲሆን፤ ከልክ ካለፈ ትእግስትም ዳርቻ አለውና፤ መጥፎ ሁኔታ ከመፈጠሩ በፊት ድርጊቱ በሚፈጸምበት ክልል ተገቢ እርምጃ መውሰድ ሁለተኛ የሌለው ብቸኛ ምርጫ ነው። የትግራይ ክልል መንግሥት ዋናው ሥራ የክልሉ ሕዝብ ደህንነትና ሰላም መጠበቅ ስለሆነ፤ ይህን ሃላፊነቱ ፈጽሞ ለድርድር ማቅረብና ማመቻመች የለበትም። ዳሩ ግን በሰላም ለመኖር የሚደረግ ጥረት ሁሉ እስከመጨረሻው መሄድ የተገባ ነው።

ከዚህ በተጨማሪም የሃገሪቱ ፌዴራል መንግሥት ችግሩን የሩቅ ተመልካች ሆኖ እጁን አጣጥፎ የሚቀመጥ ሳይሆን፤ ጥፋቱ እንዳይባባሰና እንዳይፋፋም ሳያመቻምችና ሳያዳላ በአጥፊዎቹ ላይ ተገቢ እርምጃ መውስድ የሚገባው ነው። ጥቃት በሚፈጸምበት ክልል ያሉ የመገናኛ ብዙሃን ለወገኔ ይጠቅማል በሚል ደካማ ምክንያት የሞያ ግዴታቸው በሚጻረር መልኩ መረጃን ማጣመም ሆነ መደበቅ አይጠበቅባቸውም። መንግሥት በእንደዚህ ዓይነቶቹ ጋዜጤኞች ላይ እርምጃ መውሰድ አለበት። ያለንበት ዘመን የመረጃ ዘመን እንደሆነና፤ ጤናማ የመረጃ ዙውውር ከጤናማ የደም ዙውውር አይተናነስም በሚባልበት ጊዜ የተዘባ መረጃ ማቅረብና መደበቅ ትልቅ አደጋ እንደሚያስከትል ታውቆ በክልል ሆነ በፌዴራል መንግሥት በሞያው የተሰማሩ ሰዎች ይህንን እንዲያውቁ ማድረግና የጠበቀ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ ያስፈልጋል።

የክልል ባለስልጣናት ሆኑ ከእነርሱ ዝቅ ብለው በአስተዳደር መዋቅር የሚሰሩት፤ እየጠፋ ያለው ከወርቅና ከአልማዝ የበለጠና የከበረ የዜጋ ሕይወት ነውና፤ በቸልተኝነት ለሚፈጸመው ሁሉ ቀጥተኛ ተጠያቂዎች እንደሆኑ ማወቅ ይኖርባቸዋል። ተደጋጋሚ ይቅርታ ለቀጣይ ጥፋት በር ከፋች መሆን ከቶ አይኖርበትም። ይቅርታ ማለት ሥራየንና ሃላፊነቴን በብቃት መወጣት አልቻልኩምና ልውረድ ብሎ መልቀቅያ መጠየቅና ከሚሞቆው ወንበር ፈቀቅና ገለል ማለት ነው። ይቅርታ በይቅርታ ላይ እየተከመረና እየተቆለለ፤ ባለስልጣን በወንበሩ ተደላድሎ የሚኖርባት ሃገር ኢትዮጵያ ነች። ይህ አግባብነት የጎደለው ነው፤ ባለስልጣናት በሚያሰተዳድሩት ክልል በተደጋጋሚ በዘር ምክንያት ሰዎች ሲገደሉ በተደጋጋሚ ይቅርታ ጠይቀው፤ ለሚቀጥለው እርምጃ ይቅርታ እስኪጠይቁ ይጠበቃሉ እንጂ በእነርሱ ላይ ምንም እርምጃ አይወሰድም። ይህ ግፉና ጥፋቱ እንዲጦዝና እንዲጨምር ያደርገዋል እንጂ አያበርደውም፤ ሊገታውም አይችልም። እየባሰና እየጠነከረ የመጣው የዘር ጥቃት አንዱ ችግርም ይሄ ነው። ባለስልጣናት እነርሱ በሚያስተዳደርበት ክልል ሰባ ጊዜ ሰባት ሰዎች ቢገደሉ፤ ሰባ ጊዜ ሳበት ይቅርታ ጠይቆ ምሕረት ይደረግላቸው ይሆን ወይ? ይህኔ ያ ሕዝብ ሙሉ በሙሉ ከምድር ገጽ ይጠፋል።

ኢትዮጵያ እንደ ሕብረ ብሔራዊት አገርነትዋ ሕዝቦችዋ ተመካክረው፤ ተዋድደው፤ ተፈቃቅደውና ተቻችለው ባወጡት ሕገ መንግሥት ጥላ ሥር የመታደደር መብት፤ ግዴታና ሃላፊነት ያላቸው ናቸው። በምድሪቱ በየትኛውም ክልል በሚፈጠር ተግዳሮት ላይ በሕብረት መዝመትና ችግሩን መቅረፍ ይጠበቅባቸዋል። በዚህም የፈዴራል መንግሥቱ ሥራና ተግባር ከፍ ያለ ነው።

ዜጎች ምንም እንኳን አጠቃላይ መብታቸው ሊጠበቅላቸው የተገባ ቢሆንም፤ በህዝቦች መካከል ግጭትና እልቂት መፍጠር ግን መብት እንዳይደለ ሊያውቁ ይገባል ። ዴሞክራሲ መብትንና ግዴታን የሚያካትት እንጂ መብት ብቻ የሞላው አይደለም። ሁለቱም የዴሞክራሲ መስተጋብሮች አንድ በአንድ የሚገለጹ ሳይሆኑ ባንድ ላይ የተገመዱ ወይም የተፈተሉ ናቸው። መብቱ እንዲከበረለት የሚሻ ሰው፤ በዚያችው ቅጽበት ግዴታው ማክበር የሚጠበቅበት ነው።

መብቴ ይከበረልኝ የሚል ሰው፤ የሌላው ሰው መብት እያከበርኩኝ ነኝ ወይ ማለት አለበት፤ ይህም ሊወጣው የተገባው ግዴታው ነው። ዴሞክራሲ የመብትና የግዴታ ውሁድና ቅንብር ነው። ሁለቱም ለየቅል ቢሆኑም በዴሞክራሲ ትግበራ ግን የማይነጣጠሉ ግብአቶች ናቸው። በዴሞክራሲ ማእቀፍ፤ መብት ያለ ግዴታ ስድነት ወይም ሕግ አልበኝነት ሲሆን፤ ግዴታ ያለ መብት ደግሞ ባርነት ነው።

ዴሞክራሲ መብትና ግዴታን ሚዛኑ በጠበቀ መንገድ የሚያስኬዱበት መሳርያ ነው። ሕዝብ በሰላም መኖር የሚችለው ሁሉቱም የዴሞከራሲ ግብአቶች ተዋድደውና ተጣጥመው ሲተረጎሙ ነው። ዴሞክራሲ ሰው፤ ሰው በመሆኑ የሚኖረው እንጂ ማንም በችሮታ የሚሰጠው አይደለም። አጠቃቃሙ ግን እውቀትን የሚጠይቅ ነው። በውስጡ በርካታ ዝርዝር ጉዳዮች ያቀፈና አያሌ መስተጋብሮች የሚያካትት ስለሆነ በጥንቃቄ በእያንዳንዱ ዜጋ ሊታወቅ የተገባ ነው።

ዘጎች መብታችን እንዲከብርልን የምንሻ እንጂ፤ ግዴታችን እንድንወጣ የማንፈልግ ነን። በዴሞክራሲ ሚዛን የመብትና ግዴታ ክብደት ወደ አንዱ ካዘነበለና ካጋደለ አደጋው የከፋ ይሆናል። ሁሉቱም ተሰተካክለውና ሚዛናቸው ጠብቀው ከተቀመጡ ግን ሕዝብ ሰላም ይሆናል።

ነገሬን በቃለ እግዚአብሔር እንደ ጀምርኩ፤ በቃለ እግዚአብሔር ባሳርግ መልካም ይሆናል። ሕያው ቃሉ በዮሐንስ መልእክት ላይ ወንድሙን የማይወድ ነፍሰ ገዳይ ነው ብሎ ቁርጣችንን ነገሮናል። ወንድምን ያለመውደድ ነፍስ ገዳይነት ከሆነ፤ ሕዝብን ማጥፋትና መግደል ምን ሊሆን ነው? ደግሞም ወንድምን ያለመውደድ ማለት መጥላት ማለት ላይሆን ይችላል። አልወድህም ካልኩ ያለመውደዴን እየገለጽኩ እንጂ እጠላሃለሁ ማለቴ አይደለም። አንድን ሰው ሳይወዱት ላይጠሉት ይችላሉ። ጥላቻ ያለ መውደድ ጣራ ወይም ጥግ ነው። ጥላቻ ካለ ማመውደድ በእጅጉ ከፍ ያለ ነው። ወንድሙ ያልወደደ በእግዚአብሔር ፊት ነፍስ ገዳይ ነው የሚያስብለው ከሆነ፤ ጠላትነት ምንኛ የሚያስኮንን ይሆን? አሁን በሃገራችን ነግሦ የምናየው ወንድምን ያለመወደድ ያይደለ ወገንን ጠልቶ መግደልና ማሳደድ ነው። እንደ ሃይማናተኞችና አማኞች ተጠያቅነታችን በዚህ ምድር በምንኖረው አጭር ጊዜ ብቻ ሳይሆን ፤ማብቂያ በሌለው ዘላለምም ነውና እናሰተውል። ወንድሞቻችንን እንውደድ እንጂ አንጥላ!! ከወደድናቻው ጥላቻ አይጠጋንም አይነካካንምም፤ ህዝብን ሆነ ሰውም በሰበብ አስባቡ አንገድልም። በተለይ አማኞች የሚመሩትና የሚኖሩት በጌታቻውና በአምላካቸው ሕያው ቃል ነውና፤ ምን እያደርግንና እየፈጸምን እንዳለን ቆም ብለን እናሰላስል!!

የእግዚአብሔር ልጆችና የዲያብሎስ ልጆች ተለይተው የሚታወቁት በዚሁ ነው፤ ጽድቅን የማያደርግና ወንድሙን የማይወድ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም። ዮሐ መልእክት 1፡10

Back to Front Page