Back to Front Page


Share This Article!
Share
አንደራደርም

አንደራደርም!

ይሁን ታፈረ 09-05-18

በአሁኑ ወቅት በአገራችን እየመጣ ያለውን ለውጥ ባልተገባ መንገድ አቅጣጫ ለማሳት የሚሞክሩ የግል ጥቅመኞች በአንዳንድ አከባቢዎች ህገ ወጥነት እንዲሰፍን በማድረግ እንዲሁም ህግና ስርዓት እንደሌለ ለማስመሰል ሲጥሩ ይስተዋላል። ነገር ግን እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ ተቀባይነት የሌለው ነው።

ስለሆነም መንግስት እንደ መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስከበር ቁርጠኛ መሆኑን በአቋምም ይሁን በተግባር ይህንኑ በግልፅ እያረጋገጠ ይገኛል። በቅርቡ በፌዴራል መንግስት አማካኝነት የህግ የበላይነትን ለማስከበር የተወሰዱ አገር አቀፍ እርምጃዎችን እንዲሁም ክልሎች እየወሰዱት ያለውን የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ተግባሮች አስረጅዎች ናቸው።

በተለይ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በኢትዮጵያ ሶማሌና መሰል ክልሎች አኳያ የተወሰዱት የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ተግባሮች አገራችን ውስጥ ለህግ ልዕልና የተሰጠውን ቦታ የሚያመላክት ነው። ይህ ሁኔታ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ህብረተሰቡም በህግ የበላይነት ላይ አንደራደርም! የሚል ጠንካራ አቋም በመያዝ የድርሻውን መወጣት ይኖርበታል።

Videos From Around The World

ህብረተሰቡ እዚህ አገር ውስጥ ለሚከናወኑ ማናቸውም ጉዳዩች ዋነኛ ተዋናይ ነው። ያለ እርሱ ተሳትፎ ምንም ነገር እውን ሊሆን አይችልም። ህብረተሰቡ የስርዓቱ ዋነኛ ባለቤት በመሆኑም ለውጡ በአግባቡ እንዲከናወን ከፍተኛ ኃላፊነት አለበት። መንግስት የህዝቡን በሰላም ወጥቶ የመግባት ስራዎችን ያከናውናል።

ይህን የሚያደርገው የተጀመረውና በትክክለኛ መንገድ እየተመራ ያለው ለውጥ እንዳይደናቀፍ ካለው ጽኑ ፍላጎት በመነሳት ነው። ህብረተሰቡ መንግስት የያዘውን ህግና ስርዓትን የማስከበር ሃላፊነትን በመደገፍ አንዳንድ ህገ ወጦችን አደብ ለማስገዛት ህግን በማስከበር ዙሪያ የበኩሉን አስተዋጽኦ ካደረገ ለውጡን ለማስቀጠል የሚያደርገውን የራሱን ጥረት ማገዝ ይችላል።

በስራ ላይ ያለው የህገ መንግስት የህጎች ሁሉ የበላይ ህግ ነው። ማንኛውም ህግ፣ ልማዳዊ አሰራር እንዲሁም የመንግስት አካል ወይም ባለስልጣን ውሳኔ ከህገ መንግስቱ ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈፃሚነት አይኖረውም። ማንኛውም ዜጋ፣ የመንግስት አካላት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ሌሎች ማህበራት እንዲሁም ባለስልጣኖቻቸው ህገ መንግስቱን የማክበርና ለህገ መንግስቱ ተገዥ የመሆን ኃላፊነት እንዳለባቸው ግልጽ ነው። ይህን የህግ የበላይነት አለመፈፀምና ለድርድር ለማቅረብ አይቻልም።

አገራችን ሰብዓዊ መብቶችን የምታከብረው የምትከተለው ህግና ስርዓት ስለሚያዛት ብቻ ነው። በተለይም በአሁኑ ወቅት ለውጡ አቅጣጫውን እንዳይስት ካላት ፍላጎት በመነሳት ነው። ህግና ስርዓቱ ደግሞ በህዝቦች በበርካታ መስዕዋትነት የመጣ ነው። ስለሆነም ሰብዓዊ መብቶችን በማይነካና ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ የህግ የበላይነትን የማስከበር ስራ ወሳኝ ነው። እርግጥ የህግ የበላይነትን ማክበር ለህዝቡ በተለይም ለወጣቱ የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ ነው።

የህግ የበላይነት ሲከበር ወጣቶች በህግ በተደነገገው መሰረት በየደረጃው ተጠቃሚ ይሆናሉ። በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ሁሉም ዜጋ በማንኛውም የምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴ ውስጥ የመሰማራትና ለመተዳደሪያው የመረጠውን ሥራ የመከወን መብት እንዲሁም በመንግሥት ገንዘብ የሚካሄዱ ማህበራዊ አገልግሎቶችን በእኩልነት የመጠቀም መብት እንዲኖረውም ያደርጋል።

ሕዝቦች የኑሮ ሁኔታቸው የመሻሻልና የማያቋርጥ እድገት የማግኘት መብት እንዲኖራቸውና በፈለጉበት አካባቢ በነፃነት የመዘዋወር መብት እንዲኖራቸው ያደርጋል። በብሔራዊ ልማት የመሳተፍ፣ በሚቀረፁ ፖሊሲዎችና ኘሮጀክቶች ላይ አስተያየት በመስጠት ተጠቃነታቸውን ያረጋግጣሉ።

ሰላም ተፈጥሮ በሚኖር ልማት የዜጐች እድገትና መሰረታዊ ፍላጐቶችን ይሟላሉ። መንግሥት የሚያወጣቸው ፖሊሲዎችና የሚያደርጋቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የአገሪቱን ሕዝቦች ተጠቃሚነት መብት እንዲያስከብሩ ማድረግም ይቻላል።

የህግ የበላይነት ዜጐች በመንግሥት ገንዘብ በሚካሄዱ አገልግሎቶች በእኩልነት እንዲጠቀሙም ምቹ ሁኔታዎችን ይፈጥራል። ስለሆነም የህግ የበላይነት በአስተማማኝ ሁኔታ ሲከበር ነው። የህግ የበላይነቱ ሁሉንም ዜጎች በእኩል ዓይን የሚመለከትና የተጀመረውን ለውጥ ከማስቀጠል አኳያ በቂ ግንዛቤ ይዞ ንቀሳቀስ ይገባል። በተለይ ወጣቱ በዚህ ረገድ የበኩሉን ሚና መወጣት ይኖርበታል።

ወጣቱ በአሁኑ ሰዓት የላቀ ተጠቃሚ ለመሆን ቁርጠኛ አቋም ይዞ ከመንግስት ጋር መስራት አለበት። ይህን በማድረግ በአገሩ ሰርቶ መለወጥ የሚችልበትን ዕድል ማመቻቸት ይችላል። ለዚህ ደግሚ ሰላማዊ ምህዳር በአገሪቱ ውስጥ እንዲፈጠር የአንበሳውን ድርሻ መወጣት ይኖርበታል። የህግ የበላይነት እስከተረጋገጠ ድረስ ፍትሐዊ የሃብት ክፍፍልንና ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንደሚቻል መገንዘብ ይገባዋል።

ወጣቱ ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ ይህን የህግ የበላይነትን የማስከበር ጉዳይ ችላ ይለዋል ተብሎ አይታሰብም። እንዲያውም በአንዳንድ አካባቢዎች ህግና ስርዓትን የሚጥሱ አካላትን በጨዋነት ለፖሊስ አሳልፎ እየሰጠ ነው። ይህም ነገ ትልቅ የዕድገት ባለቤት ለመሆን ያለመው ወጣት ዜጋ፤ ትኩረቱን ያደረገው ሰላምን ለማምጣት መሆኑን ያስገነዝበናል።

ወጣቱ ሁከትን እየተጠየፈ ቢሆንም፤ አንዳንድ አካላት ለህግ የበላይነት ባለመገዛት ሊያስቱት እንደሚሞክሩ መገንዘብ አለበት። እነዚህ ጥቂት አካላት ጥቅመኞችና ለውጡን የማይፈልጉ ናቸው። እናም በተቻላቸው አቅም የለውጡ እንቅፋት ሆነው ይቆማሉ።በዚህም ወጣቱን በማደናገር እርሱ ያመጣውን ለውጥ ባለማወቅ እንዲጻረረው ለማድረግ ስሞክሩ እያስተዋልን ነው።

ስለሆነም ወጣቱ ይህን ሃቅ መገንዘብ አለበት። በእነዚህ ጥቂት ጥቅመኛ ኃይሎች ባዶና የአሉባልታ አጀንዳ አራማጅነት የህግ የበላይነት እንዳይጣስ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርበታል። በአሁኑ ሰዓት መንግስት የወጣቱን ተጠቃሚነት በለውጡ ሂደት ይበልጥ ለማረጋገጥ እየሰራ ነው። ይህ ስራም ተገቢውን ትኩረት አግኝቶ ለወጣቱ ስራ ፈጣሪ የሆኑ ጉዳዩች ተመቻችተዋል። ይህም ተጠቃሚነቱን ከፍ የሚያደርገው ስለሆነ ለውጡን በንቃት መጠበቅ ይኖርበታል።

ስለሆነም የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ርብርብ የህብረተሰቡ በተለይም የወጣቱ ሚና ከፍተኛ መሆን አለበት። ወጣቱ በቅድሚያ ራሱ የህግ የበላይነትን በማክበር ለሌሎች አርአያ ሆኖ መሰለፍ ይጠበቅበታል። ቀጥሎም አቻዎቹ ህግና ስርዓትን አክብረው እንዲንቀሳቀሱ ማድረግ አለበት። እስካሁን ያለው የወጣቱ ህግን የማስከበር ሁኔታ የሚበረታታ ቢሆንም፤ አሁንም በህግ የበላይነት ላይ አንደራደርም! የሚል አቋሙን በማጠናከር ሰላምን በየቀየው አስተማማኝ እያደረገ ተጠቃሚነቱን ማስፋት ይኖርበታል።

 

Back to Front Page