Back to Front Page

11/11/11 እና የኮ/ል አብይ እርምጃ

 

 

11/11/11 እና የኮ/ል አብይ እርምጃ

 

ቀለበት ታዬ

 

ከካሳንቺስ

 

ሐምሌ 14/2011

 

 

የሲዳማ ህዝብ የራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄው በህገመንግስቱ መሰረት ጠይቀን በትእግስት ጠብቀናል የማይመለስ ከሆነ ራሳችን ሓምሌ አስራ አንደኛው ወርና በአስራ አንደኛው ቀን (11/11/11) እናውጃለን ብሎ በአንድ ድምፅ በወሰነው መሰረት ተግበራዊ ለማድረግ ቢንቀሳቀሰም በተባለው ቀን እውን ማድርግ አልተቻለም፡፡ አሁንም ግን ውሳኔው ተገባራዊ ለማድረግ በትግል እንደሆነ ይታወቃል።

 

የሲዳማ ህዝብ የራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ በትክክል መመለስና በግዜው እልባት መስጠት እየተቻለ ከህዝብ ጋር እልህ የገባው የኮ/ል አብይ መንግስት በአገሪቱ ፓርላማ ላይ እንደ ሶማሊ ክልል በሐይል ልካችሁን እናስገባለን ብሎ እንደፎከረ ይታወቃል። እግረ መንገዱ በሶማሊ ጣልቃ ገብቶ እንደ ነበረና ሐይል ተጠቅሞ የመንግስት ግልበጣ መፈፀሙን በግላጭ አመኗል። ሕገመንግስታዊው የራስን በራስ የማስተዳደር መብትን በክልሉ መጣሱ በራሱ አንደበት ተጋልጧል።

 

Videos From Around The World

ብዙ ሰው የኮ/ል አብይ ቡዱን ስልጣን ከያዘ በኋላ ሶማሊ ክልል ብቻ ጣልቃ የገባ ይመስላቸዋል። ነገር ግን መጀመርያ ጣልቃ የገባው ደቡብ ክልል የሚመራው ደህዴን ድርጅት ውስጥ ነው። በሃይለማርያም ተባባሪነት ሽፈራው ሸጉጤንና ስራጅ ፈርጌሳን ከድርጅት ሊቀመንበርነትና ምክትል ሊቀመንበርነት አውርዶ አብሮ አደጉና ሲያስነጥስ የምታስነጥሰውን ሙፍርያትን ሊቀመንበር አድርጎ በመሾም ነበር፡፡ ይህንን በማድረግ በኢህዴግ ውስጥ ሦስት ድርጅቶችን በመቆጣጠር ከህወሓት የሚመጣን ተቃውሞ በማስቀረት ለሁሉ ግዜና በእርግጠኝነት በሱ ፍላጎት ብቻ በድምፅ የሚያሸንፍበትን የውስጠ ግንባር ግልበጣ በማድረግ አስተማማኝ ሁኔታ ፈጥሯል። ቀጥሎም ህወሓት በአጋር ድርጅቶች በኩል ይመጣብኛል ብሎ ሰለሰጋ የመንግስት የሃብት ምንጭና ማስፈራርያ ተጠቅሞና በድርጅቶች ውስጥ የመከፋፈል ስራ በመስራት ሁሉም ቦታ እጁን አስገብቶ ፈትፍቷል። በቅርቡ አሟሟታቸው ግራ የሚያጋባው ዶ/ር አምባቸው (ነብስ ይማርና) ይተካሉ የተባሉትን ቀርተው፣ ያልተገመቱትና የራሳቸውን ወዳጅ ሻለቃ ተመስገን ጥሩነህን በደመቀ መኮንን በኩል ስራ አስፈፃሚ እንዲሆኑ አስደርገው የአማራ ህዝብን ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ተጋፍተው ለክልል አስተዳዳሪነት እንዲታጩ አስደረጉ።

 

በመቀጠልም የደህዴን ማ/ኮሚቴ ስብሰባ አዲስ አበባ እንዲደረግ አድርገው በቅርብ ርቀት እየመሩና ሲያሰኛቸው ደግሞ ገባ እያሉ እያስፈራሩና እያባበሉ ሁኔታውን ውስብስብ አድርገው ስብሰባው አለቀ። ደህዴንም መግለጫ አወጣ ተባለ፡፡ ነገር ግን የደህዴን መግለጫ ከማለት የኮ/ል አብይ መግለጫ ቢባል ይሻላል። በውይይቱ ልዩነት የነበራቸውና የተከራከሩ የማ/ኮሜቴዎችን ድምፅ ሸፋፍኖ በስልት አንድ ናቸው እንድንባል በሚል ምክንያት ስብሰባውን በፍፁም የማይገልፅ መግለጫ ተሰጠ።

 

ሐምሌ አስራ አንድ ሲደርስም የፀጥታ መዋቅራቸውን ተጠቅመው እንዴት ሐዋሳ ላይ የሲዳማ ጉዳይ ወደ ህውከት እንደሚቀይሩት አቅደውና አፅድቀው ሁሌም አገር ቤት አተራምሰው ወጣ እንደሚሉት አስመራ መኪና ሲነዱና በለስ ሲበሉ ታዩ። የኢትዮጵያ ህዝቦችና የዓለም ማሕበረሰብ የሲዳማ ህዝብ ጩኸት እንዳይሰሙ ኢንተርኔትና ቴክስት ብቻ ሳይሆን ስልክ ሁሉ ዘግተው እንደ ለጋጣፎው አልሰማሁም ለማለት ከዋናው የጭካኔ መምህራቸው ኢሳያስ አፈወርቅ ዘንድ ለመምክር ሄዱ። በሃዋሳና አካባቢው ህውከት በርክቶ ብዙ ሰዎች እንደ ሞቱ ከአከባቢው ሸሽተው አዲስ አበባ የመጡት እየተናገሩ ነው። በመጀመርያው ቀን ሮይተርስና ሌሎች የውጭ ሚድያዎች በሃዋሳ ከተማ ከሦስት በላይ የሞቱና ከአስራ ሦስት በላይ የቆሰሉ እንዳሉ ገልፆ ነበር። አሁን በቅርቡ ደግሞ ሁኔታው ተባብሶ ከ 17 በላይ ሰዎች እንደሞቱ በውጭ ሚድያ እየሰማን ነው። ከአካባቢው የሚወጡ መረጃዎች ግን ወደ 53 ሰዎች እንደተገደሉና ወደ 79 ሰዎች እንደቆሰሉ ነው። ከሐዋሳ ከተማ ውጭ ያለውን ሁኔታ ግን ዜና አድርጎም የዘገበው የለም። በሁሉም የሐዋሳ ዙሪያ አካባቢ የተኩስ ድምፅ እስካሁን እንዳለ ግን እየተነገረ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ የመከላከያ ሰራዊት ከተወሰኑ ቀናት በፊት ጀምሮ ሻሸመኔ ሰፍሮ እንዲቆይ ተደርጎ መቆየቱ የአደባባይ ምስጥር ነው። የሲዳማ ተወላጅ የሆኑ የሰራዊቱ አባለት ደግሞ ህዝብቻን አንወጋም እያሉ ከነመሳርያቸው ከህዝቡ ጎን እንደተቀላቀሉ ከወደ መከላከያ በሰፊው እየተወራ ነው።

 

የአገር ቤት ሚድያዎች ግን ቦታው ድረስ ሂደው መዘገብ ሲገባቸው ሌላ ስራ ላይ ተጠምደዋል። ለምሳሌ የኮ/ል አብይ ተሟጋች የሆነው ኤል ቲቪ ሽምጡን ገትሮ የሲዳማ ፓርቲ ሐላፊዎችን ቁምስቅላቸውን አሰይቷቸዋል። የጋዜጠኛ ሙያ ይቅርና ሽታ በሌለው አግባብ ጥያቄ ሳይሆን አቋም ይዞ ተከራክሯቸዋል። ሐላፊዎቹ ጥያቄቻው ሰላማዊ መሆኑን ቢያስረዱም፣ ሐዋሳ የሁሉም መሆን ትችላለች ቢሉም የተሰጠው ተልእኮ በግልፅ በሚያሳውቅበት መንገድ ጋዜጠኛው ግግም ብሎ እየተናገሩ እያሉ በመሃል አስር ግዜ እየገባ መልእክት እንዳያስተላልፉ ሲያደናቅፋቸው ታይቷል። የሚገርመው ነገር ደግሞ ለምን አትታገሱም? ሲላቸው ስንት ዓመት ታግሰናል ቢሉትም ፌደራል መንግስት አታስቸግሩት! በማለት የተሰጠው ተልእኮ እየገለፀ መሆኑን በሚያሳብቅ ሁኔታ ወርፋቸዋል። የፈዴራል መንግስት ፓርላማ ላይ ጠ/ሚኒስትሩ እንደ ሶማሊ እናንተንም ልካቹሁ እናስገባለን ሲል ምንተሰማቹሁ ብሎ እንደ መጠየቅ ፈንታ የኤልቲቪው ጋዜጠኛ የተጋው በታዘዘው ጥያቄ ብቻ ነበር።

 

ሌሎች ደግሞ ረብሻ በተቀሰቀሰባቸው አካባቢዎች ዘረፋ ተፈፀመ እያሉ ነገሩ በሃይል እንዲፈታ ሽፋን እየሰጡ ነው። ተጠያቂው መንግስት እያለ ወጣቱን እየወነጀሉ ነው። ነግር ግን ደቡብ ክልል እንዳይፈራረስ ከተፈለገ ሁኔታው መፈታት ያለበት በሃይል ሳይሆን በውይይትና በውይይት ብቻ ነው። ነገር ግን አሁንም እየተሰማ ያለው ነገር ወላይታ አካባቢም ሆን ተብሎ ብጥብጥ እንዲፈጠር በማድረግ ተጨማሪ የመከላከያ ሃይል ከአፋርና ከምዕራብ ወለጋ እየተንቀሳቀሰ ነው። ይህም ክልሉ በሐይል በመቆጣጠር የፈዴራል መንግስት ፈላጎት ለማስፈፀም የሚደረግ እንቅስቃሴ አካል ነው፡፡

 

ደርግና ኮ/ል መንግስቱ ሃይለማርያም ስልጣን ሲይዙ መስከረም ሁለት ላይ ያለምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም ነበር ያሉት። ነገር ግን ኮ/ል መንግስቱ የአንድ ትውልድ ደም አፍስሶ ነበር በህዝቦች ትግል የተገረሰሰው። ኮ/ል አብይም ፍቅር፣ ይቅርታ፣ መደመር፣ ኢትዮጵያዊነትና የፖለቲካ ምህዳር ማስፋት አሉና ትንሽ ሳይቆዩ አገራችን ኢትዮጵያና ህዝቦችዋ በጥላቻ፣ በምህረት የለሽ እርምጃና እንደጠላት ተቆጥረው ጦር ዘምቶባቸው እንዲሞቱና እንዲፈናቀሉ ለአንድ አመት ያለ ዕረፍት በለውጥ ስም ነውጥ ውስጥ እንዲገቡ አደረጉ። ይሁን እንጂ ኮ/ል አብይ ይህ ምንም አያስጨንቃቸውም። የሚያስጨንቃቸው ፈረንጆቹ አንተ ውርጋጥ ልጅ አልቻልክም፣ አገር አተራመስከው ብለው እንዳይጨኩንባቸው ነው። ሰለዚህ በሃይል ነገር መጨፍለቅ ሲፈልጉ ዋናውና መደበኛ ሚድያ አዘጋጅተው ሲያበቁ ሌላውን ዘጋግተው የህዝቡን ጥያቄ ይጨፈልቃሉ። ወለጋ ውስጥ ተሳክቶላቸዋል። በአማራ አዴፓን እንደመመርመር፣ የአብንና የባለአዳራን አባላት በሺ የሚጠጉትን አማራዎችን እየለዩ አሰሩ። ኢንተርኔትን ሸጉረው ከበላይ መመርያ እየተሰጣቸው የሚሰሩትን ሚድያዎች በብር ገዝተው መልእክታቸውን ብቻ እንዲሰማ እያደረጉ ናቸው።

 

አሁን ደግሞ እንደ ሚወዱት ወዳጃቸው ደርግ በምስራቅ ያስመዘገብነው ድል በሰሜን ይደገማል ብሎ ዘመቻ እንደከፈተው፣ ኮ/ል አብይም በሰሜንና በምዕራብ በአማራና በወለጋ ያገኘንው ድል በደቡብ ይደገማል ብለው በደቡብ ህዝቦች ላይ ጦርነት ከፍተዋል። ዩኒፍርም ለብሰው ብቅ ባይሉም አዋጅ አውጀዋል። ነገር ግን ሁሌ መድገም የሚቻል እንዳልሆነ፣ ሽንፈት ከቀመሱት የፋሽስት ደርግ ጀኔራል ተስፋዬ ጨመዳ በምስጥር ቢጠይቓቸው ያስረዷቸዋል። የሆኑትን።

 

አረ አንድ ላይ ድምፃችን እናሰማ።

 

ራስን በራስ ማስተዳደር የዲሞክራሲ ጥያቄ ነው። በዓለም አቀፍ ሕግ ሁሉ የሰፈረ ነው። የሲዳማ ህዝብ ጥያቄው ስብስብ ጥያቄ አይደለም። ክልል እንሁን ነው። ቀላል ጥያቄ ነው። በግልፅ ህገመንግስቱ ላይ የሰፈረ ነው። ሌሎች ተከትለው ይጠይቃሉ እና አይሆንም ከሆነ መልሱ ትክክል ሊሆን አይችልም። ለምን ሳላሳ ክልል አይፈጠሩም። ምን ችግር አለው። መብቱኮ ህገመንግስቱ ላይ የተቀመጠው ለጌጥ አይደለም። ከህዝብ በላይ ማንም ስልጣን የለውም አይገባቹሁም ለማለት። ስልጣን ያለው ራሱ ህዝቡ ነው፡፡ በሪፍረንደም ህዝቡ የሚሻለኝ እንደነበርኩት መቀጠል ነው ወይም ክልል ይሻለኛል ብሎ መወሰን ይችላል። ከዛ ውጭ ወደ ውጭ ነው ነገሩ፡፡

 

ስለዚህ የሲዳማ ህዝብ ብቻ ነው የመወሰን ስልጣን ያለው። ይህን የክልል እንሁን ሪፈረንደም ሳይወሳስብ ሪፍረንደም የሚደረግበትን ጊዜ ቢወሰን ነገሩ በቀላሉ ያልቃል። ሌሎች ቢጠይቁስ? ለሚለውም ተመሳሳይ ነው መልሱ፡፡ ሳናወሳስበው በቀላሉ በህገመንግስቱና በውይይት መፍታት ይቻላል። ውይይት ሲባል ጥቅምና ጉዳቱ ህዝቡ አውቆ እንዲወስን እንጂ ጊዜ ለመግዛትና ህዝቡን ለመከፋፈል መሆን የለበትም። የኮ/ል አብይ መንግስት በሃይል ለመፍታት የሚያደርገው ሙከራ፣ ግድያና እስራት ተሎ እንዲያቆም ድምፃችን ማሰማት ያለብን አሁን ነው።

 

 

 


Back to Front Page