Back to Front Page

45 ደቂቃ በቤተ-መንግስት (መለስ V አብዪ)

45 ደቂቃ በቤተ-መንግስት

(መለስ V አብዪ)

ከቢሮ እስከ ሀገር በሚለው ፊልም የተደረገ ልማታዊ ግምገማ

5 cm

ባለፉት ቀናት በኢትዮጵያ የመንግስት ሚድያዎች ይቀርባል ተብሎ የተነገረለትን እና ህዝቡ በጉጉት ይጠባበቀው የነበረውን ዶኩመንታሪ ፊልም ትናንት ዓርብ መስከረም 9፣ 2012 ዓ.ም ለህዝብ በይፋ ቀርቦ በጥሞና ተከታትሎታል፡፡ ዶኩመንታሪ ፊልሙ ደራሲው፣ ዳይሬክተሩ፣ ኣዘጋጁ፣ ኣቅራቢው በአጠቃላይ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው በጠ/ሚ ዶ/ር አብዪ አሕመድ የተከናወነ የ45 ደቂቃ ፊልም ነበር፡፡

የፊልሙ መነሻ "አንድን መሪ ቤተ መንግስቱ፣ ቢሮው፣ ግቢው፣ የስራ አከባቢው ካላፀዳ ካልለወጠ፣ ውጤታማ ስራ ሊሰራ ኣይችልም፣ አገር ማሳደግ ወይም መለወጥ ኣይችልም ስለሆነም ሁሉም ነገር ከቢሮ መለወጥ መጀመር አለበት" ከሚል አስተሳሰብ በመነሳት "ከቢሮ እስከ ሀገር" በሚል ርእስ የቀረበው ፊልም ቤተመንግስቱ እንዴት እንደተለወጠ፣ ፅዱ እንደሆነ ጠ/ሚ ዶ/ር አብዪ አሕመድ አርት በተሞላው አቀራረብ ፍንትው አድርገው አሳይተውናል፡፡ የቤተ መንግስቱ ውበት ምን ያክል እንደሆነ የፈረንሳዩ መሪ ምስክርነታቸው እንደ ሰጡም ተናግረዋል፡፡ ይህ የማይካድ ሓቅ ነው፡፡ ማንም ዶክመንታሪ ፊልሙ ያየ ሰው የሚመሰክረው ሓቅ ነው፡፡ ከመቶ ዓመት በላይ ያስቆጠረ ያረጀ ቤተመንግስት እንዲህ ኣሳምሮ፣ ውበቱና ጥንታዊነቱ ኣስጠብቆ፣ ዘመናዊነት በማላበስ በአንድ ዓመት ውስጥ ይህን ታላቅ ስራ ሰርቶ ማጠናቀቅ በጣም በጣም የሚደነቅ ነው፡፡ የፊልሙ ኣቀራረቡ፣ ኣገላለፁ፣ እንዲሁም የስእሎች፣ የቅርፃቅርፆች እና የዲዛይኑ ትርጉሙ ለምን እንደዛ እንደተደረገ፤ ማስተላለፍ የተፈለገው መልእክት ምን እንደሆነ ከጠ/ሚ አንደበት ሲገለፅ በጣም መሳጭ ነበር፡፡ በአጠቃላይ የፊልሙ አቀራረብ እና ይዘት በጣም ጥሩ ነበር ማለት ይቻላል፡፡

ይህ ፊልም በአዎንታዊ ጎኑ እንደተገለፀው መልካም ቢሆንም ግን ደግሞ ከአንድ ጠቅላይ ሚኒስተር የሚጠበቅ ስራ ነው ወይ? የሚል መሰረታዊ ጥያቄ ማቅረቡ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ የኢትዮጵያ ጠ/ሚ እንደ የማንኛውም አገር ጠ/ሚ የሚታይ አድርጌ አልወስደውም፡፡ ኢትዮጵያ 23 ሚሊዮን ህዝቧ በከፋ ድህነት ውስጥ የሚገኝባት አገር ነች፡፡ ለውጥ የሚፈልግ፣  የኑሮ መሻሻልና ብልፅግና፤ እንዲሁም ልማት፣ ሰላምና መረጋጋት መኖር አጥብቆ የሚፈልግ ከ100 ሚልዮን በላይ ህዝብ ያላት ትልቅ አገር ናት፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ ጠ/ሚ በኔ አተያይ እነዚህን በጣም በጣም ከባድ ሃላፊነቶችን የሚሸከም፣ ሌት ተቀን የሚለፋ፣ ለሁሉም ህዝቦች በእኩል ዓይን የሚያይ፣ መቶ ሚልዮን ህዝብን የሚለውጡ በዓይነቱም በብዛቱም ሰፊ ፕሮጀክቶች እየመራ የህዝብን ኑሮ ለማሻሻል የሚተጋ ሰው ማለት ነው፡፡

በአገራችን በአሁኑ ሰዓት ጠ/ሚ የሚሆን ሰው ቀድሞ ጠ/ሚ ከነበሩት ዕድለኛ የሚያደርገው አንድ ነገር አለ፡፡ እሱም ኢትዮጵያ ከድህነት ለማውጣት የሚያስችል በተግባር ውጤታማነቱ የተረጋገጠ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ የተቀመረ የልማት አቅጣጫ ያላት አገር እና ህዝብ በመሆንዋ፤ ከዚህ አቅጣጫ የመነጩ አገርን መለወጥ የሚችሉ የተጀመሩ በርካታ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ያላት አገር በመሆንዋ እውነትም ዕድለኛ ጠ/ሚ ያስብለዋል፡፡ የዚህ ጠ/ሚ ፈተና የሚሆነው ሌት ተቀን ትኩረት የሚሹ በርካታ የህዝብ ጥያቄ ያላት አገር በመሆንዋ ይህንን የህዝብ ጥያቄ ለመመለስ ሌት ተቀን መስራት እና የለውጥ ሃይሉን በማንቀሳቀስ ሌት ተቀን ማሰራት ነው፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ ሊኖራት የሚገባ ጠ/ሚ ይህን ከባድ ሀላፊነት የሚመጥን ሌት ተቀን ያለ እረፍት አገርን የሚመራ፣ ልማትን የሚያስቀጥል፣ ሰላምና መረጋጋት የሚያሰፍን መሪ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ሲታይ ባለፈው አንድ ዓመት ጠ/ሚ ዶ/ር አብዪ አሕመድ ያለ እረፍት ሌት ተቀን ተሯርጠው የፈፀሙት ነገር ቢኖር የአፄዎች ቤተ መንግስት በማፅዳት እና በማስዋብ ስራ ነበር ተጠምደው ያሳለፉት፡፡

በእርግጥ ስራው በጣም ከባድ ነው፡፡ እንኳን ከ40 ሄክታር በላይ ስፋት ያለው ቤተ መንግስት ለዛውም ለበርካታ ዓስርት ዓመታት ጥገናም እድሳትም ተደርጎለት የማያውቅ ቤተ-መንግስት ኣፅድቶ፣ አስውቦ በአንድ ዓመት ውስጥ ለዚህ ደረጃ ማብቃት፤ አንድ የግል መካከለኛ ቤት በሁለት ሶስት ዓመት ሰርቶ ለመጨረስ ያለው ጣጣ ቤት የሰራ ሰው ነው የሚያውቀው፣ /ከባድ ነው/፡፡ በመንግስት ደረጃም ቢሆን ኣብዛኛው የዓለማችን ቤተ መንግስታት ለመስራትም ይሁን ለመጠገን፣ ለማደስ፣ ለማስዋብ በርካታ ዓመታት ሲወስዱ ይታያል፡፡ ስለዚ ከቤተመንግስት ማደስ አንፃር ሲታይ ተአምራዊ አፈፃፀም ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ነገር ግን ከኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ሲታይ፣ የጠ/ሚ ጊዜ የተሻማ፣ የ23 ሚልዮን ወገኖች የሚላስ የሚበላ የሚጠጣ ያጡ፣ መጠለያ የሌላቸው ወገኖች ሁኔታ ያላገናዘበ፣ ከአንድ የኢትዮጵያን ህዝብ ችግር ለመፍታት አልሞ ከልጅነቱ ጀምሮ ለትግል፣ ለመስዋእት የወጣ ኢትዮጵያዊ ጠሚ/ር የማይጠበቅ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ ይህ ስል ከመሬት ተነስቼ አይደለም፤ ወይም ከማይጨበጥ ራኢ በመነሳትም አይደለም፡፡

የህዳሴ ጉዞ መሃንዲሱ አቶ መለስ ዜናዊ ወደ ጠ/ሚነት ስልጣን ሲመጡ፣ ከ50% በላይ የአገራችን ህዝብ በከፋ ድህነት ውስጥ እየተሰቃየ በነበረበት ጊዜ ውስጥ በመሆኑ በድህነት አሮንቋ የነበረውን ህዝብ ለማዳን ባደረጉት የሞት ሽረት ትግል እስከ ህልፈተ ህይወታቸው ድረስ ሌት ተቀን እየሰሩ፣ እየመሩ፣ ወደ የድህነቱ መጠን ወደ 25% ሲያወርዱት፤ በቀን 3 እና 4 ሰዓት እየተኙ ወይም ደግሞ በቀን 19 እና 20 ሰዓት በመስራት ነበር፡፡ ለዚህም ነው ጠ/ሚንስትሩ ለኢትዮጵያ ህዝቦች ጥቅም፣ ለአገር እድገት ሲሉ በጨቅላ ዕድሜያቸው (በ56 ዓመታቸው) ከዚህ ዓለም በመስዋእት የተለዩት፡፡ ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ በራሳቸው አንደበት እንደገለፁት "ጠ/ሚ ማለት በአፄዎች ቤተ መንግስት የታሰረ መሪ ማለት ነው" ብለዋል፤ በዚህ ሁኔታ ቤተ መንግስቱ እንደ እስርቤት ነበር የገለጡት፡፡ እንደ ጠቅላይ ሚኒስተርነታቸው ይህን ያረጀ ቤተ-መንግስት ማስዋብ እና በተመቻቸ ሁኔታ ሆኖ አገር መምራት ስላልፈለጉ ኣይደለም፣ ለዚህ የሚሆን ገንዘብ ስለታጣም አይደለም፣ እንደተባለው ከባለሀብቱም ከውጭም ቢጠየቅ ወይም ቢለመን በቀላሉ ማግኘት ይቻላል፡፡

በዓለማችን የአገር መሪ ሆኖ፣ ዘመኑ ባለፈው ቤተ-መንግስት የሚኖርም ብዙም የተለመደ አይደለም፤ ጊዜ ያለፈባቸው ቤተ-መንግስታት እንደ የጎንደሩ ፋሲለደስ ለቱሪስት ይተዋል እንጂ፡፡ እንደ አገር መሪ ዘመኑ የሚጠይቀው በቴክኖሎጂ የተካኑ ቡሌት-ፕሩፍ መኪኖች ይጠቀማል እንጂ፤ ከ40 ዓመታት በፊት በነበሩ፣ በየሄዱበት እየተበላሹ የሚቆሙ የቤተመንግስት መርሴዲስ መኪኖች የሚጠቀምም አለ ለማለት ይከብዳል፤ እነዚህም በሙዝዬም ይቀመጣሉ እንጂ፡፡ ነገር ግን ጠ/ሚ መለስ ዜናዊን፣ የኢትዮጵያ ድሀው ህዝብ፣ ከወንዝ ተጎንብሶ ዉሀ የሚጠጣ ወገን ቢሮ ሲገቡ ከፊት ለፊታቸው በግድግባ ተገትሮ ሳይሆን የሚጠብቃቸው፤ ሁሌም በልባቸው፣ በደማቸው ውስጥ ስለነበር ነበር ገጠርን ትኩረት ያደረገ የልማት አቅጣጫ የነደፉት፤ እንቅልፍ ስለነሳቸው ነበር በቀን 19-20 ሰዓት ይሰሩ የነበሩት፣ እረፍት ስለነሳቸው ነበር አንድም ቀን ስለ ቤተሰቦቻቸው ስለመዝናናት ሳያስቡ፣  መስዋእት የከፈሉት፡፡ ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ የህዝቡ ሁኔታ ስላስጨነቃቸው ነበር የቤተመንግስት እድሳት ወደ ጎን በመተው፣ ዘመናዊ መርሴድስ የመግዛት ዕቅድ በመሰረዝ፣ ከውስጥም ከውጭም የምትገኘው ሰባራ ሳንቲም ለልማቱ የሚያውሉት፡፡ እንዲህ ስለተደረገም ነበር ባለፉት 17 ዓመታት ተአምር የሚባል የኢኮኖሚ እድገት አስመዝግበው ህይወታቸውን ያጡት፡፡ ለዚህም ነው ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ በህይወት እያሉ ያላዩት ሙገሳ፣ ያላዩት ክብር፣ በቀብራቸው ወቅት ከኢትዮጵያ ህዝብ የተበረከተላቸው፡፡ ኢትዮጵያ የብዙሀን አገር የብዙ ብሄር፣ ቋንቋ፣ ባህል፣ ቀለም፣ ሀይማኖት አገር መሆንዋ ይታወቃል ነገር ግን የጠቅላይ ሚኒስተር መለስ ዜናዊ ህልፈተ ህይወት በተሰማ ጊዜ የኢትዮጵያ ህዝቦች ልክ እንደ አንድ ህዝብ፣ አንድ ቤተሰብ ነበር ሀዘኑ የገለፀው፡፡ ይህ የሆነው ዋናው ምክንያት ጠ/ሚሩ በህይወት ዘመናቸው ድህነትን ለማጥፋት ያደረጉት ጥረት ዓዋቂ ሰው ብቻ ሳይሆን ህፃናትም ሳይቀር የተገነዘቡት ስለነበር ነው፡፡

አሁን ግን ጠ/ሚ ዶ/ር አብዪ አሕመድ ያለፈው አንድ ዓመት ሙሉ በአንድ ፕሮጀክት /የአፄዎች ቤተመንግስት በማስዋብ/ በመጠመዳቸው፣ በትክክልም ስራው በርካታ ዓመታት የሚጠይቅ በመሆኑ፣ ጠ/ሚሩ በጣም ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸው እና ሌት ተቀን መድከማቸው ከውጤቱ ማይት ይቻላል፡፡ በተለይ የምህንድስና ሙያ ያላቸው እና በመስኩ የተሰማሩ አካላት በደንብ ሊገልፁት ይችላሉ በትክክል የተዋጣለት ስራ ተሰርቷል፡፡ ነገር ግን ይህ ፕሮጀክት ቢሰራም ባለፉት ሁለት ዓመታት የኢትዮጵያ ድህነት ከመቀነስ ይልቅ እየጨመረ መሄድ ጀምሯል፤ ሰላም እና መረጋጋት ታጥቷል፣ ዜጎች በማንነታቸው እየተለዩ ማፈናቀል፣ መግደል፣ ማሰቃየት የተለመደ ተግባር ሆኖዋል፡፡ በተለይ ጠ/ሚ ዶ/ር አብዪ አሕመድ ወደ ስልጣን ከመጡ ጀምሮ ችግሮቹ በከፋ መልኩ ተባብሶ ቀጥሏል፡፡ የዚህ ሁሉ ችግር ምክንያት ለካ ጠ/ሚ ኢትዮጵያን መምራት ላይ ሳይሆን ቤታቸው እና ቢሯቸው (ቤተመንግስት) በማደስ እና በማስዋብ ስራ በመጠመዳቸው ነው፡፡

ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ እያንዳንዷ ከውጭ (በብድር ወይም በእዳታ) የምትገኝ ሰባራ ሳንቲም ለልማት መዋል አለበት ሲሉ፤ ጠ/ሚ ዶ/ር አብዪ አሕመድ ግን እያንዳንዷ ከውጭ (በብድር ወይም በእዳታ) የምትገኝ ሰባራ ሳንቲም ለማስዋብ፣ ለቱሪስት፣ ለጌጣጌጥ፣ ለዘመናዊ መኪናና ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለጉብኝት መዋል አለበት ይላሉ፡፡

ለምሳሌ ጠ/ሚ ዶ/ር አብዪ አሕመድ በዶኩመንታሪ ፊልሙ ራሳቸው እየነዷት የምትታይ ዘመናዊ መርሴድስ መኪና፣ መስተዋቱ ውፍረቱ በጣም በጣም ትልቅ ነበር፡፡ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ኦባማ ኢትዮጵያ ሲጎበኙ ይዘዉት የመጡ መኪና ጥይት የማይበሳው ባለ 8 ሚሜ ውፍረት ያለው ላሜራ እና ውፍረቱ እንደዚሁ በሚሊ-ሜትር የሚለካ መስተዋት ያላት መኪና ተብሎ በዛን ሶሞን በኢትዮጵያ ሶሻል ሚድያ ብዙ መነጋገሪያ አጀንዳ ሆኖ እንደነበር የቅርብ ትዝታ ነው፡፡ የየኛው ጠ/ሚ ዶ/ር አብዪ አሕመድ ግን የመስተዋቱ ውፍረት ከ5 ሴ/ሜ (ሚሊ-ሜትር ሳይሆን ሴንቲ-ሜትር) በላይ ሲሆን ይህ ጥይት የማይበሳው ብቻ ሳይሆን ከባድ መሳሪያ የማይበግረው መኪና ነው፡፡ ለዚህ መኪና የወጣው ወጪ ምንሊሆን ይችላል የሚል አምባብያን ራሳቹ ገምቱት፡፡ ነገር ግን በአሜሪካ መንግስት ወይም በፕሬዚዳንቱ ያልተደፈረች መኪና በድሀው አገር ጠ/ሚ፣ በዶ/ር አብዪ አሕመድ መደፈሯ ነው የሚገርመው፡፡

ከዚህ መረዳት የሚቻለው ጠ/ሚ ዶ/ር አብዪ አሕመድ የሚጨነቁት ለራሳቸው እና ለቢሯቸው ውበት፣ ንፅህናና ደህንነት ሲሆን፤ ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ግን የሚጨነቁት ድህነት እንዴት እናጥፋ፣ የአገር ኢኮኖሚ እንዴት እናሳድግ፣ ህብረተሰቡ ንፁህ ውሀ እንዴት እናጠጣው፣ የአርሶ አደሩና የኣርብቶ አደሩ ምርታማነት እንዴት እናሳድግ የሚሉ ከባድ ሓላፊነቶች ነበሩ የሚያስጨንቁት፡፡ ውጤቱም ለጭንቀቱ የሚመዝን ወይም በጣም ከፍተኛና ተከታታይ ዕድገት አስመዘገቡ፡፡ ጠ/ሚ ዶ/ር አብዪ አሕመድም ጭንቀታቸው ለውበት እና ለንፅህና ነበር እና በአንድ ዓመት ውስጥ ቤተመንግስቱ እንዴት እንደለወጡት አየን፡፡ ነገር ግን በህዝብ የተሰጣቸው ከፍተኛ ሃላፊነት መወጣት አልቻሉም፡፡ እንዲያውም አገራችን ኢትዮጵያ ወደ አልተፈለገ መንገድ በከፍተኛ ፍጥነት እየተጓዘች ትገኛለች፡፡ ስለዚ ጠ/ሚ ዶ/ር አብዪ አሕመድ የአንድ ፕሮጀክት ማናጀር ሳይሆኑ የ100 ሚልዮን ህዝብ፣ የበርካታ ቢሊዮኖች ብር ትላልቅ ፕሮጀክቶች ማናጀር መሆናቸውን አውቀው ለዛ የሚመጥን አመራር ይስጡ ካልሆነ እንደ ጠ/ሚ ሀ/ማርያም ደሳለኝ በበቃኝ ተዘርሮ ገለል ይበሉ፡፡

 

ህዳሴ ኢትዮጵያ

አስተያየትዎ በ hidaseethiopia@yahoo.com ወይም hidaseethiopiaa@gmail.com ማድረስ ይቻላል

 

 

 

Back to Front Page