Back to Front Page

በኢትዮጵያ የህዝብ ምርጫ ከማራዘም ወይም ኣለማራዘም በስተጀርባ

በኢትዮጵያ የህዝብ ምርጫ ከማራዘም ወይም ኣለማራዘም በስተጀርባ

ህዳሴ - ኢትዮጵያ

ሰነ 26፣ 2011 ዓ.ም.

 

ባለፉት 25 ዓመታት በአገራችን ኢትዮጵያ በህገመንግስቱ መሰረት 5 ተከታታይ ዴሞክራሲያዊ ነፃ ምርጫ መካሄዱ ይታወቃል፡፡ እነዚህ ምርጫዎች አንዳንድ በተወሰኑ አከባቢዎች ግጭት እና ንትርክ ያነሱ ቢሆንም በአመዛኙ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ነፃ፣ ተአማኒነት ያተረፉ ምርጫዎች እንደነበሩ ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ የመሰከረላቸው ነበሩ፡፡ ይሁንና አሁን ኢህአዴግ በመበስበሱ እና ችግር ላይ በመውደቁ ምክንያት አገራችን ሰላም እና መረጋጋት ርቋት ከቆየ ጥቂት አመታት ተቆጥሯል፡፡ ይህ በመሆኑ ግን የቀጣይ ምርጫ መካሄድ ወይም አለማካሄድ ጥያቄ በማስነሳት ላይ ይገኛል፡፡ ምርጫው ይካሄድ ኣይካሄድ የሚለው ክርክር መነሻው ሲታይ የተለያዩ ቢሆንም ኣብዛኛው ግን ስልጣን ለመያዝ ካለው ፍላጎት የመነጨ ነው፡፡ ከሁሉ የሚገርመው ነገር ግን በዚህ አጀንዳ ዙርያ በኢህአዴግ ውስጥም በተቋዋሚዎች በኩልም የጋራ መግባቢያ አለመኖሩ ነው፡፡ የዚህ ፅሁፍ ዓላማ በምርጫው ጊዜ ማራዘም እና አለማራዘም ያለውን አለመግባባት ምክንያት ለማሳየት ነው፡፡ ይህንን በሁለት ጎራ በመክፈል ለማሳየት ተሞክሮዋል፡፡ እሱም በኢህአዴግ ተፈቋዋሚዎች/ተፎካካሪዎች ጎራ እና በኢህአዴግ ጎራ በሚል እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

Videos From Around The World

ሀ/ በኢህአዴግ ተፈቋዋሚዎች/ተፎካካሪዎች ጎራ

በአሁኑ ሰዓት በርካታ ተቋዋሚዎች ወይም ተፎካካሪ ፖለቲካ ድርጅቶች ህጋዊ ዕውቅና አግኝተው በአገራችን በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ተቋዋሚዎች አብዛኞቹ ባለፈው የተደረገው 5 ተከታታይ ምርጫ ቢሸነፉም ሽንፈታቸው አሜን ብለው ሳይቀበሉ ለሽንፈታቸው ምክንያት የገዢው ፓርቲ ጫና ነው ብለው ሲከሱ ይስተዋላሉ፡፡ በመሆኑም ምርጫው ይደገም ሲሉ የነበሩ ናቸው፡፡ አሁን በአገራችን ካለው ሁኔታ በመነሳት የ2012 ምርጫ ይካሄድ ይራዘም የሚሉ ክርክሮች እየተነሱ ሲሆን በተቋዋሚዎች በኩልም የጋራ መግባባት የለም የዚህ ምንጭ ለመረዳት የኢህአዴግ ተቋዋሚዎች በሁለት ከፍለን እንያቸው፡-

1.  የአሀዳዊ ስርዓት ናፋቂዎች፡- እነዚህ በዋናነት በትምክህት ወይም በነፍጠኝነት ጎራ የሚመደቡ ሲሆኑ ህገመንግስቱን ኣጥብቀው ይቃወሙታል፡፡ ከከረረ ጥላቻ ተነስተው ህገመንግስቱ ህገ-አራዊት ይሉታል፡፡ እነዚህ ሀይሎች ባለው ህገ-መንግስት ተወዳድረው አሀዳዊ ስርዓት መመስረት እንደማይችሉ ይገነዘባሉ፡፡ ያላቸው ፍላጎት በማንኛውም መንገድ ህጋዊም ህገወጥም መንገዶች በመጠቀም ህገመንግስቱ የሚናድበት እና በምትኩ ሌላ ህገመንግስት ማርቀቅ ነው፡፡ ይህን ፍላጎት ለማሟላት ደግሞ የምርጫ ጊዜ በማራዘም ጊዜ መሸመት ይፈልጋሉ፡፡ ለዚህ እንደ ዋነኛ ኣማራጭ የሚወስዱት የመፈንቅለ መንግስት እርምጃዎች መውሰድ ነው፡፡ ይህ የሚደረገው መፈንቅለ መንግስትም በክልል ሳይሆን በፌደራል ነው፡፡ በዚህም ሁለት ኣማራጮች ኣሏቸው፡፡

a.  ከተቻለ በስምምነት የሚደረግ መፈንቅለ መንግስት፡- ይህ መንገድ አሁን በአገራችን የለውጥ ሀይል ብሎ ራሱን እየጠራ ያለው የቲም-ለማ ቡድን ከዚህ የአሃዳዊ ስርዓት ናፋቂ ሀይል በመስማማት ደህንነቱ በጠበቀ አኳሀን ራሱን ከስልጣን ማግለል /ሰሙ እንደ የሱዳኑ መፈንቅለ መንግስት ሆኖ ወርቁ ግን የውስጥ ስምምነት በማድረግ ህገመንግስት ከሚፈቅደው ውጭ ስልጣን ማስረከብ ነው/፡፡ ይህ ከተሳካ ቲም-ለማ በውጭ አገር የተመቻቸ ኑሮ እንዲኖሩ የሚሸኙ ሲሆን፣ የአሀዳዊ ስርአት ናፋቂዎች ከ3-5 ዓመት የሚፈጅ የሽግግር መንግስት በማቋቋም ሌላ የአሀዳዊ ስርዓት ህገመንግስት ማርቀቅ እና የብዙሀን መብት እውቅና በመንፈግ ወደማያቧራ እልቂት መግባት ነው፡፡

b.  ሌላው አማራጭ በሀይል የሚደረግ መፈንቅለ መንግስት፡- ይህ አማራጭ የመጀመሪያው /የስምምነት/ ኣማራጭ ካልተሳካ የሚደረግ ሆኖ፤ ይህም ስልጣን እስኪያዝ ድረስ ተከታታይ መፈንቅለመንግስት ሙከራዎች ማድረግ ነው፡፡ ይህ ኣማራጭ ልክ በኣማራ ክልል እንደተፈፀመው ዓይነት ሆኖ ለዚህ ዓላማ እንቅፋት ናቸው የሚሏቸው ዜጎች መቅጠፍ ነው፡፡ ይህ ለማድረግ ደግሞ ከታች ጀምሮ ደረጃ በደረጃ እስከ ጠ/ሚ ድረስ የሚዘልቅ ግድያዎች ይኖራሉ ማለት ነው፡፡ ትምክህት ለስልጣን ብሎ የማይከፍለው ዋጋ የለም፡፡ በአማራ ክልል እንደታዘብነው የጋራ ዓላማ እያላቸውም ቢሆኑ፣ ግን ደግሞ ካላቸው የስልጣን ጥም የተነሳ መሪዎቻቸው፣ የትግል ጓዳቸው፣ በግድያ በማስወገድ ስልጣን መያዝ የነሱ ባህሪ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል፡፡

2.  የፌደራል ስርዓት ደጋፊ ግን የኢህአዴግ ተቋዋሚዎች

የፌደራል ስርዓት ደጋፊ ተቋዋሚዎች በመሰረቱ ያለውን የፌደራል ስርዓት አይቋወሙም፡፡ ይሁን እንጂ በህገመንግስቱ እና በፌደራላዊ ስርዓት መሻሻል አለባቸው የሚሏቸው ነገሮች አሉ፡፡ ቢሆንም ግን የሚያቀርቧቸው ማሻሻያዎች ህገመንግስቱን በሚፈቅደው ስርዓት መሰረት እንዲሻሻል ይፈልጋሉ፡፡ እነዚህ ሀይሎች የምርጫው ዘመን እንዲራዘም አይፈልጉም፡፡ እነዚህ ሀይሎች በኢህአዴግ ውስጥ በተፈጠረው ችግር ምክንያት የየክልላቸው ክፍተት እንደሚሞሉና በምርጫ ተወዳድረው እንደሚያሸንፉ በታላቅ ልበሙሉነት ይናገራሉ፡፡ ስለሆነም ምርጫው መራዘም አጥብቀው ይቃወሙታል፡፡

ለ/ በኢህአዴግ ጎራ

የኢህአዴግ ኦፊሻል ውሳኔ ምርጫው በተቀመጠለት ጊዜ መካሄድ አለበት የሚል ቢሆንም በኢህአዴግ እህት ድርጅቶች ውስጥ ግን ሰፊ ልዩነቶች ኣሉ፡፡ ሌላ ቀርቶ ቲም-ለማ ተብሎ የሚጠራው የኢህአዴግ ስልጣን ተቆጣጥሮ የሚገኘው ቡድን ሳይቀር በዚህ አጀንዳ ስምምነት የለውም፡፡ ቲም-ለማ በዚህ አጀንዳ /ምርጫ ይራዘም ወይስ ኣይራዘም/ እርስ በርሱ እንደማይስማሙ የታወቀ ነው፡፡ ምክንያቱ ቲም-ለማ የሁለት ጫፍ ረገጥ አመለካከቶች /የትምክህት እና የጠባብነት/ ጊዝያዊ ቁርኝት በመሆኑ፡፡ የትምክህት አቀንቃኝ አሀዳዊ ስርዓት የሚፈልግ ሲሆን ጠባብነት ደግሞ የራሱ የበላይነት የተረጋገጠበት የሌሎች ህልውና ዕውቅና ሰጥቶ መኖር ይፈልጋል፡፡ ስለዚ እዚህ ላይ ከፍተኛ ፍትግያ ይኖራል፡፡

በቀጣይ አገራዊ ምርጫ ኢህአዴግ በምርጫ እንደማያሸንፍ ከወዲሁ መገመት ይቻላል፡፡ ምክንያቱ ኢህአዴግ የሚያስብለው በትግራይ ህወሓት፣ በአማራ ብአዴን/አዴፓ፣ በኦሮሚያ ኦህዴድ/ኦዴፓ፣ በደቡብ ደኢህዴን ያጣመረ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ የሚመራ የጋራ መግባባት ያለው ግንባር ሲሆን ነው፤ ነገር ግን በአሁኑ ሰዓት ይህ ግንባር እንደ ግንባር በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ላይ የጋራ መግባባት የለውም፡፡ ህወሓት ብቻ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ጠንካራ የማይወላገድ አቋም ሲኖረው በሌሎች ግን ከዚህ እምነት ርቀው ሄዷል፡፡ በመሆኑም በቀጣይ ምርጫ የኢህአዴግ እህት ድርጅቶች ከሚከተሉት ፖለቲካዊ አመለካከት በመነሳት ከህወሓት በስተቀር በምርጫው ሁኔታ ያሸንፋሉ ኣያሸንፉም ብሎ መናገር ወይም መተንበይ ያስቸግራል፡፡

ይህንን ለመረዳት የኢትዮጵያ ፖለቲካ በሁለት ትላልቅ ጎራ ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡ ጎራውም የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ወይም የልማታዊ ዴሞክራሲ ጎራ እና የሊበራል ዴሞክራሲ ጎራ ናቸው፡፡ ከዚህ ውጭ የሆነ አንድም የፖለቲካ ድርጅት/ፓርቲ የለም፡፡ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ አራማጅ ነን የሚሉ ሀይሎች በሁለትና ሶስት ሊከፋፈል የማይችል አንድ ወይም ብቸኛ ጎራ ነው፡፡ ለዚህም ነው በየብሄሩ የተደራጁት የኢህአዴግ ኣባል ድርጅቶች አራት ቢሆኑም አብዮታዊ ዴሞክራሲ አንድ ስላደረጋቸው በኢህአዴግ ስር ተጠልለው እንደ አንድ ድርጅት ይቆጠራሉ፡፡ የሊበራል ዴሞክራሲ ጎራ ግን አንድ ሊሆኑ የማይችሉ ቢሞከርም ዘለቄታዊ የማይሆን ጋብቻ ሲሆን ታዝበነዋል፡፡

ስለሆነም በኢትዮጵያ ምርጫ የሚፋተጉት እነዚህ ሁለት /የአብዮታዊ ዴሞክራሲ እና የሊበራል ዴሞክራሲ/ ጎራዎች ናቸው፡፡ በአሁኑ ሰዓት በትግራይ እንዲሁም በኢትዮጵያ ጠንካራ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ተከታይ ህወሓት ብቻ ነው፡፡ የደቡብ ህዝቦች ክልል ደኢህዴን በውል የለየለት ነገር ባይኖርም በኦሮሚያ ክልል እና በኣማራ ክልል ያሉ የኢህአዴግ እህት ድርጅቶች ግን ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ ጎራ በመውጣት ወደ ሊበራል ጎራ ተቀላቅሏል፡፡

በመሆኑም የምርጫው ሁኔታ ትምበያ ሲታይ ከነዚህ ሁለት ጎራዎች ለህዝብ የሚጠቅም ነገር ይዞ የመጣ እና ኢትዮጵያ ላለችበት የዕድገት ደረጃ የሚመጥን ብቸኛው መንገድ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ወይም ልማታዊ ዴሞክራሲ በመሆኑ ቢወዳደር በህዝብ ምርጫ እንደሚያሸንፍ ጥርጥር የለውም፡፡ ምክንያቱ ልማታዊ ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ ተሞክሮ ውጤት ያስመዘገበና በዓለምአቀፍ ደረጃ የተመሰከረለት ፈጣን፣ ፍትሀዊ እና ዘለቄታዊ ያለው ዕድገት ያስመዘገበ በመሆኑ፡፡ ነገር ግን በአገር ደረጃ ልማታዊ ዴሞክራሲ የሚያራምድ ድርጅት ህወሓት ብቻ በመሆኑ፤ ህወሓትም በመላው አገሪቱ መወዳደር ስለማይችል በቀጣይ የአገራችን ምርጫ /ቢራዘምም ባይራዘምም/ ልማታዊ ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ ሊያሸንፍም ገዢ ሆኖ ሊቀጥልም ኣይችልም፡፡ ምክንያቱ ይህን የሚያራምድ አገራዊ ፓርቲ ስለሌለ፡፡ ስለሆነም ቀጣይ ምርጫ ቢራዘምም ባይራዘምም ሊበራል ዴሞክራሲ አሸናፊ እና ገዢ ሆኖ በኢትዮጵያ ይቀጥላል፡፡ በትግራይ ህወሓት አሸናፊ ቢሆንም በአገራዊ ጉዳይ ግን ተፎካካሪ ወይም አጋር ሆኖ ይቀጥላል፡፡

በሌላ ቦኩል በቀጣይ የአገራችን ምርጫ ሊበራል ዴሞክራሲ አሸናፊ ሆኖ ይወጣል ሲባል ግን አንድ ጠንካራ ፓርቲ ያሸንፋል ማለት አይደለም፡፡ የአገራችን ተቋዋሚዎች/ተፎካካሪዎች ሁኔታ ሲታዩ በአጠቃላይ 107 የደረሱ ሲሆኑ አብዛኞቹ የሊበራል አራጋቢዎች ናቸው፡፡ ስለዚ በቀጣይ ምርጫ ከነዚህ 107 ፓርቲዎች አንድ ወይም ሁለት ፓርቲ ብቻ ሳይሆን የሚመረጠው ሁሉም እኩል የመመረጥ ዕድል ስላላቸው ሊበራል አራማጅ ያሸንፋል ቢባልም የቱ ፓርቲ የሚለው ግን በትክክል መተንበይ ያስቸግራል፡፡ በመሆኑም በአማራ ክልል አዴፓ፣ አብን፣ ሌሎች ፓርቲዎችም ሁሉ እኩል የማሸነፍ ዕድል ኣላቸው፡፡ አዴፓ በሚያራምደው ፖለቲካ የመመረጥ ዕድሉ ከአብን ወይም ከሌሎች ብልጫ የለውም፡፡ ኦዴፓ በኦሮሚያ ክልል ሲወዳደር ከኦነግ እና ከሌሎች የኦሮሞ ድርጅቶች ብልጫ የለውም፡፡ ስለዚ አዴፓ እና ኦዴፓ በቀጣይ ምርጫ በየክልላቸው የመንግስትነት በትረስልጣን የመረከብ ዕድሉ የቀጨጨ ነው፡፡ ከኢህአዴግ እህት ድርጅቶች ውስጥ የክልሉ በትረ መንግስት የመረከብ ከፍተኛ ዕድል ያለው ብቸኛው ድርጅት የትግራዩ ህወሓት ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ትንታኔ በመነሳት ህወሓት የምርጫውን ሁኔታ ቢራዘምም ባይራዘምም በትረ ስልጣኑ በእጁ ስለሆነ፣ ስጋት የለውም፡፡ ነገር ግን ህወሓት ምርጫው በህጉ መሰረት መካሄድ አለበት ብሎ በፅናት ሲከራከር ለህገመንግስቱ ካለው ፅኑ አቋም እንጂ ለስልጣን ካለው ፍላጎት አይደለም፡፡

ሌሎች የኢህአዴግ እህት ድርጅቶች ግን ኦፊሻሊ በተያዘው ጊዜ /በ2012 ዓ.ም./ ይካሄዳል የሚል ውሳኔ ቢኖርም ግን በውስጣቸው በተለይ አዴፓ እና ኦዴፓ ምርጫው እንዲራዘም ይፈልጋሉ፡፡ ለምን ቢባል ሁለቱም ድርጅቶች በምርጫው ማሸነፍ እንደማይችሉ በእርግጠኝነት መተንበይ ስለሚቻል፡፡ እነዚህ ድርጅቶች ከልማታዊ ዴሞክራሲ ርቀው በመሄዳቸው ያላቸው ዕድል የየክልላቸው የመንግስትነት ስልጣን ከተቋዋሚዎች ከተሳካ እኩል ወንበር መጋራት ካልተሳካ ደግሞ በዜሮ መሄድ ነው፡፡ ምክንያቱ ከተቋዋሚዎች የተሻለ ነገር ይዘው ስለማይቀርቡ፡፡ ስለዚህ ምርጫው ከተራዘመ የቲም-ለማ የስልጣን ጊዜ ስለሚራዘምለት ይፈልጋል ነገር ግን ከህወሓት ከፍተኛ ተቋውሞ ይገጥመዋል፡፡

የኦዴፓ ፍላጎት፣ ከኦነግ እና መሰል ድርጅቶች ተወዳድሮ ማሸንፍ እንደማይችል ስለሚገነዘብ በተቻለ መጠን በስልጣን ለመቆየት ካለው ፍላጎት የተነሳ የምርጫው ጊዜ ማራዘምን የሚፈልግ ሲሆን፤ የአዴፓ ፍላጎት ከሁለት አቅጣጫ የሚመነጭ ነው፡፡ አንደኛው፣ የስልጣን ጊዜ በማራዘም በስልጣን ለመቆየት ካለው ፍላጎት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ኦዴፓን በመሸወድ እንደ ብ/ጀ አሳምነው ፅጌ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ በአገር ደረጃ ለማድረግ ጊዜ ለመሸመት ነው፡፡

የዚህ ሁሉ ችግር መንስኤ የኢህአዴግ እህት ድርጅቶች ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ ርቀው ወደ ጥገኞች ጎራ በመቀላቀላቸው ነው፡፡ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ለኢትዮጵያ ፍቱን መድሃኒት ነው፡፡ ባለፉት 27 ዓመታት በኢትዮጵያ ሰላም መረጋጋት፣ ልማት እና የህግ የበላይነት እንዲሰፍን ያደረገው ይህ መስመር ነበር፡፡ ኢህአዴግ ከዚህ መስመር መውጣት ከጀመረና ወደ ተቋዋሚ ጎራ ተቀላቅሎ ያለፉት 27 ዓመታት መርገም ሲጀምር ግን እነሆ የሰላም እና መረጋጋት እጦት ተባብሶ ህዝባችን ለከፍተኛ እንግልት ተዳርጓል፡፡

ሐ/ ኢትዮጵያ ከገባችበት አዘቅት ለመውጣት ሁለት አማራጮች አሏት

        አንደኛው አማራጭ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ሁኔታውን አይቶ ገምግሞ ትክክለኛ ሂስ አድርጎ ድርጅቶቹን ወደ ትክክለኛው የአብዮታዊ ዴሞክራሲ መስመር ከመለሱት ኢትዮጵያ ራስዋን ታቀናለች

ሁለቱም ካልሆነ

        ሁለተኛው አማራጭ ህወሓት እንደ 1980ዎች የኢትዮጵያ ህዝቦች በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ስር ተሰልፈው ትግል እንዲያደርጉ ከፍተኛ ጥረት ካደረገች እና ለዚህም ትርፍ መስዋእትነት ለመክፈል ዝግጁ ከሆነች፣ ኢትዮጵያ ዳግም የማንሰራራት ተስፋዋ ይለመልማል፡፡

ካልሆነ ግን ሰላም እና መረጋጋት እጦት ተባብሶ የህዝቦች ፍቺ እውን መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡

መ/ ከምርጫው ማራዘም እና አለማራዘም ውሳኔ በፊት የተደቀነ አደጋ/ስጋት

ዕላይ ለመግለፅ እንደተሞረው የአሀዳዊ ስርዓት ናፋቂዎች የምርጫ ጉዳይ ጉዳያቸው አይደለም፡፡ የነሱ ፍላጎት ከህዝብ ፍላጎት ውጭ በስምምነትም በሀይልም ስልጣን መረከብ ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት እነዚህ ሀይሎች የጠ/ሚ ዶክተር አብይ አሕመድ ታማኝ አማካሪ በመሆን በቤተመንግስት ዙሪያ ሲያንዣብቡ ይታያሉ፡፡ ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አሕመድ ኢትዮጵያን ሰላምዋን አስጠብቆ፣ አረጋግቶ መምራት አልቻሉም፡፡ በተለይ በቅርቡ በተወካዮች ምክርቤት ባደረጉት ንግግር ተስፋ የመቁረጥ እና የመሰላቸት ሁኔታዎች የታዩባቸው ሲሆን ይህ ሁኔታ ለአሀዳዊ ስርዓት ናፋቂዎች ትልቅ ማምለጥ የማይገባው ዕድል ነው፡፡ በሌላ በኩል ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አሕመድ በወሰዱት እርምጃ የአገራችን የደህንነት ተቋም ሽባ አድርጎታል፡፡ ባለፈው በትምክህት ወይም በአሀዳዊ ስርአት ናፋቂዎች በተቀነባበረ ሴራ በመከላከያ ጀነራሎች እና በአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ግድያ ሲፈፀም የአገራችን የደህንነት ተቋም ምንም ነገር ሳያደርግ መቆየቱ ምን ያክል የአመራር ክፍተት እንዳለ ያሳያል፡፡ የኢትዮጵያ የደህንነት ተቋም በአገራችን የታሰቡ ሴራዎች ገና ከምንጫቸው ጀምሮ ተከታትሎ በማክሸፍ /ለምሳሌ አዲስ አበባን እንደ ባግዳድ ሴራ/ እንዲሁም በኤርትራ ውስጥ የኢሳያስ አፈወርቂ ቤተ መንግስት የማተራመስ ብቃት እንዳልነበረው በአሁኑ ሰአት የአገራችን ከፍተኛ ኣመራሮች ደህንነት መጠበቅ ተስኖት አገራችን እየተተራመሰች ትገኛለች፡፡ በአሁኑ ሰዓት የአገር ደህንነት ተቋም ጠ/ሚ እና ቤተመንግስታቸው ከመጠበቅ ውጭ የአገርን ደህንነት የመጠበቅ ጉዳይ ብቃት እንደሌለው አሳይቷል

ስለዚህ የጠ/ሚ የመምራት ብቃት መዳከም መሰላቸት እና ተስፋ መቁረጥ፣ የደህንነት ተቋም መዳከም እንዲሁም የይምክህት የሞት ሽረት ትግል ተደማምሮ የአሀዳዊ ስርዓት ናፋቂዎች በስምምነት ወይም በሀይል መፈንቅለ መንግስት የማድረግ ሁኔታ ሚዛን የሚደፋ ይመስላል፡፡ ስለዚህ ህገመንግስቱን በሀይል የመናድ አዝማምያ ቀላል ስላልሆነ የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲሁም የመከላከያ ሰራዊታችን አመራሮች እና አባላት በጥሞና በመከታተል አገራችን ከተደቀነባት አደጋ የማውጣት ግዴታ ዜግነታዊ ግዴታችን ነው ብለው አገርን እና ህገመንግስታዊ ስርዓቱን የማዳን ሚና ሊጫወቱ ይገባል ነው፡፡

አስተያየት ካለ በሚቀጥለው ኣድራሻ ማድረስ ይቻላል

hidaseethiopia@yahoo.com ወይም hidaseethiopiaa@gmail.com


Back to Front Page