Back to Front Page

እኔም አለኝ ቁሥል ያንተን የሚመሥል

እኔም አለኝ ቁሥል ያንተን የሚመሥል

ልኡል ገብረመድህን ( አሜሪካ )

6/1/2019.

ፖለቲካ የህዝብ አሰተዳደር ጥበባዊ ክህሎት ነው ሆኖም በመርህ ካልተገራ አገር አፍራሽ ህዘብ በታኝ ሊሆን ይችላል ኢትዮጵያ ማህበራዊ ስልጣኔ ቀድሞ ከጀመሩ የአለም አገራት አንዷ ብትሆንም በሒደት በፖለቲካ አሰተዳደር ምክነያት ድህነትና ድንቁርና ተጭኗት ፣ ሰላምና መረጋጋት እርቋት ፣ አገራዊ አንድነት ማስፈን ተስኗት ፣ ዲሞክራሲና ፍትህ ማሳካት አቅቷት ቁልቁለት መንገድ ላይ ናት ። በኢትዮጵያ የፖለቲካ አለመረጋጋት አንዱ ምክንያት ሁሉም ባይሆኑም የኢትዮጵያ ምሁራን ችግር ይመስለኛል ። አንድ በቂ የፖለቲካ ተሳትፎ ያለማድረግ ሲሆን ሌላው የፖለቲካ ጥገኛ መሆን በኢትዮጵያ የዲሞክራሲ መርህ የተከተለ ህገመንግስታዊ ሰርአት እንዳይኖር ሆነዋል ። የምሁራን ማፍለቂያ የሆኑ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሳይቀሩ በኋላ ቀር አሰተሳሰብ ተጠምዶ ለአገር እና ለወገን የሚበጅ በምርምርና ጥናት የታገዘ መፍትሔ ከማፍለቅ ይልቅ ራሳቸው አንዱ ማህበራዊ ችግር ሆነዋል ። ከጥናት እና ምርምር ይልቅ የጥላቻና ዘረኝነት ማስፋፊያ ተቋም ሆነዋል ። ይህ አሳዛኝ ክሰተት ነው ። ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የፖለቲካ ተቋም ሳይሆን የጥናትና ምርምር ለለውጥ መሆን ነበረባቸው ።

Videos From Around The World

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ በከፊል ከአብዮት ጋር በሌላው ደግሞ ከዘውዳዊ አገዛዝ የተቀዳ በመሆኑ ዲሞክራሲያዊ ሰርአት ለመመስረት መነሻ ችግር ሆኖ ቆይተዋል ። በአብዮት እና ህዝባዊ ነውጥ ስልጣን የሚይዝ መንግሥት የዲሞክራሲ መርሆች ለመተግበር ይቸገራል ። በአብዮት የመጣ መንግስት ለህዝብ ጥቅምና ፍላጎት ተገዢ የሆነበት ወቅት የለም ። ይልቁንስ ህዝብ የሚጨቁን ህገ ደንብ በማርቀቅ የአፈና ተግባራት ይፈፅማል ። ህዝብም አብዮተኞች ስልጣን ሲይዙ ያጨበጭባል በአብዮትና ነውጥ ከሰልጣን ሲወገዱም ያጨበጭባል ። ይህ አሳዛኝም አሳሳቢም ጉዳይ ነው ። የፖለቲካ አብዮተኞች ከህዝብ ፍላጎት ይልቅ ለፖለቲካ ድርጅታቸው ታማኝ አገልጋዮች ናቸው ። በመሆኑም አብዮተኛ ፖለቲከኞች ለአገርና ህዝብ የሚበጅ በምክንያት ላይ የተመሠረተ የለወጥ ሀሳብ መተንተንና ማራመድ ፈፅሞ አይችሉም ። የሐሳብ ድርጅታዊ ነፃነት የላቸውም ። በዲሞክራሲ መርህ ሳይሆን በፖለቲካ ድርጅት ትዕዛዝ ጉዳይ የሚያስፈፅሙ የቁም ሙታን ናቸው ።

ከዘመነ መሳፍንት ቀጥሎ በመጥፎ የሚነሳው የወታደራዊ አሰተዳደር (ኢሠፖ) በኢትዮጵያ ያሳረፈው ማህበራዊ ሆነ ኢኮኖሚያዊ ችግር ለመተንተን ያዳግታል ። የቀዳማዊ ንጉሰ ሐይለሰላሴ ሰርአት በሐይል አስለቅቆ ወታደራዊ መንግስት በመመስረት የኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ድባብ ያጨናገፈው የደርግ ሰርአት በቀይ ሸብር ምክንያት በወጉ የማይታወቅ ህዝብ ለሞትና እንግልት ተዳርጓል ። በሰላም ለነፃነትና ዲሞክራሲ ይታገሉ የነበሩ የለውጥ ሐይሎች ስርአቱን በሐይል ለማውረድ በረሃ ዘመሙ ። የኢትዮጵያ ህዝብም በነፃነትና ፍትህ እጦት ምክንያት የውጭ ተመፅዋች ለመሆን ተገደደ ። የደርግ ወታደራዊ ስርአት የተማሩ ወጣት ኢትዮጵያውያን በግፍና ሰቆቃ የገደለ ፣ የፈጀ ፣ ያሰረ ፣ የገረፈ ፣ ለድህነትና ሰደት ተጋላጭ እንዲሆን ምክንያት ነበር ። በደርግ ሰርአት ሰቃይና ሰቆቃ ያልደረሰበት ኢትዮጵያዊ ጥቂት ቢሆን ነው ። ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር የሚል መርህ የነበረው የደርግ ሰርአት የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት እንዲከስም ምክንያት ነበር ። በመሆኑ ኢትዮጵያ ከአብዮቱ መቀጣጠል (1966 ዓ.ም ) ጀምሮ የአገር ውስጥ ምርት ሳይሆን በውጭ እርዳታ ሰር ቆይታለች ። ከፍተኛ ወታደራዊ ተቋም በመገንባት የኢትዮጵያ ህዝብ በድህነት እንዲዳዳ ተደርጓል ። ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ የደርግ ስርአት ሥር የሰደደ ጭቆና እንዲሁም ሰብአዊ መብት ጥሰት የደረሰበት ቢሆንም በተለይ ደግሞ የትግራይ እና ኤርትራ ህዝብ ላይ ግድያና አፈና የከፋ ነበር ። በመሆኑም በተለይ የትግራይ ህዝብ ከሕወሓት ጋር ግንኙነት አለው በማለት ተደጋጋሚና ተደራራቢ ችግሮች ውስጥ እንዲወድቅ ተደርጐ ነበር ። አካባቢው ለቆ እንዲሰደድ የተደረገ ህዝብ ነበር ። በመሆኑም የትግራይ ህዝብ ሆነ የኤርትራ ህዝብ በወደቀው የደርግ ሰርአት ላይ ጥላቻ አሳድሯል ።

ከ 1967 ዓ.ም ጀምሮ የደርግ ሰርአት በጦርነት ሲፋለሙ የነበሩ ጥምር የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሐይሎች በሕወሓት እገዛ ወታደራዊ የደርግ ሰርአት በሐይል ከስልጣን በማውረድ ኢትዮጵያ ለማስተዳደር በለስ ቀንቷቸው ነበር ። ኢህአዴግ በሚል ምሕፃረ ቃል ሰያሜ በመያዝ በ 1983 ዓ.ም ግንቦት ወር ላይ አዲስ አበባ የገባው የኢህአዴግ ሰራዊትና ሰርአት በመጀመሪያ አምስት አመታት የኢትዮጵያ ህዝብ ቀልብ ስቦ ነበር ። የዲሞክራሲ ፍኖተ ጅምር የታየበት ፣ ወንጀል ነክ የከተማ እንቅስቃሴዎች የታገቱበት ፣ በከፊል ፍትህ የሰፈነበት ፣ የመናገር ፣ የመፃፍና የመሰብሰብ ነፃነት ጅምር የታየበት ፣ በሌላ ጎን ደግሞ የደርግ ተቋማት የፈረሱት ፣ የከፍተኛ ተቋም መምህራን ፍትሀዊ በጎደለው ምክንያት ከሰራ ገበታቸው የተቀነሱት ፣ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ተቋማት በኤርትራውያን እጅ የወደቀበት ክሰተት ነበር ። በወታደራዊ መንግሥት (ኢሠፖ) ሰርአት ተቀጥሮ የአገሩን ደርድንበር ለማስከበር ሲፋለም የነበረው ተራ የደርግ ወታደር ሳይቀር እንዲበተን መደረጉ የኢትዮጵያ ህዝብ በኢህአዴግ ሰርአት ላይ ከፍተኛ ጥላቻና ቂም አሳድረዋል ። በመሆኑም በጊዜ ሒደት የኢህአዴግ ሰርአት በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ ተቀባይነቱ እየቀነሰ መጣ ። ኢህአዴግ የተደራጀ የአገር መከላከያ ሰራዊት መልሶ ከማደራጀት ይልቅ ደምሮ መበተኑ ታሪካዊ ስህተት ነበር ። የከፍተኛ የትምህርት ተቋም መምህራን ያለአግባብ ከሰራቸው እንዲቀነሱ መደረጋቸው በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ ጥላቻና ቁጣ ምክንያት ከመሆን ያለፈ ለኢህአዴግ ሰርአት ያስገኘው ጉዳይ የነበረ አይመስለኝም ። በመሆኑም የኢህአዴግ ሰርአት የወሰደው መምህራን የማባረር ጭፍን የፖለቲካ ውሳኔ ስህተት ነበር ።

በግንቦት 20/1983 ዓ.ም አዲስ አበባ የገባው የኢህአዴግ ሰርአተ መንግስት ግንቦት 20 ቀን የኢትዮጵያ ክብረ በዓል እንዲሆን ቢያውጅም በኢትዮጵያ ህዝብ ብዙም ተቀባይነት ሳያገኝ ዘልቀዋል ። ምክንያቱ ደግሞ የኢትዮጵያ የውስጥ ጦርነት ( Domestic War ) ስለነበር አሸናፊ እንዲሁ ተሸናፊ አይኖርም የሚል አሰተሳሰብ በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ በስፋት ይደመጣል ፣ ይነገራል ፣ ይሰማል ። ለአብነት የዓድዋ ጦርነት የውጭ ጠላት ወረራ በመፈፀሙ ወራሪው ከአገር ለማስወጣት ፍትሀዊ ጦርነት በመካሄድ የኢትዮጵያ የብስራት ድል ተደርጎ በሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ የዓድዋ ቀን ተከብሮ ፣ ተዘክሮ ፣ ታሰቦ ይኖራል ። ግንቦት 20 እንደ አገራዊ በዓል ተደርጎ የማይታይበት አብይ ጉዳይ የአንድ አገር ዜጎች የውስጥ የፖለቲካ ጭቆና ለመለወጥ ያካሄዱት የእርስ በእርስ ውስጣዊ መጠቃቃት በመሆኑ ነው ። በመሆኑም ግንቦት 20 የነፃነት ክብረ በዓል አድርጎ መሰየሙ አግባብነት የለውም የሚል አሰተያየት በስፋት ይሰነዘራል ። አለፍ ሲልም ግንቦት 20 ለጥላቻና ቂም በቀል ምክንያት ሆነዋል የሚሉ እንዳሉም መገንዘብ ያሰፈልጋል ። ግንቦት 20 ለአገር ግንባታ እንቅፋት እንደሆነ ሲተነትኑ ይታያል ። የሆነ ሆኖ ግንቦት 20 በተመለከተ የኢትዮጵያ ህዝብ አንድነት የሚያጠናክር ሆኖ አልተገኘም ። አንድ ሰርአት በሌላ ሰርአት ሲተካ መተካካቱ የድል ክብረ በዓል ቀን አድርጎ ማሰብ የድል መርህ የሚጣረሰ መሆኑን የሚናገሩ እንዳሉም ይታመናል ። ከወታደራዊ የደርግ ሰርአት መወገድ ማግስት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ለውጦች መኖራቸው ለመካድ የሚችል ሰው ያለ አይመስለኝም ። ምንም እንኳን በተፈለገው መጠን ፣ አይነትና ጥራት ባይሆንም በኢህአዴግ ሰርአት የተከናወኑ በርካታ አገራዊ ልማቶች ተከናውነዋል ። በሌላ በኩል ግንቦት 20 የነፃነት ቀን ሳይሆን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ደህንነትና ጥቅም ማጥ ውስጥ ያስገባ የጨለማ ቀን አድርጎ የሚገነዘቡ በርካታ ናቸው ። ለአብነት የኤርትራ መነጠል ፣ የአሰብ ወደብ ለጋራ ተጠቃሚነት ድርድርና ስምምነት ላይ አለመድረስ ፣ የድንበር አዋሳ ቦታዎች ያለ በቂ ጥናት ፣ ምክንያትና ድርድር ለጎረቤት አገር አሳልፎ መሰጠት ፣ በአጠቃላይ ኢትዮጵያ አለምአቀፋዊ ሆነ አህጉራዊ የንግድ ማሳለጫ ወደብ አልባ እንድትሆን ግንቦት 20 ምክንያት ሆነዋል የሚሉ አያሌ ናቸው ።

ኢህአዴግ ከምርጫ 97 በኋላ የዲሞክራሲ እድገት የሚፃረሩ የፀረሽብር ህጉን ጨምሮ አፋኝ ህጎች በማውጣት የሰበአዊ መብት ጥሰት እንዲፈፀም ምክንያት ሆነዋል ። የሰብዓዊ መብት ጉዳይ አለምአቀፋዊ በመሆኑ መከበር የነበረበት ጉዳይ ነበር ። የኢህአዴግ ስርአት የሚቃወሙ በውጭ አገራት ቡዙሃን መገናኛ በመክፈት ስርአቱ ላይ እንዲሁም የተመረጡ የስርአቱ ሀላፊዎች ላይ የማያቋርጥ የስም ማጥፋት ዘመቻ ሲፈፀም ነበር ። በተለይ የኢህአዴግ ሰርአት የደህንነትና የመከላከያ ተቋማት ላይ ከፍተኛ ትችት ሲደረግባቸው የቆዩ ተቋማት ናቸው ። መነሻው ከጥላቻ የነፃ ባይሆንም የአንድ ዘር የበላይነት ተስፋፍቷል በሚል በተለይ በትግራይ ተወላጅ የኢህአዴግ ሰርአት ሀላፊዎች ላይ የከረረና የሰላ ወቀሳና ትችት ሲተላለፍ ነበር ። ለኢህአዴግ ስርአት የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያነሳቸው የመብትና የዲሞክራሲ ጥያቄዎች በተገቢው ሁኔታ ከማስተናገድ ይልቅ አፈና መከተሉ ጥሩ አማራጭ አልነበረም ። የአገር ግንባታ ለማሳለጥ የሐሳብ የፖለቲካ ልዩነቶች በውይይት የሚፈታ አካሄድ መከተል ጥሩ የመፍትሔ አማራጭ ነበር ። ሆኖም ሰላማዊ ውይይቶች ለመተግበር የኢህአዴግ ሰርአት ለይስሙላ ካልሆነ በፖሊስ የተደገፈ ተግባራዊ አፈፃፀም አልነበረውም ። በመሆኑም የኢህአዴግ ሰርአት የሚቃወሙ የፖለቲካ ድርጅቶች በግንቦት 20 አገራዊ ክብረ በዓል ሆነ በአሁኑ የኢትዮጵያ ሰንደቅዓላማ ላይ አገራዊ ስምምነት አልነበረም ። ግንቦት 20 የኢህአዴግ ሰርአት የስርአቱ አላማ ማስፈፀሚያ ከመሆን ባሻገር የኢትዮጵያ ህዝብ የሚጋራው ክብረ በዓል ሊሆን አልቻለም ። በግንቦት 20 ሆነ የአሁኑ የኢትዮጵያ ሰንደቅዓላማ ላይ የተሟላ አገራዊ መግባባት የለም ። አገራዊ መግባባት ያለመኖሩ አደጋ ባይሆንም የኢትዮጵያ ህዝብ ድምፅ መከበር ይኖርበታል ።

ኢትዮጵያ ለሁሉም ዜጎች እኩል መብትና ክብር የምታጎናፅፍ አገር መሆን ይኖርባታል ። ለዚህም ህግና መመሪያ የሚያከብር የህዝብ አሰተዳደር መንግስት እንዲሁም መብቱና ግዴታው የሚያውቅ ህዝብ የጋራ መግባባትና መናበብ መኖርና ማደግ ይኖርበታል ። ከፋፋይ የመንግስት አሰተዳደር ለአገር ደህንነት ሆነ ለአገር ግንባታ ጠቀሜታ ስለማይኖረው በዜጎች በጎ ፍቃድና መግባባት ላይ የተመሰረተ የመንግስት አስተዳደር መኖሩ ደህንነቱ የተጠበቀ ዜጋ እንዲኖር ከዛ በላይም ለአገሩና ለህዝቡ የሚቆረቆር ዜጋ ለማብቃት የሚያግዝ ይሆናል ። የኢትዮጵያ ህዝብ በብልሹ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ምክንያት የፖለቲካ አሰተዳደር ላይ ያለው ግንዛቤ ድፍርስ ነው ። የኢትዮጵያ ህዝብ ለፖለቲካና ፖለቲከኞች ከፍተኛ ጥላቻና ቂም አለው ። የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሰልጣን አሰተዳደር የዜጎች መብትና ደህንነት ባማከለ ህገ ደንብ መሠረት አድርጎ ለዜጎች ሁለንተናዊ ለውጥ የሚሰራ ሳይሆን በዜጎች ላይ የአፈና ሲቀጥልም የመብት ጥሰት የሚፈፀም በመሆኑ ዜጎች በመንግሥት ላይ ጥላቻ ያሳድራሉ ። መንግስት የህዝብ በደል ከመከላከል ይልቅ ራሱ ህዝብ በዳይ በመሆኑ በሁሉም የኢትዮጵያ ህዝቦች ላይ አካላዊ ሆነ መንፈሳዊ ቁሰል እንዲሰፋፋ ምክንያት ሆነዋል ። መንግስት አፋኝና ገዳይ በመሆኑ በኢትዮጵያ ህዝብ ጥላቻና በቀል ሥር እንዲሰድ ሆነዋል ። ህዝብ እርስ በእርስ እንዳይተማመን ሆነዋል ። ብሔርተኝነት እንዲሰፋፋ የመንግስት አፈና እንደምክንያት ይወሰዳል ። የአገር ግንባታና የአንድነት መንፈስ እንዲዳከም የፖለቲካ ስልጣን አሰተዳደር መዛባት በምክንያትነት ይጠቀሳል ።

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሰልጣን የዜጎች ደህንነት ፣ የአገር ግንባታና አንድነት ፣ የዲሞክራሲ መርህ በተግባር የሚያስፈፅም ፣ እንዲሁም ፍትሀዊ የተፈጥሮ ሆነ ሰው ሰራሽ ሀብቶች ለዜጎች የሚያዳርሰ የመንግስት ሰርአት መገንባት ይኖርበታል ። ከጥላቻ የፀዳ ፖለቲካ ለኢትዮጵያ የመኖር እና ያለመኖር ምርጫ ነው ። የዜጎች ደህንነትና መብት የማያስከብር የመንግስት ሰርአት በኢትዮጵያ ምድር መኖር የለበትም ። በዘርና ቋንቋ ህዝብ የሚለያይ የመንግስት ሰርአት የዜጎች ሁለንተናዊ ጥቅምና ደህንነት የሚፃረር መሆን የለበትም ። ዜጎች በማንነታቸው ፣ ታረካቸወና ባህላቸው አዳብሮ ተከባብሮ እንዳይኖሩ የጥላቻ ፖለቲካ እንቅፋት ሆኖባቸዋል ። የህዝብ የፖለቲካ ተሳትፎ እንዲቀንሰ የፖለቲካ አፈና አንዱ ምክንያት ሆነዋል ። በፖለቲካ ጥላቻ ምክንያት የአንድ አገር ዜጎች በጥርጣሬ አይን እንዲተያዩ ምክንያት ሆነዋል ። ዜጎች በጋራ ለጋራ ልማትና መከባበር በጋራ እንዳይኖሩ ፣ የአገር ግንባታና አንድነት በጋራ እንዳያሳኩ የፖለቲካ አሰተዳደር ሰርአት መሰናክል ሆኖባቸዋል ።

በፖለቲካ ጥላቻ መነሾ ዜጎች ከሚኖሩት ክልል በሐይል እንዲፈናቀሉ መደረጉ ታላቅ ታሪካዊ ስህተት ነው ። ይህ የአገር ግንባታ ሆነ የአገር ደህንነትና አንድነት በጥልቀት የሚጎዳ ክሰተት በመሆኑ ጥሩ የመፍትሔ መንገድ መበጀት አለበት ። የዜጎች የመኖር መብት እየተጣሰ ስለአገር ደህንነትና ልማት ማሰብ ጫቅላነት ነው ። ዜጎች በመተሳሰብ አንድ ላይ እንዳይኖሩ የሚከለክል ተፈጥሯዊ ክሰተት ሳይሆን መርህ አልባ የመንግስት የፖለቲካ አሰተዳደር ነው ። ዜጎች የሚያከብሩት የፖለቲካ ሰርአት መገንባት ፋይዳው ለመጪው ትውለድ ማሰብ ጭምር ነው ። የኢትዮጵያ መጪው ትውለድ ፍቅርና አንድነትን እንጂ ያደረ የፖለቲካ ጥላቻ ቅሪት መውረስ የለበትም ። በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ህልውና ፈተና የሆነው አንዱ ችግር የኢትዮጵያ ህዝብ በዘር ማሰብ መጀመሩ ነው ። የእኛ የሚል እምነትና ሰሜት ተሸርሽሯል ። በጋራ ለጋራ እድገት የሚል ዜጋ ብዙም አይታይም ፣ አይሰማም ። የፖለቲካ ሰልጣን ሆነ ንግድ የዘር ሐረግ መነሻ ያደረገ ሆነዋል ። ይህ ደግሞ የአገር ደህንነት ስጋትና አደጋ እየሆነ መጥቷል ። ሰርአት አልበኝነት እንዲሰፍን የዘር ፖለቲካ ምክንያት ሆነዋል ። ፍትህ ፣ የህግ ተጠያቂነት እንዲሁም ሰላምና መረጋጋት የዜጎች አብይ ሥጋት ሆነዋል ። የሁሉም የበላይ ችግር የፖለቲካ አሰተዳደር ሰርአት በዲሞክራሲ መርህ እና በህግ የበላይነት የታነፀ ካለመሆን ጋር ተያይዞ የመጣ ችግር ነው ። ይህ ችግር እስካልተፈታ የዜጎች በሰላም የመኖር መብት መጣሱ አይቀርም ። የኢትዮጵያ ህዝብ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ስረአት ከታደሰ ይበልጥ ያዘንና የተከፋ በብዙ እጥፍ ይበልጣል ። በመሆኑም የጥላቻ ቁሰል በሁሉም የኢትዮጵያ ዜጎች ሥር ሰዶ እንደሚገኝ መገመት አያዳግትም ። በመሆኑም የጋራ አገራዊ መፍትሔ መሻት ያሰፈልጋል ። የህግ የበላይነት ማስፈን ፣ በዲሞክራሲ መርህ መመራት ፣ ተጠያቂነት ያለው የመንግስት አሰራር መከተል ፣ ለሁሉም የኢትዮጵያ ዜጎች ላለፈው የመንግስት የመብት ረገጣ ክንውን ይቅርታ መጠየቅና ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ሙሉ የሞራል ሆነ የገንዘብ ካሳ መፈፀም ፣ የህዝብ ዲሞክራሲያዊ መብቶችና ድንጋጌዎች አክብሮት መሰጠት ፣ የመገናኛ ብዙሃን ባለሞያዎች በነፃነት ህግን መሠረት አድርጎ ሞያዊ ግዴታ እንዲወጡ ማድረግ ፣ የመንግስት የፖለቲካ አፈና ማስቀረት ፣ በዘር ሐረግ ያለአግባብ የስልጣን መጠቃቀም ማቆም ፣ የዜጎች በሁሉም የክልል ቦታዎች የመሥራትና የመኖር መብት ማክበር የኢትዮጵያ ህዝብ የፖለቲካ ጥላቻ ፣ እንዲሁም ቂም በቀል እንዲሻር ያግዛል ።

የኢህአዴግ ዘር ተኮር የፖለቲካ ሰርአት ዲሞክራሲ ማዕከል ያደረገ ቢመስልም በተግባር የሆነው ግን አፈናን ማስፋፋት ነው ። የኢትዮጵያ ህዝብ ከኢህአዴግ የስርአት ስያሜ ጋር ምንም ጉዳይ የለውም ። ችግሩ የድርጅቱ ስያሜ ሳይሆን ተግባሩ ነው ። በመሆኑም የኢህአዴግ ተግባር የተለየ ሓሳብ የነበራቸው የራሱ ድርጅት ሰዎች ሳይቀር የሚያጠቃ ፣ የሚያስር ፣ ከሥራ የሚያባርር ፣ የሚያሳድድ ፣ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ስሜትና የሞራል ሰብዕና የሚያሳንስ የፖለቲካ አሻጥር ሲፈፀም የነበረ አምባገነን የፖለቲካ ድርጅት ነው ። በሰብዓዊ መብት ረገድ የኢህአዴግ የፖለቲካ ሰርአት ከወታደራዊ የደርግ ሰርአት የሚለው በጠራራ ፀሐይ በአደባባይ ሰው ያለመግደሉ እንጂ ተመሳሳይ የአፈና እንዲሁም የህግ ጥሰት ነበራቸው ። ኢህአዴግ በደህንነት ድርጀቱ ዜጎች ሲያሰቃይ ነበር የደርግ ሰርአት ደግሞ በአደባባይ ሰው ይረሸን ነበር ። ልዩነት የሰብአዊ መብት ጥሰቱ የቀንና የሌሊት መሆኑ ብቻ ነው ። ኢህአዴግ በደህንነት ድርጅቱ የፈፀመው ዜጎች የማሰቃየት ተግባር በኢትዮጵያውያን ውግዘትና ውርደት እንዲደርስበት ሆነዋል ። የኢህአዴግ ሰርአት ልክ እንደ ወታደራዊ የደርግ ሰርአት በህዝብ እንዲጠላ ሆነዋል ። የኢህአዴግ ሰርአት በኢትዮጵያ ህዝብ እንዲጠላ ምክንያት የሆነው ድርጅቱ በፈፀመው አፈናና ሰብአዊ መብት ፤ ምክንያት ነው ። በመሆኑም የኢትዮጵያ ሰርአት ለፈፀመው የዜጎች መብት ጥሰት ለኢትዮጵያ ህዝብ ይቅርታ ጠይቆ ህዝብ የሚወሰነው ከፍተኛ ቅጣት ለመቀበል መዘጋጀት ይኖርበታል ። ይህ ሰርአት በህዝብ የነበረው ከፍተኛ ተቀባይነት እንዲከስም ያደረገው በተደጋጋሚ በፈፀማቸው የአፈና መዋቅራዊ ተግባራት ምክንያት ነው ።

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ዲሞክራሲ እንዲሁም የፖለቲካ ኢኮኖሚ ሥር እንዲሰድ የታሪክ ስህተቶች ላይ ትኩረት ማድረግ አስፈለገ አይመስለኝም ። መልካም ተግባራት በማተለቅ ዛሬ ላይ ሆኖ ለነገ የሚሆን የአገር አንድነት ሰሜት እንዲያገግም ፣ ለሁሉም ዜጎች የሚበቃ የዲሞክራሲ አገር መገንባት ለፖለቲካ ድርጅቶች የሚተው ጉዳይ አይደለም ። ሁሉም ዜጎች ለመብታቸው መከበር መታገል ይኖርባቸዋል ። ጥላቻና ቂም በቀል በመተው በጋራ ለመኖር በጋራ የአገርና የፖለቲካ ሰርአት ግንባታ ላይ መረባረብ የዜግነት ግዴታ መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል ። የተሻለ የፖለቲካ ዲሞክራሲ ሰርአት እንዲገነባ የሁሉም ዜጋ የተጋ ተሳትፎ ያሰፈልጋል ። ለሁለንተናዊ መብት የቆመ ህዝብ አምባገነን የፖለቲካ ሰርአት እንዳይሰፍን ምክንያት ይሆናል ። በረጅም ጊዜ እየተከማቸ የመጣ የፖለቲካ ጥላቻ በአንድ አገር የሚኖሩ የአንድ አገር ዜጎች ማህበራዊ ቀውስና መፈናቀል ምክንያት ሆነዋል ። ላለፉት ሐምሳ አመታት በኢትዮጵያ ያልተዘራ የክፋት ዘር የለም ። የፖለቲካ ስርአቶች በመፈንቅለ መንግስት አልያም በጦርነት ተለውጧል ። በፖለቲካ አፈና ምክንያት ዜጎች አገር ለቆ ተሰዷል ፣ ለሞትና እስር ተዳርጓል ፣ ሀብት ንብረታቸው አጥቷል ፣ አገራቸው ተመልሶ እንዳይገቡ የህግ ክልከላ ተደርጎባቸዋል ቆይቷል ። በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ምድር ሳይፈፀም የቀረ የክፋት ሥራ የለም ማለት ይቀላል ። ከሞተ አንበሣ ማር ይወጣል እንደሚባል አሁን የኢትዮጵያ ህዝብ ማከናወን ያለበት ጉዳይ እንደ ህዝብ እንደ ዜጋ ለአገር ለህዝብ የሚበጅ መልካም ተግባራት ማከናወን ብቻ ነው ። የክፋት ዘሮች ሁሉም ተፈፅሟል ። የቀረ ቢኖር ለበጎ ተግባር መዘጋጀት ብቻ ነው ። በተለያዩ ማህበራዊ መስኮች የተጎዳ አገር መልሶ ለመገንባት የተራዘመ ጊዜ ቢያስፈልግም አገራዊ መግባባት ለማፋጠን ሁሉም በጋራ ለበጎ ሥራ መዘጋጀት ይኖርበታል ።

በኢትዮጵያ የፖለቲካ አሰተሳሰብ የፖለቲካ የሐሳብ ልዩነት ማስተናገድ የማይችል ተቋም አልባ በመሆኑ ለፖለቲካ ሆነ ማህበራዊ ግጭቶች ምክንያት ሆኖ ዘልቋል ። የዜጎች የመኖር መብት የሚፃረር የፖለቲካ አሰተዳደር ተስፋፍቶ የነበረ በመሆኑ ለአንድ አገር ማህበረ ኢኮኖሚ ግንባታ የበቃ ማህበረሰብ (ህዝብ ) መገንባት ሳይቻል ቀርቷል ። ሥር የሰደደ ድህነት ላይ ሥር የሰደደ ኢዲሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሰርአት ተደምሮበት የኢትዮጵያ ህዝብ የስልጣኔ ጭራ ላይ እንዲኖር ተገዷል ። በኢትዮጵያ ሰፊ የፖለቲካ አሰተሳሰብ ጥላቻ የመኖሩ ያህል መልካም መርህ ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ አሰተሳሰብ ይኖራል ። ፌደራላዊ ሰርአት ማዕከል ያደረገ የዜግነት የፖለቲካ አሰተሳሰብ ለኢትዮጵያ ህዝብ ይመጥናል የሚል አሰተሳሰብ አለኝ ። የዘር የፌዴራል ሰርአት ለአገር ግንባታና አንድነት መዳከም ምክንያት ሆኗል የሚሉ አሰተያየት ሰጪዎች እጅግ በርካታ ናቸው ። አልፎ ተርፎም ዘር ተኮር የፌዴራል ስርአቱ የዜጎች ሰብዓዊ መብት የረገጠ ፣ ለዜጎች መፈናቀል ምክንያት የሆነ ፣ የዲሞክራሲ ተቋማት ያፈረሰ ፣ ለዜጎች መሰደድና አፈና መነሻ ምክንያት አድርጎ የሚተነትኑ ዜጎች ቁጥር በርካታ ነው ። በኢትዮጵያ የዘር ፖለቲካ ፌደራል ሰርአት በተግባር ተፈትኖ የከሸፈ እንደሆነ ይተነትናሉ ። የዜጎች ህገ መንግሰታዊ መብት አላስከበረም በማለትም ይሞግታሉ ። ይህ ምክንያታዊነት ያለው አብይ መከራከሪያ አጀንዳ ይመስለኛል ። የዜጎች ሰብዓዊ መብት የማያከብር ፣ የአገር ግንባታ የማያፋጥን ፣ የአገር ደህንነትና ሰላም የማያሰፍን የፖለቲካ ሰርአት ለአንድ አገር ፈፅሞ የሚበጅ አይሆንም ። በመሆኑም የዜጎች ሰብዓዊ መብት እንዲሁም የአገር ግንባታና አንድነት የሚያስከብር ፣ የሚያስጠብቅ ፣ የሚያከናውን የፖለቲካ አሰተዳደር ሥርአት መገንባት አገራዊ ግዴታ ነው ። በዘር የፌዴራል ሰርአት የግለሰብ መብት የሚያስከብር የህግ ሥርዓት አተገባበር ላይ የአፈፃፀም ፣ የግልፅነት ፣ እንዲሁም የትርጉም ችግር አለበት ። የዘር ፖለቲካ ሥርዓት የቡድን (ዘር ) መብት እንጂ የግለሰብ መብት ላይ የህግ አፈፃፀም ጉድለትና ክፍተት ያለበት በመሆኑ ግለሰቦች ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ የዜግነት መብት ጥሰት ሲፈፀምባቸው ነበር ። በአሁኑ የኢትዮጵያ የዘር ፖለቲካ ሥርአት አንድ ዜጋ የህግ ፍትህ ለማግኘት በዘር ሐረጉ ተደራጅቶ ፍትህ መጠየቅ ይኖርበታል ማለት ነው ። ይህ ደግሞ የዜጎች ሰብዓዊ እንዲሁም የመኖር ነፃነት የሚጋፋ በመሆኑ ተቀባይነት አይኖረውም ።

በኢትዮጵያ የማንም ዜጋ መብት መከበር ማዕከል አልፍፎ ተርፎም ለዜጎች መብት መከበር ቅድሚያ የሚሰጥ የዜግነት የፖለቲካ ሰርአት ማነፅ ተገቢነት አለው ። ለዜጎች መብት መረገጥ በዘር መደራጀት የህግ መስፈን አልያም የህግ ልዕልና አያረጋግጥም ። የአንድ ግለሰብ ዜጋ ህጋዊ መብት ሳይከበር የህዝብ መብት አይከበርም ። ምክንያቱም ህዝብ የግለሰቦች ውህደት ነው ። የዜጎች መብት በመጨፍለቅ የዘር መብት ማስከበር የሚያስችል አለምአቀፍ የመብት አያያዝና አጠባበቅ መርህ የለም ። በመሆኑም የኢትዮጵያ ዜጎች ሰብዓዊ ሆነ ዲሞክራሲያዊ መብቶች የሚያስከብር የዜግነት የፖለቲካ ሰርአት መንገስ ይኖርበታል ። የግሌ ህጋዊ መብት ሳይከበር የእኔ የዘር ሐርግ የህግና ፍትህ ከለላ ያገኛል የሚል እምነት ሆነ አመለካከት የለኝም ። ምክንያቱም ለዜጎች መብት ያልቆመ የፖለቲካ ሰርአት የዜጎች የመኖር መብት የሚፈታተን ከመሆኑም ባሻገር የአገር ግንባታና አንድነት የሚያደፈርስ በመሆኑም ጭምር ነው ። ዘር ተኮር የፌዴራል ሰርአት ከእኔ ዘር በቀር ማንም አይድረሱብን የሚል እንደምታ ያለው በመሆኑ ለዜጎች መከፋፈልና መፈናቀል ምክንያት ሆነዋል ። የአሁኑ የኢትዮጵያ የዘር ፖለቲካ ፌደራል ሰርአት ዜጎች በጠላትነት የሚፈርጅ የጥላቻ ፖለቲካ የሚያራምድ በመሆኑ የኢትዮጵያ ህዝብ በስርአቱ ላይ እምነት የለውም ።

በኢትዮጵያ ጠላትና ወዳጅ የሚፈጥር ፣ የሚያስፋፋ የፖለቲካ ሰርአት ጭራሽ አያስፈልግም ። ዘር ተኮር የኢህአዴግ ሰርአት ዜጎች በጠላትነትና ወዳጅነት የሚከፋፍል ካንሰር ነው ። ወዳጅ ለጥገኝነት ፣ ለስርቆት ፣ እንዲሁም ለአድርባይነት የሚያበረታታ ሲሆን ጠላት የሚለው ደግሞ መኖሪያ በማሳጣት ማሰቃየት ፣ ማሰርና መግደል አላማ ያደረገ ሰርአት ነው ። ይህ የዘር የፖለቲካ ፌደራላዊ ሰርአት የሚከተለው ድርጅታዊ መርህ አፈና በመሆኑ የአደረጃጀት ፣ የአስተዳደርና የአስተሳሰብ ለውጥ ያመጣል ተብሎ ፈፅሞ አይታሰብም ። መፍትሔ ስርአቱን ማሰወገድ ብቻ ነው ። በኢትዮጵያ የማህበረሰብ ትስስር በጥላቻ እንዲቀሸር የኢህአዴግ የዘር ፖለቲካ አሰተዋጽኦ አድርጓል ። የኢትዮጵያ ህዝብ በጠላትነት አይን እንዲተያይ ምክንያት ሆነዋል ።

የኢትዮጵያ ህዝብ የፖለቲካ ቂም በቀላሉ የማይተው ህዝብ በመሆኑ አድሮ የመበቀል ሁኔታዎች በተደጋጋሚ ይስተዋላሉ ። አድንቆ የፖለቲካ ሰልጣን እንዳልሰጠ መሪው አዋርዶ የማውረድ ባህል ያለው ህዝብ በመሆኑ የፖለቲካ አሰተዳደር ብቃት የሚጠይቅ የፖለቲካ ሰርአት እንዲሁም የበቃ አመራር ማስፈን ይጠይቃል ። የኢትዮጵያ ህዝብ የሚመጥን የዘመኑ የላቀ የፖለቲካ አሰተዳደር ማስፈን የማይችል የፖለቲካ ስርአትና ድርጅት በኢትዮጵያ ሥፍራ አይኖረውም ። ምክንያቱም በምክንያት የሚያምን ዜጋ በስፋት እየተስተዋለ መሆኑ በቃና አበረታች መሆኑ ነው ። የሴራም ሆነ የአፈና ፖለቲካ የሚያስተናግድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ለመኖሩ እጠራጠራለሁ ። በመሆኑም ለዜጎች ደህንነትና ሰላም ቅድሚያ የሚሰጥ የፖለቲካ ሰርአት ሥር እንዲሰድ የሁሉም ዜጎች የውል ሀላፊነት መሆን አለበት ። በኢትዮጵያ ዜጎች የሚመሩት የፖለቲካ ሰርአት ማስፈን ካልተቻለ ሁሉም የሚመኘው የተፋጠነ የአገር ግንባታ ሆነ የአንድነት ስሜትና ፍላጎት ማሳካት የሚቻል አይመስለኝም ። በኢትዮጵያ ፈጣን ልማትና ሰላም እንዲረጋገጥ የእያንዳንዱ ዜጋ መብት መከበር አለበት ። የአንድ ዜጋ መብት ሳይከበር የቡድን መብት የሚከበርበት የፍትህ መርህ የለም ። ለፍትህና ፍትሐዊ የመኖር መብት እንዲሁም ደህንነት በፍትሐዊ ፍትህ የሚያምን ዜጋ መኖር አለበት ። አለዚያ ዜጋን እያፈኑ መብት አለ ማለት የመብት መርሆ መፃረር ይሆናል ። ለዜጎች መብት የቆመ የፖለቲካ ሰርአት መመሰረት የአገር አንድነትና ልማት ያፋጥናል ፣ ዜጎች ለህግና ህገ መንግስት ስርአቱ ተገዢ ይሆናሉ ፣ አስተማማኝ ሰላምና እንዲኖር ግብአት ይሆናል ፣ የጥርጣሬ ፖለቲካ ያስወግዳል ፣ ዜጎች በመከባበርና መተሳሰብ ላይ የፀና ግንኙነት እንዲያዳብሩ ያበረታታል ፣ ዘላቂነት ያለው የፖለቲካ ሰርአት ተቋም እንዲገነባ መሠረት ይሆናል ፣ ፍትህና የህግ የበላይነት መሠረት እንዲጣል ያግዛል ፣ ፍትሀዊ የሀብት ተጠቃሚነት ያሰፍናል ፣ ቂም በቀልና ጥላቻ እንዲሸር ፣ በአጠቃላይ የዜጎች ሁለንተናዊ ቀናኢ ግንኙነት የሰመረ እንዲሆን በኢትዮጵያ የሚመሰረተው የፖለቲካ ሰርአት ወሳኝነት ይኖረዋል ።

 

Back to Front Page