Back to Front Page

ስለ ODP ስብሰባ ሹክ ልበላቹህ?

ስለ ODP ስብሰባ ሹክ ልበላቹህ?

 

Alemayohu Mihrete

Arat Killo

Tikmt 2012

 

የቤተመንግስቱ የኦዲፒ ማእከላይ ኮሚቴ ስብሰባ በተመለከተ ሹክ ልበላቹህ። ሹክ ሲሉኝ የሰማሁትን ያህል ሹክ እላለሁ። ጆሮ የሰማችውንና ያደመጠችውን ያህል ሳልጨምር፣ ሳልቀንስና ሳልደብቅ ወደ እናንተ እፅፋለሁ። የሹክሹክታ ፍልስፍና ግልፅነትን የሚፈሩ አምባገነኖች ማጋለጥ ላይ የተመሰረተ የትግል ዘይቤ ነው።

 

ከመደመር ፍልስፍና በተሻለ የሹክሹክታ ፍልስፍና አንድ መፅሐፍ ሳይሆን ብዙ ቅፆች (ቮልዩም) ያላቸው መፃሕፍት መፃፍ ይቻላል። ግን ኢትዮጵያችን ያጋጠማት ችግር ለመፍታት አይደርስም። ጊዜ የለም። የስብከት መፅሐፍ ሳይሆን የተግባር መመርያ መፅሐፍ ስለሆነ ብዙ ጥናትና ምርምር ይፈልጋል። የሹክሹክታ ፍልስፍና መፅሐፍ እስኪዘጋጅ ግን ትግላችን መቆም የለበትም። መንሾካሸክን እንቀጥላለን።

Videos From Around The World

 

የኢህአዴግ የስራ አስፈፃሚና የምክርቤት ስብሰባዎች ከአሁን በኃላ በቀጥታ በሚዲዎችን አሰራጭተን እናሰማቹኃለን ያሉን አብይ አህመድ ካሉን በሁለት ዓመት ዕድሜያቸውም ንግግራቸውም አርጅቷል። ነገር ግን የተለወጠ ነገር የለም፡፡ እንዳውም የባሰ ነገር ፈፀሙ፡፡ ስትስጥ የነበረችው መግለጫ ተብዬም ጭራሽ ቀረች። ታድያ ምን አማራጭ አለን፡፡ ያለን አንድ አማራጭ ሹክሹክታ ነው። ሹክ የሚሉ የሹክሹክታ ሰዎች ዕድሜ ይስጣቸው።

 

መንደርደያ አበዛሁ መሰለኝ። በቀጥታ ወደ ወቅታዊ ሹክሹክታ።

 

ሹክ አንድ፡- አብይ አህመድ ለረዥም ጊዜ ማዕቀብ ያደረጉለት ስብሰባ ነበር የተካሄደው። እሳቸው እርካቡን ከረገጡ በሃላ የኦዴፓ ማእከላይ ኮሚቴ ተሰብስቦ አያቅም። ከረዥም ጊዜ በኃላ የተገናኘ ማእከላይ ኮሚቴ የተበታተነ ሃሳብና ፍላጎት ያለው እንደሚሆን አውቀው ነበር ስብሰባውን ዕድል ነፍገውት የቆዩት። ማ? አብይ አህመድ።

 

በኦዲፒ የውስጥ ህገ ደንብ መሰረት ከጉባኤ ቀጥሎ ትልቅ ስልጣን ያለው አካል ይህ ማእከላይ ኮሚቴ ነው። በፈለገው ሰዓት ተነስቶ ሊቀመንበሩንና ምክትል ሊቀመንበሩን አውርዶ በሌላ መቀየር ይችላል። አብይ ይህን ያቃሉም ይፈራሉም፡፡ እንደ ደብረፅዮን አስር ጊዜ ማእከላይ ኮሚቴውን መሰብሰብ አይፈልጉም፡፡ ድፍረትና በማእከላይ ኮሚቴው መተማመንን ይጠይቃልና። አብይ እንደዚህ ዓይነት ጫወታ አይወዱም። በስልጣን ቀልድ የለም! ሰለዚህ እሳቸው ባሻቸው ግዜ ብቻ ነው ማእከላይ ኮሚቴው መሰብሰብ የሚችለው፡፡

 

ሹክ ሁለት፡- ስብሰባው የተካሄደው በሚኒልክ ቤተመንግስት ውስጥ ነበር፡፡ ተሰብሳቢዎቹ ከሌላው ግዜ የገጠማቸው አስደንጋጭ ሁኔታ ነበር። ፍተሻው ለጉድ ነበር። የሁሉም የሴት ማእከላይ ኮሚቴ አባለት ቦርሳ ያለው ነገር ሁሉ ተበርብራል፡፡ ለዛውም ይዘውት አልገቡም። ከዚህ በላይ በጣም የሚያስጠላው ነገር የአካል ፍተሻው ነበር። ፈታሾቹ ሴቶች ቢሆኑም መላ አካላቸውን እየጎነታተሉና እየነካኩ አስቸግረዋቸው ነበር፡፡ ገሚሶቹ እዚህ ደግሞ ምን እንዳይኖር ነው የምትነካኪኝ ቢሉም ሰሚ አልነበረም፡፡ የፍተሻው ሁኔታ እያመማቸውም፣ ሰብኣዊነታቸው ተገፎና እዛው መፈተሻ ቦታ ቀርቶ ግዑዝ አካላቸው ብቻ ይዘው ነበር አደራሽ የገቡት።

 

ይህ አዲስ የፍተሻ ሁኔታ ስራ አስፈፃሚዎቹ አብዛኛዎቹ ለምደውታል። አቦ ለማም ድሮ የማይፈተሹ የነበረ ቢሆንም አሁን እንደማንኛውም ሰው ይፈተሻሉ። የፍተሻውን ዓላማ ስለገባቸው ግን ግዑዝ አካላቸውን ብቻ ሳይሆን ሌላውንም ጭምር ይዘው አደራሽ ድረስ እየገቡ ናቸው፡፡

 

ሹክ ሦስት፡- የማእከላይ ኮሚቴ ስብሰባ እንደተለመደው በአባ ገዳ ስርዓት በምርቃት አልተከፈተም፡፡ በዘመናዊው የፈረንጅ ባህል በኬክ ቆረሳ ነበር ስብሰባው የተሰየመው።

 

ሹክ አራት፡- ኖቤል ተሸላሚን ደፍሮ ማን ይነካል በሚል ሂሳብ ተደፋፍረው የጠሩት የማእከላይ ኮሚቴው ስብሰባ ተጀመረ። አብይ አህመድ ከዚህ በፊት ባልተለመደ ሁኔታ ረዥም ዲስኩር አደረጉ። በጣም በጣም ረዥም ንግግር። የናፍቆትም፣ የፍርሓትም፣ የተስፋ መቁረጥም፣ የደስታ ስብከትም የተቀላቀለ እጅግ ሰዓታት የወሰደ ዲስኩር ነበር። አርዕስቱ እኔ ነው። እኔ ይህን ሰራሁ። እኔ ይህን አደረኩኝ። እኔ እንደዚህ ነኝ። ከፈለኩኝ ይህ ማድረግ እችላለሁ። እኔ ትዕግስተኛ ስለሆንኩኝ እንጂ ማ ምን እያለ እንደሚውል አቃለሁኝ። ወዘተ አሉ፡፡ ተመልሰው ደግሞ እወዳቹላሁ አሉ። ይህ ሽልማት የናንተ ነው። የኦሮሞ ህዝብ ነው አሉ። ይህ ረዥም ንግግር የኮ/ል መንግስቱ ረዥሙ ንግግር አስታወሰኝ። ጥሩ ምልክት ና መመሳሰል አይደለም።

 

ሹክ አምስት፡- ለአብይ፣ ለለማ እና ለሌላው ማእከላይ ኮሚቴ የስብሰባው ድባብ ከባድ ጭንቀት የነበረው ነበር። ሁሉም ተሰብሳቢ ስብሰባው እንደምንም በሰላም አልቆ ተጨማሪ ጊዜ ሊገዛ ይፈልግ ነበር። ከስበሰባው አደራሽ ውጭ ያለው ህዝቡና ፖለቲከኛ የሚጠብቀው ውሳኔ ለመወሰን ከባድ ትግል ይፈልጋል። ነገር ግን ቤተመንግስት ውስጥ በሪፓፕሊካን ጋርድ ኮማንዶ ተከበህ ነፃ ትግል ማድረግ ከባድ ነው። ሆኖም ጌታ ለሁሉም መወጣጫ ፈጥሮ የለ ማእከላይ ኮሚቴውም እንደምንም ብሎ ስብሰባው ላይ ሳይነካካ አልፎታል። የነበረው ሁኔታና ድባቡ ምን ይመስል እንደ ነበረ ሹክ ያሉኝን ሹክ ማለት ስላለብኝ ነው።

 

ሹክ ስድስት፡- ስበሰባው ላይ የታየው አስገራሚ ነገር ደሞ የተሰብሰቢዎቹ ሃሳብ አቀራረብ ነው፡፡ ተሰብሳቢው እጁን አውጥቶ ዕድል ሲሰጠው መመርያ የተሰጠው ይመስል ሁሉም እንካን ደስ አለህ በሽልማቱ ደስ ብሎናል፣ ኮርተናል፣ ታሪክ ነው የሰራኽው ደስ ብሎናል ብሎ ይጀምራል። እንደየሰው ደግሞ ይለያያል መግብያውና መዝግያው፡፡ አንዳንዱ ግጥም መሳይ ረዥም የመግብያ ንግግር ያደርጋል። ይህን ብሎ ሊቀመንበሩ ሳይሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩን ካሟሟቀ በኃላ ውህደቱ ጥሩ ነው፣ ውህደት አይጠላም ግን ጥናቱ በሚገባ አስበንበትና ህዝብቻንም አሳምነን (ሁሉንም ህዝብ የድርጅት አባል የሆነ ይመስል) ጊዜ ወስደን ተመካክረን ብንወስን፣ ባንጣደፍ ይሻላል ይላል። ግማሸቹ ደግሞ ረዘም ያለ የማይገባህ ንግግር ያደርጋሉ። ሲጀምር አሁኑኑ ውህደት ይደረግ የሚል ይመስልና ግን ብሎ ጊዜ ብንሰጠው ይሻላል ይላል። የአብይ አህመድ ፊትም በተናጋሪዎቹ ንግግር ልክ ሲጀምሩ ተስፋ ሰንቆ ፊቱ ሲበራ ሲያጠቃልሉና ነገር ግን ሲሉ ሲከፋውና ሜክአፑ የሸፈነው ዳማው ይታያል።

 

ሹክ ሰባት፡- ሁሉም ተሰብሳቢዎች ያለምንም መንደርደርያ ፌደራሊዝም ላይ አንደራደርም፣ እኛ ለኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ መቆም የምንችለው ህብረ ብሄራዊ ፌደራሊዝም እውን ሲሆን ነው ብለዋል፡፡

 

ሹክ ስምንት፡- አብይ አህመድ ስብሰባው ላይ እጎኑ የተቀመጠውን ሰው ኦቦ ለማን ደጋግሞ አንስተዋል፡፡ ለቤቱ ምንም ልዩነት የለንም መልእክት ለማስተላለፍ እንደሆነ ሁሉም ገምቶታል። ኦቦ ለማ ጭራሹንም አንዴም ቢሆን ኦቦ ይሁን ዶክተር ብለው የሊቀመንበሩን ስም አልጠሩም።

 

ሹክ ዘጠኝ፡- ስብስባው ያለምንም ማጠቃለያ ወይም ውሳኔ ተበተነ። ወደ ድምፅ መሄድ ሁለቱም ዝሆኖች አልፈለጉም። ጉንዳኖቹም አልፈለጉም። ማን ይረገጣል ብለው። ስብሰባውም በድንገት ተጀመረ በድንገት አለቀ። በረዥሙ ሁሉም ተንፍሰው ከአደራሹ ወጡ። በሰላም ስለወጡ ደግሞ ለኔ ለወዳጁ ሹክ የሚለኝ ሰው ሹክ ለማለት በቃ። በቃ።

 

Back to Front Page