Back to Front Page

ግልፅ ደብዳቤ ለአቶ የኔነህ ስመኝየአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንትባህር ዳር

ግልፅ ደብዳቤ ለአቶ የኔነህ ስመኝ

የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት

ባህር ዳር

 

ከመሰረት ተስፉ 3-28-19

 

ጉዳዩ፡ በአቶ በረከትና አቶ ታደሰ ላይ እየደረሰ ነው እየተባለ ያለውን የሰብአዊ መብቶች መጣበብ ይመለከታል

የተከበሩ አቶ የኔነህ፥

ለመጀመር ያህል አንቱ ብየ መፃፍ እንዳለብኝ ስገነዘብ ምን ያህል እንደሸከከኝ ብነግረዎ አያምኑኝም ብየ አላስብም። እርሰዎን አንቱ ብየ ለመጥራት ከብዶኝ የነበረው ስለማላከብረዎ ሳይሆን ያራ'ኮዎ መስሎ ሰለተሰማኝ ነው። በዚህም አለ በዚያ አንቱ ብየ መፃፌ ክብረዎን የሚጨምረው ከሆነና እርሰዎንም ካልከፋዎ አይበዛበዎትም የሚል ጠንካራ እምነት ስላለኝ ሳልወድ በግድ አንቱ እያልኩ ልጠራዎ ወስኛለሁ።

ለማንኛውም ከሁሉ አስቀድሜ ላሳስበዎ የምፈልገው ይህን ደብዴቤ የፃፍኩለዎ ከርሰዎ ጋ ያለኝን ትውውቅ መሰረት አድርጌ አለመሆኑን ነው። አንድ ላይ እየኖርን አንድ ክፍል ውስጥ አብረን ስለተማርን እንዳልሆነም ይረዱልኝ። የነበረንን መቀራረብና ጓደኝነት ተመርኩዤ ለቤተሰቤ አማላጅ ለመሆን አስቤ የፃፍኩት ደብዳቤ ተደርጎ እንዲቆጠርብኝም በፍፁም አልሻም። እንደዛ ባስብ ኖሮ ስልክዎን አፈላልጌ በግለዎ ላናግረዎ መሞከር እችል ነበር። እንደሱ ለማድረግ ግን ህሊናየ ፈፅሞ እንደማይፈቅድ የሚረዱ ይመስለኛል። እርሰዎም ቢሆኑ በአማላጅነት የሚመጣበዎትን ሰው ተቀብለው አያስተናግዱም ብየ አስባለሁ።

Videos From Around The World

ሌላው እንዲገነዘቡልኝ የምፈልገው አብይ ጉዳይ ደብዳቤውን የጻፍኩለዎ አቶ በረከት ስምዖንና አቶ ታደሰ ካሳ የተጠረጠሩበትን ከባድ የሙስና ወንጀል ፈፅመዋል ወይስ አልፈፀሙም በሚለው ጭብጥ ላይ ክርክር ውስጥ ልገባ አይደለም። ይህ ጉዳይ በአቃቤ ህግና በተጠርጣሪዎቹ (ህጉ በትክክል ተግባራዊ የሚደረግ ከሆነም በጠበቃ ተወክለው) በሚያደርጉት ህግን ያማከለ ክርክር ተመስርቶ በዳኞች ሊወሰን የሚገባው መሆኑን አጥብቄ አምናለሁ። ስለዚህ ምንም እንኳ እነአቶ በረከት ከአሰራር ግድፈት በዘለለ በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ከታሰሩ ማን ከዚህ መጠርጠር ነፃ ሊሆን እንደሚችል ባይገባኝምና በአጠቃላይ ክሱ ህጋዊነት ላይ የራሴ የሆኑ ሃሳቦች ቢኖሩኝም በሌላ መድረክ እንጅ በዚህ ደብድቤ ላይ ልገልፃቸው አልፈልግም።

ይልቁንም ይህን ደብዳቤ በግልፅ እንድፅፍለዎ ያነሳሳኝ ጉዳይ እርሰዎ በሚመሩት የዳኝነት ስርዓት አለም አቀፍ ስምምነቶችንና የኢፌዴሪ ህገመንግስትን የተላለፉ ድርጊቶች ወይም ግድፈቶች እየተፈፀሙ ነው የሚሉ ቅሬታዎች እየሰማሁ መሆኔ እያሳሰበኝ ስለመጣ ነው። በተለይ ደግሞ ከጥንት ጀምሮ "በላ ልበልሃ" በሚል የመደማመጥ መርህን ተከትሎ በሚደረግ የፍትህ ይገባኛል ክርክር መርታትና መረታትን ባህሉ ባደረገ ማህበረሰብ ውስጥ "አትበል ልበልሃ" የሚል ቅኝት ያለው የሚመስል የዳኝነት ሂደት እየተከሰተ እንደሆነ ስሰማ ዝም ማለት አላስችልህ ብሎኛል። ሁኔታውን ዝም ብየ ለማለፍ ያልቻልኩበት ሌላው ምክንያት ደግሞ ለሰብአዊ መብቶች መከበር ያለኝ ጠንካራ እምነት ይመስለኛል። በዚህ ዙሪያ ከብዙዎቹ ውስጥ አንድ ተጨባጭ ምሳሌ ባነሳለዎ ደስ ይለኛል። በአንድ ወቅት አቶ ስዬ አብርሃን ለማሰር ሲባል ብቻ በአንድ ምሽት ህግ ሲወጣ ምንም እንኳ በወቅቱ የነበሩኝ መረጃዎች አቶ ስየ ችግር እንደነበረባቸው የሚያሳዩ ቢሆኑም የክሳቸው ሂደት ግን ዴሞክራሲያዊና ፍትሃዊ እንዲሆን ከነበረኝ ጠንካራ እምንት ተነስቼ ባገኘሁት መድረክና አጋጣሚ ሁሉ የሚሰማኝ አላገኘሁም እንጅ ስለህጉ ኢ-ፍትሃዊነት አቅሜ በፈቀደው መጠን ሽንጤን ገትሬ ተከርክሪያለሁ። እንዲያውም በወቅቱ አሁን የለውጥ ሃዋሪያ ነን ከሚሉት አንዳንዶቹ ሳይቀር ለሙሰኛ ምን ሰብዓዊ መብት ያስፈልገዋልና ትከራከርለታለህ በሚል ይሳለቁብኝ እንደነበር አስታውሳለሁ።

ወጣም ወረደ ከአቶ በረከትና ከአቶ ታደሰ ሰብአዊ መብቶች መጣበብ ጋ ተያይዞ እየተነሳ ያለው አንዱ አሳሳቢ ጉዳይ እነዚህ ሁለት ኢትዮጵያዊያን በተጠረጠሩበት/በተከሰሱበት ከባድ የሙስና ድርጊት ወይም ግድፈት በፍርድ ቤት ሳይረጋገጥባቸው ወንጀለኞች እንደሆኑ ተቆጥረው የሚሰጣቸውን ስም የሚመለከት ነው። እርሰዎም እንድሚያውቁት ማንኛውም ሰው የወንጀል ክስ ቀርቦበት የፍትህ ሂደቱን በተሟላ መንገድ ተጠቅሞ ከተከራከረ በኋላ የፈፀመው ድርጊት ወይም ግድፈት ከአመክንዮ ጥርጣሬ ውጭ (Beyond a Reasonable Doubt) ተረጋግጦ በፍርድ ቤት ጥፋተኛ ተብሎ እስካልተወሰነ ድረስ ንጹህ ነው ተብሎ ይታመናል። ይህ መሰረታዊ የህግ መርህ በተለያዩ የአለም አቀፍ ስምምነቶች በግልፅ የሰፈረ የተጠርጣሪዎችና የተከሳሾች መብት ነው። ለምሳሌ የአውሮጳ የሰብአዊ መብቶች ስምምነት አንቀፅ 6(2) እና በተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ የተወሰነው የአለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ስምምነት አንቀፅ 14 (2) ን ማየት ይቻላል። በአለም ላይ ያሉ ያብዛኞቹ አገራት ልምድ የሚያሳየውም ይህንኑ ነው። ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣም የወንጀል ድርጊት ወይም ግድፈት ተጠርጣሪዎች ከፍርድ ቤት ውሳኔ በፊት ንፁህ ሆኖ የመቆጠር መብት በህገመንግስቱ አንቀፅ 20 (3) በግልፅ ተደንግጓል።

ከላይ በተብራራው መንገድ የአለም አቀፍ ስምምነትና የኢፌዴሪ ህገመንግስት በፍርድ ቤት እስካልተረጋገጠ ድረስ ንፁህ ሆኖ የመገኘት መብትን እውቅና ሰጥተውና ደንግገው እያለ አማራ ክልል ላይ ግን ከተለመደው ወጣ ባለ መንገድ አቶ በረከትና አቶ ታደሰ ፍርድ ቤት ውሥጥ በተሰየመ ችሎት ላይ ሳይቀር ሌባ ሌባ እየተባሉ ሲሰደቡ ለሙያው ተገዝቶ ህግን የሚያስከብር ዳኛ አለመኖሩ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ግልፅ ሊሆንልኝ አልቻለም። ይህ ሁኔታም ከዚህ ቀጥሎ ያሉትን ጥያቄዎች እንዳነሳ አስገድዶኛል።

         ችሎት ውስጥ እግር አነባብረህ ተቀምጠሃል በሚል ገስፆ ወይም ቅጣት ጥሎ የፍርድ ቤት ስርዓትን ለማስከበር ጥረት በሚደረግበት አለም ላይ ተጠርጣሪዎች የሆኑት አቶ በረከትና አቶ ታደሰ "ሳይፈረድብን እንደወንጀለኛ ከመቁጠር አልፎ በጠበቃ እንዳንወከል የከለከለን፣ በጠበቆቻቸን፣ በቤተሰቦቻችና በራሳችን ላይም ግፍ እየፈፀመብን ያለ የተደራጀ የሚመስል ቡድን ከድርጊቱ ይቆጠብልን" ብለው ሲጠይቁ "እኛ ምንም ማድረግ አንችልም" ብለው በመመለስ የችሎቱ ታዳሚ በጭብጨባ አዳራሹን ሲያናውጠው ተግሳፅ ወይም ማረሚያ የማይሰጡ ዳኞችስ ከህግ ትምህርት ቤት ሲመረቁም ሆነ በኋላ ላይ ሲሾሙ የገቡትን ለሙያ ስነምግባር የመገዛት መሃላ አሽቀንጥረው የት ጣሉት?

         እንዲህ አይነት ችግር ሲፈጠርስ ሌላ ጊዜ እንዳይደገም እርምጃ መውሰድ ለህጋዊነት የቀረበ ሙያዊ ግዴታን የመወጣት ቁርጠኝነት አይሆንም ነበር ወይ?

         እነዚህ የተከበረውን የችሎት ካባ የለበሱ ዳኞችስ ይህን መሰል ከሙያ ስነምግባር ያፈነገጠ ተግባር ሲፈፅሙ በዝምታ ማለፍ የዳኝነት ስርዓቱን ገለልተኛነት ያሳያል ወይ?

የተከበሩ አቶ የኔነህ፥

ሁለተኛው አሳሳቢ የህግ ጥሰት ደግሞ አቶ በረከትና አቶ ታደሰ ጠበቃ አቁመው ጉዳያቸውን በሚገባ እንዳይከታተሉ የተደራጀ በሚመስለው ቡድን አባላት ክልከላ እየተደረገባቸው ያሉ ከመሆናቸው ጋ የተያያዘው ጉዳይ ነው። ይህን በተመለከተ ከተለያዩ ምንጮች እንደተረዳሁት ከሆነ አቶ በረከትና አቶ ታደሰ በተደጋጋሚ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ ከአንድ ጊዜ በላይ በጠበቃ ተወክለው አያውቁም። ይህ የሆነው አሁንም ችሎቱን ከተከታተሉ ሰዎች እንደሰማሁት የተደራጀ የሚመስለው ቡድን አባላት በፍርድ ቤቱ ዙሪያና ቅፅር ጊቢ ውስጥ በመሆን የ'ነ አቶ በረከትን ጠበቆች አንዴ የመንቀሳቀስ መብታቸውን ገድበው ችሎት ውስጥ እንዳሉ በማገት፣ ሌላ ጊዜ "እንገድላችኋለን" ሲሉ በመዛት፣ ሲሻቸው ደግሞ "እግራችሁን ቆርጠን እንጥለዋለን" በማለት እያስፈራሩ ወደመጡበት እንዲመለሱ ስላደረጓቸው ነው።

በመሰረቱ አንድን ተከሳሽ ፍርድ ቤት አቅርቦ ጠበቃ እንዳያቆም መከልከል ወይም በማንኛውም ሃይል ሲከለከል አይቶ እንዳላዩ ማለፍ የሚመስለው ህጋዊ ተጠያቂነትን ለማስፈን የሚደረግ ጥረትን ሳይሆን ቀድሞ የተላለፈን የባለስልጣናት ውሳኔ ህጋዊ ሽፋን እንዲያገኝ የሚደረግ የይስሙላ የክስ ሂደትን ነው። ምክኒያቱም በስንትና ስንት የህግ ባለሙያዎች የተዋቀረ አቃቢ ህግ የሚያቀርበውን ክስ ያለጠበቃ ራሱን ወክሎ እንዲከራከር የሚደረግ ተጠርጣሪ የህግን ስንክሳርና ውጥንቅጥነት በሚገባ ተረድቶ በመከራከር ፍትህ ያገኛል ማለት ዘበት ስለሆነ ነው። እንደኔ እንደኔ በዚህ አይነት መንገድ እስር ቤት የሚገኝን አንድ ተጠርጣሪ ጠበቃ ከልክሎ ፍርድ ቤት ከማቅረብ ይልቅ እዛው እስር ቤት እንዳለ የወንጀለኛነቱ ሰርቲፊኬትና የተበየነበት ቅጣት በፖስታ እንዲደርሰው ቢደረግ ቢያንስ ተጠርጣሪውም ከእንግልት መንግስትም የህዝብን ንብረት ከማባከን ይድናሉ ብየ አምናለሁ።

በዚህም አለ በዚያ ከላይ የተገለፀውን አይነት ክልከላ ማድረግ ህጋዊ መሰረት እንደሌለውና እንዲያውም ማንኛውም ተጠርጣሪ ወይም ተከሳሽ በመረጠው ጠበቃ የመወከል መብት እንዳለው የአለም አቀፍ ስምምነቶችም ሆኑ የኢትዮጵያ ህጎች በግልፅ አስፍረውት እንደሚገኙ ከርሰዎም የተሰወረ ነው የሚል ምንም አይነት ጥርጣሬ የለኝም። ሁኔታውን ግልፅ ለማድረግ ያህል የአለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ስምምነት አንቀፅ 14(3)(d) ን እና በተባበሩት መንግስታት የወንጀል ፍትህ ስርዓት መርሆዎችና መመሪያዎች ውስጥ መርህ ሶስትን ማስታወስ ጠቃሚ ነው ብየ አምናለሁ። በዋነኛነት ደግሞ የኢፌዴሪ ህገመንግስት አንቀፅ 20(5) እንዲሁም የወንጀለኛ መቅጫ ስንስርዓት ህግ በአንቀፅ 61 ይህንኑ መብት በማያሻማ ሁኔታ ደንግገውታል።

በሌላ በኩል ይህ ለተጠርጣሪዎች የተሰጠ በፈለጉት ጠበቃ የመወከል መብት መመዘኛ ወጥቶለት ላንዱ የሚቸር ወይም ለሌላው የሚነፈግ ሳይሆን ሁሉን አቀፍ እንደሆነ እነዚሁ ስምምነቶችና ህግጋት በግልፅ አስፍረውታል። ይህ የሚያሳየው የዚህ መብት ተፈፃሚነት ለሁሉም እኩል በሆነ መንገድ እንጅ ማንነትን፣ የፖለቲካ አቋምን ወይም አመለካከትን፣ ቀለምን፣ ጾታን፣ ቋንቋንና ሌሎችንም ሁኔታዎች ግምት ውስጥ አስገብቶ ምንም አይነት ልዩነት (All Forms of Discrimination) ሊፈጥር የማይገባ መሆኑን ነው።

ከዚህ አንፃር ሲታይ አቶ በረከትና አቶ ታደሰ በሌሎች ግለሰቦች፣ ቡድኖችና አካላት ተወደዱም ተጠሉም፣ ወይም ደግሞ ወፍ ዘራሽ ተደርገውም ይቆጠሩ ከማርስም መጡ ከጁፒተር በመረጡት ጠበቃ የመወከል መብት ግን ሰው በመሆናቸው ብቻ ሊጎናፀፉት የሚገባ የተፈጥሮ መብት ነው። ስለዚህ አቶ በረከትና አቶ ታደሰ የመረጡትን ጠበቃ አቁመው ከተከሰሱበት "ከባድ የሙስና ወንጀል" ራሳቸውን እንዳይከላከሉ የሚያደርግ ማንኛውም "ባለጊዜ ነኝ" ባይ ጉልበተኛ ህጋዊ መብትም ሆነ ስልጣን እንዳልተሰጠው እርሰዎም ይዘነጉታል የሚል እምነት የለኝም።

ሁኔታዎች ሁሉ የሚያሳዩት ይህን ሆኖ እያለ እርሰዎ በሚመሩት የዳኝነት ስርዓት ግን ቅቡል/ተገቢ የሆነውን የህግ ስርዓት ሂደት (Due Process of Law) በሚጋፋ መልኩ አቶ በረከትና አቶ ታደሰ ጠበቃ አቁመው መከራከር እንዳይችሉ መደረጉ አሁንም ምክንያቱ ምን እንደሆነ ሊገለጥኝ በፍፁም አልቻለም። ከዚህ አንፃር የሚከተሉትን ጥያቄዎች አነሳለሁ፡

         ከነገረ ቀደም እነዚህን ተጠርጣሪዎች ጠበቃ ማቆም አትችሉም ብለው የሚከለክሉ የተደራጀ የሚመስለው ቡድን አባላት ያሻቸውን ሲያደርጉ ሃይ የሚል ዳኛ መጥፋቱ ምንን ያመላክታል?

         ይህ ሁኔታ ችግር እንደሆነ እየታወቀ ለጠበቆች ዋስትና የማይሰጥበት ምክንያትስ ምንድን ነው?

         የከልካዩ ቡድን አባላት ከፍርድ ቤቱ ቁጥጥር ውጭ ከሆኑስ ለምንድነው ልክ የደርግ ባለስልጣናት ሲዳኙ እንደተደረገው የነአቶ በረከት ጉዳይስ በተዛዋሪ ችሎት እንዲታይ የማይደረገው?

         እነዚህ ሁሉ የማይቻሉ ቢሆን እንኳ ለምንድን ነው ዳኞቹ ራሳቸው በዚህ ሁኔታ የሙያ ግዴታችንን በገለልተኝነት ልንወጣ አልቻልንም በሚል ስራቸውን አቁመው ለሚመለከተው የመንግስት አካል ወይም ለህዝብ በግልፅ የማያሳውቁት? ነው በአቶ በረከትና በአቶ ታደሰ ላይ ምንም አይነት ግፍ ቢፈፀም አይገደንም የሚል ስምምነት በክልል ደረጃ ተደርሷል?

ለማጠቃለል ከዚህ በላይ ያነሳኋቸውን ሃሳቦችና ጥያቄዎች አንድ ላይ ጨምቄ ሳያቸው የአቶ በረከትና የአቶ ታደሰ ሰብዓዊ መብቶች በሚገባ የተደራጀ በሚመስል ቡድን ሲጣበቡና ሲጠራቀቁ በርሰዎ የሚመራው የአማራ ክልል የዳኝነት ስርዓት ለማስቆም ያደረገው ጥረት እንደሌለ ወይም ደግሞ በቂ እንዳልሆነ ለመረዳት ችያለሁ። በነገራችን ላይ የወንጀልን ክስ ያለጠበቃ መከራከር መብትን እንደሚያጣብብ ስለሚታመን መሞከር አይገባም ሲሉ የወንጀል ህግ ልሂቃን እንደሚያምኑ ለርሰዎም ይጠፋዎታል ብየ አላስብም። እንዲያውም በአለም ላይ ያሉ ልምዶች የሚያሳዩት ተጠርጣሪው ራሱ ጠበቃ ማቆም አልፈልግም ቢል እንኳ ዳኞች ፍትህ ይዛባል ብለው ካመኑ ለተጠርጣሪው ጠበቃ እንዲቆምለት አስገዳጅ ውሳኔ የሚሰጡበት ሁኔታ እንዳለ ነው። የወንጀል ተጠርጣሪዎችን መብት ለማስከበር ይቻል ዘንድ እነዚህንና መሰል ረጅም ርቀቶችን የሚጓዝ የፍትህ ስርዓት ባለበት አለም እየኖርን አማራ ክልል ላይ ግን ተጠርጣሪዎች ጭራሽ ጠበቃ እንዳያቆሙ የሚከለክል ቡድን መፈጠሩና ይህንንም አይን ያወጣ ህገወጥ ድርጊት እየፈፀመ የሚገኝን ቡድን የሚከላከል የፍትህ በተለይም የዳኝነት ስርዓት አለመታየቱ ፤ ቢታይም ደግሞ እጅግ በጣም አናሳ መሆኑ የተከበረውን የዳኝነት ሙያ የሚያንኳስስና ዋጋ የሚያሳጣ ተግባር ሆኖ አግኝቸዋለሁ። በነዚህ ምክንያቶች የተነሳም እርሰዎ የሚመሩት የዳኝነት ስርዓት ከአስፈፃሚው አካል ትፅዕኖ ነፃ ነው ወይ? የሚል ጥያቄ እንዳነሳ ተገድጃለሁ።

ስለዚህ ከላይ ያነሳኋቸው ሃሳቦች እንዲሁም ጥያቄዎች እርሰዎ የሚመሩትን የዳኝነት ስርዓት እየተገዳደሩ የሚገኙ ስለሆነ ለጥያቄዎቼና ለሃሳቦቼ ሙያዊ ስነምግባር የተላበሰ ትኩረት በመስጠት አስፈላጊውን የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስዱ በአክብሮት እጠይቃለሁ።

ከከበረ ሰላምታ ጋር!

 

ግልባጭ፡

         ለአግማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ፕሬዚደንት

         ለአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ጠቅላይ አቃቤ ህግ

 

Back to Front Page