Back to Front Page

ምክንያታዊት ኢትዮጵያ(Rational Ethiopia)

ምክንያታዊት ኢትዮጵያ

(Rational Ethiopia)

ፀጋዝአብ ለምለም ተስፋይ

የኢኮኖሚክስ መምህርና ጸሓፊ 5-18-19

ሀገራችን ያለችበትና ልትኾን የምትችልበት ኹለንተናዊ ማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ኹኔታ ከአስተማማኝነት ይልቅ ወደ ስጋት፤ ከሙሉ ተስፈኛነት ይልቅ አስጨናቂነቱ የጎላ እንደኾነ ያለንበት ተጨባጭ መገለጫዎች ማሳያ ናቸው፡፡

ዕውን በ21ኛው ክፍለ ዘመን ላይ የበለጸጉ የሚባሉ ሀገራት ለአንድ ዜጋቸው የሚያደርጉትን ጥበቃና ለአንድ ዜጋቸው የሚያሳዩትን የባለቤትነት ስሜት ቢያንስ ቢያንስ ካለን አቅም በመነሣት በተግባር መግለጽ እንኳ ባንችል በአሰተሳሰበና በአመለካከት ደረጃ የርሱ ባለቤት መኾን እንደምን ተሳነን? ቢያንስ እንደምን በስሜት ደረጃና በተግባቦት ደረጃ እንኳ ማዳበር አቃተን?

Videos From Around The World

በምሁራን መሐከል የሠለጠነ የውይይት ባሕል መኖር ሳይችል እንደምን ቀረ? እንደምን በሚሊዮን የሚቆጠር የተማረ የሰው ኃይል ባለባት ሀገር ችግሮቻችንን በውይይት የመፍታት ባሕል ማዳበር አቃተን? ዕውን ስለማንችል? ወይስ መቻል ስላልፈለግን? ተገደን ወይስ በዚህ ነባራዊ ኹኔታ የተሻለ ትርፍ ስለምናገኝ? ወይስ የተሻለ ትርፍ በሚያገኙ ኃይሎች ስለተዋጥን? በዚህ መኖር አስፈላጊያችን ስለኾነ? ወይስ ያለዚህ መኖር ስለማንችል?

ዕውን የቀደምት ሃይማኖቶች መገኛ የኾነች ሀገር ችግሮቿን ከስሜት ይልቅ በስሌት፣ ከኢ-ምክንያታዊ ሂደት ይልቅ በምክንያት ትመራ ዘንድ - የሃይማኖቶቿ አስተምህሮ ግድ ይሏት የለምን? እንደምን አስተምህሮቶቿ በሕብረተሰቡ የአኗኗር ዘይቤ ላይ መሠልጠን አቃተው?

እንደሀገር በኢ-ምክንያታዊነትና በምክንያታዊነት፣ በእውነተኛነትና በሀሰተኛነት፣ በአስመሳይነትና በራስን መኾን፣ በጨዋነትና በመሰሪነት፣ በቀልደኛነትና በቁም ነገረኛነት መሐከል ድንበር መለየትና መስመር ለይተን ማሰቀመጥ አቃተን?

ዕውን በሀገራችን ውስጥ የምናያቸው፣ የምንሰማቸው፣ የምናነባቸውና የምናሰተውላቸው ኹለንተናዊ ችግሮች መፈታት ስለማይችሉ ነው? ወይስ መፍታት ስላቃተን? እንደምንስ አቃተን? ቢፈቱ ማን ይጎዳል? ማንስ ይጠቀማል? የመፍቻ ቁልፍ ማዕቀፉስ ምንድነው? እንደምንስ ማስቀመጥ እንችላለን?

ጥንታዊትና ቅድስት በኾነች ሀገር ሊኖር ከሚገባው ይልቅ የማይገባው፤ መኾን ካለበት ይልቅ ሊኾን የማይገባው ይኾን ዘንድ ምን ግድ አለን?

ለአብነት፡- በፓርቲዎች ውስጥ በአመራር፣ አባላት፣ ደጋፊና ተፎካካሪ መሐከል ግጭቶች ለምን ይከሰታሉ? ችግሮቹ ከመከሰታቸው በፊት መከላከል አይቻልም ነበርን? ለምንስ አልቻልንም? ማን እንዳንችል አደረገን? ምን ለማግኘት? ምንስ አሳጣን? ለደረሰው ኹለንተናዊ ጉዳት ተጠያቂ ማን ኾነ? ተጠያቂነትን እንደምን ማስፈን ተሳነን?

በሃይማኖት ተቋማት መሐከልስ በአባቶችና በአገልጋዮች፣ በምዕመንና በሌላው መሐከል አለመግባባትና ግጭቶች ሲፈጠሩ ጉዳት ከማድረሳቸው በፊት መከላከል እንደምን ተሳነን? በሃይማኖቶቹ አሰተምህሮ መመራት ስላቃተን ይኾን? ወይስ ስለቻልን?

ዕውን የችግሮቻችን ኹሉ ምንጭ ማዕቀፍ ምንድነው? በኹለንተናዊ ፍላጎትን መሠረት ካደረጉ ግንኙነቶቻችን - በተለይ ከራሳችን፣ ከፈጣሪ፣ ከመሰሎቻችን፣ ከአካባቢያችን እና ከተፈጥሮ ጋር እንደምን ስምሙ መኾን አቃተን?

q የሰው ልጅ በዕለት ተዕለት የሕይወት እንቅስቃሴው ውስጥ "ግንኙነት" አለው፡፡ ይኸውም "ግንኙነት"፡ ከራስ፣ ከፈጣሪ፣ ከመሰል፣ ከአካባቢና ከተፈጥሮ ጋር የነበረ፣ ያለና የሚኖር ነው፡፡

በዚህም ተባለ በዚያ የሀገራችንን ነባራዊ ወቅታዊ ኹኔታ መኾን ካለበትና ሊኾን ከሚገባው ይልቅ እየኾነ ካለው ኹለንተናዊ እንቅስቃሴ አንጻር ስንመለከት እጅግ በጣም የተለያየ፣ ፈጽሞ ሊቀራረብ የማይችል፣ አብሮ ሊያሰራ የማይችል፣ ፍጹም ተቃራኒ ሀሳብና አቋም ያላቸው ኃይሎችና አካላቶች ሕብረት ፈጥረውና ሕብረት ፈጥረናል ብሎም ተስማምተናል ሲሉ መስማት የተለመደ መኾኑ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ ዕውን ይህ ይኾን ዘንድ ምን አስገደደን?

እኛ ኢትዮጰያውያን ከሌላው ሕዝብ በመሠረታዊነት የተለየ ፍላጎት እንደሌለን ይታወቃል፡፡ ሌላው ሕዝብ እንደሕዝብ በባሕሪው የሚፈልገውን እንሻለን፡፡ የሚጠላውን እንጠላለን፡፡ በጠባይ ካልኾነ በባሕሪያዊ ፍላጎቶች የመጠን፣ የመልክና የስፋት ካልኾነ በቀር የይዘትና የግብር ልዩነት እንደሌለን ካስተዋልን - ምክንያታዊት ኢትዮጵያ አታስፈልግምን? ዕውን ምክንያታዊት ኢትዮጵያ እንዴት ዕውን ልትኾን ትችላለች? ለምንስ ይጠቅመናል? ፈጣሪ ሀገራችን ነጻ ፍቃድን የኹሉ ነገር ማዕከል ወደ ሚያደርግ የዕሳቤ ሂደት ትገባ ዘንድ ይርዳን!

ቸር እንሰንብት!

Back to Front Page