Back to Front Page

ዶ/ር ዮሐንስ - እኔማ በሕወሓት ላይ ያመጽኩ ወያኔ ነኝ

ዶ/ር ዮሐንስ - እኔማ በሕወሓት ላይ ያመጽኩ ወያኔ ነኝ

(ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)

March 26, 2019

ባለፈው ሰሞን ክቡር መቅላይ ሚንስትር ወያኔ ይሁኑ! በሚል ርእስ ለጻፍኩት መጣጥፍ፤ ዶ/ር ዮሃንስ አበራ አየለ የተባሉ ጸሐፊ March 18, 2019 በአይጋ ፎረም ላይ አብዱራህማን "ወያኔ ይሁኑ" በሚል ርእስ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ የመልስ መልስ እነሆ!

ዶ/ር ዮሐንስ ማለት የካናዳው፣ የወንድሜ የአህመድ ሙሐመድ ጓደኛ፣ የኢትዮጵያን ሚሊኒየም ዝግጅት ያደመቅከው ዶ/ር ዮሐንስ ከሆንክ የእኔን ወያኔነት ከሞላ ጎደል ስለምታውቀው ወያኔ ሁን የሚል ሃሳብ ማቅረብ እንደማይገባህ አስባለሁ፡፡ የሆነ ሆኖ መልሴ በአጭሩ እኔማ በሕወሓት ላይ ያመጽኩ ወያኔ ነኝ የሚል ነው፡፡ ይህ አጭር መልስ እንደተጠበቀ ሆኖ ዶ/ር ዮሐንስ ባነሷቸው አንዳንድ ጉዳዮች ላይ ዘርዘር ያለ መልስ ማቅረብ ተገቢ በመሆኑ ወደዚያ ላምራ፡፡

Videos From Around The World

የአሁኒቱ ኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ነገር ይብስ አደናጋሪ ሆነብኝ። ለመሆኑ ትናንት የተናገሩትና ዛሬ የሚናገሩት ቅራኔ ስለመኖሩ ግንዛቤ እየወሰዱ ስላልሆነ ነው ወይስ እኛ የምንናገረው ሁሉ ተምታታም አልተምታታም ዩኒቨርሳል ሃቅ ነው የሚል የፍፁምነት ቆዳ ስለለበሱ ነው? የሚለውን የዶ/ር ዮሐንስን ሃሳብ እጋራለሁ፡፡ ምክንያቱም የሀገራችን ፖለቲከኞች ብዙዎቹ መርህ አልባ፣ አቋም የለሽ በመሆናቸው እና ትናንት የተናገሩትን ስለሚረሱት (short lived memory ያላቸው በመሆኑ) ዛሬ አይደግሙትም፡፡

ይህ ከላይ የጠቀስኩት የዶ/ር ዮሐንስ አባባል ግን እኔንም ሆነ የዛሬ ዘጠኝ ዓመት የተለየሁትን ኢዴፓን የማይመለከተን መሆኑን አስረግጨ ለመናገር እወዳለሁ፡፡ አንተም ያው ነህ፣ በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ አለህ የሚሉኝ ከሆነ መቼ የተናገርኩትን በየትኛው ጽሁፌ እንዳፈረስኩት በንጽጽር ያቅርቡልኝና ከስህተቴ ልማር፡፡ በበኩሌ ሳወግዝ የኖርኩት የህወሓትን ጨቋኝ ፖሊሲ እና የአመራሯን እኩይ ድርጊት እንጂ ወያኔነትን አልነበረም፡፡ ዛሬም ከዚህ የተለየ አቋም የለኝም፡፡ የጽሁፌ ርእስ አድርጌ ያቀረብኩትን ሃሳብ ያቀረበው ናትናዔል አስመላሽ የተባለ ከወደ ትግራይ ያገኘሁት ወዳጄ መሆኑንም ጠቅሻለሁ፡፡

ወንድሜ ዶ/ር ዮሐንስ! ወያኔነትማ የታላቅ ህዝብ የጀግንነትና የትግል አርማ መሆኑን ጠንቅቄ አውቃለሁ፡፡ አበው መልከ ጥፉን በስም ይደግፉ እንዲሉ የእኩይ ባህሪ ባለቤት የሆነቺው፣ መልከ ጥፉዋ ህወሓት ይህንን የህዝብ የነጻነት አርማ ነጥቃ የራሷ በማድረግ ይህንን ታላቅ ስም አራከሰቺው፡፡

በበኩሌ የምተቸውም፣ የምነቅፈውም፣ የምደግፈውም በምክንያት በመሆኑ ባለፉት 27 ዓመታት ምንም ዓይነት በጎ ነገር አልተሰራም ብየ አላምንም፡፡ እንዲህ ዓይነት ሃሳብም ጽፌ አላውቅም፡፡ እናም ወቀሳዎት አይመለከተኝም፡፡ በአጠቃላይ እኔ መደመርም፣ ማስደመርም ስሌት ውስጥ የለሁበትም፡፡ ለማረጋገጥ በኦገስት 2018 በፌስቡክ ገጼ የጻፍኩትን ግልጽ አቋም Timeline ላይ ማየት ይቻላል፡፡ በመሆኑም፤ ዶ/ር ዮሐንስ የ27 አመት ጨለማ በብርሃን ተካነው ሲባል ብርሃን የሆነው የአብሪ ጥይት እሳት ነውን?... ገመናው እንዳይጋለጥ ማለባበስ ነውን?... የመፈናቀልና የርሃብ ችግር ደብቆ መያዝ ነውን?... የጭፍን ደጋፊዎቻቸው ግፊትና አይዞህ ባይነት መያዣ ጆሮ የሌለው  ድስት ወጥ አብሳዩ የሲሲሊ ንጉስ የሚሉትና ሌሎችም ሃሳቦችዎ ከእኔ ጽሁፍ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የላቸውም፤ የቀረበው ሂስም አይመለከተኝም፡፡ እንዲህ ያለውን አስተያየት ለእኔ መልስ ብለው ከሚያቀርቡ ራሱን የቻለ መጣጥፍ አድርገው ቢጽፉት የተሻለ ይሆን ነበር፡፡ የሚመለከታቸው ሁሉ ይማሩበትም ነበር፡፡

ዶ/ር ዮሐንሰደ አብዱራህማን ጠቅላይ ሚኑስትሩን "ወያኔ ይሁኑ" ብለው ሲመክሩ ከወያኔነት ትክክለኛ ትርጉም ለቀው ባልሆነ የጢሻ መንገድ የሄዱ ይመስለኛል። ወያኔነትን የቀረፁት አሳሪ፣ ገዳይ፣ ደብዳቢ አድርገው ነው። ያስቀመጧቸው ሶስት ነጠብጣቦች ሊጠቅሷቸው ያልፈለጉ የወያኔ ባህርያትን ለማመልከት ያስቀመጧቸው ነጠብጣቦች ይሆናሉ ያሉትን በተመለከተ፤ አዎ ልጠቅሳቸው ያልፈለኳቸውን የህወሓት አባላትን መጥፎ ባህርያት ለማመልከት ነው፡፡ የህወሓት አባላት ባለፉት 27 ዓመታት በገዛ ወገናቸው ላይ የፈጸሙት ዘግናኝ ተግባር (አንዳንዱ በእኔም ላይ የደረሰ ነው) እንኳን ልጽፈው ሳስበውም ይቀፈኛል፡፡ በነጠብጣብ ማለፌ ጨዋነቴን ያሳይ እንደሆነ እንጂ ሊያስወቅሰኝ አይገባም፡፡ እርስዎ ራስዎ ዶማን ዶማ የማለት ድፍረት ሊኖር ይገባል ብለው የለም እንዴ? ታዲያ የህወሓትን እድፍ መጥቀሴ ለምን ስህተት መስሎ ታየዎት ዶክተርዬ? እርስዎም የራስዎን አካፋና ዶማ ይጻፉ እኔም የራሴን አካፋና ዶማ እጽፋለሁ፡፡

የወያኔን በጎ ምግባራት መግለፁ፣ የፖለቲካ ተቀባይነቶን የሚነካ መስሎዎት ከፈሩ ያሉትን በተመለከተ በዚህ ወቅት ወገንተኛ የሆንኩበት የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ስለሌለኝ የሚያስፈራኝ ነገር የሌለ መሆኑንም በዚህ አጋጣሚ ልገልጽልዎ እወዳለሁ፡፡

ወያኔ በከፍተኛ በሃገር ፍቅር የተካነ የሃገር ህልውና ጥበቃ የሃገር ስም ለማስጠራት ታሪካዊ ተግባራትን የሚሉትን የዶ/ር ዮሐንስን ቃላት ሳነብ ከት ብየ ነው የሳቅኩት፡፡ ምነው ዶ/ር ዮሐንስ? እንደ እርስዎ ያለ የተማረ ሰው ከእውነት አፈንግጦ ለስጋው ሲያደላ በጣም ያሳዝናል፣ ያስተዛዝባልም፡፡ ኢትዮጵያ በታሪኳ እንደ ህወሓት ያለ መብትና ጥቅሟን አሳልፎ የሰጠ የመንግስት አስተዳደር ገጥሟት አያውቅም፡፡ ኢትዮጵያ በታሪኳ እንደ ህወሓት ያለ ያዋረዳት፣ የበታተናት፣ ያላገጠባት፣ አገዛዝ ገጥሟት አያውቅም፡፡ ቀደምት አገዛዞች በህዝቡ ላይ ይቀልዱ ነበር፡፡ ግፍ ይፈጽሙ ነበር፡፡ ሀገሪቱን በተመለከተ ግን ቀልድ አያውቁም፡፡ ህወሓት ግን በሀገሪቱም በህዝቡም ላይ ነው ታሪክ ይቅር የማይለው ግፍ የፈጸመቺው፡፡

ኤርትራ የተገነጠለቺው በህወሓት ዘመን አይደልም እንዴ? ኢትዮጵያ የባህር በር ያጣቺው በህወሓት አይደለም እንዴ? ልክ ቅኝ ገዢዋ ጣሊያን እንዳደረገቺው ሀገሪቱን በዘር ፌዴራሊዝም የሸነሸነቺው ህወሓት አይደለቺም እንዴ? ኢትዮጵያ ቅኝ ገዢ ናት ብላ በፖለቲካ ፕሮግራሟ ላይ ያሰፈረቺው ህወሓት አይደለቺም እንዴ? የራስን እድል በራስ መወሰን እስከ መገንጠል የሚል ህገ መንግስት በማዘጋጀት ሀገሪቱን ቦምብ ላይ ያስቀመጠች ህወሓት አይደለቺም እንዴ? ስንቱን ልዘርዝረው?

ዶ/ር ዮሐንስ የህወሓት ፈተና ቀደምቶቹ መንግስታት ከገጠማቸው ፈተና በብዙ እጥፍ የከበደ ነበር ያሉትን በተመለከተ በመጀመሪያ ደረጃ፤ ሀገር መምራት ያቃተው አካል ስልጣኑን ማስረከብ ይገባዋል እንጂ ፈተናው በዛብኝ ብሎ በህዝብ ላይ ግፍ መፈጸም የለበትም፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ህወሓት አውራ ፓርቲ ምናምን እያለ ስልጣኑን በጉልበት ያዘ እንጂ የኢትዮጵያ ህዝብ በግዴታ ምራኝ አላለም፡፡

ወያኔ ማለት በማእከላዊ ምርመራ ድርጅት ውስጥ ቢሮ ዘግቶ እስረኛ የሚደበድብ አይደለም። እሱ ወያኔን የካደ ነው ብለዋል ዶ/ር ዮሐንስ፡፡ ዶክተር ህወሓት እኮ ማሰር፣ መግረፍ፣ ማሰቃየት፣ የጀመረው አዲስ አበባ ከገባ በኋላ፣ በማዕከላዊ አይደለም፡፡ በትጥቅ ትግሉ ወቅት 09 (ባዶ ዘጠኝ) በሚባለው የህወሓት የመሬት ውስጥ እስር ቤት ከእባብ፣ ከአይጥ፣ ከጊንጥ፣ ጋር ታስረው ግፍ የተፈጸመባቸውን፣ በቁማቸው የተሰቃዩ፣ ግፈኛውን ደርግ ለመታገል በርሃ የገቡ የትግራይ ልጆች ረሷቸው ወይስ አላውቅም እያሉ ነው? ህወሓት እዚያ የለመደባትን ብልግና ነው በአዲስ አበባ የቀጠለቺው፡፡ እናም በሰማይ ቤትም እኮ የተበላሹ መላእክት ወደ ምድር ተወርውረዋል እያሉ በወገንዎ ላይ ባያላግጡ ጥሩ ነው፡፡

ሌላው ዶ/ር ዮሐንስ ጥቂት ግለሰቦች የፈፀሟቸውን መጥፎ ተግባራት የወያኔነት የመዝገበ ቃላት ትርጉም አድርገው ማቅረብ አልነበረቦትም ያሉትም ተገቢ አይደለም፡፡ እነዚያ በህወሃት አባላት የተፈጸሙ ግፎች እኮ በወራሪው ጣሊያን ቢፈጸሙ የሚገርም አይደለም፡፡ እርስዎ ግፍን የሚጸየፉ ቢሆኑ ኖሮ ይህንን ግፍ የፈጸሙ ሰዎች በዚያው ባሉበት በትግራይ ክልል ፍርድ ቤት ይቅረቡ ማለት ሲገባዎት ጥቂት ግለሰቦች የፈፀሟቸው በማለት ሊያጣጥሉት መሞከርዎ ግፉን ከመፈጸም ተለይቶ የሚታይ አይደለም፡፡ በጀርመን ናዚ ፓርቲን የሚደግፍ ሃሳብ ያነሳ ሰው እኮ አሁንም ተጠያቂ ነው ናዚና ህወሓት ልዩነታቸው ምንድነው?

ዶ/ር ዮሐንስ ጥቂት ግለሰቦች የፈፀሟቸውን መጥፎ ተግባራት የወያኔነት የመዝገበ ቃላት ትርጉም አድርገው ማቅረብ አልነበረቦትም ካሉ በኋላ ትንሽ ወረድ በማለት ወያኔ ማለት በማእከላዊ ምርመራ ድርጅት ውስጥ ቢሮ ዘግቶ እስረኛ የሚደበድብ አይደለም። እሱ ወያኔን የካደ ነው ይሉናል፡፡ ይህንን ብለው ቢያቆሙም ጥሩ ነበር፡፡ አሁንም ትንሽ ወረድ ይሉና እኔን የሚያሳዝነኝ የተማሩትም ያልተማሩትም ስሜት እየነዳቸው ሁሉም መደንቆራቸው ነው። ጨፍጫፊ አንቀጥቃጭ መሆንና ጠበቅ ማለት አንድ አይነት አይደሉም። ወያኔ ጥብቅ እንደነበረ አይካድም። በጥቂት በጥባጮች ላይ እርምጃ መውሰድ ጨፍጫፊነት አይደለም ይላሉ፡፡ እንዲህ ዓይነት ስህተትን ላለማመን የሚደረግ በጢሻ ውስጥ መኳተን ጤናማ አእምሮ ካለው ሰው የሚመነጭ ካለመሆኑም በላይ ትዝብት ላይ የሚጥል ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ ስሜት የሚነዳው እና ደንቆሮው ማን እንደሆነ ለአንባቢ ፍርድ እተወዋለሁ፡፡

ዶ/ር ዮሐንስ በጽሁፋቸው መቋጫ ላይ ቀጥሎ የምለው ነገር ለራሴም ይዘገንነኛል በማለት ያነሱትን እጅግ አስደንጋጭ ሃሳብ በመጥቀስ አስተያየት ልስጥበትና ጽሁፌን ልቋጭ፡፡ በጓንታናሞና በአቡ ግሬብ እስር ቤቶች በተፈፀመው ሰቆቃ ከስልጣን የወረደ የታላቋ አሜሪካ ፕሬዚደንት የለም። አሜሪካውያን በድርጊቱ እያለቀሱና እየጮሁ ያስቀደሙት ግን ሰላምና ደህንነታቸው መጠበቁን ነው። እኔ የሚታየኝ መፍትሄ እስከ ምርጫ ድረስ የሃገር ህልውናና የህዝብ ሰላማዊ ኑሮ በማስቀደም ከህወሓት ጋር እርቅና ሰላም ተፈጥሮ በጋራ መስራት ቢሞከር ነው ይላሉ ዶ/ር ዮሐንስ፡፡

ይህ አባባል የዶ/ር ዮሐንስን ጤናማነት እንድጠራጠር ነው ያደረገኝ፡፡ ዶ/ር ዮሐንስ ሆይ! በጓንታናሞና በአቡ ግሬብ እስር ቤቶች የታሰሩት እኮ አሜሪካውያን ሳይሆኑ የዐረብ ደም ያላቸው ሙስሊሞችና ጥቁሮች ናቸው፡፡ ታዲያ የአሜሪካ መንግስት በአሜሪካውያን ላይ የሽብር ጥቃት ያደርሳሉ ብሎ የጠረጠራቸውን አሸባሪዎች በማሳሩ አሜሪካውያን መንግስታቸውን እንዴት ከስልጣን ውረድ ሊሉ ይችላሉ?

ማዕከላዊ እስር ቤት ታስረው በገዛ ወገኖቻቸው ግብረ ሰዶም የተፈጸመባቸው፣ ብልታቸውን የተኮላሹ፣ ጥፍራቸው የተነቀለ፣ አካላቸው ጎደለ፣ ከሌላ አገር የመጡ ባዕዳን አይደሉም፡፡ ይሄ ከአሜሪካው ጋር የሚነጻጸር ነው? በኔ እምነት ከሌላ አገር የመጣ አሸባሪም ቢሆን አንዴ በቁጥጥር ስር ካዋልነው በኋላ ሰብአዊ ክብሩ ሊጠበቅ ይገባል እንጂ አረመኔያዊ ግፍ ሊፈጸምበት አይገባም፡፡ በበኩሌ የጓንታናሞና የአቡ ግሬብንም የማዕከላዊንም ግፎች አወግዛለሁ!!!

እኔ የሚታየኝ መፍትሄ እስከ ምርጫ ድረስ የሃገር ህልውናና የህዝብ ሰላማዊ ኑሮ በማስቀደም ከህወሓት ጋር እርቅና ሰላም ተፈጥሮ በጋራ መስራት ቢሞከር ነው የሚለውን በተመለከተ፤ እኔ የሚታየኝ መፍትሄ ደግሞ ህወሓት የሚባል ፓርቲ እንደገና ወደ ስልጣን ከሚመጣ የሃገር ህልውና ይናጋ! የህዝብ ሰላማዊ ኑሮ ይደፍርስ! - ካልጓሸ አይጠራም ወዳጄ!!! ሕወሓት ከኢትዮጵያ ህዝብ ጫንቃ ላይ እንደ ወረደ ሁሉ ከትግራይ ህዝብ አናት ላይ እንዲወርድ ትግሉ ይቀጥላል!

ጸሐፊውን በEmail: ahayder2000@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡

 

Back to Front Page