http://aigaforum.com/images/Aiga4.jpg


Back to Front Page

ህወሓትም እንደ ናፓልዮን ቦኖፓርት

በዓል ጋዳ ሩባና

5-29-19

መግቢያ

ባለፈው ዓመት “አንበሳን ፍለጋ” በሚል ርእስ የኢህአዴግን የሃያ ሰባት ዓመታት ጉዞ ባጭሩ ለመገምገም ሞክሪያለሁ፡፡ ኢህአዴግ እንደ ድርጅት በውስጡ ተውላጠ ባህሪያት እያሳየ መምጣቱንም አመላክቻለሁ፡፡ የህወሓት ኢህአዴግ መስመር በትግል የተገኘና በተግባር የተፈተነ መሆኑ ተከራካሪዎች ከሞላ ጎደለ በአንድ ቃል ይስማሙበታል፡፡ ስለዚህ ክርክሩና ችግሩ መስመሩ ላይ ሳይሆን አመራሩ ላይ ነው ማለት ይቻላል፡፡ “በአንበሳን ፍለጋ” ፅሑፍ ላይ ያየናቸው ተውላጠ ባህሪያትም የአመራሩ ማለትም የድርጅቱ ተውላጠ ባህሪያት ናቸው፡፡

 

የኢህአዴግ ድርጅት የመጨረሻ ተውላጠ ባህሪ ካኪቶክራሲ መሆኑ አይተናል፡፡ ካኪቶክራሲ ረዘም ያለ ዕድሜ እንደማይኖረውም ተመልክተን አልፈናል፡፡ ለተውላጠ ባህሪ በተለይ ደግሞ ለፈጣንና ብዝኃ ተውላጠ ባህሪ በእጅጉ ተጋላጭ ነው፡፡ በዘመነ ካኪቶክራሲ /የጉፋያ፣ እምባጮ/ጥፉረሪያ) ስርዓት ተደብቀው የነበሩ ባሕሪያት በአንድ ጊዜና በፍጥነት የመውጣታቸው ዕድል ሰፊ ነው፡፡

Videos From Around The World

 

ዓምና “አንበሳን ፍለጋ” በሚል ፅሑፍ ላይ የአዲሱ “የኢህአዴግ የለውጥ አመራር ወይም ደግሞ ቲም” ባሕሪያት ስፅፍ ብዙ አስተያየቶች ደርሰውኛል፡፡ ከተሰጡኝ አስተያየቶች ውስጥም 1 ገና ወር ያልሞላው አመራር ይህ ይሆናል ብሎ መፃፍ የብስለት መጓደል ወይም ናይቪቲ ነው፡፡ ስለሆነም ባሕሪውን ለመገንዘብ ቢያንስ ሁለት ሶስት ዓመታት ማየት ያስፈልጋል፡፡ 2 ደግሞ ኢህአዴግን በትክክል ገምግመህ አስቀምጠሃ፡፡ ስለዚህ ቀደም ብለህ ያስቀመጥካቸው ነገሮች በትክክል እየተከሰቱ ስለሆነ በነካህ እጅህ ከግንቦት 2010 . እስከ ግንቦት 2011 . ያለውንም ጉዞ ኣመላክተን የሚሉ ይገኙበታል፡፡

 

ከዚሁ ጋር በተያያዘ መልኩም የልማታዊና ዲሞክራሲያዊው መስመራችን ዕጣ ፈንታ ምንድን ነው? የሃገራችን የፓለቲካ ሃይሎች አሰላለፍ ምን ሊመልስ ይችላል? የካኪቶክራሲው ዕድሜስ ምን ያህል ሊሆን ይችላል? ወዘተ የሚሉ ይገኙበታል፡፡

 

“አንበሳን ፍለጋ” በቁጭት ፅፌዋለሁኝ፡፡ ብዙ አንባቢም አግኝቷል፡፡ አብዮታዊና ልማታዊ መስመራችን መሪ ካገኘ በአጭር ጊዜ ለውጥ እንደሚያመጣ ጠቁሜ ነበር፡፡ አንበሳ መሪዎች ደግሞ በንቅናቄ እንደሚፈጠሩ በልበሙሉነት ፅፌያለሁ፡፡ “የአንበሳ ፍለጋ” ቀጣይ ፅሁፍም በተከታዮቼና ጠያቄዎቼ ስም “ህወሓትም እንደ ናፓሊዮን ቦኖፓርት” በሚል ርእስ በግንቦት 20 ስም እነሆ በረከት እላለሁ፡፡

1.     ወያኔ እንደ “ቀበሮም” እንደ አንበሳም

አንበሳን ፍለጋ ስፅፍ በታላቁ አሌክሳንደር ጥቅስ ነበር የዘጋሁት፡፡ የአሁኑ የዓመቱ የህወሓት ኢህአዴግ በአጠቃላይ ደግሞ የሀገራችን መንግስት ጉዞ ደግሞ በታላቁ ናፓሊዮን ቦኖፓርት ዘመን አይሽሬው ጥቅስ ልጀምር፡፡ “I am some times a fox and sometimes a Lion. The whole secret of government lies in knowing when to be the one or the other” (እኔ አንዳንዴ እንደቀበሮ ነኝ ሌላ ጊዜ ደግሞ እንደ አንበሳ ነኝ የመንግሥት አስተዳደር አካሄድ ምስጢር መቼ ምን መሆንና የትኛው መሆን እንዳለብህ ማወቁ ላይ ነው” ይላል- ናፓሊዮን ቦናፓርት፡፡

 

ይህንን ፅሑፍ በዚህ ጥቅስ የጀመርኩት በምክንያት ነው፡፡ አንዳንድ ፀሃፊዎችና ተከራካሪዎች ይህንነ የካኪቶክራሲ ስርዓት ውርጋጥነት ካዩና ካስተዋሉ በኋላ ህወሓት ምንም ይሁን ምን ስልጣኑን ሲያስረክብ ተደናግጧል፡፡ በሌላ አነጋገር (soft landing) የተረጋጋ ሽግግር አላደረገም፡፡ ባንድ ጊዜ ተደናግጦ መቐለ መሽጓል ለዚህም ለአሁኑ ችግሮች ድርሻ አለዉ በማለት ይፅፋሉ፡፡ በሌላ በኩልም ይህንን የሚያጠናክር “የእህት ድርጅት” መሪዎች ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡ ይህንን አስተሳሰብ የሚቃወም ሚዲያ ስለሌለም አስተሳሰቡም ወደ ሃይማኖታዊ ትንቢትም ይሄዳል፡፡ አንዳንድ ወገኖች “ወያኔ እንደጉምና ንፋስ ድንገት በኖ ይጠፋል” የሚል ትንቢት ነበር ሲሉም ይደመጣሉ፡፡ ስለሆነም የነበረው ትንቢት ቀኑ ደርሶ ተፈፀመ ይላሉ፡፡ እኔ ግን ከሁለቱም አመለካከቶች ውጪ ነኝ፡፡ ላስረዳ

 

1.     የሴፍቲኔትና የሴፍቲሮፕ ፓለቲካ በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች

ሴፍቲኔትና ሴፍቲሮፕ የሚባሉ ቃላት ወይንም ደግሞ እሳቤዎች መጀመሪያ ጥቅም ላይ የዋሉት በስፖርት፣ በአደጋ ተከላካይ ተቋማት ላይ ነበር፡፡ ቀጥለውም በኢንሹራንስና ማኔጅመንት ተቋማት ላይ ተስፋፋ፡፡ የዛሬ 30 ዓመታት ደግሞ ወደ ምግብ ዋስትና ፕሮግራሞች ተስፋፉ፡፡ የተለያየ ቅጥያዎችም ተበጀላቸው፡፡ 2010 . በኋላ ግን ሴፍቲኔት ሴፍቲሮፕ ወደ ፖለቲካ ዲስኮርስም መግባት ጀምረዋል፡፡

 

ሴፍቲኔት /የደህንነት መረብ/ የዝላይ ስፖርተኞች ዘለው ወገባቸው እንዳይሰበር አደጋ የሚቀንሱበት መረብ ነው፡፡ ይህ መረብ ዞሮ ዞሮ በተለይ የምሩኩዝ ዝላይ ዘላዮች የከፋ አደጋ ላይ እንዳይወድቁ የሚያደርግና የሚያግዝ የጥንቃቄ መረብ ነው፡፡ በምግብ ዋስትና ዘርፍም ሴፍቲኔተ በድህነት ላይ ያሉ ዜጎች የከፋ የምግብ ዋስትና እጦት ተጠቂ ሆነው ሰብአዊ ቀውስ በስፋት እንዳይከሰት ጉዳቱ የሚቀንስ የምግብ ዋስትና ፕሮግራም ነው፡፡ ሴፍቲኔት የከፋ አደጋ እንዳይከሰትና ተጠናክረህ የምትወጣበት ሰፊ የአደጋ መከላከያ ንድፍ ነው፡፡

 

ሴፍቲሮፕ አብዛኛው ጊዜ የእሳት አደጋ ሠራተኞች፣ የኮንስትራክሽን ሠራተኞተ ለአደጋ ጥንቃቄ የሚጠቀሙበት አደጋ ቀናሽ የጥንቃቄ መሳሪያ ነው፡፡ ይሄ የአደጋ ቅደመ ማስጠንቀቂያ ስልት አስክሬኖች የሚወጡበትና ኣውጪው አካል የሚታደግበት ስልት ነው፡፡ በዚህ ስልት የመዳን ዕድል እጅግ ጠባብ ነው፡፡ በቀጭን መንገድ ላይ እንደመጓዝ ማለት ያህል ነው፡፡

 

ሴፍቲኔት እና ሴፍትሮፕ አደጋን የሚቀንሱ የቅድመ ጥንቃቄ መሣሪያዎች ቢሆኑም ከሴፍቲኔት የመትረፍ እድልህ ሰፊ ሲሆን ከሴፍቲሮፕ ግን ከሚሊዮን አንድ እንደማለት ያህል ነው፡፡ ይህ በኢንሹራንስም፣ በስፖርትም፣ በምግብ በዋስትናም በፓለቲካም ዓለም ይሰራል፡፡

 

2008 – 2010 . የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች አደጋ ውስጥ እንዳሉ መገምገማቸው ይታወሳል፡፡ በተለይ ደግሞ 2010 . ግምገማ ከረርና መረር ያለ ነበር፡፡ ከዚህ አደጋ በፍጥነተ መውጣት እንዳለባቸው ተማምለው ወጥተዋል፡፡ አካሄዳቸው ግን ለየቅል ነበር፡፡ ውጤቱም በአካሄዳቸው መሠረት ሆነ፡፡

 

ህወሓት አደጋ ላይ ነኝ ብሎ ካመነ በኋላ የወደቀበት ቦታ ወይም ደግሞ መረብ ሴፍቲኔት/የደህንነት መረብ/ ነው፡፡ ቅድም ከላይ የተነሱ አመለካከቶች አልጋራም ያልኩትም ከዚሁ ንድፈ ሐሳብ አንፃር ነው፡፡ መጀመሪያ ህወሓት “ቲም” የሚባለው ኃይል ወደ ሥልጣን ከመምጣቱ በፊት ከስድስት ወራት በፊት ነው ትግራይን ማዕከል አድርጌ እሰራለሁ ያለው፡፡ ስለዚህ ሶፍት ላንዲንግ አላደረገም ሊባል አይችልም፡፡ ደንግጦ በሳምንት ውስጥ ሸሽቶ መቐለ መሽጓል የሚል አባባልም ስህተት ይሆናል፡፡ በትንቢት መሠረት እንደጉም በኖ ጠፍቷል የሚለውም ድንገት የተከሰተ ሳይሆን በግምገማ መሠረት የተኬደ መሆኑን ማጤን ያስፈልጋል፡፡

 

ወያነ/ህወሓት/ ትግራይን ማዕከል አድርጎ እዛው መጠናከር ተገቢና ወቅታዊ ነበር፡፡ የመጀመሪያው ምክንያት የህወሓት የረዥም ጊዜ ኮንስቲዩንሲ ትግራይና የትግራይ ህዝብ ነው፡፡ ሁለተኛው ምክንያት የተበታተነ ግን ደግሞ መስመሩን ጠንቅቆ የሚያውቅና በአጭር ጊዜ ሊሰባሰብ የሚችል ሃይል ያለው እዛው ነው፡፡ ስለዚህ ህወሓት /ወያነ/ ወደ ትግራይ መሰባሰቡ የተጠና አወዳደቅ /soft landing/ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ሪትሪት ሲያደርግ ሪትሪቱ አሳምሯል፡፡ በሌላ አነጋገር ህወሓትና አመራሩ ሶፍት ላንዲንግ አላደረገም የሚለው ክርክር ውሃ ሊቋጥር አይችልም፡፡ ህወሓት አዘላሉ አሳምሯል፡፡ የጀርባ አጥንቱ አልተሰበረም፡፡ ፓለቲከኞቹ ይህንን የህወሓት /ወያነ/ አይነት ማፈግፈግና ከአደጋ የማምለጥ ቅድመ ጥንቃቄ ፓለቲካል ሴፍቲኔት ይሉታል፡፡

 

ህወሓት /ወያነ/ በፓለቲካል ሴፍቲኔት ማፈግፈግ /ሪትሪት/ ሞዴል አንዴ በአደባባይ እየተሰደበ ሌላ ጊዜ እንደ ህዝብም ያላደረገው ነገር አደረገ ተብሎ እየተዘለፈና እየተዋረደ አቅሙን ለማሰባሰብና በአጭር ጊዜ አቅም ሊሆኑት የሚችሉትን ኃይሎችን እያሰባሰበና ችግሮቹን እየፈታ “ቀበሮ” በመሆን ለጊዜውም ቢሆን የፓለቲካ አቧሪውን ለመሻገር ሞክሯል፡፡

 

ሌላው ምክንያት ህወሓት /ወያነ/ ረጅም የትግል ታሪክ ያለው ድርጅት ነው፡፡ ማፈግፈግ ወይንም ደግሞ ፓለቲካል ሪትሪት ለህወሓት አዲስ አይደለም፡፡ ህወሓት አንዴ “የእርጐ ዝንብ”፣የጓሮ አይጥ ሌላ ጊዜ ደግሞ ከሃዲ ወዘተ እየተባለ በሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች ብቻ ሳይሆን በትግራይ ህዝብ ጭምርም ዘመቻ ተካሂዶበት እንደነበር ይታወቃል፡፡ ደርግ ከቀይሽብር በኋላ ማለትም 1970 . በኋላ የህወሓት /ተሓህት/ ታጋዮች በመንደሩ አካባቢ ሲያልፉ እሪ በማለት ጭሆት የማያሰማ መንደር እንደመንደር ይቃጠላል ብሎ ፋሽስታዊ አዋጅ አውጆ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በዚሁም መሠረት 1971 . በምሥራቅ ትግራይ በህወሓት ታጋዮች ላይ ህዝቡ ሳይወድ ደርግን ፈርቶ እሪታውን ያቀልጠው እንደነበር የህወሓት የታሪክ ማህደር ይነግረናል፡፡ ይህንን እንዴት እንደፈታው ህወሓት ጠንቅቆ ያውቃል፡፡

 

የደርግ ተደጋጋሚ ግዙፍ ወረራዎች፣ ድርቅ፣ የጨለማው ጊዜ የአውሮፕላን ድብደባ ወዘተ ለህወሓት ጥሩ ስንቅ ናቸው፡፡ ህወሓት ብቻውን ሊባል በሚቻልበት ደረጃ ደርግ ወደ መውደቂያው መቃረቡና የዲሞክራሲ ሃይሎች እንዴት መሰባሰብ እንዳለባቸው እንደ አሁኑ ዘመናዊ የመገናኛ ቴክኖሎጂ ባልነበረበት ወቅት መስመሩ ከትግራይ አልፎ እንዴት የኢትዮጵያውያን እንዳደረገው የትግል ተሞክሮው ይነግረናል፡፡ስለዚህ ህወሓት /ወያነ/ ሶፍት ላንዲንግ አላደረገም፡፡ እንደበረዶና እንደጉም በትንቢቱ መሠረት በኖ ጠፍቷል የሚለው መከራከሪያ ሚዛን የማይደፋው ሌላኛው ምክንያት ህወሓት የመጣበትን የትግል ውጣውረዶችን ካለመገንዘብና ካለማወቅ የሚመነጭም ስለሚሆን ነው፡፡

 

ህወሓት /ወያነ/ ወደመቐለ የሄደው በዛን ጊዜ መሆን የነበረበት አዲስ አባባ ላይ ተቀምጦ እንደ አንበሳ ማጓራት ሳይሆን ለአጭር ጊዜም ቢሆን መቐለ /ትግራይ/ ማእከል አድርጎ “ቀበሮ” መሆን የግድ ይል ስለነበር እንደ ናፓሊዮን ቦኖፖርት አባባል መቼ ምን መሆን እንዳለበት የሚያውቅ ድርጅት ስለሆነ ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ቀበሮ መሆኑን መርጧል፡፡ በመሆኑም ህወሓት አሁን ለተከሰተው ውድቀት ተጠያቂ የሚሆንበት አንድም ምክንያት ሊኖር አይችልም፡፡

 

ከዚህ በተፃራሪ ኦህዴድ እና ብአዴን አደጋ ላይ በመሆናቸው ለይስሙላ ተቀብለው እንደወጡ ይታወሳል፡፡ ከአደጋ ለመውጣት የተጠቀሙበት የአደጋ መቀነሻ /መከላከያ/ መሣሪያ ደግሞ ወደህዝባቸው መውረድ አልነበረም፡፡ ይልቁንም የላይኛው አመራር “የለውጥ ቲም” ተብለው ስልጣን ከጨበጡ በኋላ የአሜሪካ፣ የአውሮፓና የኤርትራ ጉዞቸውን እና የጫጉላ ሽረሸራቸውን አጧጧፉ፡፡ ይህንን የተከታተሉ ፓለቲከኞች የነዚህ ድርጅቶች አካሄድ የፓለቲካ ሴፍቲሮፕ ይሉታል፡፡ ድርጅቶቹ አደጋ ላይ መሆናቸው የተገነዘቡበት ዕድል አልነበረም፡፡ አካሄዳቸው የአውሮፕላን ተሣፋሪዎች አደጋ ይመስላል፡፡ ድርጅቶቹ ከአደጋ የመውጣት ዕድላቸው በጣም ጠባብና አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ልክ ሰማይ ላይ በሚጋይ አውሮፕላን ውስጥ ያሉ ተሳፋሪዎችን በሕይወት የማውጣት ጠባብና ፈታኝ አደጋ መከላከል ይሆናል፡፡ ጉዞውም ጨለማ ያደርገዋል፡፡

 

ኦህዴድና ብአዴን ከህወሓት በተፃራሪ ከህዝብ ተነጥለው ከነበሩበት መስመርም እጅጉን ተነጥለው የተወሰኑ ወራት ራቁታቸው ወጥተው የህዝባቸው መሣቂያና መሣለቂያ ሆነዋል፡፡ አሁን አሁን ግን አዳምና ሄዋን ገበናቸውን ለመሸፈን ቅጠል እንዳደረጉ ሁሉ ብአዴንና ኦህዴድ ገበናቸውን ለመሸፈን የትምህክተኛችን የፓለቲካ ድሪቶ ለብሰዋል፡፡ ብአዴንና ኢህዴን ከጥንቱ የፓለቲካ ነብሳቸው በሕይወት ለማትረፍ ያለው ዕድል እየጠበበ መጥቷል፡፡ ያለው ዕድል የድርጅት አስክሬናቸውን ለማግኘት ብቻ ይሆናል፡፡ አስክሬኑ በፓለቲካ ሴፍቲኔት ለማውጣት የማይታሰብ ይሆናል፡፡ በፓለቲካ ሴፍቲሮፕ ግን ጠባብም ቢሆን ይቻላል፡፡ አውጪው ግን ህዝቡ ወይንም ህወሓት አይሆንም፡፡ የፓለቲካ ሴፍቲሮፕ መርሃ ግብር የተካኑበት ምዕራባውያን ናቸው፡፡ አሁን አሁን ምዕራባውያኑ ተስፋ የቆረጡ ይመስላሉ፡፡ ስራውም ለአረቦችና ለጎረቤቶቻችን እጅ ማፍታችያ የሰጡ ይመስላሉ፡፡ ውጤቱ በጋራና በቀጣይ የሚታይ ይሆናል፡፡

 

2.     የቦታ መፈናቀል ወይም የፓለቲካ መፈናቀል?

በዚህ ዓመት ውስጥ ሃገራችን ውስጥ ከሶስት ሚሊዮን በላይ የሃገር ውስጥ ተፈናቃዮች መኖራቸው ተዘግቧል፡፡ ይህ ክስተት የአገራችንነ ገፅታ በአሉታዊ መልኩ ቀይሮታል፡፡

ይህ ኣሃዝ ትንሽ ነው ባይባልም የተጋነነ አሃዝ ግን አይደለም፡፡ ከሃገራችን ተሞክሮ አኳያ ማኔጀብል ነው፡፡ ሃገራችን 10 ሚሊዮን በላይም ቢሆን ሰብአዊ ቀውስ ሳያስከትል የመፍታት ልምዱን አቅሙም ኣላት፡፡

 

ለሃገራችን አዲስ የሆነውና የመፈናቀሎች ሁሉ መንስኤ የሆነው ግን በዓለም ላይ ያልታየው አዲሱ የመፈናቀል አይነት ነው፡፡ መፈናቀል በተፈጥሮ አደጋ፣ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በፓለቲካ፣ በልማት ሊመጣ ይችላል፡፡ እነዚህ እስከ አሁን በሃገራችንም ሆነ በዓለም የታዩ መፈናቅሎች የሚያስከትሉት አደጋ እንዳይባባስና እንዳይጨምር በመንግስታትና በዘርፉ ባለሙያዎች መፍትሄ ተቀምጦላቸዋል፡፡ ይህ በሃገራችን ከቅርብ ጊዜ የታየው መፈናቀል ግን ለአለም ማህበረሰብ ይሁን ለዘርፉ ባለሙያዎች አዲስ ነው፡፡ የመፈናቀሉ ዓይነትም የፓለቲካ አመለካከትና መስመር መፈናቀል ልንለው እንችላለን፡፡

 

ኢህአዴግ እስከ ቅርብ ጊዜ ስምንት ሚሊዮን አባላት አሉኝ ብሎ ሲነግረን ነበር፡፡ 2010 . በኋላ ግን የብአዴንና የአህዴድ አባላት ከልማታዊና ዲሞክራሲያዊ መስመር ተፈናቅለዋል፡፡ ስለዚህ 6-7 ሚሊዮን የኢህአዴግ አባል ከመስመር ተፈናቅሏል፡፡ ዓለምና ኢትዮጵያውያን በጌዲኦ፣ በጎንደር፣ በሶማሌ፣ በኦሮሚያ ስለተከሰተው መፈናቀል ሲያወሩ ይሰማል፡፡ በተቻለውም መጠን መፈናቀሉ ሰብኣዊ ቀውስ እንዳያስከትል የዕለት ደራሽ እርዳታ ሲለግስ ይታያል፡፡ ስለኢህአዲግ አባል ድርጅቶች (ብአዴንና ኦህዴድ) አባላት መፈናቀል ግን ሚዲያው ይሁን ፓለቲከኞች እንዲሁም የዘርፉ ባለሙያዎች ሲዘግቡና ሲያወሩ እምብዛም አይሰሙም፡፡

 

ብአዴን ሶስት ሚሊዮን አባላቱ ከአብዮታዊና ልማታዊ /ህዝባዊ/ መስመር ተፈናቅለዋል፡፡ መፈናቀላቸውም የድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች በተዘዋዋሪ እና በቀጥታ መንገድ አረጋግጠዋል፡፡

ኦህዴድ 3-4 ሚሊዮን አባላቱ በከፊል ይሁን ሙሉ በሙሉ ከመስመር ተፈናቅለዋል፡፡ ከደኢህዴንም ቢሆን የተወሰኑ አባላት የመፈናቀል አዝማሚያ ይታይባቸዋል፡፡ ስፋቱና ክፋቱ ግን እንደብአዴን አይሆንም፡፡ ሊሆንም አይችልም፡፡

 

ይህ የፓርቲ አባላት ከቆየው ህዝባዊና ዲሞክራሲያዊ አመለካከት መፈናቀል ብዛቱ ትልቅ ነው፡፡ ከቦታ ቦታ ከተፈናቀሉና ዓለም ከሚያወራላቸው ሶስት ሚሊዮን ተፈናቃዮች በእጥፍ ይበልጣል፡፡ ስድስት ሚሊዮን ይሆናል፡፡ የሁሉም መፈናቀሎች መንስኤም እሱ ነው፡፡ የዘርፉ ባለሙያዎች ይህ ዓይነቱ መፈናቀል silent and invisible displacement (SID) ይሉታል፡፡ ስውርና የማይታይ መፈናቀል እንደማለት ነው፡፡ አደገኛም ነው፡፡

 

ህወሓት አባላቱ ከፕሮግሪሙ እምብዛም አልተፈናቀሉም፡፡ ባለመፈናቀላቸው ለሌላው ዓይነት መፈናቀል ምክንያት አልሆኑም፡፡ SID የተባለው አደገኛ መፈናቀል ግን ከሩቅም ቢሆን እንደ ኢቦላ ቫይረስ በትኩረት እንዲያዩት ሆኗል፡፡

 

ሶስት ሚሊዮን የሃገር ውስጥ ተፈናቃዮች /IDP/ ችግራቸው ስብኣዊ ቀውስ እንዳያስከትል በዕለት ደራሽ የእርዳታ ድጋፍና በምግብ ዋስትና ፕሮግራሞች መታደግ ይቻላል፡፡ ነገር ግን የዚሁ መፈናቀል ምንጭ የፓለቲካ ድርጅቶች አባላት ከህዝባዊ መስመር መፈናቀል የወለደው ስለሆነ የፈለገውን ያህል የዕለት ደራሽ እርዳታ፣ የምግብ ዋስትናና የመልሶ ማቋቋሚያ /ERP/ ፕሮግራሞች ቢነደፉ ሊሳኩ አይችሉም፡፡ ይባስኑ ችግሩ እየተባባሰ ይሄዳል፡፡ የተፈናቃዮቹ ቁጥርም ይጨምራል፡፡

 

1.     የፓለቲካ መስመር ተፈናቃይ አባላት ቁማር

የኦህዴድና ብአዴን አባላት ከልማታዊና ዲሞክራሲያዊ /ህዝባዊ/ መስመር ከተፈናቀሉ ቆይተዋል፡፡ መፈናቀሉ በራሱ ችግር ሆኖ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ “ተፈናቃይ” /SID/ የድርጅቱ አባላት እስከ ቀበሌ ድረስ ሰፊ መዋቅር ያላቸው መሆኑ ነው፡፡ ሰፊ መዋቅር ብቻ ሳይሆን የተደራጀ፣ የታጠቀ በጎበዝ አለቃ የሚመራ “አፈናቃይ” ታጣቂ ኃይልም ያላቸው መሆኑ ነው፡፡ አንዳንዴም “ፈጥኖ ደራሽና ተወርዋሪ አፈናቃይ” ኃይልም አላቸው፡፡

 

የድርጅት የፓለቲካ ተፈናቃይ አባላት “እርዳታ አሰባሳቢ” ኃይልም አዋቅሯል፡፡ ይህ ኃይል በስመ ግብረ ኃይል የተዋቀረና “ህጋዊ” ሽፋን ያለው ቢሆንም በተግባር ግን የግል ባለሃብቱና መንግሥታዊ የፋይናንስ ተቋማትን ሃብት በጡንቻው በቀጥታ ይሁን በተዘዋዋሪ የሚዘርፍ ሆኗል፡፡ ግልፅነትና ተጠያቂነት /Transparency and accountability/ የሚባል አሠራር የለውም፡፡ በስመ ተፈናቃዮች የመሬት ወረራ፣ የሃገሪቱ የሃብት ወረራ ይታያል፡፡ የተፈናቃዮች ልየታ /targeting/ የማይታሰብ ነው፡፡ ማን ነው ተፈናቃይ፣ ከየት እንዴት ወዘተ የሚሉ በተፈናቃዩ ማህበረሰብና በህዝቡ ተሳትፎ አይካሄዱም፡፡ ስለዚህ ለዝርፊያ የተጋለጠ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በተፈናቃዮች ስም ቁማር ይሰራል፡፡ “ለታጣቂ” ኃይልም “ጋኞታ” ይቆረጣል፡፡ ለአቋማሪው ቤትም ኪራይ ይከፈላል፡፡ አቋማሪ ቤቶች የፓለቲካ ድርጅቶቹ ናቸው፡፡

 

የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች /Internally displaced people/ ችግር በዕለታዊ ደራሽ እርዳታና በምግብ ዋስትና ፕሮግራሞች ይፈታል፡፡ acute /ጊዜያዊ/ ከሆነ በዕለታዊ ደራሽ እርዳታ chronic /ስር የሰደደ ከሆነ ደግሞ በዘላቂ የምግብ ዋስትና ፕሮግራም ይፈታል፡፡ ይህ የሃገር ውስጥ ተፈናቃዮችን በዚህ ደረጃ እንዲፈናቀሉና መፍትሄ በተገቢው መንገድ እንዳያገኙ እያደረገ ያለው የድርጅት አባላት ከነበረው ህዝባዊና ዲሞክራሲያዊ መስመር መፈናቀል SID ጊዜያዊ /acute/ እና Chronic /ስር የሰደደ/ ብለን ልንከፍለው እንችላለን፡፡ Acute /ጊዜያዊ/ የተባለው የአባላት ከመስመር መፈናቀል በተለመደው የድርጅቱ /የኢህአዲግ/ ግምገማ ወይንም ደግሞ የጥልቅ ተሃድሶ ተገማግሞ ሊድንና የሚያስከትለው አደጋ ሊቀንስ ይችላል፡፡ Chronic /ስር የሰደደ/ የአባላቱ ከመስመር መፈናቀል በተለይ ደግሞ የድርጅቶቹ የላይኛው ካድሬና አመራር በዚሁ ችግር እየተሰቃየ ይገኛል፡፡ ይህ ችግር ደግሞ በተለመደው ግምገማና ጥልቅ ተሃድሶ ሊፈወስ አይችልም፡፡

የዚሁ Chronic /ስር የሰደደ/ ችግር ዘላቂ መፍትሄ ምርጫና የምርጫ ካርድ እንኳ ቢሆንም ከችግሩ አንፃር ግን ችግሩ የተወሳሰበና በቁማርም የታጀበ ስለሆነ ልክ ቁማርተኛው ገንዘቡ ተበልቶ ሲያልቅ የጋብቻ ቀለበቱን ቀጥሎ ደግሞ ሚስቱን እንደሚያስይዝ ሁሉ ይህ የተደራጀ የፖለቲካ መስመር ተፈናቃይ ኃይል /SID/ ህዝቡና አገሪቱን ለውጭ ኃይል ሊያስረክብና የባስ አደጋ ሊያመጣ ስለሚችል አካሄዱ የግድ ምርጫና የምርጫ ወቅትን እና ዉጤትን የሚጠብቅ ላይሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ አደጋውን ለመቀነስ የተለያዩ ስልቶችን ከወዲሁ ማየቱን ይጠይቃል፡፡

 

3.     የፓለቲካ ኃይሎች አስላለፍ

አሁን አሁን የሃገራችን የፓለቲካ ኃይሎች አስላለፈ ግልጽ ሆኖ ወጥቷል፡፡ ይኸውም ፌደራላዊ ሃይሎችና አሃዳዊ ሃይሎች ልንላቸው እንችላለን፡፡ ጥቂት በመሃል የሚዋልሉ ወላዋይ ድርጅቶች ያሉ ቢሆንም ዞሮ ዞሮ እነዚህ ጥቂት ኃይሉች የኃይል ሚዛኑን በማየት ወደ አንዱ አስላለፍ የመጠቃለል ባህሪ ይኖራቸዋል፡፡ የፌደራሊስት ኃይል ዋና ኮር /ማእከላዊ ሃይል ወይም አሰባሳቢ/ አሁንም ህወሓት ነው፡፡ ቀጥሎም ነባር የኦሮሞና የሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ድርጅቶችና ሕዝቦች ናቸው፡፡የሃይል አሰላለፍ መጀመሪያ የሚታየው በህዝብ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ አብዛኛው ሊባል የሚችል የኢትዮጵያ ህዝብ ህገመንግሥትና በህገመንግሥቱ የተቀዳጃቸው ራስን በራስ የማስተዳደርና የማንነት ጥያቄዎች ለማንም አሳልፎ ሊሰጥ አይፈቀድም፡፡ በሌላ በኩል ካኪቶክራቲክ መንግሥትና ድርጅቶች እንዲሁም ያለፉት ስርዓት ናፋቂዎች መልካቸውን በመቀያየር የዜግነት ፓለቲካ የመደመር ሃልዬት ወዘተ እያሉ የኣሃዳዊነትን ስርዓት ለመገንባት በመጣጣር ላይ ይገኛሉ፡፡

 

የደርግና የኃይለስላሴ የቆየ የግዛት አንድነት አስተሳሰብ በአዲስ አቁማዳ ስሙን በመቀየር የግዛት አንድነት የሚል ሕዝቡ ስለማይቀበለን “መደመር” ብንለው ይሻላል በማለት ሕዝቡን ለማጭበርበር እየሞከሩ ይገኛሉ፡፡

 

ብዙዎቻችን የመደመር እሳቤ አፍላቂ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ይመስሉናል፡፡ ከዛ አለፈ ካለም “የለውጥ ቲሙ” ይመስለናል፡፡ ነገር ግን እነዚህ ኃይሎች አይደሉም፡፡ የመደመር አዝማሪዎች የደርግ ቁንጮች ናቸው፡፡ ለዓመታት ድምፁን ሳያሰማና ሳይተነፍስ የዘለቀው የደርግ ርእዮተ አለም አቀንቃኝና አፍላቂ ከሚባሉትና የኢሠፓ የፓሊት ቢሮ አባል የነበረ / አሻግሬ ይግለጡ ከኢሳት ጋር ረዥም ቃለ መጠይቅ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ በዚህ ቃለመጠይቁ ውስጥም “አንድነት” የሚለው ቃል በግርድፉ ተቀባይነት ስለማይኖረው “መደመር” የሚል የክርስትና ስም እንደወጣለትና ጥሩ እሳቤ መሆኑ ሲናገር ተደምጧል፡፡ ይህ “የመደመር” እሳቤ “አያ ዱቡልቡሌ” ቢሆንም በዝርዝር ሌላ ቀን በሌላ ፅሑፍ እመለስበታለሁ፡፡ ለጊዜው ግን በኢትዮጵያ የሃይሎች አሰላለፍ “የመደመር” አቀንቃኞች የኣሃዳዊ ስርዓት ተከታዮችና ደጋፊዎች ናቸው፡፡

 

እዚህ ላይ አንድ ነገር መገንዘብ አለብን፡፡ በአሁኑ ወቅት የአማራ ክልል ብአዴን /ኢዴፓ/ በኦሮሚያ ክልል ደግሞ ኦህዴድ /ኦዴፓ/ ያስተዳድሩታል፡፡ በርግጥ የነዚህ ድርጅት አባል አብዛኛው ከአብዮታዊና ልማታዊ /ህዝባዊ/ መስመር ካፈነገጠና ከተፈናቀለ ቆይቷል፡፡ የፌደራሊስቱና የብሔር ማንነት አጋዥ እና አቀንቃኝ ሆኖ ይሠራል ብሎ ማሰብ ያስቸግራል፡፡ “ተላላኪና” ካኪቶክራሲው ኃይል ያለፉት ወራት ስራዬ ብሎ የአስተዳደር እርከኑን በራሱ አምሳያዎችና በተላላኪዎቹ ተክቶ ጨርሷል፡፡ ዲሞክራሲያዊና ህዝባዊ አመለካከት ያላቸው አባላቱን በየጊዜው እያሸማቀቀና ከህዝቡ እየነጠላቸው መጥቷል፡፡

 

ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን የአማራና የኦሮሚያ ክልል ህዝብ ከልማታዊና ህዝባዊ አመለካከት ፍንክች አላለም፡፡ በተለያየ መንገድ አዲሱ ጥገኛና ካኪቶክራቲክ ኃይልን እየተቃወመ ይገኛል፡፡ በአደባባይም ያለፈው የኢህአዴግ አሠራርና አመራር ይሻለናል እያለ ይገኛል፡፡ በስውርና በግልጽም ከዲሞክራሲያውያን ኃይሎች ጋር ግንኙነት በመፈጠር ላይ ይገኛል፡፡ በየአካባቢውም በመሰለው መንገድ አየተደራጀ ነው፡፡ በየመድረኩና በተገኙ ዕድሎች ካኪቶክራቲክ አመራሩን ፊት ለፊት እያጋለጠው ይገኛል፡፡

 

የኣፋር፣ የቤንሻንጉልና አንዳንድ የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች የአካባቢ ድርጅቶችና መንግስታት ፊት ለፊት ካኪቶክራቲክ መንግስቱን እየተቃወሙት ይገኛል፡፡ አጋርነታቸውም ለፌደራሊስት ኃይል ሆኗል፡፡ ካኪቶክሪቲክ ኃይሉ በኃይል ጠምዝዞና በምልጃ ጋብዞ ወደ ጎራው ሊያሰልፋቸው ቢሞክርም ፅናታቸውን በተግባር አሳይተዋል፡፡ ያልታሰቡ የጎን አጥንት ውጋት ሆነውበታል፡፡

 

በግልጽ አነጋገር አሁን አሁን በስመ ለውጥ በተስፋ ሲጨፍሩ የነበሩ ኃይሎች የማታ ማታ ከገቡበት የሰመመን እንቅልፍ በመንቃት ላይ ናቸው፡፡ በተስፋም በድለላም መጓዝ እንደማይቻል በተግባር እያወቁ ናቸው፡፡ ስንከተለው የነበረው ስርዓት /ልማታዊና ዲሞክራሲያዊ/ ናፈቀን እያሉ ይገኛሉ፡፡ የስርዓቱ መሠረታዊ ምሰሶ የሆኑት ህገመንግሥቱና ህገመንግሥታዊ ስርዓቱ፣ የፌደራል ስርዓቱ፣ የብሄር ብሄረሰቦች መብትና የማንነት ጥያቄዎች ይከበር እያሉ አደባባይ መውጣት ጀምረዋል፡፡

 

ይህ ዓይነቱ እንቅስቃሴ ድንገት የተፈጠረ አይደለም፡፡ “ቀበሮው” ወያኔ ትግራይን ማዕከል አድርጎ በመሥራቱ የተገኘ ውጤት ነው፡፡ ህወሓት ልምዱን ተጠቅሞ ካኪቶክራቲክ ስርዓቱን ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ራቁቱን አውጥቶታል፡፡ ህገ መንግሥት ይከበር፣ ፌዴራል ስርዓቱ ይከበር፣ የብሄር ብሄረሰቦች መብት ይከበር ወዘተ የመሣሠሉት ጥያቄዎች የመጀመሪያ ወራት ላይ ከትግራይ ብቻ ይሰሙ ነበር፡፡ አሁን አሁን ግን በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች የቀን ተቀን የህዝቦች ጥያቄዎች ሆነዋ፡፡

 

በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች ዲሞክራሲያዊና ህዝባዊ ጥያቄዎች ያነገቡ የተለያዩ ድርጅቶች በግልጽ ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል፡፡ በስውርና በስፋት ተደራጅተው ከወራት በኋላ ብቅ የሚሉ ዲሞክራሲያዊያን ኃይሎችና ፌደራሊስት ኃይሎችም ይኖራሉ፡፡

 

ስለዚህ የህዝቦችን ጥያቄ እስከመለሰና ሃገሪቷን ከአደጋ እስከጠበቀ ድረስ አዲስ የግንባር፣ የቅንጅትና ተመሣሣይ አደረጃጀትና የኃይል መሰባሰብ ሊኖር እንደሚችል ከወዲሁ መዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ የዚህ የፌደራሊስት ኃይል ማዕከላዊ ኃይሎች ደግሞ ህወሓትና በኦሮሞ ህዝብ ተቀባይነት ያላቸው ፌደራሊስት ድርጅቶች ናቸው፡፡

 

የሃገራችን ሁኔታ ከየካቲት 2011 . በኋላ በፍጥነት ገፅታውና አሰላለፉ ተቀይሯል፡፡ ወያነ /ህወሓት/ የትግራይ ህዝብም መንግስታቸውና የፓለቲካዊ አካሄዳቸው ከቀበሮነት ወጥተው ወደ አንበሳነት ተቀይረዋል፡፡ ከየካቲት እስከ ሚያዝያ 2011 . የነበረው አንበሳ የአደን ቦታውና የሚታደኑ እንስሳትን በመለየት የተጠመደ ይመስላል፡፡ ከግንቦት 20/2011 . ያለው ህወሓት /ወያነ/ ግን እንደ አንበሳ ማግሳት ጀምሯል፡፡ ድምፁም እንደቀደሙ መላውን ኢትዮጵያ እያዳረሰ ይሄዳል፡፡ ካኪቶክራቲክ ኃይሉና አሃዳዊ ሃይሎች በግርማ ሞገሱ እንዲደናገጡና እንዲርዱ ያደርጋቸዋል፡፡ ህወሓት አሁን አንበሳ መሆን እንዳለበት አውቋል፡፡ “እኔ አንዳንዴ ቀበሮ ነኝ ሌላ ጊዜ ደግሞ አንበሳ ነኝ የአስተዳደር/መንግሥት አካሄድ ሚስጥር መቼ ምን መሆንና የትኛው መሆን እንዳለብህ ማወቁ ላይ ነው” እንዳለው ናፓሌን ቦናፓርት ህወሓትም ልክ እንደናፓሌን መቼ ምን መሆንና የትኛው መሆን እንዳለበት አውቆ የተንቀሳቀስ ድርጅት ነው፡፡ ፓለቲካዊ ብስለት ከሌለው በስተቀር የቀበሮ አስተሳሰብ ያለው ድርጅት ቢፈልግም ፈፅሞ አንበሳ ሊሆን አይችልም፡፡ ስለዚህ ከአሁን ጀምሮ የልማታዊና ዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብ /የፌደራሊስት አስተሳሰብ/ በህዝቡ ላይ የበላይነት እያገኘ ነው፡፡ ድርጅቶቹ ተሰባስበው አመራር ከሰጡት ደግሞ ተመልሶ ሄጅሞኒው /የአመለካከት የበላይነት/ የማያመጣበት መንገድ ፈፅሞ አይኖርም፡፡

 

ትግራይ ላይ ካለፈው ዓመት ጀምሮ የተለኮሰው የዲሞክራሲና የብሔር ብሔረሰቦች መብት የሕብረቀለም ጮራ /Specturm/ በፍጥነት በካኪቶክራቶች የፓለቲካ ኣቧራ ጨልሞ ወደነበረው ሌላው የኢትዮጵያ አካባቢ በፍጥነት እየተዛመተ ይገኛል፡፡ ምሉእ ሊሆንም ጉዞው እነሆ ጀምራል፡፡

 

ህወሓት አሁን አንበሳ መሪዎች በየአካባቢው ፈጥሯል፡፡ እነዚህ አንበሳ መሪዎች የተፈጠሩት በህዝባዊ ንቅናቄ ውስጥ ነው፡፡ ህወሓት በኢህአዴግ ስብሰባ ውስጥ አሳምኖና ተከራክሮ ውሳኔዎችን በትክክል እንዲወስኑ ያደርጋል ብሎ ከእንግዲህ ማሰብ በራሱ ቅዠት ይሆናል፡፡ ከአሁን በኋላ ኢህአዴግ እንደድርጅት በውልና በህግ እስካልፈረሰ ድረስ በድምፅ እየተሸነፈ እንደሚሄድ ግልጽ ነው፡፡ ለዚህም መዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡

 

ይሁን እንጂ በየአካባቢው እየታየ ያለው የህዝቡ ለህወሓትና ለዲሞክራሲያዊና ልማታዊ /ፌደራላዊ/ መስመር ድጋፍ በኢህአዴግ ውስጥ የበላይነት /የድምፅ/ ያለው ኃይል ነገሮች ወደ ድምፅ ውሳኔ ሳይሄዱ እያድበሰበሰ እንዲሄድ የሚያደርግበት ዕድልም እንዳለ መገንዘብ ያሻል፡፡ ስለዚህ የህወሓት /የወያነ/ አንበሶች ማተኮር ያለባቸው በአዳዲሶቹ የሚፈጠሩት ፌዴራላዊ የፓለቲካ ፓርቲዎችና በህዝቦች ውስጥ መሆን ይኖርበታል፡፡

 

4.     የትግል ጥሪ አስፈላጊነት

የትግራይ ህዝብ፣ የህውሓት ታጋዮችና ደጋፊዎች ህወሓትን ከገባበት አደጋ እንዲወጣ የፓለቲካ ሴፍትኔት በመሆን ታደገውታል፡፡ አከርካሪው ክፋኛ እንዳይሰበር አድርገውታል፡፡ ማዕከሉ ትግራይ አድርጎም የተበታተነው ሃይሉ አሰባስቦ ችግሮቹን ደረጃ በደረጃ እየፈታ አሁን ያለበት ቁመና እንዲይዝና በሌለች ኢትዮጵያውያን ዘንድም እንደ ዳግመኛ የተስፋ ብርሃን እንዲታይ አድርገዋል፡፡

 

በዚህ እልህ አስጨራሽ የፓለቲካ ትግል ውስጥ የትግራይ ወጣቶች በተለይ ደግሞ ዲጂታል ወያኔዎች፣ ወጣቶች፣ ታጋዮች፣ ሴቶች፣ ሚሊሻዎች የክልሉ የፀጥታ ኃይሎች ባለሃብቶች፣ሙሁራንና በዉጭ የሚኖሩ የክልሉ ተወላጆች የበኩላቸውን እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ታይተዋል፡፡ ይህ አሁንም በተደራጀ መልኩ መቀጠል ያለበት ነው፡፡

 

ይሁን እንጂ ከትግራይ ክልል መብራት የጀመረው የህብረቀለም ጮራ /Spectrum/ አብዮትና ተስፋ ሌላ ተጨማሪ ነገሮችንም ይጠይቃል፡፡ ቅድም ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው የፓለቲካ ኃይሎች አሳላለፍ አዲስ ሊሆን እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡ ስለዚህ ህወሓት መሪ ድርጅትና ሌሎች አሁንም ተስፋ የጣሉበት ስለሆነ ሌሎች አዳዲስ የፓለቲካ ድርጅቶችን በመሣብ የስትራቴጂና የታክቲክ ግንባር ጥሪዎችን ለማድረግ በመስመሮቹ ዙርያ ግልጽ እንቅስቃሴ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡

 

ህወሓት 1970 ዎቹ መጨረሻና 1980ዎቹ መጀመሪያ ላይ “የትግል ጥሪ መፅሔቶችን” በመዘርጋት ከተለያዩ የኢትዮጵያ የፓለቲካ ኃይሎች ግንኙነትና ክርክር ማድረጉ ይታወሳል፡፡ አሁንም ቢሆን የፌደራሊስት ኃይሎችን ለማሰባሰብ ቢያንስ “የትግል ጥሪ” መፅሄቶች ያስፈልጉታል፡፡ ከአህአዴግ ልሳንና የህወሓት ልሳን ከሆኑት አብዮታዊ ዲሞክራሲያና ወይን በአሁኑ ጊዜ ይህንን ብስለት ያለው ርዕዮተ ኣለማዊ የመስመር ጥሪ መጠበቅ የዋህነትና ግብዝነት ይሆናል፡፡ ስለዚህ ህወሓት ይህንን ክፍተት ቶሎ ብሎ ከጊዜ ጋር መፍጠንና መዝጋት ይኖርበታል፡፡

 

ሌላው የላይኛው የድርጅቶች አመራር /ከፍተኛው ካድሬ/ ከፌስቡክ ውጪ ጥልቅ የርእዮተ ዓለም ብስለት የለውም፡፡ ስለዚህ የካድሬ /ቤቶቹም በተቻለ ፍጥነት ለዚሁ ለኃይሎቹ አዲስ አሰላለፍ አመቺ አድርጎ ማደራጀትና ወደ ሥራ ማስገባት ያስፈልጋል፡፡

 

የትግራይ ቴሌቭዥንና የድምፅ ወያኔ ቴሌቭዥን ካለፈው የተሻለ ቁመና ያላቸው ቢሆንም አሁንም ግን መድረኩ በሚጠይቀው መልክ እየተንቀሳቀሱ ናቸው ብሎ ማሰብ ስህተት ይሆናል፡፡ ከማህበራዊው ሚዲያ የተሻለ ጠለቅ ያለና ፓለቲካዊ ብስለት ያለው መልዕክት በማስተላለፍ በኩል ብዙ ይቀራቸዋል፡፡ ድወት ከትጥቅ ትግሉ አካሄድ ብዙ መማር ይችላል፤ ይገባዋልም፡፡ ለምርጫ የሚቀረን ጊዜ አጭር ስለሚሆን ከጊዜ ጋር መሮጥ ከምንም ጊዜ በላይ አስፈላጊ ይሆናል፡፡

 


Back to Front Page