|
ከሹማራ 2-28-19 zshumara@gmail.com
ባሁኑ ሰዓት የትግራይ ህዝብ በረጅም፥ መራራና ፈታኝ ህዝባዊ ትግል ተፈትነው እንደወርቅ ነጥረው የወጡ ውድ ጄኔራሎች ልጆቹን በመሰሪዎችና ትምክሕተኞች ተነጥቆ ጥልቅ ኃዘን ውስጥ ይገኛል፣ አሁንም በትምክህት ኃይሎች የሚቀጠፉ የውድ ልጆቹን አስከሬን እየተቀበለ ኃዘኑን ችሎ እንደ አባቶቹ፣ አያቶቹና ቅም አያቶቹ ይህችን አገር ለማዳን በትዕግስት እየተጓዘ ነው። በተቃራኒው ምን ግዜም የማይተኙለት ደመኛ ጠላቶቹ የሆኑት የትምክህት ኃይሎች መልካቸውን እየቀያየሩ በዚህ ህዝብ ላይ የስም ማጥፋትና የመከፋፈል መርዝ መርጨታቸውን ቀጥለዋል። የትግራይ ህዝብ፥ የብርቅየ ጀግና ልጆቹ የጄኔራል ሰዓረና የሜ/ጄኔራል ገዛኢ ድንገተኛ መስዋት ካደረሰበት ድንጋጤ በቅጡ ባልነቃበትና ባልተረጋጋበት ሁኔታ፥ ይህ “ወዳጅ” ነኝ ባዩ ጀኔራል አበባው በሟች ቤተሰቦችና በትግራይ ህዝብ የኃዘን ቁስል ላይ እንጨት ሰዷል። የእነዚህ የውድ የህዝብ ልጆች ቤተሰቦችና የትግራይ ህዝብ እጅግ በጣም ከባድ በሆነ ኃዘን ላይ ባሉበት ወቅት፥ እጅግ አስፀያፊና ከባህላዊ ስነ ምግባር ውጭ በሆነ መልኩ ርካሽ የፖለቲካ ነጥብ ለማስቆጠር ሲባል፣ ባልተገባ መድረክና ወቅት መርዘኛ ቃላቱን ረጭቷል። ጄኔራል አበባው በጄኔራል ሰዓረና ጄኔራል ገዛኢ የአስከሬን ሽኝት ሥነ ሥርዓት ላይ የተናገራቸው ቃላት፥ የጄኔራል ሰዓረን ስብእና፥ ጀግንነትና ስኬት ለመግለፅም ይሁን ኃዘንተኞችን ለማጽናናትና ለማበረታታት በፍጹም የማይጠቅሙ፣ በምንም ዓይነት መለኪያ አግባብነት የሌላቸውና ጊዜውንና ወቅቱን የማይመጥኑ ናቸው።
ይህ ሰው በአዲስ አበባ በሚሊየኔም አዳራሽ በተካሄደው የአስክሬን አሸኛኘት ሥነ ሥርዓት ላይ “,,,አንድ ነገር መናገር እፈልጋለሁ,,,,,የፈለገው ይፈንዳ,,,ይህ ለውጥ ከመጣ በኋላ ,,,,ሰዓረ አንደ ከሃዲ ተቆጠረ ፣ ኢትዮጵያዊነቱ አሳልፎ እንዲሰጥ ተጽእኖ ተደረገበት ,,,,,፣ የሚል በአልቧልታና በመንደር ወሬ ላይ የተመሠረተ አስነዋሪ ንግግር አድርጓል። እንደዚህ ዓይነቱ ንግግር የትምክህት ኃይሎች የትግራይን ህዝብ ለማሳቀቅና ነጥሎ ለመምታት፣ ብሎም የራሳቸውን የአገር ሻጭነትና ከሃዲነት ተግባራት በትግራይ ህዝብ ላይ ለማላከክ ከዐፄ ምኒሊክ ዘመን ጀምሮ ሲጠቀሙበት የነበረ ስልት ተቀጥላ ነው። ቀደም ሲል በነአፈ ቄሳር አፈወርቅ ገብረ እየሱስ፥ ተድላ ኃይሌ ወዘተ,,,፥ በኋላም በነፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም፥ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ፥ ሥዩም ተሾመ፥ ወዘተ,,, ለዘመናት በተከታታይ ሲካሄዱ የነበሩና አሁንም እየተካሄዱ ያሉ የትግራይን ህዝብ መለስተኛ ኢትዮጵያዊ (Less Ethiopian) አድርጎ የመሳል መሰሪ ትርክቶች አካል መሆኑንም በሚገባ መገንዘብ ያስፈልጋል። ጄኔራል አበባው “ይህ ለውጥ ከመጣ በኋላ ሰዓረ እንደ ከሃዲ ተቆጠረ” ሲል ምን ማለቱ ነው፥ ምን ዓይነት መልእክትስ ማስተላለፍ ፈልጎ ነው ብለን ብንጠይቅ ብዙም ሳንደክም ብቸኛው አመክኖያዊ ማብራሪያ (Logical explanation) ሆኖ የምናገኘው ፣ ጄኔራል ሰዓረ የጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹምነት በመቀበሉና ከጠ/ሚኒስትሩ ጋር ለመሥራት ፈቃደኛ በመሆኑ፥ በትግራይ እንደ ከሃዲ ተፈርጇል የሚል መሰሪ መልእክት ለማስተላለፍ ተፈልጎ እንደሆነ አያጠራጥርም። ይህ ግን ርካሽ ውሃ የማይቋጥር የፖለቲካ ቁማር ጨዋታ ሆኖ እናገኘዋለን። አሁንም በህወሓት በከፍተኛ የአመራር ደረጃ የሚገኙ ተጋሩ በሚኒስትርነትና በሌላ የመንግስት የሥራ ኃላፊነት እየሰሩ ባሉበት ሁኔታ፣ የትግራይ ህዝብ መሪዬ ናቸው ብሎ ያለበትን የመሰረተ ልማት ቸግሮች እንዲፈቱለት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ እያቀረበ ባለበት ሁኔታ (የአክሱም ሐወልት ጥገና ጥያቄ እንደ አብነት መጥቀስ ይቻላል)፥ ጄኔራል አበባው እንደዚህ ዓይነቱ አልቧልታ መንዛቱ ከላይ እንደተገለፀው ያው ትምክህተኞች የትግራይን ህዝብ ታሪክ ለማጠልሸት የሚጠቀሙበት የተለመደው መናኛ የስም ማጥፋት ዘመቻ ሆኖ እናገኘዋለን። ከዚህም ባለፈ ይህ የጄኔራል አበባው አባባል በቀጥታ ይሁን በተዘዋዋሪ “የቀድሞ የሀወሓት መሪዎች መቀሌ ሄደው መሸጉ” እየተባለ የሚነዛው እኩይ ፕሮፖጋንዳ አካልም ነው። በነገራችን ላይ እነዚህ መቀሌ መሸጉ የሚባሉት ሰዎች የመጀመሪያዎቹ የጠ/ሚ አብይ ከሥራ የማባረር ዘመቻ ሰለባዎች የሆኑ የህወሓት ነባር ታጋዮችንና ፣ እድሜያቸው ለጡረታ ያልደረሰና ከፍተኛ ብቃትና ችሎታ ያላቸው ግን ተጋሩ በመሆናቸው ብቻ ጠ/ሚኒስትሩ በሰጡት ቀጥተኛ ትእዛዝ ከሥራ የተገለሉ የጦር መኮንኖችን የሚያጠቃልል ሲሆን፣ እነዚህ ከሥራ የተገለሉ ተጋሩ የሚኖሩበትን ቦታ የመምረጥ ሙሉ መብታቸውን ተጠቅመው በፈለጉበት ቦታ እየኖሩ ይገኛሉ። የት መኖር እንዳለባቸውም ማንንም ማስፈቀድ አይጠበቅባቸውም። የትምክህት ኃይሎች ግን እያንዳንዷን የተጋሩ እንቅስቃሴና ሥራ አሉታዊ መልክ በመስጠት የትግራይን ህዝብ ለማሳቀቅና ለማጠልሸት ከሞመከር ቦዝነው ስለማያውቁ “መቀሌ የመሸጉ” እያሉ ጥዋትና ማታ እየቆዘሙ ይገኛሉ። ከሥራ የተገለሉ የሌላ ብሄር ተወላጅ ባለሥልጣናትን ባሕር ዳር፣ ጎንደር፣ አዳማ ወይም ሐዋሳ መሸጉ የማይሉበት ምክንያትም የትምክህት ኃይሎች ምንግዜም ቢሆን የጥቃት ዒላማቸው በትግራይ ህዝብ ላይ ያነጣጠረ በመሆኑ ነው። ሌላው “ ኢትዮጵያዊቱ አሳልፎ እንዲሰጥ ተጽእኖ ተደረገበት,,,” የሚለው የጄኔራል አበባው መርዛማ ንግግር ነው። ጄኔራል ሰዓረና ጓዶቹ የኢትዮጵያ ሥረ መሠረት ከሆነ ክልልና ህዝብ የተወለዱ፥ ለኢትዮጵያ ህዝቦች ነፃነትና እኩልነት እድሜ ልካቸው የታገሉና ለዚሁ ዓላማ ውድ ህይወታቸውን ለመስጠት የቆረጡ ታጋዮች ናቸው። ጄኔራል ሰዓረና አብሮ አደግ የትግል ጓዶቹ ለኢትዮጵያዊነት በተግባር የሚሰው፥ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረ ሰቦችና ህዝቦች መብታቸው ተከብሮ ኩሩ ኢትዮጵያውያን እንዲሆኑ የታገሉና ለአገራቸው ብልፅግና የሠሩና የሚሠሩ እንጂ እንደትምክህተኛ ሊሂቃን የወሬ ኢትዮጵያውን አይደሉም። ጄኔራል ሰዓረና አብሮ አደግ የትግል ጓዶቹ ኢትዮጵያን ካንገት በላይ እያሞካሹ በጎን ለገበያ የሚያቀርቧት አስመሳዮች አይደሉም። ለዚህም ነው የትግራይ ህዝብና መሪ ድርጅቱ ህወሓት በከፍተኛ የፌደራል መንግሥት ባለሥልጣናትም ጭምር እየደረሰባቸው ያለውን የማጥላላት ፕሮፖጋንዳና የስም ማጥፋት ዘመቻ ችለው በኢትዮጵያዊነታቸው ፀንተው እየተጓዙ የሚገኙት።
ጄኔራል አበባው፥ ጄኔራል ሰዓረ እንዲህ ዓይነት ተፅእኖ ይደርስበት እንደነበር ይነግረኝ ነበር ለማለትም ዳድቶታል። እንደእዚህ ዓይነት አወዛጋቢ የሆነ፥ ተናገረ የተባለው ሰው በእማኝነት ቀርቦ ማስተባበያም ሆነ ማረጋገጫም መስጠት በማይችልበት ሁኔታ፣ በሕይወት የሌለ ሰው ነግሮኛል ብሎ እንደዚህ ዓይነት ንግግር መናገር ኢሞራላዊ ነው። ለርካሽና መሰሪ የፕሮፖዳንዳ ጠቀሜታ ካልሆነ በስተቀር ለምንም የማይጠቅም እኩይ ተግባርም ነው። ጄኔራል አበባው በራሱ ተነሳሽነት ያቀደውን ወይንም በሌላ አካል የተሰጠውን ተልእኮ ለመፈጸም ሲል የጄኔራል ሰዓረንና የጄኔራል ገዛኢን የአስከሬን ሽኝት ፕሮግራም ለርካሽና መሰሪ ፕሮፖጋንዳ መድረክነት ተጠቅሞበታል። ይህ አስነዋሪ የጄኔራል አበባው ንግግር ምናልባትም፥ በነጄኔራል ሰዓረ አሟሟት ዙሪያ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለማደብዘዝና የትኩረት አቅጣጫ ለማስቀየር ሆን ተብሎ የተቀነባበረ ትወና ነው ብሎ አለማሰብም አይቻልም። ሆኖም ይህ የነጄኔራል አበባው ሴራ አልሠራም። የጄኔራል ሰዓረ የቀብር ሥነ ሥርዓት አዲስ አበባ ላይ በመፈጸም፣ ለዚሁ ለነጄኔራል አበባው የበሬ ወለደ ውሸትና መሰሪ ትርክት ማረጋገጫ እንዲሆን ተፈልጎ የነበረ ቢሆንም አልተሳካላቸውም። የትግራይ ህዝብ ጀግኖቼን እኔው ራሴ እቀብራቸዋለሁ ብሎ ከሊቅ እስከ ደቂቅ በነቂስ በመውጣት የልጆቹን አስከሬን በክብር ተቀብሎ፣ ለውሸት ትርከት ማጣፈጫነት የሚንጠባጠብ የአዞ እንባ ሳይሆን፥ ከጥልቅ ልባዊ ፍቅር የመነጨ እውነተኛና ትኩስ የፍቅር እንባ እያነባ በክብር የቀብር ሥነ ሥርዓታቸውን ፈጽሟል። ህዝባዊ ክብር አጎናፅፎም ሸኝቷቸዋል። በዚሁም የነጄኔራል አበባው መሰሪ ፕሮፖጋንዳ እና የውሸት ትርክትም እንደተወለደ ሞቶ እንዲቀበር አድርጎታል። በክብርና ሞገስ በክብር ላለፉት ጀግኖች! ፈጣሪ ነፍሳቸውን በገነት ያኑርልን
Back to Front Page |