Back to Front Page

አብይ ኖቤሉ ይገባዋል!።

አብይ ኖቤሉ ይገባዋል!

 

አልማዝ በዳኔ

ጥቅምት 2012

ከፍንፍኔ

 

ለምን ይሆን ብዙ ኢትዮጵያውያን የጠቅላይ ሚኒስተር የአብይ አህመድ ዓሊን የሰላም ኖቤል ሽልማት የሚቃወሙት? ኤርትራውያን ወንድሞቻችን ሳይቀሩ ለምን አጥብቀው ይቃወሙታል? ቅናት ወይስ ስላልገባቸው ነው? ከመቃወማቸው በፊትስ የተሸለሙበት ዋና ምክንያት ምን እንደሆነ አውቀው ነው ወይስ ሳያዉቁ ነው እየተቃወሙ ያሉት? ብለን ብንጠይቅ የተቃውሞው ምክንያት ሊገባን ይችላል።

እንደኔ አብይ አህመድ ዓሊ የሰላም ኖቤል ሽልማቱ ይገባዋል የሚል የግል እምነት አለኝ። ኖቤል ሽልማት ማንም የሚያገኘው ሽልማት አይደለም። ኖቤል ሽልማት ለማግኘት መወዳደር ይጠይቃል። ተወዳድረህ ማሸነፍ ይገባል። ተወዳድሮ ለማሸነፍ የመወዳደርያ መመዘኛ ነጥቦችን ማለፍ ወይም ማሟላት ይጠይቃል። ሰለዚህ ጠቅላይ ሚኒስትር አብቾ ይህን ከባድ መወዳደርያ ነጥብ አሟልተውና ተወዳድረው እንዳሸነፉ ትንሽም ጥርጣሬ የለኝም። ያሟሉዋቾው ዋና ዋና መመዘኛ ነጥቦችን ለአስረጅነት የሚከተሉት ናቸው፡፡

Videos From Around The World

) ኖቤል ሽልማት ለመሸለም ራስህን መሸጥ ይገባል።

አብይ አህመድ ዓሊ ኖቤል ሽልማት ያገኙት ይህን የመጀመርያውን የመወዳደርያ መመዝኛ ነጥብ በሚገባ አሟልተው ስለተገኙ ነው። አንዳርጋቸው ፅጌ እንዳረጋገጡት ስልጣን ከመያዛቸው ስድስት ዓመት በፊት የግንቦት ሰባት አባል እንደነበሩ ገልፀዋል። ከዛ በፊትም ብዙ ውስጥ አዋቂዎች አብይ የውጭ አገር የስለላ ድርጅት መልምላቸው ከግንቦት ስባት ጋር እንዲገናኙ ገዝተው እንዳስረከቡዋቸው በተደጋጋሚ ገልፀዋል። በተጨማሪም ቤተሰባቸውንም በሌላ ሽፋን ወደ አሜሪካ ዴንቨር ወስደው ቤት ተከራይተው ባለቤታቸውንም ቸርች ስራ አስቀጥረው እያኖሩ ነበር። ባለቤታቸው ኢትዮጵያን ለቀው መሄድ የማይፈልጉ የነበሩ ቢሆንም በሌላ ችግር ምክንያት ተለያይተው ቆይተዋል። ትዳሩም በዚህ እክል ፈርሶ ቆይቷል። ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስተር ሆኖው እንደተሾሙ በኢትዮጵያ የአሜሪካው አምባሳደር ማይክል ሽምግልና አማካኝነት ባለቤታቸው ወ/ሮ ዝናሽ ተጠርተው ለተቀዳሚ እመቤትነት በቁ። ራስህን መሸጥ ኖቤል ያሸልማል። ችክ የሚል ምንም አያገኝም።

) የተሰጠህን ተልእኮ በብቃት መፈፀም ኖቤል ያሸልማል።

አብይ አህመድ ዓሊ ከጌቶቻቸው የተሰጣቸውን ተልእኮ በሚገባ ፈፅመዋል። ሳይጠሩ አቤት ሳይላኩት ወዴት የሚሉት ጠቅላያችን ስልጣን ከተቆጣጠሩ በኃላ በውጭ ገዥዎቻቸው የታዘዙትን ሁሉ ከሚጠበቅባቸው ውጤት በላይና በአጭር ጊዜ አስመዝግበዋል። የኢህአዴግ ሊቀመንበር ሆነው የኢህአዴግን አሰራርና መርሆ ባልተከተለ በግላቸው ውሳኔ እየወሰኑ ጌቶቻቸውን አስደስተዋል። ኢህአዴግን እየወነጀሉ ፀረ-ህዝቦችንና አሸባሪዎችን ወንጀል እንዳልሰሩ አድርገው የታሰሩትን ፈተው፣ አስመራ የነበሩትን በክብር ተቀብለውና ካይሮ የነበሩትን በአውሮፕላናቸው ጭነው በመግባት ወያኔን ማናደድ ትልቅ ጀብድ መስለዋቸው ስርዓት ደረማምሰው አገር ለስርዓት አልበኝነት ዳረጉ። ሁሉንም እንወዳለን ብለው ግብፅንም ደመኛ የኢትዮጵያ ጠላት የሆነውን ኢሳያስን አሞካሹ፡፡ ለአገሩ የለፋውን መለስን አግላይ አድርገው ወቀሱ። ኢህአዴግን እና የኢትዮጵያ አለኝታ የሆኑ መስራያቤቶችን እንደ መከላከያ፣ ፌደራል ፖሊስ እና የድህንነትን መስራያቤቶችን ወንጅለው ሪፎርም በሚል አገራቸውን በቅንነት የገለገሉ በለሞያዎችና ሃላፊዎች የተሰገሰጉ ወያኔዎች ተብለው ተጠራረጉ። በቡዙ ድካም የተገነቡ ተkሞችንም ማፍረስ ተያያዙት። የውጭ ስለላ ድርጅቶች እንዳሻቸው የፀጥታ መስርያቤቶችን ገብተው እንዳሻቸው ፈነጩ፡፡ የአገሪትዋ ጥብቅ ሚስጥሮች እንዲያዩና እንዲበረብሩ በነፃ ዕድል ፈቀዱላቸው። ታድያ ይህ ስራ ኖቤል አያሸልምም!

) ሉአላዊነትን አሳልፎ መስጠት ኖቤል ያሸልማል።

የኤርትራና የኢትዮጵያ ግጭትን በሰላም የመፍታት እንቅስቃሴ የቆየ እንቅስቃሴ ነው። ጥናቱም ዕቅዱም የተጠናው አብይ አህመድ ስልጣን ከመያዛቸው በፊት ነበር። አብይ አህመድ የጨመሩት አንዳች ነገር የለም። ነገር ግን ወያኔ ከአዲስ አበባ አባረርኩት እሱ ነበር ሰላም እንዳይመጣ ዕንቅፋት የነበረው አሉ፡፡ በሁለቱም ወንድማማች አገሮች ዋናው የሰላም ዕንቅፋት የነበረውን ኢሳያስ አፈወርቅን ከተጠያቂነት አድነው ውሉ ያልታወቀ ስምምነት አደረጉ። ስምምነቱ ይዘቱ እስካሁን ማንም አያቀውም። ብቻ ደንበር አብረው ከፈቱ። ሲዘጋ ግን አብረው አልተገኙም። ኢሳያስ ዘጋው። የአብይ መንግስት ስለመዘጋቱ ምክንያት ምንም ሳይገልፅ ቆየ። ደሴ - መቐለ መንገድም ተዘግቶ መቼ ገለፀ። በኃላ በህዝብ ሲጠየቅ የተዘጋው መንገድ እየተሰራ ስለሆነ ነው ብሎ ምክንያት ሰጠ። አሁንም አልተከፈተም። የኢትዮጵያ ሉአላውነት ደንታውም አይደለም። ከግብፅ ጋር እያደረገው ያለው ግላዊ ግንኙነት እና ስምምነት ለዘመናት ተከብሮ የኖረው የአገራችን ሉአላዊነት የጣሰ ነው። ኢንጅነር ስመኘውን አስገድሎ/ገድሎ የኢትዮጵያ ህዝብ ግድቡን ለመስራት የነበረው የሞራል መነሳሳትና የእንጨርሰዋለን መንፈስ ኩፍኛ ጎዳው። በሶማልያ የነበረንን ፖሊሲ በሚፃረር መንገድ ከአረቦች የተሰጠው መመርያ በመከተሉ አሁን ኢትዮጵያ የነበራት ተቀባይነት በሞቃዲሾም በሪጅናል መስተዳደሮችም ዜሮ እንዲሆን አደረገው። የአረቦቹ ጣልቃ ገብነት በሶማሊያ ብቻ ሳይሆን በኤርትራም፣ በግብፅም፣ በሱዳንም ነው። የነበረው የኢትዮጵያ ሉአላዊነትና ጥቅም የሚያስጠብቅ ትቶ በፔትሮ ዶላር ተገዝቶ ዝብርቅርቁ እንዲወጣና ጥቅማችን አሳልፎ ሰጠ። ይህ አልበቃ ብሎ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ሪፎርም በሚል በውጭ በተሰጠው ዕቅድ መሰረት ቻይናዎችን ከምስራቅ አፍሪካ የማስወጣት ፕላንና ስኬታሙ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ የኢኮኖሚ ፖሊሲ መቀየር አቀደ:: ምንም እንከን የሌላቸውን የኢትዮጵያ ህዝብ ንብረት የሆኑትን አየር መንገዳችን፣ ቴሌኮሚኒኬሽን፣ የመንግስት ባንኮች፣ ባቡር መንገድና ሌሎችን ተቋማጥ ለውጭ ካምፓኒዎች ለመሸጥ በቁርጠኝነት የሚተጋውን ኖቤል ሽልማት አይገባውም ማለት ስለ ሽልማቱ መመዘኛ አለማወቅን ያሳያል።

) ሸላሚው ወይም ከሽላሚው በስተጀርባ ያለው ሃይል የእርካታ መጠን ያሸልማል።

ሀያላን አገሮች ሌሎች አገሮችን የሚቆጣጠሩበት ዘዴዎችና መሳርያዎች ብዙ ናቸው። በIMF፣ በWorld Bank፣ በUN፣ በNGOs፣ በሃይማኖት፣ በሚድያ እና . . . ወዘተ አድርገው ይቆጣጥራሉ። በነዚህ መንገዶች መቆጣጠር ሳይችሉ ሲቀሩ፣ አገሮች አፈንግጠው እምቢ ሲሉ፣ ሉአላዊነታችንን አናስደፍርም ብለው አሻፈረኝ ሲሉ፣ ቀኝ ገዥዎቹ ማዕቀብ ተጠቅመው ነፃ አገራት ላይ ችግር እንዲፈጠርባቸው ያደርጋሉ። ከውስጥም ተቃውሞና አመፅ እንዲፈጠር ያደርጋሉ። እነሱን የሚገለግሉ እንደ ጠቅላያችን ያሉ ሰዎች መርጠው ያዘጋጃሉ። የመለመልዋቸው እያዘዙና ከፍተኛ ብር እያፈሰሱ የመንግስትና የአስተዳደር ለውጥ እንዲመጣ ያደርጋሉ። አንዳንዴ ይሳካላቸዋል። አንዳንዴ ሳይሳካላቸው ይቀራል። በኢትዮጵያ ለረጅም ግዜ በተደጋጋሚ ሙከራ ሲያደርጉ ቆይተው አሁን ተሳክቶላቸዋል። ሰላም አገኙ። በአብይ አህመድ ዓሊ። ታድያ ለዚህ ላስደሰታቸው ሰው ቢሸልሙ እንዴት አይገባውም እንላለን። ይገባዋል እንጂ!

ሰለዚህ ራሳችን መመዘኛ እየፈጠርን አይገባውም ማለት ትክክል አይደለም። ነገር ግን

         ሦስት ሚልዮን የተፈናቀለ ህዝብ ያላት አገር የሚመራ መሪ እንዴት ኖቤል ይገባዋል?

         ጆኖሳይድ በሶማሊ፣ በኦሮሚያ፣ በቤንሻንጉልና በቅማንት የሚፈፅምባት አገር መሪ የኖቤል ሽልማት እንዴት ይታሰባል?

         ፖለቲካ እስረኞች ፈታሁ ያለ መንግስት በብዙ ሺ የሚቆጠሩ የኦሮሞ፣ የሶማሊ፣ የአማራ፣ የትግራይ፣ የሲዳማና የአፋር ተወላጆች በግል ቂም ሳይቀር የፖለቲካ እስረኞች ያደረገ መሪ ኖቤል ወይስ ኖ በል ነው የሚገባው?

         በብዙ ክልሎች በፓርላማ ያልፀደቀ፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ በግል የታወጀ አስቸካይ ጊዜ አዋጅ የምትተዳደር ሰላም የናፈቃት አገር የሚያስተዳደር መሪ ኖቤል ሽልማት አገኘ የሚል ዜና ለማመን እንቸገራለን።

         ልትፈርስና ልትበተን የደረሰች አገር መሪ የሰላም ኖቤል ሽልማት በማግኘቱ እንካን ደስ አለን ለማለት እንዴት ይቻላል?

የኢትዮ-ኤርትራ ሰላም ብቻውን ከሆነ መመዘኛው የት ነው ያለው ሰላም አሳዩን እያሉ የሁለቱም አገሮች ህዝቦች ይጠይቃሉ። መልስ ግን የለም፡፡ ለሽልማቱ መመዘኛ አውጪውና አወዳዳሪው መልማዩ ነው፡፡ የሸለመውም መልማዩ ነው፡፡ ሰለዚህ ከማያገባቹህ ጉዳይ ገብታቹህ አትፈትፍቱ። አይገባውም አትበሉ! ይገባዋ ያሉት እነሱ፡፡

እነሱ ደግሞ ባስቀመጡት መስፈርት እንጂ በናንተ በኢትዮጵያ ህዝቦች በተቀመጠ መስፈርት አይደለም የሸለሙት። ወርቁ፣ ገንዘቡና የሚሸልሙት እነሱ ስለሆኑ እኛ መመዘኛቸው ትተን በራሳችን መስፈርት እየሰፈርን ሽልማቱ አይገባውም አንበል። እኛ ማለት የምንችለው በራሳችን መስፈርት ሰፍረን መሪያችን መሆን አትችልምና ይብቃ! ውረድልን ማለት ብቻ ነው የምንችለው። ሰለዚህ የምንችለውን እናድርግ። አሜን።

 

Back to Front Page