Back to Front Page

ኪነት በኢትዮጵያ፡ መሪ ናት አገልጋይ፤ ህዝባዊ ናት ልሂቃዊ?

ኪነት በኢትዮጵያ፡ መሪ ናት አገልጋይ፤ ህዝባዊ ናት ልሂቃዊ?

 

ዮሃንስ አበራ (ዶር.) 5-26-19

 

የሰው ልጆች ከተፈጥሮ ጋር ያላቸውን ቁርኝት፤ እንዲሁም እርስ በርስ ያላቸውን ግንኙነት የሚገልፁት በዘፈን በድራማ በስነፅሁፍና በስእል አማካይነት ነው፡፡ ኪነት አሁን ያሉትንና በፊት የነበሩትን ግንኙነቶች መገለጫ ብቻ ሳትሆን ለወደፊትም ምን አይነት ግንኙነቶች ሊኖሩ እንደሚገባ የመምከር ሚናም ትጫወታለች፡፡ ስለዚህም ኪነት ያለውንና የነበረውን በማሳወቅ በማሞገስና በመተቸት እያዝናናች የማስተማር አገልግሎት ታበረክታለች፡፡ የኪነት ባለሙያ ማለት ከህብረተሰቡ ኋላ ኋላ ` የሚከተል ሳይሆን ነገሮች ቀድመው የሚከሰቱለት አርቆ ማየት የሚያስችል ከስልጠናና ከተፈጥሮ በተገኘ ጥበብ የተካነ ስለሆነ ህበረተሰቡን ወደ ቀና ጎዳና የመምራት ሃላፊነትም ተሸክሟል፡፡ በርግጥ ኪነት እንደየወከለችው ወይንም እንደተገኘችበት ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ መደብ የተለያየች ልትሆን ትችላለች፡፡ ተራው ህዝብና ልሂቃን የሚጋሯ ቸው ኪነታዊ እሴቶች እንዳሉ ሁሉ የየራሳቸው የሆነ የኪነት አለም የሚፈጥሩበት ሁኔታም አለ፡፡ ኪነት ያለሚድያ እጅ-እግር የላትም፡፡ ሚድያውን የሚቆጣጠረው ደግሞ የኢኮኖሚ ልሂቁ ስለሆነ፤ የኢኮኖሚ ልሂቁም ማየትና መስማት የሚፈልገው ስለራሱ ህይወት ብቻ ስለሆነ ሰፊው ህዝብ የማይመለከተውን ህይወት የሚያንፀባርቁ የኪነት ውጤቶችን እያየ ሲያድንቅና ሲመኝ ይኖራል፡፡ 

Videos From Around The World

ወደ ሃገራችን የኪነት እውነታ ስንመጣ ኪነት በኢትዮጵያ የተለያዩ መልኮች ጥቅም ላይ ሲውል ኖሯል፡፡ የጥንቱ መገለጫዎች የቤተእምነት ስእሎች ነገስታት ነክ ስነፅሁፎችና የአዝማሪ ሙገሳና ነቀፋ ነበሩ፡፡ እነዚህ ሁሉ አሁንም ያሉ ቢሆንም ድራማ ተጨምሮባቸውና በቴክኖሎጂ ተራቀው የየራሳቸው አለማት ሆነዋል፡፡ ዘመናዊነት የተላበሰ ኪነት የጀመረበት በንጉሱ ዘመን ፍቅርና ሃይማኖታዊ፤ ንጉሳዊና መስፍናዊ የሆኑ፤ እንዲሁም የሃገር ፍቅርን የሚያንፀባርቁ ዘፈኖች ስእሎችና ድራማዎች የነበሩት ያህል ማህበራዊ ህይወትን፤ ችግርና ደስታን፤ ሃብትና ድህነትን፤ ፍትህንና ነፃነትን በቀጥታም በተዘዋዋሪም የሚገልፁም ነበሩ፡፡ ሰአልያንና፤ በግል ከሚሰሩት ባመዛኙ አንጋሽ አወዳሽ ከሆኑት አዝማሪዎች በስተቀር አብዛኛዎቹ የኪነት ባለሙዎች የመንግስት ተቀጣሪ ደሞዝተኞች ነበሩ፡፡ ከአድማጭ ሽልማት በስተቀር ሌላ የገቢ ምንጭ ያልነበራቸው እነዛ የዛ ዘመን ከያንያን ሊተኩ የማይችሉ ድንቅ ኪነት ውጤቶችን አስረክበው አልፈዋል፡፡ በንጉሳዊ ስርአት የነበረው የፖለቲካ የንግግር ማእቀብ ሳይበግራቸው ከያንያኑ ሲደር ሷቸውና ሲዘፍኗቸው የነበሩት ድራማዎችና ዜማዎች ይዘታቸው ወደታች ወርደው የተራውን ህዝብ ኑሮ ብሶቱንና ምኞቱን የሚያነፀባርቁ ነበሩ፡፡ የዚህ ዘመን ኪነት የህዝብ ንብረት እንጂ ሸቀጥ ያልሆነበት ጊዜ ነበር፡፡ እነ በሃይሉ እሸቴ ስለጉቦ፡ ስለ ሴተኛ አዳሪነት ችግር በስሜት ተውጠው የሚዘፍኑበት ጊዜ ነበር፡፡

የወታደራዊው ሶሳሊስት አስተዳደር ዘመን ለኪነት ከርሰ መቃበር የተቆፈረበት ጊዜ ነበር፡፡ አድሃሪ ተብሎ የወደቀው የንጉሱ ስርአት አለምልሞት የቆየውን ህዝባዊ ኪነት በደርግ ዘመን ከጦር መሳሪያ ያላነሰ የህዝብ ማስፈራሪ ሆነ፡፡ የወጣቶችን በአደባባይና በየስርቻው መጨፍጨፍን አንደታላቅ ሃገራዊ ድል አድርጎ የሚስል ሆነ፡፡ ሙሉ በሙሉ በደርግ እጅ የወደቀው ኪነት ሁለት ተቃራኒ አገላለፆች ነበሩት፡-"ኪነት ለአብዮት"ና "ህዝባዊ ኪነት"። ህዝባዊ ላልነበረው አብዮት አማራጭ ቅፅል መጠቀሙ ቅራኔ ነበር፡፡ የኣስተዳደር መዋቅር ይመስል በኢትዮጵያ ውስጥ ኪነት ቡድን ያልነበረው የከተማና የገጠር ቀበሌ የነበረ አይመስለኝም፤ ከቀበሌ እስከ ከፍተኛ ወይንም ወረዳ ሁሉ መዋቅር ነበረው፡፡ ኪነት አበበ ሲባል አርቲስት ደበበ እሸቱ "ኪነት እንደ አሸን ፈላ" ያለውን ያስታውሰኛል፡፡ በትግል ወቅት የነበረውም ኪነት ባመዛኙ ስራዊቱን የሚየበረታታ ነበር፡፡ ለአስራ ሰባት አመታት የኢትዮጵያ ኪነት በበርሃም በከተማም በፖለቲካና በጦር ዘመቻ ውስጥ ተነክራ የህዝቡን ኑሮ፡ ብሶቱን ምኞቱን የምታንፀባርቅበት እድሉም፡ እቅሙም፤ ድፍረቱም አልነበራትም፡፡ የህዝብ መጎሳቆል ከአብዮትና ከትግል የበለጠ ሆኖ እንዳይታይ ጥረት ሲደረግ ነበር፡፡ ህዝቡ አብዮቱ ወይንም ትግሉ እስኪሳካ ድረስ ችግሩን ዋጥ አድርጓት እንዲቆይ በሚደረገው የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ኪነት ለአብዮትም ኪነት ለትግልም ሲሳተፉ ነበር፡፡ ለምሳሌ አንድ በትግል ወቀት የተዘፈነ የትግርኛ ዘፈን አለ፡፡ እንዲህ ይላል፡- "ድርቅ ያልፋል፤ ትግልንና መሪ ድርጅትን በድርቅ ሰበብ መርሳት ተገቢ አይደለም"፡፡ ይህ ስሜት አልባ የሆነ ዘፈን በቅርብ ቀን በቴሌቪዥን ቀርቦ አይቼዋለሁ፡፡ ድርቅ እንኳን ትግልን ፈጣሪን ሊያስረሳ ይችላል፡፡ የትግሉ መሪ መለስ ዜናዊ በድርቁ ጊዜ የተናገረውና የዚህ ዘፈን ይዘት ተቃራኒ ነው፡፡ መለስ "ህዝቤ ድርቅ ባስከተለው ረሃብ እያለቀ ነው፤ ለማን ነው የምታገለው"  ሲል፡ ዘፈኑ ደግሞ ድርቅን ችለህ ታገል ብሎ ይመክራል፡፡ ኪነት እንዲህ ዉሉ እንደጠፋባት ደርግ ወድቆ ኢህአዲግ የሚመራው መንግስት ተመሰረተ፡፡

ይህ አዲስ ዘመን ኪነት ከከፍተኛ ቁጥጥር ወደ ስርአት አልባ የገበያ ውድድር ከጫፍ ወደ ጫፍ የዘለለችበት ዘመን ነው፡፡ ላለፉት ሁለት አስርት አመታት ድራማና ሙዚቃ እንደ ማንኛውም ሸቀጥ በገበያ ጥናት የሚመረት ይመስላል፡፡ አንድ አይነት ደረጃ ያለው ሳሙና ወይንም ውሃ የሚያመርቱ ፋበሪካዎች ለማስታወቂያ በሚመረጡ ሴቶች የፈገግታ ድምቀት ምርታቸውን እንደሚያወዳድሩ ሁሉ በተለይ በየጊዜው የሚለቀቁት የአማርኛና የትግርኛ ዘፈኖች ተመሳሳይነት ለማለባበስ የሚሞከረው በሌለ ስፖርታዊ የስክሰታ ቄንጥና እንደህግ የተደነገገ ይመስል ከሁሉም ዘፈን ክሊፖች የማይጠፉት ሴቶች ውበት ነው፡፡ አሁን አሁን የዘፈን ክሊፖች ውስጥ የሚታየው ነገር ከስፊው ህዝብ እውነታ የራቀ፤ ጥቂት ባለፀጎች የሚቀማጠሉበትን ሕይወት የሚያንፀባርቅ እየሆነ ነው፡፡ በክሊፖቹ ባመዛኙ የቅንጦት ህይወት ያሳዩና አልፎ አልፎ ከላያቸው ላይ ልብሳቸው የረገፈ የተጎሳቆሉ ሰዎች እስክስታ ሲወረዱ ብልጭ እያደረጉ ማሳየት የተለመደ ሆኗል። የዚህ መልእክቱ አብዝሃዎቹን አናሳ አስመስሎ ከማቅረብና ባለፀጋ ደምበኞቻቸውን ከማሳቅ የዘለለ ጥቅም የለውም፡፡ ዘፈኖችና ክሊፖቻቸው ጥበብን ተላብሰው፤ የህዝቡን እውነተኛ ህይወት አሳይተውና ወደጋራ መልካም እሴት መርተው የሚሻያግሩ ሳይሆኑ ሁሉንም ለማስድስት ሲጥሩ የዘፈኖችን ለዛ የሚያጠፉ ናቸው፡፡ አገሩ ሳይነሳለት የቀረ እንዳያኮርፍ አየተባለ ዘፈኑ ለዛው እስኪያጣ ድረስ የአውራጃና የወረዳ ስም ዝርዝር "ይነበባል"፡፡ አገራችን ከፍተኛ በሆነ ማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊና፤ ፖለቲካዊ ችግር ውስጥ ተነክራ እያለ የኢትዮጵያ ኪነት የየክልል የበላይነትነን በማንፀባረቅ የፖለቲካን ልዩነት በማስፋት ላይ ከመጠመድዋ ሌላ ያለ ፍቅር ዘፈን ሌላ ግጥም የሚገጥምላት አጥታ የተቸገረች ትመስላለች፡፡ ኪነት በአሁኑ ጊዜ ለኢትዮጵያ እውነታ ባእድ ሆናለች፡፡

በትግርኛ ዘፈኖች ላይ ያለው የክሊፕ ስራ ግን ቅጥ ያጣ ይመስላል፡፡ የአንድ ብሄር ባህላዊ ዘፈንና አጃቢ ምስሉ ማንፀባረቅ ያለበት የአብዛኛውን የብሄሩን ህዝብ አኗኗርን ነው፡፡ በተለየ አሳሳች መነፅር እያየነው ወይንም በተለየ ካሜራ እያነሳነው ካልሆነ በስተቀር በትግርኛ ዘፈኖች ክሊፖች ላይ የሚታዩት ሴቶችና ወንዶች ከሰማየ ሰማያት የወረዱ መላእክት እንጂ ሁላችንም የምናውቃቸው እናቶቻችንና እህቶቻችን የሚወክሉ አይደሉም፡፡ መቸም አምለሰት ሙጬ የፋሽን ትርኢት የምታሳይበት ልብስ ለብሳ አባ አለም ለምኔ (ሰብለ) ሆና ብትሰራ ኖሮ ታሪኩን ለሚያውቅ ሰው አስቂኝ ይሆን ነበር፡፡ የዘፈን ክሊፕ ማለት ገፀባህርይ ውከላ ነው እንጂ የሌለ ነገር ለገበያ ተብሎ አይፈጠርም፡፡ በርግጥ የትግርኛ ዘፈን ድርሰትና ቅንብር ባመዛኙ ቅጥ ያጣ ወጪ በሚወጣበት የሰርግ ድግስ የሚመራ ይመስላል፡፡ ይህ ቅጥ ያጣ አርቲፊሻልነት በትግራይ የባህል አለባበስ፤ ፀጉር አሰራር መኳኳልና የወርቁ ጌጥ ክብደት ታሪክ ያልተለመደ ነው፡፡ እያስከተለ ያለው ማህበራዊ ችግርም ቀላል አይደለም፡፡ የዚህ አለቅጥ መሽሞንሞን ወጪው ከፍተኛ ስለሆነ በቪድዮ ይህን ያዩ እማወራዎች የትዳር ጓደኞቻቸውን ኪስ ማጎድጎዳቸው አልቀረም፡፡ ለልጆቻቸው ሰርግ ስጦታ ሰባት ፎቅ ከሚስሩት ስዎች ጋር መወዳደር ጉዳት አለው፡፡ ሓብታሙም ይኑር ድሃውም ከድህነት ይውጣ፡፡ ኪነት ግን የሁሉንም ኑሮ ታንፀባርቅ፡ እንጂ ባህልን እንደሸቀጥ አትቸርችረው፡፡

Back to Front Page