Back to Front Page

የአብዱራህማን "ወያኔ ይሁኑ"

 

የአብዱራህማን "ወያኔ ይሁኑ"

ዶር. ዮሃንስ አበራ አየለ

3-18-19

 

ናትናዔልን ጠቅሰው ጠቅላይ ሚንስትሩን ለስድስት ወር ወያኔ ይሁኑ ፣ ማለት "የሚታሰረውን አስረው፣ የሚገረፈውን ገርፈው፣ እንደ ወያኔ ፀጥ ለጥ አድርገው ያስተዳድሩ" ብለው ያሳሰቡበት ፅሁፍ ሳነብ የአሁኒቱ ኢትዮጵያ ፓለቲከኞች ነገር ይብስ አደናጋሪ ሆነብኝ። ለመሆኑ ትናንት የተናገሩትና ዛሬ የሚናገሩት ቅራኔ ስለመኖሩ ግንዛቤ እየወሰዱ ስላልሆነ ነው ወይስ እኛ የምንናገረው ሁሉ ተምታታም አልተምታታም ዩኒቨርሳል ሃቅ ነው የሚል የፍፁምነት ቆዳ ስለለበሱ ነው?

Videos From Around The World

እየሱስ ድጋሚ ወደ ምድር የመጣ እስኪመስል ድረስ ለጥቂት ወራት ሰፍኖ የቆየው ፌስታ በስጋትና ለቅሶ ሲቀየር "ካፈርኩ አይመልሰኝ"፣ እውነታውን ማመን መሞት ያህል ሆኖ ነው እንጂ የበፊቱን አስተዳደር መናፈቅ ከተጀመረ ሰነባብቷል። እውነት ብለዋል፣ ማለቴ "ወያኔ ይሁኑ" ማለትዎ። ሰይጣን አሳስቷቸው ተውት እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወያኔ ነበሩኮ! የነበረውን ስርአት በማስተካከል ማስቀጠል ይችሉ ነበር። በመንግስታት መቀያየር ምክንያት እድሜ ልኩን ከዜሮ ሲጀምር የኖረው የኢትዮጵያ ህዝብ እንደገና ሌላ ዜሮ ብቻ ሳይሆን ከዜሮ በታች እንዳይጀምር ማድረግ ነበረባቸው። የ27 አመት ጨለማ በብርሃን ተካነው ሲባል ብርሃን የሆነው የአብሪ ጥይት እሳት ነውን? ብርሃን ማለት በወያኔ ዘመን ረስተነው የኖርነውን የርሃብ እልቂት ፎቶ ማየት ነውን? ከጨለማ መውጣት ማለት በዲሞክራሲና በነፃነት ስም የህዝብ ዲሞክራሲያዊ መብትና ነፃነት ገፈው ሽብር ያነገሱ፣ ከመንግስት አቅም በላይ የሆኑ፣ የወጣት ቡድኖችና የጎበዝ አለቆች እንደልብ እንዲንቀሳቀሱ መፍቀድ (መተው) ነውን? የመሪዎች ወይንም በውጩ አለም አድናቆት ያገኘው ለውጥ ገመናው እንዳይጋለጥ ማለባበስ ነውን? የውጭ ገፅታ እንዳይበላሽ አገር ውስጥ ያለውን የመፈናቀልና የርሃብ ችግር ደብቆ መያዝ ነውን?

"ከበሮ ሲያዩት ያምር ሲይዙት ይደናገር" የተባለው ለከበሮ አይደለም ለፓለቲካ እንጂ። አዲስ መሪዎች ወደ ስልጣን ከመውጣታቸው በፊት የችግሮች ሁሉ መፍትሄ የሚሆን ታአምራዊ ዘዴ በእጃቸው የጨበጡ ይመስላቸዋል። የጭፍን ደጋፊዎቻቸው ግፊትና አይዞህ ባይነት ሲጨመርበት መሪዎቹ አይነህሊናቸው ይጨፈንና ተአምር ሰሪዎች የሆኑ ያህል ሆነው ይሰማቸዋል። ከነሱ በፊት የነበረው ገዳይ እነሱ አዳኝ፣ በፊት የነበረው አሳሪ እነሱ ፈቺ፣ በፊት የነበረው ገራፊ እነሱ አቃፊ እንደሆኑ ይሰማቸዋል። እዚህ ላይ አንድ የዘነጉት ጥያቄ አለ። ይህ ጥያቄ እንዲህ ነው፦ ለምንድን ነው የበፊቱ መንግስት እነዚህን ድርጊቶች ሲፈፅም የነበረው? ሲወለዱ ግፈኞች ሆነው ስለተፈጠሩ ነው? አይደለም! ስልጣን መያዝ ቀላል ባይሆንም ይዞ ማቆየቱ ግን እጅግ በጣም የከበደ ነው። ስልጣን ይዞ ማቆየት የሚከብደው የስልጣን ተቀናቃኙ ባመዛኙ መያዣ ጀሮ ሳይኖረው እንደተጣደ ድስት ስለሚሆን ነው። መያዣ ጀሮ ሳይኖረው የተጣደ ድስት በታችም፣ በላይም በጎንም ቢይዙት ያቃጥላል። ስለዚህ ወጡ እንዳይቃጠል በመስጋት ጊዜ ስለሚያጥር ትእግስት ያልቅና ድስቱን እንዲሁ ለማውረድ ሲሞከር ድስቱ ወድቆ እንክትክቱ ይወጣል። ወጥ አብሳዩ ድስቱን ለመስበር ፍላጎት የለውም፤ ግን ደግሞ ድስቱ ጀሮ ከሌለውና ወጡ ሊቃጠል ከሆነ ያኔ እርምጃው የደመነፍስ ጉዳይ ይሆናል። ይህ የሁሉም መንግስት እጣ ነው። ማንም የፈለገ ቢል ውሎ አድሮ ወደዛ መግባቱ ሳይታለም የተፈታ ነው።

"ያልተነካ ግልግል ያውቃል" አሉ። በአራተኛው ምእተአመት ቅድመ ክርስቶስ ዳዮኒስየስ ሁለተኛ የሲሲሊዋ ሳይራኩስ ንጉስ ነበር። ዳሞክሊስ የሚባል ከመኳንንቶቹ አንዱ ንጉሱ የሚኖረውን የምቾች ኑሮ እያነሳ ይነዘንዘው ነበር። ይህ ንዝንዝ የመረረው ንጉስ ዙፋኑ ምቾች ብቻ ሳይሆን መከራም እንደሆነ ለዚህ ሰውየ ግልፅ ማድረግ ፈለገ። በተግባር ካላየ በቃላት ብቻ እንደማይገባውም ግንዛቤ ወሰደ። ንጉሱ ባለሟሉን ይጠራና ለአንድ ቀን ዙፋኑ ላይ ተቀምጦ ንጉስ እንዲሆን ይጠይቀውና ለአንድ ቀንም ቢሆን አለሜን ልቅጭ ብሎ አሰበና በደስታ የንጉሱን ሃሳብ ተቀበለ። ይህ ጉጉ ባለሟል ዙፋኑ ላይ ተቀምጦ መዝናናት ሲጀምር ንጉሱ በአናቱ ልክ በእጀታው ጣርያው ላይ በአዲት ነጠላ የፈረስ ጭራ ፀጉር የታሰረውን ሰይፍ አሳየው። የአንድ ቀኑ ንጉስ አንድ ሰአትም መቆየት አልሆነለትም። አሁን አሁን ፀጉሯ ተበጥሳ ሰይፉ አናቴን ይበረቅሰኛል ብሎ ሲሳቀቅ ቆየና ይቅርብኝ ብሎ ከዙፋኑ ወረደ። ከዛ በኋላም ለንጉሱ አዘነለት። እንደመተቸት የሚቀል ስራ የለም።

ህወሓት ከደርግ የተቀበለችው አሁን ካለው ህዝብ ብዛት ግማሹን ያህል ነው። ህዝቡ ሰላሙን ስላጣጣመውና ልጆቹ ውለው በሰላም ሲገቡለት ወለደ ተዋለደ ኢትዮጵያን በወጣት ሞላት፤ ብሄራዊ ውትድርና በማይሄድ ወጣት፣ በገፍ ወደ 40 ዩኒቨርሲቲ የሚገባ ወጣት፤ በዛ መጠን ስራ የሚፈጥር ሳይሆን ከመንግስት ስራ የሚፈልግ ወጣት። የህወሓት ፈተና ቀደምቶቹ መንግስታት ከገጠማቸው ፈተና በብዙ እጥፍ የከበደ ነበር። የህወሓት አስተዳደር መነፃፀር ያለበት ወደፊት እንጂ ወደኋላ አይደለም። ያለፉት ሁለቱ መንግስታት የህወሓት መንግስት ያልተሳካለትን እነሱ ያሳኩት ነበረ ብሎ ማሰብ ከየዋህነት ካለፈ ናፍቆት ብቻ ነው የሚሆነው። ህዝብን በጦርነት ስሜት ወጥረህ መግዛትና ሰላም አድርገህ የሁሉም እየጨመረ የመጣውን ፍላጎት ማሟላት መቻል አንድ አይነት አይደሉም። የኋላው ከበፊቱ የበለጠ አስተዋይነት፣ ነገር የመሸከም ችሎታ፣ የነፃ ትችት ሁካታ የማስተናገድ ትእግስት ይጠይቃል። የሰላም ሁኔታን ከማስተዳደር የጦርነት ሁኔታን ማስተዳደር ይቀላል። ህወሓት የገጠመው ፈተናም ራሱ የፈጠረውን ሰላም ማስተዳደር ነበር።

ከይቅርታ ጋር ኢህአዲግ ሳይሆን ህወሓት የምለው ለ27 አመታት አገሪቱን ያስተዳደረው ህወሓት ነው ብለው ሶስቱም አባል ፓርቲዎች ስላሳወቁ (ስለካዱ) ነው። እንግዲህ የህወሓት መጥፎውን ብቻ ሳይሆን በጎ ስራውንም ጭምር ጠቅልሎ ለራሱ ይይዛል። ጌታቸው ረዳ እንዳለው ምርጥ ምርጡን ለኛ ብቻ ግርድ ግርዱን የህወሃት ብቻ ማለት አይቻልም።

አብዱራህማን ጠቅላይ ሚኑስትሩን "ወያኔ ይሁኑ" ብለው ሲመክሩ ከወያኔነት ትክክለኛ ትርጉም ለቀው ባልሆነ የጢሻ መንገድ የሄዱ ይመስለኛል። ወያኔነትን የቀረፁት አሳሪ፣ ገዳይ፣ ደብዳቢ አድርገው ነው። ያስቀመጧቸው ሶስት ነጠብጣቦች ነበሩ (...)። ነጠብጣቦቹ ወዘተ ለማለት ነው ወይስ ሌሎች ሊጠቅሷቸው ያልፈለጉ የወያኔ ባህርያትን ለማመልከት ነው። ወዘተ ለማለት ከሆነ ይገባኛል ወያኔን ገዳይ፣ አንቀጥቅጦ ገዢ፣ አሳሪ፣ ደብዳቢ ማለቱ አላረካዎ ሲል ግን ደግሞ ሌሎች የሚያደሙ ቃላት ፍለጋ ስለታከተዎ ያስቀመጧቸው ነጠብጣቦች ይሆናሉ። ምናልባት ነጠብጣቦቹ ከላይ እንደገለፅኩት የወያኔን በጎ ምግባራት መግለፁ፣ የፓለቲካ ተቀባይነቶን የሚነካ መስሎዎት ከፈሩ እረዳልዎታለሁ። ህሊና እንደ ግሉኮስ በመርፌ አይወጋም። ዶማን አካፋ ሳይሆን ዶማ የማለት ድፍረት ሊኖር ይገባል። ከእርሶ የበለጠ፣ ምናልባትም ከሁላችን የበለጠ፣ የወያኔን በጎ ስራዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳምረው ያውቁታል። ወያኔ ይሁኑ ብለው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሃሳብ ሲያቀርቡ ክፉ ክፉ ተግባሮችን መርጠው ነው የመከሯቸው። ይህ መልካም ነገር አይደለም። ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሊያዝንብዎ ይችላሉ።

መምከር የነበረብዎ ወያኔ የህዝቡን ሰላም ለመጠበቅ፣ እንደበፊቱ በረሃብ እንዳያልቅ ለማድረግ፣ የችግሮች ምንጭ የሆነውን ድህነትን መንግሎ ለመጣል፣ በከፍተኛ ጥበብና የሃገር ፍቅር የተካነ የሃገር ህልውና ጥበቃ፣ ከውጭ መንግስታት ጣልቃ ገብነት ነፃ የሆነች አገር ለመፍጠር፣ ከቀደሙት ለመድረስና የሃገር ስም ለማስጠራት የተከናወነው የኢኮኖሚ እድገት ላይ ያከናወናቸው ታሪካዊ ተግባራትን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ነበር። ጥቂት ግለሰቦች የፈፀሟቸውን መጥፎ ተግባራት የወያኔነት የመዝገበ ቃላት ትርጉም አድርገው ማቅረብ አልነበረቦትም።

ወያኔነት ብዙ ሰዎች ከሚያስቡት ተቃራኒ ትርጉም ያለው ነው። ይህን ያህል በመረረ ጥላቻ የሚነሳው ወያኔነት ትርጉሙም አመጣጡም የግፍ አግዛዝን እምቢ ማለት ነው። እንዲያውም ከተፈለገ መባል የነበረበት ህወሓት ወያኔ ሊሆን አልቻለም ነው። ስሙን የተከሉት የመጀመሪያዎቹ ወያኔዎች ገበሬዎች ነበሩ። ቀረጥ በዛብን፣ የግፍ አገዛዝ መረረን ብለው ነበር የተነሱት። ስለዚህ ወያኔነት ፍትህ መፈለግ ማለት ነው። ይህ ማለት በቢልዮኖች የሚቆጠረው የአለም ህዝብ ፍትህ ፈላጊ ነውና ወያኔ ነው። ወያኔ ማለት በማእከላዊ ምርመራ ድርጅት ውስጥ ቢሮ ዘግቶ እስረኛ የሚደበድብ አይደለም። እሱ ወያኔን የካደ ነው። ለምን ሲባል ለፍትህ ሲታገሉ የነበሩ የህወሓትና የኢህአፓ አባላት ሲደበደቡና ሲገደሉ የነበሩት እዚሁ ቤት ነበር። ወያኔ የታገለው ይህ እንዳይደገም ነው። በሰማይ ቤትም እኮ የተበላሹ መላእክት ወደ ምድር ተወርውረዋል። ይህ ማለት መልአክነት ብልሹነት ማለት አይደለም።

እኔን የሚያሳዝነኝ የተማሩትም ያልተማሩትም ስሜት እየነዳቸው ሁሉም መደንቆራቸው ነው። ጨፍጫፊ አንቀጥቃጭ መሆንና ጠበቅ ማለት አንድ አይነት አይደሉም። ወያኔ ጥብቅ እንደነበረ አይካድም። 100 ሚልዮን ህዝብ ለመጠበቅ በጥቂት በጥባጮች ላይ እርምጃ መውሰድ ጨፍጫፊነት አይደለም። ደካማና የህዝብ አላማ የሌለው መንግስት ብቻ ነው የጥቂቶችን መብት አስከብራለሁ ሲል ብዙሃኑን ለአደጋ የሚያጋልጠው። ትክክለኛ ስልጣን ማለት በቀረበ አስቸጋሪ ምርጫ ላይ በቆራጥነት መወሰን ማለት ነው። ሁሉንም ለማስደሰት የሚሞክር መሪ ውድቀቱ ከዛ ይጀምራል።

ቀጥሎ የምለው ነገር ለራሴም ይዘገንነኛል፣ ግን የሚመር ሃቅ ነው። በጓንታናሞና በአቡ ግሬብ እስር ቤቶች በተፈፀመው ሰቆቃ ከስልጣን የወረደ የታላቋ አሜሪካ ፕሬዚደንት የለም። አሜሪካውያን በድርጊቱ እያለቀሱና እየጮሁ ያስቀደሙት ግን ሰላምና ደህንነታቸው መጠበቁ ነው። እኔ የሚታየኝ መፍትሄ እስከ ምርጫ ድረስ የሃገር ህልውናና የህዝብ ሰላማዊ ኑሮ በማስቀደም ከህወሓት ጋር እርቅና ሰላም ተፈጥሮ በጋራ መስራት ቢሞከር ነው። ለጠቅላይ ሚኒስትሩም ከታላቅ አክብሮት ጋር አገር የሌለው የኖቤል ሎውሬት ለመሆን ባይሞክሩ እላለሁ። ሰላም ማምጣት በአፍሪቃ ቀንድ ሳይሆን በኢትዮጵያ ውስጥ ነው። ኢትዮጵያን ሰላም በማድረግዎ ፈረንጆች ልማዳቸው ነውና ቢያኮርፉ እኛው የበለጠ የታሪክ ሽልማት እንሰጥዎታለን።

 

Back to Front Page