Back to Front Page

ሃሳብ ልዕልና መወዳደር ጥሩ፣ ግን ምንጩ ምንድ ነው? እንዴትስ ይረጋገጣል?

 ሃሳብ ልዕልና መወዳደር ጥሩ፣ ግን ምንጩ ምንድ ነው? እንዴትስ ይረጋገጣል? 

ኢዮብ አብርሃም  (ከ VOR (Voices of Reason) 11-2-19

 ባሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ በስፋት ከሚነሱ ጉዳዮች አንዱ “የሃሳብ ልዕልና” የያዘ ያሸንፋል የሚል ይገኝበታል። የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር አብይ አህመድ ደጋግመው ያነሱታል። እሳቸውን ተከትለው ደግሞ ሚድያን ጨምሮ ሌሎች ብዙ ሰዎችም ባያብራሩትም ይጠቅሱታል። 

የ ”ሃሳብ ልዕልና” ሲባል ታድያ ምን ማለት ነው? ሃሳብ ራሱስ ከየት ይመጣል? ጠለቅ ወዳለ ፊሎሶፉያዊ ወይም አካዳሚያዊ ትንተና ሳንገባ በቀላሉ “ሃሳብ” በሰው ልጆች አእምሮ ተቀርፆ እየሰፋና እያደገ የሚሄደው ሰዎች ከተፈጥሮው አለምና በማህበራዊው አለም ውስጥ ከሚያካሂዱት መስተጋብር ጋር በተያያዘ ነው። በመሆኑም ከዚህ ሁኔታ ውጭ ከባዶ የሚመጣና የሚያድግ አይደለም ማለት ነው።

በማህበራዊ እንቅስቃሴ በተለይ ደግሞ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ውድድር ጋር ተያይዞ የሃሳብ ልእልና ሲባልም አንድ ሃሳብ በአንድ ጉዳይ ላይ ተመስርቶ በዝያው ጉዳይ ላይ ከተመስረቱ ሌሎች ሃሳቦች ጋር ሲወዳደር ያለው ብልጫ ወይም ትክክለኛነት የሚያመላክት ነው ብለን መውሰድ እንችላለን።

እዚህ ላይ የአንድ ፖለቲካ ፓርቲ አቅዋም ወይም ሃሳብ ትክክለኛነቱ ወይም ከሌሎች ሃሳቦች ጋር ሲነፃፀር የሚኖረው ልዕልና በምን ይረጋገጣል የሚል ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ይሆናል። በሳይንሳዊ መንገድ ጉዳዩን ስናየው በማህበራዊ ሳይንስ ላይ የተመሰረቱ ሃሳቦች ትክክለኛነት እንደ ተፈጥሮ ሳይንስ በቤተ ሙከራ ውጤቶች ላይ ተመስርቶ የሚረጋገጥ አይደለም።

ታድያ በአንድ ሃገር የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚወክሉትን የህብረተ ሰብ ክፍል ጥቅም መሰረት በማድረግ ተደራጅተው ሲንቀሳቀሱና እርስ በርስ ሲነፃፀሩ የአንድ የፖለቲካ ፓርቲ ሀሳብና አቅዋም ልእልና ወይም ትክክለኛነት በምን ይረጋገጣል?

ወደ አንድ የተጠናከረ መድብለ ፓርቲ ስርአት ይሸጋገራል ተብሎ ተሰፋ በሚደረግበት ሃገር  ላይ የሚያራምዱት ሃሳብ ወይም አቅዋም ምን ይሁን ምን የብዙ ፓርቲዎች ወይም የፖለቲካ ቡድኖች በፌዴራል/ሃገር ይሁን በክልል ደረጃ መኖርና በነፃ መንቀሳቀስ ዲምክራሲን ከማስፋትና ለህዝቡ ኣማራጮችን ከማቅረብ አንፃር ወሳኝ ጉዳይ እንደሆነ ግልፅ ነው። መድብለ ፓርቲ የተባለውም ለዚሁ ነው። የዚህ ተቃራኒ አካሄድ ሚድያን ጨምሮ የሚመሪትን የመንግስት መዋቅር በመቆጣጠር የኔ ሃሳብ ወይም የፖለቲካ ፕሮገራም ብቻ ነው ትክክል በማለት መንቀሳቀስና በልዩ ልዩ መንገድ ተፅእኖ መፍጠር የህግ የበላይነትን ያለማክበርና ዲሞክራሲያዊ የፖለቲካ ውድድር ጨዋታን መጣስና ማፈን ይሆናል።

የፖለቲካ ፓርቲዎችና ቡድኖች በሂደት እየተጣመሩና አንዳንዶችም እየከሰሙ እንደሚሄዱ ይታወቃል። የፖለቲካ ፓርቲዎች ያላቸውን ሃሳብ፣ አቅዋም መስረት በማድረግ የፓርቲያቸውን ፕሮገራም/ዝርዘር ማኒፌስቶ በመቅረፅ ለመራጩ ህዝብ ያቀርባሉ። ሚድያን ጨምሮ በልዩ ልዩ  መድረኮች ክርክር በማካሄድ እያንዳንዱ ፓርቲ የሱ ፕሮግራም የላቀና ከሌሎቹ ጋር ሲነፃፀር “ልእልና” ያለው መሆኑን ያስረዳል። ምረጡኝ እያለም ይቀሰቅሳል። ውሳኔው የመራጩ ህዝብ ይሆናል። መራጩ ህዝብ ላንዱ ፓርቲ ድጋፉን የሚሰጠው የፓርቲው ፕሮግራም መብቴን ያስከብርልኛል፣ ጥቅሜን ያስጠብቅልኛል፣ ችግሬን ይፈታልኛል … ወዘተ በማለት በማነፃፀር ይሆናል።

Back to Front Page

የመራጩን ውሳኔ ማክበርና መቀበል የፖለቲካ ፓርቲዎች ግዴታ ይሆናል። ከዲምክራሲ ስርአት ግንባታ ሂደት አንፃርም ወሳኝ ሚና ይኖረዋል።  ለፖለቲካ ፓርቲዎች ፕሮገራም መሰረት የሚሆነው “ሃሳብ” ልእልናው የሚረጋገጠውም በዚህና በዚህ መንገድ ብቻ ይሆናል። ይህ ትክክለኛ የዲሞክራሲ መንገድ ነው። የፈለገው ምክንያት ይቅረብ ይህን ስርአትና አካሄድ ያማክበርና በታማኝነት ያለመፈፀም ፀረ-ዲሞክራሲ ነው። በተጨማሪም ሰላምን የሚያጠናክር ሳይሆን የባሰ ቀውስን የሚያስከትል፣ የሃገርና የህዝቦችን አንድነት የሚያጠናክር ሳይሆን የሚበታትን ይሆናል። ህዝቡም ሰላምን እንደሚፈልግ ሁሉ ለምርጫው ዝግጁ እንደሆነ ጥርጠር የለውም። ለዚህም ነው ለዲሞክራሲ የቆሙ ሁሉ የህዝቡን በምርጫ የመወሰን ስልጣን እንዲከበርና የ2012 ምርጫም በተያዘለት ቀን እንዲካሄድ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኙት።

በዚህ ሂደት ከሌሎች ፓርቲዎች ፕሮግራሞች/ማኒፌስቶዎች ጋር በሚነፃፀር መንገድ የፓርቲዎች ሃሳብ “ልዕልና” ይለያል ማለት ነው።  በመሆኑም ከፖለቲካ ፓርቲዎች የፕሮግራሞች ውድድርና የመራጩ ህብረተ ሰብ ውሳኔ ውጭ “የሃሳብ ልእልና” ብሎ ነገር የለም።