Back to Front Page

ወቅታዊ ችግሮቻችን ቁጥር አንድ

ወቅታዊ ችግሮችን

ቁጥር አንድ

 

ባይሳ ዋቅ -ወያ 11-29-19

******

ከብዙ ዓመታት የውጪ አገር ኑሮ በኋላ ወዳገሬ ከተመለስኩ ዓመት ሊሆነኝ ነው። ከኢትዮጵያ የወጣሁት ዓዋቂ የሚባል የዕድሜ ደረጃ ሳልደርስ ስለነበር ካገር የወጣሁት የኢትዮጵያን ሕዝብ የኑሮ ዘይቤ፣ ባሕላዊ እሴቶችና ሌላ ሌላም የሕዝቡ መገለጫ የሆኑትን ቅርሶች በውል ሳላውቅ ነበርና ተመልሼ የማሕበረሰቡ አካል ለመሆን መጀመርያ ላይ ትንሽ አዳግቶኝ ነበር። ዛሬ ግን ከሞላ ጎደል ተለማምጃለሁ ማለት ይቻላል። ማታ ማታ እግራችንን እናፍታታ ብለን ከጓደኛዬ ጋር የመንገዱን ጥግ ይዘን ስንኳትን፣ ከግራና ከቀኝ በሚፈስሰው ከሞላ ጎደል ወጣት በሆነው የሰው ጎርፍ ካንዱ ዳር ወደ ሌላኛው መላተሙንም ተለማምጄአለሁ። መልመድ ያቃተኝ ትልቁ ነገር ግን አዲስ አበባ ያኔ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ በነበርኩበት ዘመን የነበራት ሕዝብ ቁጥር ባንድ ትውልድ ዘመን ይህን ያህል ተበራከቶ ማየቱን ነው።

አዎ! ያገሪቷ ሕዝብ ቁጥር ማመን ከሚያቅተን በላይ ጨምሯል። ከጥቂት ዓመታት በፊት ሃምሳ ሚሊዮን የማይሞላ ሕዝብ የነበራት አገር ዛሬ የመቶ ሃያ ሚሊዮን ሕዝብ ባለቤት ሆና ከአፍሪካ አሕጉር ሁለተኛውን ደረጃ ይዛለች። ይህ የሕዝብ ቁጥር መጨመር ካስከተላቸው በርካታ ወቅታዊ ችግሮች ጥቂቶቹን ለመዘርዘር ያህል፣ አጠቃላይ የኑሮ ውድነት፣ የቤት እጥረት፣ የትራንስፖርት ችግር፣ የብልሹ አስተዳደር መስፋፋት (ሰዎች የመልካም አስተዳደር ጉድለት ይሉታል)፣ የሕጋዊ ሌቦች መብዛት፣ የቢሮኪራሲው ብልሹነት፣ የጉቦ ባሕል መስፋፋት፣ የጽንፈኞች መብዛትና የተጓዳኝ ግጭቶች መስፋፋት፣ የተፈናቃዮች ችግር እና በሙሉ እንዘርዝራቸው ከተባለ መጽሓፍ ሊወጣቸው የሚችል የችግሮች ካታሎግ ይገኛሉ። ያን ሁሉ ችግር አንስቶ አንድ ባንድ ለውይይት ማቅረቡ ተግባራዊ የሚሆን ስላልመሰለኝ፣ ላሁኑ የታዘብኳቸውን አሥር ያህል ወቅታዊ ችግሮቻችን ብቻ በማከታተል ላካፍላችሁ ወስኛለሁና በጥሞና ተከታተሉኝ። ለዛሬው ቁጥር አንድ ብዬ ያቀረብኩት የችግሮቻችን ሁሉ ችግር ነው ብዬ የገመትኩትን የወጣቱን ሥራ አጥነት ጉዳይ ነው

Videos From Around The World

ከላይ ባንድ ስንኝ ጠቅሼ ያለፍኩት የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር መጨመር (population growth) አመላካች የሆነውን የሕዝብ ጎርፍ በሚል ሁለት ቃላት ሥር ለማጠቃለል የሞከርኩት ሥራ አጥቶ በየሜዳው የተኮለኮለውና ቢያንስ ቢያንስ የሁለተኛ ደረጃ ከፍ ብሎም የዩኒቬርሲቲ ትምህርቱን ጨርሶ ምርታዊ ሊሆን ያልቻለውን ወደ ስምንት ሚሊዮን የሚጠጋ የወጣቱን ትውልድ ነበር። የዚህ የሥራ አጡ ትውልድ ክምችት በተለምዶ እንደሚታወቀው በዋና ዋና ከተሞች ብቻ ሳይሆን በየየዞኑ፣ በየወረዳውና በቀበሌ ደረጃ መሆኑን ራሴ በተዘዋወርኩባቸው የኢትዮጵያ ገጠሮች አስተውያለሁ። በተቻለኝ መጠን በየቦታው ተሰብስበው የማገኛቸውን ሥራ አጦች ጊዜ ወስጄ በሥነ ሥርዓት አነጋግሬአለሁ። ብዙዎቹ ለነሱ የማሳየውን መቆርቆር ሲያመሰግኑ ያን ያህል ደግሞ እዚህ ችግር ውስጥ የከተተን የናንተ ትውልድ ነው? ብለው በቁጭት ያነጋገሩኝም ነበሩ። ግምታቸው ትክክል ወይም ስህተት ነው ብዬ ሳልገመግማቸው ወይም ሙግት ሳልገጥም፣ ረጋ ብዬ ያለፈውን ሕይወታቸውን፣ አሁን ያሉበትንና ለወደፊት ምን እንደሚያስቡ ለማጥናት ሞክሬያለሁ። በዚያም መሠረት የችግሩን መንስዔ፣ ግዙፍነት፣ ባገሪቷ ላይ ሊያመጣ የሚችለውን አደጋና መንግሥት በአስቸኳይ መውሰድ ያለበትን እርምጃ የሚያሳይ ረቂቅ ፕሮጄክት አዘጋጅቼ ገዢ ፍለጋ ጉዳዩ ይመለከታቸዋል ብዬ የማስባቸውን የመንግሥት መሥርያ ቤቶች ደጅ እያንኳኳሁ ነው። ለጊዜው ገዢ ባላገኝም፣ ማንኳኳቴን ግን ቀጥዬበታለሁ። ይህ በኔ ግምት፣ የችግሮች ሁሉ ችግር የሆነው የስምንት ሚሊዮን የተማረው ወጣት ሥራ ማጣት ጉዳይከኤንጂኔር ታከለ ኡማ ጥቃቂን የአዲስ አበባ ከተማ የመንግሥት ፕሮጄክት ባሻገር፣ ያገራችን የፖሊቲካ ድርጅቶች ለጉዳዩ ቅድሚያ ሰጥተው የፖሊቲካ ቅስቀሳ አጄንዳችቸው ውስጥ አለማካተታቸው ግን የባሰ አሳስቦኛል።

የችግሩ መንስዔ

ሥራ አጥነት በሁሉም አገር ያለ ማሕበራዊ ክስተት ነው። አደጉ በተባሉት አገራት እንኳ ሥራ አጥነት አለ። ልዩነቱ ግን ባደጉት አገራት አንድ ዜጋ ተምሮ ሥራ ቢያጣ ወይም ይሠራ ከነበረበት መሥርያ ቤት ተሰናብቶ ወይም ራሱን አሰናብቶ ሥራ አጥ ቢሆንም፣ መንግሥት ያዘጋጀው የደህንነት መረብ safety net - ስላለ፣ ሥራ አጡም ሆነ ቤተሰቡ ለችግር አይዳረግም። ሌላ ሥራ እስኪገኝለት ድረስ መንግሥት አስፈላጊውን እንክብካቤ ያደርጋል ማለት ነው። እንግዲህ ልዩነታችን ሥራ በማጣት ላይ ሳይሆን፣ አንድ ዜጋ ሥራ አጥ ሲሆን መንግሥት የሚያደርግለት እንክብካቤ ላይ ነው።

ላገራችን ስምንት ሚሊዮን ወጣት ሥራ ማጣት መንስዔ ናቸው ብዬ የገመገምኩት የሚከተሉት ናቸው።

ሀ) በኔ ግምት ትልቁ ያገራችን ችግር በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ በማይገኝለት መልኩ እየጨመረ የሄደው የሕዝባችን ቁጥር ጉዳይ ነው። የሕዝብ ቁጥር መጨመር ብቻ ሳይሆን፣ ከሌላው ዓለም በተለየ መልኩ፣ የወጣቱ ቁጥር መጨመሩ ነው። በመንግሥት ዘገባ መሠረት ወደ 75% የሚጠጋው ያገራችን ሕዝብ ዕድሜው ከሰላሳ ዓመት በታች ነው። ወደ ስምንት ሚሊዮን የሚጠጋው ሥራ አጥ ወጣቱ ትውልድ የዚህ የ 75% አካል ነው ማለት ነው። በመሠረቱ የአንድ አገር የሠራተኛ ጉልበት መብዛት ተፈጥሮ በነጻ የሚለግሰው ውድ ሃብት ነው። መንግሥት ግን ይህንን ተፈጥሮያዊ ኃብት ባግባቡ ለመጠቀም ከሠራተኛው ጉልበት ጋር ተመጣጣኝ የሆነ ብሄራዊ ፖሊሲ አቅዶ ሥራ ላይ ካላዋለ በስተቀር፣ ይህ በነጻ የተገኘው የሠራተኛ ጉልበት አገራዊ ሃብት መሆኑ ቀርቶ አገራዊ ጥፋት ሊያስከትል የሚችል ኃይል ሊሆን ይችላል። ለዚህም ነው የሠራተኛ ጉልበት እንደ ኒዩክሌር ኃይል ነው የሚባለው፣ በደንብ ከተጠቀሙበት የኃይል ማመንጫ ሆኖ ያገሪቷን ኤኮኖሚ አሳድጎ የዜጎችን ኑሮ ያሻሽላል። አለበለዚያ ደግሞ ቦምብ ሆኖ ዜጎችን ሊጨርስ ይችላል።

ለ) ሌላው ለወጣቶቻችን ሥራ አጥነት ቁጥር መጨመር ከባድ አስተዋጽዖ አድርጓል ብዬ የማስበው ከዚሁ ከሕዝብ ቁጥር መጨመር ጋር ተያያዥ የሆነው፣ ያገሪቷ የኤኮኖሚ ዕድገትና የትምህርት ፖሊሲው አለመጣጣም ነው። ያደጉ አገራት ለአገራቸው የሚያስፈልጋቸው በተለያየ የቴክኒክ ሙያ የሠለጠኑ ወጣቶችን እንጂ ከፍተኛ የዩኒቬርሲቲ ድግሪ የተቀዳጀ አለመሆኑን ስላመኑበት አብዛኛውን ወጣት ትውልድ ገና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ሲጨርሱ ወደ ሙያ ትምህርት ቤት (vocational training) እንጂ ዩኒቬርሲቲ እንዲገቡ አይገፋፏቸውም። አስቀድሞ በተቀየሰው ብሄራዊ የሥራ ፖሊሲ መሠረት አገሪቷ የሚያስፈልጋት ብዙ የሙያ ትምህርት ቤት ተመራቂዎች በመሆኑ ከሙያ ትምህርት ቤት የሚመረቁ ወጣቶች የሥራ ማጣት ችግር አያጋጥማቸውም። ባገራችን ግን ሁኔታው የተለየ ነው። የክልል መንግሥታትን የፖሊቲካ ሥልጣን ፍላጎት ለማርካት በሚመስል መልኩ በየክልል ዋና ከተሞች ብቻ ሳይሆን በዞኖች ሳይቀር ከአርባ በላይ የሚሆኑ የመንግሥትና የዚያኑ ኃይል የሆኑ የግል ዩኒቬርስቲዎች ተሠርተው በያመቱ ከሰባ አምስት ሺህ በላይ ዜጎችን በድግሪ እያስመረቁ ነው። አገራችን በዛሬው ሁኔታ ለዚህ ሁሉ የድግሪ ባለቤት ሥራ ለመፍጠር የሚያስችል አቅም ለመፍጠር አልቻለችም።

ሐ) አገሪቷ በያመቱ የሁለት አኃዝ ዕድገት እያሳየች ነው እየተባለ ቢሰበክም ያገሪቱ ኤኮኖሚ ፖሊሲ የተቀየሰው ጥቂቶችን ብቻ ለማበልጸግና አብዛኛውን ግን ለማደህየት ነበር። ቅድሚያ የተሠጣቸውም ፕሮጄክቶች፣ ባብዛኛው የታይታይ መዋቅርን ብቻ ያማከለና (በተለይም የሕንጻ ግንባታ) ያገሪቷን የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ሃብትን ባግባቡ ሥራ ላይ ለማዋልና ዘላቂ የሥራ ዕድል ለመፍጠር የታቀዱ አልነበረም። ወጣቱ በሥራ የሚጠመደው ሕንጻው ተገንብቶ እስኪያልቅ ብቻ ነው እንጂ ከዚያ በኋላ እንኳን ለወጣቱ የሥራ ዕድል መፍጠር ይቅርና ለባለሕንጻዎቹም ራሳቸውም ትርፍ ሊያመጣ የማያስችል የተሳሳተ ብሄራዊ ኤኮኖሚያዊ ፖሊሲ ነበር።

ችግሩ በአስቸኳይ መቀረፍ አለበት፣

ይህ ዛሬ ባገራችን የተንሰራፋው የወጣቱ የሥራ አጥነት የጭለማ ድባብ ባስቸኳይ መቀረፍ አለበት የምለው ያለ ምክንያት አይደለም። አዎ! ለዓመታት ሲከማች የነበረውን ማሕበራዊ ችግር ባጭር ጊዜ መፍትሄ ይፈለግለት ብሎ መለፈፍ አንድም የሁኔታውን ምንነት በውል ካለማወቅ አለያም በተግባር ሊተገበር አለመቻሉን እያወቁ መንግሥት ለማሳጣት የሚደረግ የፖሊቲካ ቅስቀሳ ነው። ያ ማለት ግን ችግሩን ለመቅረፍ መንግሥትና ማህበረሰቡ በአስቸኳይ ብሄራዊ የሆነ ወጣቱን ምርታማ የሚያደርግ ሁለንተናዊ ፖሊሲ ማውጣት የለበትም ማለት አይደለም። ምክንያቱም ይህ ብሄራዊ ችግር ባጭር ጊዜ ውስጥ ካልተቀረፈ ወይም ለሥራ አጡ ወጣት ትውልድ ተስፋ የሚሠጥ አንዳች ዓይነት ፖሊሲ በአስቸኳይ ካልተቀየሰ የአገራችን ብቻ ሳይሆን የቀጠናው ሰላምና መረጋጋት ራሱ ችግር ውስጥ እንደሚገባ ጥርጥር የለውም። ይህ ሥራ አጥቶ፣ የወላጆቹን ሃብት አሟጥጦ ተምሮ ለወላጆቹ መድረስ በነበረበት ሰዓት እንኳን ላሳደጉት ይቅርና ለራሱም በልቶ የሚያድርበትን ገቢ በሕጋዊ መንገድ ሊገኝ ያልቻለው ትውልድ፣ ቀስ በቀስ ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ የዕለት ጉርሱን ለማግኘት ይገደዳል፣ ወንዶቹ ጨለማን ተገን አድርገው መዝረፍን፣ ሴቶቹም እንደዚያው ማንነታቸውን እየደበቁ መንገድ ላይ ወጥተው በሴተኛ አዳሪነት መተዳደር ይጀምራሉ። በዚህ ሁኔታ የሚገኙ ሥራ አጥ ወጣቶች ለአደንዛዥ ዕጽ አዟሪዎች የተመቻቸ ኃይል በመሆናቸው በቀላሉ ይመለመሉና ዕጹን በማዟዟር የወንጀል ተግባር ይሰማራሉ። መንገድ ላይ እስካሉ ድረስ ደግሞ ማንም ዴማጎግ ቀርቦአቸው ላንድ ዓላማ ተነሱና ተሰለፉ ብሎ ሬንጄርና ክላሽኒኮቭ ከሰጣቸው ያላንዳች ማወላወል ይከተሉታል። በቅርቡ በመዲናችንና ባንዳንድ ከተሞች የምንታዘባቸው የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች መቶ በመቶ ሊባል በሚቻል መልኩ ተሳታፊዎቹ እነዚህ መንገድ ላይ የሚውሉ ሥራ አጥ ዜጎቻችን ናቸው። በግሌ እስካሁን ድረስ አንድም የመንግሥትም ሆነ የግል ድርጅት ሠራተኛ ወይም የሙያ ማህበር አባላት ሥራቸውን አቁመው ለተቃውሞ ሰልፍ የወጡበትን ጊዜ አላየሁም።

ለዚህ ነው ችግሩን በአስቸኳይ መቅረፍ ባይቻልም ተስፋ ሰጪ የሆነ ብሄራዊ ፖሊሲ እንኳ በአስቸኳይ መቀየስ ግድ ይላል የምለው። በኔ ግምት፣ የትምህርት ጥራትን ከማሻሻልና የኤኮኖሚውን ፖሊሲ ከመቀየር በተጨማሪ መንግሥት ሁለት ተጓዳኝ እርምጃዎችን በአስቸኳይ መውሰድ አለበት። የመጀመርያው እንቅስቃሴ የኢንዱስትሪውን ዘርፍ (በየከተማውና በገጠራት) ለማሳደግ አገራዊ ዕቅድ ማውጣትና እቅዱም የሚተገበርበትን መርሃ ግብር ማውጣት ነው። አዎ! ይህ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊተገበር ባይችልም አስፈላጊው ትኩረት ከተሠጠው በጥቂት ዓመታት ውስጥ ጥራት ያለው ለውጥ ሊያመጣ ይችላል ባይ ነኝ። ሁለተኛው ተጓዳኝ የእንቅስቃሴ ዘርፍ ደግሞ፣ ሥራ አጡን ወጣት ትውልድ ለዓለም የሥራ ገበያ ለማቅረ ዕቅድ ማውጣት ነው። ከመጀመርያው እንቅስቃሴ አንጻር ሲታይ ይህ እንቅስቃሴ በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤት ሲያሳይ ይችላል፡፡ እንደሚታወቀው፣ ያደጉ የአውሮፓና የዓረብ ባህረ ሰላጤ አገራት ባገራቸው እየተከሰተ ካለው የሠራተኛ ጉልበት እጥረትና ተፈጥሮ ባደላቸው የዘይት ሃብት ምክንያት ከራሳቸው ሕዝብ ውጪ ለሌሎችም የሥራ ዕድል የመክፈት አጋጣሚ ስላለ ይህንን አጋጣሚ ተጠቅሞ ወጣቶቻችንን ለገበያው ማመቻቸት ግድ ይላል።

የነዚህን ስምንት ሚሊዮን ወጣት ትውልድ የሥራ አጥነት ችግር የሚቀረፍበት ዘዴ ካሁኑ ካልተቀየሰና የሚተገበርበት መንገድ በመንግሥትና በባላሃብቶች እንዲሁም በማህበረሰቡ ርብርቦሽ ካልተደረገበት ዛሬ ሥልጣን ላይ ያለውም ሆነ ከሚቀጥለው ምርጫ ባኋላ የፖሊቲካ ሥልጣን የሚጨብጠው ማንኛውም ፓርቲ ወይም የፓርቲዎች ጥምረት መንግሥት ተደላድሎ ሥልጣን ላይ ይቀመጣል ብሎ ማሰብ የሕልም እንጀራ ነው። ስለዚህ ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ለዚህ ችግር መፍትሄ ነው ብሎ የሚያስበውን ብሄራዊ ፖሊሲ ይፋ ማድረግ ያለበትን ያህል፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም በሚቀጥለው ምርጫ ሥልጣን እንይዛለን ብለው ካሰቡ ለዚህ ሥራ አጥ ትውልድ ያላቸውን ፖሊሲ ካሁኑ ለሕዝብ ይፋ ማድረግ አለባቸው።

እስካሁን ከተገነዘብኩት ግን፣ በኢትዮጵያ ምድር ላይ እየተንቀሳቀሱ ካሉት ወደ መቶ ከሚጠጉ የፖሊቲካ ፓርቲዎችና ድርጅቶች ለነዚህ ሥራ አጥ ወገኖቻችን ያላቸውን አጄንዳ ለሕዝብ ያቀረበ ወይም ሊያቀርብ የሚሞክር አላየሁም። ሁላቸውም የሥራ አጥነቱ ላስከተላቸው ሰበቦች መፍትሄ ነው ብለው የሚገምቱትን መሰንዘር እንጂ የችግሩን መሠረታዊ ምክንያት ለመመርመርና ለመቅረፍ አንዳችም እንቅስቃሴ ሲያደርጉ አይታዩም። በየቦታው የሚቋቋመው የኮሚቴዎቹ ብዛት፣ የባላደራው ውትወታ፣ የየብሄሩ ምሁራን ስብሰባ፣ የሚዲያው ዘገባ ወዘተ ክስተቶችን አጋንኖ ሕዝብን ለባሰ ግጭት ከማዘጋጀትና ለሰበቦቹ ጊዜያዊ መፍትሄ ከመፈለግ ባሻገር ሥራ አጡን ወጣት ምርታማ ለማድረግ የሚያስችል አቅጣጫ ለመቀየስ ስብሰባ አድርገው ሲወያዩ አይታይም።

መደረግ ያለበት፣

በኔ ግምት ጠቅላላው ያገራችን የፖሊቲካና የኤኮኖሚ ችግር ጥያቄ ሊፈታ የሚችለው ይህ የወጣቱ ሥራ አጥነት ችግር ከተፈታ በኋላ ብቻ ነው ባይ ነኝ። ስምንት ሚሊዮን ጊዜውን ጠብቆ ለመፈንዳት ትክ ትክ የሚለውን ቦምብ ባገሪቷ ከዳር እስከ ዳር ተቀብሮ እያለ ተረጋግቶ አራት ኪሎ የሥልጣን ወንበር ላይ ተደላድዬ እቀመጣለሁ ብሎ ለምርጫ መዘጋጀት የዋህነት ይመልስለኛል። አዎ! ችግሩ ሥር የሰደደ ስለሆነ በአስቸኳይ መፍትሄ ሊገኝለት አይቻልም። ለዚህም ይሆናል የፖሊቲካ ድርጅቶቻችን ደፍረው ስለዚህ ጉዳይ በአደባባይ ሊናገሩ ወይም፣ ሕዝቡን ሊወያዩ የማይሹት! ችግሩ በአስቸኳይ ሊፈታ ባይችልም መፍትሄ ፍለጋውን በጋራ ሆኖ ለመጀመር መወያየትና ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀት ግን የማይቻልበት ምክንያት የለም።

በዚያው ልክ ደግሞ፣ ዛሬ በአክቲቪሲቶችና በፖሊቲካ ድርጅቶች እየተቀነቀኑ ያሉት የማንነት ጥያቄ የአዲስ አበባ ባለቤትነት በየዩኒቬርሲቲዎች እየተከሰቱ ያሉት ብሄር ተኮር ግጭቶች ወዘተ ሊፈቱ የሚችሉት ባገሪቷ ሰላም ከሰፈነ ብቻና ብቻ መሆኑ መታወቅ አለበት። ስምንት ሚሊዮን ጊዜውን ጠብቆ የሚፈነዳ ቦምብ ባገራችን ከዳር እስከዳር ተቀብሮ እስካለ ድረስ ደግሞ እንኳን ባገራችን በቀጠናውም ሰላም ሊሰፍን አይችልም። ስለዚህ ያለን አማራጭ አንድና አንድ ብቻ ነው። መንግሥት የውጭ አገር የሥራ ገበያውን ማመቻቸትና ለገበያው ፍላጎት የሚመጥን ዕውቀትን ችሎታ ያላቸውን ወጣቶችን በማቅረብና ባገር ውስጥ ደግሞ ከራሳችንም ሆነ ከዓለም ዓቀፍ ተቋማት በሚገኘው እርዳታ ሥራ አጥ ወጣቱን ምርታማ ለማድረግ የሚያስችል የንግድ እንቅስቃሴና የፋብሪካ ግንባታ ላይ ማተኮር አለበት።

ተቃዋሚ ድርጅቶችና አክቲቪሲቶች እንዲሁም ጉዳዩ የሚያሳስበን ዜጎች ደግሞ የችግሩን ሰበቦች እያጋነንና ለግል የፖሊቲካ ጥቅም ብቻ ሲባል ችግሩ ያስከተላቸውን ሰበቦች ለፖሊቲካ ገበያ አቅርቦ ማኅበረሰቡን ለባሰ ችግር ለመዳረግ ከመንቀሳቀስ ተቆጥበን፣ ዘላቂ ሰላም ሊያሰፍን በሚችልና ወጣቱን ምርታማ ለማድረግ የሚያስችልን ፍኖተ ካርታ ለመንደፍ በየሙያችን ተሰልፈን አብረን እንሥራ። ከሚከፋፍለን ይልቅ የሚያስተሳስረን ይበልጣልና አገራችንን ከመፈራረስና የሕዝባችንን አንድነት ለማቆየት የምንመኝ ከሆነ ዛሬ ከሁሉም በላይ አስቀድመን ማድረግ ያለብንና መደረግ ያለበት ይኸው ብቻ ይመስለኛል።

በቸር ይግጠመን።

አዲስ አበባ፣ ኅዳር 2019 ዓ.ም

wakwoya2016@gmail.com

******

Back to Front Page