Back to Front Page

“ለጥላቻ ንግግር” ሕግ ያስፈልጋል?

(ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)

4-20-19

ለዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነኝ ወንድሜ አቶ ሙሼ ሰሙ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ የሚያዝያ 5 ቀን 2011 ዓ.ም እትም ላይ “ስለ ሕግ ሳይሆን ስለ ሪፐብሊኩ አምላክ” በሚል ርእስ የጻፈው መጣጥፍ ነው፡፡ (ሙሼን “አንተ” ያልኩት ባለን የ30 ዓመታት ጓደኝነትና ቀረቤታ ምክንያት ነው)

የአቶ ሙሼ ጽሁፍ ትኩረት ያደረገው “… አማራጭ ማህበራዊ መድረክ መሆን የሚገባው ፌስቡክ ሜይን ስትሪም ሚዲያ ወደመሆን እየተንደረደረ ነው፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው በዋናነት በመንግሥት በኩል ያለው የመረጃ አቅርቦት ክፍትትና መረጃን በሞኖፖል በሚያገኙ የፌስቡክ አጋፋሪዎች ምክንያት ነው፡፡ እነዚህ የፌስቡክ አርበኞች ተገቢ ባልሆነ መንገድ ያገኙትን መንግስታዊ፣ ሀገራዊ፣ ድርጅታዊ፣ ማህበረሰባዊና ግለሰባዊ ሚስጥር ኃላፊነት በማይሰማው መንገድ ፌስቡክ ላይ በመዘክዘክ አደጋ እየፈጠሩ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በሀገራዊ ሚስጥር እና በሕዝብ መረጃ የማግኘት መብት መካካል ያለው ቀይ መስመር ተጥሷል፡፡ … ጠቅላይ ሚንስትሩን ጨምሮ የመንግስት ባለስልጣናት ቃለ መሃላ ከፈጸሙባቸው ጉዳዮች አንዱ የሪፐብሊኩን ሚስጥር መጠበቅ በመሆኑ ባለፉት ዓመታት ሲካሄድ የነበረውን ትግል ለማገዝ የተከፈቱ ኢ-መደበኛ የመረጃ በሮች መዘጋት አለባቸው፡፡ መረጃ ለሁሉም ዜጋ በመደበኛ ተቋም አማካይነት ሊሰራጭ ይገባል፡፡ … ማንም አክቲቪስት፣ ማንም ውስጥ አዋቂ ነኝ ባይ ማወቅ ከሚገባው በላይ መረጃ ሊኖረው አይገባም” በሚሉት ጉዳዮች ላይ ነው፡፡

Videos From Around The World

የጥላቻ ንግግርን ለማስቆም በሚል ሰበብ እየተረቀቀ ያለውን ሕግ በተመለከተም “የፌስቡክ ችግር ምንጊዜም ወቅታዊ ስለሆነ የሕግ ማዕቀፍ በማውጣት ብቻ የሚፈታ አይደለም፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሕግ ጊዜያዊ ችግር ከመቅረፍ ያለፈ ትርጉም የለውም፡፡ እንዲህ ዓይነት ህግ እንዲያውም ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን የማፈን ውጤት ሊያመጣ ይችላል” የሚል ስጋት እንዳለው ይገልጻል ሙሼ፡፡

እነዚህን የሙሼን ሃሳቦች እኔም እጋራቸዋለሁ፡፡ በተለይም “እንዲህ ዓይነት ህግ ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን የማፈን ውጤት ሊያመጣ ይችላል” የምትለዋን ሃሳብ በመያዝ ነው የጽሁፌን ርእስ “የጥላቻ ንግግር ሕግ ያስፈልጋል?” የሚል እንዲሆን ያደረግኩት፡፡ ትኩረቴም በዚሁ ዙሪያ ይሆናል፡፡

በዚህ ጽሁፍ በቅድሚያ በእንግሊዝኛ “Hate speech” የሚለውን ጽንሰ ሃሳብ ትርጉም እናያለን፡፡ የጽንሰ ሃሳቡን ትርጉም ብቻ ሳይሆን በሌሎች ሀገሮች ያለውን ተሞክሮ አለፍ አለፍ ብለን ለመጠቃቀስ እሞክራለሁ፡፡ በመጨረሻም በእኛስ ሀገር ምን ቢደረግ ይሻላል? የሚለውን ጥያቄ በማንሳት ምክረ-ሃሳብ ለማቅረብ ይሞከራል፡፡

“Hate Speech” - የፅንሰ ሃሳቡ ምንነት

የጥላቻ ንግግርን በተመለከተ ከሚነሱት አከራካሪ ጉዳዮች አንደኛው “የጽንሰ ሃሳቡ ትርጉም ምንድነው?” የሚል ነው፡፡ በርግጥ በዚህ ጽንሰ ሀሳብ ዙሪያ ወጥነት ያለው፣ ሁሉም ሀገሮች የሚስማሙበት ትርጉም ለማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በየሀገሩ በርካታ ክርክሮች ይደረጋሉ፡፡ የክርክሮቹ መነሻ የጥላቻ ንግግር በሚለው ጽንሰ ሀሳብ ውስጥ ምን ምን ነገሮች ይካተቱ የሚለው ነው፡፡

በእንግሊዝኛ “Hate Speech” የሚለው ጽንሰ ሃሳብ ወደ አማርኛ ሲመለስ “የጥላቻ ንግግር፣ ክፉ ቃል፣ መጥፎ ንግግር” የሚል ቀለል ያለ ቀጥተኛ ትርጉም ልንሰጠው እንችላለን፡፡ “የጥላቻ ንግግር ማለት በግለሰብ ወይም በቡድን፣ በብሔር፣ በዘር፣ በሃይማኖት ወዘተ. ላይ በማነጣጠር በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ መንገድ የሚያስቆጣ ቃልን መወርወር ማለት ነው” የሚል ትርጉምም በአንዳንድ ሰነዶች ላይ ሰፍሮ ይገኛል፡፡ በዚህ ጽሁፍ ውስጥ የቀረቡት ሃሳቦች እነዚህን ትርጉሞች መሰረት በማድረግ ይሆናል፡፡

በሌሎች ሀገሮች ያለ ተሞክሮ

የጥላቻ ንግግርን በተመለከተ ህግ ማውጣት ያስፈልጋል ወይም አያስፈልግም? የሚል ውዝግብ እንደቀጠለ ቢሆንም፤ የተለያዩ ሀገሮች መንግስታት ጉዳዩን ካሉበት ማህበረሰብ ችግርና ፍላጎት በመነሳት ውሳኔ ያሳለፉበት ሁኔታ ይታያል፡፡ አንዳንድ ሀገሮች የጥላቻ ንግግር ማድረግ ወንጀል ነው በሚል መንፈስ በወንጀለኛ መቅጫ ህጎቻቸው በተደነገገው መሰረት ውሳኔ እንዲያገኝ ማድረግን መምረጣቸው ይስተዋላል፡፡ ሌሎች ሀገሮች ደግሞ የተለየ ህግ በማውጣት ውሳኔ መስጠታቸው ይታያል፡፡ በዚሁ መሰረት አንዳንድ ሀገሮች ያወጧቸውን ድንጋጌዎች አለፍ አለፍ ብለን እንመልከት፡፡

በመሰረቱ ክፉ ቃል መናገርን በየትም ሀገር ያለ ማህበረሰብ አይወደውም፡፡ እናም የጥላቻ ንግግር በማህበረሰብ የተጠላና የተወገዘ ችግር ነው፡፡ አንዳንድ ሀገሮች ይህንን ችግር ለመቅረፍ መጥፎ ንግግር የሚዳኝበት ህግ አውጥተዋል፡፡ ይህንን ህግ ካወጡ ሀገሮች ውስጥ የሚከተሉት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ከአውሮፓ ሀገራት እንጀምር፡፡

በፊንላንድ “የጥላቻ ንግግር” በሚለው ፅንሰ ሃሳብ ትርጉም ዙሪያ ሰፊ ውዝግብ አለ፡፡ በአንድ በኩል፤ “የጥላቻ ንግግር ማለት ዘረኛ ቅስቀሳ ማድረግ ማለት ነው የምንል ከሆነ ይህንን በተመለከተ በፊንላንድ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ ውስጥ የተካተተ ህግ አለ፡፡ እናም ለብቻው ህግ ማውጣት አያስፈልግም” የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ፤ “የጥላቻ ንግግርን በተመለከተ ህግ አወጣለሁ ማለት የማይፈለጉ ትችቶና አስተያየቶች እንዳይቀርቡ ዝም ማሰኘት ነው፡፡ ውይይትንም ይገታል፡፡ እናም የጥላቻ ንግግር ማለት ምን ማለት ነው በሚለው ትርጉም ዙሪያ ስምምነት ሳይፈጠር ስለ ‘የጥላቻ ንግግር’ ህግ ማውራት አስቸጋሪ ነው” ይላሉ፡፡ በጽንሰ ሃሳቡ ትርጉም ዙሪያ በፊንላንድ የፓርላማ አባላት መካከልም ስምምነት የለም፡፡

ዘርን፣ የቆዳ ቀለምን፣ ዜግነትን፣ አካላዊ ገጽታን፣ ፆታን፣… መሰረት ያደረገ ስም ማጥፋት፣ ስድብ፣ ጥላቻ፣ ማግለል፣… የመሳሰሉ ወንጀሎችን በተመለከተ በፈረንሳይ የወንጀለኛ መቅጫ እና የፕረስ ህግ ውስጥ ድንጋጌ ተቀምጧል፡፡ እነዚህ ወንጀሎች ከዘር ማጥፋት ጋር የተያያዙ መሆናቸውም በህጉ ውስጥ እንዲካተት ተደርጓል፡፡ በዚህም ምክንያት ፈረንሳይ የተለየ “የጥላቻ ንግግር” ህግ የላትም፡፡

የጥላቻ ቅስቀሳ ማድረግ፣ ስድብ፣ ስም ማጥፋት ወዘተ. በጀርመን የወንጀል ህግ መሰረት እስከ አምስት ዓመት የሚደርስ የእስር ቅጣት የሚያስከትል ወንጀል ነው፡፡ አንድ የጀርመን ዜጋ ከጀርመን ሀገር ውጪ ሆኖ “የጥላቻ ንግግር” ቢያደርግ እንኳ በዚህ ህግ መሰረት እንደሚቀጣ ተደንግጓል፡፡ አይስ ላንድ በምትባል ሀገር በአደባባይ መሳደብ፣ መዝለፍ፣ ስም ማጥፋት፣… ለሁለት ዓመት የእስር ቅጣት ይዳርጋል፡፡

“የጥላቻ ንግግር አሜሪካንን እየመረዛት ነው፣ ይህንን ጥፋት በህግ ድንጋጌ ማቀብ ግን ችግሩን አይፈታውም” ይላሉ የአሜሪካ ሊቃውንት፡፡ በዚህም ምክንያት አሜሪካ በህገ መንግስቷ እውቅና የተሰጠውን ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን ምክንያት በማድረግ የጥላቻ ንግግርን የሚያቅብ የተለየ ህግ አላወጣቺም፡፡

ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት በህንድ ህገ መንግስት በአንቀጽ 19 (1) መሰረት እውቅና የተሰጠው መብት ነው፡፡ በዚሁ አንቀጽ በንዑስ አንቀጽ 2 ላይ ደግሞ “ስም ማጥፋትን” በተመለከተ ሃሳብን በነፃነት በመግለጽ መብት ላይ “ምክንያታዊ ገደብ” ሊደነገግ እንደሚችል ተቀምጧል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ በአየር ላንድ ህገ መንግስት ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ተደንግጓል፡፡ ይሁን እንጂ በመገናኛ ብዙሃንም ይሁን በአደባባይ በሚደረግ የጥላቻ ንግግር ላይ ይህ መብት ሊገደብ እንደሚችል እ.ኤ.አ በ1989 በወጣ ህግ ተደንግጓል፡፡

የቤልጅየም ህገ መንግስትም ዘረኝነትንና ጥላቻን በህገ ወጥነት ይፈርጃል፡፡ በእንግሊዝ የጥላቻ ንግግርን ወንጀል የሚያደርጉ የተለያዩ ድንጋጌዎች ወጥተዋል፡፡ ተመሳሳይ የህግ ድንጋጌዎች በሰርቢያ፣ በፖላንድ፣ በሩሲያ፣ በሩማንያ፣ በሲንጋፖር፣ በደበብ አፍሪካ፣ በአውስትራሊያ፣ በብራዚል፣ በካናዳ፣ በዩክሬን፣ በቺሊ፣ በክሮኤሽያ፣ በዴንማርክ፣ በስዊድን ህገ መንግስትና ሌሎች ህጎች ውስጥ የጥላቻ ንግግርን በተመለከተ ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች ተቀምጠዋል፡፡

እንደ ፌስቡክ፣ ጉግል፣ ማይክሮ ሶፍት እና ትዊተር ያሉ ማህበራዊ የግንኙነት አውታሮችን የሚመሩ የኢንተርኔት ባለቤቶች በጥላቻ ንግግር ዙሪያ የሚያራምዷቸው አቋሞች አሏቸው፡፡ እነዚህ ተቋማት የአውሮፓ ህብረትን የስነ-ምግባር ህግ ድንጋጌዎች በጋራ በመቀበል “ፖስት የተደረጉ የጥላቻ ንግግሮችን” በ24 ሰዓት ለማስወገድ ተስማምተዋል፡፡

ምክረ-ሃሳብ - በእኛስ ሀገር ምን ቢደረግ ይሻላል?

ወደ እኛ ሀገር እንምጣ፡፡ አቶ ሙሼ ሰሙ ባለፈው ሳምንት ጽሁፉ እንዳመላከተው በየእለቱ እየተፈበረከ በማህበራዊ ሜዲያ የሚለቀቅን የጥላቻ ንግግር ማቀቢያ ህግ በመደንገግ ማስቆም ይቻላል? የጥላቻ ንግግርን በተመለከተ ህግ ማውጣትስ ያስፈልጋል ወይስ አያስፈልግም? የሚለው ጥያቄ በአግባቡ መፈተሽ ይገባዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡

በአሜሪካ አንድን ግለሰብ ወይም ቡድን መጥላ ወንጀል አይደለም፡፡ በአሜሪካ የጥላቻ ንግግር ማድረግም ወንጀል አይደለም፡፡ የጥላቻ ንግግር ማለት ምን ማለት እንደሆነ ብያኔው በህግ ካልተቀመጠ በስተቀር የጥላቻ ንግግርን ከትችት፣ የጥላቻ ንግግርን አስተያየት ከመስጠት ለይቶ ማወቅ አስቸጋሪ ነው - በአሜሪካ፡፡

በእኛም ሀገር ይህ ሁኔታ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል የሚል እምነት አለኝ፡፡ በመሆኑም ይህንን ህግ ከማውጣታችን በፊት ሁለት ነገሮች ቢታዩ ጠቃሚ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ አንደኛ፤ ሃሳብን በነፃነት በመግለጽ መብት እና በጥላቻ ንግግር መካከል ያለው ዳር ድንበር ምንድነው? ሃሳብን በነፃነት መግለጽ ማለት የጥላቻ ንግግር ማድረግን ይጨምራል? ሁለተኛ፤ አዲስ ህግ ከማውጣት ይልቅ እንደ ወንጀል የጥላቻ ንግግር በወንጀለኛ መቅጫ ህግ ምላሽ ሊያገኝ አይችልም ወይ?

እዚህ ላይ “ለመሆኑ የአንተ አቋም ምንድነው?” የሚል የግልጽነት ጥያቄ ሊቀርብ እንደሚችል አስባለሁ፡፡ የህግ ባለሙያ ባልሆንም የሀገራችን የወንጀለኛ መቅጫ ህግ አፍ እላፊ፣ ስድብ፣ዘለፋ፣ ስም ማጥፋት፣…  የመሳሰሉ መለስተኛ ወንጀሎች ሲፈጸሙ አጥፊዎች የሚቀጡበት ድንጋጌ እንዳለው ሰምቻለሁ፡፡

በሌላ በኩል፤ እንደ ፌስቡክ ባሉ የማህበራዊ ሜዲያ አውታሮች ከአፍ እላፊና ከተራ ስድብ የዘለሉ፣ መረን የለቀቁ የጥላቻ ንግግሮችና የበሬ ወለደ ውንጀላዎችና ፍረጃዎች በስፋት እንደሚሰራጩም አስተውያለሁ፡፡ ግን ይህ ሁኔታ በህግ ድንጋጌ ሊቆም ይችላል? አይመስለኝም! እናም በኔ እይታ መፍትሄው ህግ ማውጣት ሳይሆን በማስተማር የህብረተሰቡን አመለካከት መለወጥ፣ መብትና ግዴታውን የተገነዘበ፣ ወንጀልን የሚጸየፍ ዜጋ ለማፍራት መጣር ነው፡፡

   ጸሐፊውን በEmail: ahayder2000@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

 

Back to Front Page