Back to Front Page


Share This Article!
Share
አቶ በረከት ስምዖን አቶ ዮሃንስ ቧያለው እንዳለው በኢትዮጵያና በአማራ ህዝብ ጉዳይ ጣልቃ ገብ ነበር ማለት ይቻል ይሆን?

አቶ በረከት ስምዖን አቶ ዮሃንስ ቧያለው እንዳለው በኢትዮጵያና በአማራ ህዝብ ጉዳይ ጣልቃ ገብ ነበር ማለት ይቻል ይሆን?

ከእውነቱ ይታያል 1-11-19

በቅርቡ አቶ በረከት ካደረጋቸው ንግግሮች መካከል የኤርትራው ፕሬዚደንት አቶ ኢሳያስ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እየገቡ ነው የሚለው ግምቱ ይገኝበታል። እሱን ተከትሎም አቶ ዮሃንስ ቧያለው ከአማራ መገናኛ ብዙሃን ጋ ባደረገው ቃለመጠይቅ አቶ በረከት ስለ አቶ ኢሳያስ በኢትዮጵያ ውስጥ ጣልቃ የመግባት ያለመግባት ጉዳይ ለመናገር የሞራል መሰረት የለውም የሚል ሃሳብ ሲያስተላልፍ አደመጥኩት። አቶ ዮሃንስ ለዚህ አባባሉ የሚያቀርበው ምክንያት ደግሞ ታዲያ አቶ በረከት ኤርትራዊ ሆኖ እያለ የብአዴን/ኢህአዴግ አመራር ሆኖ ሲሰራ በኢዮጵያና በአማራ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባቱን አምኖ ለምን ይቅርታ አልጠየቀም የሚል ነው።

ስለ እውነት እንነጋገር ከተባለ አቶ ኢሳያስ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እየገቡ እንዳለ የሚመስሉ ሁኔታዎችን እያየንና እየሰማን ነው። በዚህም ምክያት ይመስላል የኢትዮጵያ መንግስት የርሳቸውንና የአጋሮቻቸውን ፍላጎት የሚያሟሉ ውሳኔዎች ሲያሳልፍና ሌሎች እንቅስቃሰዎችን ሲያደርግ የሚታየው። ይሁንና የዚህ ፅሁፍ አላማ የአቶ ኢሳያስ በኢትዮጵያ ውስጥ ጣልቃ የመግባት ያለመግባት ጉዳይ ላይ ስላልሆነ ዝርዝር ውስጥ አለመግባትን መርጫለሁ። ከሁኔታው አሳሳቢነት በመነሳት ግን ወደፊት የራሴን ሃሳብ ይዠ መቅረቤ አይቀርም።ለማንኛውም የዚህ ፅሁፍ ዋና አላማ አቶ በረከት ስምዖን አቶ ዮሃንስ ቧያለው እንዳለው በኢትዮጵያና በአማራ ህዝብ ጉዳይ ጣልቃ ገብ ነበር ማለት ይቻል ይሆን ወይ? በዚህ መነሻነትስ ይቅርታ መጠየቅ ይኖርበት ይሆን ወይ? የሚሉትን ጭብጦች ማየት ነው። እነዚህን ጭብጦች በሚገባ ለመረዳት ደግሞ ከዜግነትና ከማንነት ጋ እያገናዘቡ መመርመሩ ተገቢ ነው።

Videos From Around The World

ዜግነት ማለት በቀላል አገላለፅ የአንድ ሉአላዊ አገር አባልነት ማለት ነው። አንድ ሰው የአንድ አገር ዜጋ ከሆነ ዜጋ በሆነበት አገር ጥበቃ ይደረግለታል ብቻም ሳይሆን የተለያዩ መብቶችንም ይጎናፀፋል። ዜጋው በበኩሉ ለሃገሩ የተለያዩ ግዴታዎች ውስጥ ይገባል። ዜግነት በተለያየ መንገድ ሊገኝ ይችላል። ይህ ደግሞ በየሃገራቱ ህግ የሚወሰን ጉዳይ ነው። ዜግነት የሚገኝባቸው ዋና ዋና መንገዶች ግን ሁለት ናቸው። አንደኛው በትውልድ (By Birth) ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በሂደት (Naturalization) ነው። በትውልድ ሲባል በሁለት መንገድ የሚታይ ነው። የመጀመሪያው በትውልድ ጊዜ ከአባት ወይም ከእናት ወይም ደግሞ ከሁለቱም ዜግነት የሚቀዳ ነው። ሌላው ደግሞ የአንድ ሃገር ህግ የሚፈቅድ ከሆነ ከወላጆች ጋ ሳይተሳሰር ሰው አንድ አገር ውስጥ በመወለዱ ብቻ የሚያገኘው ዜግነት ነው። ከዚህ አንፃር ሲታይ አቶ ዮሃንስ ቧያለው የአቶ በረከትን ኢትዮጵያዊነት ጥያቄ ውስጥ ማስገባቱ ከድፍንነት፣ ካላዋቂነትና ውስጥ ከሚንተከተክ የለየለት ጎጠኝነት የሚነሳ ካልሆነ በስትቀር ሌላ ምክንያት ሊኖረው አይችልም። ምክንያቱም አቶ በረከት በትውልድ ኢትዮጵያዊ መሆኑን በሚከተለው መልኩ ማሳየት ስለሚቻል ነው። አቶ በረከት በተወለደበት ጊዜ ኤርትራ የኢትዮጵያ አካል ነበረች። በዚህ ወቅት እናቱም አባቱም ኢትዮጵያዊያን ነበሩ ማለት ነው። ይህ የሚያሳየው ደግሞ አቶ በረከት ሲወለድ ኢትዮጵያዊ ሆኖ አልነበረም ብሎ ለመከራከር የሚያስችል አንድ ጋት የሚያራምድ ማስረጃ ማቅረብ የማይቻል መሆኑን ነው። ኤርትራ ከኢትዮጵያ ተለይታ የራሷን መንግስት ስታቋቁምም አቶ በረከት ከኢትዮጵያዊ ዜግነቱ ወደ ኤርትራዊነት እንዳልቀየረ 101 % እርግጠኛ ሆኘ መመስከር እችላለሁ። አቶ ዮሃንስም ሊገነፍል የደረሰው የጎጠኛ አስተሳሰቡ እየተናነቀው ሊዋጥለት አልቻለም እንጅ በዚህ ረገድ ያለው እውነታ ይጠፋዋል ብየ አላስብም።

እንዲያውም ያሉ ተጨባጭ ማስረጃዎች ሁሉ የሚያሳዩት አቶ በረከት እንክት ያለ ኢትዮጵያዊ መሆኑን ነው። ለምን ቢባል አቶ በረከት ገና በለጋ እድሜው ለትግል ሲወጣ የኢህአፓ አባል ሆኖ እንጅ የሻዕቢያ አባል ሆኖ አልነበረም፤ ኢህአፓ ደግሞ ኢትዮጵያዊ እንጅ ኤርትራዊ ድርጅት ሆኖ አያቅም። ከዛም በኋላ የኢህዴን መስራችና አመራር ሆኖ ትግል ላይ ሲቆይ በሙሉ ኢትዮጵያዊነት ስሜት እንጅ የሻብዕያ ወይም የኤርትራ መንግስት ተወካይ ሆኖ ነው ሲባል አልሰማሁም። በኋላም በብአዴንና በኢህአዴግ ውስጥ በአመራርነት ሌት ከቀን ሲለፋና ሲማስን፤ በወቅቱ በነበረው የኢትዮ-ኢርትራ ጦርነት ወቅትም ከማንም በበለጠ እላይ እታች ሲል የነበረው በሙሉ ኢትዮጵያዊነት ስሜት እንጂ በኢርትራዊነት ወይም በሻብዕያ ወኪልነት አልነበረም። አቶ ዮሃንነስ እነዚህን ፍሬ ነገሮች ሊያፋልስ የሚችል አሳማኝ የሆነ ማስረጃ ከየትም ሊያመጣ አይችልም።እንዲያውም እኔ ያለኝ አሳማኝ መረጃ የሚያሳየው አቶ በረከት ስምዖን ባባቱ ወገን አያቱ የላስታ ሰው እንደሆኑ ነው። ከዚህ አንፃር ሲታይ አቶ ዮሃንስ የአቶ በረከትን ኢትዮጵያዊነት ሊክድ የሞከረበት መንገድ ፍፁም ፉርሽ ነው።

አሁን ደግሞ የአቶ ዮሃንስን ክስ (Allegation) ከማንነት ጋር አዛምደን እንመልከተው። የኢፌዴሪ ህገመንግስት ማንነትን ለመለየት ካስቀመጣቸው መመዘኛዎች ውስጥ ቋንቋ፣ ስነልቦና፣ ባህልና መልክአምድራዊ ትሥስር ዋና ዋናዎቹ ናቸው። አሁን አሁን ደግሞ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል በብሄር የተደራጁ ኢትዮጵያዊያን ማንነት በደም ይገኛል እያሉ ሊያሳምኑን እየሞከሩ ነው። ይሁንና በኢትዮጵያ ህገመንግስትም ይሁን በአለም አቀፍ ህጎችና አሰራሮች ደም የማንነት መገለጫ ነው ትብሎ አልሰፈረም፤ ሊሰፍርም አይገባውም። ምክንያቱም የሰው ማንነት በደም ይለያል የሚል የምርምር ውጤት እስካሁን የተገኘ አይመስለኝም። በዚያ ላይ የሰው ማንነት በግልፅም ይሁን በስውር ደም ውስጥ ተፅፎ ይገኛል የሚል ማስረጃ አይቸም ሰምቸም አላቅም።

ለማንኛውም ከቋንቋ አንፃር አቶ በረከትን ስንቃኘው ከአማርኛ ተናጋሪዎች በላይ አማርኛ ተናጋሪ እንደሆነ ነው የምናውቀው። መናገር ብቻም ሳይሆን እነ አቶ ዮሃንስ እና መሰሎቹ ያልሞከሩትን ሁለት መጽሃፍትና ሌሎች በርካታ የስልጠና ፅሁፎችን የፃፈው በአማርኛ ቋንቋ ነው። ስራ ቦታም ይሁን ቤቱ እንዲሁም ሌሎች አካባቢዎች ላይ ሰዎች ጋ የሚግባባው በአማርኛ ነው። ስለዚህ የአቶ በረከት የስራም ይሁን የመግባቢያ ቋንቋ አማርኛ መሆኑ የሚያጠራጥር አይደለም። ስነልቦናውን በተመለከተም አቶ በረከት ከአማራ ህዝብ ጋር የተቆራኘ እንጅ ሌላ ሆኖ አያቅም። እንደቀልድም ይሁን በቁምነገር ሲናገር የሚሰማው ጎንደሬ እንደሆነ እንጅ ኤርትራዊ እንደሆነ አይደለም። በባህሉና በወጉም ቢሆን አቶ በረከት ከጎንደር አማራነት ጋ የተቆራኘ እንጅ ሌላ ሆኖ አያቅም። በዚህ ረገድ በቻለው መጠን የጥምቀትን አመታዊ ክብረ በዓል የት እንደሚያሳልፍ ወይም ለማሳለፍ እንደሚፈልግ መጠየቅ ካላዋቂነት ከሚሰጥ ድምዳሜ ያድናል። መልክአምድራዊ ትስስርን በተመለከተም የአቶ በረከትን ጎንደር ከተማ ላይ መወለድና ለትግል እስኪወጣ ድረስ እዛው ማደግ የሚያፈርስ ማስረጃ ከየትም አይገኝም። ይህ ከሆነ ታዲያ በምን መመዘኛ ነው አቶ ዮሃንስና መሰሎቹ አቶ በረከት የብአዴን/ኢህአዴግ አባልና አመራር ሆኖ ለአማራና ለኢትዮጵያ ህዝብ መልፋቱና መድከሙን እንደጣልቃ ገብነት ቆጥረው ይቅርታ መጠየቅ አለበት እያሉ ሙሾ የሚያወርዱት? ያው የለየለት ጎጠኝነታቸው አልለቃቸው ብሎ እንጅ።

እንዲያው አልሆነም እንጅ አቶ በረከት ዜግነቱን ያገኘው በሂደት (Naturalization) ቢሆን ኖሮ በኢትዮጵያ ባጠቃላይና በአማራ ክልል በተለይ ለሰራው ስራ ይቅርታ መጠየቅ ይኖርበት ይሆን? ብሎ መጠየቅም ለተነሳው ጉዳይ አግባብነት ያለው ይመስለኛል። ይህም ቢሆን ግን ዋጋ ያለው መከራከሪያ ሆኖ ሊቀርብ የሚችል ጭብጥ አይደለም። ምክንያቱም በሂደትም ሆነ በትውልድ ዜግነት ያገኙ ሰዎች ዜጋ በሆኑበት አገር የሚደረግላቸው ጥበቃና የሚጎናፀፏቸው መብቶች እንዲሁም ዜጋ ለሆኑበት አገር የሚገቡት ግዴታ ምንም አይነት ልዩነት የለውም። በአጠቃላይ ከላይ ከተገለፁት ማብራሪያዎች አንፃር ሲታይ አቶ በረከት ለአማራና ለኢትዮጵያ ህዝብ ሲሰራ ጣልቃ ገብ ነበርና ይቅርታ ይጠይቅ የሚለው የአቶ ዮሃንስ ቧያለው ክስ ምንም አይነት ህጋዊ መሰረት የሌለው እንቶ ፈንቶ ሃሳብ ነው። አቶ በረከት መወቀስ ካለበትም እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ በትክክለኛ ማስረጃ ተደግፎ በቀረበ ጥፋት እንጅ ከጎጠኝነት በሚነሳ የጥቃት ክስ በማቅረብ ሊሆን እንደማይገባው አቶ ዮሃንስ ቢረዳው መልካም ነው እላለሁ።

 

 

 

Back to Front Page