Back to Front Page

አዲስ አበባ ብቻ ሳትሆን ኢትዮጵያም ባለአደራ ምክር ቤት ያስፈልጋታል

አዲስ አበባ ብቻ ሳትሆን ኢትዮጵያም ባለአደራ ምክር ቤት ያስፈልጋታል

ዶር. ዮሃንስ አበራ አየለ 4-5-19

በቪድዮ ምስል በተደገፈ ሪፓርት ላይ የጌዴዎ ተፈናቃይ ተወካዮች ደጋግመው ያነሱት አንድ ጥያቄ ነበር፦ "መንግስት አለ?" የሚል። መልሱ በጥያቄው ተመልሷል ብየ አስባለሁ። በመላ አገሪቱ ማንም ተራ ግለሰብ/ ቡድን ይሁን ባለስልጣን ያሰኘውን ሰርቶ ምንም ሳይጠየቅ የሚቀር ከሆነ፤ ጠያቂ/ከሳሽ ከመሆን ተጠያቂ/ተከሳሽ መሆን በቀለለበት ጊዜ፤ በየብሄሩ ቋንቋ የተሰየሙ የወጣት አጥፊ ቡድኖች እንደ ለውጥ ሃይል ሲቆጠሩና ሌላውም ይህን እያየ በ86 ቋንቋ የወጣት አሸባሪ ቡድኖች ተፈጥረው በህግ ጥላ ስር ህግ ሲያፈርሱ፤ መሪዎቹ ለውጡን ወደ ብሄር ድል ቀይረው ለዛው ብሄር ጥቅም ብቻ ዘላቂ አወቃቀር ሲያመቻቹ፣ ቀሪውን ህዝብ ባይተዋርና ባላንጣ አድርገው ግራ ሲያጋቡት፤ ሚድያው ተበታትና ከግራቪቲ ህግ እንደወጣች ፕላኔት በየአቅጣጫው፣ በግብታዊነትና በአደገኛ ሁኔታ ሲምዘገዘግ፤ ፌደራል መንግስት ጥርስ የሌለው አምበሳ ሆኖ ወደ ክልሎች በማይዘልቀው ሚድያ አገር ሲያስተዳድር፤ መሪዎቹ ከጋዜጠኞች፣ ከአክቲቪስቶች፣ ከተቃዋሚ ሆነ ከደጋፊ ፓርቲዎች የሚቀርብባቸውን ትችት በማስተባበል ላይ ተጠምደው የየእለት ስራ ላይ ብቻ በማተኮራቸው፤ ችግር አለ ብሎ ከማመንና በጋራ ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ እንደተለመደው "ለውጡ ያልተዋጠላቸው ሰዎች ሴራ ነው"፣ "ሽግግር ስለሆነ ገና ለስምንት ወር ያህል ብጥብጡ ይቀጥላል" የሚሉ "አይዞኝ ልክ ነኝ" እና "አይዟችሁ አትስጉ" አይነት ማዘናጊያዎች በአደባባይ ሲናገሩ ሳይና ስሰማ የጌዴዎ ተፈናቃዮች ጥያቄ የኔም ጥያቄ ይሆናል።

አዲስ አበባ የራስዋ ፓሊስ ሃይል የላትም፣ ራስዋ የመረጠችው አስተዳዳሪ የላትም። ስሟ ግን በራስዋ ቻርተርና በዲሞክራሲያዊ መርህ የምትተዳደር ከተማ ናት። ይቺ ከተማ ተቆርቁራ መቶ አመት እስኪሆናት ድረስ በዙሪያዋ የነበረው ሸዋ የሚባል ጠቅላይ ግዛት/ ክፍለሃገር ነበር እንጂ ኦሮሚያ የሚባል ክልል አልነበረም። ይህ በብሄር ፓለቲካ የተፈጠረው ክልል መጠየቅ ካለበት የሚጠይቀው ክልል ሆኖ ከተመሰረተ ጀምሮ ባሉት 25 አመታት ነው። ሰማንያ ከመቶ በሆነው የአዲስ አበባ እድሜ በዙሪያዋ የነበረው ሸዋ አማሮች፣ ኦሮሞዎች፣ ጉራጌዎች፣ ከምባቶች፣ ሃድያዎች የተካተቱበት ጠቅላይ ግዛት/ ክፍለሃገር ነበር።  ከሸዋም ቢሆን አዲስ አበባን የበለጠ የሚመለከተው መናገሻ ሲባል የነበረው አውራጃ ነው። ይህ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ያለችበት ተብሎ የተሰየመው ግዛት ከመላ አትዮጵያ የመጡ በየትናንሽ ከተሞቹ የሰፈሩበት ነበር።  አውስትራልያ ርእሰ ከተማዋ የሆነችው ካንቤራ የምትገኝበት "ካቲታል ተሪተሪ" የሚባል የራስዋ ግዛት አላት። ይህ ማንም ስቴት የኔ የሚለው አይደለም። ስቴቶች የየራሳቸው የሆኑ እንደ ሲድኒ፣ ሜልቦርን ያሉ ታላላቅ ከተሞች አሏቸው እንጂ መላው አውስትራልያ የደከመበትን የኔ ነው ብለው ለመቀማት አልሞከሩም።

Videos From Around The World

በአዲስ አበባ አንድ ክፍለ ዘመን እድሜዋ ወደ ከተማዋ እየጎረፈ መኖሪያ ያደረጋት ከመላ ኢትዮጵያ የመጣ ህዝብ ነው። "አዲስ አበባ ቤቴ" የሚለው የአለማየሁ ዘፈን የኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙር ነው። ስለዚህ አዲስ አበባ የኗሪዎቿ መሆንዋ ለጥያቄነት የሚበቃ አይደለም። የዚህ ባለቤትነት መገለጫው የከተማው ህዝብ በነፃ ምርጫ የሚመሠርተው አመራር ነው። አስተዳዳሪና ህግ አስከባሪ ከውጭ ከተመደበለት ግን ከቅኝ አገዛዝ የተለየ አይሆንም። ለዚህም ነፃ አውጪ ያስፈልገዋል። ወደ አንድ ብሄር ፓለቲካ ፍላጎት አድልቶ የስልጣን ሽኩቻ መልክ እንዳይዝ በመጠንቀቅና አሳታፊ እንዲሆን በማድረግ የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክር ቤት የአዲስ አበባን ህዝብ ነፃነት ሊያስከብር ይችላል። እንቅስቃሴው የተቀደሰ አላማ ቢኖረውም ለሰላማዊ መንገድ እንጂ ለመፋጠጥ እድል መስጠት የለበትም። ይህን ካደረገ ግን ለተቃራኒው ወገን የሚፈልገውን አጋጣሚ መፍጠር ይሆናል።

ስለ አዲስ አበባ ባለቤትነት የኦሮሞዎች ጥያቄ ጉዳይ የሚያስገርሙኝ ነገሮች አሉ። አንደኛ የኔ ናት እያለ ያለው የአዲስ አበባ ዙርያ ኦሮሞ ሳይሆን ከ500 ኪሜ በላይ ከአዲስ አበባ የሚርቀው የሃረር የቦረናና የወለጋ ኦሮሞም ጭምር መሆኑ ነው። ተመሳሳይ ርቀት ያለው የትግራይ፣ የሱማሌ፣ የጋምቤላ፣ የጎንደር ህዝብ ተመሳሳይ ጥያቄ ያላቀረበው አዲስ አበባ ዙርያ ካሉት ኦሮሞዎች ጋር ቋንቋው አንድ ስላልሆነ ነው? የባለቤትነት መብት የሚወሰነው በቋንቋ መመሳሰል ሳይሆን ሌሎች ብዙ የህግ መለኪያዎች አሉ። እንዲያውም ሌሎቹ ብሄሮች ከዙሪያው ሳይሆን ከተማው ውስጥ በመኖራቸው የባለቤትነት ጥያቄ ቢያቀርቡ ለሎጁክ የተጠጋ ይሆናል።

ጥያቄው አዲስ አበባ ድሮ ኗሪ የነበሩት ማህበረሰቦችን አፈናቅላ ተቆረቆረች ከሆነ የባለቤትነት ጥያቄ ማቅረብ ያለባቸው የዛ ማህበረሰብ ልጆች ወይንም የልጅ ልጆች ናቸው እንጂ አዲስ አበባ የት እንደምትገኝ የማያውቀው የባሌ-ጎሮ ዙርያ ገበሬም ጭምር አይደለም። በአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ተቃውመው ሲያምፁ የነበሩት የአምቦ ወጣቶች ነበሩ፤ መቶ ኪ.ሜ. ርቀው!

አዲስ አበባ ሳትመሠረት ከቦታው ነበሩ የተባሉት የኦሮሞ ማህበረ ሰብ አባላት የተፈናቀሉት ያለ ክፍያ ከነበረ ወራሾቻቸው ካሳ ከነወለዱ በፍርድ ቤት ተከራክረው የማግኘት መብት አላቸው። ያኔ በነበረው ዋጋ በስምምነት ወይንም ትክ ቦታ ተሰጥቷቸው ከነበረ ጉዳዩ የተዘጋ ይሆናል። በህግ ሳይሆን በጉልበት የሚሆነው ነገር መስመሩ ሌላ ነውና በፅሁፌ አላስተናግደውም። ታላቋ የአለም ንግድ ማእከል የሆነችው ኒውዮርክ የተቆረቆረችው ማንሃታን በምትባል፣ የሌናፔ ቀይ ህንድ ጎሳ መኖርያ በነበረችው ደሴት ላይ ነው። ደሴቷ ከሌናፔ ጎሳ በዳች ኩባንይ የተገዛችው በ17ኛው ምእተአመት በ60 ዳች ጊልደር ነበር (አሁን 1000 ዶላር)። የሌናፔ ህንዶች አሁን ብድግ ብለው "ኒውዮርክ የኛ ናትና አስረክቡን" አሉ እንበል። ይህ ጥያቄ የኒውዮርክ ኗሪዎችን ከቢላደን ጥቃት የበለጠ ሳያደነግጣቸውና ሳያስገርማቸው ይቀራል? የመላ አሜሪካ ብቻ ሳይሆን የአለም ህዝብ ንብረት የሆነችው ኒውዮርክ ሌሎች ሚልዮኖች በእንግድነት የሚኖሩባት የሌናፔ ንብረት ትሆናለች ማለት ነው። ሎጂክ በሳይበር ኤጅ ወደኋላ ሲመለስ!

የአሜሪካ ባላባቶች ነን የሚሉት ከአውሮፓ የ"መጡባቸው" ነጭ "ስደተኞች"ን ለማገድ ያላደረጉት ነገር የለም። የዘነጉት ነገር ግን አሜሪካ የነሱም እንዳልሆነች ነው። በሰው ልጅ አዝጋሚ ለውጥ የምናምን ከሆነ ነባር ነን የሚሉት ቀይ ህንዶች በእስያ አቋርጠው በአላስካ በኩል አሜሪካን እስከ አርጀንቲና ጫፍ ድረስ የሞሏት ስደተኞች የአፋርዋ የሉሲ ዘመዶች ናቸው። የሚመርም ቢሆን ታሪካዊ ሃቅ አምኖ መቀበል የታላቅ ህዝብ ባህርይ ነው። ኦሮሞዎች አዲስ አበባ ካለችበት መጥተው የሰፈሩት ከ500 አመት በፊት ነበር። ይህ ቦታ ሰው ያልነበረበት ባዶ ስፍራ አልነበረም። አክሱም እኮ ከደቡብ አረብ ፈልሰው በመጡ ህዝቦች የተፈጠረች ናት። ነባሮቹ ጥቁሮች የኛ ስልጣኔ ነው ሲሉ አይሰማም። የርስት ጭቅጭቅ ታሪክ እያደረገ ባለውና አለምን ትንሽ መንደር ለማድረግ የተጀመረው የማይቀለበስ የግሎባላይዜሽን ሂደት ውስጥ ወደኋላ ተመልሶ በ"ነበረ አልነበረ" ጭቅጭቅ የልማት ጊዜን ማባከን ፋይዳ ቢስ ነው።

አዲስ አበባ ቆሻሻዋን የምትጥልባቸው፣ወሃ የምትቀዳባቸው፣ ለአሸዋና ድንጋይ መሬታቸውን የምትቆፍርባቸው ማህበረሰቦች ለይታ በማወቅ በመመዝገብና የጋራ ቋሚ ኮሚቴ በማቋቋም ምክክርም ድርድርም ልዩ ጥቅም አሰጣጥም ላይ የምትነጋገርበት ህጋዊ ስርአት የመፍጠር ህጋዊ ግዴታ አለባት።  ይህ ጉዳይ በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉት ግለሰቦችና የአዲስ አበባ አስተዳደር ጉዳይ እንጂ የኦሮሚያ ክልል ጉዳይ አይደለም።  ድንጋይ ለማውጣት የእርሻ መሬቱ ከተቆፈረበት የሱሉልታ ገበሬ እኩል የጭሮ ምዕራብ ሃረርጌ ገበሬ ከአዲስ አበባ ልዩ ጥቅም የሚጠይቅበት ሎጂክ የት አገር የተቀመረ ነው? የመስኖ መሬቴ የለገዳዲ ውሃ ተኝቶበታል ብሎ ከአዲስ አበባ መንግስት ጋር የሚደራደረው እኮ ግለሰብ እንጂ ቡድን ወይንም ብሄር አይደለም። የቡድን መብትና የግለሰብ መብት ድንበሩ ግልፅ ካልሆነ የፓለቲካ መጠቀሚያ ይሆናል። ይህ መላቅጡ የጠፋበት የ"የኔ ነው" ጥያቄን ለማስፈፀም አቅም ያገኙ ሰዎች የከተማዋን ስልጣን ከጨበጡ ማርከሻ መፍትሄ መፈለግ ያለበት ኗሪው ተደራጅቶ የራሱን መብት በማስከበር ነው።

ልክ እንደ አዲስ አበባ ኢትዮጵያም በመንግስት ሳይሆን በግለሰቦችና በቡድኖች እጅ ነው ያለችው ብየ መከራከር እችላለሁ። ከመግቢያየ ላይ የዘረዘርኳቸው ችግሮች የተፈጠሩት የኢህአዴግ መንግስት አለ ወይስ የለም የሚለው ጥያቄ መልሱ "አዎ"ም "አይደለም"ም ስለሆነ ነው። በአንድ በኩል አገሪቱ ኢህአዲግ ሊቀመንበር አድርጎ በመረጠው ጠቅላይ ሚኒስትር እየተመራች ነው በሚል ኢትዮጵያ በኢህአዲግ የሚመራ መንግስት አላት ይባላል። በሌላ በኩል ደግሞ ኢህአዴግ የሚባል መንግስት የህወሓት የሽፋን ቅፅል ስም ነበር፣። የህወሓት/ ኢህአዲግ መንግስት ነበር አገሪቱን ለ27 አመት ያስተዳደረው አሁን ከስልጣን ወርዷል ተብሎ አመት ሙሉ ተጨፍሯል። ግራ የሚያጋባው ነገር ኢህአዲግ ከስልጣን ተባረረ እያለ የሚጨፍረው ራሱ ኢህአዲግ መሆኑ ነው! ከስልጣን የወረደ መንግስት አገሪቱን እያስተዳደረ ነው የሚለው የተሳከረ አባባል አገሪቱ መንግስት የላትም ከማለት የተሻለ አማርኛ አይደለም። በአሁኑ ጊዜ መንግስት አለ ከተባለ በአንድ ግለሰብ አከራካሪ ስብእና ላይ የተመሠረተ "አውቶክራሲ" ነው። ከመሪው ጀምሮ ግለሰቦች ሆኑ ቡድኖች የየራሳችን ነው ለሚሉት የ86 ብሄር የቤት ስራ በመስራት ላይ በተሰማሩባት አገር ማእከላዊ መንግስት አለ እንዴት ይባላል? ቢሮክራሲው ተረጋግቶ ስራውን ስለቀጠለ ብቻ የተረጋጋ መንግስት አለ አያሰኝም። ይህ ነገር ሰውን የሚያዘናጋ ነው። ቢሮክራሲ የሚፈርሰው በዝግታና በርግጠኝነት ነው፤ የመንግስት ሳይሆን የሃገር መፍረስ እውን ሲሆን። ስለዚህ ከመንግስት መፍረስ ወደ መጨረሻው የቢሮክራሲ መፍረስ ሳንሸጋገር ከአገሪቱ ታላላቅ ሰዎች የተውጣጡ፣ ከፓርቲና ብሄር ፓለቲካ ነፃ ሆነው ኢትዮጵያን ከዚህ መቅሰፍት አውጥተው ታሪክ የሚሰሩ ሰዎች ያሉበት የባለአደራ ምክር ቤት ተቋቁሞ አገሪቱን ወደ ምርጫና ከምርጫ በኋላም እስክትረጋጋ ድረስ የሚቆይ ቢሆን። ይህ ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትሩን የሚተካ አይደለም። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ተግባር ቴክኒካዊ የሆነ የማኔጅመንት ስራ ነው። የኢትዮጵያ ባለአደራ ምክር ቤቱ ሃላፊነት ግን አገርን ከመበታተን አደጋ የማዳን ታሪካዊ አደራ ነው። ታከለ ኡማ የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክር ቤትን እንደተቀናቃኝ ሳይቆጥሩ ድጋፍ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ሁሉ ዶር. አብይም ለኢትዮጵያ ባለአደራ ምክር ቤት ከምስረታ እስከ ስኬት ድረስ ከጣልቃ ገብነት የተቆጠበ ድጋፍ እንዲሰጡ ይጠበቃል።

ይህን አገር የማዳን ስራ መስራት ተስኖን ኢትዮጵያ የተበታተነች እንደሆነ ይችን ጥንታዊትና የነፃነት ፋና የሆነችውን የአለም ህዝብ ቅርስ (ኢትዮጵያ) ብትፈርስ የአለም ታሪክ ይቅር አይለንም። ተበታትነንም 80 መንግስታት ሆነን በሰላም እንኖራለን ማለት ዘበት ነው። ኢትዮጵያ ሲያልቅላት ለመበተን ያሰፈሰፈ ሁሉ አብሮ እንደሚያልቅለት መገንዘብ ይኖርበታል። ጎርፍ የሚወስደው እያዝናና ነው፤ እየሆንን ያለነውም ይኸው ነው። ታላቁ እንግሊዛዊ ደራሲ ዶር. ሳሙኤል ጆንሰን "ብሄረተኝነት የወስላቶች የመጨረሻ ምሽግ ነው" ብሏል። ተነሱ! ይህን ቆሻሻ ምሽግ እናፍርስ! የተሻለች ኢትዮጵያ ለመጪው ትውልድ እናውርስ! አሁን ከእለት ጉርሳችን እየቀነስን የምናስተምራቸው ልጆቻችን በጥብጠናት በምናልፈው አገር ውስጥ እንዴት ሆነው ሊኖሩ እንደሚችሉ ለደቂቃም ቢሆን እናስብ።

ባለፈው፣ መስቀል አደባባይ ላይ ቀይ መብራት ይዞኝ ቆሜ ሳለ የለመድኩት የኛው አገር ጎዳና ተዳዳሪ ሳይሆን የስምንት አመት እድሜ የሚሆነው አረብ ህፃን ልጅ የመለመኛ ፅሁፍ ይዞ ወደ መኪናየ መስኮት ተጠጋ። የሶርያ ስደተኛ መሆኑ ደመነብሴ ነገረኝ። ወዲያው መብራት ስለቀየረ በፍጥነት ማሽከርከር ነበረብኝና ወደፊት በረርኩ። አይምሮየ ግን ከኔ ጋር አልነበረም። ይህ ትምህርት ቤት መዋል የነበረበት ልጅ ወላጆቹ ወይንም ወንድሞቹ ወይንም ለህፃናት ሃላፊነት ያለበት መንግስት ለቀጣዩ ትውልድ ሳይጨነቁ ስለራሳቸው ስልጣን መቀማማት ብቻ እያሰቡ መጪውን ትውልድ መና አደረጉት። እኛ እየሰራን ያለነው ከዚህ በምን ይለያል? "ኢትዮጵያ የሚጠብቃት አምላክ አላት" የሚለውን አጉል ፈሊጥ እየደጋገሙ መዝናናት በእሳት መጫወት ነው። ሶርያን የሚጠብቅ አምላክ የለም? እንዲያው በድንጋይና እንጨት ስናምን ኖረን ለኛ የአምላክ መኖር ያሳወቁን ከሶርያ የመጡ ሚስያናውያን አይደሉ?  ምርጥ የእግዚአብሆር ልጆች ስለሆንን ምንም ብንቀብጥ ለክፉ አይሰጠንም እያሉ እንደ ስለት ልጅ መመፃደቅ አደገኛ ነው። አምላክ የሚረዳው መጀመሪያ ራሳቸውን የሚረዱትን ነው። ከታች አምላክ ሸራ ወጥሮ ይቀበለኛል ብሎ ከፎቅ መዝለል ቂልነት ነው።

Back to Front Page