Back to Front Page

ኢትዮጲያ ይገባታል ፤ ወሳኙ ሽልማት ግን የህዝቦቿ ይሁንታ ነው

ኢትዮጲያ ይገባታል ፤ ወሳኙ ሽልማት ግን የህዝቦቿ ይሁንታ ነው

አበበ ተ/ሃይማኖት (ሜ/ጄ)

11-03-19

በመጀመሪያ ለመላው ኢትዮጵያዊያን አገራችን የኖቬል ሽልማት አሸናፊ በመሆንዋ እንኳን ደስ አለን ለማለት እወዳለሁ፡፡ ዘግይቷል የሚባል ካልሆነ ለአገራችን የሚበዛበት አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ምድረ ቀደምት (The land of origin) ፤ ነፃነትዋን ጠብቃ የኖረች፤ አፍሪካውያን ወንድሞቻችን ነፃ እንዲወጡ ቁልፍ ሚና የተወጣች፤ ፈጣን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ያረጋገጠች፤ በህዝብ ብዛት ከአፍሪካ ሁለተኛ፤ በቀይባህር ክልል ጠንካራ ከሚባሉት አገራት ስትሆን በዓለም የሰላም ማስከበር እንቅስቃሴ ውስጥ በሰው ሃይል ከፍተኛውን አስተዋፅኦ ያላት ሀገር ያልተሸለመች ማን ይሸለማል? ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር አብይ አህመድ የዚች ታላቅ ሀገር መሪ በመሆናቸው ባገኙት ሽልማት እንኳን ደስ አለዎት ማለትም ይገባል፡፡እንደ ሀገር ያገኘነውን ክብር በተሟላ መንገድ ሳናጣጥም እላይ የተገለፀውን በመርሳት በውስጥ ፖለቲካዊ ትኩሳት ጠቅላይ ሚኒስቴራችን ይገባቸዋል አይገባቸውም እያልን ሰጣ ገባ ውስጥ መግባታችን እጅጉን ይገርመኛል፡፡

ለቀድሞው የአሜሪካን ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ የተሰጠው አወዛጋቢ የኖቬል ሰላም ሽልማት ለልእለ ኃያሏ ሀገር መሪ እንደማነቃቂያ ተደርጎ ነበር የተወሰደው፡፡ በአሜሪካ የሚደረግ ትንሽም ለውጥ በዓለም ሊኖረው የሚችለው ትልቅ ትርጉም ያገናዘበ ይመስላል ፡፡ ኢትዮጵያችን ይገባታል ካልን በመሪዋ በኩል የተገኘውን ማነቃቅያ መሰረት አድርገን የሀገራችን ውስጣዊ እድሎች ተጠቅመን ያሉብንን ዘርፈ ብዙ ችግሮች እየቀረፍን ሀገራችን ወደተሟላ ሰላም ልማትና ዲሞክራሲ እንዴት ትመራ ነው ዋናው መወያያ አጀንዳ መሆን ያለበት፡፡ ድህነትነና ፀረ- ድሞክራሲ እያሉ ትምክህት እና ጠባብነት ናቸው መሰረታዊ ችግሮቻችን እያሉ ህዝቦችን ለማታለል ሞሞከር ትተን ዲሞክራሲን በዘላቂነት ለመገንባት ሰላምን እንዴት ማረጋገጥ አንችላለን የሚለውን አንኳር አጀንዳ ማድረግ ነው የሚጠበቅብን፡፡

ማጣጣም ስንል ከጥንት ጀምሮ የተገኙትን የሃገራችንን የኢትዮጵያ መንፈስ የሚያንፀባረቁትን ድሎች ታሳቢ ባደረገ መልኩ አሁን ያለውን ዴሞክራሲያዊ ሕገ-መንግስት (ካስፈለገ መሻሻል እንደተጠበቀ ሆኖ) እሴቶቹ፤ፖለቲካዊ ሂደቱና ፖለቲካዊ መዋቅሮቹ በሚገባ ተገንዝበን ለተግበራዊነቱ እንዴት መረባረብ እንዳለብን ነው መሆን ያለበት፡፡ አሁን ያለው ቀወስ ከሕገ-መንግሰት ውጭ ለመፍታት መሞከር ወደ እማያበራ ጦርነት ሊያስገባን ይችላል፡፡

ዴሞክራሲያዊ ሕገ-መንግስታችን እናጣጥመው የጥንካሪያችን መሰረት ስለሆነ

ለዚህ ፅሁፍ ሲባል፡- ሕገ-መንግስታዊነት ማለት ስልጣን እንዴት እንደሚሰጥ፤ እንዴት እንደሚከፋፈል እና እንደሚገደብ የያዘ ስርዓት ማለት ነው፡፡ ዴሞክራሲ፡- በህዝብ የሚወሰን መንግስት ነው (Government by the people) ሕገ-መንግስታዊ ዴሞክራሲ፡- ስንል የህዝቦች የተሟላ ሰብዓዊ መብቶች ዕውቅና በመስጠት ነፃና ፍትሓዊ ምርጫ ጨምሮ በቀጥታ በሚያደርጉት ተሳትፎ የህዝብ ወሳኝነታቸውን የሚያረጋግጡበት ስርዓት ነው፡፡

ሊህቃን የመሪነት ሚና ቢኖራቸውም የህዝቦች ድምፅ በተሟላ የሚሰማበት ነው ስንል ህዝቦች በየወቅቱ የሚኖራቸው ግንዛቤ መሰረት ሰብአዊ መብቶቻቸውን ከጥቅሞቻቸውና እሴቶቻቸው አያይዘው የሚያሰሙት ድምፅ ወሳኝነት ነው፡፡ ሰብአዊ መብቶች አለም አቀፋዊ ይዘት ያላቸውና የማይከፋፈሉ ቢሆኑም እንደ የህብረተሰቡ እሴቶች እና ቁሳዊ ጥቅሞች ወደ ተግባር ሲውሉ ግን በተለያየ መንገድ ይሆናል፡፡ በፖለቲካዊ፤ማህበረ-ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ ተጨባጭ ሁኔታዎች ሰብአዊ መብቶች ጎልተው ዕውቅና የሚገለፁበት ፖለቲካ ማጠንጠኛዎች ሊለያዩ ይችላሉ፡፡ ሰብአዊ መብቶች በባዶ አካባቢ የሚረጋገጡ አይደሉም ፡፡በአንድ አገር ውስጥ ባሉት ህዝቦች ቁሳዊ ጥቅሞችና እሴቶች መሰረት ያደረጉ ናቸው፡፡ እንደ ኢትዮጵያዊ ዜጋ፤እንደ ብሔር አና ሌሎች ማንነቶችን መሠረተዊ ጥቅሞችና እሴቶች እንደ መሆን ያለበት ግቦች ሳይሆን እንደ መብቶች የተቀበለ ሕገ-መንግሰት መጠበቁ ተገቢ ነው፡፡

ሕገ-መንግሰታዊ ስርዓት በሶስት ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡ የመፅደቁ ሂደት፡ ይዘቱና ትግበራው፡፡ በማናቸውም አገር የመፅደቁ ሂደት ችግር የሌለበትና በሰነድ የተዘጋጀው ሕገ-መንግስትና በትግበራ ክፍተት የሌለበት ያለ አይመስለኝም፡፡ በትግበራ ያለው ክፍተት ለመግለፅ (Formal constitution and living constitution) ብለው ይጠሩታል፡፡ በኛ ሃገር ኋላቀር ፖለቲካዊ ባህል ባለበት መካከለኛ መደብ ጠንካራ ባልሆነበት ሁኔታ እጅግ ዘመናዊና ዴሞክራሲያዊ ሕገ-መንግስት በመተግበር ላይ ክፍተቱ ሕገ-መንግስት አለወይ እስኪባል ድረስ ነበር፡፡ ለማሻሻል ብንሞክርም እንኳን በአጭር ጊዜ ዴሞክራሲያዊ ሃገሮች የደረሱበት የትግበራ ደረጃ ልንደርስ አንችልም፡፡ ፖለቲካዊ ባህሉ፤ ልፍስፍስ ተቋሞች ወዘተ ባለበት ከኛ ጋር እያንዣበበ የሚኖረው፡፡ ደረጃ በደረጃ ግን ማሻሻል አለብን፡፡ ሕገ-መንግስቱና ትግበራው ለየብቻው ማየቱ ተገቢ ነው፡፡ ሕገ-መንግስቱ በየጊዜው ሊሻሻል ቢችልም ለብዙ አስር ዓመታት ፕሮግራም በመሆኑ በተግባር ባለው ችግር ብቻ ልንመዝነው አንችልም፡፡

ሕገ-መንግሰቱ በተግባር አለ ወይስ የለም እሰኪባል ድረስ በእጅጉ ስለተናደ ይህን ለማስተካከል ህዝቦች በሰላማዊ መንገድ ታግለው ስላልቻሉ ነው ወደ አመፅ ያመሩት፡፡ የመፅደቁ ሂደትም በጣም አከራካሪ ነው፡፡ አንዳንድ ሊህቃን ካልተተገበረ ምን ዋጋ አለው በሚል ለይዘቱ ብዙ ትረጉም አይሰጡትም፡፡ እንደ አገር ለመቀጠል አንድ የሕጎች የበላይ ሕግ ያስፈልገናል፡፡ በእጃችን ያለውን ሕገ-መንግሰት የሚሻሻል አንቀፆች ካሉት እየተወያየን ለኢትዮጵያ ህዝቦች አቅርበን ሰላማችን ማስጠበቅ፤ልማታችንን ማስቀጠል ይኖርብናል፡፡ በመፅደቁ ሂደትና በትግበራ የነበሩት ክፍተቶች ለማረም ዕድል ይሰጠናል፡፡ በኔ አመለካከት የኢፌዲሪ ሕገ-መንግስት ሠፊ (comrehensive) እና ተራማጅ ነው፡፡ ሦስት ትውልድ ሰብአዊ መብቶች ያካተተ በመሆን ከአሜሪካው ዓይነት ሕገ-መንግስት ስናወዳድረው በሁለት ትውልድ የላቀ ነው፡፡ ሕገ-መንግስታችን እንደማናቸውም የበላይ ዴሞክራሲያዊ ሕግ ሦስት ክፍሎች አሉት፡፡ የዴሞክራሲ እሴቶች፤ፖለቲካዊ ሂደቶችና ፖለቲካዊ መዋቅሮች ናቸው፡፡

የዴሞክራሲ እሴቶች ስንል

የሚያነቃቃ ሽልማትም ሆነ በሀገራችን እየተካሄደ ያለው ለውጥ ትልቅ ድረሻ መሆን ያለበት በሕገመንግሰታችን ውስጥ የሰፈሩ እና በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌ እውቅና የተሰጣቸውን ዋና ዋና እሴቶች አጉልቶ ማውጣት ነው፡፡ ከዚህ አንፃር መሠረታዊ የሚባሉት እንደሚከተለው አቀርበዋለህ፡፡

ሀ) የህዝብ ፈቃድ/መስማማት (Popular consent) ፍትሃዊ መንግስት ስልጣን ከሚያስተዳድረው ህዝብ ፈቃድና ስምምነት ውጪ ሊሆን አይችልም፡፡ ህዝቦች በቀጥታታም ይሁን በተወካዮቻቸው ውሳኔዎች ላይ የሚሳተፉበት እሴት ነው፡፡ ለህዝቦች ፈቃድ ዝግጁ መሆን ማለት ህዝቦች ባልፈለጉበት ጊዜ ከስልጣን መውረድን የሚያካትት ነው፡፡ የስልጣን ምንጭ ህዝቦች ናቸው ከሚል አስሳሰብ፡፡

በአብዛኛው ዴሞክራሲዊ አገሮች በተወካይ የሚደረግ ፈቃድ ላይ የሚመሰረት ቢሆንም እንደ ሲውዘርላንድ ያሉ አገሮች ግን ቀጥተኛ (direct democracy) እና ተወካይ (Representative democracy) አዋህደው የህዝብ ፈቃድ መሰረት ያደረገ ዲሞክራሲን ወደ ተሻለ ጫፍ ይወስዱታል፡፡ የኤፌድሪ ሕገ-መንግስት በዚህ ረገድ በዋናነት የተወካይ ዴሞክራሲን የሚከተል በመሆኑ የህዝብ ወሳኝነትትን የበለጠ ለማረጋገጥ ቀጥተኛ ዴሞክራሲ እንዲኖር ማድረግ ያሰፈልጋል፡፡ በወሳኝ ጉዳዮች ለምሳሌ እንደ ሕገ-መንግሰት ማሻሻል ዓይነት ጅምረን በቀጣይነት ማሰፋትና ማጥለቅ ይኖርብናል፡፡

ለ) ክብር ለግለሰብና ቡድኖች

የመጀመሪያው የሰብአዊ መብት ትውልድ ትኩረቱ ግለሰብ ላይ ነው፡፡ ግለሰቡ ትክክለኛ (Common sense) ፤ ምክንያታዊ አስተሳሰብና ፍትሃዊነት እምቅ ዓቅም አለው ተብሎ ስለሚገመትና ይኸው አቅም የመንግስታት የስልጣን ተቀባይነት ምንጭ በመሆኑ ነው፡፡

የኤፌዴሪ ሕገ-መንግስት የግለሰብ ክብር በተሟላ ተቀብሎ ከዛ በላይ ግን የግለሰብ የላቀ መገለጫዎች የሆነው የሦስተኛው ትውልድ የሆነው የቡድን በተለይ የብሔር ክብር ይጨምራል፡፡ የግለሰብ እና የብሔር ክብር ውጥረት ቢኖሩም ለሁለቱም እውቅና በመስጠት እና ተግባራዊ በማድረግ ነው የሰው ልጅ መብቶች የሚረጋገጠው ይላል፡፡ የቡድኖች መብት ሳይረጋገጥ የግለሰብ መብት በተሟላ አይረጋገጥም ከሚል የሚነሳ ነው፡፡ በኔ አመለካከት በምዕራባዊያን ያለው ቀውስ ከዚህ በሚመነጭ የእድል እኩልነት፤የግልና የቡድን ነፃነት የተሳሳተ አቅጣጫ በዋናነት ለናጠጡ ሃብታሞች መቆሙ ነው፡፡ እንደነ ሲውዘርላንድ ያሉ አገሮች ይህን ለማሰተካከል ስለሚሞክሩ በተነፃፃረ የተሻለ መረጋጋት ይታይባቸዋል፡፡

ሐ) የእድል እኩልነት (Equality of opportunity)

የግለሰብ ክብር የሚጎለብትበት እንዱ የዴሞክራሲ እሴት የሆነው እኩልነት ነው፡፡ ሁሉም ሰብአዊ ፍጡራን እኩል ነው የተፈጠሩት እኩል በመፈጠራቸው ምክንያት በተፈጥሮ (inherent) ና የማይገሰሱ መብቶች ይኖረዋል የሚል ነው የመጀመሪያ ትውልድ ሰብአዊ መብት አስተሳሰብ ፡፡ነገር ግን

ሰው በመሆናቸው እኩል ተፈጠሩ ቢባሉም ገና ከመወለዳቸው በፊት የአእምሮ የአካል ልዩነት እንዲኖራቸው እየተደረገ ነው፡፡ የተሸለ ኑሮና አስተሳሰብ ያለው ቤተሰብና ከድሃ በመሃይምነት የተዘፈቀ ቤተሰብ የሚወለድ በእናቱ አመጋገብ፤ እረፍት፤ ጤና ወ.ዘ.ተ. ምክንያት ህፃናት እኩል ዓቅም ይዘው አይወለዱም፡፡ እኩል ቢወለዱም እንኳን የሚቀበላቸው ድባብ የተለያየ ነው፡፡ አሁንም በምግብ፤ ጤና፤ አለባበስ ወ.ዘ.ተ. ከአደጉ በኋላ የሚያገኙት የትምህርት ብቃት (quality) ይህን አልፈው እንኳን የስራ እድልና የማደግ እድል እኩል አይሆንም፡፡ በዚህ ምክንያት የግለሰብ ክብር ለመጠበቅ ፖለቲካዊ እኩልነት ብቻ በቂ ስለማይሆንና ለድሃው ተጨማሪ መብት ካልተረጋገጠ የእውነት ፖለቲካዊ እኩልነት ስለማይኖር ነው የማህበራዊ፤ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ መብቶች አውቅና እንዲሰጣቸው የተደረገው፡፡ ዓለም አቀፍ ስምምነት የማህበራዊ፤ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ መብቶች የተባበሩት መንግስታት እ፣አ፣አ 1966 ተቀበለ፡፡ ፍትሓዊና በተመቻቸ ሁኔታ ስራ የማግኘትን፤ማህበራዊ ደህንነትን፤በቂ ምግብ፤ልብስና መጠልያ ጨምሮ ደረጃው የጠበቀ አኗኗርን፤ጤናና ትምህርትን የሚያጠቃልል መብቶች ይዟል፡፡ 71 አገሮች ሰያፀድቁት በሰብዓዊ መብቶች የምትመፃደቀው አሜሪካ፤ ከአሜሪካ ዴሞክራሲ ወዲያ የሚሉ ኢትዮጵያዊን አምላኪዎቿ በሚያሰፍር ሁኔታ እሰከ አሁን አላፀደቀችም፡፡ እ፤አ፤አ 1979 በፕሬዚደነት ካርተር ቢፈረምም፤ የሬፓቢሊካን ፕሬዚዳንቶች እንደ እነ ሬጋንና ቡሽ የመሰሰሉት የማህበራዊ፤ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ መብቶች ሳይሆኑ እንደ ማህበራዊ ግቦች የሚወሰዱ እንጂ አስገደጅ በሕግ የሚደነገጉ መብቶች አይደሉም በሚል በአንድ በኩል ዴሞክራቶች ደግሞ መብቶች ብለው ቢቀበሉም በየጊዜው ለሚያገጥማቸው ጊዜያዊ ፖለቲካ ፍጆታና ጥቅም ወደ ሰኔት ስላለቀረቡ እሰከ አሁን ደረስ አልፀደቀም፡፡ የአቦማ ኬር (Oboma Care) ዕጣ ፈንታም የሁለተኛ ትውልድ ሰብአዊ መብቶች እንደ መብት አለመቀበል ጋር ተያይዞ መታየት አለበት፡፡ ሁለተኛው የሰብአዊ መብቶች ትውልድን የኢፌድሪ ሕገ-መንግስት እንደ መብት መደንገጉ ተግብራዊ እንዲሆን በመንግስት ላይ ግዴታ ይጥላል፡፡

መ) የግልና የቡድን ነፃነት (Liberty)

ነፃነት፡- ሁሉም ግለሰቦች የራሳቸውን ግቦች ለማሳካት የሚኖራቸው በህግ ብቻ የሚገደብ ስፋ ያለ እድል ነው፡፡ የነፃነት ቁም ነገር የግለሰብ የራስን እድል በራስ መወሰን ነው (Self-determination) ነፃነት ከውጪ ሊመጣ የሚችለውን ክልከላ (freedom from) ብቻ ሳይሆን ግለሰብ ግቦችን ለማሳካት በአዎንታ የመንቀሳቀስ ነፃነትን ጭምር ነው፡፡የግለሰብ ነፃነት ህብረተሰባዊ እድገት በማምጣት ላይ ቁልፍ ሚና ስላለው ግለሰብ የበለጠ ነፃነት መኖር የተሸለ የኑሮ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡

የኢፌዴሪ ህገ-መንግስት የአንደኛውን የሰብአዊ መብት ትውልድ (እላይ የተገለፀውን) ተቀብሎ በአለም ላይ ቅቡልነት እያገኘ የመጣውን የሶስተኛ ትውልድ ሰብአዊ መብት አካል የሆነውን የቡድን መብት ያካታል፡፡ የብሔሮች፤ ብሔረሰቦች፤ ህዝቦች ነፃነት (liberty) የራስን እድል በራስ መወሰን ይጨምራል፡፡ በአገራችን ሁኔታ ይህ የማይታለፍ ህዝቦች የታገሉለትን መብት መሆኑን ይቀበላል፡፡ የአገራችን ህዝቦች እነሱ በመረጡት የግለሰብ ማንነት ይህን በቡድን ማንነት አጣምሮ የላቀ ዴሞክራሲያዊነት እንዲኖር አድርገዋል፡፡ መንፈሱም የማናቸውም ህዝብ አሱ ይበጀናል በሚለው ፖለቲካዊ አደረጃጀትና ተሳትፎ እድል ይሰጣል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝቦች ዘላቂ ሰላም፤ ልማትና ዴሞክራሴ የሚረጋገጠው እና የኢትዮጵያ አንድነት እየለመለመ የሚሄደው ሁሉንም ማንነቶች (የግልና የቡድን) የሚያስተናግድ ፖለቲካዊ ስርዓት ሲኖር ነው ከሚል እምነት ነው፡፡

Videos From Around The World

ብሔር ብሔረሰቦች ህዝቦች ተደራጅተን ለመንቀሳቀስ እንፈልጋለን ባሉበት ሁኔታ የጎሳ ፖለቲካ (የብሔር ፖለቲካ ለማሳነስ ይመስላል) በህግ ይታገድ ማለት ፀረ-ዴሞክራሲያዊ ነው፡፡ በብሔር ፓርቲ ማደራጀት ስህተት ነው የሚሉ ወገኖች ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ካላቸው ሃሳባቸውን አደራጅተው ወደ ኢትዮጵያ ህዝቦች አቅርበው የህዝቡን ፈቃድ/ስምምነት ያግኙ፡፡

ለህዝቦች ፈቃድ/ስምምነት ከቀረቡ ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል ስለሚያውቁ ከህዝቦች ተሸሽገው የጎሳ ፖለቲካ ብለው ይታገድ ይላሉ፡፡ ሰጎን ራስዋን ከአሽዋ መካከል እንደምትደብቅ ዓይነት ነው፡፡ ይህ ሕገ-መንግስት የኢትዮጵያ ህዝቦችና የኢትዮጵያ ህዝቦች ብቻ ናቸው ለማሻሻልም ጠቅልሎ ለመቀየርም የሚችሉት፡፡ በነሱ አጠራር የጎሳ ፖለቲካ በህግ ለማገድ የሚችል የጎበዝ አለቃና ድርጅት ካልሆነ ሕጋዊ አካል ሊኖር አይችልም፡፡

ሰ) የልማትና የአካባቢ ደህንነት መብቶች

የሦስተኛ ትውልድ ስብአዊ መብቶች እላይ ከተገለፁት መብቶች በተጨማሪ በቅርብ ጊዜ እውቅና ያገኙ አንደ የልማትና የአካባቢ ደህንነት መብቶችን ያጠቃልላል፡፡የስቶክሆልም መግለጫ ተብሎ የሚታወቀው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በእ.ኤ.አ. በሰኔ 16 ቀን 1972 መግለጫ እንደ የመጀመሪያ የአካባቢ ደህንነት ዓለም ዓቀፋዊ ሕግ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መግለጫ እንደ አስገዳጅ ሕግ ባይወሰድም፡፡ እ.ኤ.አ. ዲሴምበር 4 1986 የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ ልማት እንደ መብት ተቀብለዋል፡፡ የሪዮ መግለጫ ተብሎ በሚታወቀው እ.ኤ.አ. በ 1992 በተባበሩት መንግስታት የአካባቢ ጥበቃ እና ልማት ኮንፈረንስ በተባበሩት መንግስታት የተቀረፀ አጭር ሰነድ ይገኛል፡፡

ሕገ-መንግስታችን እነዚህን በቅርብ ጊዜ በዓለም ደረጃ እውቅና ያገኙትን መብቶች ክልሎች አንቀፆች በተጨማሪ በ43ና 44አንቀፆች በማያሻማ መልኩ ተቀምጧል፡፡ የሕጎች ሁሉ የበላይ በመሆኑ ልንታገልላቸው የሚገቡ መብቶች የጎናፅፉናል፡፡ ሕገ-መንግስት እንደ መብት ካልስፈረ በየጊዜው የመጣ መንግሰት እንደፈለገው ሊጫወትበት እንደሚችል የአሜሪካ ምሳሌ በመውሰድ ማብራራት ይቻላል፡፡ በሕገ-መንግሰቷ የሰፈሩትን መብተች በመተግበር በተነፃፃሪ ጥሩ ሪኮርድ አላት፡፡ንጹህ ታዳሽ ኃይል በመጠቀም የካርቦን ልቀትን ለመቀነስ ቅድሚያ በመስጠት በኦባማ አስተዳደር መጨረሻ አሜሪካ የፓሪሰ የአየር ንብረት ስምምነት ፈራሚ ብትሆንም እ.ኤ.አ. ሰኔ ወር 2017 የትራምፕ አስተዳደር ለአሜሪካን ኢኮኖሚያዊ እና ኢነርጂ እንቅፋቶች ናቸው በሚል የፓሪሰ የአየር ንብረት ስምምነት ከመልቀቅ በሻገር በርካታ የአካባቢ ንብረት ህጎችን እንዲጣሱ ተደርገዋል፡፡ የአካባቢ ደህንነት መብት በአሜሪካን ሕገ-መንግስት ሰፍሮ ቢሆን ኖሮ ስምምነቱ የላይኛው ሕግ መሰረተ ያደረገ ስለሆነ በቀላሉ ለማፍረስ አይቻለም ነበር፡፡

የሰው ልጆች በሙሉ ነፃ እና በእኩልነት የተወለዱ መሆናቸው መሰረት አድርጎ ሁሉም ደህንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን፡ በተገቢው የኑሮ ደረጃ የመኖር መብት፤ የግለሰቦችና የህዝቦች በራስ የመወሰን መብት፤ የልማትና የተጠበቀ የአካባቢ ዓየር ንብረት መብቶችን የረጋገጠ ፍትሃዊ በሆነ ስርጭቱ መሠረት በታቀደ አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ ፣ ማህበራዊ ፣ ባህላዊ እና ፖለቲካዊ ሂደት ያለው ሕገ-መንግሰት ማግኘት መታደል ነውና በእጅ ያለ ወርቅ እንዲሉ በመተግበር ባለ ችግር ተማረን ምን ዋጋ አለው ለማለት አንችልም፡

ዴሞክራሲ እንደተሳሰሩ ፖለቲካዊ ሂደቶች

የተሳሰረ ወይም ቀጣይነት ያለው ሒደት በስፖርት ውስጥ እንደ ዱላ ቅብብል ሩጫ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ የመጀመርያው ፘጭ የትም ያህል ፋጣን ወይም ቀርፋፋ ይሁን የሩጫው ውጤት በሱ ብቻ የሚወሰን ባለመሆኑ በተከታታይ ያሉት ቀጣይ ራጮች የሚያሳዩት ፍጥነት ወይም ዝግመት የሩጫወ ውጤት ይወስነዋል፡፡ የሀገራችን የዴሞክራሲ ሒደት ስንመለከት አሮጌው ኢህአዴግ የቱን ያህል ይሳካለት ወይም አይሳካለት አዲሱ ኢህአዴግ በለውጥና ቀጣይነት (change and continuity) መርህ የነበረውን ደካማ ጎንና ጠንካራ ጎን ያለ ምንም ማቅማማት በሚታይ ሁኔታ አውቅና እየሰጠ መጓዝ የጠይቃል፡፡

እላይ የተገለፁት እስቴች ተግባራዊ ለማድረግ የተሳሰሩ ፖለቲካዊ ሂደቶችና ፖለቲካዊ መዋቅር ያስፈልጋል፡፡ የፖለቲካዊ ሂደቱ ማዕከል የህዝቦች ሙሉ እውቅና ያለው መንግስት እንዲኖር እና ህዝቦች በቀጥታ የሚሳተፉበት የነፃና ፍትሃዊ ምርጫና እርሱን ተከትሎ የሚመሰረተው መንግስት ይዘት ነው፡፡ የምርጫው ህግ እስከምን ድረስ የበለጠ የህዝብ መንግስት ያደርገዋል የአብላጫ ድምፅ፤ የተመጣጠነ (proportional) ወይስ ድብልቅ ማለት የአብላጫ እና የተመጣጠነ ድብልቅ ስርዓት ነው ወይ መከተል አለብን ተደራድርን መወሰን ይገባናል፡፡፡፡

የህዝቦች ፈቃድ/ ተስማሚነት የበለጠ የሚያረጋግጠው ተመጣጣኝ የምርጫ ውጤት ቢሆንም እንደአገራችን ያሉት ብዙሃነት እንደእድል የሚመዘንበት አገር ተግዳሮችን ለመቀነስ እና በተነፃፃሪ ቀጣይነት ያለው የሰከነ መንግስት እንዲኖረን ድብልቁ የተሸለ ይመስላል፡፤ በዚህ ረገድ ሕገ-መንግስታችን መሻሻል ያለበት ይመስለኛል፡፤

የፖቲካዊ ሂደቱ አንድ መለኪያ የአብዝሓ (Majoritarian) ነው ወይስ የውህዳን/ሕድጠን፤ መብት ባካተተ መልኩ የቋሚ አብዝሓ አምባገነንነት ወይስ የወሑዳን መብት ጭምር በስምምነት የሚያረጋግጠውን (consociational) ስርዓት ነው፡፡ እንደ አሜሪካን ያሉ አገሮች የአብዝሓ ዓይነት ስርዓት ሲከተሉ እንደ ሲውዘርላንድ ያሉት ደግሞ ወደ consociational የተጠጋ ነው፡፡ ኢፌድሪ ሕገ-መንግስት የወሑዳን መብት ለማስከበር ጭምር በተወካዮችና የፌደራሉን ምክር ቤት ውክልና፤ የራሳቸውን አስተዳደር እንዲኖራቸው ሚናቸውም ህዝብ ራሱ ሲፈልግ ክልል የመመስረት ግልፅ የሆነ መብት በመደረጉ እና የማሻሻያ አንቀጽ ህዝቦች በቀጥታ የሚሳተፉበት ሁኔታም አይመቻችም፡፡ እዚጋ መሻሻል ያለበት ይመስለኛል፡፡ ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ እና የመደራጀት የመሰብስብና የመቃወም መብቶች የፖለቲካዊ ሂደቱ አካል ሲሆኑ የማያሻማና እላይ የተገለፁትን እሴቶች ተግባራዊ ለማድረግ በሚያስችል መንገድ ተዋቅረዋል፡፡

ዴሞክራሲና የተሳሰሩ ፖለቲካዊ መዋቅሮች

የዴሞክራሲያዊ እሴቴት ወደ መሬት ለማውረድ ፖለቲካዊ ሂደቱ እነደሚያስፈልግ ሁሉ ሂደቱ የተሳካ እንዲሆን አንዱ በአንዱ ላይ የተሳሰሩ ፖለቲካዊ መዋቅሮች በግድ ያስፈልጋሉ የፓርቲ ስርዓት፤ interest group፤ ሚዲያና ሌሎች ተቋሞች በመንግስትና በህዝቦች መካከል የሚገናኙና የህዝቦች ፈቃድና ስምምነት ዋስትና የሚሰጡ ናቸው፡፡ ሕገ-መንግስታችን የሕብረ-ፓርቲ ስርዓት መሟላት ያለበት ስርዓቶች ያሟላ ይመስለኛል፡፡ ህዝቦች በፈለጉት ፓርቲ የመደራጀት ፓርቲዎች በነፃነት የመስራት እና በምርጫ መወዳደርና መንግስት የመመስረትን መብት የሚያረጋግጥ ነው፡፡ የሲቪል ማህበራት የሚዲያ ነፃነትን ያረጋግጣል፡፡ ሕገ-መንግትታዊ ስርዓቱ በአንድ በኩል ፌደራሊዝምን፤ የስልጣን ክፍፍልና ቁጥጥር እና የህዝቦች መሰረታዊ መብቶች በምእራፍ ሦስት በማስቀመጥ የተሟላ መዋቅራዊ ይዞታ ያለው ነው፡፡

ሕብረ-ብሔራዊ ፌደራላዊ ስርዓት መሆኑ ከኢትዮጵያ ሁኔታ ጋር እና ከሦስተኛ ትውልድ መብቶች አንፃር ሲታይ የተሻለ ተስማሚ አማራጭ ይመስለኛል፡፡ የግለሰቦች ከፍተኛ መገለጫ የሆነውን የብሔር መብት ማረጋገጥ ያለፉትን ችግሮች የሚፈታ ብቻ ሳይሆን በጠንካራ ብሔሮች የተሳሰረች ጠንካራ ኢትዮጵያን ለመመስረት የሚያስችል ነው፡፡ ማናቸውም ስርዓት የራሱ ተግዳሮቶች እንዳለው ሁሉ ብዙ ጥንቃቄ እና ብልሃት የሚያስፈልገው ቢሆንም የህዝቦች ፈቃድ/ ተስማሚነት፤ ክብር ለግለሰብና ለብሔሮች እኩልነት ያለው እድል ለማረጋገጥ እና በራስ የመወሰን (self-determination) የሚገልፀውን የግለ-ሰብ እና የብሔሮች የሚያረጋግጥ በመሆኑ እጅግ የተሸለ አማራጭ ይመስለኛል፡፡ ይህ ሕገ-መንግስት ህዝቦች በመሰላቸው እንዲወስኑ የሚያደርግ በመሆኑ ሕብረ-ብሔራዊ ፌደራል ስርዓት እንቃወማለን የሚሉት ወገኖች በመጀመሪያ በብሔሮች ህልውና ላይ ቀጥሎም ምን ዓይነት ፌደራሊዝም እንደሚፈልጉ በተሟላ መንገድ ወደ ህዝቦች ሃሳባቸውን ያቅርቡ እና ህዝቦች እንዲወስኑ ሊደረግ ይችላል፡፡

ሕገ-መንግሰቱን ያለ ማወላወል በመተግበር ሰላማችንን እናረጋግጥ

የሕግ የበላይነት ስንል በዋናነት ሕገ-መንግስታችን ማክበር እና ማስከበር ነው፡፡ ፖለቲካዊ ስርዓቱ ሕገ-መንግስት መሰረት አድርጎ ብቻ ይንቀሳቀስ ማለት ነው፡፡ ሕገ-መንግስቱን የሚፃረሩ ሕጎች/መመሪያዎች እና አሰራሮች ውድቅ ስለሆኑ ይታገዱ ይወገዱ ማለት ነው፡፡ ሕግ መሰረት ያደረገ ግልፅነትና ተጠያቂነት ይንገስ ማለተም ነው፡፡

ዋናው እና ወሳኙ የኢትዮጵያ ህዝቦች ለመብታቸው እያደረጉ ያሉትን ትግል ሰላማዊ እና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ብቻ ያለማቋረጥ ሲቀጥሉበት ነው፡፡ ሃንቲገተን (1991፡164) ዴሞከራሲ የገነቡት አገሮች እንዴት ነው የተስሩት? ብሎ ጠይቆ ራሱ ሲምልስ በዴሞከራሲያዊ መንገድ ብቻ ሁሉም መሰረታዊ ጉዳዮች በውይይት፣ በድርድርና በግልግል ና በመስማመት ለመፍታት መቻል፡በስለማዊ ሰልፍ በምርጫ ዘመቻና ክንውን፤ በመንግስት እና ተቃዋሚዎች ያሉ ሊህቃን በድፍርት በመታግል ማስተባበር ሲችሉ ነው፡፡

ተቃዋሚ ድርጅቶች፤ ገዢው ግንባር እና ሕገ-መንግስታዊ ተቋማት ሕገ-መንግስታዊ ግዴታዎች እንዳይወጡ የሚከላከል አመለካከት፣ አደረጃጀት፣ አሰራር ወዘተ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት የሚያስችል ስትራቴጂዎች ማዘጋጀትና መተግበር ይገባል፡፡ ይህ ሲደረግ የኖቬል ሽልማት በእውነትም እያነቃቀን ነው ማለት ነው፡፡ የሕግ በላይነት ለማረጋገጥ አገር-በቀል የአስተዳደር ስርዓት ተቋማዊ ማድረግ ይጠይቃል፡፡

ሰላም ለማረጋገጥ የታሪክ ትርክት ማለዘብ ይጠይቃል

እሳት መማገድ/ማቀጣጠል በሁሉም ብሔር/ ብሔረሰቦች የሚገኙ ፅንፈኞች ሁነኛ ስራ ሆነዋል፡፡ በሊህቃን መሃከል ያለው የታሪክ ሽሚያ በቁስል ላይ እንጨት የመጨመር አካሄድ በህዝቦች ውሰጥ እየሰረፀ በመሆኑ ለግጭት ምክንያት እየሆነ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ታሪክ የሚያኮራም የሚያሳፍርም ነው፡፡ እንደ ሁሉም ቀደምት አገሮች የነፃነትና የግፍም ታሪክ ነው፡፡ በጥሩ ታሪካችን ራሳችንን እንደምናቀና ሁሉ በህዝቦች በደረሰው በደል በአንድ በኩል አገሪቱ የኃልዮሽ ጉዞና የድህነት አረንቋ መዘፈቃችን በሌላ በኩል አንገታችን እንድንደፋ ያደርገናል፡፡ ታሪካችን በተስተካከለና ሚዛናዊ በሆነ መልክ መቅረብ አለበት፡፡ ገናናትን ብቻ ወይም ግፎችን ብቻ እየጮሁ ህዝብ ለህዝብ ማጋጨት በተለይ ግፎችን ወደ አንድ ብሔር ማላከክ ማስተካከል ይገባል፡፡ አማራውም የገናነትም የጭቆናወም ተቋዳሽ ነበርና፡፡ ታሪክ እናውቃለን ለሚሉ ግልገል ናዚዎች ለማስገንዘብ ከአንድ ድህረ-ገፅ ያገኘሁትን የሎሬት ፀጋዬ ገብረመደህን ፅሑፍ እንድጠቀስ ፍቀዱልኝ፡፡

አባቶቻችን አብረው መኖር ስለሚያውቁ ነው የ8 ሺህ ዓመት ስልጣኔ ያቆይሉን፡፡ ስለዚህ የኔ ዘር ካንተ ዘር ይበልጣል የሚል የሰይጣን ጨዋታ ቢቀር ይሻላል ማንም ከማንም አይበልጥም

የሰላም ሽልማቱ ፍትሓዊ ምርጫን አውን እንዲሆን ያነቃቃል፡፡

ምርጫ ካልተካሄደ ኢትዮጵያ ትበታተናለች የሚሉ ሟርተኞት ትተን፤ምርጫ የህዘቦች ሉዓላዊነት መገለጫ በመሆኑና እንደራሱ የቻለ ቁልፍ ምዕራፍ (milestone) ተወስዶ ሕገ-መንግስታዊ በሆነ መንገድ ከተካሄደ ትልቅ እምርታ ይኖረዋል ተብሎ ስለሚገመትና በአሁኑ ጊዜ ገዢው ግንባር ጨምሮ አብዘኛዎቹ ትርጉም ያላቸው ፓርቲዎች ምርጫ በሕጉ መሰረት ይካሄድ የሚል አቋም ስላለቸው በአመቱ መጨረሻ የሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ሰላሚዊ ና ፍትሓዊ እሰከ ሆነ ለአገራችን ትልቅ ተሰፋና መሰረት ነው፡፡

ማነቃቅያው ፖለቲካዊ ሙሱና በመታግል ይታጀብ

 

ሰላም የሚታጣው በሕብረተሰባችን ባለው ኋላቀርነትና በ ፖለቲካዊ ሙሱና ምክንያት ነው፡፡ ፖለቲካዊ ሙስና የሚባለው የፖለቲካ ውሳኔ ሰጪዎች ፖለቲካዊ ስልጣናቸውን በመጠቀም ስልጣናቸውን፤ክብራቸውን እና ሀብታቸውን ለመጠበቅ ሲንቀሳቀሱ ነው፡፡ ከፍተኛ ባለስልጣናት ፖለቲካዊ ተቋማትን፣ ሕጎችን እና አሰራሮችን በማዛባት ስልጣናቸውን ከሕግ ውጭ ለማደላደል የሚደረግ እንቅስቃሴ ነው፡፡

ከነሁሉ ችግሩ ማለት ነፃነታቸው ያረጋገጡ ብሔራዊ ድርጅቶች አለመኖር እና ተቋማዊዎችን ለማዳከም የነበረው እንቅስቃሴ ቢኖርም ከ1983-1993 የዴሞክራሲ የጫጉላ ሽርሽር (Honeymoon) የነበረበት ወቅት ነበር ለማለት ይቻላል፡፡ በ1993 በኢህአዴግ ውሰጥ በተለይ በህወሓት ውሰጥ ከፍተኛ የፖለቲካ ቀውስ በመነሳቱ እና የአንዱ ቡዱን ስልጣን ጥያቄ ውስጥ በመግባቱ የዴሞክራሲ ጭንብል ወልቆ ችግሮችን በውይይት፤በመቻቻልና በድርድር ከመፍታት ይልቅ ከሃሳብ ፍጭት ጎን ለጎን የመንግስት ተቋማትን ማለት የሀገር መከላከያ፤የውሰጥ ደህንነትን፤ፖሊስን ዓቃቤ ሕግን ፍርድ ቤቶችን፤የመንግስት መገናኛ ብዘሃንን ወ.ዘ.ተ እንደ ግል ንብረት በመጠቀም ነው አሸናፊነቱ ያረጋገጠው፡፡ በ1997 በነበረው ምርጫ እንደገና ስልጣኑ አደጋ ውስጥ ስለገባ በዛን ጊዜም ካዛ በኋላማ ሁሉም ጥያቄዎች በአሰተዳደራዊና ፀጥታዊ በሆነ መንገድ እንደ ፖለሲ በመከተል እላይ የተጠቁሰትን ተቋማት በመጠቀም ሕዝቦችን ማፈን ስለቀጠለበት በህዝቦች ዓመፅ ከስልጣን ተገለለ፡፡

ፖለቲካዊ ሙሱና መታገል የሚቻለው የሕግ ልዕልና በአካታች ፖለቲካ ሲታጀብ ብቻ ነው፡፡ አዲሱ ኢህአዴግ በመጀመሪያ አካታች ፖለቲካ ለማንገስ በመሞኮሩ ፖለቲካዊ ሙሱና በቁርጠኝነት ለመዋጋት ያለመ መስሎ ነበር፡፡ የፖለቲካዊ እስረኞች መፈታት፤ በውጭ የነበሩ በሽብርተኝነት ተፈርጀው የነበሩት ተቋዋሚ ፖለቲካዊ ድርጅቶች በሰላም እንዲታገሉ ማመቻቸት፤የታፈኑት ሚድያዎች መለቀቅ አና ልዩ ልዪ ሪፎርሞች በመካሄዳቸው ሁለተኛወ የዴሞክረሲ የጫጉላ ሽርሽር ተጀመረ ብለን ተስፋ አድርገን ነበር፡፡ አድሮ ቃርያ እንዲሉ አካታች ፖለቲካ እየደበዘዘ አሁንም የመንግስት ተቋማት በአጠቃለይ የመንግሰት መገናኛ ብዙሃን በተለይ የጥቂት ሰዎች ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ተገዢ መሆን ጀምረዋል፡፡ መገናኛ ብዙሃኑ (የክልሎች ጭምር) ሕገ-መንግሰቱ ማእከል አድርጎ ሁሉም አማራጭ ሀሳቦችና የህዝቡ ጥያቄዎች ከማሰተናገድ ይልቅ የአንድ አስተሳሰብ ቱልቱላ የሆኑበት ሁኔታ መታዘብ ጀምረናል፡፡

በወቅቱ ጄኔራል ክንፈን አስሮ አቶ ሃይለማርያምን ሸልሞ የሕግ በላይነት ይረጋገጣል ወይ? ብየ እንደፃፍኩት በአሮጌው ኢህአዴግ መንግሰት የተፈፀሙትን ሙሱናና የሰብኣዊ መብቶች ጥሰት የጥቂት ሰዎችና የአንድ ድርጅት ብቻ በሚመስል መልኩ እርምጃ መውሰድ ተጀመረ፡፡ ይባስ ብሎ በዶክሜንታሪ ፊልም የካንጋሮ ፍርድ ቤት ተሰየመ፡፡ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፊልሙን ያቆማል ወይም ያጠፉትን ይጠይቃል ሲባል በሚያሳፍር ሁኔታ ዝምታን መረጠ፡፡ ህዝብ በተደደጋሚ ሲፈናቀል ላይኞቹ አመራር በኃላፍነት መጓደል እንኳን ሲጠየቁ አንሰማም፡፡ የሕግ የበላይነት ጥያቄ ውስጥ መግባት ጀመረ፡፡ታጥቦ ጭቃ የመሆን አዝማሚያ እየታየ ነው፡፡

ፖለቲካወ ዕድገቱ የተለያዩ ኃይሎች ፍጥጫ ወደ አደገኛ አዝማምያ እያመለከተ ነው፡፡ በጥቅሉ ሕብረ-ብሔራዊ ሕገ-መንግሰትዊ ስርዓቱን የሚደግፉና የሚቃዎሙ ሲሆኑ በአቋማቸው ምክንያት ስልጣን እንዳያጡ የተለያዩ እንቅስቃሴ እየታዘብን ነው፡፡ ገዢው ግንባር ኢህአዴግ የሚባል ድርጅት አለ ወይ እስኪባል ድረስ የአይዶሎጂና የፖለቲካ አስተዳደር መሰረታዊ ልዩነት የሚታይበት ሆነዋል፡፡ ይወቀው አይወቀው፤ይተግብረው አይተግብረው ህወሓት አብዮታዊ ድሞክራሲ እና ፌዴራላዊ ስርዓቱ እከተላለህ ሲል አዴፓ አብዮታዊ ድሞክራሲ አሽቀንጥሮ በምን እንደተተካ ሳነውቀው አሁን ያለው ፌዴራላዊ ስርአት የሚቀወምም ይመስላል፡፡ ኦዴፓ እና ደህዴን የፕሮገራም ለውጥ ባያደርጉም ሲከተሉት የነበረውን አይዶሎጂ የተው አሁን ባለው ፌዴራል ስርዓት የተከፋፈለ አቋም ያለቸው ነው የሚመስሉት፡፡ በአጠቃላይ ኢህአዴግና እህት ድርጅቶቹ የጠራ ፕሮግራም፤ሰትራተጂና ታከተክ የሌላቸው በደመነፍስ የሚንቀሳቀሱ፤በአክቲቪስቶች ኦክሲጅን ህይወት የሚዘሩ፡ አክቲቪሰት መሪዎች ያሉት፤ እየተወናጀሉ በአሽሙር የታጀበ ብሽሽቅ ፖለቲካ ገብተው የአገራችን ጊዜ፤ሃብትና ሰላም እያባከኑ ናቸው፡፡ ልዩነታቸውን ተቀምጠው በሰከነ መንገድ በውይይትና በድርድር ከመፈታት ይልቅ ወደ ሶስተኛ ወገን/ባንዳ በማሳበብ ችግሮቻቸውን ውደ ሌላው የሚያጣብቁበት (blame shift) የትግል ዘዴዎች ሲጠቀሙ እናያል፡፡ እስከ መቼ?

ተቋዋሚ ፓርቲዎች በተለይ በኦሮሚያ፤በአማራና በደቡብ (በብሔር የተደራጁ) ከማናቸውም በላይ ህዝባዊ ተቀባይነት ያላቸው ይመስላል፡፡ ሰላማዊ ፍትሓዊ ምርጫ ከተካሄደ ቢያንስ ከፍተኛ ተፎካከሪዎች የሚሆኑበት ዕድል ይታያል፡፡ ልክ እንደ ኢህአዴግ የጠራ ፕሮግራምና ሰትራታጂ የላቸውም፡፡ የድርጅትና የገንዘብ አቀማቸው ተግዳሮቶች ናቸው፡፡ ስትራተጂካዊ/ታክቲካዊ መሰረት የደረገ እስከ ውህደት የሚሄድ ግንባር መመስረት ጊዜ የማይሰጠው ነው፡፡ የዜጋ ፖለቲካ አራማጆች በተወሰኑ ከተማዎች ትርጉም ያለው ድምፅ ሊያገኙ ይችላሉ፡፡አጋር ድርጅቶች ከድርጅታዊ ነፃነት አኳያ ሲታይ ከአፋር ክልል ውጭ የባሰ ነው የሚሉ ፖለቲካዊ ተንታኞት አሉ፡፡ አሁንም በፌደራል መንግሰት ቀትተኛ ትእዛዝ የሚንቀሳቀሱ ናቸው፡፡ የፖለቲካ ተፅእኖአቸው እንዴት ያበልፅጉ መታየት ያለበት ጉዳይ ነው፡፡

በኢትዮጲያ ውሰጥ ያለው የፖለቲካዊ መጫወቻ ሜዳ ከስትራተጂ አኳያ ሕብረ-ብሕራዊ ስርዓቱን የማስቀጠልና የመቀይር ሲሆን በታክቲክ ደረጃ የውሁድ ፓርቲ አደረጃጀትና በነበረው የመቀጠል ነው፡፡ አንዴ አሁን ያለውን ፈዴራል ስርዓት እንቀበላለን ሌላ ጊዜ የሚቀዎሙ የሚመስሉ መርህ የለሽ ስልጣን የሚያጠናክሩበት ብቻ በማሰብ ዥዋ ዢዌ የሚጫወቱም አሉ፡፡

በአሮሚያ ያለው ሁኔታ እንደምሳሌ ብንወስድ አብዛኛዎቹ ተቋዋሚ ድርጅቶች ፈዴራል ስርዓት መቀጠል አለበት ሲሉ የኢህአዴግ ውህድ ፓርቲ የሚቃወሙ ወይም ጊዜው አይደለም የሚሉ እንደሆነ የናገራል፡፡ በሌላ በኩል በገዢው ፓርቲ ኦዴፓ በስትራተጂም በተባለው ታከቲክም ከፍተኛና ልዩነት እንዳለ ይሰማል፡፡ በፈዴራል ስርዓቱ አንደራደርም የሚሉ እንደሉ ሁሉ አጀንደውን በማለሳለስ ወይም ወደ ጎን በማሽቀንጠር በሚገባ ዝግጅት ያልተደረጋበት፤ የአመራሩ መግባበት በሌለበት፤ አቀላጥፎ ያለቀለት ጉዳይ ለማድረግ በከፍተኛ ሩጫ እየተሞከረ ነው፡፡ በቅርብ ጊዜ የተከናወነው የኦዴፓ ማእከለይ ኮሚቴ ስብሰባ መግለጫ ውህድ ፓርቲ በሚመለከት ምንም አለማለቱ የሚገርም ሲሆን ያለውን ልዩነት ለማድበስበስ የተደረገ ሙከራ ነው ይላሉ አንደንድ ተንታኞች፡፡ በፈዴራል ስርዓቱ ጠንካራ አቋም የሌላቸው አመራሮች ውህድ ፓርቲ በመመስረት ስርዓቱን ቀስ በቀስ ለመሸርሸር የታቀደ ነው ከሚል በጥርጣሬ የሚያዩት እና አበክረው የሚቀወሙት አመራር አሉ፡፡

ኦዴፓ እንደ ፓርቲ ለመቀጠል በመጀመሪያ ስለ ሕገ-መንግሰታዊ ስርኣቱ ጠለቅ ያለ ውይየት አደርጎ መስማማት አለበት፡፡ የማይታለፍ ቀይ መስመር ማስቀመጥ ይገበዋል፡፡ አሁን በምንሰማቸው ድብልቅልቅ ያሉ መግለጫዎች እርስበርስ የሚጣረሱ ተግባሮች በኦሮሚያ ይሁን በአገር ደረጃ የከፍተኛ ግጭት ምክንያት ሊሆን ይችላሉ፡፡ ሌሎችም ድርጅቶች የጠራ ፕሮገራም፤ ሰትራጂዎችና ታክቲኮች እንዲኖራቸው መወያየትና መደራደር ያስፈልጋቸዋል፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒሰትር ኢህአዴግ ቢኖርም ባይኖርም ኢትዮጵያ ትኖራለች፤ኢህአዴግ ተወሃደም ፈረሰም ኢትዮጵያ ትኖራለች፤፤ኢህአዴግም ሆነ የትኛውም ፓርቲ ከመመስረቱ በፊት ኢትዮጵያ ነበረች፡፡ ባሉት ነገር ሙሉ በሙሉ እስማመለህ፡፡ ድርጅትን እንድናመልክ የሚፈለጉ ሰዎች በዛ ብቻ ተጠቃሚ ስለሆኑ ነው፡፡ አፄ ኃይለስለሴ ከሞቱ ኢትዮጵያ ትፈርሳለች ብለው በተማሪዎች እንቅስቃሴ እንደንሳተፍ ሲየስፈራሩን የነበሩትን እንደስተውስ ያደረገኛል፡፡ ነገር ግን የአንድ ደርጅት መደረጃትና መፍረስ በተለይ ሙሉ መግባበት እሰከ አለተደረሰበት ለግጭቶች መነሻ ወይም ማክርርያ ሊሆን ይችላል፡፡ ጥድፍያው ለምንድነው?

አዲፒ በተለይ ውሁድ ፓርቲ የሚለው ክንፍ በኦሮሚያ ተሰሚነቱ እየቀነሰ በመምጣቱ፤ደህዴን የብሐሮች ርእሰ-ወሰነ ሲደረግ እንደ ድርጅት ሊፈርስ ስለሚችል፤ አዴፓ እንደ ታክቲክ ስለወሰደውና የአጋር ድርጅት አመራሮች የተባሉትን መፈፀም ስላለባቸውና እንደ ስልጣን መወጣጫ ስለ ወሰዱት በይድርስ ድርስም ቢሆን ለመቀለቀል ወስነዋል የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ በኦዲፒ ብሎም አህአዴግ ያላቸውን ልዩነት በድርድር ካልፈቱት ድሮም አሁንም በመንግሰት ላይ የተጣበቀ መዥገር በመሆኑ ግልፅነት እና ተጠያቂነት በሌለበት ሁኔታ ፖለቲካዊ ሙስና ቢንር በትእግሰት እየጠበቀ ያለ ህዝብ ወደ ዓመፅ እንዳይሄድ ያስፈራል ይላሉ፡፡ ይህ ሁኔታ የመንግሰት መዋቅርን በተለይ የፀጥታ ኃይሎችን በአንድ ወይም በሌላ መልኩ የሚጋብዝ ይሆናል፡፡ የራስህን ፖለቲካዊ ስልጣን ለማደላደል ሲባል አንደ ማስፈራረያ የተለየ አቋም ያላቸውን ለሀገር ደህንነት አደጋ ሳይሆን ልዩ ትኩረት በመስጠት መቀጣጫ ፤ማግለያ ፤በቤተሰቦቻውና ደጋፊዎቻቸው ህይወት ንብረት ሕገ-ወጥ እርምጃዎች ለወሰዱ ይችላል፡፡ ሁሉም ፖለቲካዊ ሃይሎችና ሕገ መንግስታዊ ተቋሞች በተለይ ተሸላሚው መሪያችን እንደ ጠቅላይ ሚኒስቴርና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ የመከላከያ ሃይላችን፤ የሀገር ውስጥ ደህንነት፤ ፖሊስ አቃቤ ህግ ወ.ዘ.ተ ሕገ-መንግስታዊ ግዴታቸውን ብቻ እንዲወጡ፤ እንደ ተቋም በማናቸወም ፖለቲካ እንቅስቃሴ ሕገ-ወጥ ጣልቃ ገብነት እንደይኖር የማድረግ ግዴታ አለባቸው፡፡ ካልሆነ ሁለተኛወ የዴሚክራሲ ሽርሽር ገደል ሊገባ ነው፡፡ ለአገሪቱ አደገኛ ነው፡፡

የድህነት መባበስ ሰላም ሊያሳጣ ይችላል

የኑሮ ሁኔታ እጅግ እየሻቀበ ነው፡፡ ታችኛወ የሕ/ሰብ ክፍል ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰበት ነው፡፡ ተስፋ የመቁረት አዝማሚያ እየታየ ነው፡፡ ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶቹን ማስጠበቅ የመንግስት ግዴታ ነው፡፡ እየተጠራቀሙ የመጡ ችግሮች በአንዴ ለመቅረፍ ባይቻልም ኢኮኖሚወ ተስፋ ሰጪ ሆኖ እንዲነቃቃ ማደረግ ይገባል ፡፡ የችሮታ ጉዳይ አይደለም የሕግ በላይነት ማረጋገጥ እንጂ፡፡

እንኳን ለግንቦት 20 አደረሰዎት በሚል ፅሑፌ በግንቦት 2010 ለጠቅላይ ሚንስተር አቢይ አሕመድ የፃፈኩትን ላስታወሳቹህ፡፡ እርካብና መንበር በተሰኘው ስለ አመራርና ፖለቲካ ኢኮኖሚ በሚያትተው መፅሃፋቸው አገሪቱ መከተል ያለባት የድሃ አለኝታ (Pro Poor) ፖለሲ መሆን እንደለበት አበክረው ይገልፃሉ፡፡ዓለማችን ለጥቂት ሃብታሞች እንቁላልዋን ስትጥልለት ለተቀረው ሰፊ ህዝብ ግን የሚተርፈው ኩስ ነው ይላሉ።

የኒዩ ሊበራሊዝም አስከፊነት፣ ያስከተለው ቀዉስ እና አደገኛነቱ፣ ይህ ስርዓት በባህሪው ስላለው ፀረ ህዝብነትና በኛ ሁኔታ እንዴት እንደማይሰራ በሰፊው ተንትነዉታል። ጠቅላይ ሚኒስቴሩ በዚህም አላበቁም የልማታዊ መንግስት አስፈላጊነትና ለኛ ሁኔታ ያለው ተስማሚነት አበክረው ገልፀዉታል። በዚሁው መፅሃፍ ገፅ 159 ላይ የሚከተለዉን ድምዳሜ ያስቀምጣሉ

በግራም ሆነ በቀኝ ዛሬ ላይ ሆነን ኒዮ ሊበራሊዝም ካጠላበት የካፒታሊስት ስርዓት ይልቅ ካፒታሊስታዊ ስርዓትን በልማታዊ መንግስት የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ጉዞ በማስደገፍ የኢንዱስትሪ ልማት ለማረጋገጥ ጠንክሮ ከመስራት ዉጭ በዕድገት ወደሃላ ለቀሩ አገራት የምርጫ ሳይሆን የህልዉናም መሰረት መሆኑ አያጠያይቅም።

በሳቸው አገላለፅ አዋጪው መንገድ ልማታዊ መንግስትነት ቢሆንም አሁንም ድረስ ኒዮ ሊበራል ሃይሉ ያለው ጫና እና ግፊት ቀላል አለመሆኑን ለመግለፅ የሚከተለዉን ይላሉ፡፡ እንደ ቀን ፀሃይ የጠራዉን እዉነታ ወይም ተጨፈኑና እናሞኛቹህ በማለት በሬን ካራጁ አጥፊን ከጠፊው በማር በተለወሰ መርዝ አስማምተው ለማኖር ሰፊው ህዝብ ከእባብ እንቁላል እርግብ እንዲጠብቅ ሁሉንም አቅም በመጠቀም በስብከታቸው ገፍተዉበታል። ብለው ለኒዩ ሊበራል ፖለቲካል ኢኮኖሚ ያላቸዉን የመረረ ትችት ይሰነዝራሉ። ከቃልና ተግባራቸው ተስማምተው መዝለቅ ያቃታቸው ብለዉ የሚተችዋቸው ኒዩ ሊበራሎች የህዝቦች ሉኣላዊነት መገለጫ የሆኑትን ምክርቤቶች፣ የስልጣን እርከኖች ለጥቂት ኮርፖሬሽኖች ጥቅም ሲባል እንዴት እንደሚያሽመደምዱዋቸው ይገልፃሉ (ገፅ 146 ይመልከቱ)።

ጠቅላይ ሚንስተር አብይ ኢኮኖሚውን ለማነቃነቅ በቂ ትኩረት ሰጥተዋል? ምንስ ማድረግ አለበቸው? እየተከተሉት ያሉት ፖለሲ እላይ የተጠቀሰውን ያንፀባረቃል? ኢኮኖሚው የማነቃቃት ጉደይ ጊዜ የማይሰጥ ነው፡፡

በተሟላ የደህንነት ፖሊሲና ተቋማዊ በሆነ መንገድ ያልተመራ ስምምነት ሰላምን ያደፈርሳል

ከኤርትራ ጋር የነበረው የሰላም መናጋት ለማስቆም ማንም ባልገመተው ሁኔታ ጠቅላይ ሚንሰተሩ ሰላም ለማምጣት የሔዱበት ርቀት እጅግ የሚያስመሰግን ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ሽልማቱ ተገቢ ነው፡፡ ሆኖም ስምምነቱ ግልጽነትና ተቋማዊነት የጎደለው በመሆኑ እና የኤርትራ ፕሬዚዳንት በሃገራችን የውስጥ ጉዳይ ሲፈተፍቱ እስከ ጨዋታው አልቀዋል Game Over ዓይነት አገላለፅ ድረስ ሲሄዱ አለማስቆም ቢያንስ ተቃውሞ አለማቅረብ ሽልማቱ አወዛጋቢ ያደርገዋል፡፡ አካፋን አካፋ ካላልን ግብዝነት ይነግሳልና ክቡር ጠ/ሚኒሰትር በህወሓት ለማፌዝ፤ ምናልበትም ለማስፈራራት በኢትዮጵያንና ኤርትራዊያን ንፁሃን ሰላማዊ ዜጎች በደም የተጨማለቁትንና ፀረ-ሰላም የሆኑትን የኤርትራው ፕሬዚዲንት የሰላም አባት አድረገው የሰላም ካባ አልብሰው በመቐለ ወይዛዝርት መሳለቅ ከስዎ የሚጠበቅ አልነበረም፡፡ ክቡር ጠ/ሚኒስተር ፕሬዚደነቱን የሰላም ጋቢ ማልበስ እኮ የካሣ ኮሞሹኑ የኤርትራ ፀብ ጫርነት ውሳኔ ስህተት ነው እያሉ እኮ ነው፡፡ ከኤርትራ ጋር ዘለቂ ሰላም የሚረጋገጠው የአልጀርስ ስምምነት በመሻር ወይም አዲስ ድርድር ተካሂዶ የኢትዮጵያ ሉዐላዊ የባህር በር ሲረጋገጥና በድንበር አካባቢ ያሉት ህዝቦች እንባ በሚመልስ መልኩ ሲቋጭ ነው፡፡ በዛን ጊዜ የላቀ ሽልማት ከአንድ ሚኒሰትሪ፤ በአንድ አደራሽ ለአንድ ጊዜ ሳይሆን በመላው የኢትዮጵያ ህዝቦች ልብ የሚነግስ ሽልማት ነው የሚሆነው፡፡

የኢትዮጵያ የደህንነት ፖሊሲና ስትራተጂችዎች ባልተዘጋጀበት እና የ1994 ዓ.ም የተደመረ መሆኑን ባለረጋገጥንበት ሁኔታ ከቀይ ባህር ምዕራብ ይሁን ምስራቅ አገሮች የምናደረጋቸው ድርድሮች በጥንቃቄ መደረግ አለበት፡፡

 

ሽልማታችን በወሳኝነት የሚያሸበርቀው የውስጥ ሰላም ሲረጋገጥ ነው

ተስፋችን መጨላለም ከጀመረ ሰንበትበት ብሏል፡፡ በህዝቦች መካከል መጠራጠር በስፋት እየታየ ነው፡፡ ነገ ከነገወዲያ በክፋት አየር ተሞልቶ ሁላችንም ከሚያሰጨንቀን ከወደሁ የሰላም አየር ለመተንፈስ የሚያስችለንን እንቅስቃሴ እንጀምረው፡፡ በሁሉም ክልሎች በተለያየ ደረጃ የሚታይ መጠራጠር፤ ግጭትና በተወሰኑት ደግሞ የጦርነት ድባብ ይታያል፡፡

በሶማልያ ና በአፋር ክልሎች ገባ ወጣ የሚሉ ግጥቶች፤በደቡብ ክልል ብሔር ብሔረሰቦች ህገመንግስታዊ መብቶቻቸውን በሚጠይቁበት በተለይ ሲዳማ በቀን 11/11/2011 ዓ.ም የቆረጠበት ጊዜ አስቀድሞ ከህዝቡ ጋር ተደራድሮ ዘላቂ መፍትሔ አለመፈለግም የሚያስተዛዝብ ነው የሆነው፡፡ አሁንም ያልተፈቱ ለግጭት ሊዳርጉ የሚችሉ የመብት ጥያቄዎች በአግባቡ ካልተፈቱ አደገኛ ሁኔታ ይፈጠራል፡፡በአማራና ትግራይ ክልሎች ያለው የጦርነት ድለቃ የሚያሰተሳስብ ነው፡፡ኦሮማራ እንደ ጤዛ በኖ አሁን ደግሞ በኦሮሞና አማራ ልህቃን መካከል መካረር ይታያል፡፡

አሁን እየተጋገለ ያለው ፖለቲካዊ ዝንፈት (polarization) በዚህ ከቀጠለ ሁሉም የክልል መንግስታት ወደ አላቀዱት ጦርነት እና ውድመት ሊያመራ ይችላል፡፡ አንዱ ለመስፈራት ብሎ ግዛቴን በኃይል አስመልሳለህ ብሎ የጦርነት ነጋሪት ቢጎሸም እና ሌለው እከላከላለህ ብሎ ክተት ቢያወጅ እነሱ ራሰቸው ወደማይቆጣጠሩት ሁኔታ ሊገባ ይቻላል፡፡ የጦርነት የእስረኛ አጣቢቂኝ (war prisoners' dilemma) ሊያጠቃቸው የችላል፡፡ እነዛ መጥፎዎች ናቸው፤ ጦርነት ናፋቂዎች ናቸው ከሚል እና ሳያጠፉን እናስወግደቸው የሚል አስተሰሰብ ያድግና በሆነ ያልታሰበ ክስተት ሊጫር የችላል፡፡ አንዴ ከተጀመረ ደግሞ ለማሰታገስ አስቸጋሪ ነው፡፡በራሳቸው የማይተማመኑ ሞራል የለሽ መሪዎች አገር/መሬት የሸጠ እንደይባሉ በፅንፈኞት ፖለቲካ እየተነዱ ወይም በዴሞከራሲ እና ሰለም የማይጠቀሙ መሪዎች ፍትሓዊ እና ሕጋዊ በሆነ ድርድር ወደ መፍቲሔ ከማምጣት ይልቅ ሰላም ወይም ጦርነት በሌለበት ሁኔታ ውሰጥ ተደበቀው ሊኖሩ ስለሚፈልጉ ህዝቦች እነዛን መሪዎች አሽቀንጥረው ራሳቸው መፈተሔ ማመጣት የጠበቅባቸዋል፡፡

የፌዴራል መንግሰት፤ የሁሉም የክልል መስተዳድር መሪዎች፤ የኃይማኖት አባቶች፤ሽማግሌዎችና ሊሂቃኖች እየተከሰተ ያለው ችግር በህዝቦች መካከል ለረጅም ዘመናት የተገነባው ቤተሰባዊ ኃይማኖታዊ፤ ባህላዊና ሞራላዊ እሴቶች መሰረት ችግሩን በውይይት በመመካከርና በመረዳዳት እንዲፈታ እንዲደረጉ በከፍተኛ ኃላፊነት መወጣት ይገባል፡፡ማናቸውም የድንበር ይሁን የማንነት ጥያቄዎች ሰላማዊና ሕገ መንግስታዊ በሆነ መንገድ ማስተናገድና ዘላቂ መፍትሄ መሻት አስፈላጊ ነው፡፡ በሁሉም ህዝቦች መካከል የቆየውን ታሪካዊና ባህላዊና ኃይማኖታዊ ትስስር የሚያጠናክሩ ሰፋፊ ሥራዎች ለመስራት ህዝባዊ ኮንፈረንሶች ማዘጋጀትና በመካከላቸው መተማመን እንዲሰፍን መስራት የስፈልጋል፡፡
አሁን ባለው መጋጋል ፌዴራል መንግስቱ ራሱን እንደሌለ ቆጥሮ (Irrelevant) አድርጎ ማያቱ የሚገርም ነው፡፡ መሪዎች ጦርነትን በመጫራቸው ለሚፈጠረው ውድመት ብቻ ሳይሆን ግዴታቸወን በለመወጣትም የሚያሰጠይቅ መሆኑን መገንዘብም ያስፈልጋል፡፡ መሪዎቹ ጥጋቸውን ይዘው ወጣቱን ኢትዮጵያዊ በጦርነት ለመማገድ የሚደረገው ሙከራ ወንጀል ነው፡፡ ስለዚህ የሁሉምም ህዝቦች ቅድሚያ አጀንዳ መሆን ያለበት፤ ህዝቦችን እርስ በርስ ለማጫረስ ጦርነት እየቀሰቀሱ ያሉትን በህብረት ታግለው ማሸነፍ ነው፡፡

በማጠቃለል ሽልማቱ እንደሃገር ይገባናል፡፡ እንደሃገር ማነቃቂያ የምንወስደው ከሆነ ብቸኛው አማራጭ የሕግ የበላይነት ማረጋገጥ ነው፡፡ ሕገ-መንግስታችንን ማክበርና ማስከበር ነው፡፡ ተቋሞቻችን የህዝቦችን ሰብአዊ መብቶች ማክበርና ማስከበር ማለት ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ፖለቲካዊ ሊህቃን ወደ ድርድር፤ግልግል ና ስምምነት ደርሰው ሰላም እንዳይድረሱ የተለያዩ እንቀፋቶችን መቅረፍ ያስፈለጋቸዋል፡፡ ሁሉ ነገር ነጭ ወይም ጥቁር አንደኛው ከሌላው ጋር ሊታረቅ የማይችል (mutually exclusive) ና ቂመኝነት (vindictive) እና አጥፊ ተጋላጭነት(destructive confrontation) ለግልግል እነቅፋት ነውና በቀጣይነት እንታገለው፡፡

ባለፈው ታሪክ ሳይሸከሉ መሰረታዊ የሆኑ መንታ ችግሮቻችን ማለት ድህነትና የዲሞክራሲያዊ እጥረት ላይ ይረባረቡ ማለት ነው፡፡ በመንግስት በኩል ሊኖር የሚችለው ፖለቲካዊ ሙስና ሕገ-መንግስታዊ ተቋሟት፤ፖሊቲካ ድርጅቶች፤ ማህበራት እና ጠቅላላ ህዝቡ በንቃት መታገል ይኖርባቸዋል፡፡ የፀጥታ ክፍሎች የአንዱ ወይም የሌለው ፖለቲካዊ ድርጅት/ብዱን ሕገ ወጥ መሳርያ እንደይሆኑ መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል፡፡ ሽልማቱ ማነቃቂያ እንጅ ዋናው ሽልማት በሕዝቦቻችን የሚሰጠው በመሆኑ ሰላም ልማት ዲሞክራሲ ማረጋገጥ ይገባል፡፡

ሰላም መቶ በመቶ ያሸንፋል ተብሎ የተጠራው ድግስ ስከታተል ፊታውራሪ ተክለሃዋርያት ተክለማርያም አስታወስኩና ከህይወት ታሪካቸው ላይ የተቀነጨበውን ኣስተማሪ ጥቅስ ከማህዴሬ መዝዤ አነበብኩትና እንደተለመደው ለባለስልጣኖቻችን ላከፍል ወደድኩኝ፡፡

ንጉሶች እና ባለጊዜዎች ከጥፋት የሚደርሱት በከንቱ ውዳሴና በከንቱ ትምክህት ነው፡፡ ፍጡሮች መሆናቸውን ይረሱትና ሁሉም ማድረግ የሚችሉ፣ ሁሉም ለነሱ ደስታና ክብር የተፈጠረ ይመስላቸዋል፡፡ በዙሪያቸው የሚከቧቸው ጥቅም ፈላጊዎች ሁሉ ይህንን እያስመሰሉ እንዲያምኑበት ያደርጓቸዋል፡፡ ታዲያ ከሕግ በላይ መሆን፤ ከፍጡር በላይ መሆን ያምራቸውና በዘፈቀደ እንስራ ይላሉ፡፡ የሚከራከሯቸውን፤ የማያደንቋቸውን እንደጠላት ያዩዋቸዋል ያጠቋቸዋልም፡፡

 

 

Back to Front Page