Back to Front Page

በዚች አገር ለመሆኑ ህግ ማክበርና ማስከበር ያቃተው ማነው?

በዚች አገር ለመሆኑ ህግ ማክበርና ማስከበር ያቃተው ማነው ?

ፍስሃ መረሳ

8/4/19

አገር በብቃት መምራት ያቃተው በስልጣን ላይ ያለው ፅንፈኛው ቡዱን የራሱን መሰረታዊ ችግር ለመደበቅ ሲል በየጊዜው የማስመሰያ አጀንዳ በመቅረፅ እሱ በሚቆጣጠረው ሚድያ ሳይቀር የፈለገውን አካል መወንጀልና በየአደባባዩ መዝነፍ ዛሬ ዛሬ የተለመደ የዕለት ተዕለት ስራው አድርጎታል ፡፡ ስልጣን ከተቆናጠጠበት ጊዜ ጀምሮ በየጊዜው በሚያሰራጫቸው መርዘኛ የፕሮፖጋንዳ ስራዎችም ዋነኛ ትኩረቱ በትግራይ ህዝብና ድርጅቱ እንደሆነም በግልፅ የሚታወቅ ጉዳይ ነው ፡፡ የሰሙኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫና የፌደራል ፍርድ ቤቶች ፕሬዝደንት በፍትህ መድረክ ላይ ያሰሙት ንግግር መነሻም በትግራይ ህዝብ ያነጣጠረ የቆየ ዘረኛ የፕሮፖጋንዳ ስራቸው አንድ ኣካል መሆኑም ለማንም ግልዕ ነው ፡፡ የአሁኑ የሁለቱም ባለስልጣናት ንግግር ትኩረት ያደረገውም በነሱ አነጋገር የትግራይ ክልል ህግ የማያስከብር እንደሆነና በተለይ ፕሬዝዳን~ ደግሞ መፍሄ ያሉትም በመሰንዘር መንግስታቸው ሌላ ወታደራዊ የሃይል አማራጭ መፈለግ እንዳለበት ነው በግልፅ ያስቀመጡት ፡፡ ይህ የተለመደ ዲስኩራቸው ለትግራይ ህዝብ አዲስ ባይሆንም አጀንዳዉ በዚህ ሰዓት ለምንስ በተለይ ከአንድ ገለልተኛ መሆን የሚጠበቅበት የፍትህ ኣካል በፖለቲካ ስራ ላይ በመግባት ለምን ይህን ኣደገኛ መልእክት ለማስተላለፍ ተፈለገ? በርግጥስ እነሱ እንደሚሉት የትግራይ ክልል ህግ የማይከበርበት ክልል ነውን ? ማነውስ ህግ ማስከበርና ማክበር ያቃተው ? ህግ የሚሉትስ የትኛው ህግ ነው? የሚሉ የተወሰኑ ነጥቦች በማንሳት ማብራራያ መሰጥት ሁኔታውን በበለጠ ለመረዳት የሚያግዝ ይሆናል የሚል እምነት ስለላኝ የተወሰኑ ጉዳዮችን ለማብራራት እሞክራለሁ ፡፡

Videos From Around The World

ህግ ማስከበርና ማክበር ያቀተውስ ማነው ?

በስመ ለውጥ ኢህአዴግን በመግደል ወደ ስልጣን የመጣው ጥገኛው ቡዱን ስልጣን ከያዘበት ቀን ጀምሮ ዋነኛ ተግባሩ አድርጎ የወሰድው የአገሪቱ ህገ መንግስታዊ ስርኣት የማፍረስ ስራ መሆኑን ብዙ ማስረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል ፡፡ በዚህ አንድ አመት በስልጣን ላይ ያለው ሃይል የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች በሙሉ ፍቃዳቻው ተወያይተውበት ያፀደቁት ህገ መንግስት ለማፍረስ ያልፈነቀለው ድንጋይ የለም ሊባል ይችላል ፡፡ ከሁሉ በፊት ህዝቦች በህገ መንግስት የተሰጣቸው ራሳቸውን በራሳቸውን የማስተዳደር ያልተገደበ መብት ወሳኙ የሉኣላዊነታቸው መገለጫ የሆነ የክልል አስተዳደር በማፍረስ የራሱን ተቀጥያና ኣስፈፃሚ የሆነ ኣካል ለመተካት ካለው ፍላጎት የመነጨ ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ጀምሮ እስከ ደቡብ ክልል በመዝለቅ የነበረውን መንግስት በሃይል በማፍረስ ህገ መንግስታዊ ስርኣቱን ለመቀየር ይሳከለታል ወይ የሚል ጥያቄ መልሱ ሌላ ጉዳይ ሆኖ የሃይል እርምጃው ግን ኣጠናክሮ ቀጥሎበታል ፡፡ ወደፊትም ይህ እስትራተጂ ከመተግበር ወደላ እንደማይል የአሁኑ ተግባሩ በቂ ማሳያ ነው ፡፡ በዚህ አጭር ጊዜ ከትግራይ ክልል በስተቀር በቀጥታና በተዘዋዋሪ ወደድክም ጠላህም የኛን ውሳኔና አመራር ተቀበል እየተባለ እምቢ ላለ እስከ ወህኒ ቤት በማውረድ ክልሎችን ያፈረሰበት ሁኔታ እንዳለ በቅርቡ በህዝብ ተወካዮች ሳይቀር በአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስተር ሳይቀር በይፋ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የተወሰደ እርምጃ በደቡብ ክልልም ይደገማል እስከማለት የደረሰበት ሁኔታ እንዳለ ሁላችን የሰማነው ጉዳይ ነው ፡፡ ህገ መንግስታዊ ስርኣቱ ይከበር ብለው ለጠየቁና የተቃወሙ ኣብዘኞቹ ክልሎች የዚህ ባለጡንቻ ነኝ የሚል ቡዱን ዱላ እንደቀመሱም ለማንም የማይደበቅ ሃቅ ነው ፡፡ ክልሎችን በማፍረስ የራሱን ጥገኛ ስርኣት ለመገንባት ካለው ፍላጎት የተነሳ ይህ ቡዱን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ህገ መንግስቱ እንዳይሰራ ለማድረግ እሱ በባላይነት የሚቆጣጠረው የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ህግ በማርቀቅ ህገመንግስቱን በቀጥታ የሚፃረሩ እንደ የወሰንና የማንነት ኮሚሽን ያሉ ኮሚቴዎችን በማዋቀር ክልሎችን በሃይል ለማፍረስ የሚያስችል አዋጅ እንዲፀድቅ የተደረገበት ዋነኛ ምክንያትም ስርኣቱን ለማፍረስ ካለው ፍላጎት እንደሚመነጭ ግልፅ ነው ፡፡ በማያሻማ ቋንቋ ሲቀመጥ ይህ ቡዱን ህገ መንግስታዊ ስርኣቱን ማፍረስ ነው አላማው ፡፡ ራሱ ባመጣው ጣጣ አገሪቱ ወደ ከፍተኛ ቀውስ በማስገባት ሌላው ቀርቶ የፀጥታ መዋቀሩን በማሰማራት የዜጎችን ሰላምና ድህንነት መጠበቅ አቅቶት በዚህ አጭር ጊዜ በአገራችንታሪክ በማነኛውም ጊዜ ታይተው የማያውቁ ኣሳፋሪና አለምን ያስደመሙ ድርጊቶች የመታየታቸው መሰረታዊ ምክንያት የዚህ ህገ መንግስታዊ ጥሰት ውጤት መሆኑ ራሱ በስልጣን ላይ ያለው ሃይልም ሳይወድ የተቀበለው ሃቅ ነው ፡፡

የሚገርመው ነገር ግን ይህ ሃይል አሁን ለማስመሰል ህግ ይከበር እያለ በየመድረኩ ሲለፈልፍና ህግ መንግስታዊ ስርኣቱን አክብረው ለሄዱ ክልሎችን ሲወነጅል መሰማቱ ነው ፡፡ ህግ ማስከበር ቢችልማ እሱ ከመጣበት ክልል ሳይቀር ከ3 ሚልዮን ህዝብ በላይ ሲፈናቀል እሱ የት ነበር? መንግስት ቢኖርማ በጠራራ ፀሃይ ዜጎች በወጡበት ሳይመለሱ በ21ኛው ክ/ዘመን በየመንገዱ እንደእንስሳ ተሰቅለው አይገደሉም ነበር እኮ ፡፡ በህግ የዜጎችን ሂወትና ንብረት ድህንነት የመጠበቅ ሃላፊነት የተሰጠው የፀጥታ መዋቅር ባለበት አገር መንገድ መዝጋት ንብረት መዝረፍ መስረቅ ማውደም የዕለት ተዕለት ክስተት ባልሆነ ነበር ፡፡ ሌላው ይቅር ባለፈው አንድ ወር የታየው የከፍተኛ አመራሮች ግድያ ህግ ሊያስከበር የማይችል መንግስት እንደሆነ ነው ቁልጭ አድርጎ የሚያሳየው ፡፡ ስለዚህ ይህ ሃይል ራሱ መንግስት ህግ ከማስከበርና ከማክበር ይልቅ በማፍረስ ቀንደኛ ተዋናይ በሆነበት ሁኔታ ህግ የማስከበር ብቃትና ኣቅምም ሞራልም በሌለበት ሁኔታ በየትኛው ሞራልና የህግ አግባብ ነው የትግራይ ክልልን ህግ ኣላከብርም ብሎዋል በሚል ሊፈረጅና ሊወቀስ የሚችለው ?

 

በርግጥስ ትግራይ ህግ የማይከበርበት ክልል ነው ?

ይህን ጥያቄ ለመመለስ ብዙ ትንታኔ መስጠት የሚያስፈልግ አይመስለኝም ፡፡ በትግራይ ህዝብና በነሱ ያለው ልዩነት ግልፅ እስከሆነ ድረስ ይህ ቅራኔ መፈጠሩ የማይቀር ነው ፡፡ የትግራይ ህዝብና መንግስት ከመጀመርያው ጀምሮ ያለው ኣቋም ግልፅ አድረገዋል ፡፡ የትግራይ ህዝብ ሁሌም የኢትየጵያ ህዝብ ተዋያይቶ ያፀደቀው ህገ መንግስታዊ ስርኣት ይከበር ነው ጥያቄው ፡፡ የትግራይ ህዝብ ማንነቴና ሉኣላዊነቴን ለማንም ሃይል አሳልፌ አልሰጥም ከማንም ጋርም አልደራደርም ነው ግልፅና የማያሻማ አቋሙ ፡፡ የትግራይ ህዝብ በዘርና በጥላቻ በራሱና በሌሎች ህዝቦች እየደረሰ ያለው ጥቃት ይቁም ነው ደጋግሞ በየጊዜው የገለፀው ሃሳብ ፡፡ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሊረዱልን የሚገባ መሰረታዊ ጉዳይም ህግ ባለበት አገር ዜጎች በሚቀርብላቸው ማስረጃ እንጂ በሃሰተኛ ዶክመንተሪ ፊልም እየተሰራ በሚድያ በማስተላለፍ ሰው በዘሩና በፖለቲካ ኣቋሙ ወህኒ ቤት መውረድ የለበትም ነው ጥያቄው ፡፡ ስለዚህ ልዩነቱ በስልጣን ላይ ያለው ሃይል ህገ መንግስታዊ ስርአቱን አፈርሳለሁ አታፈርስም መሆኑም ያው የኢትዮጵያ ህዝብ ኣውቆት ያደረ የማያከራክር ጉዳይ ነው ፡፡ የትግራይ ክልል ሰላሙን ኣስጠብቆ መቆየቱና የዘመኑ አጋፋሪዎች ቀጭን ትእዛዝ ኣለመቀበሉ ካላቹሁ ቁጭትና ቂም በቀል የተነሳ ካልሆነ በስተቀር ይህ ቡዱን በሌሎች የኔ የተሻለ ቤዝ አለኝ ብሎ የሚኩራራበት ክልል ሳይቀር ባንኮች በጠራራ ፀሃይ ሲዘረፉና ከፍተኛ ባለ ስልጣናት መገደላቸው እየታወቀና ከፍተኛ የህግ ጥሰት ተፈፅሞ እያለ ለነዚህ ክልሎች ህግ አክባሪዎች ብሎ እንደ ሞዴል በመውሰድ በአንፃሩ ግን ሰላሙን አስጠብቆ ህገ መንግስታዊ ስርኣቱን ላስከበረ ክልልና ህዝብ መሸለምና እንደ ሞዴል መውሰድ ቀርቶ መወንጀሉ መነሻው ምን እንደሆነ በተለይ ለትግራይ ህዝብና መንግስት መልእክቱ ግልፅ ነው ፡፡ ህገ መንግስታዊ ስርአቱን ሙሉ በሙሉ በማፍረስ በውጭ ሃይል የሚመራ ጥገኛ ስርኣት ለመገንባት የሚደረገው ጉዞ አልቀብልም ብሎ የፅንፈኛች አፍራሽ ተግባር ለመታገል በመወሰኑና በጥብቅ መታገሉን ይህን ህዝብ ለመወንጀል የተጠነሰሰ ሴራ መሆኑን ለማንም ሊደበቅ የማይችል ጉዳይ ነው ፡፡

 

ታድያ ምን ተፈልጎ ነው ይህ አዲስ ነጠላ ዜማ በዚህ ጊዜ መልቀቅ የተፈለገው ?

ፅንፈኛው ሃይል ራሱ ባመጣው ጣጣ አሁን አገሪቱ ወደ ከፍተኛ ቀውስ እንደከተታት ያው በገሃድ የሚታይ ይቅር ለኛ ኢትዮጵያውያን ለመላው የአለም ህዝብም የማይደበቅ ሃቅ ከሆነ ቆይተዋል ፡፡ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ያለው ፖለቲካዊ ውጥረት በማየትና በመገምገምም ምን ያክል ይቺ አገር ልትወጣበት ወደማትችል አዘቅት እንደገባች መገንዘብ አያዳግትም ፡፡ የዚህ ቀውስ መሰረታዊ መነሻም በስልጣን ላይ ያለው ሃይል በሚከተለው የተሳሳተ መንገድ መሆኑም ግልፅ ነው ፡፡ ይህ ችግርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ እንደሚሄድና በቀጣይም ማቆምያ እንደሌለው ስለታወቀ አሁን ስልጣን ይዞ ለመቆየት ያለው ብቸኛ አማራጭ ከውስጥም ከውስጥም ሰርኣቱን ለማፍረስ ከተሰለፉ ሃይሎች ተቀርፆ የተሰጠውና እንደተለመደው የትግራይ ህዝብን ለማዳከምና ለመምታት እንዲመች ብለው የመረጡለትን አዲስ ነጠላ ዜማ በመያዝ የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ ይዞ መቀጠል ስለሆነ በዚህም በዛም የጥላቻ ዘመቻው እንደአዲስ በግልፅ ተጀምረዋል ፡፡ በመጨረሻ ግን አንድ ግልፅ መሆን ያለበት ጉዳይ ይህ አፍራሽና ዘረኛ ዘመቻ እንደማያዋጣና እንደበፊቱ በእንጭጩ እንደሚከሽፍ አሁንም በነሱ ሽንፈት እንደሚገባደድ ቢያውቁት የተሻለ ይሆናል ፡፡ የትግራይ ክልል ግን ሰላሙን በማስጠበቅ በተግባር እየታየ እንዳለው ያለውን አቅም በማቀናጀት ልማቱን እንደሚስቀጥል ምንም ጥርጥር የለውም ፡፡

Back to Front Page