Back to Front Page

የኢትዮጵያ የውስጥ ችግር ምርጫ በማካሄድ ብቻ የሚፈታ አይመስለኝም ።

ኢትዮጵያ የውስጥ ችግር ምርጫ በማካሄድ ብቻ የሚፈታ አይመስለኝም

በልኡል ገብረመድህን (ከአሜሪካ )

4.12.2019

      የኢህአዴግ ሊቀመንበር ዶክተር አብይ አህመድ የኢትዮጵያ ህዝብ የጠየቀው ለውጥ አስፈጽማለሁ በማለት በመጋቢት ወር 2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ ተሾሙ ህዝቡም ከተገዢነት ወጣን ከብሔር ፖለቲካ በሰላም ተፋታን ከሰብዓዊ ጥሰት ተላቀቅን ከመፈናቀል ዳን ሰላምና አንድነት ይሰፍናል የአገር ግንባታ ይፋጠናል እርቀ ሰላም ይወርዳል የሚል ታላቅ እምነት ነበረው የኢትዮጵያ ህዝብ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ዘርና ሐይማኖት አልጠየቀም ምክንያቱም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ቀርቦ ቃለ መሃላ ሲገቡ የኦሮሞ ህዝብ መሪ ሳልሆን የኢትዮጵያ ህዝብ መሪ ነኝ ብሎ ነበር ከኢህአዲግ መር የዘር ፖለቲካ መንግስት አሰተዳደር ጋር ሲፋለም የቆየው የአዲስ አበባ ወጣት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ድጋፍ ለመስጠት በተጠራው የሰኔ 16, 2010 የአዲስ አበባ ከተማ የድጋፍ ሰልፍ የአዲስ አበባ ህዝብ በነቂስ በመውጣት ድጋፊን ገልፆ ነበር ። በድጋፍ ሰልፉ ላይ ባጋጠመ የቦምብ ፍንዳታ በርካታ ዜጎች ላይ ጉዳት መደረሱ ይታወቃል ።ሆኖም  ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰልጣን ከያዙ አመት ሳይሞላቸው የአዲስ አበባ ህዝብ ላይ ክህነት ተፈፀመበት ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመሩት የኦሮሞ የዘር ፖለቲካ ድርጅት (የቀድሞ ኦህዴድ ፣ የአሁኑ ኦዴድ= ኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት ) በመግለጫ ሳይቀር አዲስ አበባ ከተማ የሚመለከቱ የተዛቡ አመለካከቶች ማራመድ ጀመር ። በህገ መንግሥቱ መሠረት የኦሮሞ ህዝብ ከአዲስ አበባ ልዩ ጥቅም ይገበዋል ፣ አዲስ  አበባ ከተማም የኦሮሞ ዋና ከተማ ናት የሚሉ ኋላ ቀር እና ዘረኛ ሐሳቦች ጠቅላይ ሚኒስትር ከሚመሩት የኦሮሞ የዘር ድርጅት በስፋት ሲነገር ለአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ህዝብ ተቆጣ ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የኢትዮጵያ ህዝብ ለማስተዳደር ሰብዕና የላቸውም ፣ ዘረኛ ናቸው ፣ ለኢትዮጵያ ህዝብ አይመጥኑም ፣ ዘረኝነት ያብቃ ፣ የዘር ፖለቲካ ሰለቸን ፣ የሚሉ መልዕክት አዘል ትችቶች ከአዲስ አበባ ህዝብ ማስተጋባት ጀመሩ ። የአዲስ አበባ ህዝብም በጠቅላላ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሰተዳደር ላይ እምነት በማጣቱ ምክንያት የአዲስ አበባ ከተማ ባለአደራ ቦርድ ለመሰየም ተገደዋል ። በመሆኑም በታዋቂው የሰብዓዊ መብት ተሟጋችና ጋዜጠኛ አቶ እስክንድር ነጋ የሚመራ የአዲስ አበባ ከተማ እሰከ መጪው አገር አቀፍ ምርጫ ድረስ የሚመራ የአመራር ቦርድ ተመስርቶ ሥራ ጀምሯል ። የኢትዮጵያ ህዝብ አዲስ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ምዕራፍ ይመጣል ብሎ ተስፋ አድርጐ ነበር ።የኢትዮጵያ ህዝብ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አዲስ የለውጥ ምዕራፍ ያመጣሉ ብሎ በጉጉት ጠብቆ ነበር ። እየሆነ ያለ ግን ለየቅል ነው ። ዶክተር አብይ የዘር ፖለቲካ አስቀጣይ ፣ በፌዴራል ስርአት አወቃቀር ላይ የማይደራደሩ ፣ የህግ የበላይነት ማስፈን የተሳናቸው ፣ ጥሩ ጥሩ አገር ነክ ህዝባዊ ንግግሮች የሚያደርጉ ግን በተግባር የከሸፉ ፣ የዜጎች መፈናቀል ማስቆም ያልቻሉ ፣ የህግ ተፈላጊዎች ለህግ ማቅረብ ያልቻሉ መርሕ አልባ መሪ ሆነዋል ። የኦነግ ታጣቂዎች አገር ሲያፈርሱ ፣ ባንክ ሲዘርፉ ፣ ሰው በቀን ቁልቁል ዘቅዝቀው ሲያርዱና ሲገድሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ኦነግን አላወገዙም ፣ እርምጃም አልወሰዱም ። ከዛሬ የተሻለ ጊዜ የለም በሚል የፖለቲካ ስሌት የአዲስ አበባ ከተማ የባለቤትነት ጥያቄ በአክራሪ የኦሮሞ ማህበረሰብ መነሳቱ አግባብነት አልነበረውም ። አዲስ አበባ ከተማ የሁሉም የኢትዮጵያ ዜጎች መኖሪያ እንጂ የኦሮሞ ልዩ ጥቅም የሚከበርባት ተራ ከተማ አይደለችም ። የአዲስ አበባ ጉዳይ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ከፍ ያለ ዋጋ ያሰከፍላቸዋል።

Videos From Around The World

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በመጀመሪያ ሶስት የሥራ ወራት ውስጥ ህዝብ ያስደሰቱ መልካም ተግባራት የፈፀሙ ቢሆንም በርካታ መቀረፍ የነበረባቸው የህዝብ ችግሮች ጠቅላይ ሚኒስትሩ በገቡት ቃል መሠረት መፈፀም ባለመቻላቸው ህዝብ ለጠቅላይ ሚኒስትር የነበረው ተስፋና ተቀባይነት ቀንሰዋል ። የኢትዮጵያ ህዝብ ጥያቄ ፍትህ ፣ ሰበአዊ መብትና ዲሞክራሲ ይከበር የሚል ነው ። ለዚህም ገለልተኛ የፍትህና የዲሞክራሲ ተቋማት መኖር አለባቸው ። የተጀመሩ ቢኖሩም ህዝቡ የጠየቀው ያህል አይደለም ። በኢህአዴግ አሰተዳደር ለተፈፀሙት የህዝብና የአገር በደሎች ተጠያቂ የሆኑ ግለሰቦች በህግ ተጠያቂ ያለመሆናቸው አንዱ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የአስተዳደር ድክመት ተደርጎ ይወሰዳል ።ሌሎች ተጠያቂ ሳይሆኑ  በትግራይ ተወላጅ ከፍተኛ አመራር ነበር ላይ ያነጣጠረ እስራት መፈፀሙ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሰተዳደር ላይ ጥርጣሬ እንዲፈጠር  በር ከፋች ምክንያት ሆነዋል ። ትግራይ የሚያስተዳድረው የዘር ፖለቲካ ፖርቲም የጠቅላይ ሚኒስትር ዘር ተኮር የእሰር እርምጃ አውግዞታል ። አገርና ህዝብ ላለፉት 29 የመንግስት ስልጣን አመታት ይዞ ሲመራ የቆየው የኢህአዴግ ሰርአት የአራት ዘር ተኮር ድርጅቶች ግንባር ሲሆን ለልማቱና ጥፋቱ በጋራ እንጠይቅ የሚለው የትግራይ ክልል የዘር ፖለቲካ ድርጅት ሓሳብ የሚጋራ ህዝብ በርካታ ነው ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከፍተኛ የሰበአዊ ጥሰት እንዲሁም የአገር ሐብት ብክነትና ስርቆት የፈፀሙ በየክልሉ በዘር (ብሔር ) ከለላ ሰር ያሉ ተጠርጣሪዎች  ለህግ ማቅረብ አልቻሉም ። አቅሙም የላቸውም ። ይህ ያለማድረጋቸው በየክልሉ ህግ አልባነት ነግሷል ። በበርካታ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ተንታኞች ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ላይ የሚሰነዘረው መሠረታዊ ሀሳብ የዶክተር አብይ የኢትዮጵያ ቀጣይ ጉዞ አመላካች ሰነድ አልባ መሆናቸው ነው ። በዚህ የተነሳ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ምሁራን የዶክተር አብይ አሰተዳደር ከነበረው የቆየ የኢህአዴግ አመራር የተለየ እንዳልሆነ ያሰምሩበታል ። ዶክተር አብይ የኢኮኖሚ ሆነ የፖለቲካ ቀጣይ የኢትዮጵያ ጉዞ አመላካች ሰነድ እስከአሁን ለኢትዮጵያ ህዝብ ይፋ አላደረጉም ። የኢትዮጵያ ህዝብ የአቶ ለማ መገርሳ የለውጥ ቡድን በአመራር ክህሎት ችግር በቅልበሳ ማዕበል እንደተመታ በመናገር ላይ ነው ።

     የኢትዮጵያ መፃኢ ችግሮች ከግምት ያላስገባ የችኮላ ህገ መንግስት በኢህአዴግ ተፅእኖ መፅደቁ ስህተት ነበር ። የአሁኑ የኢትዮጵያ ህገ መንግስት ከመፅደቁ በፊት የኢትዮጵያ ህዝብ በስፋትና ጥልቀት አልተወያየበትም ። የህገ መንግስት አርቃቂ ኮምሽን ሰብሳቢ የነበሩ ዶከተር ነጋሶ ጊዳዳ ይህንን ሐቅ አረጋግጧል ። የፀደቀው ህገ መንግስት የኢትዮጵያ ህዝብ ጊዜ ወሰደው ወይይት እንዳላደረገበት የሚያስረዱ ብዙ በቂ ምክንያቶች አሉ ። የኢትዮጵያ ህዝብ ንቃተ አልዳበረም ፣ ለመብት መከበር የብሔር ፖለቲካ አደረጃጀት ያሻል ፣ የዜግነት (የግለሰብ ) መብት ሳይሆን የብሔር መብት ተመራጭነት አለው ፣ ዘርንና ቋንቋን መሰረት ያደረገ የፌደራል አስተዳደር አወቃቀር ለኢትዮጵያ ቀጣይ እድገትና ሰላም ያመጣል በሚል በምርምርና ጥናት ያልዳበረ ህገ መንግስት አሁን የኢትዮጵያ ህዝብ ከድህነት ያልተናነሰ ችግር ሆነዋል ። የአሁኑ የኢትዮጵያ ህገ መንግስት መነሻ ምክንያቶች አንዱ ያለፉት ጨቋኝ የኢትዮጵያ የአገርና ህዝብ ገዢዎች አንዱ ነበር ። የኢትዮጵያ ሀገ መንግሰት  የህዝብ ጭቆና ዳግም በኢትዮጵያ እንዳያንሰራራ ታሳቢ ያደረገ የስጋት ህገ መንግስት እንጂ ቀጣይ የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ እድገት ፣ ሰላምና መረጋጋት ፣ የህዝቦች አንድነትና መከባበር ላይ ያተኮረ አለነበረም ። የዜግነት መብትና ክብር የማያጎናፅፍ ህገ መንግስት ችግሩ ብዙ ነው ። ግለሰብ ብቻውን ታግሎ መብቱ ማስከበር ስለማይችል በዘሩ (ብሔሩ) ተጠርንፎ (ተደራጅቶ ) መብቱ ማስከበር ይችላል የሚል መነሻ ሀሳብ ያለው የአሁኑ የኢትዮጵያ ህገ መንግስት ለኢትዮጵያ ህዝብ ከነቀርሳ በሸታ በላይ ነው ። አንድ ብሔር (ዘር) (ጎሳ) በዘሩና በቋንቋው በክልሉ መናገር እና መዳኘት ካልቻለ የት ሒዶ ይናገር ፣ ይዳኝ የሚሉ አንዳንድ የዘር  ( Ethnic Nationalism ) ፖለቲካ ተንታኞች  በአስተሳሰብና አመለካከት ችግር ማዕበል የተመቱ በመሆናቸው የሚያቀርቡት መከራከሪያ ሀሳብ የኢትዮጵያ ህዝብ አይመጥንም ። አንዳንዶቹ የኢትዮጵያ ህዝብ የዲሞክራሲ አሰተሳሰብ አድማስ እንጭጭ በመሆኑ ህዝቡ የዘር ፖለቲካ ፅንሰ ሀሳብ አልተረዳውም ይላሉ ። ለኢትዮጵያ የዘር ፖለቲካ እንኮ አማራጭ የለውም ለማለት የሚዳዳቸው አንዳንድ የሀሳብ ድህነት ያላቸው ሰዎች የሚደመጥ ጉዳይ ነው ። ለመሆኑ በምን የፖለቲካ መርህ መሰፈርት ቢለካ ነው  የኢህአዴግ ከዘር ፖለቲካ የተሻለ አማራጭ የለውም የሚባለው ? ። ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በአሀዲዊ (None federal State ) ስርአት ውሰጥ በነበረችበት ወቅት የኢትዮጵያ ጎሳዎች (ብሔሮች) በገዢዎቻቸው የመብትና የኢኮኖሚ ጭቆና ይደርስባቸዋል ነበር የሚለው ሀሳባዊ ምክንያት እውነታነት ቢኖረውም ለነበረው ችግር መፍትሔ በዘር መደራጀት አልነበረም ። ምክንያቱም ያለ ገለልተኛና ጠንካራ የፍትህና የዲሞክራሲ ተቋማት በሌለበት አገር በዘር ተደራጁ አልተደራጁ የአገር ግንባታ ፣ አንድነትና ሰላም እውን አይሆንም ። የህግና የሀሳብ የበላይነት የማይከበርበት አገር ላይ የዘር ፖለቲካ ታክሎበት በእሳት ላይ ላምባ ይሆናል ። ሌላ የዘር ፖለቲካ የሚያቀነቅኑ አንዳንድ ደካማ ሰዎች የሚያነሱት ሀሳብ የዘር ፖለቲካ የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት እያደገ በሚመጣበት ጊዜ እየከሰመ ይሄዳል የሚል ነው ። ጉዳዩ በከፊል እውነታ ሲኖረው ነገር ግን ለየኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት እድገት ፀር የሆነው የዘር ፖለቲካ በምን የፖለቲካ መርህ የሂሳብ ግልብጦሸ ቢሰላ ከኢኮኖሚ እድገት ጋር ትይዩ የሚሔደው ? ። አንድ የብሔር ማህበረሰብ በሌላ የክልል ማህበረሰብ በሰላም ጥሮ ግሮ መኖር ካልቻለ በምን የፖለቲካ ሂሳብ ነው የጋራ ምጣኔ ሀብት እድገት የሚሳካው ? ።  የአሁኑ የፌዴራል ስርአቱ አወቃቀር ለጭቁን ብሔሮች የህልውና ጉዳይ ነው ለሚሉ የዘር ፖለቲካ አራማጆች የትኛው ጭቁን ብሔር እንደሚወክሉ አይታወቅም ። ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ ያለፉት ስርአቶች ሰለባ ሆኖ ቆይተዋል። ማን ጨቋኝ ማን ተጨቋኝ እንደነበረ የሚያሰረዳ ሰነድ የለም ። የተለየ ጎሳ በተለየ ሁኔታ የጭቆና ግፍ የደረሰበት ብሔር በኢትዮጵያ አልነበረም ። ቋንቋና ዘር መሠረት ካደረገወ የአሁኑ የኢትዮጵያ ፌደራል አወቃቀር የተሻለ የፌደራል አወቃቀር የለም ብሎ መደምደም አይቻልም ። ሁሉ ጊዜ የተሻለ የፌደራል አወቃቀር ሰርአት ይኖራል ።  እንኳንስ በኢትዮጵያ ምድር በመላ አለም የሚኖሩ ህዝቦች በዘራቸውና በቋንቋቸው ኮርቶ በሚኖሩበት የሀያ አንደኛ ክፍለ ዘመን እንዴ የጋምቤላ ፣ የቤንሻንጉል ፣ የአፋር ፣ የኮንሶ ፣ የሸናሻ ፣ የወላይታ ፣ የትግራይ ፣ የአማራ ፣ የኦሮሞ ፣ የሐረሪ ፣ የኢትዮጵያ ሶማሌ እንዲሁም ሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች ከሚኖርበት ቦታ ውጭ በቋንቋቸው መዳኘትና መናገር የማይችሉ ? ። የዘር ፖለቲካ የሚያራምዱ ዜጎች መሠረታዊ የጥላቻ ችግር ያነገቡ ይመሰላሉ ። የሚሻለው ለአገር ግንባታና መረጋጋት በሚበጅ አጀንዳዎች ላይ መወያየት ይጠቅማል የሚል እምነት አለኝ ። ፖለቲካ የተወሰኑ ግለሰቦች የእልህና የጥላቻ መርዝ ማከፋፈያ ቀፎ ሳይሆን በፖለቲካ መርህና ትንታኔ ላይ የቆመ የህዝቦች መብትና ሁለንተናዊ ጥቅም እንዲሁም ደህንነትና ሰላም የሚያጎናጽፍ በመንግሥትና ህዝብ መሀል ድልድይ ሆኖ የሚያገለግል መሆን ይኖርበታል ። ነውም ። ፖለቲካ የብዙሃን እንጂ የግል ፍላጎት ማሳለጫ መሳሪያ አይደለም ። አንድ የመጨረሻ አብይ ጉዳይ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ባለብዙ ጎሳ አገሮች በብሔር (ዘር ) የተደራጀ የፖለቲካ ድርጅት የላቸውም አልያም በዘር ፖለቲካ መመሰረት በህግ የተከለከለ ነው ። ታድያ ምንድነው ኢትዮጵያን ከሌሎች ባለብዙ ጎሳ የአለም አገሮች የተለየ የሚያደርጋት?። ኢ

     ኢትዮጵያ በህዝብ የተመረጠ ህዝባዊ መንግስት እንጂ የብሔር መንግስት የሚያስፈልጋት አገር አይደለችም ። ለኢትዮጵያ የኦሮሞ ዘረኛ መንግስት ሆነ የአማራ ዘረኛ መንግስት ሆነ የትግራይ ዘረኛ መንግስት ሆነ የደቡብ ዘረኛ መንግስት አገዛዝ ስር መገዛት የለባትም ። የመንግስት ሰልጣን ከአንድ ብሔር ወደ ሌላ ብሔር መሸጋገሩ የኢትዮጵያ ህዝብ ንቀትና ውርደት እንጂ ክብርና ልዕልና አይደለም ። የአሁኑ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የኢትዮጵያ ህዝብ ጠቅላይ ሚኒሰትር ለመሆን የሚያስችል  አገራዊና ህዝባዊ ሰብዕና የላቸውም ። ምክንያቱም ዶክተር አብይ የኦሮሞ ብሔር ድርጅት መሪ እንጂ የኢትዮጵያ ህዝብ በኢትዮጵያዊነት አጀንዳ በኢትዮጵያ ህዝብ የተመረጡ አይደሉም ። በቀጣይ በሚደረገው የኢትዮጵያ አገር አቀፍ የፖለቲካ ሰልጣን ምርጫ ላይ ብሔር ወክሎ የሚወዳደሩ የፖለቲካ ፖርቲ ድርጅቶች የህዝብ ቅቡልነት ችግር ያጋጥማቸዋል የሚል ቅድመ ትንተና በሙሉ ልብ መናገር እችላለሁ ። በቀጣዩ አገራዊ ምርጫ ተወዳድሮ ለማሸነፍ በመጠባበቅ ላይ ያሉ ዶክተር አብይ አህመድ የኦሮሞ ህዝብ ወክሎ የሚወዳደሩ በመሆናቸው ለአገራዊ ድል (መመረጥ ) የሚያስችላቸው የኢትዮጵያ ህዝብ ይሉኝታ የሚያገኙ አይመስለኝም ። ነገር ግን ምርጫ ከመድረሱ በዘር ሰር የተዋቀረው የኢህአዴግ ፖለቲካ ድርጅት ከዘር ፖለቲካ ሰለባነት አውጥቶ አገራዊ ቅርጽና የፖለቲካ ይዘት እንዲኖረው ካደረጉ ብሔር ተኮር ካልሆኑ አገር በቀል የህዝብ ፖለቲካ ድርጅቶች ጋር የመፎካከር እድል ሊኖራቸው ይችላል ። በአሁኑ ጊዜ ኢህአዴግ የሚል ሰም በኢትዮጵያ ህዝብ የተጠላ የፖለቲካ ድርጅት ሰም ሆነዋል ። ኢህአዴግ ከዘር ፖለቲካ ተላቆ አገራዊ መዋቅርና የፖለቲካ ይዘት ለውጥ ካልመጣ የኢትዮጵያ ህዝብ ዳግም ችግር ውስጥ የሚነከር አይመስለኝም ። በርካታ ዜጎች የኢህአዴግ ግንባር የፖለቲካ ድርጅት በምርጫ እንዳይወዳደር እገዳ እንዳጣልበት የጎላ ፍላጎት አላቸው ። ለዚህ እንደ ምክንያት የሚያቀርቡት ኢህአዴግ ባለፉት የስልጣን ዘመናት የፈፀማቸው ሰብአዊና አገራዊ ግድፈቶችና ጉድለቶች ላይ ያተኮሩ ናቸው ። በቀጣዩ የኢትዮጵያ አገር አቀፍ ምርጫ ለዶክተር አብይ የህዝብ ድጋፍ የሚያሰባስቡ ትግራይ ከሚያሰተዳድር የኢህአዴግ ግንባር የፖለቲካ ድርጅቶ በቀር ሌሎች የግንባሩ ድርጅቶች የህዝብ ድጋፍ ለማግኘት የሚቸገሩ ይሆናሉ ። በመሆኑም ዶክተር አብይ ከአገር አቀፉ ምርጫ በኋላ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ ለመቀጠል የሚያስችል የህዝብ ይሉኝታ የሚያገኙ አይሆንም ።

    በኢትዮጵያ አገር አቀፍ ምርጫ ከመደረጉ በፊት መከናወን የሚኖርባት አብይት ጉዳዮች አሉ ። እንደሚታወቀው በየ አሰር አመቱ የሚካሔደው የህዝብ ቆጠራ ( Population Census ) በዘንድሮ ለመካድ ተወስኖ በፀጥታ ስጋት ላልተወሰነ ጊዜ መተላለፉን ይታወቃል ። በመተላለፉ የራሱ የሆነ ችግር ቢኖረውም ሰላምና መረጋጋት ባልሰፈነበት ወቅት የህዝብ ቆጠራ ሥራ መከወን አሰቸጋሪ በመሆኑ መተላለፉ ተገቢነት አለው ። የህዝብ ቆጠራ ለማካሄድ በተለያዩ ክልሎች መፈናቀል የደረሳቸው ወገኖች ወደ ነበሩበት ቦታ መመለስ ይኖርባቸዋል ። በተመሳሳይ መልኩ የሚቀጥለው አገር አቀፍ ምርጫ ለማካሄድ መሰራት ያለባቸው የፖለቲካ ፣ የህግ  ፣ የምርጫ ቦርድ ፣ የፀጥታ ፣ እንዲሁም የፍትህ  ጉዳዮች በግልጽ መፍትሔ ማግኘት ይኖርባቸዋል ። ፍትህ ሳይሰፍንና ሳይረጋገጥ ፣ አገራዊ ሰላምና እርቅ ሳይመጣ ፣ የክልል ገዢዎች ክልላዊ ወታደራዊ መዋቅር መሰርቶ ባሉበት ወቅት ፣ እንዲሁም ዜጎች እንደ እንሳሳት በየቦታው ተጥሎ ባሉበት ጊዜ ፣ እንዲሁም የዘር ፖለቲካ ንዳድና ጡዘት እንደ ሰደድ እሳት በተስፋፋበት ወቅት ምርጫ ማካሄድ አይደለም ማሰቡ ራሱ ግብዝነት አልያም የህዝብ ሀላፊነት ከግምት ያላስገባ ተግባር ይሆናል ። ከምርጫ በፊት ህዝብ መረጋጋት አለበት ። ከምርጫ ፍትህ መስፈኑ መረጋገጥ አለበት ።ከምርጫ በፊት የዘር ፖለቲካ መቆም አለበት ። ከምርጫ በፊት በህግ የሚፈለጉ ወንጀለኞች ለፍርድ መቅረብ አለባቸው ። ከምርጫ በፊት ከቦታው የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቦታዎች መመለስ አለባቸው ። ከምርጫ በፊት የህገ መንግስት አንቀጾች መሻሻል አለባቸው ። የህዝብ ችግሮች ባልተፈቱበት የፖለቲካ ምርጫ የሰልጣን ውድድር ተሸናፊ እና አሸናፊ የሌለው እልቂት ያስከትላል ። በአሁኑ ወቅት ተሸናፊ የፖለቲካ ድርጅት ለአሸናፊው የፖለቲካ ድርጅት ሰልጣን በሰላም ለመቀያየር የሚያስችል መደላድል የለም ። በየትኛውም ክልል በነፃነት መንቀሳቀስ ባልተቻለበት ጊዜ ላይ ሆኖ አገር አቀፍ ምርጫ እንዴት ማከናወን ይቻላል ? ።የኢህአዴግ ካድሬዎች ልዩ የፀጥታ ሰራዊት ደጀን አድርጎ በመንቀሳቀስ ባሉበት ጊዜ በምን የፖለቲካ ሂደትና ሒሳብ ምርጫ ማካሄድ ይቻላል ? ። አገራዊ ምርጫ የዜጎች ሁለንተናዊ መብቶችና ጥቅሞች የሚወስኑበት ወሳኝ ማህበራዊ ክሰተት በመሆኑ ህዝብ በነፃነት ወጥቶ የፈለገው እንዲመርጥ የህዝብ ሰላምና መረጋጋት የቅድሚያ ቅድሚያ መሆን አለበት ።

     በኢትዮጵያ ከአገር አቀፍ ምርጫ በፊት ለበርካታ አመታት ተዘርቶና ተስፋፍቶ የቆየው የዘር ጥላቻና የዘር ፖለቲካ ማከም ያሰፈልጋል ። በኢህአዴግ ስርአት የተጎዳ በርካታ ህዝብ አለ። ኢህአዴግ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አማካይነት ድርጅቱ የፈፀማቸው ሰብዓዊና ህገ መንግሰታዊ ጉድለቶችና ግድፈቶች ለኢትዮጵያ ህዝብ ይቅርታ ቢጠይቅም ለማካሰ ያቀረበው መፍትሔ የለም ። መታደስ ለመናገር የማይሰለቸው ድርጅት በለውጥ የኢትዮጵያ ህዝብ ከመካሰ ይልቅ ከነበረበት ብሶ ለሴራ ፖለቲካ እንዲሁም ለሰላም መደፍረስ መነሻ ምክንያት እየሆነ ይገኛል ። የዘር ጥላቻ ዋልታ መርገጡ እየታወቀ ለችግሩ መፍትሔ ከመፈለግ በግብታዊነት ምርጫ ማካሄድ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል ። ኢህአዴግ ምርጫውን ቢያሸንፍ መልሶ  የለየለት አምባገነን ድርጅት ይሆናል ። ምክንያቱም የተማከለና ያልተመጣጠነ መንግሰታዊ ሐይልና አቅም ያለው በመሆኑ ወደ ሐይልና አፈና እርምጃ መግባቱ የማይቀር ጉዳይ ነው ። ለምሳሌ ፡ አሁን ያለውን የዘር የሐይል ፖለቲካ አሰላለፍ እንኳን ብናይ በኦሮሞና አማራ የዘር ፖለቲካ አራማጅ ድርጅቶች ለስልጣን ሸሚያ የሚደረገው ትንቅንቅ በቅርብ ለሚከታተል ሰው በቀላሉ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ደካማነት መገንዘብ ይቻላል ። ሁለቱም (የአማራ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት እና የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት ) ለአገር ፖለቲካ ግንባታ ሆነ የምጣኔ ሀብት ለውጥ ሆነ ለመጪው ትውልደ ጠብ የሚል ሰራ የሚሰሩ አይደሉም ። እንደ ትልቅ ድል የሚወሰዱት  የትግራይ ክልል ገዢ የፖለቲካ ድርጅቶች ተባብሮ ከአዲስ አበባ ማስወጣታቸው እንጂ ምንም አገራዊ ራእይ የላቸውም ። ካላቸውም የኢህአዴግ ዲሞክራሲ ማዕከላዊነት ራእይ ብቻ ነው ። ይልቁንም ሁለቱ ለስልጣን የሚጎነታተሩ ባላንጣዎች ናቸው ። ተግባራቸውም የአንድ ዘር (ነኦሮሞ ወይም የአማራ) ለመንግስታዊ ሰልጣን ማብቃት ነው ። አሁን የኢትዮጵያ ፖለቲካ በኦሮሞ እና አማራ እጆች ወድቀዋል ። ሁለቱም ተባብሮ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከዘር ፖለቲካ የፀዳ ማድረግ ካልቻሉ ፣ ራሳቸውም ከዘር ፖለቲካ ካልፀዱ ምርጫ ተደረገ አልተደረገ የኢትዮጵያ ፖለቲካ የውስጥ ግጭት ሆኖ ይቀጥላል ።  አሁን በኢትዮጵያ ያለው የደፈረሰ ሰላም ላይም ሆኖ ለኢትዮጵያ ህዝብ አንድነትና ህልውና የሚያበቃ ፣  ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ የሚወክል ሀገ መንግስትና መንግስት መመሰረት ካልተቻለ ቀጣዩ የኢትዮጵያ ህዝብ እጣፈንታ አንድም በዘር ፖለቲካ አዙሪት እየተናጠ እና እየተጋጨ በነውጥ መኖር ፣ አልያም  በአምባገነን የዘር ፖለቲካ መሪዎች እየተገዛ መኖር  ይሆናል ።

       በኢትዮጵያ አንዳንድ ክልሎች ለሚነሳ እሳት ለማጥፋት አንድ የረባ የእሳት ማጥፊያ አውሮፕላን ወይም ሄሊኮፕተር የሌላት አገር  አንድነቷንና ህልውናዋን ማስጠበቅ ያልተቻለ ፣ የተበከለ ውሃ ከእንሰሳት ጋር አብሮ የሚጠጣ እንዲሁም ዳቦ በሙዝ የሚመገብ ህዝብ ይዞ በምን የፖለቲካ ሒሳብ ምሰራቅ አፍሪካን አንድ ውህድ የንግድ ቀጠና ማድረግ ይቻላል ? ። የዶክተር አብይ አህመድ አሰተዳደር የኢትዮጵያ የፖለቲካ አቅጣጫ ከሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር መምከር የሚያስፈልግበት ጊዜ አሁን መሆኑን ለማሳሰብ እፈልጋለሁ ። የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያቀራርብ የፖለቲካ ሰርአትና ህገ መንግስት የህዝብ ፍላጎትና ጥያቄ በተሟላ መልኩ የሚያስተናግድ የፖለቲካ አሰተዳደር መሠረት ለመጣል ከአሁን የበለጠ ጊዜ ላይገኝ ይችላል ። ህዝብ ሳይበታተን ፣ አገር ሳይፈርሰ ሰልጣን ለመንጠቅ የሚደረገው እሽቅድድም ቆም ብሎ በሰከነ እይታ ማየት ያሰፈልጋል ። ሰልጣን የህዝብ መሆኑ አምኖ ለህዝብ ጥያቄዎች በቅድሚያ ማስተናገድ ያስፈልገናል ። ያሉት አገራዊ ችግሮች ከህዝብ ጋር መሞከር ያሰፈልጋል ። በልመና የሚደገፍ ኢኮኖሚ ተይዞ ቀጣይ የኢትዮጵያ ህልውና ማስቀጠል አይቻልም ። ከሀላፊነት ጋር ሁሉም ሳይሸፋፈን መወያየትና መነጋገር ያስፈልገናል ። ጠቅላይ ሚኒሰትሩ የሚያማክሩ የምጣኔ ሐብት በቂ እውቀትና ልምድ ያላቸው ከፖለቲካ በፀዳ ሞያዊ ትኩረት ላይ ያተኮሩ የኢኮኖሚ መርሕ ቀረፃ ( Fundamental Economic Reforms ) የሚያስፈልግበት ወቅት መሆኑን መናገር እፈልጋለሁ ። በኢትዮጵያ የሥራ አጥ ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ በማሻቀብ ላይ መሆኑ ለኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት መደፍረስ አንዱ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል አያጠራጥርም ። በኢትዮጵያ በመንግሥት የቁጥጥርና የክትትል ችግር ምክንያት በርካታ ንብረትና ገንዘብ ያለአግባብ ይባክናል አልያም በባለስልጣናት ይሰርቃል ። በየክልሉ ለሥራ አጥ የሥራ እቅድ ማሳለጫ የሚመደብ ገንዘብ የታቀደለት ግብ ሳያሳካ በጀቱ ይከስማል ። ሥራ አጥነት ለኢትዮጵያ ውስጣዊ ያለመረጋጋት አንዱ ምክንያት ነው ። በመሆኑም መንግስት ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ መረባረብ ይኖርበታል ።

    በኢትዮጵያ ከምርጫ በፊት የህዝብና አገር ህልውና እየተፈታተነ ያለው የኦነግ እንቅስቃሴ ፖለቲካዊ አልያም ህጋዊ መፍትሔ ያስፈልገዋል ። የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባር ለኢትዮጵያ አንድነትና ህልውና አደጋ ነው ። የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሰላም ጥሪ ተቀብሎ ከአስመራና ከግብፅ እንዲሁም ከሌሎች አገሮች ኢትዮጵያ የገባው የኦነግ አክራሪ ድርጅት ኢትዮጵያ ከመጣ አንድ አመት ሳያሰቆጥር በተለያዩ ቦታዎች ህዝብ በመግደል ፣ የአገር ሐብት በማውደም ላይ ያስገኛል ። በሞያሌ በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎች በኦነግ ታጣቂዎች ተገለዋል ፣ ተፈናቅለዋል ፣ እንዲሁም ንብረታቸው ወድመዋል ። በቡራዩ በጋሞ ህዝብ ላይ የዘር ማጥፋት ጥቃት በኦነግ መሪነት ተግባራዊ ሆነዋል ። በሐረርና ድሬዳዋ በአማራና የኢትዮጵያ ሶማሌ ህዝብ ላይ በኦነግ ተገለዋል ፣ ተፈናቅለዋል ፣ ንብረታቸው ወድመዋል ። ኦነግ የአዲስ አበባ ህዝብ ላይ ጥቃት ለመፈፀም ልዩ የወታደራዊ ሐይሉ በማሰልጠንና በማስታጠቅ ላይ ነው ። የኦነግ አገር የማፍረስ እቅድ በጌዲዮ ህዝብ ላይ ያደረሰው በደል በታሪክ የሚዘከር ይሆናል ። ኦነግ የጉጂ ኦሮሞ ጎሳ ውሰጥ ሰርጎ በመግባት ከሐምሳ ሺሕ የጌዲዮ ህዝብ ከጉጁ እንዲፈናቀል ተደርገዋል ። ህዝቡም በከፍተኛ የህይወት ሰቆቃ ላይ ይገኛል ። ኦነግ ለደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ሰላምና መረጋጋት ትልቁ የስጋት ምንጭ ነው ። ኢትዮጵያ ሲገባ አንድ ሺህ አምስት መቶ ታጣቂ ሰራዊት የነበረው የኦነግ ተገንጣይ ድርጅት  18 የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ባንኮች በቀን ዘርፎ በወሰደው የህዝብ ገንዘብ በአስር ሺህ የሚገመቱ ምልምል ወታደሮች በማሰልጠንና በማስታጠቅ መሆኑ የሚያሳዩ መረጃዎች አሉ ። ኦነግ በቅርቡ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ውሎ ከሚሴና ሸዋ ሮቢት በከፈተው የሽብር ጥቃት ከ 15 ሰዎች በላይ ሲገደሉ ግምቱ የማይታወቅ ንብረት አውድመዋል ። የኦነግ አክራሪና ተገንጣይ ድርጅት ውስጣዊ ድጋፍ የሚያገኘው ጠቅላይ ሚኒስትር ከሚመሩት የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት መሆኑን የሚያሳዩ ወሰጠ መረጃዎች አሉ ። የአሁኑ የኢህአዴግ ሊቀመንበር ዶክተር አብይ አገርና ህዝብ በኦነግ ታጣቂዎች ሲጠቃ ግልጽ ህጋዊ እርምጃ በኦነግ ላይ ያለመውሰዳቸው በበርካታ ኢትዮጵያውያን ቁጣ ቀስቅሷል ። ዶክተር አብይ ለምን ኦነግን እሹሩሩ እንደሚሉት ለብዙዎቻችን ግልጽ አይደለም ። ኦነግ የአገር ውሰጥ እንዲሁም የውጭ አገር ባለሀብቶች ላይ ግድያ የፈፀመ በህግ የሚጠይቅ ወንጀለኛ እና አሸባሪ ድርጅት ነው ።

    አገርና ህዝብ በኦነግ ወታደራዊ ጥቃት እየታመሰ ፣ በዘር ፖለቲካ ፅንፈኞች የአገር አንድነት እየተናደ ፣ ዘር ላይ ያተኮረ የዜጎች  መፈናቀል ባልተገታበት ፣ ህጋዊ ፍትህ ባልሰፈነበት ጊዜ ፣የዜጎች ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብት በተገደበበት ወቅት ፣ የህዝብ ቆጠራ በተራዘመብት ሁኔታ ፣ መቶ የሚጠጉ የፖለቲካ ፖርቲዎች ባልተቀናጁበት ሁኔታ ፣ የኢኮኖሚ ማሽቆልቆል እየታየ ባለበት ወቅት ፣ አገር በቀል ከብሔር የፀዳ የፖለቲካ አደረጃጀት ያላቸው የፖለቲካ ድርጅቶች በአግባቡ መንቀሳቀስ ባልቻሉበት ሁኔታ እንዴት አገር አቀፍ ምርጫ ማካሄድ ይቻላል ? ። የኢትዮጵያ ውስጣዊ ችግር በምርጫ ብቻ የሚፈታ አይሆንም ። የእምነት ቦታዎች የፖለቲካ አጀንዳ ከማራመድ ይልቅ እምነታቸው በሚያዘው መሠረት ለአገርና ለህዝብ ሰላም ዘብ መቆም ነበረባቸው ። ቤተ እምነቶች ዜጋን የማነፅ ፣ መልካምነትን የማስተማር ፣ ሰላምና አንድነት በህዝቦች መካከል እንዲወርድ መፆምና መፀለይ ነበረባቸው ። አሁንም የኢትዮጵያ ህዝብ ችግር ውሰጥ እንዳይገባ የእምነት ቤተ እምነቶች የላቀ አስተምህሮ እንዲያከናውኑ ይመከራል ። ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም በተመሳሳይ መልኩ ለአገርና ህዝብ የሚበጁ ወቅቱን ያገናዘቡ የኢኮኖሚ ሆነ የፖለቲካ ሆነ የማህበራዊ ጉዳዮች በምርምርና ጥናት የበኩላቸው አገራዊ አሰተዋጽኦ ማድረግ የዜግነት ግዴታ ይመስለኛል ። የኢትዮጵያ ህዝብም ከዘር ፖለቲካ አሰተሳሰብ በቶሎ ተላቆ የቆየውን በአብሮነት የመኖር ፣ የመተሳሰብ ፣ የመረዳዳትና የመከባበር ባህሉ ማጠናከር ይኖርበታል ። አሁን ባለው ሁኔታ በኢትዮጵያ የሐይማኖት ጦርነት እንዳይቀሰቀስ ስጋት አለኝ ።

   የዶክተር አብይ አህመድ አሰተዳደር በቅርቡ መውሰድ ያለበት እርምጃዎች ፦ የምርጫ ሒደት በሚመለከት የህግ ማሻሻያ ማድረግ ፣ በኦነግ ላይ አፋጣኝ ህጋዊ እርምጃ መውሰድ ፣ ህግን መሠረት በማድረግ ሰላምና መረጋጋት ማስፈን ፣ በአዲስ አበባ ጉዳይ ላይ እጆ አለማስገባት ፣ የጋራ መኖሪያ ቤት እድለኞች ቤታቸው እንዲረከቡ ማድረግ ፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት ማጉላት ፣ ለፍርድ የሚፈልጉ ተጠርጣሪዎች ለህግ ማቅረብ ፣ በእስር ቤት ያሉ ተጠርጣሪዎች የፍርድ ሒደት እንዲፋጠን ማድረግ ፣ የክልል ልዩ ሐይል አደረጃጀት በአዋጅ መከልከል ፣ ህገ ወጥ የመሳሪያ ዝውውር ላይ ከፍተኛ ክትትል ማድረግ ፣ ያለፍቃድ መሳሪያ የታጠቀ ማንኛውም ሰው ለህግ ማቅረብ ፣ የዘር ፖለቲካ አደረጃጀት በአዋጅ ማገድ ፣ እንዲሁም የኢህአዴግ የለውጥ ሽግግር ማፋጠን ።

   

 

    

Back to Front Page