Back to Front Page

የሰሜኑ ፖለቲካ ወዴት ማምራት አለበት?

የሰሜኑ ፖለቲካ ወዴት ማምራት አለበት?

(Dagnew Mache A. ዳኛው ማቸ ኣስገደ) 01/10/2011 ዓ.ም

የሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የፖለቲካ አካሄድ ካልተስተካከለ ሃገራችንን ወደ ከፋ የታሪክ ጠባሳ ማምራቷ አይቀሬ እየመሰለ ነው፡፡ የወቅቱ የሰሜን ኢትዮጵያ ፖለቲካ የብሽሽቅና የግለሰቦችና የጥቂት የግለ ሰቦች ስብስብ ረታሁ ተረታሁ ምልልስ እንጂ ዉሃ የሚቋጥር የረዥም ጊዜ የፖለቲካ መስመር የያዘ አይመስልም፡፡ የዚህም መነሻ ኦሆዴድና ብአዴን ስልጣንን ፍለጋ ህወሓትን ለማግለል በፈጠሩት የእጠቀምበታለሁ የሚመስል የከሸፈ እቅድ (ህወሓትን ወደ መቐለ መሸኘቱ እንዳለ ሆኖ) ከመዘርጋቱ ይጀምራል፡፡ ይህ ማለት ህወሓት በፖለቲካ ከተሸነፈች ስልጣኑን እኔ እቆጣጠራለሁ እኔ እቆጣጠራለሁ ያሚል ስሌት በሁለቱም ፓርቲዎች ይዘዉ መነሳታቸውን ነው፡፡ ይሁንና ከሁለቱም ፓርቲዎች የህወሓት የፖለቲካ ስልትን መስበር የሚችልና እርስ ብርሳቸዉም አሰማምቶ የሚመራ ባለ እዉቀት ፖለቲከኛ ስለጠፋ (እድሉን ስላላገኙም ልሆን ይችላል) ተዋህደው ልብ ለልብ እንኳን ባይሆን ሆድ ለሆድም መገናኘት አልቻሉም፡፡ በተቃራኒው ህወሓትን መገሰፅና አልፎም አማራጭ መፈለግ ጀምሮ የነበረዉና ዲሞክራሲና መልካም አስተዳደር በጥብቅ በመሻት ላይ የነበረዉ የትግራይ አብዛሃኛው የሕብረተሰብ ክፍል (በግምት) በብአዴንና ኦሆዴድ መርህ አልባና የዲሞክራሲ መሠረት ያልነበረዉ ግንኙነት ምክንያት ከህወሓት ጋር እንደ የትግሉ ዘመን እንዲጣበቁ እድል ፈጥሯል፡፡ ይህ የትግራይ ህዝብና የህወሓት ግንኙነትም በጠቅላይ ሚንስቴር አብዪ የትግራይ ህዝብ ታሪክንና ጀግኖችን ማንቋሸሽና በትግራይ ህዝብ ላይ ጦርነት ሲያዉጁ የነበሩት የኢሳት ጋዜጠኞችን ስህተታቸውን እንኳ ሳይነግርዋቸው እሰይ አበጃቹህ ማለት እስኪመስልባቸው ድረስ ተፍ ተፍ እያሉ እዉቅና መስጠትን ተከትሎ መላላት ጀምሮ የነበረው ግንኙነት መልሶ በጣምኑ እንዲጠብቅ ሆነዋል፡፡ አሁንም በህግ ሽፋን የኢትዮጵያ ህዝብ በሌብነታቸው የሚያዉቃቸው ግለ ሰዎች አጠገቡ በክብር ጎልቶ የትግራ ሌቦች ማለት ሲጀመር የትግራይ ህዝብ በህግ ልዕልናና በፍትህ አይደራደርምና በአብዪ አስተዳደር ተስፋ ቆርጦ የህወሓት ችግሮች በይደር በመያዝ አቅፎ ተቀበላት፡፡ የአብዪ አስተዳደርንም በጉያህ ያሉት ዘራፊዎች አቅፈህ ይዘህ ምን ከርቁ ታማትራለህ በማለት ህግና ፍትህ ምን ማለት እንደሆነ በተግባር ማስተማር ቀጠለ፡፡ ለዚህም የትግራይ ህዝብን አበጀህ አንተ ጀግና ህዝብ ያስብለዋል፡፡ ባይሆንማ ንሮ በዚህ ስዓት ኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነት ዉስጥ ነበር የምትሆነው፡፡

Videos From Around The World

ብአዴንና ኦሆዴድ ይህንን ችግራቸው ለመሸሸግ ይረዳቸው ዘንድም የኤሪትሪው ፕረዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋርም አላማው ግልፅ ያልሆነ ነገር ግን ህወሓትን አጣብቅኝ ዉስጥ የመክተት የሚመስል መርህ የሌለው ግንኙነት መፍጠር ተጀመረ፡፡ አልፎም የትግራይ ምልሻ ድንበር ላይ ብርድና ፅህይ እየመታዉ ሲብስም እየተዋጋ ባለበት ሁኔት ኢሳያስን ኢህአደግ ባቀናት አዲስ አበባ ከተማ (መለስን ክዳ) ኢሳያስን የጀግና ካባ አለበሰች፡፡ ይህ ለትግራይ ህዝብ (ለኢትዮጵያ ህዝብም ቢሆን) ምን ማለት እንደሆነ መገመት አፍንጫህን በቀኝ እጅህ የመንካት ያህል ቀላል ነዉ፡፡ ይሁንና አላማውና ዉስጠ ሚስጥሩ ህዝብ ያላወቀውና መርህ አልባ ስለነበር አልተሳካም፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ህወሓት አንድም የፖለቲካ ሻጥርና መድሎ ደርሶባት ሁለትም በራሷ እስቲ እነዝህ ነፈዝ የት እንደሚደርሱ ልይ ብላ ጥጓ ይዛ ትመለከትና ምናልባትም በ27 ዓመታት ያላደረገችውን የትግራይ ህዝብን ይቅርታ ጠይቃ ለመካስ እየስራች ነበር (ሙሉ በሙሉ ባይሳካላትም አንፃራዊ ሰላምን ግን አስጠብቃለች)፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን የኦሮሞ ፖለቲካ መጠነኛ መረጋጋት ያገኘ ይመስል ስለ ነበር ስልጣንን ተደላድሎ የመዉሰድ ስራም ሲሰራ እንደነበር ግልፅ ነው፡፡ ይህም የፖለቲካ ሚዛኑ ከሰሜን ወደ ደቡብ አምጥተነዋል ብለዉ እስከ መናገር አድርስዋቸው ነበር፡፡ የኋላ ኋላ ግን የቤት ስራ በዝቶባቸው ሲበታተኑና ሰዎችን ሲቀያይሩ እነዲሁም በሞትና በመፈናቀል የታጀቡ ግጭቶችን ናላቸው ሲዞር ምን ያህል ዝግጁ እንዳልነበሩ አይተናል፡፡ ድሮዉስ ምንም ሳይዝ የሃገሪቱ የፀጥታ መዋቅር (ደህንነት፣ ፌደራል ፖሊስና መከላከያ) ካፈረስ ጠቅላይ ሚንሰቴር ምን

 

የፖለቲካ ልህቅነት ይገኝና፡፡ ቀጥሎም መርህ አልባው የሁለቱም ግንኙነት በዉል በማነቀው (ግን በስልጣን ሽኩቻ ምክንያት በሚመስል) ምክንያት ስፈረካከስ ታይቷል፡፡

ይህ ሁሉ ሆኖ ሲያበቃ የፈደራል መንግስት ከወደ ሰሜን አከባቢ የሚታዩ የፖለቲካ አለመስማማት የወለዳቸው ግጭቶችና አለመግባባቶችን በዝምታ ማለፉ አጀያብ ያስብላል፡፡ በጣም የሚገርመዉ ደግሞ በፌደራል ምንግስት የሚተዳደሩት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዉስጥ እንኳን ተማሪዎች በዘራቸው ሲገደሉና ሲንገላቱ ጠቅላዩ ዝምታ መምረጣቸዉን ብቻ ሳይሆን የራሷ አሮባት የሰው ታማስላለች እንደሚባለው የሌሎች አገሮች ችግርን ለመፍታት (ከተሳካለቸው መልካም ነው ብያለሁ) ጉዞ ስያዘወትሩ ትዝብትን ያስጭራል፡፡ የታሰሩት አስፈትተው ይዘው መጥተዋል ብላችሁ እንዳትሞጉቱኝ፤ እያወራን ያለነዉ በገዛ ሃገራቸዉ እየሞቱ ስላሉት ወጣት ባለተስፋ ኢትዮጵያዉያንን ነውና፡፡ ይህም ለእኔ የሚሰጠኝ ትርጉም የሰሜኑ አለመረጋጋትን የሚሹት (ለጊዜዉም ብሆን፤ የወደፊቱን አብረን የምናየዉ ይሆናል) እንደ ሆነ ነዉ፡፡

 

ይህን ተንተርሶ የሰሜኑ ፖለቲከኞችና ምሁራን ምን ማድረግ ይገባችዋል የሚለዉን እንይ፡፡ 1. የእነ ጃዋር የእስላም ሃገርና መንግስት የመመስረት የረጅም ጊዜ ህልምንና አላማን ተረድቶ የፌደራል መንግስት በዝህ የንድፍ ሃሳብ ቀያሾች ጃዋርና መሰሎቹ መምራትንና መማክርት ማድረግን እንድያቆምና ኢትዮጵያ የብዝሃ እምነቶች መኖርያ መሆንዋን አብዝቶ መፃፍና በጥናት በማስደገፍ ኢትዮጵያን የማይበጅ አካሄድን መቃወም፣ 2. በአማራና በትግራይ ያለው የብሽሽቅ የፖለቲካ አካሄድ ትርጉም ባለዉ ሁኔታ ግልፅ አድርጎ በማሳየት አቅጣጫቸውን እንድያስተካክሉ መምከርና መገሰፅ፤ ብአዴንና ህወሓት አልሰማ ካሉ የፈጠራቸው ህዝብ ነዉና ከስመዉ በሌላ ባለራዕይ ፓርቲዎች እንዲተኩ ማድረግ (ታድያ አደራ አብንና ዓረናን እንዳትሉ፤ ሩቅ የሚሄድ ዐላማም ራእይም ስለሌላቸው)፣ 3. የሰሜኑ ፖለቲካ እንድስተካከል የህዝቦቻችን የታሪክ፣ የእምነት፣ የሃረግና የደም (ሃረጋችን አንድ በደም የተዋለድን የተዛመድን)ና በስነ ልበናዊ ግንባታችን መመሳሰል የሚሳዩ ነገሮች ላይ ትርክት ማብዛት ይበጃል፡፡ ይህም የሚደረገዉ ሌላዉን ለማግለል ሳይሆን (ማግለል ራሱ አይገልፀንም) እንደጥንቱ ኢትዮጵያ አንድ ሆና ትቀጥል ዘንድ ችግሮቻችንን በመፍታት ችግሮቻቸው ከፈቱ የደቡብ፣ ምስራቅ፣ ምዕራብና መሃል አገር ወንድሞቻችን ጋር በመቀራረብና በመመካከር ኢትዮጵያችንን ለማዘመን መሆን ይኖርበታል፡፡ ለዚህም አብዝቶ መስራት፣ 4. አሁን ያለዉ ስህተት (በተለይ የፌደራል መንግስት) አብዝቶ መተቸት፡፡ ኤሪትርያ በመሄድዋ ከልብ እያዘንን ከሆነ (አሰብን ብቻ ማለም ትተን)፣ በመሃላችን የነበረዉና አሁንም ሙሉ በምሉ ያላባራዉ ጦርነት እንደጎዳን የምናስብ ከሆነ ትግራይን የመግፋትና የማሸማቀቅ ዕቅድ የንጋት ቅዠት መሆኑን ማስረዳት፡፡ ነገ አማራዎችና ትግራዎት ጦርነት ቢገጥሙ (በፍፁም የሚሆን አይመስለኝም፤ ማን ማንን ወግቶ ልገድልና ልያቆስል ነው፤ ድብልቅልቅ ያለ እኮ ነው) የዛሬ 20 ዓመት ብኋላ ምን ታሪክ እንደሚተረክ በማስተዋል ከ20 ዓመታት በፊት የተሰራውን ስህተት መድገምና ማለም ቅዠት መሆኑን አምኖ ያለዉ የህዝቡ አንድነትን ማጠናከር (የማይጠቅም ፀብ አጫሪነትን ማስቆም) አለብን፡፡ 5. ጦማርያንና በማሕበራዊ ምድያም (ፎረማለ ምድያም) ላይ የምትንቀሳቀሱ ወንድሞችና እህቶች በደብረፅዮንና አምባቸው ምሃል ያለዉ ክፍተት እንርሳዉ፡፡ እነሱ እኮ እንድ አደራሽ ዉስጥ ቁጭ ብለዉ ይጨባበጣሉ ይወያያሉ፡፡ ብአዴንና ህወሓት መሃከል ያለዉ መኮራረፍ እኛን ልገዛን አይገባም፡፡ እነሱ እኮ ኣብረዉ ተርበዋል፣

የማይገባቸውን በልተዉም ጠግበዉ አብረዉ ህዝብ ላይ ፈንጭተዋል፣ የሚዘረፈም ዘርፈዋል፣ መልካም ነገርም ለኢትዮጵያ አድርገዋል፣ ለወደፊቱም ብዙ መልካም ነገር ይሰሩ ይሆናል፡፡ ታርቀዉም አብረዉ ይጨፍሩ ይሆናል (ብያንስ እንደ ግለስብ)፡፡ በትልቁም ሰዎቹ ነገ ከነገ ብኋላ ተጠርተው ማለፋቸው አይቀሬ ነው፡፡ ታድያ እኛ ሳንተዋወቅ በርቁ በማህበራዊ ምድያ ምን የባኩሰናን? ለምንስ የታሪክ ጠባሳ ፍለጋ ላይ ያስጠምደናል (መልካሙን ማን ልተገብርልን ነዉ)? ሃሳብን መሰርት አርገን ስለሃገራችን ማዉራት እንዴት ያቅተናል? በሶሻል ምድያ በሚለጠፉ ሃሳቦች ላይ አስተያየት ለመስጠት ለምን የፀሃፊዉ ብሄር ፍለጋ ፕሮፋይሉን ለማየት እንሞክራለን? ሃሳቡ ላይ ያለን አመለካከት ለምን በሃሳብ አንገልፅም (ወቸ ጉድ! አህያ፣ አንበጣ በሊታ ምን አመጣዉ)? አህያነቱም አንበጣ በሊታነቱም ተነጥለህ መሆንና ማድረግ እንደማትችል ብታዉቀዉ ራስህን መስደብህን ሲገባህ (ያዉ ከገባህ!) አንገትህ ትደፋለህ!!! ስለዚህ ይህ ወንዝ የማሻግርና ከሌሎች ጋር ማንጋባበት አጉል እምቡር እምቡር ማለቱንና መሰዳደቡን ትተን መርህ ወዳለዉ የሃሳብ ዉይይት መግባት አለብን፡፡ 6. የታሪክ ሽምያን ማቆም አለብን፡፡ ቅዱስ ያሬድ፣ ንጉስ ላሊበላ፣ ቴዎድሮስ፣ ዮዉሃንስ፣ ምንሊክ፣ አሉላ፣ በላይዘለቀና ሌሎችም ቢሆኑ የሁላችንም እነጂ ያንዳችን አይደሉም፡፡ እስቲ ንገረኝ ማናቸዉ ናቸዉ ወይ ስለ አማር ወይ ስለ ትግራይ የተሰዉት፣ የኖሩት፣ የተጠበቡት? መልስ የለህም! ታድያ ምን እዝህ በማያገባን የእኔ የእኔ እያልን ጊዜያችንን እንገድላለን፣ እንልፈሰፈሳለን? ከእነዚህ ብህዋላም እኮ ሐዲስ ዐለማዮህንና ገብረህወት ባይከዳኝንም ታሪክ ሰጥቶናል፡፡ መለስንም በዓይናችን አይተናል (ደሞ ስደቡኛ! መለሰ ከነ ሁለመናዉ የጋራችን ነዉ፤ የኢቲዮጵያ ፕረዚደንትና ጠቅላይ ሚኒስተር እነጂ የትግራይ ምንም ሆኖ አያቅም)፡፡ እና አሁንም የተሻሉ ለመፍጠርም የሰሜኑ ኢትዮጵያ ማህፀነ ለምለም ነው (ለዚህ ፅሑም አዉድ እንድያመች እንጂ ኢትዮጵያ ማህፀነ ለምለም ናት፤ አብዲሳ አጋን፣ ባልቻን፣ አባ ጅፋርን፣ ካዎጠናን፣ ከፋን፣ አለማዮ አቶምሳንና ሌሎችን መጥቀስ ይቻላል)፡፡ ግን ግን በማይረባ የጥላቻ ስብከት ሸፍነን ቦታ አሳጣናቸው፡፡ እናም የሁላችንን ሆነዉ ያለፉት መሪዎች፣ ተዋጊዎች፣ ምሁራንና የሃይማኖት አባቶችን ታሪክ ሳይፈቅድልን መሻማት መሞከር የጊዜ ክሳራን እንጂ መልካም ነገር አናገኝበትም፡፡ እነሱም መቸም ቢሆን ያንዳችን ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ይህ ከናፈቀንና ወደልባችን ካልተመለስን ለወደፊቱ የኔ አምባቸው፣ ደብረፅዮን፤ ገዱ፣ አባይወልዱእያልን ልንጣራ ይሆናል (ከዚህ ፈጣሪ ይሰዉረን)፡፡ ደሞ ጀግና ያልሆኑትን በግድ ጀግና ልናደርግ (ችግራቸዉን ፈትተዉ ታርቀዉ የህዝቡን ንሮና የኢትዮጵያ መፃኢ እድል ላይ በጥልቀት ከልብ መስራት ከጀመሩ ጀግና ለመባል ይበቁ ይሆናል)፡፡ 7. ፍቺም የግድ ከሆነ (ሆ!) ሰላማዊ ፍችን ማስብና የወደፊት ጂኦፖለቲካንን መረዳትን እንጂ እንካ ስላንክያ ወድያ ይባል (ወድያ መባል ያለበት እንኳን ፍቺ ማሰቡን ነው!)፡፡ እናማ ውንድም እህቶቼ የረጋ ወተት ቅቤ ይወጣዋል ነዉና ነገሩ፣ በግል ምክንያቶቻቸው የሰከሩት ፖለቲከኞቻችን ጋር መስከር ተያይዞ ገደል መግባት መሆኑን እንረዳ፡፡ ተረድተንም ከስሜት ወጥተን ናና ተዋጋልኝ ካልሆነ እኔ ስልጣኔንና ምቾቴን አጣለሁ ለምለን ገደል ግባ! ህዝብና ሃገር እንጂ አንተማ በምቾትም ባይሆን መሞትህ መች ይቀራል ማለት ይልመድብን፡፡

ቸር ያሰማን!

Back to Front Page