Back to Front Page

ስለ ሰላም እንዘምር፤ለዘላቂ ሰላም እንታገል!

ስለ ሰላም እንዘምር፤ለዘላቂ ሰላም እንታገል!

ታጁ ሙሓመድ ያሲን

22/03/2012ዓ/ም

muhamedyassintaju@gmail.com

ኢትዮጵያ ከደርግ ውድቀት በኋላ አይታው የማታውቀውን የሰላም እጦት ላይ ትገኛለች።ዜጎች ለስራ በሰላም ወጥተው በሳላም ለመመለስ እርግጠኛ መሆን የማይችሉበት ደረጃ ተደርሰዋል። ተማሪዎች በሄዱበት ዩኒቨርሲቲ ተምረው ተመርቀው መውጣታቸው እና እንዲማሩ ከላካቸው ቤተሰባቸው ለመገናኘት እርግጠኛ መሆን አልቻሉም።ቀደም ሲል ተጋሩ ብቻ በማንነታቸው ምክንያት እየተገደሉ ትግራይ የተገደሉ ልጆችዋ ሬሳ ስትቀበል እንደቆየች የሚታወቅ ጉዳይ ነው።ይህ ብሄር ተኮር ጥቃት በአሁኑ ሰዓት አድማሱ በማስፋት ሁሉንም የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች በሌላ ክልል የተገደለውን ልጃቸው ሬሳ መቀበል ጀምረዋል።የኢትዮጵያ የሰላም እጦት ጣርያ ነክቶ ሃገሪቱ እንደምትበተን እርግጠኛ በመሆን መቼ ነው የምትበተነው? ስትበትንስ ምን ያህል ህዝብ ያልቅ ይሆናል?በዝያን ግዜ በንፅፅር ሰላሙን ጠብቆ የሚዘልቅ ክልል ይኖር ይሆን?ወደሚሉ ጥያቄዎች የተሸጋገርንበት ወቅት እንገኛለን።ይህ የመበታተን አደጋና የህዝቦች የእርስበርስ እልቂት ቀጥለው ባሉት አራት አምስት ወራት ጎልቶ እንደሚወጣ ግምቶቹ እተበራከቱ መጥተዋል።ይህ ሁኔታ ይበልጥ ስለ ሰላም ለሚዘምሩና ለዘላቂ ሰላም ለሚታገሉ ህዝቦች እና ሰላም ወዳድ አመራሮች ግዜ እንዲያጡ በማድረግ አጣቢቅኝ ውስጥ የሚከታቸው ይሆናል።ይሁን እና ህዝቦች ሰላማቸው ሲነጠቅ እጅ እና እግራቸው አጣጥፈው ስለማይቀመጡ ከተቻለ ኢትዮጵያ ወደነበርችበት ሰላምዋ ተመልሳ ዘላቂ ልማት የምታመጣበት አልያም መበታተንዋ እርግጥ ከሆነ ደግሞ የህዝቦች ኢልቂት የሚቀንስበት መንገድ ለመጦቆም በማሰብስለሰላም እንዘምር፤ለዘላቂ ሰላም እንታገል በሚል ርእስ ይህንን አጠር ያለ ፅሁፍ ተዘጋጅተዋል።በዚህ ፅሑፍ ውስጥ የተቀመጡ የሰላም ጠንቅ ምክንያቶች እና መፍትሄዎች ላይ በመደገፍም ይሁን በመቃወም ለመወያየት ከሚፈልግ ሁሉ ፀሓፊው ለመወያየት ዝግጁ ነው።

1.  በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ለምን በሰላም እጦት ተናጠች?

Videos From Around The World

ከደርግ ውድቀት በኋላ ኢትዮጵያ ላለፉት 27 ዓመታት በልማት ፣ ሰላም እና ዲሞክራሲ መንገድ ስትጓዝ እዛም እዚህም አልፎ አልፎ የሚከሰቱ ግጭቶች መኖራቸው የማይካድ ነው።በእነዚህ ዓመታት ከተፍኛ ግጭቶች ተከስተዋል ከሚባሉት ውስጥ የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት እና የ97ዓ/ም ምርጫ ይጠቀሳሉ።በሁለቱም ግጭቶች የህዝብ መፈናቀል፣ንብረት ወድመዋል፣የዜጎች ህይወት ተቀጥፈዋል ኣካላቸውም ጎድለዋል።በእነዚህ ወቅቶች የኢትዮጵያ ህዝብ ተስፋ የመቁረጥ እና የመበታተን አደጋ አልተስታዋለበትም ብቻ ሳይሆን በመሪ ድርጅቱ ኢህአዴግና ድርጅቱ በሚመራው መንግስት ግጭቶቹ እንደሚፈቱ እርግጠኛ ነበር።በዚህ ምክንያት ህዝቡ ሙሉ ድጋፉ ለኢህአዴግ እና ኢህአዴግ ለሚመራው መንግስት ሰጥተዋል።ኢህአዴግም ከህዝብ ባገኘው ድጋፍ ታግዞ ተክስቶው የነበሩ ግጭቶች መፍትሄ እንዲያገኙ በማድረግ ወደ ቀጣይነት ያለው የልማትና የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ገብተዋል።ኢትዮጵያ በፍጥነት እያደጉ ካሉ ሃገራት ተርታ ተጠቃሽ እንድትሆን አስችለዋታል።በዲፕሎማስያዊ መስክም እምርታ ማስመዝገብ ችላለች።ይህ ሐቅ በኢትዮጵያ ህዝቦች እንዲሁም በዓለም አቀፍ ተቋማት ሳይቀር የተረጋገጠ ሐቅ ነው።

ከላይ የተጠቀሰው የ27 ዓመት የኢትዮጵያ ጉዞ ሐቁ ይህ ከሆነ ታድያ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ለምን በሰላም እጦት ተናጠች?የሚል ጥያቄ መመለስ የግድ ይላል።ይህ ጥያቄ መመለስ ያለበት ከኢትዮጵያ የውስጥ ሁኔታ ትንታኔ መጀመር ይገባል።ኢህአዴግ በውስጣዊ ችግሮቹ ምክንያት ኢትዮጵያ የመምራት አቅም እየተዳከመ መምጣቱ፤በውስጡ የተፈጠረውን ዝቅጠት ምክንያት ተሸንፎው የነበሩ የትምክህት አስተሳሰሰቦች እና ተግባራት እንዲያቆጠቁጡ እድል ፈጠረ።ይህንን ችግር ህዝቦች ብሶታቸው ለመግለፅ ኢህአዴግ የተሻለውን አመራር እንዲሰጥ የሚጠይቁ ሰልፎች እና ግጭቶች እዛም እዚህም መታየት ጀመሩ።ኢህአዴግ ከፍተኛ የክራይ ሰብሳቢነት ዝቅጠት ወድቆ ስለ ነበር በጥልቀት መታደስ ዳግም በጥልቀት መታደስ በሚሉ መድረኮች ድርጅቱ ከድክመቶቹ ለመውጣት ቢሞክርም ከድጡ ወደ ማጡ ሆነበት።በዚህ ግዜ በኢህአዴግ ውስጥ ወደ ገዢ መደብ ለመሸጋገር በዝግጅ ላይ የነበረውን ሃይል የስልጣን ዝፋኑን ተረከበ።

ይህ በኢህአዴግ ውስጥ ለረጅም ግዜ ዝግጅት በማድረግ የኢህአዴግ መዝቀጥ ሲጠበባቅ የነበረ የትምክህት ሓይል ድርጅቱ ሙሉ ለሙሉ ህዝባዊ ስብእናውን ካጣ በኋላ ስልጣኑን በመረከብ ኢትዮጵያ እሱ ወደሚፈልጋት መንገድ እንድትጓዝ መምራት ጀመረ።በልማታዊ ዲሞክራሲ መስመር ምትክ የመደመር እሳቤ አንግቦ መንቀሳቀስ ጀመረ።ፍቅርና ይቅርታን ሰበከ።በኢትዮ ኤርትራ የነበረ የጥላቻ ግንብ በማፍረስ የፍቅር ድልድይ ሰራሁኝ አለ።እስረኞች ፈታ፤በስደት የነበሩ ኢትዮጵያውን ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ አደረገ፣የፖለቲካ ምህዳር ለማስፈት በሚል በሽብር እና በአገር ክህደት ታግደው የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶች እና ግለሰቦች ወደ አገር ውስጥ ገብተው እንዲታገሉ ጥሪ አቀረበ ።ሁሉንም እስከ መስከረም 2011ዓ/ም ጓዛቸው ጠቅልለው ገቡ።በአንፃሩ በፌዴራል ስልጣን የነበራቸው የህወሐት አመራሮች ከስልጣናቸው አስወገደ ሌቦች ናቸው ያላቸውን የህወሓት አመራር እና ታጋዮች አሰረ።ቀደም ሲል የተገለፀውን እርምጃዎች በመውሰዱ እዛም እዚህም ውዳሴዎች አገኘ።የ100ቀናት በዓለ ስሜት በአዲስ አበባም በባህርዳርም ተከበረ።ለውጥ ለውጥ ሸተተ።በእነዚህ ድጋፍ የሰከረውን የለውጥ ሐይል ጉልበት ይሆኑኛል የሚላቸው ንግግሮች አደረገ።የቀን ጅቦች ብዙ ሰው ሳያላምጥ የዋጠው አባባል ነበር።በእነዚህ ስራዎች በከተሞቹ ሰፊ ተቀባይነት ያገኘ መሰለ።

የኢትዮጵያ የሰላም እጦት ሁኔታ ግን ከግዜ ግዜ እየተባባሰ ሄደ።የህዳሴው ግድብ መሃንዲስ እንጅነር ስመኘው በቀለ በመስቀል አደባባይ በጠራራ ፀሐይ ተገድሎ ተገኘ።ዜጎች በድንጋይ ተወግሮው፣በጩቤ እና በገጄራ ተወግተው እና አንገታቸው ተቀልተው ተገደሉ።በጅምላ መቃብር ተቀበሩ።ህዝቦች በብሄር ተኮር ጥቃት በሚልዮኖች የሚቆጠሩ ከቀያቸው ተፈናቀሉ።ይህ ሁሉ ችግር ሲፈጠር የስልጣን ዙፋኑን የተቆጣጠረው የለውጥ ሃይል ነኝ ብሎ እራሱን የሰየመው ሐይል ስብከት ብቻ ሁኖ ቀረ።በ2011ዓ/ም መጨረሻ ሰኔ 15 ቀን የአማራ ክልል መንግስት አመራሮች እና የኢትዮጵያ ጠቅላይ ኢተማጆር ሹም ተገደሉ።ይህ ፍፃሜ ለኢትዮጵያ ህዝብ ከፊት ከነበሩ ችግሮች ተዳምሮ ተስፋ አሰቆራጭ ተግባር ሁኖ ቀጠለ።

በዚህ ያለበቃ የለውጥ ሐይል ነኝ ባዩ በድን ውሁድ ፓርቲ እመስረታሎህ በሚል እንቅስቃሴ በመጀመሩ ምክንያት ጣርያ ለመንካት በመቃረብ ላይ የነበረውን የሰላም እጦት ጫፍ እንዲረግጥ አደረገው።በአሁኑ ሰዓት በውሁድ ፓርቲ ምስረታ ምክንያት ከትግራይ እና ዓፋር ውስጥ ካሉት ዩኒቨርሰቲ ውጭ ያሉ ዩኒቨርሲቲዎች መበጣበጣቸውን ቀጥለዋል።አንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲውን ለቀው እንዲወጡ እያደረጉ ናቸው።ይህንን የሚያባብስ መግለጫ በለውጥ ሐይል ነኝ ባዩ በመሰጠቱ ምክንያት ይበልጥኑ ተካረዋል።መንግስት ዩኒቨርስቲዎች እስከ መዝጋት እንደሚሄድ ዝተዋል።ይሁን እና ህዝቡ ያለው ስጋት ዩኒቨርሲቲዎች እንዳይዘጉ አይደለም።የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ልጆቹ የእርስበርስ ብጥብጥ መተላለቅ ሳያስከትል ወደ ክልላቸው በሰላም ይመለሱ ይሆን? ከቤተሰባቸው ይገናኙ ይሆን? ነው የህዝቡ ጥያቄ።

ከላይ ከተጠቀሱ ነጥቦች ለመገንዘብ እንደሚቻለው በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በሰላም እጦት እየተናጠች ያለቸው በስመ ለውጥ የስልጣን ዙፋኑን የተቆናጠጠው ሐይል በሚከተለው ፀረ ህዝብ አመራር መሆኑን መረዳት ይቻላል።

ከውጭ ሁኔታ ስንመለከት ደግሞ ቻይና ወደ ዓለም መሪነት ለመምጣት በምታደርገው እሽቅድድም እና አሜሪካ ከመሪነትዋ ላለመውረድ የሚደረግ ከባድ ፍኩክር ተጠምደው እንዳሉ ይታወቃል።ይህ ሁኔታ የዓለም ሰላምም እየተፈታተነው ያለ ጉዳይ ነው።የምዕራቡ እና የዓረቡ መንግስታት ቻይና ከኣፍሪካ ማስወጣት የሚቻለው የአፍሪካ ቀንድ በመቆጣጠር ነው የሚል እምነት በመያዝ ፖሊሲ ቀርፀው በመረባረብ ላይ ናቸው።ይህን ሁኔታ የተመቻቸበት አገር ደግሞ ኢትዮጵያ ነች።ኢትዮጵያ ያላት ተፈላጊ ጂኦ ፖለቲካዊ አቀማመጥ እንደተጠበቀ ሆኖ በኢህአዴግ መዝቀጥ ተጠቅሞ ስልጣን የጨበጠውን ሐይል ምርጥ ተላላኪ አግኝተዋል።የስልጣን ዙፋኑን የተቆጣጠረው የነውጥ ሐይል እና የምዕራቡ እና የዐረቡ መንግስታት በጋራ በሚፈጥሩት ችግር ነው ኢትዮጵያ በሰላም እጦት እየተናጠች ያለችው።

ኢትየጵያ በሰላም እጦት እየተናጠች ያለችው የለውጥ ሐይል ነኝ ባዩ በሚያራምደው ፀረ ሕገ መንግስትና ፀረ ሕብረ ብሄራዊ ፌደራሊዝም ስርዓት ተግባር ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ ይህ ሐይል ለውጭ ጣልቃ ገብነት የተመቸ በመሆኑ ምክንያት የምዕራቡ እና የዓረቡ መንግስታት በኢትዮጵያ ጉዳይ እንደፈለጉት የሚፈተፍትበት ዕድል ስለ ፈጠረላቸው ጭምር ነው።

2.  ይህ የለውጥ ሐይል ነኝ ባይ ቡድን ከድክመቶቹ የመማር እድል ይኖሮው ይሆን?

አንድ ፖለቲካዊ ስርዓት የሚመራ ፖለቲካዊ ድርጅት ከድክመቶቹ የመውጣት ዕድል አለው?ወይስ የለውም?የሚለው ጥያቄ ለመመለስ ብዙዎቹ የፖለቲካ ተንታኞች ህዝብ ለማታገል የሚያስችል የጠራ ህዝባዊ መስመር፣ ህዝባዊ ውግንናው እና ለህዝብ ጥቅም ሲል የሚያካይደው የውስጥ ትግል እንደመመዘኛ ሲጠቀሙ ይስተዋላሉ።በዚህ ፅሁፍም ለዚህ የስልጣን ዙፋኑን የተቆጣጠረው የለውጥ ሐይልነኝ ባይ ሐይል ከላይ የተጠቀሱትን መመዘኛዎች በመጠቀም በስልጣን ላይ ያለውን ሐይል የመዳን እድል አለው ወይስ የለውም የሚል ይተነትናል።

አሁን ኢትዮጵያ በመምራት ያለውን ሐይል የኢህአዴግን ዝቅጠት በመጠቀም በጎዳና ነውጥ(በቀለም አብዮት)የመጣ ሐይል ነው።ይህ ሐይል ከውስጥም ከውጭም ነውጡን ሲመራ ህዝብን የሚያታግል መስመር እና የተሻለ አማራጭ በማቅረብ ሳይሆን የህዝብን ብሶት በማጋጋል እና የኢህአዴግ የውስጥ ድክመት ይበልጥኑ እንዲባባሱ በማድረግ ወደ ስልጣን የመጣ የነውጥ ሐይል ነው።ይህ የነውጥ ሐይል ስልጣን ከያዘ ከአንድ ዓመት ተኩል በላይ ያስቆጠረ ቢሆንም እስካአሁን ድረስ ይህ ነው የሚባል የመታገያ መስመር በግልፅ ማስቀመጥ አልቻለም።በቅርቡ ታትሞ የቀረበ ራሱን ሪኦቶ (አይደሎጂ)እንዳልሆነ ያወጀ መሆኑን የሚነገረለት መፅሓፍ መደመር በግልፅ ያስቀመጠው የመታገያ መስመር የለውም። እንዲያውም በስመ አገር በቀል እሳቤ የኒዮ ሊበራሊዝም እሳቤን ወደ ኢትዮጵያ እንዲገባ ያደረገ እንደሆነ እና አሃዳዊ ስርዓትን የሚያቀነቅን መሆኑ የብዙ ፖለቲከኞች እና ሙሁራን ድምዳሜ ነው።ከዚህ በተጨማሪ በቅርቡ በስመ ውህደት ራሱን ብልፅግና ፓርቲ ብሎ የሰየመ ቡድን ስራ አስፃሚ ኮሚቴው እና ምክርቤቱ ህገ ደምብ ተወያይቶ ሲያፀድቅ የሚታገልለት ፕሮግራም ግን እስከአሁን ድረስ ግልፅ ማድረግ አልቻለም።ከዚህ ተግባር መረዳት የሚቻለው በኢህአዴግ ውስጥ በነበረበት ግዝያትም ይሁን የአንደ ዓመት ተኩል የስልጣን ጉዞ የጠራ መስመር ከማቅረብ ይልቅ ራሱን በመደበቅ ግዝያዊ የህዝብ ሰሜት በመጠቀም በስልጣን የመቆየት ስልት ለመከተል መምረጡን አመላካች ነው።ስለዚህ ህዝብን የሚያታግል የጠራ መስመር ባለ መያዙ ምክንያት ከድክመቶቹ እና ውድቀቶቹ የመማርም የመዳንም እድል የለውም።

በቀለም አብዮት ወደ ስልጣን የመጣውን ሐይል የጠራ ህዝብ የሚያታግል መስመር እንዳልያዘ ቀደም ሲል የተገለፀ ሲሆን በህዝባዊ ውግንና መነፀር ወደ መመልከት እንሸጋገር።ይህ ሐይል ወደ ስልጣን የመጣው የኢህአዴግ ዝቅጠት በመጠቀም እና የጎደና ነውጥ በማቀጣጠል ነው።በዚህ የጎደና ነውጥ ወጣቶች ከፈዴራል መስግስት እና ወጣቶቹ እርስ በራሳቸው በብሄር ተኮር ግጭት እንዲጋጩ በማድረግ የብዙ ወጣቶች ሂወት ቀጥፈዋል።ይህ የለውጥ ሐይል ነኝ ባይ ብዱን የወጣቶች ደም እና አጥንት ከቁብ ሳይቆጥር በፍጥነት ወደ ስልጣን የሚወጣበትን መንገድ እያማተረ የነበረ ሐይል ነው።ለስልጣን በነበረው ጥማት ምክንያት ፍጅቱ ከውስጥም ከውጭም ሁኖ በመምራት እንዲባባስ እያደረገ የነበረ ቡድን ነው።ስልጣን ከተቆጣጠረ በኋላም ያለ ነውጥ ስልጣኑን ማቆየት ስለ ማይችል እዛም እዚህም ግጭቶች በመምራት እና በማቀጣጠል ወገኖች በግፍ እንዲገደሉ ህዝቦች ከቀያቸው እንዲፋናቀሉ እየደረጋ ያለ ሐይል ነው።በዚህ ሰላም እጦት ምክንያት ለ27 ዓመታት ኢትዮጵያ ያስመዘገበችው እድገት በግልፅ ወደ ኋላ እየተመለሰ ያለበት ሁኔታ እየታየ ነው።ኢትዮጵያ በዓመት ከ10 % በላይ እደገት እያዝመዘገበች የነበረች፤ግሽበት ከ10 % በታች እንዲሆን ያስቸለች አገር ነበረች።የስልጣን ዙፋኑን የነውጥ ሐይሉ ከተቆጣጠረው ወዲህ ግን እድገትዋ ወደ 7 % አጠቃላይ ግሽበት ደግሞ 17 % ደርሰዋል።የሰላም እጦቱ የኢኮኖሚ መዳከም ወልዶ ህዝብ በኑሮውድነት የሚሰቃይበት ሁኔታ ፈጥረዋል።የኢትዮጵያ ሁኔታ እንዲህ እያለ የነውጥ ሐይሉ የሰላም እጦትን ችግር የሚፈታ እርምጃዎች ከመውሰድ ይልቅ ሰላምን የሚያውኩ እርምጃዎች፤የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የሚያድግበት መንገድ ከመቀየስ ይልቅ በስልጣን የሚቆዩባቸው ካርዶች በመምዘዝ (የንግድ ተቋማት ወደ ግል እንዲዛወሩ፣ውሁደ ፓርቲ ምስረታ ምርጫ እንዲራዘም በማድረግ)ህዝብን እያወናበደ ያለ ፀረ ህዝብ ሐይል ነው።ይህ የነውጥ ሐይል የህዝብ ውግንና የሌለው ፀረ ህዝብ ሐይል በመሆኑ ምክንያት ከድክመቱ የመማር እና የመዳን እድል የለውም።

ህዝብን የሚያታግል የጠራ መስመር እና ለህዝብ ወግኖ ከመታገል አንፃር በማየት የለውጥ ሐይል ነኝ ባይ ሐይል ፀረ ህዝብ መሆኑን እና ከድክመቱ የመማርም የመዳንም እድል እንደሌለው ተመልክተናል።ቀጥለን ለህዝብ ጥቅም ሲባል የሚካሄዴውን የውስጥ ትግል በሚል መመዘኛ ይህንን የነውጥ ሐይል ወደ መመዘን እንሸጋጋር።

ከላይ እንደተመለከትነው ህዝብን የሚያታግል የጠራ መስመር የሌለው እና የህዝብ ውግንና የሌለው ሐይል ፀረ ህዝብ ሐይል ነው የሚሆኖው።ከድክመቶቹ የመማርም የመዳንም እድልም አይነሮውም።ይህ ማለት ደግሞ ለህዝብ ጥቅም ሲባል የሚካሄዴው የውስጥ ትግል አይኖርም ማለት ነው።ይህ ሐቅ እንደተጠበቀ ሁኖ በኢትዮጵያ ስልጣኑን የተቆጣጠረወን ሐይል በተግባር እየተገለፀበት ያለውን መንገድ እና በዚህ ሐይል ውስጥ ያሉትን ቅራኔዎች መመልከት ይበልጥኑ ግልፅ ያደርገዋል።

ይህ በነውጥ መንገድ ወደ ስልጣን የወጣውን ሐይል ለህዝብ ጥቅም ሲል የሚያካሄደው የውስጥ ትግል የለም።የዚህ የነውጥ ሐይል ያለው ዓላማ የያዘውን ስልጣን ዘለአለማዊ ማድረግ ነው።ይህንን ዓላማው ለማሳካትም የተላያዩ እርምጃዎች በመውሰድ ላይ ነው።በመጀመርያ የወሰደውን እርምጃ ህገ መንግስቱ እንዲናድ ማድረግ ነው።በዚህ መሰረትም ህገ መንግስት የሚደረምስ ተግባራትን ሲፈፅም ከርመዋል።ፓርላማ እና ፈዴሬሽን ምክርቤት አቅመቢስ እንዲሆን አድርጎታል።ሁለቱም ምክሪ ቤቶች ህገ መንግስት በግላጭ ሲጣስ ትንፍሽ ሳይሉ አልፈውታል።የኢትዮጵያ ሱማልያ እና የደቡብ ህዝቦች ክልላዊ ስልጣናቸው ተጥሶ በኮማንድ ፖስት ሲተዳደሩ ሁሉቱን ምክርቤቶች ለምን ክልላዊ ስልጣናቸው ተጣሰ ብለው እንኳን መጠየቅ አልቻሉም።የፈደሬሽን ስልጣን ለወሰን ኮሚሽን ተላልፈ ሲሰጥ ፓርላማ አዋጁን ሲያፀድቀው ፌዴሬሽን ምክርቤትም የኔ ስልጣን ነው ብሎ ትንፊሽ ማለት አልቻለም።የህገ መንግስትና ህብረ ብሄራዊ ፌደራሊዝም መፍረስ ቀስ በቀስ የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲለማመደው እየተደረገ ነው።

ይህ የነውጥ ሐይል ስልጣኑን ለማራዘም ሲል ኢህአዴግ በማፍረስ አዲስ ፓርቲ ለመመስረት በመሯሯጥ ይገኛል።ይህ አዲስ ፓርቲ በነውጡ ሐይሉ አጠራር ብልፅግና ፓርቲ በመመስረት የያዘውን ስልጣን ይዞ ለመቀጠል የሚያስችለውን ስራ እየሰራ ይገኛል።ይህ እንቅስቃሴ ክልል ማእከል አድርገው ለሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች የማክሰም ዓላማ አንግቦ እንዲከስሙ አድርገዋል።ይህንን ሂደት በማጠናከር አሃዳዊ ስርዓት የመመለስ እንቅስቃሴው አጧጥፎታል።

ከላይ ከተጠቀሱት በተጨማሪ ስልጣን የማራዘምያ መንገድ ምርጫን እንድራዘም ማድረግ ነው።ይህንን የነውጥ ሐይሊ ለምርጫ ዝግጅት ሲያደርግ ካለ መተያቱ በተጨማሪ በየ5 ዓመቱ ምርጫ ማካሄድ የግድ አይደለም ለ30 ዓመታት ያለመርጫ የሚመሩ መንግስታት እንዳሉ መስበኩን አጠናክሮ ቀጥለዋል።

ይህንን የነውጥ ሐይል ከላይ የተጠቀሱትን እርምጃዎች ሲወስድ በይፋ ሲሆን ከዚህ ኢፋዊ እንቅስቃሴ በተጨማሪ ኢፋ ያልሆኑትን ተግባራት እንዲፈፀሙ እና የስልጣን ዕድሜው እንዲራዘም እያደረገ ነው።መንግስት በሚያስተዳድረው አገር እንዲያውም የሰላም ኖቤል ተሸላሚ ሐይል ባለበት አገር የህዳሴው ግድብ መሃንዲስ እንጅነር ስመኘው በቀለ ተገድለዋል።ግድያው እያጣራሁት ነው ሲል ቆዩቶ እንጅነር ሰመኝ ራሱን አጠፋ የሚል መግለጫ ሰጠ።የአማራ መንግስት ሃላፊዎች መፈንቅለ መንግስት ነውበተባለለት እንቅስቃሴ ተገደሉ።የኢትዮጵያ ጠቅላይ ኢተማጆር ሽምም በዛን ግዜ ተገደሉ።የአማራ ክልል ሃላፊዎች እና የጠቅላይ ኢተማጆር ሹም ግድያ ከአራት ወራት በላይ የመጣራት ግዜ ፈጅቶ የተልፈሰፈሰ መግለጫ በመስጠት ተጠቃለለ።በኦሮምያ ክልል የመንግስት ሐላፊዎች በጠራራ ፀሐይ ማን እንደሚገድላቸው የማይታወቅ ተገድለው እየተገኙ ነው።ባንኮች በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ በብዛት ተዘርፈዋል።በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ማንነት መሰረት ያደረገ ጥቃት ተፈፅመዋል።እነዚህ ተግባራት በነውጥ ሐይል ታቅደው በጥንቃቄ እተገመገሙ እና እየተመሩ የተፈፀሙ መሆናቸውን ብዙዎቹ ይስማሙበታል።

የነውጥ ሐይሉ በወሰዳቸው እርምጃዎች ቅራኔዎች እየተካረሩ የመጡበትን ሁኔታ ተፈጥረዋል።የመጀመርያው ቅራኔ ከነውጥ ሐይል ውስጥ ያለውን ቅራኔ በግዜ ሂደት እየጨመረ እና እየተጠናከረ መጥተዋል።ይህ የነውጥ ሐይል ማእከሉ ስልጣን መቆጣጠር ስለ ሆነ ስልጣኑን የሚቀናቀኑ ግለ ሰዎች የማስወገድ እርምጃ በመውሰድ ለማስታገስ እየሞከረ ቢሆንም ቅሬታን ቅሬታን እየወለደ የውስጥ የመታማመን ሁኔታ ከግዜ ወደ ግዜ እየተሸረሸረ የሄደበት ሁኔታ ተፈጥረዋል።ውስጥ ለውስጥ በመብላላት ያለውን የውስጥ ቅራኔ ጎልቶ መታየት ያልጀመረ ቅራኔ መስሎ ቢታይም የህዝብ ትግል ተጠናክሮ በሚወጣበት ግዜ ይህ ሓይል በላቀ ደረጃ እርስ በርስ የሚባላበት ሁኔታን ይፈጠራል።

ከዚህ በተጨማሪ ይህንን የነውጥ ሐይል በወሰዳቸው እርምጃዎች ምክንያት እየታየ ያለ ቅራኔ በህገ መንግስት እና ሕብረ ብሄር ፈዴራሊስት ሐይሎች መሃከል እና የአሃዳዊ ስርዓት አቀንቃኞች መሃከል ቅራኔው እየተካረረ መጥተዋል።ይህ ቅራኔ በቅጡ መፍታት ካልተቻለ ኢትዮጵያ ወደ መበታተን መንገድ የሚወስዳት ቅራኔ ነው።ህዝባዊ መሰረት በነበረው ኢህአዴግ ኢትዮጵያ እየተመራች በነበረችበት ወቅት እነዚህ ቅራኔዎች ህገ መንግስታዊ መልስ እንድያገኙ በማድረግ እንዲፈቱ አድርገዋል።የ27 ዓመታት የሰላም ጉዞም ከውነዋል።የነውጥ ሐይሉ የስልጣን ዙፋኑን ከተቆጣጠረ ወዲህ ህገ መንግስቱ እንዲናድ በማድረጉ ምክንያት እነዚህ ቅራኔዎች ተካረው ኢትዮጵያን እስከ መበታተን የሚያስችል ዓቅም ፈጥረዋል።

ሌላው ቅራኔ የህዝብ ተጠቃሚነት ማእከል ያደረገ እና ባለ ሀብቱ ብቻ ተጠቃሚነት ማእከል ያደረገ ትግልም በመካረር ላይ ያለ ቅራኔ ነው።የነውጥ ሐይሉ አየር መንገድ፣ቴሌ፣የሃይል ምጭ የመሳሰሉ ተቋማት ወደ ግል እንዲሚያዛውራቸው ከገለፀበት ቀን ጀምሮ ቅራኔው መካረር ጀምረዋል።የመጀመርያው ቅራኔ በነዚህ ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞች ህልውና አደጋ በመውደቁ ምክንያት ሰራተኞች ከፍትኛ የዋስትና ማጣት አደጋ እንዲደቀን አድርገዋል። ሌላው ቅራኔ ደግሞ እነዚህ ተቋማት ህዝብ በብዛት የሚገለግልባችው እና ለማስፋትም የመንግስት የተመረጠ እና የተቀናጀ ጣልቃ ገብነት የሚጠይቁ በመሆናቸው ምክንያት በለሃብቶቹ ከተቆጣጠሩት ዋጋቸው በድሃ ህዝብ የማይቀመሱ ይሆናሉ እንዲሁም በለሃብቶች ትርፍ በሚያገኙበት ቦታ ብቻ ስለሚያተኩሩ የተዘነጉ ህዝቦችን ይፈጥራል ከሚል የኢትዮጵያ ህዝቦች ከፍተኛ ስጋት ተደቅኖባቸዋል።ከዚህ በተጨማሪ የኑሮ ውድነቱ ጣርያ ነክተዋል እና ቅራኔው ይበልጥ እየተካረረ እንዲሄድ ያደርገዋል።

ከላይ በዝርዝር እንደተገለፀው የነውጥ ሐይሉ የፈጠራቸው ወይም እንዲባባሱ ያደረጋቸው ቅራኔዎች እና የፈፀማቸውን ወንጀሎች ለማስተካከል መሞከር ራስህን ማጥፋት ነው የሚሆንበት።ኢትዮጵያ ውስጥ የነውጥ ሐይሉ የፈጠራቸውን ቀውሶች ለማረም የግድ የነውጥ ሐይሉ ለህግ ማቅረብን ይጠይቃል።ከላይ የተጠቀሱ ችግሮች እና ቅራኔዎች የለውጥ ሐይል ነኝ ባይ ቡድን ይፈታቸዋል ብሎ መጠበቅ ከእባብ እንቁላል እርግብ ለማግኘት እንደመመኮር ይቆጠራል።ታድያ ምንይደረግ?ለሚለው ጥያቄ ወደ መመለስ እንሸጋገር።

3.  ስለ ሰላም እንዘምር፤ለዘላቂ ሰላም እንታገል!

የፌዴራል ስልጣን የተቆጣጠረው የነውጥ ሐይል ከድክመቶቹ የመማር እድል የለውም።ይልቁንስ የጥገኛ ፍላጎቱ ለማርካት ሲል የኢትዮጵያ ሉአላዊነት አሳልፎ በመስጠት ከእጃዙር ቀኝ ገዢዎች በጥብቅ በመተሳሰር እየሰራ ነው።ስለዚህ ይህንን ሐይል ከስልጣኑ በማስወገድ እና በምትኩ ተራማጅ ለህዝብ ጥቅም የሚዋደቅ ሐይል ወደ ስልጣን ሊመጣ ካልቻለ በስተቀር ችግሩ የሚፈታ አይደለም።ይህንን የነውጥ ሐይል ከስልጣኑ የማስወገድ እና በምትኩ ተራማጅ ሐይል ወደ ስልጣን የማስመጣት ትግል እንዲሁ ቀላል ልሆን አይችልም።አንደኛው ምክንያት ወደ ስልጣን የመጣውን ሐይል ተለዋዋጭ በህሪ ያለው ነው።ይህንን ተለዋዋጭ ባህሪ ያለውን ሐይል በስመ ለውጥ ህዝብን በማደናገር ወደ ስልጣን የመጣ ከመሆኑ በተጨማሪ ስልጣኑን ለማራዘም ሲል ወደ ፋሽስት ሐይል ለመሸጋጋር ሰፊ እድል ያለው ቡድን ነው።ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ የኢትዮጵያ ተራማጅ ሐይሎች ያልተጠናከሩበት የሐሳብ አንድነት ያልፈጠሩበት ትግሉን የሚያስተባብር አንድ አገር አቀፍ ድርጅት ማደራጀት ያልቻሉበት ሁኔታ መኖሩን ትግሉ በጣም ውስብስብ እንዲሆን ያደርገዋል።

በአንፃሩ ለትግል የተመቸ እድልም አለ።አንዱ እና ዋነኛው እድል የኢትዮጵያ ህዝብ በስመ ለውጥ ለተወሰነ ግዝያት በመደናገር ላይ ቢቆይም የ27 ዓመታት የልማት የሰላም እና የዲሞክራሲ ጉዞው እና በዚህ ሁለት ዓመት ውስጥ ያጋጠመው የሰላም እጦት እና የኑሮ ውድነት መናር በማነፃፀር የ27 ዓመት መንገድ ትክክል መኖሩን ማገናዘብ ጀምረዋል።ይህንን ግንዛቤ ከገጠሩ ማህበረሰብ ማለትም በአርሶአደሩ እና በአርብቶ አደሩ ብቻ የተፈጣረ አይደለም።በመጀመርያዎቹ ግዝያት በመደናገር ለነውጥ ሐይሉ የደገፈ እና ያሞካሸ የከተማ ነዋሪ የአዲስ አበባ እና የባህርዳር ነዋሪ ጨምሮ ከተመኩሮው መማር መጀመሩ ለሚታገሉ ሐይሎች ዕድል የሚፈጥርላቸው ነው።

ሁለተኛው ለትግል የተመቸ ዕድል ነው ተብሎ መቀመጥ ያለበት በነውጥ ሐይሉ ውስጥ ቅራኔዎች እየተካረሩ መምጣታቸው ነው።ጎልቶ ባይታይም የነውጥ ሐይሉ ከውስጥ የመፈራከስ ምልክት እየታየ ነው።ለዚህ ጥገኛ ሐይል በመደገፍ ላይ የቆዩ የእጃዙር ቀኝ ገዢዎችም በስልጣን ያለውን ሀይል በዚህ መንገድ ከቀጠለ ቀጣይ ጥቅማቸው ወደ አደጋ እንዳይጥለው በመስጋት ቆሞው ወደ ማሰብ የገቡቡት ሁኔታም እየተፈጠረ ነው።የዚህ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችለው የምእራቡ ሚድያዎች በመጀመርያ ግዝያት ሙሉበሙሉ የነውጥ ሐይል በመደገፍ ተጠምደው የቆዩ ሲሆኑ ከቅርብ ግዜ ወዲህ ግን አልፎ አልፎ ቢሆንም በነውጥ ሐይል ላይ ያልተጠበቁ ወቀሳዎች መሰንዘር ጀምረዋል።እንዲሁም የሰላም ኖቤል ተሸላሚው ጠቅላይ ሚኒስተር በተባበሩት መንግስታት ጎረቤት አገራት ያውካል የሚል ክስ ቀርቦበታል።በዚህ ሁኔታ ከቀጠለ ለእጃዙር ቀኝ ገዢዎች ሌላ ሐይል ወደ ማፈላለግ ሊያስገባቸው ይችላል።ይህ ሁኔታ ለታራማጅ ሐይሎች ለሚያካይዱት ትግል ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል።

ሰስተኛ ለትግሉ የተመቸ ዕድል ተደርጎ መወሰድ ያለበት ህወሓት እና የትግራይ ህዝብ በሰላም ልማት እና ዲሞክራሲ ጎደና ተጠናክረው መቀጠላቸው ነው።በዚህ ሁለት ዓመት 360 ዲግሪ ተከበው እያሉ የሰላም የልማት እና የዲሞክራሲ እቅዳቸው ሳያቆራርጡ በመተግበር ላይ ተጠምደው ነው ያሳለፉት።የኢትዮጵያ የሰላም ሁኔታ ጫና ቢፈጥርም ኢንቨስትመንት ፍሰቱ ሰላም ወደ አለበት ትግራይ ማጋደሉ አልቀረም።የትግራይ ህዝብ፣መንግስት እና ህወሓት ይህንን ሂደት በጥንቃቄ ነው እየተመለከቱት እየመሩት እና እየተጠቀሙበት ያሉት።በትግራይ ክልል ይህንን ሁኔታ መፈጠሩ በመላው ኢትዮጵያ አንድም ሁለትም ወይም ከዛ በላይ ለህዝብ የሚጠቅም የሰላም የዲሞክራሲ እና የልማት ዓላማ አንግቦ ለሚታገል ሐይል ጉልበት የሚፈጥርለት ነው።ለትግሉ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥሩ እድሎች እነዚህ ብቻ ናቸው ባይባልም እነዚህን ምቹ ሁኔታዎች በመጠቀም መታገል ይቻላል።

ከላይ የተጠቀሱ ለትግሉ ምቹነት የሚፈጥሩት እና እንቅፋት የሚሆኑት በትክክል በመገምገም እና የትግል አቅጣጫ በመቀየስ መታገል ይጠይቃል።ከዚህ በመቀጠል የትግል አቅጣጫው ምን መምሰል እንዳለበት ወደ ሚዳስሰው ይዘት እንሸጋገር።

3.1.የሰላም ጥያቄ የወቅቱ አንገብጋቢ ጥያቄ ነው።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ መታገል ለሚፈልግ ሐይል መታገል ካለበት ለዘላቂ ሰላም መሆን አለበት።በኢትዮጵያ ሰላም የታጣው የስልጣን ዙፋኑን የተቆጣጠረው ሐይል በፈጠረው ፀረ ህዝብ አቋም መሆኑን በፅናት ማመን ይጠይቃል።ይህንን የነውጥ ሐይል ከስልጣኑ እስካልተወገደ ድረስ ኢትዮጵያ የ27 ዓመት ሰላምዋ መመለስ ይቅር እና ከመበታተን እንደማትድን በፅናት ማመን ይጠይቃል።በዚህ አቋም ወላዋይ አቋም መያዝ ፍፅም አይቻልም።መፍትሄም ሊያመጣ አይችልም።ይህንን አቋም በመላው የኢትዮጵያ ህዝቦች በፅናት መያዝ ያለበት አቋም ነው።ለህዝብ እታገላሎህ የሚል ሐይል በፅናት መጨበጥ ያለበት አቋም ነው።ይህንን አቋም ከተያዘ በኋላ የስልጣን ዙፋኑን የተቆጣጠረው እና የሰላም ጠንቅ የሆነውን ሐይል ለማስወገድ ቆርጠህ መነሳትን ያስፈልጋል።ከዚህ በመቀጠል ለዘላቂ ሰላም ለሚደረግ ትግል ማጧጧፍ ነው።ይህንን ትግል በተበታተነ መንገድ ሊፈፀም ስለማይቻል ከአከባቢ ሰላምና ደህንነት ጥበቃ ጀምሮ እስከ ትግሉን የሚያስተባባሩ የፖለቲካ ድርጅቶች አደረጃጀታቸውን ማጠናከር አስፈላጊም ተገብም ነው።

3.2.ሰላም ለማስከበር ሕገ መንግስት እና ሕብረ ብሄራዊ ስርዓቱ መጠበቅ እና ማስጠበቅ የግድ ይላል።

ህገ መንግስታዊ ስርዓቱ እየተናደ ያለው የስልጣን ዙፋኑን በተቆጣጠረው የነውጥ ሐይል ምክንያት መሆኑን ጥርት ያለ አቋም መያዝ አለበት።ህገ መንግስቱ በመናዱ ምክንያት ህብረ ብሄራዊ የፈዴራል ስርዓት አብሮ እየተናደ እንዳለ ማመን ይጠይቃል።ህብረ ብሄራዊ ፈዴራል ስርዓት እየናደው ያለው ደግሞ በስመ ለውጥ አሃዳዊ ስርዓት ለመመለስ እየተፍጨረጨረ ያለውን የነውጥ ሐይል ነው ሓላፊነቱ የሚወስደው።በዚህ ምክንያት ነው ኢትዮጵያ በሰላም እጦት እየተናጠች ያለቸው የሚል የፀና ኣቋም መያዝን ይጠይቃል።ይህንን አቋም በመያዝ ህገ መንግስቱ እና ህብረ ብሄራዊ ፈደራል ስርዓቱ ለመጠበቅ እና ለማስጠበቅ የሚደረገውን ትግል አጠናክረህ መቀጠልን ይጠይቃል።ይህንንም በተደራጀ መንገድ መፈፀም አለበት።

3.3.    ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር እንዲኖር መታገል።

በዚህ ወቅት በኢትዮጵያ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ይኖራል ብሎ ማሰብ ከባድ እየሆነ መጥተዋል።የስልጣን ዙፋኑን የተቆጣጠረው የነውጥ ሐይል ስድስተኛው የኢትዮጵያ አገር አቀፍ ምርጫ የሚያካሄደው መሆኑንና አለመሆኑ ለኢትዮጵያ ህዝብ እንቅጩን አልተነገረውም።የነውጥ ሐይሉ ምርጫ ለማካሄድ ዝግጁነትም ፍላጎትም የለውም።ይልቁንስ ምርጫው እንዳይካሄድ በሙሉ አቅሙ እየሰራ ነው።ይህንን ድርጊት ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር እንዳይኖር ከማድረጉ በላይ ኢትዮጵያን የሚበትን ተግባር ነው።የነውጥ ሐይሉ በህዝብ ትግል ተገዶ 6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ እንድያካሄድ የሚያስችል ትግል መካሄድ ያስፈልጋል።ይህንን የህዝብ ትግል ሰላማዊ የስልጣን ሽግግርን ከመረጋገጡም በላይ ኢትዮጵያ ከመበታተን አደጋ ይታደጋታል።

3.4.    በሐይማኖቶች ውስጥ የመንግስት ጣልቃ ገብነት እንዲቆም መታገል።

የስልጣን ዙፋኑን በተቆጣጠረው የነውጥ ሐይል ምክንያት በኢትዮጵያ ሁሉንም እምነቶች(ሐይማኖቶች)የጥቃት ዒላማ ሆኖዋል።ይህንኑ ሁኔታ ሊፈጠር የቻለው መንግስት በስፋት በሃይማኖት እጁን ማስገባት በመጀመሩ ምክንያት ነው።ይህን ድርጊት የሐይማኖት መሪዎች በመንግስት ስልጣን ላይ ከፍተኛ ተደማጭነት ለማግኘት የሚራኮቱበት ሁኔታን ፈጥረዋል።በአንፃሩም በዚህ ውድድር ያልተሳካለት የሃይማኖት መሪ የበታችነት እንዲሰማው በሱ ስር ያሉ አማኞች ቅሬታ እንድይዙ እና ወደ ያልተፈለገ ጥላቻ እንዲሸጋገሩ እያዳረገ ነው።በዚህ ምክንያት በሁሉም በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ሐይማኖቶች መረጋጋት አይታይም።ይህንን ችግር ለመፍታት የመንግስት ጣልቃ ገብነት በማንኛውም ሃይማኖት ላይ መቆም አለበት።መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ ላይ፤ሐይማኖት በመንግስት ጉዳይ ላይ ጣልቃ አይገባም።መንግስታዊ ሐይማኖት የለምየሚለውን ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱ መከበር አለበት።ይህንን ተግባራዊ ሊሆን ካልቻለ ሁሉንም በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ማንኛውም እምነቶች አደጋላይ ይወድቃሉ።ሁሉንም እምነቶች ከአደጋ ለመታደግ አማኞች ያለምንም መዋላዳት ለዘላቂ ሰላም በፅናት መቆም ይጠበቅባቸዋል።

የፖለቲካ ሐይሎችም የመንግስት እና የሃማኖቶች ነፃነቶች እንዲደባለቁ በማድረግ ሁሉንም ሐይማኖቶች አደጋ እንዲጋረጥባቸውን እያዳረገ ያለውን ሐይል በትግል ለማስወገድ ፅኑ አቋም በመያዝ መታገል ይገባቸዋል።

3.5.    ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የሕብረ ብሄር ፌደራሊስት ሓይሎች ተደራጅቶው መታገል አለባቸው።

የህብረ ብሄር ፈዴራሊስት ሐይሎች ተዳራጅተው የመታገል አስፈላጊነት ግልፅ ሁኖ መቀመጥ ይኖርበታል።የህብረ ብሄር ፈደራሊስት ሓይሎች ዋነኛ ዓላማቸው የተደራጁለት እና የሚታገሉለት ብሄር ብሄረሰብ ህልውና ለማስጠበቅ ነው።የትግራይ ህዝብ ብሄራዊ ህልውና ብቻ አደጋ የወደቀ የሚመስለው የዋሁ ሰው ቁጥሩ የሚናቅ አይደለም ።የአማራ፣የኦሮሞ፣ የኢትዮጵያ ደቡብ ህዝቦች፣የአፋር፣የኢትዮጵያ ሱማል ፣የቤንሻንጉል ወዘተ ብሄር ብሄረሶቦች እና ህዝቦች ማንነት አደጋላይ መውደቁ የማይረዳ ሰው ከግምት ውስጥ ማስገባት ይጠይቃል።ብሄራዊ ማንነቱ ከመዘንጋቱ ምክንያት ሰው መሆኑን የተነዘጋ የአንድ ብሄር ተወላጅ ሰው ነኝ የሚል ቲሸርት ለብሶ የሚሮጥ ቅጥአምባሩ የጠፋው የማንነት ቀውስ የገባ ሰው ስታይ ደግሞ አደጋው የከፋ ያደርጋዋል።ስለዚህ የህብረ ብሄር ፈደራሊስት ሐይሎች የስልጣን ዙፋኑን በተቆጣጠረው የነውጥ ሐይል ምክንያት የሚታገሉለት ማንነት እና ህዝብ አደጋ መውደቁን ግልፅ አቋም መያዝ ይጠበቅባችዋል።ይህንን አቋም በግልፅ በመጨበጥ ብያንስ ኢትዮጵያን ከመበታተን መታደግ ባልተቻለበት ወቅት የሚተጋሉለት ማንነት እና ህዝብ መታደግ ይችላሉ።ለብሄራቸው በሄረሰባቸው ህዝብ ከአጋጠመው አደጋ ለመከላከል ሲባል የነበራቸው ልዩነት በማጥበብ የህዝባቸው ህልውና ለማረጋገጥ በጋራ ለመታገል ስለሚያስችላቸው ህዝባቸው በተቻለ መጠን ከጥቃት መታደግ ያስችላቸዋል።በዚህ ምክንያት ነው የሁሉንም ብሄር ብሄረቦች እና ህዝቦች ህልውና አዳጋ ወድቋዋል የሚል አቋም ሁሉንም የህብረ ብሄር ፈደራሊስት ሐይሎች የፀና አቋም መሆን አለበት የሚባለው።

የብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ህልውና በዚህ የነውጥ ሐይል አደጋ ላይ ወድቀዋል የሚል የፀና አቋም ከያዙ የህብረ ብሄር ሐይሎች ግንባር በመፍጠር የነውጡን ሓይል ታግሎ በማስወገድ በእኩልነት የተመሰረተች ዲሞክራስያዊት ኢትዮጵያ ለመገንባት መስራት ይጠብቃባቸዋል ። ይህንን ዓላማ ይዘው የሚታገሉለት ምክንያት ከተበተነች ኢትዮጵያ በዲሞክራስያዊ እኩልነት የተመሰረተች ኢትዮጵያ ስለምትሻል ነው።

ምንም እንኳን የህብረ ብሄር ፈደራሊስት ሐይሎች የተቻላቸውን ትግል ቢያደርጉ ከውስጥም ከውጭም በሚኖር ተጨባጭ ሁኔታ ኢትዮጵያ የመበታተን አደጋ ሊያጋጥማት ስለሚችል በዚህ ወቅትም የብሄር ብሄረሰባቸው ህዝብ ከሚያጋጠመው አደጋ በመከላከል ዙርያም በቀጣይነት መደጋገፍ ይጠበቅባቸዋል።

የሕብረ ብሄር ፈደራሊስት ሐይሎች የመደራጀት እና የመጠናከር ጉዳይ ከቆሙለት ህዝብ ደህንነት ከመጠበቅ አንፃር ያለው ፋይዳ በመረዳት በፍጥነት ተግባራዊ መሆን ያለበት ነው።ይህንን አደራጃጀት ከመጣናከር አንፃር ደግሞ ህወሓት የጎላ ሚና መጨዋት እንዳለበት ይታመናል።

ህወሓት ህብረ በሄር ፈደራሊስት ሐይሎች ግንባር እንዲመሰረት እና እንዲጠናከር መስራት አለበት ሲባል ለትግራይ ህዝብ ዘላቂ ደህንነት ከመጠበቅ አንፃር ጠቀሜታ ስላለውም ጭምር ነው።የትግራይ ህዝብ እና ህወሓት የመጀመርያ ምርጫቸው በመከባበርና በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ዲሞክራስያዊ አንድነትን ነው።ሁለተኛ ምርጫቸው ከባርነት የራሳቸው እድል በራሳቸው ለመወሰን ይፈልጋሉ።በዚህ ምክንያት የህብረ ብሄር ፈደራሊስት ሐይሎች መጠናከር ከተቻለ ኢትዮጵያን ከመበታተን ያድናት ይሆናል።ካልተቻለ ደግሞ በመልካም ጉርብትና አብሮ ለመኖር ያግዛል።ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች ህወሓት እና የትግራይ ህዝብ የህብረ ብሄር ፈደራሊስት ሐይሎች እንዲጠናከሩ የሚችሉትን ሁሉ ማድረግ ይጠብቅባቸዋል።

በማጠቃለል የስልጣን ዙፋኑን የተቆጣጠረው የነውጥ ሃይል እየፈፀመው ካለው ፀረ ህዝብ ተግባር እንዳማይቆጠብ፤ይህ ሐይል ከስልጣኑ እስካልተወገደ ድረስ ኢትዮጵያ መታደግ እንዳማይቻል የተገነዘበ ትግል ማድረግ ይጠይቃል።እንደዚህ የመሰለ ትግል ለማካሄድ በጥንቃቄ እና በተደራጀ መንገድ መከሄድ ይኖሩበታል።ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ለህልውናው ሲል ዓቅሙን የሚፈቅደው ትግል ማድረግ ይጠበቅበታል።የኢትዮጵያ ህብረ ብሄር ፈደራሊስት ሓይሎች መሪነት በብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ትግል ሊደርስ ከሚችል እልቂት እና ኢትዮጵያን ከመበታተን መታደግ ይቻላል።

ድል ለህብረ ብሄራዊ ፈደራሊስት ሓይሎች!!!


Back to Front Page