Back to Front Page


Share This Article!
Share
“የተረሳች ሀገር”

“የተረሳች ሀገር”

ፀጋዝአብ ለምለም ተስፋይ 2-25-19

የኢኮኖሚክስ መምህርና ጸሓፊ

  በሰው ልጅ ኹለንተናዊ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ውስጥ ፍላጎትና ግንኙነት የማይነጣጠሉና የየራሳቸውም ባሕሪያዊና ጠባያዊ መገለጫዎች ያሏቸው ቁልፍ ጉዳዮች ናቸው፡፡ የማንኛውንም አካል - ያለፈ፣ ያለና የሚመጣ ኹለንተናዊ ሂደት ያለነዚህ ማሰብ ፈጽሞ የማይቻል ነው፡፡

  አንድ ሰው ሌላን ሰው ረሳኝ አልያም ረስቶኛል የሚለው ምን ሲኾን ነው? እኛስ ሰውን የምንረሳው ምን ስንኾን ነው? መረሳትና መርሳት፡- ካለመታወስ፣ ካለመጠየቅ፣ ካለመሰማት፣ ካለመገናኘት፣ ከትኩረት ማጣት ጋር፣ መኾንና ማድረግ ከሚገባን ነገር አንጻር ሳናደርግ ስንቀር እንደየዐውዱ በተለያየ መልኩ የሚገለጽ ነው፡፡

Videos From Around The World

   መረሳትም ኾነ መርሳት የሰውን ኹለንተናዊ ኹኔታዎች ይጎዳል፡፡ በፈጻሚውም ኾነ በተፈጻሚው አካል ላይ ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ -  ተጽዕኖዎችንም ያሳድራል፡፡ ይህ በነጠላ በግለሰብ አልያም በቡድን ደረጃ ያለ ነው፡፡ እንደሀገር የወሰድነው እንደኾነ - ሀገር ትረሳለችን?

  ሀገርን ማን ያስታውሳታል? ማንስ አይረሳት ዘንድ ይጠበቃል? አንድ ሀገር ዜጎቿ ካላሰቧትና ካላስታወሷት ማን ሊያስታውሳት ይችላል? ሀገር ያለ ዜጎች - ዜጎችም ያለ ሀገር ትርጉም ይኖራቸው ይኾን?

  ዜጎቿ የማያስቧትና የማያስታወሷት ሀገር ከዕድገት ይልቅ ውድቀት፤ ከእውነት ይልቅ ሀሰት፤ ከግልጽነት ይልቅ ድብቅነት፤ ከሕብረት ይልቅ መለያየት፤ ከነጻነት ይልቅ ባርነት፤ ከተግባር ይልቅ ወሬ፤ ከዕሳቤና ሀሳብ ይልቅ ስሜት የሚሠለጥንባት ብሎም መገለጫዎቿ እንደሚኾን የታወቀ ነው፡፡   

  ስለኾነም ሀገር በጥቅሉ ዜጎች ሲኖራት - ዜጎች በአንጻሩ ገዥዎች፣ መሪዎች፣ ምሁራን፣ ተማሪዎች፣ ሰራተኞች፣ ሚድያዎች፣ ባለሙያዎች፣ - - - ወዘተ ተብለው የተለያየ በተለያየ መልክ ይቀመጣሉ፡፡ እነዚህም በጥቅሉ ዜጎች ከመሰኘት በዘለለ ሀገርን እንደሀገር ብያኔ እንዲኖራት ለሕልውናዋ ትልቅ ሚናን ይጫወታሉ፡፡

  ከዚህ ተነሥተን የሀገራችንን ኹለንተናዊ ነባራዊ ኹኔታዎች ስንመለከት ምን ላይ ነን? ማን ምን እያደረገ ነው? የሚለውን ከማዕቀፍ አንጻር እንደሚከተለው መመልከት እንችላለን፡፡

  ለዚህም መነሻ የሚኾነን ኹለንተናዊ ዕውነት (Truth) እና እውነታ (Reality) - ያለንበት ኹለንተናዊ ጥሬ ሃቅ ይኾናል፡፡ በሀገራችን መልካም ተብለው ሊጠቀሱ የሚችሉ ነገሮች ቢኖሩም ከተነሣንበት ርዕሰ ጉዳይና ትኩረት ከሚያሻው አንገብጋቢ ጉዳይ ስንመለከት ከ3 ሚሊዮን በላይ የተፈናቀለባት፣ ሞትና ስደት አዛም እዚም የሚሰማባት፤ የሕግ የበላይነት አሳሳቢ ደረጃ ላይ የሚገኝባት፤ በሶስት ቦታዎች አስቸኳይ ጊዜ የታወጀባት፤ ሰላም በራሱ በብዙ ቦታዎች ጥያቄ የኾነባት፤ የገዥው ፓርቲ አመራሮች አንድነትና ሕብረት በአደባባይ እጅጉን በተቃርኖ የተሞላባት፤ ፍትህና መልካም አስተዳደር ብዙ የሚቀርባት፤ ማስመሰልና ትያትር በአደባባይ እጅጉን የተንሰራፋባት፤ ኢኮኖሚያዊና የብድር ቀውስ አፍጦ የመጣባት፤ የውጭ ጣልቃ ገብነት እንዳለ በሰፊው የሚታማባት፤ አንገብጋቢ ጉዳዮች እጅጉን የተበራከቱባት፤ ሕልውናዋ እንደሀገር ጥያቄ ምልክት ውስጥ የገባበት፤ በብዙ ቦታዎች የመንግሥት የታችኛው መዋቅር በግለሰቦችና ቡድኖች እንደበሶ የሚናጥባት፤ ሕግና ሥርዓት በአደባባይ የሚጣስባት፤ ጦርነትና የጦርነት ወሬ በአደባባይ ያለ እፍረት በ21ኛው ክፍለ ዘመን እንደጀብዱ የሚቀነቀንባት - - - ወዘተ ኹለንተናዊ ኹኔታ ውስጥ ናት፡፡

  ከዚህና መሰል ኹለንተናዊ ኹኔታዎች በመነሣት ዕውን ኢትዮጵያ - የተረሳች ሀገር አይደለችምን?     

1.  ገዠዎች

  ሀገራችን ለረዥም ጊዜ ባሳለፈችውና እያሳለፈች ባለቸው የሥልጣን ፖለቲካ ውስጥ ገዥዎችን እንጂ መሪዎች በብዛት ፈርተውባት እንደማያውቁ የአደባባይ ዕውነት (Truth) እና እውነታ (Reality) ነው፡፡

   የሀገራችን ገዥዎች እጅግ ከጥቂቶች በተግባርም ሰላም፣ ልማትና የመሰረታዊ ለውጥ ፍንጮችን እያሳዩ ካሉ ሃቀኛ መሪዎች ውጭ አብዛኛዎቹ ገዥዎች ሀገራቸውን አልረሱምን?

   አብዛኛውን ጊዜያቸውን በተራ ጥቃቅንና አነስተኛ፣ እርባና በሌላቸው የኮሰሞቲክስ ትያትርና ትኩረት የመሳቢያ ሁነቶቸ የሚያሳልፉ አይደሉምን?

  ከሥራ ይልቅ ወሬ ላይ፤ ከሕብረትና ከአንድነት ይልቅ ጠላት ፍለጋ ላይ፤ ከዛሬና ነገ ይልቅ ትላንት ላይ፤ ከዕሳቤና ርዕዮት ይልቅ ተራ ትርጉም አልባ የባዶ ቃላት ክምር ጥቅሶች ላይ፤ በጥልቀት ትርጉም ባለው መንገድ ከሚተነተኑ ነገሮች ይልቅ ስሜት ቀሰቃሽ፤ ከዘላቂ ይልቅ ጊዜያዊ ነገሮች ላይ ትኩረት እንደተደረገ ማንም የማይክደው ጥሬ ሃቅ ነው፡፡

   ዕውን ሕግ አውጪ፣ ሕግ ተርጓሚና ሕግ አሰፈጻሚ አካላት መኾንና ማድረግ የሚገባቸውን እያደረጉ ነው? አጀንዳ መኾን የሚገባውን አጀንዳ አድርገዋል? ቀዳሚ ሊኾን የሚገባውን ቅድሚያ ሰጥተዋል? መጠየቅ የሚገባቸውንስ ጠይቀዋል?

   ለአብነት፡- ፓርላማው ዕውን በተጨባጭ ስለተጨባጭ የሀገራችን ነባራዊ ኹኔታ ከጥቃቅንና አነስተኛ ጉዳዮች በዘለለ ትኩረት ሰጥቶ ሰርቷል? የሚመለከተውን አካልስ ጠይቋል? ዕውን ፓርላማው ኢትዮጵያን አልረሳትም?

 

 

2.  ምሁራን

  የሀገራችን ምሁራን ምን እየሰሩ ነው? ዕውን ሀገራችን እንዳለችበት አሳሳቢ፣ አስጨናቂና አስፈሪ ኹለንተናዊ ነባራዊ ኹኔታዎች እየተንቀሳቀሱ ነው? ዕውን ምሁራን በአስተሳሰብና አመለካከት፣ በስልትና በስትራቴጂ ብሎም በተግባር ደረጃ ሀገራቸውን አልረሱምን? ማድረግ የሚጠበቅባቸውን እያደረጉ ነው?

  ዕውን ምሁራን በአደባባይ ጎልቶ ከወጣው እልም ካለ አስመሳይነትና ሆድ አዳሪነተ ተላቀው - በምክንያትና በአመክንዮ በነጻ ሕሊናቸው፣ በያዙት ክህሎትና ባዳበሩት ልምድ ተጠቅመው - ነባራዊ ኹኔታዎችን እየተመለከቱ ነው? ወይስ ከነፈሰው ጋር ነፍሰው የግርድና ሥራ እየሰሩ? እየመሩ ወይስ እየተመሩ? እያሸረገዱ ወይስ በነጻነት ሕዝባዊ ውግንና ይዘው ቆመዋል? ለያዙት፣ ሊይዙትና ሊመሩበት ከሚገባው ኹለንተናዊ አቋም፣ መርሕና ዲሲፕሊን አንጻር እየተጓዙ ነው? ለዚህስ ኹለንተናዊ መሰዋዕትነት እየከፈሉ ነው ወይስ እያስከፈሉ?   

3.  ሚድያዎች

  ሚድያዎቻችን ትኩረታቸው ምን ላይ ነው? ሰፊ ጊዜያቸውንስ እየሰጡ ያለው ለምንድነው? ከ3 ሚሊዮን በላይ ተፈናቃዮች ባሉባት ሀገር፤ የሕግ የበላይነት በአደባባይ በሚረገጥባት ሀገር፤ ሰላምና የሰላም ጥያቄ ጎልቶ በወጣባት ሀገር ለውጭ እግር ኳስ እንኳ የተሰጠውን ትኩረት ለሀገር ነባራዊ ጥሬ ሃቆች መስጠት ለምን አልቻለም? ይህን ማድረግ ያልቻለ ሀገራዊ ሚድያ - ሀገሩን አልረሳምን? ሀገርን መርሳት ማለት በበቂ ኹኔታ ሀገርን አለማሰብ፣ አለማስታወስ፣ ስለሀገር አለመጨነቅና አለመጠበብ አይደለምን?

   ሚድያዎቻችን ከጥቃቅንና አነስተኛ ትርኪ ሚርኪ ትርጉም አልባ ፍሬ ከርስኪ መወድሶች፣ ተራ ፕሮፕጋንዳዎች፣ ትኩረት ከማዛባት በዘለለ ምን እያደረጉ ነው? ዕውን ሚድያዎቻችን በአስተሳሰብና አመለካከት፣ በስልትና በስትራቴጂ ብሎም በተግባር ደረጃ የኢትዮጵያውያን ናቸው? ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ኹለንተናዊ ጥቅም የሚተጉ ናቸው?

  ዕውን ሚድያዎቻችን የሀገር ጉዳይ እንቅልፍ ይነሳቸዋል? በእንቅልፍ የመነሣትና በቁጭት የመንገብገብ ኹለንተናዊ ባሕሪያትና ጠባያት ይታይባቸዋልን?

4.  ነጋዴዎችና ባለሀብቶች

  ሃገራችን እንዳለችበት አስጨናቂ፣ አስጊ፣ አስፈሪና እጅግ አሳሳቢ ነባራዊ ኹኔታ ነጋዴዎችና ባለሃብቶቿ እያሰቧት ይኾን? ዕውን ሀገርን ከኹለንተናዊ ውድቀትና ፈተና ሊታደግ የሚችል - አለፍ ሲል የራሱን ጥቅሞች አሳልፎ ሰጥቶ - ሀገርን ሊታደግ የሚችል ሀገራዊ ነጋዴና ባለሃብት አላት? ወይስ ስለጥቅሙ እሷን አሳልፎ የሚሰጥ?

  አሳልፎ የሚሰጣትና አሳልፎ የመስጠት ተግባርን በኮንትሮባንድ፣ ገንዘብ በማሸሽ፣ በሙስና በሕገ ወጥ የመሣሪያ ዝውውር ውስጥ በስፋት የሚሳተፉ አካላት ባሉበት፤ ሕግ ላይ የሠለጠኑና የራሳቸውን ፍላጎት በተለያየ መንገድ የሚያሳኩ አካላት እዛም እዚም በሚታዩበት - ዕውን ሀገር አልተረሳችም?

5.  የሃይማኖት ተቋማት

   የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች በምዕመናን አልተቀደሙም? የሃይማኖት መሪዎች ቀድሞ የነበራቸው ቦታ፣ ክብር፣ ተሰሚነት፣ ተጽዕኖና የመሪነት ቦታ አላቸውን? እርስ በራሳቸውስ ስምምነት፣ ሕብረት፣ አንድነትና የመንፈስ መግባባት አላቸውን?

   የሃይማኖት መሪዎች ምዕመኖቻቸውን አልረሱም? ዕውን የምዕመኖቻቸው ኹለንተናዊ ነባራዊ ኹኔታ ያሳስባቸዋል? ያስጨንቃቸዋል? እንቅልፍስ ይነሳቸዋል? የማሳሰብ፣ የማስጨነቅና እንቅልፍ የመነሣት ተግባርስ ይታይባቸዋል? ዕውን ቁጭት፣ እልህና ትጋትስ አላቸው? ዕውን በውስጣቸው ይህን ማድረግ ያልቻሉ - እንደምን ሀገርን ሊያስቡ ይችላሉ? የሃይማኖት መሪዎች ሃገራቸውን ትርጉም ባለው መንገድ አልረሱም? ለሀገር ግንባታ (Nation Building) እና ሕብረተሰብን በማነጽ (Reshaping Society) ላይ ያላቸው ሚና ምን ይመስላል?

   የሃይማኖት ተቋማት በሙሉ ሃይማኖታዊ ዕሴቶችን ባለማስጠበቃቸው ምዕመናን የሚባሉ ወገኖች ራሳቸው፣ አብዝሃ ምዕመን እያየና እየሰማ ሰዎች አልተፈናቀሉም? አልተገደሉም? አልተሰደዱም? ዕውን የሃይማኖት ተቋማት ልዕልና በቀድሞ ቦታው አለ? ራሳቸውን ማስጠበቅ ያልቻሉስ - እንደምን ሀገርን ሊያስታውሱ ይችላሉ? ራሱን ያላስታወሰ ሌላውን - ከሱ ባሻገር ያለውን ሊያስብ ይችላል? ራሱን ያልተቆጣጠረ ሌላውን እንደምን ሊቆጣጠር ይቻለዋል?   

6.  የኪነ ጥበብና ሥነ ጥበብ ባለሙያዎች

   እንደሀገራችን ነባራዊ ኹኔታ ሥነ - ጽሑፋዊ ጥበቦቻችን (ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ብሎም ፖለቲካዊ የኾኑ ማንነቶቹ የሚገለጹባቸው ድርሰቶች (ልብ ወለዶችና ኢ ልቦለዶች)፣ ግጥሞች፣ ተውኔቶች፣ ሥነ ቃሎች፣ መነባንቦች - - - ወዘተ)፤ እይታዊ ጥበቦቻችን (የሥዕል፣ የፎቶ ግራፍ፣ የምልክት ሥራዎች፣ የፊልም፣ የድራማ፣ የጭውውት፣ የኪነ - ህንጻ ሥራዎች፣ የፋሽን፣ የዲዛይን፣ - - - ወዘተ)፤ ትዕይንታዊ ጥበቦቻችን (የሙዚቃ፣ የትያትር፣  የውዝዋዜ፣ የጭፈራ፣ ባሕላዊ የሐዘንና የደስታ መገለጫዎች የኾኑ ተግባራት፣ ለመንፈሳዊ አገልግሎት የሚውሉ የሃይማኖት በዓላት መገለጫዎች)፤ የዕደ ጥበብ ሞያዎቻችን (የእንጨትና የቆዳ ሥራ፣ የሽመና ሥራ ፣ የጌጣ ጌጥ ሥራ - - - ወዘተ) ሥራዎች በሙሉ ናባራዊ ጥሬ ሃቆችን የሚገልጹ ናቸው?

  ዕውን ነባራዊ ዕውነት (Truth) እና እውነታን (Reality) መግለጽ ያልቻለ ጥበብ እንደምን ጥበብ ሊሰኝ ይችላል? ዕውን በዘርፉ ውስጥ ያለው ባለሙያ ሀገሩን አልረሳም? ዕውን ያለመርሳት ሥራ እየሰራ ነው? ኹለንተናዊ ሥራዎቻችን መሬት ላይ ያለውን ጥሬ ሃቅ ያንጸባርቃል?

7.  ልዩ ልዩ አካላት

   ከላይ ከተጠቀሱ ዋነኛ አካላት ባሻገር ተፎካካሪ ፓርቲዎች ዕውን ሀገራቸውን የማስታወስ ሥራ እየሰሩ ነው? ዕውን ለሥልጣን ብለው ችግር ላይ ችግር አልጨመሩም? ዛሬም በ21ኛው ክፍለ ዘመን በሀገራችን እዛም እዚም የርስ በርስ ጦርነት የለም? አጀንዳዎቻቸው ሀገር ያለ መርሳት ናቸውን?

   መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች፣ ማሕበራትና ቅንጅቶችስ ከወዴት አሉ? ከፖለቲካ ባሻገር ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ኹለንተናዊ እንቅስቃሴዎቻቸው ከወዴት አለ? ዕውን ሀገር አሉኝ የምትላቸው - የምትመካባቸውና በብቃት የምትመሰክርላቸው ኾነው ተገኝተዋልን?

   ስለኾነም በሀገራችን ዕውነተኛ፣ አስተማማኝና ዘላቂ መሠረታዊ ለውጥ ይመጣ ዘንድ ዜጎች ሀገራቸውን ሊረሱ - ሀገርም ዜጎቿን ልትረሳ አይገባም፡፡ የተረሳች ሀገር መሠረታዊ ለውጥ አታመጣም፡፡ የተረሳች ሀገር ዘመናዊ፣ ተወዳዳሪ፣ ሥልጡንና ሕልው መኾን አትችልም፡፡ የተረሳች ሀገር ካልተረሳች ሀገር ጋር ፈጽሞ አትወዳደርም፡፡ ወደድንም ጠላንም ያልተረሳች ሀገር - የተረሳችን ሀገር ትገዛለች፡፡ የተረሳች ሀገር - ያልተረሳች ሀገር ባሪያና ገረድም ትኾናለች፡፡ ፈጣሪ ሀገራችን ነጻ ፍቃድን የኹሉ ነገር ማዕከል ወደ ሚያደርግ የዕሳቤ ሂደት ትገባ ዘንድ ይርዳን!

ቸር እንሰንብት! 

Back to Front Page