Back to Front Page

ፎረም-11

ፎረም-11

ከሹም ባሕሪ ዑስማን

6-21-19

መነሻ

የፅሑፉ መነሻ የሆነኝ በዓል ጋዳ ሩባና የፃፉት ተከታታይ ፅሑፍ ነው፡፡ ሃሳባቸውን ወድጀዋለሁ፡፡ አንብሳን ፍለጋ በሚለው የመጀመሪያ ፀሑፋቸው ላይ የምጨምረውም የምቀንሰውም ሃሳብ የለኝም፡፡ ህውሓትን እንደ ናፓሊዮን ቦነፓርት በሚለው ፅሑፍ ላይ ግን መሰረታዊ እንኳን ባይባልም ኣንድ ሁለት ሃሳብ ላሰቀምጥ-ወይም ደግሞ ልጨምርበት፡፡

ኢኒኪ- (አንድ ማለት ነው-በቋንቋችን)-የኣሁኑ ካኪቶክራቲክ መንግስት መጥፎ ነገር ብቻ ሳይሆን ጥሩ ነገር ያለው መሆኑንም ላስቀምጥ፡፡ ሳይደፈርስ ኣይጠራም አንደሚባለው ለውጡ የሃገራችንን የታጀለ ፖለቲካ እንዲደፈርስና ኣሁን እየታየ ያለው ጥርት ያለ የሃይል ኣሰላለፍ እያደረ እንዲጠራ የበኩሉን ኣስተዋፅኦ ተጫውቷል፡፡ የለውጥ ቲሙ ሁሉም በሮች በርግዶ ባንዴ በመክፈቱ ብዙ ነገሮች ተንጧል-እየቆየ ግን ጠርቷል፡፡ ስለዚህ ይህ ኣዎንታዊ ሚና ነው ሊባል ይችላል፡፡ ሳይደፈርስ ኣይጠራም-ተብሎ የለም?

Videos From Around The World

ናሞያ- (ሁለት-ይህም በቋንቋችን ነው)፡፡ የለውጥ ቲሙ የፖለቲካ ምህዳሩ በማስፋት በኩልም በጎ ሚና ኣለው ወይም ደግሞ ነበረው ብለን ብንወስደው መልካም ይሆናል፡፡ ለኣመታት የተዘጋጉ በሮችንና ልሳኖች ከፍቷል፡፡ ኣያያዙና ኣካሄዱ ላይ ችግር ቢኖርበትም መከፈቱ በራሱ በጎ እርምጃ ነው ተብሎ ቢወሰድ ጥሩ ይመስለኛል፡፡

ሲዲሖይ-(3)-ሶስተኛው ነጥቤ ከላይ ከተነሱት ሃሳቦች ለየት ይላል፡፡ ወደ ዋናው ፅሁፌም መንደርደርያ ይሆነኛል፡፡ ህወሓትም እንደ ናፓሊዮን ቦናፖርት በሚል ፅሁፍ ኣንበሳ መሪዎች መታየት ጀምረዋል የሚል ሃሳብ በወሳኝ መልኩ የምጋራው ቢሆንም እንኳን ኣሁንም ግን ትክክለኛው ኣንበሳና የኣዋሽ ፓርኩ የመንግስት ቅልብ ኣንበሳ መለየት መቻል ይኖርብናል፡፡ዉድ ኣንባብያን የኣዋሽ ፓርኩ የመንግስት ቅልብ ኣንበሳ ደግሞ ምን ማለት ነው ትሉ ይሆናል፡፡ ላብራራው፡፡

1.      የኣዋሸ ፓርክ ደምወዝተኛ ኣንበሳ

አንበሳ በተፈጥሮም በሂደትም ራሱ ጥሮግሮ-የሚታደኑ እንስሳትን አድኖ የሚኖር የዱር አራዊቶች ንጉስ ነው። የአደንን ሂደት ከእናቱ ገና በልጅነቱ ይማራል። የእጆቹ ወይም ክርኖቹ ጡንቻዎቹና አእምሮውንም በሂደት እያዳበረ ይመጣል-በዛው ልክም ኩራትና ጀግንነትን ይጎናፀፋል፡፡

አዋሽ ፓርክ ውስጥ በዚህ ዓይነት ሂደት ውስጥ ያለፉና አሁንም ያሉ የዱርና የፓርኩ አንበሶች በብዛት ይገኛሉ፡፡አልፎ አልፎም በቱሪስቶች ይጎበኛሉ-ከሩቁ፡፡

ከነዚህ ኣንበሶች የተለየ ሌላ ደሞወዝተኛና የመንግስት ቅልብ አንበሳም በፓርኩ ውስጥ ይገኛል፡፡የዚህ ልዩና ቅልብ ደሞወዝተኛ አንበሳ ታሪክ እንዲህ ነው፡፡ታሪኩን ልጀምር-ይፈቀድልኝ፡፡

ሃረር ዉስጥ የዛሬ 20 ዓመት ኣንድ የመንግስት ባለስልጣን የኣከባቢው ማህበረሰብ ጥሩ ነገር እየሰራህልን ነው በማለት ሽልማት ከህዝቡ ይሸለማል፡፡ ሽልማቱ (ስጦታው) እንደ ኣሁኑ ዘመን ባለ ስልጣናት ሽልማት ብሉኮና ጋቢ ኣልነበረም፡፡ ደቦል ኣንበሳ (ትንሽ ኣንበሳ) ነበር፡፡ ሽልማቱ ለየት ያለ ቢሆንም ህዝብ ፊት እምቢም እሽም ለማለት እድል የሚሰጥ ኣልነበረም፡፡ ባለ ስልጣኑም ደቦል ኣንበሳዉን ከመኪናው ጀርባ ይዞ ሃረር ውስጥ ኣንዱ ትንሽየ ከተማ ውሰጥ ይገባል፡፡ ደቦል ኣንበሳው እንደ ውሻው ኣስሮ ቤት ውስጥ እንዳያሰቀምጠው ቀለቡም ችግር ነው፡፡ እያደገ ሲሄድም መዘዙ ብዙ ነው፡፡ ታድያ ይህን የተገነዘበ ባለ ስልጣን ለከተማው ወጣቶች በስጦታ መልክ መልሶ ያበረክትላቸዋል፡፡ የከተማው ወጣቶችም ትንሽ ቤት ቢጤ ሰርተው ኣንበሳውን በገንዘብ ካርኒ እየቆረጡ ህዝብ እንዲያየው ማድረግ ጀመሩ፡፡ ይሁን እንጂ ከተማዋ ኣነስተኛ ስለነበረች የታሰበው ገቢ ኣልተገኘም፡፡ ኣንበሳው ከሚገኘው ገቢ ቀለብ ሊያገኝ ኣልቻለም፡፡ ቀናትና ኣመታት በሄዱ ቁጥርም ኣንበሳው በረሃብ ተሰቃየ፡፡ ቀጨጨ፡፡ ኣንበሳ ሳይሆን በድርቅ የተጠቃ ከብት መሰለ፡፡ ሞት ኣፋፍ ላይም ደረሰ፡፡ በስተ መጨረሻ ፈጣሪ ደረሰለት፡፡

ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ ድንገትም ነበር፡፡ ድንገተኛው ኣጋጣሚም የእስረኛውን ኣንበሳ ህይወት በከፊልም ቢሆን የሚታደግ ኣጋጣሚ ተገኘ፡፡ ኣንዲት የውጭ ሃገር ዜጋ የእንስሳት መብት ተከራካሪ ቦታው ድረስ ትገኛለች፡፡ ኣንበሳውን ስታየውም ግርምትና ድንጋጤ ይፈጥርባታል፡፡ ሁኔታዉም ለኣለምና ለእንስሳት መብት ተቆርቃሪዎች ኣሳውቃለሁ ኣለች-በቁጣ ǃǃ ይህንን ኣንበሳ ኣንድ ነገር ካልተደረገ ወየላችሁ-ኣለች፡፡ ዜናውም ወድያዉኑ ሳይዉል ሳያድር ከፍተኛ የመንግስት ኣመራሮች ዘንድ ደረስ፡፡ መጀመሪያ ላይ እና ምን ይጠበስ ኣይነት መልስ ነበር ኣሉ፡፡ በስተመጨረሻ ግን ነገሩ የኣገሪቱ ገፅታ እንደሚያበላሽ ስለታወቀ ድርድር ተደረገ፡፡

ኣንበሳዉም ከሃረር ትንሽዋ ከተማ መጥቶ በኣዋሽ ፓርክ ኣንድ ጊዚያዊ ማቆያ ቤት ተሰርቶለት በየቀኑ በመንግስት በጀት ፍየል እየተገዛለት እንዲኖር ይደረግ ተባለ፡፡ ከሲኦል ወደ ኤዶም ተዛወረ፡፡ ኣንባብያን ምን ነው ወደ ኣ/ኣበባ ኣንበሳ ግቢ ወይንም ደግሞ ወደ ቤተ መንግስት እንዲገባ ያልተደረገው ብላችሁ ለመጠየቅ እንዳትዳዱ፡፡ እዚህ ጋ ቢገባ የባሰ ገፅታ ያበላሻል-ኣይደል?

ትንሽ ወራት ኣዋሽ ማገገምያ ላይ እንደ ቆየም ደሞዝተኛው እና ቅልቡ ኣንበሳ ዳግም ህይወት ዘራ፡፡ ነብሱም ኣንሰራራ፡፡ እንደ ኣመሉና እንደተፈጥሮ ህግ ማግሳት ጀመረ፡፡ በዛን ወቅት ታድያ ኣዋሽ ፓርክ ጫካ ዉስጥ የነበሩ ኣንበሶች ማግሳቱን ሰምተውና ተደናግጠው ምን ነው ከመካከላችንና ከመንጋው ድንገት የተለየ ኣንበሳ አለ እንዴ? በማለት ቅልቡ ኣንበሳ ወዳለበት ቦታ ሌሊት ሌሊት እየመጡ ይጎበኙታል፡፡ በራሳቸው ኣንበሳዊ እና እንስሳዊ ቋንቋም ለመግባባት ይሞክራሉ፡፡ መልእክትም ይለዋወጣሉ፡፡ ልክ እስረኛ እንደሚጠይቅ የሰው ልጅ ትእይንት ያሳያሉ፡፡

የሚገርመው ነገር ደሞወዝተኛው ኣንበሳ እንደ ኣገሳሱ ከሆነ የሁሉም የፓርኩ ኣንበሶች አውራ (መሪ) ነው የሚመስለው፡፡ ሌሊት ሌሊት እየመጡ ጓደኞቹ (ዘመዶቹ) ሲያዩት ግን ክንዱ የዛለና ቅሬታ፣ ብሶት (grievance) ያለበት ሆኖ ያገኙታል፡፡ ከወባ ትንኞችና (ቢንቢ) ከፌንጣዎች እንዲሁም ከኣይጦች ጋር ቤት ዉስጥ ሲራራጥ ያዩትና የታዘቡት የጫካ ኣንበሶቹ እውን ይሄ ፍጥረት የኛ ዘር ነው ወይስ ተሳስተን ነው እዚህ የተገኘነው በማለት ለስኣታት ተደንቀውና ተደምመው ሲመለከቱት የፓርኩ ኣንዳንድ ባለሙያዎች ኣጭልቆው ያያሉ፡፡

ደመወዝተኛውና ቅልቡ ኣንበሳ ለስሙ ነው ሚያገሳው እንጂ የማደን ሞራሉም ክህሎቱም የለዉም፡፡ እኔን ኣስረው ያሰቃዩኝ ሰዎች በሰማይም በምድርም ተጠያቂዎች ናቸው-የእጃቸውን እሰጣቸዋለሁኝ እያለ የሚያገሳው ለቢንቢዎችና ለፌንጣዎች ነው፡፡ ብሰቱ መቋረጫ የለውም፡፡ ኣንዳንዴ ራሱንም ይነክሳል-ከሰውነቱ ጋራ ይጣላል፡፡

ታድያ ይህንን የደመወዝተኛው ኣንበሳ ኣገሳስ ቅሬታ፣ብሶት (grievances) መሆኑ እንዲሁም የጫካው ኣንበሶች ኣገሳስ ደግሞ እውነተኛ ኣገሳስ መሆኑ የፓርኩ ባለሙያዎች ነግረውኛል-ፓርኩን በጎበኘሁበት ኣጋጣሚ፡፡ ይገርማል፡፡

ይህንን የኣዋሽ ፓርክ ደመወዝተኛ ኣንበሳ ታሪክ ያመጣሁትም ያለምክንያት ኣይደለም፡፡ ኣሁን ኣሁን ኣብዛኛዎቹ የህወሓት ኣመራሮች ኣንበሳ መሪ መሆን ጀምረዋል፡፡ ህዝቡም ከህዝባዊ ንቅናቄው ብዛት ያላቸው ኣንበሳ መሪዎችን በየደረጃው ፈጥሯል፡፡ እዚህ ላይ በዥታ የለብኝም፡፡ ነገር ግን ግልፅ መሆን ያለበት ጉዳይ ኣሁንም ድረስ ጥቂት የድርጅቱ መሪዎች እንደ እንበሳ ማግሳት ቢጀምሩም ኣገሳሳቸው እንደ አዋሽ ፓርኩ ቅልብ ኣንበሳ የብሶት እና የቅሬታ /grievances/ እንዳይሆንና ጭሆቱና እንቅስቃሴው ከቢምቢዎችና ከፌንጣዎች ጋር እንዳይሆን እሰጋለሁ፡፡ መሪዎቻችን ዋናው ጠላት በኣግባቡ መለየት ይኖርባቸዋል፡፡ የትግሉ ትኩረትና ክንዳቸው በዋናነት ማረፍ ያለበት ዋና በሚባል ጠላት ላይ መሆን ይኖርበታል፡፡ ዋናውን ጠላት በመምታት በኩል እግረመንገዳቸው ቢምቢዎችና ፌንጣዎችን ኣምክነው (ሽባ ኣድርገው) ቢያልፉ ትክክል ይሆናል፡፡ ይህ ማለት የፕሮፖጋንዳ ብትሩ በነዚህ በኩል ኣልፎ ዋናውን ጠላት ላይ ማረፍ ኣለበት፡፡ ኣለበለዝያ ምቱ በየት በኩል ኣልፎ የትና ማንጋ ያርፋል የሚል የትጥቅ ትግላችን ጊዜ የፕሮፖጋንዳ ኣካሄድ ዳግም ማየትና መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ እኛ ልማት፣ሰላምና ዴሞክራሲ ታግለን ህዝቡን መርተን መጥተን ኣሁን የእህት ድርጅት ኣመራሮች በግልጽ ክደውናል፡፡ በታገልን፣ በለፋንና በሰራን ጭራቅ ተመስለን ቀርበናል፡፡ ተዘልፈናል፡፡ በየመድረኩ ኣዋረደውናል፡፡ በማለት ተደጋጋሚ እሮሮ ማሰማት ዞሮዞሮ ብሶትና ቅሬታ /grievances / ነው፡፡ ይህ መናገር ኣያስፈልግም ማለት ኣይደለም፡፡ ይህን ሂስ ለመሰንዘር የዳዳን ንግሩ በተገቢ ቦታና ወቅት መሆን ኣለበት በማለት ነው፡፡ ጠላቶቻችን የተዘፈቁበት ኣዘቅትና ኣከሄድ እኛም መድገም የለብንም፡፡ የነሱ ክህደት የዋናው የፖለቲካ ስራችንን ማእከል መሆን የለበትም፡፡

2) የፖለቲካ ቅሬታ ወይስ የቅሬታ ፖለቲካ?

የሃይለማርያም ደሳለኝ መንግሰት ኮርማ ኣልባ በረት የሚል ንፅፅር (analogy) በደንብ ይገልጸዋል፡፡ የኣብይ ኣህመድ መንግስት ደግሞ የቅሬታ ፖለቲካ (poletics of grievances) የሚል በደንብ የሚገልፀው ይመስለኛል፡፡ ለመሆኑ የፖለቲካ ቅሬታ፣የቅሬታ ፖለቲካ ባህሪና መገለጫዎች ምንድን ናቸው? በምንስ ይመሳሰላሉ? በምንስ ይለያያሉ? መጨረሻቸውስ ምንድን ነው? የሚሉ ጥያቄዎች ግልፅ ለማድረግ የሚከተሉት ቁምነገሮችን እንይ፡፡

የካኪቶክራቲክ መንግስት ኣንዱ ባህሪ የቅሬታ ፖለቲካ ነው፡፡ላለፉት ችግሮች እኔ የለሁበትም (Not Me) ፖለቲካ ይጠቀማሉ፡፡ የሁሉም የሃገሪቱ ችግሮች ምንጭና ተጠያቂ ሶስተኛ ወገንን ፍለጋ ይሯሯጣሉ፡፡ ይህ ኣይነት የፖለቲካ ሰበብ የበለፀጉ ሃገሮች ካኪቶክራቲኮችና የታዳጊ ሃገራት ካኪቶክራቲክ መንግሰትታት ባህሪ ነው፡፡ ለምሳሌ የዶናልድ ትራምፕ መንግስት ካኪቶክራቲክ መንግስት መሆኑ ኣብዛኞቹ ፖለቲከኞች ይስማሙበታል፡፡ የትራምፕ መንግስት ኣሜሪካን ለዚህ የዳረጋትና ለውድቀትም ተጠያቂ የሚያደርገው የሜኪሲኮ ስደተኖችን እና መጤዎች ናቸው እያለ በተደጋጋሚ ሲለፍፍ ይሰማል፡፡ ኣሜሪካን ከወደቀችበት ኣዘቅት ለማስወጣትም መፍትሄው የሜክሲኮ-ኣሜሪካ ድንበርን ማጠር እንደሆነ ያስቀምጣል፡፡

የኛው ሃገር ካኪቶክራቲኮችም የሃገሪቱ ችግሮች ምንጭና ዋነኛ ተጠያቂ ህወሓት (ወያነ) ነው፡፡ እኛ የለንበትም ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ መፍትሄውም የህወሓት ኣንዳንድ ኣመራሮችና የትግራይ ተወላጅ ኣይከኖችን ተጠያቂ ማድረግ፣ ማሳደድና ማጠልሸት ነው ይላሉ፡፡ በተግባርም ለዚሁ ተግባራዊነት ይሯሯጣሉ፡፡

ካኪቶክራቶች ኣንዱና ዋነኛ የህዝብ ግንኘነት ስራቸው ክፋትን መፈለግና እዛው ላይ ድርሰትና ልበወለድም ቢሆን ፅፈው ነጋ ጠባ መለፈፍ ነው፡፡ የዘርፉ ፖለቲከኞች የቅሬታ ፖለቲካ (grievance) ኣንዱ ተግባርና ስራ ክፋትን መፈለግ (identifyning the vellian) ነው ይላሉ፡፡ ይህ ተግባር በኣደጉት ሃገራት ካኪቶክራቶችና በታዳጊ ሃገር ካኪቶክራቶች ውስጥ ይታያል፡፡ የኢትዮጵያ ካኪቶክራቲክ መንግስትም ይህንን ባህሪ ተላብሶ በተግባር ሲንቀሳቀስ ይታያል፡፡ ላለፉት የሃገሪቱ ችግሮች ይሁን ኣሁን ላሉት ችግሮች ተጠያቂው ወያነ/ ህወሓት-ኣለፍ ሲልም ግለሰቦችን እየጠሩ የጭራቅ ድርሰት ያሰራጫሉ፡፡

የቅሬታ ፖለቲካ ባለፈው ኣንድ ኣመት በመንግስት መሪዎች ፣ በፓርቲ መሪዎች፣ በተፎካካሪ መሪዎች፡ በተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች እንዲሁም በጎረቤት ኣገር መሪዎች ዘንድ በተቀነባበረ መንገድ ነጋ ጠባ የህዝብ ግንኙነት ዋነኛ ስራቸው ሆኖ ታይቷል፡፡ የጨለማ ዘመን፣ የኋሊት ጉዞ ዘመን፣ የሰብኣዊ መብት ጥሰት፣ የስደትና ድህነት ዘመን ወዘተ እየተባለ በኣደባባይ ይገለፃል፡፡ ያለፉት 27 ኣመታት የኢትዮጵያ ችግር ህወሓትና ተጋሩ እንዳሆኑ በኣደባባይ ይናገራሉ፡፡ ከህወሓት ውስጥም ክፋት እና ጭራቅ(identifying the vellian) ተፈልጎ ድርሰት ይሰራል፡፡በተግበርም ተሰርቶ ተሰራጭቷል፡፡ በመንግስታዊና በሌሎች ሚድያዎች ኣመቱ ሙሉ የተዘፈነውም ይሀው የ(vellian) እና የብሶት ፣ቅሬታ ፖለቲካ (grievances) ነበር፡፡

የቅሬታ ፖለቲካ ኣራማጆች እንደ ኣዋሽ ፓርኩ የመንግስት ቅልብተኛ ኣንበሳ በየተሌቭዥን መስኮትና በየኣዳራሹ ስያገሱ ይሰማሉ፡፡ የሚያገሱት ግን የቅሬታ ፖለቲካ ነው፡፡ እንዲህ የሆንከው በህወሓት ነው፣ እንዲህ የሚያደርገው የህወሓት ኣመራር ነው፡፡ እኛ ከደሙ ንፁህ ነን-የለንበትም ይላሉ፡፡ ነጋ ጠባ ንግግር ስያደርጉ ከፊት ለፊታቸው የሚመጣቸውናየሚታዩዋቸው የቀድሞ ኣለቆቻቸው ናቸው፡፡ ኣንዳንዴ ኡገርና ሆረር ይሆኑባቸዋል፡፡ ምንም ፖለቲካ የማያውቁ ህፃናትና የሃይማኖት መሪዎችንም ቢሆን ስብሰበው ህወሓትና ኣንዳንድ የቀድሞ የድርጅቱ ኣመራሮችን (vellian) ኣድርገው ያቀርባሉ፡፡ ልክ የኣዋሹ የመንግስት ቅልብ ኣንበሳ ከቢንቢና ከፌንጣ ጋር እንደሚጣላ እነሱም ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ ይወጣሉ፡፡

የቅሬታ ፖለቲካ ከውጭ ሃገራት የመጡ ተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ የኣገር ውስጥፓርቲዎች፣ ኣክቲቪስት ነን ባዮች የህዝብ ግንኙነት ስራቸው ኣድርገው ሲሰሩበት ይታያል፡፡ ለምሳሌ የታንድ (TAND) መሪዎች የሚታያቸው የ1978 .ም የህወሓት ማሌሊት ግምገማ ነው፡፡ ከዚህ ሆረር መውጣት ኣልቻሉም፡፡ የኣብን መሪዎችም የቅሬታ ፖለቲካ ዋነኛ የህዝብ ግንኙነት መሳሪያቸው ነው፡፡ በተመሳሳይ ኣብዛኛዎቹ የኦሮሞ ኣክቲቪስቶችም ከዚሁ የቅሬታ ፖለቲካ ክፋት ፍለጋ የህዝብ ግንኙነት ስራ የተላቀቁ ኣይደሉም፡፡

የጎረቤት ሃገር መሪዎችም የቅሬታ ፖለቲካ ነጋ ጠባ ለኣመታት ዘምረዋል፡፡ የኤርትራ ችግር ዋነኛው ተጠያቂው ወያነ ነው ብለው ሰብከዋል፡፡ የኤርትራ መሪ ከሃገራችን ካኪቶክራቶች የሚለዩበት ኣንድ ኣጋጣሚ ግን ኣለ፡፡ የኛዎቹ የሁሉም ችግር ምንጭ ወያነ ነው ብለው መዘመር ሲጀምሩ እሳቸው ግን ወያነ ከንግዲህ ጌም ኦቨር በማለት ከኛዎቹ ትንሽ ለጊዜውም ቢሆን ተሸለው ተገኝተዋል፡፡ በተግባር ውስጥ ለውስጥ ያጡዙት እንጂ ጌም ኦቨር ማለታቸው በተወሰነ መልኩ ይለያቸዋል፡፡

የቅሬታ ፖለቲካ ራእይ የለውም፡፡ የዘርፉ ፖለቲከኞች Dead End ይሉታል፡፡ ቀድሞ የሞተ እንደ ማለት ነው፡፡ ፕሮግራምም የለዉም፡፡ የሚገርመው ነገር ኣንዳንድ ጋዜጠኞች የኢህኣዴግ ኣመራሮችን ኣብዮታዊና ልማታዊ መስመር የምትቃወሙ ከሆነ ምንድነው ኣዲሱ ፕሮግራሞችሁና ራእያችሁ ብለው ሲጠይቋቸውና ሰያፋጥጧቸው ይሰማሉ፡፡ ካኪቶክራቲክ ድርጅት ያዉም በቅሬታና ብሶት ፖለቲካ የተዘፈቀ የፖለቲካ ፓርቲና መንግስት ራእይና ፕሮግራም ፍፁም ሊኖረው ኣይችልም፡፡ ቀድሞ የሞተ (Dead End) ነውና፡፡

የቅሬታ ፖለቲካ ይህን የመሰለ ባህሪና መገለጫ ያለው ደካማ ፖለቲካዊ ኣስተሳሰብ መሆኑን ከላይ ለማየት ሞክረናል፡፡ ደካማ መንግስታት ከውጭ ሃገራት ፖለቲካ ኢምፖርት ሲያደርጉ ኣይተናል፡፡ ኒዮሊበራሊዝም ታዳጊ ሃገራት በተለይ በጥገኛ ኣመራሮች የሚመሩ ሃገራት ኢምፖርት የሚያደረጉት ርእዮተ-ኣለም ነው፡፡ ይህ የኒዮሊበራሊዝም ፖለቲካ ኢምፖርት የማድረግ ባህል ኣዲስ ነገር ኣይደለም፡፡ ኣሁን ኣሁን ግን ለፖለቲካ ተንታኞች ኣዲስ የሆነ ክስተት እየታየ ነው፡፡ የቅሬታ ፖለቲካ ከተፈጥሮህ ተነስተህ በራስህ በኣገር ውስጥ የምትፈጥረው ኣስተሳሰብ ሆኖ እያለ የኛዎቹ ካኪቶክራቲክ ሃይላት ግን የቅሬታ ፖለቲካን ኢምፖርት ማድረጋቸው ነው፡፡ ኣዲስ የቅሬታ ፖለቲካ ኢምፖርት ቢያደርጉ ባልከፋ ነበር፡፡ እኚህ መሳቅያ የኛዎቹ ካኪቶክራቶች ኢምፖርት ያደረጉት ግን ያገለገለና ባለቤቱ ጌም ኦቨር ብሎ በኣደባባይ የተፋውን የቅሬታ ፖለቲካ ነው፡፡ በሌላ ኣነጋገር ኤርትራ ውስጥ ከ 20 ዓመታት በላይ ኣገልግሎት ሰጥቶ ውጤት ያላመጣ፣ ኣገልግሎቱን የጨረሰና ሳልቫጅ ተብሎ የተጣለ የቅሬታ ፖለቲካ ነው፡፡ የኛዎቹ ካኪቶክራቶች ይህ ሴልባጅ ፖለቲካ በኣዲሰ የመደመር ሻንጣ ወይም ቦርሳ ሸፍነው ለኣገራችን ህዝቦች ካለፈው ኣመት ጀምረው ለገበያ ኣቅርበውታል፡፡

የቅሬታ ፖለቲካና የፖለቲካ ቅሬታ ሁለቱም ለየቅል ናቸው፡፡ ብስለት ያለው መንግስት ይሁን የፖለቲካ ድርጅት የፖለቲካ ቅሬታ ሊያቀርብ ይችላል፡፡ ይህ በኣለም መንግስታት ዘንድ እንዲሁም የዲሞክራሲን መርህና ኣሰራር በሚከተሉ ኣካላት ዘንድ የተለመደ ነው፡፡

በዚህም መሰረት ህወሓት ከኢህኣዴግ ኣባል ድርጅቶች በተለየ የፖለቲካ ቅሬታ በኣደባባይ ሲያሰማ ነበር፡፡ ህገ-መንግስት ሲጣስ ስልጡን በሆነ መንገድ ህገ- መንግስቱ እንዲከበር ተንቀሳቅሷል፡፡ በተለያዩ ኣከባቢዎች መፈናቀሎችን እንዲቆሙ በፅናት ታግሏል፡፡ይህ መፈናቀል ትክክል እንዳልሆነ በየጊዜው ቅሬታውን እየገለፀ መጥቷል፡፡ የቅሬታ ፖለቲካም የከሰረ ፖለቲካ መሆኑና ኢትዮጵያውያንን የማይጠቅምና ችግሮቻችንን እንዳናይ የሚያደርግ መሆኑን በኣደባባይ ተናግሯል፡፡ ይህ ኣይነት ኣካሄድ ከሴልባጅ ፖለቲካ ኣካሄድ የተለየና በባህሪውም ተራማጅ ነው፡፡ የፕሮፖጋንዳ ስልቱም ተከላካይ ሳይሆን ኣጥቂ ነው፡፡

3) እንሶስላ ወይስ ጉሽርጥ?

ኣንዳንድ ወገኖች የኢህኣዴግ ኣባል ድርጅቶችን ኣቋምና የከፍተኛ ኣመራሮች መግለጫ በመስማት የድርጅቱ መስመር እውን ኣሁንም ኣብዮታዊና ልማታዊ ዴሞክራሲ ነውን? በማለት ደጋግመው የጠይቃሉ፡፡ እነዚህ እህት ድርጅቶች በመሰረታዊው የውግንና መስመሮች ላይ እየተለያዩ እንዴት ኣብረው ይቀጥላሉ ? በመሰረታዊ የውግንና ጥያቄዎች ማለትም በህገ-መንግስቱና በፌደራሊዝም እንዲሁም በማንነት ጥያቄዎች ላይ ግልፅ የሆነ ዝንፈትና ልዩነት እየታየ እንዴት ተመሳሳይ እጅ ኣውጥተው የጋራ መግለጫ ኣውጥተው ይለያያሉ?

ለምሳሌ በኣንደኛ የኣለም ጦርነት ወቅት በተራማጅ ሃይሎች መካከል ብዙ ልዩነቶች የነበረ ቢሆንም የያኔው ተራማጆቹ ትኩረት ያደረጉበት ዋነው ነጥብ ውግንና የሚያሳዩ /የህዝብና የጭቁኖች ወገን መሆንና ያለመሆንን በግልፅ በሚያሳዩ/ መስመሮችንና ኣመለካከቶችን በመለየት ነበር፡፡ ይህም ማለት የጦርነቱ ባህሪና ኣሰላለፍ ብዙዎችን ኣሰላለፋቸውን ያሳየና የለየ ነበር፡፡

ታድያ ኣሁን ህወሓትና ኣዴፓን መለየት ለምን ተሳነ? ህዝቡ በግልፅ ልዩነቱ እየታየው የድርጅቱ ኣመራር በተለይ የህወሓት ኣመራር ለምን ተሳነው? ዝንፈትንና ልዩነትን ተይዞ እሽርሩ ማለት ለምን ያህል ጊዜ ይሆን?

የሰሜን ኢትዮጵያ እናቶች እጃቸውና እግራቸውን የሚዋቡበት ባህላዊ የመዋብያ እፅዋቶች ኣሉ፡፡ ኣንዳንድ ግዜ ባለዉቃቤ ወንዶችም መዋብያው ይጠቀሙበታል፡፡ ይህ እፅዋት እንሶስላ (ሳስላ) ይባላል፡፡ እነሶስላ ኣበቃቀሉ ድንችንና ካሮትን ይመስላል፡፡ ከኣፈር ስር ይበቅላል፡፡ ተሰብስቦም ለገበያ ይቀርባል፡፡ እናቶች ከገበያ ገዝተው በዉሃ ኣጥበው፣ ልጠው፣ ጨፍልቀው እግርና እጃቸውን ለቀናት ይዘፈዝፉታል፡፡ ሌሊት ሊተኙ ሲሉም ጭስ ነገር ኣድርገው ያደርቁታል፡፡ ሳምንታት እየቆየ ሲሄድ እጃቸው ይቀላል-ቆይቶም ይጠቁራል፡፡ ውበትም ይሰጣል፡፡

ገበያ ላይ የሚቀርብ ሁሉ ግን እንሶሰላ ኣይደለም፡፡ እንሶሰላ የሚመስል ጉሽርጥ የሚባል ኣለ፡፡ በኣይን እምብዛም ኣይታወቅም፡፡ ሰዎች በድንገት እንሶሰላ እየመሰላቸው ከገበያ ይገዙታል፡፡ እነደ እንሶሰላም ያዘጋጁታል፡፡ ሶሰት ቀናት ተዘፍዝፎም ቢሆን ግን ዉጤቱ እንደ እንሶሰላ ኣይነት ኣይሆንም-ፍሩሽ ይሆናል፡፡ ትንሽ ለነገሩ ቀላ ይልና በሂደት ይጠቁራል ቢባልም የሰማይ ያለህ ይሆናል፡፡ ታድያ እናቶች እየቆዩ ሲሄዱ የተጠቀሙበት የመዋብያ እፅዋት እንሶሰላ ሳይሆን ጉሽርጥ መሆኑን ይነቁበታል፡፡

የኢህኣዴግ ኣባል ድርጅቶች የፖለቲካ መስመር ልዩነት ያላቸው መሆኑ ህወሓት የሚያውቅ ይመስለኛል፡፡ ለህዝቡ ግልፅ ሆኖ እያለ ለድርጅቱ ኣመራሮች የሚሰወርበት ምክንያት ኣይኖርም፡፡ እንድያውም ኣሁን ኣሁን ውቃቤ ያላቸው ወንዶችም እንሶሰላ ይጠቀማሉ እንዳልነው ከኢህኣዴግ እህት ድርጅቶች ዉጪ የሆኑ የብሄር ድርጅቶች ለህገመንግስቱና ለፌደራል ስርኣቱ ከኦዴፓና ኣዴፓ በላይ ወግነው ይታያሉ፡፡

ኣዴፓና ኦዴፓ ግን የኣብዮታዊ ዴሞክራሲ እንሶሰላ ሳይሆን ጉሽርጥን ተውበዋል፡፡ በስብሰባና በጉባኤ መስመራችን ኣሁንም ኣብዮታዊ ዴሞክራሲ ነው ይበሉ እንጂ ርእዮተኣለማቸው የቅሬታ ፖለቲካ ወይንም ደግሞ ጉሽርጥ እንደሆነ የኣደባባይ ሚስጥር ሆኗል፡፡ በኢህኣዴግ ዉሰጥ ያለ እውነተኛ ልማታዊና ኣብዮታዊ ዴሞክራሲ የህወሓቱ ነው፡፡ ህወሓት እንሶሰላን ከጉሽርጥ ለይቶ ትክክለኛው የኣብዮታዊ ዴሞክራሲ እነሶሰላ ተውቦ ይታያል፡፡ የኣዴፓና የኦዴፓ ግን መጀመርያ ላይ ያልለየ ቢሆንም ኣሁን ኣሁን እያደረ ግን ጉሽርጥ መሆኑ ይታወቃል፡፡

ስለዚህ የህወሓት ኣመራር የሌሎች ኣባል ድርጅቶች መስመር ገና ጉዞ ላይ እያለ ከጅምሩ ምን ሊሆን እንደሚችል የተገነዘበ ቢሆንም እንሶስላና ጉሽርጥ መጀመርያ ጊዜያት ላይ በቀላሉ ሊለዩ ስለማይችሉ ለመለየትና ህዝቡ ከተሞክሮው በግልጽ እንዲገነዘብና እንዲተፋቸው ትንሽ ጊዜ የጠበቀ ይመስለኛል፡፡

ኣሁን ምርጫው እየተቃረበ ሲመጣ ኦዴፓና ኣዴፓ ሁለት ምርጫዎች ይኖራቸዋል፡፡ ኣንደኛው ምርጫ ካኪቶከራሲ በባህሪው ቀድሞ የሞተ (Dead End) ስለሆነ ራእይና መስመር የለውም፡፡ ከቅሬታ ፖለቲካ ውጪ ይሀ ነው የሚባል ፕሮግራም ስለማይነሮው እነዚህ ድርጅቶች ድርቅ ብለው የሃገራችን ችግሮች ምንጩና ተጠያቂ ህወሓትና የትግራይ ህዝብ ሳይሆኑ እነ እገሌ የሚባሉ ኣመራሮች ናቸው ሊሉ ይችላሉ፡፡ እነ እገሌ ተብየ ኣመራር ነበር፡፡ ሰዎችም ማስረጃና መረጃ ሲታጣባቸው በይቅርታና በመደመር ፍልስፍናችን ለህዝብ ስንል ይቅር ብለናቸዋል ሊሉ ይችላሉ፡፡ ይህንን ኣስታከውም መስመራችን ኣሁንም ኣብዮታዊ ዴሞክራሲ ነው የተቀየረ ነገር የለም በማለት ለማጭበርበር ሊሞክሩ ይችላሉ፡፡

ይህ ጠባብ እድል ቢሆንም ዝግ ግን ኣይደለም፡፡ ፕረዚዳንት ትራምፕ የሚደርጉትን ነገሮች በማየት የኛዎቹ ካኪቶክራቶች ኣይኔን ለጨው ብለው ሊቀርቡ የችላሉ፡፡

ሁለተኛ ምርጫቸው ህዝቡስ ምን ይለናል በማለት የጌቶቻቸውና የኣማካሪዎቻቸውን የኒዮሊበራል መስመር እንዳለ ቀድተውና ቋንቋውን ኣዘባራርቀው ማኒፈስቶ ብለው ሊመጡ ችላሉ፡፡ ይህ መጭው ማኒፈስቶ ደግሞ ከልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መስመር ጋር ፊትለፊት የሚጋጭና የሚቃረን ስለሚሆን ራቁታቸው የሚያወጣቸው ይሆናል፡፡ ይህ ኣማራጭ መንታ ስልቶች ይኖሩታል፡፡ ኣንደኛው ስልት ቀጣዩ ምርጫ በተቀመጠለት የጊዜ ሰሌዳ ከተካሄደ እነደምንም ብለው ህጋዊና ህገወጥ መንገድ በመጠቀም፣ ስውር እና ዘመናዊ የምርጫ ውጤትን ተጠቅመው በማጨበርበር የኣሸናፊነት ደወል ሊደውሉ ይችላሉ፡፡ ለዚሁም የድግስ ቀጤማቸውን ጎዝጉዘው፣ ዳሳቸውን ተክለው የደስደስና የኣሸናፊናት ጥሩምባ የሚነፉላቸው የምራባውያን መንግስታት፣ የቀለም ኣብዮት ተቋማት፣ የውጭና የኣገር ዉስጥ ሚድያዎች፣ ምርጫው ሊታዘቡ የሚገቡ ሆን ተብሎ የሚገቡ የምርጫ ታዛቢዎች የምርጫ ቦርድም ጭምር ከወዲሁ ለእንደዚሁ ኣይነት ስራ የተዘጋጁ ይመስላሉ፡፡ ሁለተኛው ስልት የምርጫ ጊዜ በተለያዩ ምክንያቶች እንዲራዘም በማድረግና ይህንን ተከትሎ በሃገሪቱ ውስጥ ብጥብጥና ኣለመረጋጋት እንዲከሰትና ኣሁን ያለው የኢህኣዴግ መንግስት በህገመንግስቱ መሰረት ህጋዊነቱ እንዲያጣና በዚህም ሰበብ ተደርጎ በሃገሪቱ የኣሁኑ ህገመንግስት ፈርሶ ከሁሉም ተቃዋሚዋችና ከመንግሰትም ጭምር ግዚያዊ የሽግግር መንግስት እንዲቋቋምና ይህም ጊዝያዊ የሽግግር ቻርተር በማውጣት ኣዲስ የህገምንግስት ኣርቃቂ ኮምሽን በመሰየም ኣዲስና ለራሳቸው የሚመች ህገመንግስት ሊያፀድቁ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ከላይ ያየናቸው ስልቶች ኣዴፓና ኦዴፓ ታሳቢ ኣድርገው እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ መገመት ተገቢ ይሆናል፡፡ ይህንን የማድረግ ፍላጎታቸው ሰፊ ነው፡፡ እንደኔ እንደኔ የህወሓት ኣመራር እህት ድርጅቶቹ ይህንን እንደሚያደርጉ ወይንም ደግሞ ብያንስ የሴራወ ተባባሪ እንደሆኑ እንቅስቃስያቸውን በማየት ከወዲሁ ግንዛቤ የወሰደ ይመሰለኛል፡፡ እንደ ጉሽርጥ በጊዜ ሂደት እንዲጋለጡ እየጠበቃቸው ይመስለኛል፡፡ በሂደትም ጉሽርጥ ከገባችው ሴት ይልቅ እንሶሰላ የገባው ባለውቃቤ ወንድ ይሻለናል የሚል ይመስለኛል፡፡ እንሶሰላ የገቡ ባለውቃቤ ወንዶችን ተመስለው የሚቀረቡ ወይም ደግሞ የቀረቡ የፖለቲካ ድርጅቶች በሃይል ኣሰላለፉ ጎደና ህገመንግሰቱና የፌደራል ስርኣቱ በዋናነት የሚደግፉ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

4) ፎረም-11

ህገ-መንግስቱና ፌደራል ስርኣቱን በተመለከተ ኣሁን ኣሁን ብዙ ፅህፎች እየተፃፉ ነው፡፡ የፖለቲካ ሃይሎች ኣሰላለፍም ግልፅ እየሆነ የመጣ ይመስለኛል፡፡ የፅሁፌ መነሻ የሆኑት የበዓል ጋዳ ሩባና ፅህፎች ብዙ ሰው እንዳነባባቸው ከኣከባቢዬ ተገንዝቢያለሁ፡፡ እኔና ጓደኞቼ ከፀሃፊው ጋር በመሰረታዊ የሃሳቡ ይዘት ተግባብተናል ፡፡ በህገመንግሰቱና በፈደራል ስርኣቱ ዙርያ ከህወሓት ጋር ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ሃሳብ ኣለን፡፡

በህገመንግስቱ፣ በፌደራል ስርኣቱ እንዲሁም በብሄር ብሄረ ሰቦችና ህዝቦች የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት እሰከ መገንጠል (ኣንቀፅ 39) ተመሳሳይ ሃሳብ ካለን ፎረም -11 በሚል ስያሜ ፅሁፍ እያቀረብን ብንወያይና ለሃገራችን ገንቢ ሚና ብንጫወት ተገቢ ይመስለኛል፡፡

እንደኣጋጣሚ ባዓል ጋዳና ሹም ባሕሪ ኢትዮጵያን በመሰራት ረዥም ታሪክ እንዳላቸው የኢትዮጵያ ታሪክ ይመሰክራል፡፡

ኣሁንም ከሰሜን እየፈነጠቀ ያለው የፖለቲካ ሕብረ ቀለም ጮራ (spectrum) ኣፋር ላይም ተፋፍሞ ቀጥሏል፡፡ ቀጣዩ የፎረም-11 ፅሁፍ ከሌሎች የፖለቲካ ህብረ ቀለም ከፈነጠቃባቸውና ጮራው ከተዳረሰባቸው ኣከባቢዎች እንደሚሆን ባለ ሙሉ ተስፋ ነኝ፡፡

 

 


Back to Front Page