Back to Front Page

GAME OVER ያልኩት ገና ነው! ክፍል ሁለት

GAME OVER ያልኩት ገና ነው!

 

ኡስማን ሙሉዓለም፣ ከሓራ ገበያ

4-7-19

 

ክፍል ሁለት

 

በክፍል አንድ በአገራችን ያሉት ችግሮችና መንስኤዎቻቻው ምን እና ምን እንደሆኑ ለማየት ሞክርላሁኝ፡፡ የኢሳያስ መንግስት ይሁን አጋሮቹና አጨፋሪዎቻቸው ከረፈደም ቢሆን ጫወታው እንዳላበቀለት እንደተገለፀላቸው ገልጫለሁ፡፡ ዋናው ነገር መፍትሄው ምንድር ነው? ነው፡፡

 

 

በኛ በኢትዮጵያውያን በኩል ምን ይደረግ?

በትግራይ ህዝብና በመሪው ድርጅቱ ሕወሓት ይሁን በሌሎች ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦችና ድርጅቶቻቸው ምን መደረግ አለበት? በሚለዉ አስተያየት ስሰጥ እንደ አንድ ትግራዋይ ኢትዮጵያዊ ለአገሬ የሐሳብ አስተዋፅኦ ለማድረግ እና ለውይይት የሚሆኑ ነጥቦችን በማማመለከት እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ እንዲያዳብረው በማለት ነው።

 

 

የትግላችን ስልቶች ዓላማ፣

የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ማእከል ሆኗ ያለችውን ትግራይን በአገር ውስጥ ካሉት ጠላቶች ይሁን ከባዕድ ቅጠረኞች በመከላከል የበለጠ ማጠናከርና እንደመነሻ መንጠርያ በመጠቀም ኢትዮጵያ ሀገራችን ከመፍረስ መታደግ።

 

የትግሉ ስልቶች መርሆች፣

-      ከሁሉም በፊት እነዚህ እየገጠምናቸው ያሉትን ሃይሎች ማንነት ተገንዝበን እንፋለማቸው፣

o   ተስፋ የቆረጡና መውደቅያቸው የደረሰ ስለሆነ ይዘውን እንዳይወድቁ ጥንቃቄ ማድረግ።

 

-      ህዝባችን ከጎናችን ማሰለፍ የአሸናፊነት ምንጭ መሆኑን መገንዘብ፣

o   ጥንካሪያችንና እኛን ከሚጠሉ ሐይሎች መለያችን ህዝባዊ ወገንተኝነታችን መሆኑን አለመርሳት፣ የህዝቦች የበላይነትና የእኩልነት አመለካከት ትጥቃችን በማድረግ ማንኛውም ህዝብ ማክበርና በእኩል አይን ማየት፡፡ ገዥዎችን ከህዝቡ ለይቶ መመልከት፣ እነሱ የኛ የሚሉትን ህዝብ ጥብቅና የቆሙ መስለው ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት ሲፈልጉ መሳርያ አንሆንም ብለን መቆም፣ ህዝባዊ ወገንተኛ አሰላለፋችን ማሳመር።

Videos From Around The World

 

-      ህገመንግስታዊነትና ፈደራሊዝም የሁሉም ችግሮቻችን መፍትሔና የሰላማችን ምንጭ እንደሆነ የተገነዘበ አተያይና አካሄድ መጨበጥ፣

 

 

የትግሉ ስልቶች

 

1ኛ) በአሁኑ ወቅት የትግራይ ህዝብ እያሳየው ያለው አንድነት አጠናክሮ መቀጠል፣

የትግራይ ህዝብ ጥቃት ስለደረሰበት ብቻ አይደለም መተባበርና አንድነቱን ማጠናከር ያለበት። የትግራይ ህዝብና መሪ ድርጅቱ ህወሓት ከመቼው ጊዜ በላይ አንድነታቸው ማጠናከር የሚያስፈልገው የጥልቀት ተሃድሶ መስመር በእውነት በማድረጉና ህዝብን ማእከል አድርጎ መፍትሔ የሚሰጥ ድርጅት ያለው ትግራይ ውስጥ መሆኑ አውቀው GAME OVERን እውን ለማድረግ እየተረባረቡ ስላሉ ጭምር ነው ። ዘላቂነት የሚኖረውም በዚህ የትግል ፅናትና አንድነት ላይ ሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦችንም ከጎኑ ሲያሰልፍ ብቻ ነው።

 

በትግራይ ውስጥ የሚታዩ ችግሮች የትግራይ መንግስትና ህዝብ ፈጥነው በመመካከር ሊፈቱት ይገባል። እነዚህ የሚታዩት ችግሮች እንዲፈቱ ሳይሆን የትግራይ ህዝብና መንግስትን የሚያለያዩ አጅንዳ ሆነው እንዲቀጥሉ የሚፈልጉ የትግራይ ህዝብ ጠላቶችን ቀዳዳ ዕድል ልንሰጣቸው አይገባም። ሊያሸንፉን የሚችሉትም ውስጣችን ደካማ ሲሆን ነው። አሁንም የኛው ተወላጅ የሆኑ ከዳተኞችን በጥቅም ደልለውና በገንዘብ ሃይል ቅሬታ ያላቸውን በመመልመል አንድነታችንን ለማመስ እየሰሩ ናቸው። እነዚህን የምንታገልበት መንገድ መጀመርያ በምክር፣ ምክር አንሰማም ካሉ ደግሞ ድርጊታቸውን በማስረጃ አስደግፈን ስናጋልጣቸውና ተቀባይነታቸው ስናሳጣቸው ነው። ለመሪዎቻችንም እስካሁን እየሰጠንው ያለውን ድጋፍ አጠናክረን ስንቀጥል ነው። አየኻ ናይና እንቀጥልበት።

 

2ኛ) የትግራይን ህዝብ ይሁን የኢትዮጵያን ህዝቦች ትጥቅ ለማስፈታት የሚድረገውን እንቅስቃሴ አጥብቆ መታገል፣

አድሃሪዎች ሁሌም ህዝብን ይፈራሉ። ቢታጠቅም ባይታጠቅም ማታለል ሳይችሉ ሲቀሩ በሃይል ለማንበርከክ ይዳክራሉ። አብሶ የታጠቀ ከሆነ ትጥቁን በመቀማት ጊዜ ለመግዛት ይሞክራሉ። የኢትዮጵያ ህዝብ ከአሁን በኃላ አሁን ባለው ሁኔታ በአንድነት የመቀጠል ዕድሉ መንምኗል። ኢትዮጵያ ግን ምንም ብትቀጥን ጠጅ ናት በእንግዳ ደራሽ በውኃ ፈሳሽ የምትፈርስ አይደለችም ተብሎ ስለተቃዠ በአይናችን ውልቅልቅዋ እየወጣ እያየንና እንደኛ ኩራት ይሰማቸው የነበሩ ሶማሊያ፣ ሊብያ.፣ የመን፣ ሶርያ ጠጅ ስላልሆኑ ነው የፈራረሱት ብለን ራሳችንን እናታልል ካልተባልን በስተቀር በስመ ለውጥ ውስጣችን ታምሶና የውጭ ሃይሎች መጫወቻና መሳለቅያ ሁነናል። ከመበታተናችን በፊት ታግለን አገራችን ለማዳን የገዥዎቻችን ትጥቅ የማስፈታት ውሳኔ መቃወምና ከህዝብ ጫንቃ እንዲወርዱ ማስገደድ ጊዜ የማይሰጥ ጉዳይ ነው። የዚህ ትጥቅ ማስፈታት ዋና ዒላማ ደግሞ በቀደምትነት GAME OVER ተብሎ ሲሳቅበት የነበረው የትግራይ ህዝብና መሪ ድርጅቱ ነው። ይህን ሴራ በማንኛውም መንገድ ማክሸፍ ተገቢም ግዴታም ነው።

 

3ኛ) ዲጂታል ወያኔ ከመቼውም ጊዜ በላይ ማጠናከር፣

አሁንም መልኩ እየቀያየረ ዘረኛ የጥላቻ ዘመቻ ግንባር በፈጠሩ ሚድያዎች በትግራይ ህዝብም በሌሎች ህዝቦችም ላይ እየተጠናከረ ነው። ዋስትናችን የሆነውን ሕገመንግስት ላይ በግላጭ መቃወም ብቻ ሳይሆን በተግባርም እየተጣሰ ትናንት ተፈተው የነበሩ ችግሮች ሕገመንግስቱ በመናዱ ሁሉም ቦታ ችግር ተፈጥሮ ህዝቦች ለእልቂት ለመፈናቀል ለስደት ሲዳረጉ ተመልሰው የናዱትን ሕገመንግስት ተጠያቂ የሚያደርጉ ሚድያዎች ችላ ማለት ተገቢ አይደለም። ጠብ ጫሪነታቸው ባለ መታከት በማጋለጥ ልንታገላቸው ይገባል። በሶሻል ሚድያም ሰፊ የማወናበድ ስራ እየሰሩ በትግራይ ያለው አመራር ውስጥ ልዩነት እንደተፈጠረና አመራሩ የሚጠቀመውን መፈክር አንግበው ሊያኮላሹት እየተንቀሳቀሱ ነው። ዲጂታል ወያኔም በሁሉም የሚድያ መስኮች ትግሉን በጀመረው መንገድ ማፋፋም ይጠበቅበታል። ከሌሎች ህዝቦችም ግንባር ፈጥሮ ትግሉን ከፍ ወዳለ ደረጃ አድርሶ የፀረ ህዝቦችን እንቅስቃሴ ማጋለጥና የእስከአሁኑ ድሎች ጠብቆ ወደ ሙሉ ድል ማሸጋገር ይኖርበታል። ከሌላው ህዝብ ጋር በጥርጣሬና በጥላቻ እንድንተያይ የሚያደርጉትን ደባ ማክሸፍ የምንቸለው ህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ እንዲጠናከር ማድርግ ከቻልን መሆኑ ተገንዝበን ትኩረት ሰጥተንና ዲጂታሊም ግንባር ፍጠርን ስንረባረብ ነው። ትግላችን በሁሉም የሚድያ ዘርፎች በተከታታይና በማያቃርጥ መንገድ በማቀጣጣል GAME OVER እንበላቸው።

 

4ኛ) ለድርድር ዝግጁ መሆን፣

 

ቅድመ ሁኔታ፣

       ድርድሩ ለህዝብ ይፋ መሆን አለበት።

 

       በድርድሩ የሚኖሩ ቅድመ ሁኔታዎች፣

1.   በለውጥ ስም በቂም በቀልና በግፍ የታሰሩትን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መፍታት፣

2.   ከኢህአዴግ ውሳኔ ውጭ የተፈቱ ወንጀለኛቾ እና ከውጭ አገር የገቡ ወንጀለኞች (በፍ/ቤት የተፈርዶባቸው) ይቅርታ እንዲጠይቁ ወይም የማይጠይቁ ከሆነም በምንም የፖለቲካ ጫወታ እንዳይገቡ መገደብ (የናዚ ፓርቲ አባላት በጀርመን ገደብ እንደተደረገባቸው ዓይነት)፣

3.   በትግራይ ህዝብና በህወሓት ብቻ ላይ ያነጣጠሩ የማጥቆር ዘመቻዎች በይፋ ይቅርታ ይጠየቅባቸው፣

4.   የውጭ ዜግነት ያላቸው ሰዎች በኢትዮጵያዊነት ስም ተደራጅተው ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ማድረግ የሉዓላዊነት ጥያቄ የሚያስነሳ ጉዳይ ስለሆነ ዜግነታቸው በሂደት እስኪያገኙ ድረስ ከማንኛውም ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ እንዲቆጠቡ ማድረግ፡፡ ይህ ከፖለትካ ምህዳሩ መስፋትና መጥበብ ምንም የሚያገናኝ ነገር የሌለዉ ከመሆኑ በተጨማሪ ብዙ ኢትዮጵያውያን ሊሂቃን ፓርቲ መስርተው ተቃውሟቸውን እያሰሙ ለዓመታት የቆዩ ሰላሉ ለነሱ ቅድሚያ ሰጥቶ ምቹ ሁኔታ መፍጠርና ማበረታት አሰፋለጊ መሆኑን፣

5.   የዕርቅ ኮሚሽን ተብለው የተመረጡ አባላት ለራሳቸው ችግር ያለባቸው ናቸው፡፡ አብዛኛዎቹ ጥላቻ ሲስብኩ በህዝብ ላይ ግፍ የፈፀሙና ፖለቲከኞችም ያካተተ ስለሆነ ፈርሶ አዲስ መስፈርት በጋራ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ወጥቶ ገለልተኝነታቸው የተመሰከረላቸው ነፃ ሰዎች ያካተተና ሁሉም የሚስማማበት እንዲሆን ማድረግ፣

6.   በለውጥ ስም የገቡማ ኢትዮጵያዊነታቸው ያልቀየሩ በኤርትራ፣ በሶማሊያና ኬንያ የነበሩትን ፈጥነው እንደ ፖለቲካ ድርጅት የሚያስፈልጋቸው ሕጋዊ መስፈርት አሟልተው በቀጣይ የአገራችን ዕጣ ፋንታ እንደዜጋ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ማድረግ፣

 

የድርድሩ አላማ

       ኢትዮጵያ አገራችን ከገጠማት አደጋ ያለ ተጨማሪ ኪሳራ በድርድርና በውይይት ለመታደግ መቻል፣

 

በድርድሩ መሳተፍ ያለባቸው በቅድመ ተከተልና መዘጋጀት ያለባቸው መድረኮች፣

    i.      ድርድሩ መጀመርያ ደረጃ በህዝብ ተመርጠው በስልጣን ላይ ባሉት ገዥ ፓርቲዎች መካከል ይሁን፡፡ አጋር ፓርቲዎችንም ያካተተ መሆን አለበት፡፡

   ii.      የተወካዮች ምክርቤት እና ፌዴሬሽን በተገኙበት ከሁሉም አካባቢ ህዝብ የወከላቸው እንዲሳተፉ ማድረግ፣

  iii.      ከሁሉም አካባቢ ከፍተኛ ትምህርት ቤቶችና በሌላም ስራ የሚገኙ ሙሁራንና ወጣቶችን ያካተተ መድረክ።

  iv.      ቀጥሎ ህጋዊና ኢትዮጵያ ዜጎች የሆኑ ተቃዋሚ ፓርቲ ያካተተ መድረክ። እነሱም የራሰቸው አጅንዳዎች በጋራም በተናጠልም አቅርበው የሚወያዩበት መድርክ፣

 

በአጠቃላይ በሚካሄዱ የውይይት መድረኮች ተሳታፊዎች ግልፅ የሆነ መስፈርት ወጥቶ ይጋበዛሉ። አንድ አካል የፈለገውን ብቻ የሚጠራበት አካሄድ መኖር የለበትም፡፡

አጀንዳ።

1.  የጥልቀት ተሃድሶ ውሳኔዎች ምን ነበሩ? እንዴትስ ተፈፀሙ፣

2.  የኢህአዴግ ምክርቤት ምርጫ ጊዜ ራሱን ከውስጥ ያደራጀ ሃይል እንደነበረ በራሳቸው አንደበት የተነገረውን ማጣራትና በድርጅቱ አሰራር መስረት እርምት ማድረግ፣

3.  ለውጥ በሚል ሰበብ ከህገመንግስት ውጭና ከኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚና ምክርቤት ውሳኔ ውጭ የተወሰኑ ውሳኔዎች መመርመር፣

 

4.  ከውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ውጭ የተፈፀሙ ግንኝነቶች መመርመር፣ የውጭ ጣልቃገብነት መመርመር፣

5.  ለውጥ ከተደረገ በኃላ በአገሪቱ የተፈጠሩ አዳዲስ ሁኔታዎችን መገምገም፣

6.  በንኡሳን (minority) ህዝቦች የተፈፀሙ ጥቃቶች መመርመር፣

በነዚህ አጀንዳዎች ገዥው ፓርቲ በግልፅ የሚያስማሙትና የሚለያዩት ተወያይቶ ሌሎች ግምገማዎቹና ቀጣይ አቅጣጫ ላይም ውይይት አካሂዶ የደረሰውን ድምዳሜ ያለ ምንም ሽፍንፍን ለህዝቡ ይፋ እንዲሆን ማድረግ። ከስብሰባ በኃላ የተዛባና የተሸፋፈነ መግለጫ እንዳይቀርብ የሚያደርግ አሰራር መቀየስና ታዛቢዎች እንዲሳተፉ ማድረግ የጠበቅበታል።

 

5ኛ) ከኤርትራው የኢሳያስ ቡድን እየተሸረበብን ያለውን ሴራ መከላከልና ማክሸፍ፣

የኢሳያስ ቡድን በእብሪት በአገራችን ላይ ወረራ ሲፈፅሞብን ለመከላከል ከባድ መስዋእትነት ተከፍሏል። ከጦርነት በኃላም በተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ ቢደረግለት አሻፈረኝ ሲል የቆየው ቡድን በዋናነት በኤርትራ ህዝብ ግፊት፣ በውጭ ሃይሎች ግፊትና ህወሓት ተዳክሟል GAME OVER በሚል የተሳሳተና የቅዠት ስሌት ቢሆንም ኢህአዴግ የቀየሰው የሰላም ጥሪ (አብይ የራሱ የግሉ ተነሳሽነት አድርጎ የሚሞካሽበት) ተቀብሎታል፡፡ ይሁን እንጂ የሁለቱ አገር ህዝቦች ሰላም መስፈኑ ሲያስደስታቸው ኢሳያስ ግን መጀመርያ የነበረው የአሸናፊነት ስሜቱ እየሟሸሸ ሲጠፋው ደሙ ገንፍሎበታል፡፡ ቀንና ሌሊት በሌላ ሴራ መጠመዱ ደግሞ ገሃድ ሆኗል፡፡ ሰለሆነም ይህንን የተለመደ ሴራ ተገንዝበን ሁኔታውን በጥሞና በመከታተልና ዝግጁ መሆንን ይጠይቃል። የአብይ መንግስት ያደረገው ምስጥራዊ ግንኙነት (ለኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚም ድብቅ መሆኑ ይታወቃል) ለዋናው ባለቤቱ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝቦች በግልፅና በዝርዝር መገለፅ አለበት። የአገር መከላከያ ሠራዊታችንም በተጠንቀቅ ቆሞ ሁኔታውን መከታተል ይኖርበታል። አልገመትንም። ሓይል ቀንሰን ነበር የሚል ምክንያት በአገር ጉዳይ ተገቢ አይደለምና። ኢሳያስ በቃሉ ተገኝቶ አያቅም። ከድሮ ጀምሮ አቋሙ እንደሚዋዥቅ የሚታወቅ ነው። የአልጀርስ ስምምነት አልቀበልም ሲል ቆይቶ በሁኔታ ተገፍቶ እሺ ተቀብያለሁ ይላል። ባድመን ሳታስረክቡ ውይይት የለም ሲል ከርሞ ባድመ ሳይረከብ ታረቅኩኝ ብሎ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ሀይል የገነባውን ልማት ይመርቃል። ዛላምበሳ ተከፈተ ብሎ ተገዶም ቢሆን ዛላንበሳ ድረስ መጥቶ አስከፍቶ ሲያበቃ GAME OVER ገና ነው ሲባል ዝጉት ብሎ ያዘጋና ሁመራ ኡምሓጀርን ከፈትኩኝ ይላል። በምንም ግዜና ሁኔታ አይታመንም። ለዚህም ነው የኤርትራ ህዝብ ኢሳያስ ቢሞትም መሞቱን እርግጠኛ ለመሆን እንደሚቸገር የሚቀልደው።

ሰለሆነም የፈረደበት የዳር ደንበሩ ህዝባችንም ሁኔታውን በጥንቃቄ መከታተል የሚኖርበት። ፌደራል መንግስትም ትጥቅ ማስፈታት ሳይሆን የሚጠበቅበት ህዝቡ በተለይም ሚሊሻው የእስከሁን ድረስ ከመከላከያ ጎን በመሆን ሠራዊታችን ያልሸፈነውን ቦታዎች ሲጠብቅና ልዩ ግዴታ ለብቻው የተሰጠው ሳይኖረው ያለምንም ክፍያ በነፃ በማገልገሉና ላደረገው አስተዋፅኦ መካስ ይጠበቅበታል። የካሳው ጉዳይ በኢህአዴግ ተወስኖ (እንደሁሉም ውሳኔዎች) በፈዴራል መንግስት ተግባራዊ ሳይሆን የቀረ ጉዳይ ነው። አሁንም የአልጀርስ ስምምነቱ ሁሉ ኢትዮጵያዊና የአፍሪካ ሕብረት ተሳትፎበትና ህዝብ ለህዝብ የበለጠ በሚጠናከርበት አግባብ የተጀመረው ሰላም ስርዓት ይዞ ግልፅነት ላይ ተመስርቶ እንዲፈፀም ከኤርትራ ወንድሞቻቻን ጋር የጀመርነውን ግንኙነት ማጠናከር ይገባል።

 

6ኛ) በሰላም በሕገ መንግስቱና በፌደራሊዝም ዙርያ የጋራ ግንባር ፈጥሮ በአፋጣኝ ትግል ለመጀመር ጥሪ ማድረግ፣

ህወሓት ከኢህአዴግ ሊሰለፍ የሚችል ሃይል ከተገኘ (በፀሓፊው እምነት ኢህአዴግ ያለፈው መጋቢት ወደ ሁለት ተከፍሎ በቀጣይም መከፋፈሉ ብስቦት አሁን ወደ አንድ ግለሰብ ያሰኘውን የሚያደርግበት ነገር ነው ብሎ ያምናል) ከአጋር ድርጅት፣ ከተቃዋሚ ድርጅቶች ጋር በመሆን አገር ለማዳን በሚደረግ ትግል የማንንም ፍቃድ ሳያስፈልገው ባሰኘው መንገድ መደራጀት ወቅታዊና ጊዜ የማይሰጥ የነብስ አድን ስራ አድርጎ መፈፀም አለበት፡፡ የህዝብን የሰላም የልማትና የዲሞክራሲ ጥያቄ ለመመለስ፣ የአገሪትዋ ህዝቦች ከእልቂት ከመፈናቀልና ስደት ብሎም ኢትዮጵያ አገራችን እንደ ሶርያ ከመፍረስ ለመታደግ ህዝቡን ለማስተባበር የሚችል ህዝባዊ ውግንና ያለው ሃይል ማሰባሰብ እንዲቻል ግልፅ ጥሪ ማድረግ ይገባል፡፡ ይህን በማድረግ ከምርጫ በፊትና ምርጫው በሕገመንግስቱ መሰረት የሚፈፀምበት የትግል ስልት በጋራ አቅደው አገራችን ከመብታትን የሚታደጉበት አቅጣቻዎች በአስቸካይ መቀየስ ያስፈልጋል።

 

ማጠቃለያ

ከላይ የተቀመጡት ስልቶች በተናጠል የሚፈፀሙ ሳይሆን ተጣምረውና ተጎራርሰው አንዱ የትግል ስልት ሌላውን በመደገፍና የሌሎች ስልቶችም ድጋፍ ተመርክዞ ሳይነጣጠሉ የሚፈፀሙና በተነሳሽነትና በፈጠራነትም እየዳበሩ የሚሄዱ ናቸው። ከሁኔታዎች ፈጣን ለውጦችም ስልቶቹ እየታደሱ እንድሚሄዱ ታሳቢ ያደረግና በአፈፃፀምም የአመራር ጥበብ ታክሎበት ስኬታማ ውጤት ለማስመዝገብ የሚያስችሉ እንዲሆኑ የሁላችሁም ሃሳብ በውይይት እንዲታኩልብት ዘንድ ይሁኑ፡፡

 

ህዝባዊነት ህዝበኝነትን ያሸንፋል!

አሁንም እናሸንፋለን!

ኢትዮጵያ እንዳትፈርስ በትግል እንታደጋታለን!

 

ኡስማን ሙሉዓለም፣ ከሓራ ገበያ

መጋቢት 2011

 

Back to Front Page