Back to Front Page

መሣሪያና ገንዘብ አዘዋዋሪዎቹ እነማን ናቸው? አሁንስ “Fake News” እየመሰለን ነው!

መሣሪያና ገንዘብ አዘዋዋሪዎቹ እነማን ናቸው? አሁንስ “Fake News” እየመሰለን ነው!

(ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)

5-25-19

በዚች መጣጥፍ በሁለት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ትኩረት አደርጋለሁ፡፡ አንደኛ፤ በህገ ወጥ የጦር መሣሪያና በገንዘብ ዝውውር ዙሪያ የሚያጠነጥን ይሆናል፡፡ ሁለተኛ፤ ጠቅላይ ሚንስትሩ የሚሾሟቸውን ባለ ስልጣናት እና ለሀገራዊ ቦርድና ኮሚቴ አባልነት የሚመርጧቸውን ግለሰቦች በሚመለከት ነው፡፡ ሁለቱንም ጉዳዮች በየተራ ለማየት እሞክራለሁ፡፡

ህገ-ወጥ መሣሪያና ገንዘብ አዘዋዋሪዎቹ እነማን ናቸው?

ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር ዓብይ ስልጣን ከያዙ ወዲህ ባሉት ጊዜያት በመንግስት መገናኛ ብዙሃን አማካይነት ከምንሰማቸው ዜናዎች ውስጥ “በአዋሽ የጉምሩክ ፍተሻ ጣቢያ ይህን ያህል የጦር መሳሪያ ከመሰል ጥይቶች ጋር ተያዘ፡፡ በባህር ዳር ኬላ ይህን ያህል ሽጉጥ ከጎንደር ወደ መሀል አገር ሲጓጓዝ ተያዘ፡፡ በአዲስ አበባ መግቢያ ይህን ያህል ሚሊዮን ዶላር ተያዘ…” የሚሉት ተደጋግመው ይደመጣሉ፡፡

Videos From Around The World

እነዚህን ዜናዎች በተመለከተ በህብረተሰቡ ዘንድ ተደጋግመው የሚነሱት ጥያቄዎች “እነዚህን የጦር መሳሪያዎች ሲያንቀሳቅሷቸው የነበሩት እነማን ናቸው? ያን ያህል መጠን ያለው የውጭ ሀገርና የኢትዮጵያ ብር ያጓጉዝ የነበረው ግለሰብ ወይም ቡድን ማን እንደሆነ ፍንጭ የለም? ገንዘቡና መሳሪያው በራሱ አቅምና ጉልበት መኪና ላይ ተጭኖ ነበር የሚጓጓዘው?...” የሚሉ ናቸው፡፡ ለእነዚህ ጥያቄዎች በቂ መልስ ያላገኘው ህብረተሰብ ዛሬ ዛሬ እነዚህን ዜናዎች ሲሰማ “ይሄ ነገር ‘Fake News’ (የውሸት ዜና) ይሆን እንዴ? ማለት ጀምሯል፡፡

ወንጀልን መከላከል የፖሊስ ሥራ ብቻ አለመሆኑ ተደጋግሞ ሲነገር እንሰማለን፡፡ “በህዝብ ድጋፍ ያልታገዘ የወንጀል መከላከል ሥራ አጥጋቢ ውጤት አያስገኝም፡፡ ህዝብን ያላሳተፈ የወንጀል መከላከል እንቅስቃሴ በአንድ እጅ ማጨብጨብ ነው” ይላል ፖሊስ ራሱ፡፡ በዚህ አባባል የዚህ ጽሑፍ አቅራቢም ይስማማል፡፡ ምክንያቱም (አንድ መቶ ሚሊዮን ህዝብ በሚኖርበት ሀገር) የፖሊስ ኃይል ውሱን ስለሆነ በአንድ ጊዜ ሁሉም ስፍራ ሊገኝ አይችልም፡፡ ህዝብ ግን በሁሉም ስፍራ ይኖራል፡፡ ህዝብ በየአካባቢው በይፋም በስውርም የሚደረገውን እንቅስቃሴ ያያል፡፡ የሚነገረውንና የሚንሾካሾከውን ጭምር ይሰማል፡፡ “ከህዝብ የሚሰወር ነገር የለም” የሚባለው በዚህ ምክንያት ነው፡፡

በሌላ በኩል ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው መንግስታዊ አሰራር ህገ መንግስታዊ እውቅና የተሰጠው የመንግስት ተቋማት ሊከተሉት የሚገባ የአሰራር መርህ ይመስለኛል፡፡ ይሁን እንጂ ፖሊስ ይህንን የአሰራር መርህ ወደ ጎን በመተው የተጠርጣሪዎችን ማንነት በመደበቅ የወንጀለኞች ጫካ መሆኑ እየተስተዋለ ነው፡፡ ፖሊስ የተጠርጣሪዎችን ማንነት ይፋ ባለማድረግ የወንጀለኞች ሽፋንና ከለላ እየሆነ ነው፡፡ ለምን? በበኩሌ፤ ፖሊስ የተጠርጣሪዎችን ማንነት ይፋ የማያደርገው በሁለት ምክንያቶች ይመስለኛል፡፡ አንደኛው ምክንያት ከወንጀሉ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ተጠርጣሪዎች እንዳይበረግጉና እንዳይሰወሩ ለማድረግ ሲሆን፤ ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ የተጠርጣሪዎችን ሰብአዊ መብትና ክብር ለመጠበቅ በማሰብ ይመስለኛል፡፡

እንደኔ እንደኔ ሁለቱም ምክንያቶች አሳማኝ ሆነው አይታዩኝም፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ፖሊስ ህዝብ የሚሳተፍበት የወንጀል መከላከል ሥራ እሰራለሁ እስካለ ድረስ “ተጠርጣሪዎች ይሰወራሉ” ብሎ መስጋት የለበትም ባይ ነኝ፡፡ ቢሰወሩም ህዝብ መንጥሮ አውጥቶ ይሰጠዋልና! በሁለተኛ ደረጃ “የተጠርጣሪዎችን ሰብአዊ መብት ለመጠበቅ” የሚለውን በተመለከተ አንድ ሰው “በወንጀል ተጠርጣሪ ነው” ማለት ቢያንስ ቢያንስ ለመጠርጠር የሚያበቃ በቂ ሁኔታ ተሟልቷል ማለት ነው፡፡ አንድን ሰው “ለመጠርጠር የሚያበቃ በቂ ሁኔታ” ከተሟላ ደግሞ፤ በበኩሌ የተጠርጣሪውን ማንነት ይፋ ማድረግ ሰብአዊ መብቱንም ሆነ ክብሩን የሚነካ ሊሆን አይችልም የሚል እምነት አለኝ፡፡ እንዲህ ያለው ሁኔታ በየትም ሀገር ተግባራዊ የሚደረግ አሰራር መሆኑንም የህግ ባለሙያዎች ጭምር የሚያውቁት ነው፡፡

ከእነዚህ እውነታዎች በተጨማሪ በበኩሌ ሁለት ተደማሪ ሀቆች ይታዩኛል፡፡ በተለይም አሁን ሀገሪቱ ካለቺበት የሰላምና የፀጥታ ስጋት አኳያ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ አዘዋዋሪዎችንና የህገ ወጥ ገንዘብና የኮንትሮ ባንድ እቃ አሸጋጋሪ ተጠርጣሪዎችን ማንነት ይፋ በማድረግና ባለ ማድረግ መካከል ለህዝብና ለሀገር የሚያስገኘውን ጥቅምና ጉዳት መመዘን አስፈላጊ ነው፡፡ ሁለተኛ የፍትህ አካላት በፍርድ ሂደት ውሳኔ እስከሚሰጡ ድረስ (በሁሉም ጉዳዮች ሳይሆን) ወቅታዊ የህዝብ ሰላምና ደህንነት ስጋት በሆነ ወንጀል በተጠረጠሩ ሰዎች ላይ ህብረተሰቡ “ኅሊናዊ የሞራል ፍርድ” የመስጠት መብት የለውም ወይ? የሚለው ጥያቄ መታየት አለበት የሚል እምነት አለኝ፡፡

በበኩሌ፤ የወንጀል ሰለባ የሆነ ማህበረሰብ በፍርድ ቤት በሚሰጥ ፍትህ ብቻ እርካታ ያገኛል፣ ጉዳቴን ህግ ተበቀለልኝ ብሎ የእርቅ ስሜት ያድርበታል የሚል እምነት የለኝም፡፡ አንዳንድ ጊዜ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ማህበረሰባዊ ቁስል በፍርድ ቤት ውሳኔ ብቻ አይሽርም፡፡ እንዲያውም የፍርድ ቤት ውሳኔ የባሰ ብስጭት ሊፈጥርበት የሚችል አጋጣሚ ይኖራል ብየ አስባለሁ፡፡ እንዲህ ባሉ አጋጣሚዎች ላይ ማህበረሰቡ በውስጡ ያለውን ስሜትና የኅሊና ፍርድ እንዲናገር ማድረግ ጠቃሚ ነው ይላሉ የማህበራዊ ሳይንስ ሊቃውንት፡፡

የሹመት ሀትሪክ

ሃሳቤን በአንዲት እድሜ ጠገብ አባባል ልጀምር፡፡ “ከእንጨት … ከሰው መርጦ ለሹመት” ይላሉ አበው፡፡ ይህቺ አባባል ብዙ ነገር ትናገራለች፡፡ በሀገራችን ዘመናዊ የመንግስት አስተዳደር ስርዓት እውን መሆን የጀመረው በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግስት እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ ንጉስ ምኒልክ የመጀመሪያውን የሚንስትሮች ምክር ቤት በ12 ሚንስትሮች ያዋቀሩት በ1900 ዓ.ል ነበር፡፡ እነዚያ ተሿሚ ሚንስትሮች ምን ዓይነት ስብጥር እንደነበራቸው በበኩሌ አልመረመርኩም፡፡ ይሁን እንጂ ተሿሚዎቹ የተመረጡት “… ከሰው መርጦ ለሹመት” በሚለው መስፈርት ሊሆን እንደሚችል አስባለሁ፡፡

በርግጥ ከበግ ወይም ከግመል አሊያም ከፈረስ መርጦ ሹመት ሊሰጥ ስለማይችል ይቺ አባባል አስቂኝ ገጽታ አላት፡፡ አስቂኝ ገጽታዋን ተትን ውስጧን ስንመረምር ግን ሌላ ምስጢር ብልጭ ብሎ ይታየናል፡፡ ይህ እውነታ ብልጭ እንዲልልን “ከሰው መርጦ” የሚለውን ሐረግ ወስደን ማየቱ ጠቃሚ ነው፡፡ በዚያ ዘመን “ሰው የሚባለው ‘ሰው’” ማን ነው? የሚለውን ጥያቄ ስናነሳ፤ ሰው ማለትማ የተማረ፣ የተመራመረ ለማለት ሳይሆን “መደባዊ ማንነት ያለው ሰው” ለማለት መሆኑን እንረዳለን፡፡ ስለዚህ በዚያ ዘመን ስልጣን ይገኝ የነበረው “የእከሌ ልጅ/ቤተሰብ” ተብሎ ደምና አጥንቱ ተቆጥሮ፣ ለስርዓቱና ለአልጋው ያለው ታማኝነትና ቅርበት ታይቶ የሚመረጥበት ሁኔታ እንደነበር እንገነዘባለን፡፡

ይሄ የምኒልክ ዘመን የተሿሚ መምረጫ መስፈርት ወደ አፄ ኃ/ስላሴም ዘመን ተሸጋግሯል ብየ አስባለሁ፡፡ በአፄ ኃ/ስላሴ ዘመን “የእከሌ ልጅ/ቤተሰብ” ተብሎ ደምና አጥንቱ ተቆጥሮ፣ ለስርዓቱና ለአልጋው ካለው ታማኝነት በተጨማሪ የትምህርት ዝግጅትና ብቃት በመስፈርትነት የሚካተትበት ሁኔታ እንደነበርም ማስተዋል ይቻላል፡፡ በዘመነ ደርግ ዘርና አጥንት ቆጠራው ችላ ቢባልም መደባዊ ማንነትና ታማኝነት ዋነኛ መስፈርቶች ሆነው መቀጠላቸው ታይቷል፡፡

ወደ ኢህአዴግ ስንሸጋገር መስፈርቶቹ በርካታ እንደነበሩ ለመገንዘብ ይቻላል፡፡ ሌሎቹን መስፈርቶች ለጊዜው እንለፋቸውና በኢህአዴግ ዘመን ከእውቀትም፣ ከልምድም በላይ የሹመት ዋነኛው መስፈርት የድርጅት አባል መሆን ነበር፡፡ አንድ ሰው የፈለገውን ያህል ሊቅ ቢሆን የኢህአዴግ አባል ካልሆነ አይሾምም፡፡ የድርጅት አባል ከሆነ ዘበኛም ቢሆን ሚንስትር ተደርጎ ሊሾም እንደሚችል የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር በአደባባይ ነግረውናል፡፡ የኢህአዴግ ሲቪል ሰርቪስ ምስቅልቅሉ የወጣው በዚህ መስፈርት ምክንያት እንደነበር መገንዘብ ሊቅነትን የሚጠይቅ ሆኖ አይታየኝም፡፡

በዚህ ከንቱ መስፈርት ምክንያት በርካታ ሀገራቸውን መጥቀም የሚችሉ እውቀትም፣ ልምድም፣ ግንዛቤም ያላቸው ዜጎች እድሉን ተነፍገዋል፡፡ በዚህ ከንቱ መስፈርት ምክንያት እውቀትም፣ ልምድም፣ ግንዛቤም የሌላቸው የድርጅት አባላት ስልጣን ጨብጠው ነገር ግን ወንበር ከማሞቅ የዘለለ ፋይዳ ያለው ስራ ሳይሰሩ ከወንበራቸው ላይ ተሽቀንጥረው ወርደዋል፡፡ የሚያሳዝነው አንዳንዶቹ በተመደቡበት የሚንስትርነት ሹመት ፋይዳ ያለው ስራ አለመስራታቸው በግምገማ ጭምር ቢረጋገጥም ተጨማሪ ገንዘን እንዲያገኙ የሦስትና የአራት ድርጅቶች የቦርድ ሰብሳቢ ወይም አባል የሚደረጉበት አጋጣሚም ነበር፡፡

Back to Front Page

ወደ ዘመነ ዶ/ር ዓብይ እንለፍና ባለፈው አንድ ዓመት የሆነውን ለማየት እንሞክር፡፡ ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ ከቀደምት የኢህአዴግ ጠቅላይ ሚንስትሮች ለየት ያሉ የሚያስመሰግኗቸውን እርምጃዎች ወስደዋል፡፡ በዚህም እርምጃቸው አንዳንድ ዜጎች ባላቸው እውቀት፣ ልምድና ግንዛቤ ሀገራቸውን የማገልገል እድል አግኝተዋል፡፡ አንዳንዶቹ ጠቃሚና ውጤታማ ስራዎችን ለመስራት ጥረት ማድረግ ጀምረዋል፡፡

ይሁን እንጂ አሁንም ጉድለቶች ይስተዋላሉ፡፡ በጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዘመን የኢህአዴግ አባል ያልሆኑ አንድ ሚንስትር እንደነበሩ እናስታውሳለን፡፡ ይህ አሰራር ተጠናክሮ መቀጠል ሲገባው በጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር ዓብይ ዘመን የድርጅት አባል ያልሆነ አንድም ሚንስትር አለመኖሩ እጅግ የሚያሳዝን ነው፡፡ አሳዛኙ ነገር ይህ ብቻ አይደለም፡፡ በጠቅላይ ሚንስትር መለስ እና በአቶ ኃ/ማሪያም ዘመን የተለያዩ ድርጅቶች የቦርድ አባል በመሆን “ሀትሪክ የሰሩ” (ከሦስት ድርጅት በላይ የቦርድ አባል የሆኑ) ባለስልጣናት ነበሩ፡፡ አሁን በዘመነ ዶ/ር ዓብይ ደግሞ (ሀገሪቱ ሰው ያጣች ይመስል) ለተለያዩ ሀገራዊ ኮሚቴዎች አባል በመሆን “ሀትሪክ የሰሩ” ግለሰቦችን እያየንና እየሰማን ነው፡፡ የሚገርመው ነገር አንዳንዶቹ ግለሰቦች “ሀትሪክ” መስራታቸው ብቻ ሳይሆን ለተሰየሙበት ሀገራዊ ኮሚቴ አባል ለመሆን የሚያስችል በቂ የትምህርት ዝግጅትም ልምድም የሌላቸው መሆኑ ጭምር ነው፡፡

በመሰረቱ የተለያዩ ማንነቶችን ግምት ውስጥ ያስገባ ስብጥር ለመፍጠር የሚያደርጉት ጥረት ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይን የሚያስመሰግናቸው ነው፡፡ ይሁን እንጂ ቀምመው ካስቀመጧት “ቅርጫት ውስጥ” ያሉ ሰዎችን ብቻ ሁልጊዜ እያወጡ መጠቀማቸው በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ያሉ ጠቃሚ ሥራ ሊሰሩ የሚችሉ ዜጎችን እድል የሚያሳጣ መሆኑን ልብ ሊሉት ይገባል፡፡

ከፍ ሲል እንደገለጽኩት ቀደም ባሉት ዓመታት ብዙዎቹ ሚንስትሮች በሁለትና ሦስት ተቋማት የቦርድ አመራር አባል ሆነው በመስራታቸው በጊዜ ማጣት እዚያም እዚህም ሲንደፋደፉ የአንዱንም ተቋም ስራ በቂ ጊዜ ወስደው፣ ጥርት አድርገው መስራት አለመቻላቸው ይስተዋል ነበር፡፡ ከዚያ ድክመት ትምህርት ባለመወሰዱ ዛሬ በሁለትና በሦስት ሀገራዊ ኮሚቴዎች ውስጥ እንዲሰሩ በዶ/ር ዓብይ የተመደቡ ግለሰቦችም ተመሳሳይ ሁኔታ እንደሚገጥማቸው ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡

   ጸሐፊውን በEmail: ahayder2000@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

Back to Front Page