Back to Front Page

ውህደት፥ ቅልጠት (ክስመት)፥ እብጠት ፥ እብደት በመጨረሸም ውድመት ገና ያልሻረ የታሪክ ጠባሳ

ውህደት፥ ቅልጠት (ክስመት)፥ እብጠት ፥ እብደት በመጨረሸም ውድመት ገና ያልሻረ የታሪክ ጠባሳ

ውህደት፥ ቅልጠት፥ እብጠት: የሚሉት ኣስተሳሰቦች በ1970ዎቹ ዓመታት የኢትዮጲያ የፖልትካ መድረክ የወረሩ ምንጫቸው በውል የማይታወቅ ከኣውሮፓ ዓለም የተሸመቱ የወፍ-ዘራሽ ተኦሪዎች (ነባቢ-አይምሮዎች) ናቸው ለማለት ይቻላል::


በኢትዮጵያ አዳዲስ የፖልትካ ድርጅቶችን መፍጠርና የተሻለ ጉልበት ገንብቶ ብሎም በእሽቅድምድሙ ጥሎ ለማለፍ ሲባል ድርጅት መጠፍጠፍ ባህል በሆነበት ዘመን: በእነዚህ ተኦሪዎች ሳቢያ በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ይህ ነው የማይባል ውድመትና ጥፋት ማስከተላቸው የማይካድ የታሪክ ሀቅ ነው::ይህንን እውነታ ከታሪክ መዘክር ያነበብነው ብቻ ሳይሆን የህይወትና የዓይን ምስክር የሆንበት የታሪክ ክስታት ስለሆነ ፈጽሞ መካድ አይቻልም:: የዛ ዘመን ውህደት፥ ቅልጠት፥ እብጠት ፥ እብደት በመጨረሸም ውድመት እንዳይደገም: በወቅቱ እንደኣሸን የፈሉ ብልጭ ድርግም ያሉ ደርጅቶችን በዘመን በዘመናቸው ከፋፍለን ከማየታችን በፊት የአስተሳሰቦቹን ምንነትና ምንጭ አንድ በአንድ እንቃኛለን::

Videos From Around The World


ውህደት የሚለው ቃል (merger) ከሚለው ከእግሊዘኛ ቃል ወደ አማሪኛና አፋን ኦሮሞ (afaan Oromo) የተተረጎመ ሲሆን ሁለት ወይም ከሁለት የበለጡ ጥቃቅን ፋብሪካዎችን በማወሃድ ተወዳዳሪውን ፈብሪካ ውጠው (ልክ ትልቁ ዓሣ ትንሹን ዓሣ እንደሚውጥ ማለት ነው) በኣሸናፍነት ለመውጣት በሚደረግ እሽቅድምድም የሚያገለግል መሳሪያ (mechanism) ነው:: ይሀው ቃል በኣፋን ኦሮሞ በቁ-በቅሱ (baquu fi baqsuu) ተብሎ ተተረጎመ::ኦሮሞ በባህሉም ሆነ በገዳው ስርዓቱ ብረትን ያቃልጣል እንጂ ድርጅትን አያቀልጥም፥ ይህን ነጥብ በኋላ እመለስበታለሁ:: የተውሶ ራእይ ወረርሽኝ ይሏችኋል ይህ ነው:: መቅለጥ ቅልጠት የሚለውም ቃል (wither away)ከሚለው የእንግሊዘኛ ቃል የተወሰደ ሲሆን የውደት ሂደት ውጤት ነው ፥ ይህ ማለት ጥቃቅን ፋብሪካዎች ከተወሃዱ በኋላ ይቀልጣሉ (ይጠፋሉ) ማለት ነው::በነገራችን ላይ በታሪክ እንደ ፈረንሳይ ያሉ የኢምፓየር ገምቢ ሀይሎች ህዝቦችን በአንድ ማሰሮ አቅልጠው (ጨፍልቀው) (melting-pot) በ(assimilation) አንድ ትልቅ የጭቆና ሀገር በሀይል ሲገነቡ ታይተዋል::ይህንን ነጥብ በኋላ ለብቻው እመለስበታለሁ። እብጠት የሚለው ቃል (fission-expansion)ከሚለው የእንግሊዝኛ ቃል የተወሰደ ሲሆን አንድ ፋብሪካ ኣድጎ (ኣብጦ)ሲፈነዳ ወይም ወደ ለሎች ቅርንጫፍ ሲከፋፈል የሚያገለግል ዘዴ ነው::

ዘመነ ኢዲዩና ዘመነ ኢሕአፓ
የኢዲዩና የኢሕአፓ ፖልትካ በገነንበት ዘመን ጥቃቅን ድርጅቶችን አዋህዶና ኣቅልጦ አንድ ኣሃዳዊ ፖርቲ (unitary party) የመፍጠር አባዜና እብደት ልበለው መሳ ለመሳ የገነነበት ዘመን ነበር:; ከበስተጀርባው የነበረው ድብቅ ዓላማም አሃዳዊውን ፓርቲ ከፈጠሩ በኋላም ሁሉንም የኢትዮጵያ ዘጎች ጨፍልቆ የሚገዛ አሃዳዊ መንግሥት መፍጠር ነበር:: ኢዲዩና የኢሕአፓ: እንደዓለሙት አዳሃዊ ፓርቲ በውህደት ፈጥረው በኋላም አሃዳዊ መንግስት ጠፍጥፈው የኢትዮጲያን ህዝቦች ጨፍልቀው ለመግዛት የነበራቸው እልም እንደ እምቧይ ካብ ተናደ:: ተዋህደው ኣንድ አሃዳዊ ፓርቲና መንግስት ፈጥረው በስልጣን ማማ ላይ በጋራ መውጣት ይቅርና አጭር የጫጉላ ዘመናቸው ኣልፎ በተቀረው ዘመናቸው እንደድመትና እይጥ ሲባሉ በመጨረሻ ላይ ደርግ ደርሶባቸው ሁለቱንም በላቸው:: ኢሕአፓ ከትግራዩ ግንባር ጋር ተቀላቅሎ አሃዳዊ ግንባርና መንግስት ለመፍጠር ወደ ኣሲምባ ተራራ ያደረገው ጉዞም ህልም ሆኖ ቀረ። ኢሕአፓ እንደኣለመው የትግራይ ሃርነት ግንባርም: ምንጣፍ ዘርግቶ አበባ ነስንሶ ሳይሆን ክላሹን ወልውሎ ጠመንጃውን ኣጉርሶ ነው የጠበቀው:: በመጨረሻም በትግራይ የጦር ሜዳ ለይ በሁለቱ ድርጅቶች መካከል በተደረገው ፍልሚያ የትግራይ ሕዝባዊ ሀርነት ግምባር የኢህአፓን አፍርሶ አባላቶችን ግማሾቹን ሲያጠፋቻው ሌሎቹን ማርኮ ኢህድን የሚባል ተቀጵላ ድርጅት እንድፈጠረ የማይካድ የታሪክ ሀቅ ነው:: በኦሮሞ ህዝብ ስም የተቋቋመውም የበስተኋለኛው የኦህዴድ ድርጅትም ከዝሁ ደርጅት አብረክ እንደተገኘ የሚታወስ ነው::

የመኤሶን ክፍለ ዘመን
በታዋቂው ምሁር ህይሌ ፊዳ የተመሰረተው መኤሶን በ(1980ዎቹ) በኢትዮጵያ የፖልትካ መድረክ ላይ አውራ ተዋናይ (political protagonist) እንደነበር የታወቀ ነው:: የደርግ መንግስት እንደእንሰሳ በአራት እግሮቹ በሚዳዳበትዘመን ደርግን የፖልቲካ ሀሁና አቡጊዳ እርሳስ አስጨብጦ ያስተማረው መኤሶንና ሀይሌ ፊዳ መሆናቸው ታሪክ እይረሳውም:: የመኤሶንና የደርግ የፖልትካ ጋብቻ እንደልማዱ የጨጉላውን ጊዜ ጨርሶ ደርግ በሁለት እግሮቹ መሄድ ሲጃምር መኤሶን «አበጠ» ብሎም «ፈረጠጠ» ተባለና ደርጉ ድርጅቱን የማጥፋት ጦርነት አወጀ፥ ሀይሌ ፊዳና ከፍተኛ የአመራር አባላት ታሰሩ፥ የተቃሩት ተረሻኑ። እስከዛሬ ድረስ መተኪያ ያልተገኘለት የፖልትካ ሊቅ (ጠቢብ) ሀይሌ ፊዳ በግርፋት ጠፍሮቹ ከወላለቁ በኋላ መገደሉን በእስር ቤት በነበርኩበት ጊዜ ሰምቻለሁ::

የአብዮታዊ ሰደድና የወዝሊግ ጋብቻና ክፍለ፡ዘመን
የደርጉ መንግስት መኤሶንን በፈርጠጭነት ወንጀል አሳቦ ካጠፋውና ኢጭአት የሚባለውን ድርጅት በአኮብካቢነት ከሶ ካባረረ በኋላ የወዝሊግ ከሚባለው ድርጅት ጋር ጊዜያዊ የታክትክ ጋብቻ ፈጠረ።በማከታተልም ሁለቱ ድርጅቶች «በኮሚንስቶች ውህደት የወዛደሩን ፓርቲ እንመሰሪታለን» ኣሉና የጋራ ማእከላዊ ኮሚቴ አቋቋሙ። ውሎም ሳያድር «ወዝሊግ አብዮታዊ ሰደድ ውስጥ ወርጎ ገባ» ተባለና ጋብቻው (ውህደቱ) ፈረሰ:: በመጨረሻም አብዮታዊ ሰደድና የወዝሊግ አንዱ ሌላውን ቀርጥፈው ተበላሉ።
የኢማሌድህና የህብረት ክፍለ-ዘመን

«በማርክሥስት ሌኔንስት ህብረት የኤትዮጵያን የሰርቶኣደር ፓርቲ እንመሰርታለን» ብለው እነሆ ኣምስት ድርጅቶች በ1980ዎቹ ህብረት ፈጠሩ፤ ከህብረቱም በኋላ እንደህልማቸው ቀልጠው ሊወሃዱ ማለት ነበር። ነገር ግን ምንም ዓይነት እፍረት የማይሳማው አቡዬ ደርጉ ሁሉንም ድርጅቶች ተራ በተራ በልቶ ቀበራቸው፥ በድርጅቶቹ የቀብር ሥነሥርዓት ማብቂያ ላይ በኮሚኒስቶች ውህደት ኢሳፓኮን መሰረትኩ ኣለና አቡዬ ደርጉ በሰርቶኣደሮች ፓርቲ ስም የፋሽስት ወታደራዊ አምባገነን ፓርቲ መስርቶ ኣረፈ።ኣምስቱም ድርጅቶች የውህደት የቅልጠት የእብጠት ጭቃ ሲያቦኩ ቆይተው በመጨረሻ ላይ ኣንዱ ሌላውን ተራ በተራ የእቀበረና ኣንዱ በሌላውን መቃብር ላይ ቁጭ ብሎ ተስካር እየበላ የማታ ማታ ሁሉም ኣበጡ፥ ሁሉም ፈነዱ: ሁሉም ቀለጡ፥ ሁሉም አበዱ ሁሉም ጠፉ።

የኦዲፍና (ODF) የኦዲፓ (ODP) የውህደትና የቅልጠት እንቆቅልሽ (ያልቀዘቀዘ ትኩስ ተመክሮ)

የኦሮሞና የኢትዮጵያ ጭቁን ህዝቦች የዘመናት ትግል ምስጋና ይግባውና በ2016 የኢትዮጵያ የፖልትካ ካባቢ አየር በውጥ ማእበል ተናዋጠ:: አፋኙን ሥርኣት ለማስወገድና በእኩልነት፥ በነፃትና በእውነተኛ ዴሞክራሲ ላይ የተመሰረተች ሕብረቤሄራዊ ፌዴራላዊ ሀገር: ለመገንባት ሲሉ በሽህ የሚቆጠሩ ቄሮዎችና ቀሬዎች መሰዋታቸው የቅርብ ትውስታ ነው::


እኔና የትግል ጓዶቼም የኦርሞ ህዝብ የነፃነት ትግል ከደረሰበት ደረጃ አንስተን ወደ ከፍተኛ ምዕራፍ ለመሸጋገር ኣልመን የዛሬ ስድስት ኣመት ኦዲፍን መሰረትን:: እኔም ከመስራቾቹ አንዱ ከመሆኔም በላይ የዛሬን አያደርገውና የስራ አስፈጳሚ ኮሚቴ አባል ነበርኩ።በስድስቱ የትግል ዘመናት የኦሮሞ ህዝብ ትግል ከገባበት የስትራታጂና የታክቲክ አጣብቅኝ አውጥተን ወደፊት ለማስወንጨፍ የሰላማዊ የፖልቲካ ሥልት ቀይሰን ሌት ተቀን (ዳከርን) ታጋልን:: በኢሕአዴግና በኦፕዲኦ ውስጥ የታፈነው የለውጥ ሀይል ኣገግሞ እንዲወጣ ያልፈነቀልነው ድንጋይ ያልበጠስነው ቅጠል አልነበረም:: የህወሃት አምባ ገነን መንግስት እንደተዳከመና የነለማ መገርሳ ቡድን በትግሉ መድረክ ላይ ብቅ እንዳለ የመጀመሪያውን የድጋፍ ድምፅ ያሰማው ኦዲፍ መሆኑ በዝሕ አጭር ጊዜ የሚረሳ ኣይደለም። በማከታተልም አራት ከፍተኛ የአመራር አባላት የሚገኙበት ልኡካን ወደ ሀገር ቤት ሰደድን:: አመኔታችንን አሳልፈን የሰጠናቸውና የሰደድናቸውሉ ሉኡካን ከኦዲፓ ከፍተኛ አመራር ጋር በአካል ተገናኝተው መከሩ:: ዉሎ ሳያድር የኦዲፍና የኦዴፓ መኣከላዊ ኮሚቴ ተሰብስቦ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተዋህዶና ቀልጦ አንድ ትልቅ ድርጅት ለመፍጠር ወሰነ፤ በእለቱም ፈንጠዚያ በፈንጠዚያ ሆነ።ግና እስከ ዛሬ ድረስ ዉህደቱም ቅልጠቱም ዓናችንን ኣፍጠን ስንጠብቀው ቀልጦ ቀረ:: ቅልጠቱና ውህደቱ ሽውዶ በመቅረቱ እንደእኔ ያለውን የውህደት፥ የቅልጠት፥ የእብጠት ፥ የእብደት በመጨረሸም የውድመትድራማ የዓይንና የህይወት ምስክር ሆኖ ያለፈውን ጎልማሳ ሸውዶ ማልፍ አይቻልም:: ኦዲፍ ወደ ሀገር ቤት የላካቸው መልእክተኞች በዚያው ቀልጠው መቅረታቸውና ኦዴፓም በጣት የምቆጠሩትን ግለሰቦች በመንጠቆ ቀልቦ የወሰደበትና ሰፊውን የድርጅቱን ኣመራርና አባላት በአዉላላ ሜዳ ላይ በትኖ የተወበት ሁኔታ ፊቺ ካልተገኘላቸው የዘመኑ የኦሮሞና የኢትዮጵያ የፖልትካ እንቆቅልሾች አንዱ ነው::

ማጠቃለያ:
ጎበዝ ፥ የኢትዮጵያ ፖልትካና ታሪክ መራራ ሀቆች እንደምያረጋግጡት በውህደት፥ በቅልጠት፥ በእብጠትና በእብደት ሀገር ዘቀጠ እንጂ ኣልተገነባም:: በውህድትና በቅልጠት አሃዳዊ ፓርቲ መፍጠር «ያስወግዳል» የሚባለውን «የዘረኝነት ፖሊትካ-the so-called ethnic politics» የበለጠውኑ ያባብሳል እንጂ ሲፈውስ አላየንም:: «ያለዝባል» የተባለውን «የጽንፈኝነት ፖልትካ» የበለጠውኑ ሲያካረውና ሲያጦዘው ታዘብን እንጂ ሲያለሳልሰው አላየንም:: የውህደትና የቅልጠት፥ ፖሊትካ ያለውን አንድነት ሲያፈርስና ሲያላላ አያን እንጂ ደምሮ ሲያዋህድ ኣላየንም።ህብረበሄራዊውን የፌዴራል ሥርዓት ሲያዳክም እንጂ ሲያጠናክር አልታየም:: በውህድትና በቅልጠት አሃዳዊ ፓርቲ መፍጠር: የኦሮሞና የኢትዮጵያ ህዝቦች ለዘመናት የታገሉለት መሰረታዊ ጥያቄዎች የሚያድበሰብስ እንጂ በትክክል የሚመልስ አይደለም። የኦሮሞንም ሆነ የኢትዮጵያ ሊሂቃን የበለጠውኑ የሚከፋፍል እንጂ የሚያቀራርብ እይሆንም።የተጀመረውንም ዴሞክራሲያዊ ሽግግር የሚያወሳስብና የሚያደናቅፍ እንጂ የሚያፋጥንና የሚያቃልል ሆኖ አይታሰብም::


ጎበዝ: እውነቱን ተነጋግሮ የመሽበት ማደር ወይም መጠላት ይሻላል:: የኢትዮጵያ ሊሂቃን በውህደትና በቅልጠት ኣንድ ወጥ አሃዳዊ አገራዊ ፓርቲ የመፍጠር ኣዙሪት (የድብብቆሽ)ጨወታ ኣስኳሉ የስልጣን ጥያቄና የወንበር ሽሚያ ነው።ሌላው በፖልትካ ስልጣን መሳሪያነት መንግስትን በግል ይዞ ሀብትን ማግበስበስ ነው።መተሳሰብና ሰጥቶ መቀበል ካለ የኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሀገረ መንግስት ለሁልም ይበቃል።ተሳስቦ ሀገሪቷ ያፈራችውን መጋራት ካለ የኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሀብት ለሁሉም ይበቃል። ከሁሉም የሚገርመው የትናንትናው ኢህአፓዎች የዛሬዎቹ ግንቦት ሰባቶችና አዜማዎች በውህደትና በቅልጠት አሃዳዊ አገራዊ ፓርቲ የመጠፍጠፍ አባዜ ሲያመነዥኩ መታየታቸው በቀይ ሽብር ዘመን የቀበሩዋቸውን ሰማዕታት የትግል ጓዶቻቸውን የዘነጉ ይመስላሉ:: በእኔ እይታ በአሁኑ ጊዜ ኦሮሚያም ሆነ ኢትዮጵያን የሚያስፈልጋት በዉህደትና በቅልጠት አንድ አሃዳዊ ኢትዮጵያዊ ድርጅት ብቻ መፍጠር ሳይሆን ዴሞክራሲያዊ የመድብለ-ፓርቲ ሥርዓት(multi-party system) ኣስፍኖ አሳታፊ፥ አቃፊና አወዳዳሪ የፖልቲካ አዉድማ በሰጥቶ መቀበልና ውይይት ዴሞክራሲያዊ ሽግግር (Democratic transition through dialogue and compromise) ማድረግ ነው።በጉጉት የሚጠበቀው መጪው የባለ-ብዙ ፓርቲ ምርጫ (multi-party election) በስኬታማነት እንዲጠናቀቅ ቀድመው መሰራት የሚገባቸው ሥራዎች ወዝፎ ማስቀመጥ ሳይሆን ፈጥኖ ማጠናቀቅ እጅግ አስፈላጊ ነው:: ምርጫው ከመድረሱ በፊትና ከተጠናቀቀ በኋላም ሃገራዊ እርቅና ሰላም ማውረድ ለነገ የሚባሉ ሥራዎች አይደሉም።ህገመንግስቱን በሁሉም ተሳትፎ ኣደብሮ የህብረቤሄራዊውን የፌዴራል ሥርዓት ዴሞክራሲያዊ የማድረግ ሥራ በቀላሉ የሚታለፍ አይደለም:: ከምርጫው ማግስት አሸናፊው ፓርቲ የሀገሪቷን ሰላምና የሕግ የበላይነት አረጋግጦ የድህነት ችግር ለመቅረፍ ፊቱን ወደ ኢኮኖሚ እድገት ማዞር ይጠበቅበታል:: የተስፋፋውን የሙሰኝነትና የጉቦና ባህል ማረም እንዲሁም የሰፈነውን ብልሹ አስተዳደር በመልካም አስተዳደር መተካት ኣፍጠው የሚጠብቁ ሥራዎች ናቸው። እነዚህ ኣንገብጋቢ ስራዎችና አጃንዳዎች እያሉ ድርጅቶችን ኣቅልጦ የማወሃድ ጊዜ በሚሰጥ ሥራ ላይ መጠመድ አስፈላጊ አይመስለኝ። ስለዚህ ውህደትና በቅልጠት አሃዳዊ አገራዊ ፓርቲ የመጠፍጠፍ አባዜ ላይደገም ያዬ ይመስክር የቀበረ ያርዳ። የውህደት፥ የቅልጠት፥ የእብጠት ፥ የእብደት በመጨረሸም የውድመት የጭለማ የታሪክ ጉዞ ምዕራፍ ዘግተን በእኩልነት፥ በነፃነት፥ በእውነተኛ አንድነት ለሁላችንም የምትሆን ሕብረቤሄራዊ ፌዴራላዊ ደሞክራሲያዊት ኢዮጵያን በጋራ እንገንባ::

አማን ከድር ቃምሰሬ
ትሮምሶ፣ ኖርዌይ
ጥቅምት 21/10/2019 ዓም

ጉለሌ ፖስት

 

 

Back to Front Page