Back to Front Page

መሬት ወረራም ቤት ማፍረስም ወንጀል ነው

(ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)

6-3-19

ለዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነኝ አዲስ አድማስ ጋዜጣ ቅጽ 20 ቁጥር 1010 በግንቦት 17 ቀን 2011 ዓ.ል እትም “በአዲስ አበባ በህገ ወጥ መንገድ የተገነቡ ቤቶች ሊፈርሱ ነው” በሚል ርዕስ ያሰፈረቺው ዜና ነው፡፡ ጋዜጣዋ ዜናውን የዘገበቺው “ከተማዋን አስወርሬ ማለፍ አልፈልግም” ያሉትን የከተማዋን ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማን ዋቢ በማድረግ ነው፡፡

Videos From Around The World

ያው እንግዲህ መርዶ ነጋሪነታችን ቀጥሏል፡፡ ዛሬም ስለ መሬት ወረራ፣ ዛሬም ስለ ህገወጥ የቤት ግንባታ፣ ዛሬም ስለ ቤት ማፍረስ፣ ዛሬም ስለ ህዝብ መፈናቀል እየጻፍን ልንተክዝ ነው፡፡ ለምን ብትሉ መሬት ወረራውም፣ ህገወጥ ግንባታውም፣ ቤት ማፍረስና ህዝብ መፈናቀሉም ቀጥሏልና ነው፡፡ ይህ ሁኔታ መቼና እንዴት ነው ሊቆም የሚችለው? የሚለው ጥያቄ ተገቢ ምላሽ ሊሰጠው እንደሚገባ አምናለሁ፡፡ መቼ እንደሚቆም አላህ ይወቅ! እንዴት ሊቆም እንደሚችል ግን በጽሁፌ ማጠቃለያ አካባቢ ምክረ ሃሳቤን ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡

ኢትዮጵያ ሀገራችን በታሪኳ እንደዚህ ዘመን ጥላቻ፣ ሽኩቻ፣ አሉባልታ፣ መፈናቀል፣ መሬት ወረራም ሆነ ቤት ማፍረስ ተንሰራፍቶ፣ ህዝቧን አንገላቶ፣ አስከፍቶና አፈንቅሎ፣ አሳዝኖና አስለቅሶ … ያለፈ ክፉ ጊዜ፥ መጥፎ ወቅት ገጥሟት የሚያውቅ አይመስለኝም፡፡ ኢትዮጵያ በታሪኳ ከዘመነ መሳፍንት ቀጥሎ የተልፈሰፈሰ ማዕከላዊ መንግስት ገጥሟት የሚያውቅም አይመስለኝም፡፡

የህዝብን ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅ፣ በየአቅጣጫው የሚለኮሰውን ሁከትና ብጥብጥ ማስቆም፣ ህገ ወጥ መሬት ወረራን መግታት፣… ያልቻለው መንግስታችን “አህያውን ፈርቶ ዳውላውን” እንዲሉ በጠራራ ፀሐይ፣ በይፋ የተወረረ መሬትን ለማስመለስ “ቤት አፈርሳለሁ፣ ዜጎችን እበትናለሁ” የሚል አዋጅ በጠራራ ፀሐይ፣ በይፋ ማስተጋባት ጀምሯል፡፡

አንዳንድ ሰዎች “መጠለያ ኖሮን ሥራ ባይኖረን ችግሩ ዝቅተኛ ነው” ይላሉ፡፡ ለምን? ሲባሉ “ሥራ ባይኖር ለምኖ መብላትም ይቻላል፡፡ መጠለያ ከሌለ ግን ሁሉም ነገር የለም፡፡ መጠለያ የማግኘት መብት የለንም ማለት ደግሞ የመኖር ዋስትና የለንም ማለት ነው” ይላሉ፡፡ ይህ አባባል አከራካሪ ሊሆን እንደሚችል አስባለሁ፡፡ አስተያየት ሰጪዎቹም ያነሱት የመጠለያን ከፍታ ለማሳየት ይመስለኛል፡፡

በርግጥ ቤት የለሽነት፣ የጎዳና ዳር ነዋሪነት የሦስተኛው ዓለም እጣ ፋንታ ብቻ አይደለም፡፡ በቅርብ ዓመታት በአሜሪካ ትምህርት ቤቶች በተደረገ ጥናት 1.3 ሚሊዮን ተማሪዎች ከቤት አልባ ቤተሰብ የመጡ መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡ በአሜሪካ በድንኳን የሚኖሩ ሰዎች ጥቂት የሚባሉ አይደሉም፡፡ በዚህም ምክንያት በአሜሪካ ከሃያ ከተሞች የተውጣጡ ሰዎች “የቤት የለሾች ብሄራዊ ማህበር” የሚባል ተቋም ተመስርቶ እንደነበር ይነገራል፡፡

ከተሞች ልዩ ባህሪ አላቸው፡፡ ከተማ ማለት እድገት፣ ከተማ ማለት ስልጣኔ ማለት ነው፡፡ ሀገራዊ እድገት በተጠናከረ ቁጥር የከተማ ነዋሪው ቁጥር ይጨምራል፡፡ በከተሞች በመንግስት በኩል መከናወን ከሚገባቸው ተግባራት አንዱ ለዜጎች መጠለያ ማዘጋጀት መሆን ይገባዋል፡፡ በዚህ ረገድ ደርግ የቀበሌ ቤቶችን ከ0.25 ሣንቲም ጀምሮ እስከ አንድ መቶ ብር ድረስ እንዲከራዩ በማድረግ ለዘመናት ቤት አልባ ለነበሩ የከተማ ነዋሪ ሸማ ሰሪዎች፣ አንጥረኞች፣ ሸክላ ሰሪዎች፣ ወዛደሮች፣ የመንግስት ሰራተኞች… መጠለያ መስጠቱ ብዙዎችን ያስደሰተ ነበር፡፡

ኢህአዴግ መጣና ደርግ መጠለያ የሰጣቸውን ምንዱባን እያፈናቀለ ቀደም ሲል ወደነበሩበት ድህነትና በረንዳ አዳሪነት መለሳቸው፡፡ ታስቦበት ይሁን ሳይታሰብ ኢህአዴግ የዘመተው በድሃዎች ላይ ነበር፡፡ ኢህአዴግ ለድሃ ትኩረት እሰጣለሁ (pro-poor ነኝ) ቢልም ተግባሩ በተቃራኒው እንደነበር ለሃያ ምናምን ዓመታት የታዬ ሀቅ ነው፡፡

መጠለያን በተመለከተ ሀገራችን ኢትዮጵያ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ፈርማለች፡፡ “መጠለያ” የማግኘት መብት በተ.መ.ድ ዩንቨርሳል ዲክላሬሽንና በሌሎች የህግ ሰነዶች ውስጥ እውቅና የተሰጠውና ጥበቃ የተደረገለት “የሰብአዊ መብት” አካል መሆኑ ይታወቃል፡፡

በእነዚህ ዓለም አቀፍ የህግ ሰነዶች ውስጥ “The Right to Housing is a Human Right” የሚል የህግ ጽንሰ ሃሳብ ሰፍሮ ይገኛል፡፡ ይህ ጽንሰ ሃሳብ ወደ አማርኛ ሲተረጎም “መጠለያ የማግኘት መብት ሰብአዊ መብት ነው” እንደማለት ነው፡፡ ይህንን መብት ለማስከበር እ.ኤ.አ በ1996 በኢስታንቡል በተደረገው ስምምነት ላይ መንግስታት በየሀገሮቻቸው “በቂ መጠለያ የማግኘት መብትን የማበረታታት፣ ጥበቃ የማድረግ እና የማረጋገጥ” ኃላፊነት የሚጠበቅባቸው ግዴታ መሆኑ ተገልጿል፡፡ በተባበሩት መንግስታት የሰፈራ ፕሮግራም ስብሰባ ላይም ይህንን ስምምነት የሚያጸና ውሳኔ ተላልፎ እንደነበር ይታወሳል፡፡

በተ.መ.ድ ትርጉም መሰረት “መጠለያ የማግኘት መብት” ማለት፤ “በግዴታ ከመፈናቀል፣ ከማስፈራራት እና ከወከባ ህጋዊ ጥበቃ የማግኘት፣ የኪራይ ክፍያው የምግብ - የትምህርት - የጤና ወጪዎችን የማይነካና ተመጣጣኝ የሆነ፣ ለመኖሪያ ምቹ የሆነና በቂ ስፋት ያለው፣ ከቅዝቃዜ፣ ከሙቀት፣ ከዝናብ፣ ከንፋስ ወይም ከሌሎች ለጤና ተስማሚ ካልሆኑ አደጋዎች የመጠበቅ፣ ንጹህ የመጠጥ ውሃ - ኤሌክትሪክ - የቆሻሻ ማስወገጃ ያለው፣ ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ የሆነ፣ ለሥራ - ለትምህርት - ለጤና ተቋማት ቅርብ የሆነ፣ ባህላዊና መንፈሳዊ ተግባራትን ለመፈጸም ምቹ የሆነ” ማለት ነው፡፡ አበው “ጽድቁ ቀርቶብኝ በወጉ በኮነነኝ” እንዲሉ ይህንን የተ.መ.ድን ድንጋጌ መመኘት ለኢትዮጵያውያን ቅንጦት ነው፡፡

በተ.መ.ድ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ድንጋጌ መሰረት እያንዳንዱ ሰው መጠለያ የማግኘት መሰረታዊ ሰብአዊ መብት ያለው መሆኑ ብቻ ሳይሆን፤ መንግስት ለዜጎች ምቹ መጠለያ በተመጣጣኝ ዋጋ የማቅረብ ግዴታ እንዳለበት ጭምር ተገልጿል፡፡ በተመድ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ውሳኔ መሰረት “በግዳጅ ማፈናቀል መጠለያ የማግኘት መብትን የማሳጣት የሰብአዊ መብት ጥሰት” መሆኑም ተገልጿል፡፡

እነዚህ ሁሉ ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች ብቻ ሳይሆኑ በኢፌዴሪ ህገ መንግስት መሰረት መንግስት የዜጎችን መብትና ጥቅም የማስጠበቅ እንጂ የማፈናቀልና መጠለያ የማሳጣት እርምጃ የመውሰድ መብት የሌለው መሆኑን ያሳያል፡፡

ይሁን እንጂ፤ በኢትዮጵያ ቤት ማፍረስ የሚገርም ነገር አይደለም፡፡ የህይወታችን አካል ከሆነ 27 ዓመታት ተቆጠሩ፡፡ እናም የሰሞኑ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አዋጅ አላስገረመኝም፡፡ የገረመኝ ነገር ከንቲባው ቤት ማፍረስን እንደ “ተራ ነገር” ቆጥረው፣ እንደ መደበኛ ተግባራቸው አስበው “ከተማዋን አስወርሬ ማለፍ አልፈልግም” ማለታቸው ነው፡፡

እንደኔ እንደኔ ይሄ የከንቲባው አባባል የተወረረ መሬትን ማስመለስ ብቻ ሳይሆን ሁለት ውጤቶችን የሚያረጋግጥ ይመስለኛል፡፡ አንደኛ፤ ባለስልጣኑ የተሰጣቸውን ከተማን የማስተዳደር ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ባለመወጣታቸው መሬት መወረሩንና ህገወጥ ግንባታ መካሄዱን ያረጋግጣል፡፡ ሁለተኛ፤ ዜጎችን መጠለያ ማሳጣትና ማፈናቀል ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችን የሚጻረር የሰብአዊ መብት ጥሰት መፈጸሙን ያረጋግጣል፡፡

ዛሬ በየመገናኛ ብዙሃኑ “በዜጎች ላይ ሰብአዊ መብት በመጣስ” ክስ የተመሰረተባቸው ግለሰቦች እኮ ትናንት እንደ ኢ/ር ታከለ ኡማ ባለስልጣናት ነበሩ፡፡ ኢ/ር ታከለ ይህንን ልብ ሊሉት ይገባ ነበር፡፡ በሰብአዊ መብት ጉዳይ ያጠፉት ጥፋት የህወሓት ቁንጮ መሪዎችን ከተጠያቂነት እንዳላዳናቸው ሁሉ ኦዴፓም የአሁኖቹን ሰብአዊ መብት ገፋፊዎች ነገ ከተጠያቂነት የሚያድኗቸው አይመስለኝም፡፡

መሬት ወረራ እንዴት ይቁም? - ምክረ ሃሳብ

የህግ ባለሙያዎች እንደሚሉት ከሆነ በሀገራችን ህግ መሰረት መሬት ወረራም ሆነ ህገወጥ የቤት ግንባታ ወንጀል ነው፡፡ በሌላ በኩል፤ በየትኛውም መንገድ የተገነባን ቤት ማፍረስ ወንጀል መሆኑን በመግለጽ “ህገወጥ ተግባር በህገወጥ እርምጃ መፍትሄ ሊሰጠው አይገባም” ይላሉ የህግ ባለሙያዎቹ፡፡ ቤት ከማፍረሱ ጋር ተያይዞ ሰዎችን በማፈናቀል መጠለያ መሳጣት የሰብአዊ መብት ጥሰት ነው፡፡ እና ምን ይደረግ?

እኔ በለገጣፎ ከተማ ነው የምኖረው፡፡ የዛሬ አምስት ዓመት ከለገጣፎ ወደ አዲስ አበባ አቅጣጫ ስመለከት ዓይኔ የሚያርፈው ካራሎ ተራራ ላይ ችምችም ብሎ የበቀለው የባህር ዛፍ ላይ ነበር፡፡ አሁን አሁን ወደዚያ አቅጣጫ ሳማትር ዓይኔ የሚያርፈው ጫካው ውስጥ ችምችም ብለው የተሰሩ ህገወጥ ቤቶች ላይ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ያንን አካባቢ ባየሁ ቁጥር ሁለት ስለት ያለው የሀዘን ሰይፍ ይገዘግዘኛል፡፡ በአንድ በኩል ዛፎች መጨፍጨፋቸው ያሳዝነኛል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ማረፊያ ያጡ ወገኖቼ “የመጣው ይምጣ” በሚል መንፈስ የመንግስት ደን መንጥረው፣ ህገወጥ ቤት ሰርተው፣ ምንም ዓይነት መሰረተ ልማት በሌለበት አካባቢ ጎስቋላ ኑሮ መኖራቸው ያሳዝነኛል፡፡

እንደኔ እንደኔ እነዚህ ዜጎች ባይቸግራቸው ኖሮ በእንደዚያ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ የመኖር ውሳኔ የሚወስኑ አይመስለኝም፡፡ እናም መንግስት መጠለያን ለዜጎቹ ማቅረብ ሰብአዊ መብትን የማክበር ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ በተለይም አነስተኛ ገቢ ላላቸው ዜጎች ኮንዶሚኒየም ብቻ ሳይሆን በአነስተኛ ገንዘብ የሚከራዩ፣ እስከ መቶ ወለል ያላቸው ረዣዥም ፎቆችን (high rise low cost houses) በብዛት መገንባት ይገባዋል፡፡

ሰሞኑን የአዲስ አበባ አስተዳደር እንዳለው መሬት በመሸጥ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት የሚሯሯጡ ደላላዎችና “መሬት ወራሪ” ባለሀብቶች መኖራቸውም ይነገራል፡፡ እነዚህን አልጠግብ ባዮች ያለ ምህረት ለፍርድ በማቅረብ አሳማሚ ቅጣት እንዲቀጡ ማድረግና የፍርድ ሂደቱንም በየዕለቱ በመገናኛ ብዙሃን በመዘገብ ሌሎች እንዲማሩበት ማድረግ ነው መፍትሄው ፡፡

ሌላው መከናወን የሚገባው መሰረታዊ ጉዳይ፤ ህገወጥ የመሬት ወረራውን እና ህገወጥ ግንባታውን በጥብቅ መከላከል ነው፡፡ ይህንን የመከላከል ሥራ ለመስራት ደግሞ እያንዳንዱ ዜጋ በየሚኖርበት አካባቢ የሚያየውንና የሚሰማውን ለሚመለከተው የመንግስት አካል የማሳወቅ ግዴታ ማስቀመጥና ይህንንም በቀበሌ መስተዳድሮች በኩል ተግባራዊ ማድረግና መከታተል ተቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባል፡፡ ለዚህም ይረዳ ዘንድ የእለት ሁኔታ መመዝገቢያ መዝገብና የመዝገብ ሹም በየአካባቢው በማስቀመጥ እያንዳንዷን ነገር በመመዝገብ ለየት ባሉ ሁኔታዎች ላይ እርምጃ መውሰድ ተገቢ ይሆናል፡፡ ይህንን ተግባር በየሰፈሩ ያሉ ስራ አጥ ወጣቶች ተደራጅተው እንዲሰሩ ማድረግ ይቻላል የሚል እምነት አለኝ፡፡

   ጸሐፊውን በEmail: ahayder2000@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡


Back to Front Page