Back to Front Page

“ኹሉን አወቆች-ሀገር ያፈርሳሉ!!!”

ኹሉን አወቆች

-ሀገር ያፈርሳሉ!!!”

ፀጋዝአብ ለምለም ተስፋይ

የኢኮኖሚክስ መምህርናጸሓፊ

(ሸክም የበዛበት ትውልድ፡ 2009 እና

የምሥራቃዊት ኮከብ፡ 2010 መጻሕፍት አዘጋጅ)

   አንድ ሀገር በየትኛውም መመዘኛ በአንድ ሞያ አትቆምም፡፡ ሀገር በአንድ ዘርፍ ተመሥርታም ኾነ ታንጻ አታውቅም፡፡ ሀገር እልፍ አላፍ ኹለንተናዊ ሞያዎች በነበሯቸው፣ ባሏቸውና በሚኖሯቸው ዜጎች የተመሰረተችና የምትመሰረት፤ የታነጸችና የምትታነጽ የህዝብ መኖሪያ ናት፡፡

   ኹለንተናዊ ሞያዎቹም (ሚናዎቹም) መሪነት፣ ገዥነት፣ ወታደርነት፣ መምህርነት፣ ገበሬነት፣ አምራችነት፣ ነጋዴነት፣ ፈላስፋነት፣ ጸሓፊነት፣ ደራሲነት፣ አናጢነት፣ ሃኪምነት፣ ተማሪነት፣ ተመሪነት፣ ሰላይነት፣ ጋዜጠኝነት፣ አስተባባሪነት፣ ቀማሚነት፣ ሃይማኖተኛነት፣ የሃይማኖት አባትነት፣ ሊቅነት፣ ገጣሚነት፣ ሹፌርነት፣ ተመራማሪነት፣ ረዳትነት፣ ባርነት፣ ጌትነት፣ አባትነት፣ ልጅነት፣ እናትነት -  - - ወዘተ ተብለው የተከፈሉና ሊከፈሉ የሚችሉ ናቸው፡፡

  አንድ ሰው ከአንድ በላይ ዘርፎች (ሚናዎች) ሊኖሩት፤ በሕይወት ውጣ ውረድ ውስጥ አንዴ አንዱን - ሌላ ጊዜ ደግሞ ሌላውን፤ ከአንዱ ዘርፍ ወደ ሌላው ፈልጎም ይኹን በኹኔታዎች አስገዳጅነት ሊቀይር ይችላል እንጂ በምንም ተአምር ኹሉንም ሊኾን አይችልም፡፡

  ኹሉን አወቅነት ምንድነው? ኹሉን አዋቂዎች እነማን ናቸው? ኹሉን አውቃለሁ - በኹሉ ጉዳይ እጄን ማስገባት አለብኝ ብሎም እኔ ካልኩት ውጪ ሌላ የለም የሚል አስተሳሰብና አመለካከት፣ ስልትና ስትራቴጂ ከፍ ሲልም ተግባር (ድርጊት) ነው፡፡ ኹሉን አዋቂዎች የኹሉ አዋቂነት ባህሪና ጠባያትን በንቃት (Consciously) አልያም ያለንቃት (Unconsciously) የያዙ ግለሰቦችና ቡድኖች ናቸው፡፡

Videos From Around The World

   እንዲህ አይነት ግለሰቦችም ኾኑ ቡድኖች በሀገር ፖለቲካ - ብዙ ይላሉ፤ ስለኢኮኖሚ ቢነሳ ያነሣሉ፤ ስለሃይማኖት ቢነሳ - ለማስተማር ወደኃላ አይሉም፤ መግለጫ ሲሰጥ - ይተነትናሉ፤ ዜናዎችን ያደርሳሉ፤ አዲስ ሙዚቃ ቢወጣ - ቀድመው አድናቂና ዘላፊዎች እነሱ ናቸው፤ መጻሕፍት ቢወጡ - ገምጋሚ ኾነው ብቅ ይላሉ፤ ስለታሪክ ቢነሳ - እንደታሪክ ባለሙያ ይሰየማሉ፤ ፎቶ ቢወጣ - ሕብረተሰቡን መስለው ይቀርባሉ፤ በዓል ቢመጣ - ባለበአል ይኾናሉ፤ ስለፍቅር ቢነሳ አሉ - ስለኳስ ቢነሳ አሉ - ስለሱስ ቢነሳ አሉ - ስለትዳር ቢነሳ አሉ - ስለትምህርት ቢነሳ አሉ - ኸረ እንዲያውም ስለዩኒቨርስቲ ሕይወት ቢነሳ - ምንም እንኳ ዩኒቨርስቲ ገብተው ባያውቁ አሉ - ምንም እንኳ ስለሃይማኖት ግድ የሌላቸው - ሥርዓተ ሃይማኖት ተግባሪ ባይኾኑ ስለሃይማኖት ከተነሣ ከጳጳሱ ቀድመው አቤት የሚሉ እነሱ ናቸው  - - -  የማያገባቸው አልያም አያገባንም የሚሉት ጉዳይ የለም፡፡ በኹሉ ጉዳይ አሉ - አለንም ይላሉ፡፡ ኸረ ይባስ ብሎም መንጋዎቻቸው ‘አሉ’ ብለው ይመሰክራሉ፡፡

  ኹሉን አወቆች በኹሉ ጉዳይ ካልመራን፣ ካልገዛን፣ አስተያየት ካልሰጠን፣ ካልተነተን፣ ካልተደመጥን፣ ካልጻፍን፣ ካልሸጥን፣ ካልታየን - - -  ባዮች ናቸው፡፡ በማናቸውም ጉዳይ ላይ አንደበታቸው ይከፈታል፤ እጃቸው ለመጻፍ አይቦዝንም - በኹሉ ቦታ ካልተገኘን ይላሉ ያለነሱ ሌላ ያለ ስለማይመስላቸው እንኳንስ ለሌላው ለራሳቸው ጊዜ የላቸውም፡፡

   ይህን ዕውነት (Truth) እና እውነታ (Reality) ምንም እንኳ በብዙ ቦታዎች በተለይ በጓደኝነት፣ በጉርብትና፣ በሥራ ባልደረብነት፣ በገዥነት - - - ወዘተ መጠኑና አድማሱ የሚለያይ ቢኾንም ይታያል፡፡ በማህበራዊ ሚድያዎች ያለው ግን ለብዙዎች የተጋለጠ በመኾኑ ለአብነት እጅጉን የተመቸ ይኾናል፡፡ በዚህ መድረክ ተጽዕኖ የፈጠሩና ይፈጥራሉ የሚባሉ ግለሰቦችና ቡድኖች አለፍ ሲልም ተቋማቶች የማይገቡበት ጉዳይ ምን አለ? በዚህ ጉዳይ ከኔ እከሌ ይሻላል የሚሉበት ምን አለ? በብዙ ጉዳይስ ካልገባን ሲሉ ወዴት - ወዴት? እነማን ናችሁ - የሚላቸውስ ማን ነው? ድርሻችሁንና ሚናችሁን እወቁ - ያለና የሚልስ ማን ነው?

  ኹሉን አዋቂነት በመንጋዎች ይከበባል፡፡ ሕልውናው መንጋን በማበራከትና ባለማበራከት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ መንጋዎች ኹሉን አዋቂዎችን በኹሉ ጉዳይ የሚያወቁ አድርገው እንዲስሏቸው በንቃት (Consciously) አልያም ያለንቃት (unconsciously) ኹለንተናዊ ሥራ እንደተሰራባቸው አያውቁም፡፡ ለነሱ መምህራን ብቻ ሳይኾኑ መሪዎቻቸው አድርገው ይከተሏቿል፡፡ የኹሉን አወቅነት ኹለንተናዊ ርካሽ ፕሮፕጋንዳ መንጋዎችን ስለመፍጠሩና ስለማበራከቱ የሚነግራቸው ስለሌለና የነገራቸውንም ስለማያደምጡ መንጋዎች የኹሉን አወቅነት ባሪያዎች ኾነው ያገለግላሉ፡፡

  በአንድ ፓርቲ ውስጥ አመራር (ከፍተኛ፣ መካከለኛና ዝቅተኛ)፣ አባል (ሙሉና እጩ)፣ ደጋፊ፣ ተፎካካሪና ተቃዋሚ ይኖር ዘንድ ባህሪያዊ ነው፡፡ በዚህ ኹለንተናዊ እንቅስቃሴና ግንኙነቶች ውስጥ እርስ በራስ በመንፈስ የመዋሃድ፣ ተግባብቶና ተረዳድቶ የመስራት፣ ተጽዕኖ የመፍጠርና ያለመፍጠር፣ ልዩነት የማምጣትና ያለማምጣት ጉዳይ ከጥንካሬና ከድክመት አንጻር የሚታይና የሚተነተን ነው፡፡

  ኾኖም ግን የሚና ጉዳይ እንደድርሻ አንዱ በሌላኛው ላይ ከገባ የፓርቲው ህልውና ጥያቄ ምልክት ውስጥ ይገባል፡፡ ተፎካካሪ ስለሚፎካከረው ፓርቲ የውስጥ ጉዳይ ካልገለጽኩና ካልተነተንኩ አለፍ ሲልም ካላዘዝኩ ካለ፤ ደጋፊ እንደአባልና አመራር ሀሳብ ልስጥ - ልዘዝ - ልደመጥ ካለ፤ እጩ አባል እንደሙሉ አባል ባለመብት ልኹን ካለ፤ ዝቅተኛ አመራር እንደከፍተኛ አመራር ውሳኔ መስጠት /መሰጠት/ አለብኝ /አለበት/ - - -  ካለ እና ፓርቲው በዚህ ኹለንተናዊ ተጽዕኖ ስር ከወደቀ በእውነት ፓርቲው ሞቷል፡፡ ያልተቀበረው ባለድርሻ አካላቱም ፖለቲካሊ ስለሞቱ ነው፡፡ ይህም ብቻ ሳይኾን ባይው በራሱ በቁሙ የሞተ ነው፡፡

  ዛሬ በሀገራችን የምናየው ዕውነት (Truth) እና እውነታ (Reality) ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ ገዥው ፓርቲ ማድረግ ስላለበት ነገር ከፓርቲው አመራሮች በላይ ‘አክቲቪስቶች’፣ ‘ተንታኙ’፣ ‘ጸሐፊው’፣ - - -  ወዘተ ሲዘባርቅ መስማትና ማንበብ የተለመደ ነው፡፡

  ስለአንድ ጉዳይ ሕይወቱን ሙሉ (እጅግ ለረዥም ዓመታት በሞያው ላይ የቆየ ሰው) የሚያውቅ እያለ በትርፍ ጊዜው ስለጉዳዩ የሰማ፣ ያነበበና የጻፈ ሰው ከዛ በላይ ካልተደመጥኩ፣ ካልታየሁና ካልተቀበላችሁኝ ሲል መመልከት - ነውርን ጌጣቸው ያደረጉ ግለሰቦችና ቡድኖች በርካቶች ኾነው በአደባባይ የሚንቀሳቀሱ በስም እየጠሩ ከነግብራቸው እከሌ እከሌ ማለት የሚቻል ቢኾንም በወቅቱ ነባራዊ ኹኔታ አንጻር ማለቱ ካለማለት የተሻለ ይኾናል፡፡

   በዚህ ጉዳይ ‘ኸረ አይመለከተንም!’፣ ‘ኸረ ድርሻችንን እንወቅ!’፤ ‘ኸረ በኹሉ ጉዳይ ይመለከተኛል ማለት  አላዋቂነት ነው!’ ያሉ እንዳላዋቂ፣ እንደፈሪ፣ እንደጅል፣ እንደዘመኑ እንዳልገባቸው ሲቆጠሩ በተግባር በአደባባይ ተመልክተናል፡፡

   ከሚያውቁት በላይ የማያውቁት፤ ካስተዋሉት በላይ የማያስተውሉት፣ ከበሰሉት ይልቅ ጥሬዎች፣ በተግባር ከኖሩበት ይልቅ ያልኖሩበት /ኖረውበት የማያውቁ/፤ ብዙ ኹለንተናዊ ዋጋ ከከፈሉ ይልቅ ኹለንተናዊ ዋጋ በማስከፈል የሚታወቁ በአደባባይ ሲሞገሱ፣ ሲሸለሙና እውቅና ሲቸራቸው - የማይገባቸውን መድረክ ተቆጣጥረው ህዝቡን በኹለንተናዊ መንገድ ሲያደናግሩት ተመልክተናል፡፡ በዚህም ኹለንተናዊ ህዝባዊ መድረኮች በማይገባቸው ግለሰቦች፣ ቡድኖችና ተቋማት ስር ሲገቡ - በማይገባቸው መንገድና በማይገባ አካሄድ ሲጠቀሙበት የደረሰው ኹለንተናዊ ጉዳት በኹለንተናዊ የአኗኗር ዘይቤያችን የሚስተዋል እውነታ (Reality) ነው፡፡

   እንዲህ አይነት የኹሉን አወቅነት ምግባሮች በበርካታ ግለሰቦችና ቡድኖች ላይ የሚታይ ከመኾኑም ባሻገር በገዥዎች ላይም በጉልህ የሚስተዋል ነው፡፡ አንድ ሰው የሀገር ገዥ ስለተባለ ኹሉ ነገር ላይ የሚያውቅ ይመስለዋል፡፡ ከ50 ዓመታት በላይ በሃይማኖት አስተምህሮ የቆዩ አባቶችን የሃይማኖት ሥልጠና ልስጥ ሲል ቅንጣት ታክል እንኳ አያፍርም፡፡ ስለኹሉ ጉዳይ በርግጠኝነት ድምዳሜ ሲሰጥ ለአስተዋዩ ይጨንቃል፡፡ የማያስተውለውን በእጅጉ ያደነባብራል፡፡

   የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስተር አንድ ቀን እንኳ አድርገውት የማያውቁትን የኛዎቹ ግን ‘ካላሠለጠን’፣ ‘ካላስማርን’፣ ‘ካልተነተን’፣ ‘ካልጻፍን’፣ ‘ካልተናገርን’ - - -  ሲሉ "አዲስ ምዕመን ከጳጳስ ይበልጣል" የሚለውን ብሂል በእጅጉ እንድንመረምር ግድ ይለናል፡፡

   በአንድ ሀገር ውስጥ በየትኛውም መንገድ ይኹን ጊዜ ሚናውን መለየት ያልቻለ ህዝብ ሊሠለጥን ከቶ አይችልም፡፡ ስለኹሉ ጉዳይ ይመለከተኛል፡፡ ያገባኛል ብሎ ሚናውን ሳይለይ የሚጓዝ ግለሰብ፣ ቡድን ኾነ ተቋም እንደሽንት ግመል የኋልዮሽ እንጂ ወደፊት ፈጽሞ ሊጓዝ አይችልም፡፡ ባህሪያቱም ኾኑ ጠባያቱ የሕልውናው መሠረት በመኾን ፍሬ አልባ - ጎጂ ያደርጉታል፡፡

  ዛሬ ዛሬ በሀገራችን ኹለንተናዊ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ መምህር ተማሪ - ተማሪ መምህር፤ የሃይማኖት አባት ፖለቲከኛ - ፖለቲከኛ የሃይማኖት አባት፤ መሪ ተመሪ - ተመሪ መሪ፤ አንባቢ ጸሓፊ - ጸሓፊ አንባቢ፤ አዋቂ ታዋቂ - ታዋቂ አዋቂ፤ ባለሙያ ገዥ - ገዥ ባለሙያ፤ ደራሲ ተደራሲ - ተደራሲ ደራሲ፤ ተጫዋች ተመልካች - ተመልካች ተጫዋች፤ ደጋፊ መንጋ - መንጋ ደጋፊ፤ ምሁር አላዋቂ - አላዋቂ ምሁር፤ - - - ወዘተ መዘበራረቆችን፣ መደነባበሮችና በተግባር የኾኑባቸውን ኹለንተናዊ ኹነቶች እናውቃለን፡፡

   ሀገር - ሚናቸውን ያለዩ፣ ሚናቸውን መለየት የማይችሉ ዜጎች ከተበራከቱባት በምንም መንገድ ኹለንተናዊ መሠረታዊ ለውጥ ልታመጣ አትችልም፡፡ ሚናውን መለየት የማይችል ሕብረተሰብ እርስ በራሱ የማይደማመጥ፣ የማይከባበርና የማይተማመን ይኾናል፡፡ በዚህም ያለመደማመጥ፣ ያለመከባበርና ያለመተማመን ዋጋን እንጂ ፈጽሞ ተቃራኒውን አግኝቶ አያውቅም፡፡ ሊያገኝም አይችልም፡፡

   ዕውን እኛ ኢትዮጵያውያን በተለይ ሕዝባዊ ጉዳዮች ላይ በቀጥታም ይኹን በተዘዋዋሪ የምንሳተፍ ዜጎች እርስ በራሳችን መደማመጥ፣ መከባበርና መተማመን እንደምን አቃተን? ኹሉን አወቆች እጅግ ስለተበራከቱብንና ስለሰለጠኑብን አይደለምን?   

   አልበርት አንስታይን "The difference between genius and stupidity is; genius has its limits." ማለቱ እጅጉን ተደጋግሞ ይጠቀሳል፡፡ ኹሉን አወቆች ገደብ አልባ - ሚናተኞች ገደብ ያላቸው፤ ኹሉን አወቆች አቋም አልባ - ሚናተኞች ባለአቋም ናቸው፡፡ ድርሻን ማወቅና በድርሻ ውስጥ መኖርን አለማወቅ እጅግ ከኹሉ የከፋ ተወዳደሪ የሌለው መሐይምነት ነው፡፡ ከሕብረተሰብ ኹለንተናዊ እንቅስቃሴ አንጻር ካስተዋልነው - ኹሉን አወቅነት በግለሰብ፣ በቡድንም ኾነ በተቋም ደረጃ የሕብረተሰብ ካንሰር መኾን ነው፡፡

   እንደሀገር እያንዳንዳችን እንደዜጋ በሀገራችን ላይ ሊኖረን ስለሚገባ ሚናና ድርሻ ትርጉም ባለው መንገድ መጠየቅ፣ መመራመርና ማስተዋል ካልቻልን ፈጽሞ ልንሠለጥን አንችልም፡፡ በሕይወታችንም ቢኾን የሥልጡንነት ፍሬ ሊገኝብን አይችልም፡፡ የማንኛውም ሕብረተሰብ የሥልጡንነት መለኪያ ትርጉም ባለው መንገድ ዜጋዊ ሚናን ማወቅ፣ መረዳትና መገንዘብ ብሎም በዛ ውስጥ ኹለንተናዊ ትጋትን በግለሰብ፣ በቡድንና በተቋም ኹለንተናዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ማዳበር ስለመኾኑ የሥልጡኖች ታሪክ ዐቢይ ምስክር ከመኾኑም ባሻገር ያለመኾን ማሳያ ደግሞ ኹለንተናዊ የትላንትና ዛሬ አኗኗራችን ማሳያ ነው፡፡    

  ሀገራችን ትርጉም ባለው መንገድ ሚናቸውን መለየት የቻሉና የሚችሉ ዜጎች ፈርተውባታልን? ኹሉን አወቆች ሀገር አፍራሾችና ሻጮች እንደኾኑት ኹሉ ሚናቸውን መለየት የቻሉ ዜጎች ሀገር ገንቢና ጠባቂዎች ናቸው፡፡ ኹሉን አወቆች የሀገር ካንሰር ሲኾኑ ሚናተኞች የሀገር መድህን፤ ኹሉን አወቆች የሀገር ማፈርያ እንደኾኑት ኹሉ ሚናተኞች የሀገር አለኝታዎች ናቸው፡፡ ፈጣሪ ሀገራችን ነጻ ፍቃድን የኹሉ ነገር ማዕከል ወደ ሚያደርግ የዕሳቤ ሂደት ትገባ ዘንድ ይርዳን!

ቸር እንሰንብት!


Back to Front Page