Back to Front Page

በኢትዮጵያ ሥርዓት አልበኝነት መስፈን ፣ ግጭትና የሰላም መደፍረስ አብይ ምክንያት የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ መንግስት አሰተዳደር አመራር አቅም ማነስ እንዲሁም የለውጥ አቅጣጫ መዛነፍ ነው ።

በኢትዮጵያ ሥርዓት አልበኝነት መስፈን ፣ ግጭትና የሰላም መደፍረስ አብይ ምክንያት የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ መንግስት አሰተዳደር አመራር አቅም ማነስ እንዲሁም የለውጥ አቅጣጫ መዛነፍ ነው ።

ልኡል ገብረመድህን (ከአሜሪካ )

6.27.2019

ቅዳሜ ሰኔ 15 ቀን 2011 .ም በኢትዮጵያ የተከሰተ ጉዳይ ያልተገመተና ለማመን የሚያዳግት እንዲሁ አስደንጋጭ ሆኖ በታሪክ ማህደር ሰፍሯል ። እንደ መንግስት አገላለጽ የኢትዮጵያ መከላከያ ጦር ባልደረባ የነበሩ ብርጋዴር ጀነራል አሳምነው ፅጌ የተቀነባበረ የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት የመግደል ተግባር መፈፀሙ የኢትዮጵያ ህዝብ ያሳዘነ ክሰተት ነው ። የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕስ መስተዳድር ዶክተር አምባቸው መኮነን ፣ እንዲሁም ከፍተኛ የክልሉ የሥራ አመራር ነበሩ አቶ አዘዝ ዋሴ ፣ እንዲሁም አቶ ምግባሩ ከበደ የግድያ ሰለባ ሆነዋል ። በተመሳሳይ ጊዜና ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ መኖሪያ ቤታቸው እያሉ በጠባቂዎቻቸው አማካይነት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ጦር ኢታማጆር ጀነራል ሰዓረ መኮነን እንዲሁም ሜጀር ጀነራል ገዛኢ አበራ ተገድሏል ። ድርጊቱ የኢትዮጵያ ህዝብ ያሳዘነ ሆኗል ። በግሌ ለሟች ቤተሰቦች እና ወዳጅ ዘመዶች መፅናናትን ስመኝ ለሟቾቹ ነብስ ይማራሉ እላለሁ ።

Videos From Around The World

ህዘብ የማይገዛው የመንግስት ስልጣን ባለበት አገር መሰረተ ሰፊ የማህበረ ኢየሱስ ፖለቲካ ችግሮች አልፎ አልፎ መከሰታቸው አይቀርም ። መነሻ ምክንያት ደግሞ ህገ መንግሰቱ ነው ። በኢህአዴግ ስርአተ መንግስት 1987 .ም የፀደቀው የኢትዮጵያ ህገ መንግስት ካለፉት የአገሪቷ ህገ መንግስታዊ ሠነዶች በንፅፅር የተሻለ ቢሆንም በአፈፃፀም ላይ በርካታ ችግሮች ነበሩት ። አንዱ እና ትልቁ ችግር የዜጎች ሁለንተናዊ መብት ማክበር እና ማስጠበቅ አልቻለም ። በኢትዮጵያ ህገ መንግሰታዊ ጥሰት ያልተፈፀመበት ዜጋ ጥቂት ቢሆን ነው ። በሁሉም አካባቢ በሁሉም ማህበረሰብ በአገሩ ሠርቶ ፣ አፍርቶ ፣ አምርቶ እንዳይኖር በሥርዓት አልበኞች ሲጎዳ ቆይቷል ። ለችግሩ መባባስ በየደረጃው የሚሰሩ የኢህአዴግ ሥራ አመራሮች ምክንያት ነበሩ ። የኢህአዴግ ሰርአት ሀላፊነት እና ተጠያቂነት የጎደለው ሥርአት ስለነበር በተደጋጋሚ ለጋጠሙ አገር በቀል ችግሮች ሥር ነቀል መፍትሔ ማበጀት ሳይቻል ቆይቷል ። ሌላው አገራዊ አንድነት ሰሜት እየቀነሰ በአንፃሩ የማንነት ሰሜት እያገነገነ መምጣቱ ብሔርተኛ አመለካከት እንዲሰፋፋ ምክንያት ሆነዋል ።

በማንነት ፓለቲካ ውሰጥ የተፈጠረ ብሔርተኝነት ምክንያት የጋራ አስተሳስብ ለጋራ ጥቅም ከማዳበር ይልቅ በሁሉም ማህበረሰብ ማለት በሚያስችል ሁኔታ መጠራጠርና መቃቃር እያንሰራራ መጣ ። የኢትዮጵያ ዜጎች በመንግስት አሰተዳደር ላይ እምነት ማጣት ለሰላምና መረጋጋት አብይ ምክንያት ሆኖ ቆይቷል ፣ አሁንም የችግሩ አሳሳቢነት እንደተወዘፈ ይገኛል ። በማንነት ፓለቲካ ምክንያት ዜጎች ፍትሀዊ አሰተዳደር እና ፍትህ አጥቶ እንዲኖሩ የኢህአዴግ ሰርአት የአንበሳ ድርሻ ይወሰዳል ። በየደረጃው የሥልጣን እርከን ከከፍተኛ እሰከ አነሰተኛ የአመራር ብልሹነት በመፈጠራቸው የኢትዮጵያ ህዝብ በመንግሥት ላይ መተማመን እንዳያሳድር ምክንያት ሆኖ ዘልቋል ። ለኢህአዴግ ሰርአት መሠረት የሆነ ብሔር ላይ የቆመ የፖለቲካ ሰርአት የኢትዮጵያ ህዝብ ከመቀራረብ ይልቅ መራራቅ ፣ ከመተሳስብ ይልቅ መጎዳዳት ፣ ከመረዳዳት ይልቅ መሰገብገብ ፣ በአጠቃላይ ከእኛነት ይልቅ የእኔነት አመለካከት አዳብሯል ።

በኢትዮጵያ የብሄር ፓለቲካ የሁሉም ችግሮች ብቸኛ ምክንያት ተደርጎ ባይወስድም አገር የመበተን አቅም እንዳለው በጥሞና መገንዘብ ያስፈልጋል ። የዘረኝነት የፖለቲካ መርህ መጨረሻው መጠፋፋት ከመሆን ያለፈ ትርጉም ሆነ እርባና የለውም ። አክራሪ ብሔርተኝነት ምንጩ የፖለቲካ ዘረኝነት በመሆኑ በህዝቦች መካከል መራራቅ እንዲሁ ማህበራዊ ቅራኔ እንዲፈጠር እንደ ግብአት ማገልገሉ የማይቀር ጉዳይ ነው ። የፖለቲካ ብሔርተኝነት ያለፈው ማህበራዊ እንዲሁ ፖለቲካዊ ስህተቶች እያጣቀሰ የተረጋጋ አገር እና ህዝብ እንዳይኖር እንደ ምክንያት ይወሰዳል ። አክራሪ ብሔርተኝነት የመጨረሻ ግቡ የፖለቲካ በላይነት ለማስቀጠል የመንግሥት ሰልጣን መያዝ ነው ። የመንግሥት ሰልጣን ከተቻለ በህዝብ ምርጫ ካልተቻለ ደግሞ በሐይል ሰልጣን ለመያዝ ይዳዳል ። ከፍተኛ የመንግሥት ባላስልጣናት በማገት አልያም በመግደል የመንግሥት ሰልጣን ለመቆጣጠር ማሰብ በራሱ መሸነፍ ቢሆንም በአገር እና በህዝብ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ መፈጠሩ አይቀርም ። በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እየታየ ያለው የመጠፋፋት አዝማሚያ አንዱ የዘረኝነትና የብሔርተኝነት አንዱ ማሳያ አይነተኛ ምልክት ነው ።

የኢህአዴግ የልማትና የእድገት መሐንዲስ የነበሩ የቀድሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለሰ ዜናዊ የጀመሯቸው ታላላቅ የልማት አውታሮች በወቅቱ መጠናቀቅ ያለመቻላቸው በአገር ደረጃ ያለመረጋጋት እንዲሰፍን ምክንያት ሆኗል ። የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሀላፊ የነበሩ ኢንጅነር ስመኘው በቀል በጠራራ ፀሐይ በመስቀል አደባባይ መገደል የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አሰተዳደር ላይ ጣት የቀሰረው ህዝብ በርካታ ነበር ። የኢንጂነሩ የግድያ ሁኔታ በአግባቡ ሳይጣራ ተድበስብሶ የታለፈ ጉዳይ በመሆኑ የግድያ ምርመራ በገለልተኛ የዘርፉ ባለሞያዎች እንደገና መታየትና ጥልቅ ምርመራ መከናወን አለበት ። የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የኋላ ታሪክ በሚገባ ያልታወቀ በመሆኑ በከፍተኛ የመንግስት ባላስልጣናት የሚፈፀመው የግድያ ሴራዎች ከተጠያቂነት ነፃ አይሆኑም ። በኢትዮጵያ ተፈጥሮ ለኢትዮጵያ ህዝብ ነፃነት በከፍተኛ ታማኝነት አገራቸው እና ህዝባቸው ሲያገለግሉ የቆዩ ጀነራል ሰአረ መኮነን እንዲሁ ሜጀር ጀነራል ገዛኢ አበራ በምንም ምክንያት መገደል አልነበረባቸውም ። ጉዳዩ የእግር እሳት ያህል ያቃጥላል ፣ ያማል ፣ ያሳዝናል ። በተመሳሳይ ሁኔታ የአማራ ክልላዊ መንግስት አሰተዳደር ከፍተኛ የሥራ ሀላፊዎች ላይ የተፈፀመ ቅትለት ( ግድያ ) ምንም ይሁን ምን እጅግ አሳዛኝ ክሰተት ነው ። በጭራሽ መፈፀም ያልነበራት አሳፋሪ ድርጊት ነው ። የጉዳዩ ጥልቀት ሰፊ በመሆኑ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የመንግስት አሰተዳደር ብቃትና አመራር እንደገና መጤን አለበት ። የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የኋላ ታሪክ በአግባቡ መታየትና መመርመር ይኖርበታል ። ጠቅላይ ሚኒሰትሩ ይሰሩበት ከነበረ የኢትዮጵያ መረብ ደህንነት ድርጀት ጋር በተያያዘ ገና ያልተጣራ ውዝፍ የኋላ ታሪክ አላቸው ። በግልጽ እየተፈፀሙ ላሉት ወንጀሎች መነሻ ምክንያቶች በግልጽና በገለልተኛ የምርመራ ተቋም መመርመር አስፈላጊነቱ የላቀ ነው ። የጠቅላይ ሚነስትር ዶክተር አብይ አህመድ የለውጥ አቅጣጫ በግልጽ ባለመታወቁ ለሰላምና መረጋጋት እጦት ምክንያት ሆኗል ። ከአማራ ክልል የመንግስት ባለስልጣን ግድያ እንዲሁም ከኢታማዦር ሹም ጀነራል ሰዐረ መኮነን እና ከሜጀር ጀነራል ገዛኢ አበራ ህይወት መጥፋት ጋር በተያያዘ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አሰተዳደር ላይ የተቀናጀ የወንጀል ሴራ ጥልቅ ምርመራ መጀመር አለበት ። ከግድያው ጋር መንግስት የሚሰጠው እርሰ በእርሱ የሚጣረስ መረጃ መንግስት በተገደሉ ከፍተኛ የመንግስት ሀላፊዎች እጁ እንዳለበት የሚያመለክት ነው ።

ህገ መንግስት በሚፃረር መልኩ ክልሎች ልዩ የፀጥታ ሀይል እያሰለጠኑ ይገኛል ። በአማራ 300,000 ፣ በትግራይ 250,000 ፣ እንዲሁ በኦሮሚያ 400,000 ልዩ የፀጥታ ሐይል አሰልጥኗል ። በድምሩ የክልሎች የሐይል አሰላለፍ ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በቁጥር በልጦ ይገኛል ። ይህ በራሱ አንድ የፀጥታ ችግር ነው ። ክልሎች ልዩ ሐይል የማሰልጠን ተግባር ተገቢም አልነበረም ። የልማት በጀት ይሻማል ፣ በሒደት የግጭት መነሻ ምክንያት ይሆናል ። ክልሎች የህገ መንግስት ጥበቃና ከለላ እያላቸው ልዩ የፀጥታ ሰራዊት ማሰልጠን በህገ መንግሥቱ ላይ የእምነት ማጣት ምልክት ነው ።

ኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት እየራቃት ነው ። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች በማንነታቸው ጥቃት ይፈፀምባቸዋል ። መንግስት ከህዝብ ጎን ሆኖ ሰላም ማስፈን አልቻለም ። ድህነት መልሶ በማንሰራራት ላይ ነው ። ለሥራ የደረሰ የሥራ አጥ ቁጥር ከፍተኛ ነው ። የህዝብ ቁጥር በአማካይ በአመት አምስት በመቶ ይጨምራል ። ነገር ግን የኢትዮጵያ አመታዊ ጠቅላይ የአገር ውስጥ ምርቷ ከስድስት በመቶ አይበልጥም ። አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ በእርሻ ምርት ላይ የተመሠረተ ነው ። የአየር ፀባይ ተለዋዋጭ በመሆኑ ህዝቡ ለድርቅ ተጋላጭ ነዉ። ከእርሻ መር ኢኮኖሚ በፍጥነት መውጣት ካልተቻለ ከፍተኛ የምጣኔ ሀብት መቃወስ ያስከትላል ። የኢኮኖሚ እድገት ማሽቆልቆል የእርስ በእርሰ አላስፈላጊ ጦርነት በማንኛውም ጊዜ ሊከሰት ይችላል ። የፌዴራል ክልሎች የቅድሚያ ትንበያ ያላቸው ይመስል የልዩ ሐይል ሰራዊት ሰልጠና በመሰጠት ላይ ይገኛሉ ። ይህ አይነቱ የስልጠና ስልት በተዘዋዋሪ ብሔራዊ አገልግሎት ማለት ነው ።

አሁን እዛም እዚያ ኡኡታ ነግሷል ። ዘረኝነት የወለደው ጠባብ ብሔርተኝነት ወገኔ ተደፈረ ፣ የኦሮሞ የበላይነት ፈፅሞ አልቀበልም ፣ የአማራ ህዝብ ለጥቃት ተጋላጭ ሆኗል ፣ የፌዴራል መንግስት በክልላችን ጣልቃ መግባት የለበትም ፣ ሕወሓት በሰጠን አጀንዳ እየተላለቅን መቀጠል አንችልም ወዘተረፈ እያሉ የከረሙ የአማራ ክልል መስተዳድር የፀጥታ ሀላፊ የነበሩ ብርጋዴር ጀነራል አሳምነው ፅጌ የክልሉ የመንግስት ባለስልጣናት ግድያ ወንጀል ተጠርጣሪ የነበሩ ቢሆኑም በክልሉ ፀጥታ ሐይል ተገድሎ መቃብር መውረዳቸው መንግስት አውጇል ። ብርጌድ ጀነራሉ ከዚህ ቀደም ህገ መንግሥቱ በሐይል ለማፍረስ ተንቀሳቅሷል በሚል ወንጀል ተከሶ እድሜ ልክ ተበይኖባቸዋል ነበር ።የአማራ እና የትግራይ አዋሳኝ መንገዶች እንዲዘጉ የብርጋዴር ጀነራል ከሳምነው ፅጌ ተፅእኖ ቀላል እንዳልነበረ መገመት አያዳግትም ። የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን መምጣት ተከትሎ በምህረት ከእሥራት የተለቀቁ እኝህ ግለሰብ የአማራ ክልል መስተዳድር የፀጥታ ሀላፊ ሆኖ ከተሾሙ በአንድ አመት ውስጥ ችግር ውሰጥ ገቡ ። የደረሰው ችግር አብይ ምክንያት የኢትዮጵያ ህገ መንግስት በዘር ፖለቲካ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ነው ። በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሚመራው የኦሮሞ የዘር ድርጅት ለስልጣን በላይነት በሚያደርገው ጥንስስ ሴራ በአማራ አክራሪ ብሔርተኞች ተቀባይነት ባለማግኘቱ የተፈፀመ ወንጀል ሆኖ ሒደቱ ማቆምያ ያለው አይመስልም ።

በሌላ ጎን ከአማራ ክልል መስተዳድር ባለስልጣናት ግድያ ጋር ተያያዥነት ይኖረው አይንሮው በማይታወቅ ሁኔታ በኢትዮጵያ አንድነት የማይደራደሩ የሁለቱ ጀግኖች ማለትም የኢታማዦር ሹም ጀነራል ሰአረ መኮነን እና ሜጀር ጀነራል ገዛኢ አበራ አሟሟት ሴራ እና ድራማ ከቤተመንግስት አካባቢ ይመሰላል ። በመጀመሪያ መንግስት የሁለቱ ጀግኖች ገዳይ ተይዟል ፣ ቀጥሎም አልተያዘም ገዳይ ራሱን አጥፍቷል የሚል የመንግስት ማስተባበያ መቅረቡ የጉዳዩ ውስብስብነት ይበልጥ ተጋላጭ ያደርጓቸዋል ። በሁሉም ጀግኖች ግድያ መንግስት የሚያውቀው ይኖራል ለማለት የሚያስችል የመረጃ ክፍተት አለ ። በመሆኑም የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ መንግስት ለሁለቱ ጀነራሎች መሞት ሀላፊነት እና ተጠያቂነት መውሰድ ያለበት ይመስለኛል ። ከግድያ በስተጀርባ ያለ እውነታ በገለልተኛ የፍትህ ተቋም መጣራት አለበት ። በአገር ፍቅር ለአገር አንድነት በታታሪነት ሲያገለግሉ የነበሩ እኝህ ሁለቱ ጀነራሎች ያለምንም በቂ ምክንያት መግደል ተገቢ አልነበረም ። የአገር እና የህዝብ አለኝታ ሆኖ ለአገራቸው ሲሰሩ መገደላቸው በምንም መስፈርት ተቀባይነት የለውም ። በመሆኑም የሟች ቤተሰቦች ፍትህ ማግኘት አለባቸው ። በግድያ ሴራ የተሳተፉ ወንጀለኞች በገለልተኛ አካል ተጣርቶ ለፍርድ መቅረብ አለባቸው ። በቂም በቀል አገር ሆነ ህዝብ ማስተዳደር ፈፅሞ የሚሆን አይደለም ። ፍትህ ለሟች ቤተሰቦች ፣ ፍትህ ለኢትዮጵያ ህዝብ ፣ ፍትህ ለትግራይ ማህበረሰብ ፣ ፍትህ ለአማራ ማህበረሰብ ።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የለውጥ መሰመር በግልፅ መሬት ያልነካ በመሆኑ ለኢትዮጵያ ሰላምና ፀጥታ መናጋት ምክንያት ሆኗል ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በየትኛውም የለውጥ መሰመር እንደሚጓዙ ለማንም ግልጽ አይደለም ። አብዮታዊ ዲሞክራሲ ይሁን ሊብራል ዲሞክራሲ የሚታወቅ ግልጽ ጉዳይ የለም ። የኢኮኖሚ ስርአቱ እርሻ መር ይሁን ኢንዱስትሪ በግልፅ አይታወቅም ። የልማት ሸግግሩ አንደኛ ይሁን ሁለተኛ ፣ አልያም ሶሰተኛ በወል አይታወቅም ። የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እጣፈንታ በግልጽ አይታወቅም ። በዘር ፖለቲካ ምክንያት እየተፈፀሙ ያሉ ደረቅ ወንጀሎች እንዴት መፍትሔ እንደሚያገኙ የተነደፈ የመፍትሔ ሀሳብ በግልፅ አይታወቅም ። የአገር ሐብት ዘርፎ በአገር ውስጥ እና በውጭ አገራት የሚኖሩ የቀድሞ የመንግስት ባለስልጣናት ከኢትዮጵያ ህዝብ እና አገር ያሸሹት ሀብት መቼ እና አንዴት ወደ ህዝብ እንደሚመለስ የሚታወቅ የለም ። የሰላም መደፍረስ መንስኤዎች ተለይቶ ህጋዊ የመፍትሔ አቅጣጫ በየደረጃው እየተወሰደ ቢሆንም ችግሩን የሚመጥን መፍትሔ መሆን አልቻለም ። ለአብነት የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተማሪዎች በተረጋጋ መንፈስ ትምህርታቸው መከታተል አልቻሉም ። በከተሞች የዝርፊያ ወንጀሎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው ። የኑሮ ውድነት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው ። የመንግስት ሰራተኞች የደመወዝ እርከን ጭማሪ እንዲሁም የመኖሪያ ቤት ጥያቄ በማቅረብ ላይ ይገኛሉ ። የውጭ ንግድ ቀንሷል ። በዲፕሎማሲ መስክም የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ግንኙነት እንከን ገጥሞታል ። ግብፅ የአባይ ግድብ ግንባታ ለማስቆም የማትቆፍረው ጉድጓድ የለም ። የጎረቤት አገር ሱዳን አለመረጋጋት ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አሰተዳደር ስጋት ነው ። ሱዳን መንግስት አልባ አገር እንድትሆን የግብፅ ፍላጎት ነው ። ግብጽ በሱዳን አመክንዮ ኢትዮጵያ ላይ የሽብር ጥቃት ለመፈፀም ትሻለች ። በመሆኑም የሱዳን አለመረጋጋት ለኢትዮጵያ መልካም አይደለም ። ሌላው የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አሰተዳደር አለመረጋጋት ለግብጽ የገና ስጦታ ያህል ነው ። ግብፅ የኦሮሞ ወጣቶች (ቄሮ) መንግስት በአመፅ ለመገልበጥ ከፍተኛ የገንዘብ ሆነ የፕሮፓጋንዳ ሴራ ተዋናይ ነበረች ።

የጠቅላይ ሚኒሰትር ዶክተር አብይ አህመድ አሰተዳደር በበርካታ ስንጥቅ ችግሮች የታጠረ ነው ። የመንግስት ከፍተኛ የሥራ ሀላፊዎች የሴራ ግድያ አንዱ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የላቀ ችግር ነው ። በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚማሩ ተማሪዎች በዘር መገዳደል ሌላው ችግር ነው ። በአማራ ክልል መስተዳድር የተፈፀመው የአጥፍቶ መጥፋት ግድያ በኢትዮጵያ የተረጋጋ የፖለቲካ ሰርአት እንዳይኖር አብይ መሰናክል ይሆናል ። ሁኔታው ሰላማዊ የፖለቲካ የሰልጣን ሽግግር እንዳይኖር መነሻ ምክንያት ሊሆን ይችላል ። ሌላው የብሔር አክራሪ ፖለቲከኞች መበራከት ለዲሞክራሲ ግንባታ እንቅፋት ከመሆኑም በላይ የሰላምና መረጋጋት ጠንቅ ነው ። በመሆኑም ለችግሩ መፍትሔ በአጭር ጊዜ ውሰጥ የህገ መንግስት ማሻሻያ ማድረግ ያሰፈልጋል ። ኢትዮጵያ አሁን ባላው ሁኔታ የምትቀጥል ከሆነ የሐይማኖት ጦርነት ውሰጥ የመግባቱ አጋጣሚ ጠባብ አይደለም ። አሁን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የፖለቲካ አፈና እንዲሁ የሰብአዊ መብት ጥሰት ችግር ውስጥ የሚገቡ ይመሰላል ። ይህ ከሆነ ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኦሮሞ ብሔርተኝነት የበላይነት የማስቀጠል ህልም በእንጭጩ ይቀጫል ።

ለሞቱት አፀደ ገነት ያኑርልን ፣ ለሟች ቤተሰቦች መፅናናትን ይቻር አሜን !

 

 


Back to Front Page