Back to Front Page


Share This Article!
Share
ለመምህሬ መልስ ልስጥ፤ ከሳቸው የበለጠ ባላውቅም

ለመምህሬ መልስ ልስጥ፤ ከሳቸው የበለጠ ባላውቅም

ዶር. ዮሃንስ አበራ አየለ 1-03-19

ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም በቀለም ትምህርት ችሎታቸው እጅግ አድርጌ የማደንቃቸው ሰው ናቸው። ለሁሉም መንግስታት የማይቆረጠሙ ጥሬ መሆናቸውና ከቡድን ስቴንስል ተራብተው ሳይሆን የራሳቸው ጭንቅላት ሙሉ ተጠቃሚ  በመሆናቸውም አከብራቸዋለሁ። የፈፀሙት የእግዚአብሄርን ትእዛዝን ነው። አምላክ አንጎል ሲያድለን በቡድን ሳይሆን ለየግላችን እንድንጠቀምበት ነው። እንስሳትን ብቻ ነው በጋራ እንዲጠቀሙ አድርጎ የፈጠራቸው፤ ነጩን ለየብቻ ቢሰጣቸውም።

Videos From Around The World

የምጋራቸው ብዙ የተናገሯቸው ቁም ነገሮች አሉ፣ ለምሳሌ፦ 100 ሚልዮን ህዝብ እዚህ ቁጭ ብሎ አናሳ ቁጥር ላለው ብራም ስደተኛ ከመስመር ያለፈ ትኩረት የመስጠቱ ጉዳይ ያስከተለው የሞራል ዝቅጠት፤ ለብሄር ጉዳይ ከልክ ያለፈ ትኩረት በመስጠት ኢትዮጵያን መርሳት የተቀመጡበትን የዛፍ ቅርንጫፍ እንደመገዝገዝ የሚቆጠር ቂልነት መሆኑ፤ ስልጣንን ተአማኒነት ባለው ምርጫ ለህዝብ ማስረከብ ተስኗቸው በራስ ወዳድነት አገሪቱን ወደ እንደዚህ አይነት አጣብቂኝ ውስጥ የከተቷት ተከታታይ መንግስታት ሁሉም የታሪክ ተጠያቂዎች መሆናቸው።

ሌላው የወደድኩላቸው ግምገማ የእስረኛ ምህረት አሰጣጥና አፈታት ላይ የተናገሩትን ነው። ህወሓት የነካችው ሁሉ ወደ እባብነት ተቀይሯል ብሎ የሚያምነው ያሁኑ መንግስት ኢህአዲግ (ጥላቻና ቂም የቋጠሩ ሁሉ ሦስቱን ትተው ህወሓት የሚሉት) በፓሊስ ክትትል፣ ወንጀል መስራቱን የእምነት ቃል በመስጠት፣ አንቀፅ በተጠቀሰበት የፍርድ ቤት ውሳኔ የታሰረውንም የህሊና እስረኛውንም አንድ ላይ ሽብርተኛ መንግስት (አሁን ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመሩት በ2008 የተዋቀረው የኢህአዲግ መንግስት መሆኑ እንዳይዘነጋ) ሽብርተኛ ብሎ አስሮሃል ብሎ በጅምላ መፍታቱ የማያዋጣ የፓለቲካ ቢዝነስ ነው። ወንጀለኞች ጠንካራ መንግስት አይወዱም። የሚሻላቸው ህግ ማስከበር ላይ ብፁእ ነኝ እያለ የሚንዘላዘልና ህዝቡን ሁሉ እንደፃድቃን ስብስብ የሚቆጥረውን መንግስት ነው። ማንኛውም መንግስት ስልጣን ላይ ሲወጣ ከሱ በፊት ስለነበረው መንግስት ጭርስ አድርጎ መናገር የለበትም። የህዝብ ባህርይ በዚህም በዛም ያው ስለሆነ ወረቱ እስኪያልቅ ነው እንጂ ለአዲሱ መንግስትም ያው ነው። ከዚህ ሁሉ አገር አንቀጥቅጥ የሆነ ሰርግና ምላሽ በኋላ በከፋ ሁኔታ ወደ ድሮው እየተመለሰ መሆኑ እየታየ ነው። ነግ በኔ እያሉ መጠንቀቅ ይበጃል። ይህን ከማድረግ ይልቅ ከአያያዝ ጉድለት፣ ወይንም በደጋፊዎች ላይ በጣሉት ጭፍን እምነት የደጋፊው እውነተኛ ገፅታ እየተከሰተ ሲሄድና "አዲሱ" መንግስት መዋከብ ሲጀምር ለተደፋ የብርጭቆ ውሃ ሁሉ "ከስልጣን መውረዳቸው ያልተዋጠላቸው ናቸው ያደረጉት" እየተባለ ማይክ በቀረበለት ሃላፊና ግለሰብ ሁሉ መነገሩ ጠቃሚ አይደለም ብቻ ሳይሆን ትክክለኛን ጠላት ከመለየት ያዘናጋል። ችግር የፈጠረውም እኮ አብሮ "ይህን የምትሰራው ወያኔ ናት" ቢል ሰው ሁሉ ይስማማል! ይህ ጉዳይ አንድ በቅርቡ ያየሁትን ካርቱን አስታወሰኝ። ካርቱኑ የአየር ንብረት ለውጥ ያስከተለው ጉዳት ሁለገብ ሆኖ መቅረቡ የተጋነነ መስሎ የተሰማቸው ሰዎች ያዘጋጁት ነው። አንድ ሰው በጩቤ ተወግቶ አውራ መንገድ ላይ ወድቋል። የከበቡት ሰዎች ማን እንደወጋው ግምታቸውን እየተናገሩ ይንጫጫሉ። አንዱ፣ ምናልባትም ወጊው፣ ወደተሰበሰበው ሰው ጠጋ አለና "የወጋው የአየር ንብረት ለውጥ ነው" ብሎ ሲናገር የተለያየ ግምት ይዘው የነበሩት ሁሉ፣ የአየር ንብረት ለውጥ ምን ማለት እንደሆነ የማያውቁትም ጭምር፣ በአንድ ድምፅ "እሱስ ይሆናል፣ ልክ ነው፣ አያደርግም አይባልም!" ብለው በስምምነት ተለያዩ።

ፕሮፌሰር መስፍን ጃንሆይን "ንጉስ እንጂ አፄ መባል የለባቸውም፤ ኢትዮጵያዊ ያልሆነ ህዝብ በቅኝ ግዛትነት ያጠቃለሉ ስለሚያስመስልባቸው እያሉ ይፈታተኗቸው ነበር። የወሎ ድርቅ በህዝብ እንዲታወቅ በማድረግ ባያቅዱትም የንጉሱን የስልጣን እድሜ ለማሳጠር አስተዋፅኦ አድርገዋል። በደርግ ዘመንም ውይይት ክበብ አልገባም፣ በብሄረሰቦች ኢንስቲትዩት አልሳተፍም እያሉ እምቢተኝነት ያሳዩ እንደነበር ይታወቃል፤ ከኮሎኔል መንግስቱ ጋር ቴኒስ ይጫወቱ ነበር ተብለው ከመታማታቸው በስተቀር።

በዘውዱ ዘመን በዩኒበርሲቲ ተማሪዎች እንቅስቃሴ ውስጥ በንቃት ሲሳተፉ ከነበሩት መምህራን አንዱ ቢሆኑም የዶር. እሸቱ ጮሌ ያህል የማያወላውል አቋም አልነበራቸውም። ለዘውዳዊ ስርአቱ የነበራቸው ተቃውሞ ሂሳዊ ድጋፍ እንጂ ስር ነቀል ለውጥ እንዲመጣ አልነበረም በሚል ተማሪዎች ፕሮፌሰሩ ላይ የተሟላ እምነት አልነበራቸውም።

ይህን ፅሁፍ ያዘጋጀሁት እንደ "ሃርድ ቶክ" ጋዜጠኛ ሳይሆን እንደጎበዝ ተማሪ በዝምታ አስተማሪዋ የሚያስተምረውን ስታዳምጥ የቆየችውና የተባለውን ከማጠናከር የዘለለ፣ በሌሎች ላይ እንደምታደርገው፣ አንድም ከረር ያለ ጥያቄ ያላነሳችው የኤል ቲቪ ቃል ጠያቂ የፈጠረችውን ክፍተት ለመሙላት ብየ ነው።

ፕሮፌሰር መስፍን የደርግንና የ"ወያኔ" አመራርን "ሃላፊነት የማይሰማቸው ጎረምሶችና ዱርየዎች" አይነት እንደሆኑ አድርገው ሲገመግሙ የስልጣን ከበሮ በሰው እጅ ሲያዩት ቀላል ቢመስልም እንደዛ መናገር መብታቸው ነው።  እንደ ችግር መታየት ያለበት በየዘመኑ ስልጣን ላይ የወጡት ሁሉ ህዝብን የመበደል የየራሳቸው ድርሻ የነበራቸው መሆኑ እየታወቀ ከደርግና ከ"ወያኔ" የሚበልጥና ተሻሽሎ መቆየት የነበረበት ዘውዳዊ ስርአቱ ነው ብለው በድፍረት መናገራቸው ነው። የጃንሆይ አገዛዝ ምርጥ እንደነበር የተናገሩት የማወዳደሪያ መመዘኛቸው ወጥ የሆነ መሆኑን ሳያረጋግጡ ነበር። ሦስቱንም መንግስታት በትክክል ማወዳደር ወይንም ማነፃፀር የሚቻለው በአንድ ሚዛን ላይ እያስቀመጡ ነው። እነዚህ ግን የየራሳቸው ልዩ ባህርያት፣ርእዩት፣ አመጣጥ፣ አገር አቀፍና አለም አቀፍ ሁኔታዎች የነበሯቸው ስለሆኑ አወዳድሮ ደረጃ ማውጣት ከግል ስሜት ብዙም የሚርቅ ትንተና አይደለም።

የጃንሆይ መንግስት ገበሬዎችን ችላ አላቸውና ደኸዩ ብለው መንግስትን እንደ ኩባንያ ሲፈርጁ ታላቅ ድፍረት ቢሆንም ዝም ተባሉ። ይህ ለርሳቸው የዛ መንግስት ዴሞክራሲያዊነት ማረጋገጫ ሆነላቸው። የታሰሩት ግን ስለተሳደቡ ሳይሆን (ዘውዳዊው መንግስት ያቀዳጃቸው መብታቸው ነበረና)  ተሹመሃል ሲባሉ እምቢ በማለታቸው የንጉሥ ትእዛዝ ስለጣሱ ነበር። የንጉሡን አስተዳደር ከመናፈቃቸው የተነሳ የተናገሯቸው ሁለቱ ነገሮች የሚጣረሱ መሆናቸውን ልብ አላሉም። ማሳሰር የነበረበት እንዲያውም ዘለፋው ነበር፣ ዘለፋ ህግ የማይፈቅደው ወንጀል ስለሆነ። የንጉስ ይሁን የእግዚአብሄር ትእዛዝ ማንም ሰው በየትኛውም አለም ሹመት አልቀበልም ማለት በህግ የተከበረለት መብቱ ነው። ህግ የሚፈቅደውን ትተው ህግ የማይፈቅደውን እስራት ሲፈፅሙ ዴሞክራሲያዊ መባላቸው ይገርማል። የገዛ ልጅን ምንም ቢወዱት ገብረ እግዚአብሄር እንጂ እግዚአብሄር ብለው ስም አያወጡም።

የጃንሆይ ዘውዳዊ/ ፊዩዳላዊ ስርአት (ፊዩዳላዊ ያከልኩበት ከእንግሊዙ ዴሞክራሲያዊ ዘውድ ጋር እንዳይምታታ ብየ ነው) ከሁሉም የተሻለ መሆኑን የገመገሙት በርስዎ ላይ በደረሰው ወይም ባልደረሰው ነገር ላይ ብቻ ተንተርሰው ነው። ስለ ታላቁ ፈላስፋ አሪስቶትል የሚነገር ቀልድ አለ። የምርምር ዘዴ ሳስተምር አዘውትሬ እንደምሳሌ አነሳዋለሁ። ከቀናቱ በአንዱ አሪስቶትል አንድ አዲስ ግኝት አለኝ ብሎ ደቀመዛሙርቱን ይሰበስባቸዋል። እንዲህም አለ፦ "ሴቶች 30 ጥርስ ነው ያላቸው"። ደቀመዛሙርቱ ተገርመው "እንዴት ደረስክበት?" ብለው ቢጠይቁት እንዲህ ብሎ መለሰ፦ "ቀላል ነበር፤ ሚስቴ ሰላሳ ጥርስ ነው ያላት"። እንደሳቸው ያለ በምርምር ዘዴ እውቀት ጣርያ የነካ ሰው ሳያውቁት ነው የተናገሩት ብል ያስኮንነኛል።

እነዚህ ነገስታትና መሳፍንት ዘዴኞች ናቸው። በተለይ የተማረው እንዲጠላቸው አይፈልጉም። ከጀርባ በሚልዮን የሚቆጠርን ህዝብ እያጎሳቆሉ ከፊታቸው መልካቸውን የሚያሳምሩላቸው ሰዎች ይፈልጋሉ። መሪዎቻችን ሁሉም በአለም ደረጃ (በተለያየ ሁኔታ ቢሆንም) ታዋቂነት ያፈሩ ነበሩ፣ ናቸውም። ይህ የሆነው መልካም ሽፋናቸውን ብቻ ለአለም ስለሚያሳዩ ነው። ለዚህም የሚረዷቸው ምሁራኑ ናቸው። ህዝብ ከየቤቱ ሆኖ ቢንጫጫ ሰሚ የለውም። ምሁሩ በሚያደንቃቸው ጌቶቹ ላይ የሚነሳው የራሱ ጥቅም የተነካ እለት ብቻ ነው።

ዘውዳዊው ስርአት "የወንዜ ልጅ" ከሚባባሉት ከፕሮፌሰር መስፍን ጋር እየተኮራኮረ ሲሳሳቅና "በፊዩዳሊዝም ዴሞክራሲ" ሲሞጋገስ በደቡብ፣ በኦሮሚያ፣ በሌሎችም የነበሩ በሚልዮኖች የሚቆጠሩ መሬት አልባ ጭሰኞች በገዛ ቀያቸው ባዳ ሆነው፣ ያፈሩትን ለወራሪ እያስረከቡ፣ የሲኦል ህይወት ይገፉ ነበር። ይህን ግፍ ለማስቀጠል ነበር ፕሮፌሰር መስፍን ጃንሆይ ዙፋናቸውን ለልጃቸው ቢያስረክቡ ኖሮ ብለው የተቆጩት? ራሳቸው ያለእፍረት እያደረጉት የትግራይ ምሁራን ላይ ሲደርሱ የህወሓት መንግስት ደጋፊዎች መሆናቸው ለምን እንዳስገረማቸው ራሱ አስገራሚ ነው።

ይህ ትችት የማከብራቸውና የማደንቃቸው አስተማሪየን ለማንኳሰስ የታቀደ አይደለም። አሁንም አክብሮቴ የፀና ነው። ለማለት የፈለግሁት አገራችን በሳቸው ደረጃ የደረሱና ሁለገብ የሆነ እውቀት ያላቸው ሰዎች ብዙ ናቸው የሚባሉ አይደሉም። አሳቸውን ቀና ብየ መምከር ከአቅሜ በላይ ቢሆንም እንደ ፕሮፌሰር መስፍን ያሉ ዜጎች ቢሰማሩ ላገራችን ይበጃል ብየ የምለው እንደመደዴው አንድ ፅንፍ፣ አንድ ጥግ ይዘው መወራወር ሳይሆን 100 ሚልዮን ህዝብ፣ "ወያኔ" እያሉ የሚገልቧቸውም ጭምር፣ እኩል እንደልጆቻቸው አይተው የሽምግልና ስራ እንዲሠሩ ነው። አለበለዚያ ሁሉም የሌላውን ጩኸት ላለመስማት ጀሮውን ደፍኖ ብቻውን የሚጮህ ከሆነ ይቺ አገር ከህልምነት ወደ አስፈሪ ቅዠትነት ትቀየራለች።

 

 

Back to Front Page