Back to Front Page

ሁላችንም እንሩጥ!!

ሁላችንም እንሩጥ!!

 

ሞላ ምትኩ 4-9-19

 

ወይዘሮ ፋጡማ ህይወታቸው እስካለፈበት 2010 ዓም  ድረስ  ከጎረቤታቸው ወይዘሮ በለጡ ጋር  ለበርካታ አሰርት ዓመታት በሰላም በመተሳሰብና በመከባበር ኖረዋል ። የፍቅር ከተማ  በሆችው ከሚሴ።

 

በዚችው ቤት ሶስት ሴቶችንና አራት ወንዶችን ወልደው አሳድገው ለወግ ማረግ አድርሰዋል ። ወይዘሮ በለጡም በተመሳሳይ መልኩ ሁለት ሴቶችና ሶስት ወንድ ልጆቻቸውን   አሳድገው ለወግ ማረግ አድርሰዋል ። እንህ ሁለት ቤተሰቦች ኑሯቸው የተደበላለቀና ይህ የዚህ ነው የማይባል   እንደ አንድ ቤት ነበር የኖሩት ።

 

 ወይዘሮ በለጡ እንድህ ይላሉ "የኔ ልጆች ከፋጤ ልጆች ለይቸ ያየሁበት ቀን ፈጽሞ አልነበረም ። ፋጤም በተመሳሳይ መልኩ ። ልጆቻችን አብረው ውለው አብረው በልተው አብረው ያድሩ ነበር ። ለወግ ማረግ ደርሰው የየራሳቸው ኑሮ መስርተው ከቤት ከወጡ በህዋላም  በዓውዳመት ቀን እየመጡ ተሰብስበን በደስታ በፌሽታ ነበር የምናሳልፈው ።  ልጄ! አሁን ነገር አለሙ ሁሉ ተቀየረ " አሉ ።

 

በደሴ ሆስፕታል ያገኘህዋቸው ወይዘሮ በለጡ ስቃ እየተናነቃቸው ንግግራቸውን ቀጠሉ ። "ፋጤ የዋህ ሰው ስለነበረች ይህን ዘመን አመጣሽ ወረርሽን እና ጉድ ሳታይ እግዚአብሄር ነፍሷን በሰላም አሳረፈላት። እኔ አለሁ ለጉድ የጎለተኝ ። የፋጤ ልጅ ከወንድሙ ከኔ ልጅ ጋር ሲደባደብ ሲገዳደል እስከማይ በመቆየቴ እግዚአብሄርን አማረርኩት ። ምንአለ የፋጤን ዕጣ ፈንታ በሰጠኝ አልኩ " አሉና ስቅስቅ ብለው አለቀሱ።

 

ራሳቸውን መቆጣጠር አልቻሉም ። ትንሹ ልጃቸ በተነሳው ብሄር ተኮር ግጭት ተመትቶ  እህቱ ወደ ደሴ ወስዳ በደሴ ሆስፕታል እያሳከመችው  መሆኑንም  አወጉኝ ። የፋጤ ልጆች በአንድ ጎራ የሳቸው ልጆች ደግሞ በሌላ ጎራ መሰለፋቸውን ሲገነዘቡ አለመኖርን መረጡ። የነበራቸውን ፍቅር አብሮነት መተሳሰብና መቻቻል ተሸርሽሮ በባላንጣነት የሚተያዩ አንዱ ሌላውን  ሲገድል በማየታቸው መኖርን ጠሉ። "ለ80 ዓመታት የጎለተኝ ይህንን ሊያሳየኝ ነው" አሉና እጅጉን አዘኑ ።

Videos From Around The World

 

እንደዚህ ዓይነቱ  ሀዘን የሁሉም ኢትዮጵያዊ ሀዘን ሆኗል ። በአሁኑ ወቅት በበርካታ የአገሪቱ ክፍሎች ዋይታ በዝቷል ። ወንድም በወንድሙ ጨክኗል ። ሰው ከሰብአዊ እይታው ወጥቶ ወደ አውሬነት እየተቀየረ ነው ማለት ያስደፍራል ።

 

አብሮነት ፍቅርና መተሳሰብ ለጥላቻና ለተንኮል ስፍራቸውን ለቀዋል ። ይህ ሁሉ እየሆነ ያለው በፖለቲከኞችና እነሱን በሚከተሉ የእነሱን ፍላጎት በሚያራግቡ  የሚዲያ ተዋናዮች አማካይነት መሆኑን በርካቶች ያምናሉ ። እሳቱን የማቀጣጠል "ማን ከማን ያንሳል?"  የሚል የድንቁርናና የግለኝነት አስተሳሰብ እንዲሰርጽ "የኔ እና  ለኔ"  የሚሉ የመስገብገብ ባህሪ እንድሰፋ በህዝቦችመካከል መቃቃር ቁርሾ ግጭትና ደም መፋሰስ እንዲፈጠር ተደርጓል።  በዝህ መልክ ወደ ቀውስ ገብተናል ። ቀልባችን ሸሽቶናል። ተነጥቀናል።

 

ከገባንበት ቀውስ  ለመውጣት  መጀመሪያ ወደ ቀልባችን መመለስ የግድ ይላል። ሁላችንም ራሳችንን እንፈትሽ ። ለእውነት ከእውነት የየራሳችንን ህጸጽ እንመርምር ። ሰበብ አስባብ ይቁም። ወደ ሌሎች ጣት መቀሰርም ሆነ  በሌሎች ማላከክ ይብቃ። ለችግሩ መፈጠር በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሁላችንም እጅ አለበት። እኔ ከደሙ ንጹህ ነኝ የሚል ሰው አይኖርም ። 

 

ስልጣን ፈላጊው፣ ስልጡንን ለማረዘም የሚያላዝነው፣ በገንዘብ እየተገዛ ጠብ አጫሪ ተግባር የሚፈጽመው፣  በምን ተግዴ በራሱ ደሴት ሆኖ የሚታዘበው፣  ሙሁሩ፣ ፖለቲከኛው፣  ነጋዴው፣ አርሶ አደሩና  ሁሉም ዜጋ ለችግሩ መፈጠር ድርሻ አለው ። ሁሉም  ደግሞ የችግሩ ገፈት ቀማሽ መሆኑ አይቀሬ ነው ።

 

ከደሙ ንጹህ ነኝ ብሎ እንደ ጲላጦስ እጁን በውሀ የሚታጠብ ይኖራል ተብሎ አይገመትም። በሰላም መደፍረስና መረጋገጥ ሁሉም ተጎጂ ሁሉም ተጠቃሚ ነው ።  ስለዚህ "ሳላውቅ በስህት ሳውቅ በድፍረት የሰራሁትን ሃጥያት ሁሉ ይቅር በለኝ" ብለን ወደ ቀልባችን እንመለስ። የድርሻችንን ወስደን የመፍትሄ አካል እንሁን ። ሁሉም በያለበት በአቅሙ ለሰላም ዘብ ይቁም።

 

ወሎ ገራገሩ የፍቅር የአንድነት የመቻቻልና የአብሮት ተምሳሌት  እንደዚህ ከሆነ ከዚህ በህዋላ እንካስ ምን ቀረ ። ወደ ቀልባችን ካልተመለስን የጠፋ ካልተካን  የተጎዳ ካልካስን ነገሮች ወደ ነበሩበት ካልመለስን መጻኢ ዕጣ ፈንታችን የከፋ እንደሚሆን ትንተና አይፈልግም።

 

 በመሆኑም መላው የአገራችን ህዝቦች ሰላማችን ያለው በጃችን ነው። ወደብጥብጥ እንድንገባ ለሚገፋፉን፣

 ለሚያነሳሱንና ለሚቀሰቅሱን ጆሮ ዳባ ማለት ይኖርብናል ። ህግን የማያከብሩና የማያስከብሩ   በየደረጃው ያሉ አመራሮችንም አልቻላችሁም አትመሩንም ብለን ማስወገድ የኛ ድርሻ ነው።

 

በተለይ ወጣቱ ከእንደዚህ አይነት ሁውከትና የእርስ በርስ የመገዳደል አጀንዳ  ወጥቶ የተረጋጋች አገር ትኖረው ዘንድ ከሌሎች ሰላም ወዳድ ዜጎች ጋር በመሆን ሊሰራ ይገባል። 

 

ሙሁራንም በየሚዲያው እየወጡ ከችግር መውጣት የሚያስችለንን መላ ማሳየት ይጠበቅባቸዋል ። ሚዲያዎችም እጅ እጅ ከሚል  አባባሽ ዘገባ ወጥተው መፍትሄ ጠቋሚ ስራዎችን ቢሰሩ መልካም ይሆናል።

 

መቸም ነገርን ነገር ይወልደዋልና እሩቅ ሳልሄድ የቅርብ ጊዜና የቅርብ አገር ተሞክሮ ማንሳት ማሳያ ይሆናል። መቸስ ተሞክሮ የጠላት የወዳጅ የሚል የለውምና የግብጽን ተሞክሮ  እንመልከት። ፕሬዚደንት ሙባረክ ከስልጣ እንደተወገዱ ግብጽን ለመጎብኘት ዕድል አግኝቼ ነበር ።

 

ግብጽ የሙባረክ መንግስት መውደቅን ተከትሎ ቀውስ ውስጥ ገብታ ነበር። በጄኔራል ታንታዊ ይመራ የነበረው ወታደራዊ መንግስ ህዝቡን ለማረጋጋትና አገሪቱን ለማዳን የተለያዩ ጥረቶችን ያደርግ ነበር ።

 

በዚያን አስከፊ ወቅት የግብጽ ሙሁራንና ሚዲያ ምን ያደርጉ ነበር?  የሚለውን  ነው የኔ ነጥብ ። አገር ውሰጥ ይኖሩ የነበሩ ሙሁራን  ሙሁራን ተሰባሰቡ ። በውጭ ይኖሩ የነበሩ  እንደ መሀመድ አልባራዳይ የመሳሰሉ በዓለም ደረጃ አንቱ የተባሉ ሙሁራን ከውጭ አገራት ወደ አገራቸው ተመለሱ። ከሞቀና የተደላደለ የውጭ ኑሮ በብጥብጥ ማዕበል ተዘፍቃ ወደ ነበረችው አገራቸው ተመለሱ።

 

ልዩነቱ ከዝህ ይጀምራል ። እኛ በቀውሰ ጊዜ ከውጭ ወደአገር ቤት ወይስ ከአገር ቤት ወደ ውጭ ነው የምናመራው? መልሱን ለህልናችን እንተወው። ግብጻውያን ሙሁራን ግን በሁከትና ብጥብጥ ወቅት ከያሉበት ወደ  አገራቸው መመለሳቸውና ተሰባስበው መፍትሄ መሻታቸው ለአገራቸው ያላቸውን ፍቅር የሚያሳይ ነው።

 

ግብጻውያን ሙሁራኑ አንድ ላይ እየመከሩ ለህዝባቸውና ለመንግስታቸው ይበጃል ያሉትን ምክረ ሐሳብ በየዕለቱ ማቅረብ ጀመሩ። በተለያየ መልክ ለህዝባቸው መግለጫ በመስጠት አረጋጉ።

 

ሚዲያው በበኩሉ ምንም ነገር ሳይደብቅም ሳያጋንንም  መረጃ እያቀረበ  የየዕለቱን መረጃ በተለያየ መልክ ሙሁራንን በማቅረብ ህዝብን ለማረጋጋት ሰራ። በየዕቱ ኢኮኖሚው ላይ የፈጠረው ጫና የተጎዱ ሰዎች   በሚመለከት መደረግ ስላለበት ሁኔታ አገሪቱን ከውድቀት ለማውጣት ከማን ምን እንደሚጠበቅ በተለያየ መልክ ለህዝብ በማቅረብ አገራቸውን ከጥፋት ታደጉ።

 

ከዝህ አኳያ የኛ አገር ሲታይ እውነታው ለየት ይላል ። ግን ውጭ ያሉት እንኳን ባይመጡ አገር ቤት ያሉት ድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል ። በመሆኑም  ሁሉም ወደ ቀልቡ ተመልሶ የድርሻውን  ለመወጣት መወሰንና መተግበር የግድ ይላል ። እስካሁን ባለው ሁኔታ ምን ያህል አስተዋጽኦ እንዳደረግን የየራሳችንንእናውቃለን እና ከመፍረሳችን በፊት ወደ ቀልባችን እንመለስ ።

 

መንግስትስ ምን ይጠበቅበታል? የሚለውን ጥያቄ በመመለስ ጽሁፌን እቋጫለሁ።  መንግስት መንግሰት መሆን አለበት። የመጀመሪያ ተግባሩ ህግን ማስከበርና የዜጎቹን ደህንነት መጠበቅ ነው። ይህንን ማረጋገጥ ከመንግስት ይጠበቃል።

 

ይህንን የሚያስከብርበት መንገድ እንደየ አስፈላጊነቱ ሊለያይ ስለሚችል የሚከተለውን መንገድ ለህዝብ ይፋ በማድረግ ስራውን ሊሰራ ይገባል።  ህዝብ ሰላምን ስለሚፈልግ ከመንግስት ጎን ይሰለፋል። መንግስት እና ህዝብ ከተባበሩ ደግሞ  አደፍራሽ ራሱ ይደፈርሳል። መንግስት ህዝብን አደራጅቶ ማንቀሳቀስና መምራት ካልቻለ ግን በአገሪቱ ስርአት አልበኝነት ይሰፍናል። አገሪቱ እንደ አገር መቀጠልዋንም ያጠራጥራል።

 

በሁከትና ብጥብጥ ህዝቡን ወደአላስፈላጊ ትርምስ ይገባል። አገርም ትበተናለች።  ከዚያ በህዋላ የሚደረግ ጥረት  የፈሰሰን  ውሀን  ለማፈስ  ከመሞከር የተለየ አይሆንም። ይልቅ ጊዜው አሁን ነው። ውሀው ሙሉበሙሉ ከመፍሰሱ በፊት ያለ የሌለ አቅማችንን ተጠቅመን አገራችንን ከመፍረስ መታደግ የሚቻለው። እንሩጥ። ሁላችንም ባለን እናግዝ ። ለአገራችን ህልውና የቻልነውን እናድርግ።

Back to Front Page