Back to Front Page

የ ጌታቸው አስፋ የፍርድቤት መጥርያ ላሞች ባልዋሉበት ኩበት ለቀማ፡

የ ጌታቸው አስፋ የፍርድቤት መጥርያ ላሞች ባልዋሉበት ኩበት ለቀማ፡

መግቢያ

ከገራገር ዘበርጋ /14/09/2011 ዓ.ም/

አንባቢያን ይህንን ፅሑፍ ለማዘጋጀት የተገደድኩበት ዋናው ምክንያት ባሁኑ ወቅት ባገራችን የፖለቲካና የፍትሕ ሂደት ውስጥ የማይገናኘውን ክስተት ምንም ከማይቀራረበው እውነታ በማዛመድ፡ መጠየቅ ያለበትን ወደ ጎን በመተው ወይም በመሸለምና በመሾም ሌላውን ወገን ግን ተጠያቂ ለማድረግ ብዙ ሽርጉድና ሸፍጥ የሚሰራበት ፖለቲካና የፍትሕ ሂደት ተብየው ድራማ እየተፈጸመ እኔን አይመለከተኝም! በማለት በዝምታ ማለፉ ሕሊናን የሚቆረቁር በመሆኑ በመሬት ላይ ያለውን እውነታ ከሕግና ከፍሬነገሩ ጋር በማዛመድ ትክክለኛውን ስእል ሕዝቡ እንዲያውቀው ለማድረግ ነው፡፡

የፀረ ሽብር ጉዳይ

በመስከረም 2001 ዓ.ም በኒውዮርክ ከተማ በነበሩት ሁለት መንትየ ሕንጻዎች ላይ አሸባሪዎች አውሮፕላኖችን ጠልፈው ከሕንጻዎቹ ጋር በማላተም በውስጡ የነበሩት ሰዎች እንዲያልቁና ሕንጻዎቹም አንዲፈራርሱ ካደረጉ በኃላ ኃያሏ አሜሪካ ተደፈርኩ ብላ ጡንቻዋን ለማሳየት ሰብብ ፈጥራ ኢራቅን ወርራ የሳዳም ሑሴን መንግስትን ያፈራረሰች ሲሆን ከዚያ በመቀጠልም አሸባሪዎች በአፍጋኒስታን፡ በኢራቅ፡ በሰሜን ሳሄል አገሮች፡ በናይጀሪያ፡ በሶማሊያ ወዘተ አገራት የሽብር ጥቃታቸውን እያስፋፉ እንደመጡ የሚታወቅ ነው፡፡ ይህም በመሆኑ የዓለም አገራት አሻባሪዎችን ለመቆጣጠርና ለመከላከል የሚያስችላቸውን ሕግ በየጊዜው ሲያውጁና ተግባራዊ ሲያደርጉ ተስተውሏል፡፡ ኢትዮጵያም ብትሆን የሽብር ሰለባ ከመሆን የተረፈችበት ጊዜ ስላልነበረ ጉዳዩ ስታስጠናና የሌሎች አገሮች ልምድንም ስትቀምር ከቆየች በኃላ በ2001 ዓ.ም ነሐሴ ወር ላይ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አውጥታ አሸባሪ ብላ የፈረጀቻቸውን አካላትና ግለሰቦችን ስትከታተልና ለፍርድ ስታቀርብ ከርማለች፡፡ ይህ አዋጅ እስካሁን ድረስ በስራ ላይ ያለ ሲሆን በቅርብ ቀናት ሌላ ማሻሻያ የተደረገበት አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ለመጽደቅ በሂደት ላይ እንዳለ ይነገራል፡፡

Videos From Around The World

በዚህ አዋጅ መግቢያ ላይ እንደተገለጸው የአገሪቱ ሕዝቦች ደህንነትና ያገሪቱ ጥቅም ከማንኛውንም የሽብር አደጋ መጠበቅና መከላከል በማስፈለጉ፡ አገሪቱ አሸባሪ ብላ የሰየመቻቸው አካላትን ተጠርጣሪ ግለሰቦች በማስረጃና በመረጃ አስደግፎ ለሕግ ማቅረብ እንደሚያስፈልግና ለዚሁም ጠንካራ የሕግ ማእቀፍ ማውጣትና ማደራጀት አስላጊ ሆኖ በመገኘቱ፡ አገሪቱ የአህጉራዊና የዓለም አቀፍ ግዴታዎቿን ለመወጣት ሽብርተኝነትን መከላከልና ግዴታዋን መወጣት እንዳለባት ግንዛቤ ተወስዶ ሕጉ እንደወጣ ይደነግጋል፡፡

ከዚያም በመቀጠል በዝርዝር አዋጁ ላይ ሽብርተኝነት ማለት ምን እንደሆነ፡ በሽብርተኝነት የሚጠረጠር አካል ወይም ቡድን ወይም ግለሰብ ምን ዓይነት ድርጊት የፈጸመ ወይም ሊፈጽም ያሴረ እንደሆነ ወዘተ የሚያብራሩ በርካታ አንቀጾች ያሉት ሲሆኑ፡ ይህንን ጉዳይ የሚያስፈጽሙና የሚከታተሉት አካላትና ሰራተኞችም እነማን እንደሆኑ በአንቀጽ 28፡ 29 እና 30 ላይ በግልጽ ሰፍሯል፡፡ ግርታን ላለመፍጠርና ሌላ ትርጉምም ላለመስጠት አንቀጾቹን እንዳሉ ኮፒ ፔስት አድርገን አቅርበነዋል፡፡ ከዚያም አንባቢ በማያሻማ ሁኔታ በፀረ ሽብርተኝነት የሚሳተፉት አካላትና አባላት እነማን እንደሆኑ ለመለየትና ኃላፊነትን ከባለስልጣንና ከግለሰብ ጋር አጣብቆ ፍርድ ለመስጠት ይመቸዋል፡፡
አንቀጽ 28 በግልጽ እንዳሰፈረው በፀረ ሽብርተኝነት ጉዳዮች ላይ የሚሳተፍ ፖሊስም ይሁን ዓቃቤ ሕግ በክፍሉ ኃላፊዎች ዘንድ ስለታታሪነቱና ብቃቱ የተመሰከረለትና በቂ የስራ ልምድ ያለውና በስራው ስልጠና የወሰደ መሆን እንዳለበት የተጠቀሰ ሲሆን ሁለቱም አካላት ማለትም ፍትሕ ሚኒስቴርና ፌዴራል ፖሊስ የሽብርተኝነትን ጉዳዮች የሚከታተሉ የስራ ክፍሎችን እንደሚያደራጁ:

28. የሽብርተኝነት ድርጊትን ስለሚከታተል ዐቃቤ ሕግና ፖሊስ

1/ በሕግ በተሰጠው ስልጣን መሰረት

የሽብርተኝነት የወንጀል ጉዳይን የሚከታተል ዐቃቤ ሕግ ወይም ፖሊስ፡-

ሀ/ አግባብነት ባለው ሙያ ቢያንስ ከአምስት ዓመት በላይ የስራ ልምድ ያለው፡ በስራው ስልጠና የወሰደና በስራው ታታሪ የሆነ እና

ለ/ እንደአግባብነቱ ከፍትሕ ሚኒስቴር ወይም ከፌዴራል ፖሊስ የበላይ ኃላፊዎች የሙያ ብቃትና የስነ ምግባር ማረጋገጫ ምስክርነት ያገኘ መሆን አለበት፡

2/ የፍትሕ ሚኒስቴር የሽብርተኝነት ጉዳዮችን የሚከታተል የተለየ ክፍል ያደራጃል፡

3/ የፌዴራል ፖሊስ የሽብርተኝነት ጉዳዮችን የሚከታተል የተለየ ክፍል ያደራጃል፡

29. የሽብርተኝነት ጉዳዮች ስለሚከታተሉ የደህንነት ሰራተኞች

በብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የሽብርተኝነት ጉዳዮችን የሚከታተሉ የመስሪያ ቤቱ ሰራተኞችን መርጦ ይመድባል፡፡

የሽብርተኝነት ጉዳይን የሚከታተል የተለየ የስራ ክፍል ያደራጃል፡

30. ስለብሄራዊ የፀረ ሽብርተኝነት አስተባባሪ ኮሚቴ

1/ የሽብርተኝነትን ድርጊት ለመከታተልና ለመቆጣጠር የፍትሕ ሚኒስቴር፡ የብሄራዊ የመረጃ ደህንነት አገልግሎት እና የፌዴራል ፖሊስ የስራ ኃላፊዎችን ያቀፈ ብሄራዊ የፀረ ሽብርተኝነት አስተባባሪ ኮሚቴ ይዋቀራል፡፡

2/ የብሄራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ኮሚቴውን ይመራል፡፡

3/ ኮሚቴው የጋራ የረ ሽብርተኝነት እቅድ ያወጣል፡ የጋራ የፀረ ሽብርተኝነት ግብረ ኃይል በማደራጀት ተቋሞቹ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት የሚያደርጉትን ጥረት በማቀናጀት በጋራና በተደጋጋፊነት እንዲሰሩ ይደረጋል፡፡

በአንቀጽ 29 መሰረት ደግሞ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ሽብርተኝነትን የሚከታተል የስራ ክፍል እንደሚያደራጅና ለዚሁም ሰራተኞችን መድቦ እንደሚያሰማራ፡

በአንቀጽ 30 መሰረት ደግሞ የብሄራዊ የፀረ ሽብርተኝነት አስተባባሪ ኮሚቴ የፍትሕ ሚኒስቴር፡ የፌዴራል ፖሊስና የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ኃላፊዎችን ያቀፈ እንደሚሆን፡ አስተባባሪ ኮሚቴው የጋራ የስራ እቅድ አውጥቶ እንደሚሰራ፡ ኃላፊዎቹ ስራቸውን በቅንጅትና በመደጋገፍ እንደሚሰሩ፡ ኮሚቴው በብሔራዊ መረጃና ደህንነት ኃላፊ እንደሚመራ ይደነግጋል፡፡

ተጠሪነት

ከላይ በሕግ የተቋቋመው የብሄራዊ የፀረ ሽብርተኝነት አስተባባሪ ኮሚቴ ተጠሪነቱ በወቅቱ በስልጣን ላይ ላለው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሌለበት ጊዜ ለምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው፡፡

አዋጁ በ2001 ዓ.ም ወጥቶ አስተባባሪው ኮሚቴ ሲቋቋም በስልጣን ላይ የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ሲሆኑ፡ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደግሞ እንደአግባብነቱና እንደአገልግሎታቸው አቶ አዲሱ ለገሰና አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ናቸው፡፡ ከአቶ መለስ ዜናዊ የነሐሴ 2004 ዓ.ም ሕልፈት በኃላ ደግሞ የአስተባባሪ ኮሚቴው ተጠሪነት ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ (ከደኢሕዴን) እና ለምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን (ብአዴን /አዴፓ) ሆኖ በዚሁ መልክ እስከ መጋቢት 2010 ዓ.ም የዶ/ር ዓብይ አሕመድ የስልጣን ርክክብ ድረስ ይሸጋገራል ማለት ነው፡፡

ከ2001 ዓ.ም አዋጁ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ እስከ መጋቢት 2010 ዓ.ም ድረስ የፍትሕ ሚኒስትር ሆነው ያገለገሉት አቶ ብርሃን ኃይሉ፡ አቶ ጌታቸው አምባዬ (ሁለቱም ከብአዴን/አዴፓ) ሲሆኑ፡ ምክትል ሚኒስትር ደግሞ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ (ከኦሔዴድ/አዴፓ) ነበሩ፡፡

ከ2001 ዓ.ም አዋጁ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ እስከ መጋቢት 2010 ዓ.ም የፌዴራል ፖሊስ ኃላፊዎች የነበሩት ደግሞ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ (ከኦሔዴድ/አዴፓ) እና አቶ አሰፋ ባዩ (ከደኢሕዴን) ናቸው፡፡

ከ2001 ዓ.ም አዋጁ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ እስከ መጋቢት 2010 ዓ.ም የመረጃና ደህንነት ኃላፊ የነበሩት ደግም አቶ ጌታቸው አሰፋ (ከህወሓት) ናቸው፡፡

ስለሆነም የብሄራዊ የፀረ ሽብርተኝነት አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት ሆነው እስከ መጋቢት 2010 ዓ.ም ድረስ የዘለቁትና የተፈራረቁት ከላይ ስማቸው የተጠቀሰው የመንግስትና የፓርቲ የስራ ኃላፊዎች መሆናቸው ነው፡፡

 

የፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ አተገባበር

የፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ ከወጣ በኃላ ከላይ የተጠቀሰው አስተባባሪ ኮሚቴም ይሁን የኮሚቴው አባል መስሪያ ቤቶች ግዳጃቸውን ተወጥተዋል ወይስ አልተወጡም ብለን ስንጠይቅ መልሱ የምናገኘው በሕጉ በተሰጣቸው ስልጣን መሰረት የሰሩትንና ያስገኙትን ውጤት በመገምገም ልንተርክ እንችላለን፡፡ እዚህ ላይ የአስተባባሪው አካል የስራ ኃላፊዎች በሕግ አውጪው ወይም በበላይ አለቃቸው የተሰጣቸውን ሕግ በትክክልና ሳያዛንፉ መተግበር እንጂ ሕጉ ግድፈት ይኑረው አይኑረው እነሱን የሚመለከት ጉዳይ አለመሆኑን ማጤን ያስፈልጋል፡፡ በአዋጁ መሰረት በአሸባሪ ቡድኖችና በደጋፊዎቻቸው ወይም በውጭ ኃይሎችና መንግስታት ጣልቃ ገብነት በአገሪቱና በሕዝቦቿ ጥቅም ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ነቅታችሁ ስሩ፡፡ የሚል ይዘት ያለው ሕግ ነው የተሰጣቸው፡፡ ይህንን ሕግ ተግባራዊ ስታደርጉ በመንግስትና በሕዝብ ንብረት ላይ ወይም በዜጎች ላይ ጉዳት እንዳይደስ ተከታትላችሁ ግዳጃችሁን ፈጽሙ! አንዳችም ፀጥታን የሚያደፈርስ ኮሽታ መሰማት የለበትም! የሚል ቀጭን ትእዛዝ ተሰጥቶዋቸው ሲሰሩ የከረሙ ስለሆነ ከዚህ ቀጭን ትእዛዝ አንጻር ምን ሰሩ? ምንስ አሳኩ? ምንስ ሳይሳካላቸው ቀረ? የሚሉትን ጥያቄዎች በመመለስ የስራ ተግባራቸውን መመዘን ይቻላል፡፡

በመሰረቱ እውነት እንናገር ከተባለ የኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይሎች ከ2001 ዓ.ም አዋጁ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ በሕዝብ ተወካዮችና በአዋጁ እንዲሁም በመንግስት ውሳኔ አሸባሪዎች የተባሉትን ቡድኖችንና አባላቱን እንዲሁም ተጠርጣሪ ግለሰቦችን ተከታትሎ ለሕግ በማቅረብ የተዋጣለት ስራ አከናውነዋል ብንል ስሕተት አይሆንም፡፡ ሆኖም በአዋጁ ግድፈት ምክንያት የግለሰቦች መብት ተረግጦ ከሆነ ተጠያቂዎቹ ከላይ በሕግ ስልጣን የተሰጣቸው አካላት ወይም ኃላፊዎች ወይም ሰራተኞች ሳይሆኑ በዋናነት ተጠያቂ የሚሆነው ሕጉን ያወጣው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 547 አባላት እንጂ የስራ ኃላፊዎቹ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ምክንያቱም የስራ ኃላፊዎቹና ሰራተኞቻቸው እንደአንድ በግዳጅ ላይ የሚሰማራና ጥያቄ መጠየቅ የማይቻለው ወታደር ተደርገው ነው መወሰድ ያለባቸው፡፡ ምናልባት ሕግ አውጪው ባይጠየቅም እንኳን ጠቅላይ ሚኒስትሩና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያሉበት የስራ አስፈጻሚ አካል ወይም ካቢኔ ከአስተባባሪው ኮሚቴ በበለጠ ከፍተኛውን ኃላፊነት የሚወስድ መሆኑን መዘንጋት አይገባም፡፡

አስተባባሪው ኮሚቴ በስራ ሂደቱ፡-

-   በየጊዜው በአገሪቱ ላይ አደጋ ለማድረስ ከጎረቤት አገራት ፈንጂ ይዘው ባዲስ አበባና በሌሎች ከተሞች በመንግስታዊና በሕዝባዊ ተቋማት ብሎም በግለሰብ ሕይወት ላይ አደጋ ሊያደርሱ የተንቀሳቀሱ አሸባሪዎችን ተከታትሎ በመያዝ እፁብ ድንቅ የሆኑ ተግባራትን ሲያከናውኑ መክረማቸውን መዘንጋት አንችልም፡

-   ከኤርትራ መንግስትና በዚያች አገር ከለላ ባገኙት ቡድኖች ተልእኮ እየተሰጣቸው ወደ ኢትዮጵያ ሾልከው እየገቡ አደጋ ሊያደርሱ የነበሩትን ቡድኖችና ግለሰቦችን ከመቅጽበት ተከታትሎ በመያዝና ለሕግ በማቅረብ ከፍተኛ አስደናቂ የደህንነት ተግባራትን አከናውኗል፡፡

-   ከሌሎች ዓለም አቀፍ የደህንነትና የፖሊስ ተቋማት ጋር በመቀናጀት እነአንዳርጋቸው ፅጌ የመሳሰሉትን በወቅቱ የአሸባሪ ቡድን መሪዎችን ከየመን ሰንዓ ድረስ ሄደው ጠልፈው በመያዝ ድንቅ ግዳጃቸው ፈጽሟል፡፡ ወዘተ...

እንግዲህ ባሁኑ የለውጥ ጊዜ መነጽር እንመዝነው የሚል የተሳሳተ ምዘና ካልወሰድን በስተቀር ከላይ የተጠቀሰው አስተባባሪ ኮሚቴ እስከ መጋቢት 2010 ዓ.ም ግዳጁን በሕጉ መሰረት በመፈጸም ያገሪቱንና የሕዝቦቿ ደህንነትን በቅጡ አስጠብቀዋል ብለን ለመደምደም እንችላለን፡፡

 

የሰብአዊ መብት ረገጣና ፈጻሚዎቹ

በመሰረቱ አዋጁ በሕገ መንግስቱ ላይ ከተቀመጡት የሰብአዊ መብት አያያዝ ድንጋጌዎች አንጻር ሲመረመር ግድፈቶች እንደነበሩበት ግልጽ ነው፡፡ ሆኖም ግን አዋጁን ያወጣው አካል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስለሆነ ሕግ አውጪው አካልን ለምን ከህገ መንግስት ድንጋጌዎች ጋር የሚጣረስ አዋጅ አወጣህ? ብሎ የጠየቀው አካል የለም፡፡

አገሪቱን ለረጅም ዓመታት ሲመራ የቆየው የኢሕአዴግ መንግስት እንደመሆኑ መጠን በዚህ ሂደት ውስጥ በተለይም ከ2006 ዓ.ም ወዲህ የኢሕአዴግ መንግስት ጥርስ አውጥቶ ሲናከስ እንደከረመና ይባስ ብሎም በማንአለብኝነት የፀረ ሽብር ሕጉን በመለጠጥ የዜጎችን መብት ሲጋፋ እንደነበረ ያደባባይ ሚስጢር ነው፡፡ በተለይም በሚልዮኖች የሚቆጠሩ የዩኒቨርሲቲዎች፡ የቲቪኢቲ፡ የ12ኛና የ10ኛ ክፍል ተመራቂዎችና ወጣቶች በእቅድ መሰረት ወደ ስራ ለመሰማራት የሚያስችላቸው ሁኔታ ስላልተመቻቸና የሚመለከታቸው የክልል መንግስታትም ይሁኑ የፌዴራሉ መንግስት ተዘጋጅቶና ስርዓት አበጅቶ ስላልቆየ የስራ ፈላጊ ወጣቶች ቁጥር በሚልዮኖች የሚቆጠርና ለአመጽ የሚያነሳሳ ሁኔታ ስለተመቻቸ በኦሮሚያ፡ በአማራ፡ በደቡብና በሌሎችም ክልሎች የስራ መፍታት ብሶት ፖለቲካዊ ሽፋንና ገጽታ እየያዘ መቀጠሉ አልቀረም፡፡ ይህም አመጽና ተቃውሞ ትርጉሙ እየተለጠጠና የአሸባሪ ቡድኖች እጅ እንዳለበት ተደርጎ እየተወሰደ በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ወደ እስር ቤት እንዲወረወሩና ባልፈጸሙት ጉዳይ የአሸባሪነትና የተቃዋሚ ቡድኖች ስም እየተለጠፈባቸው ፍዳቸውን ስያዩ እንደነበር ይታወቃል፡፡

የኢሕአዴግ መንግስት የወጣቶችን የስራና በኢኮኖሚው የመጠቀም የመብት ጥያቄዎችን መመለስ ሲያቅተውና ራሱም የመልካም አስተዳደር ኃላፊነቱንና የዲሞክራሲ ምሕዳሩን ማስፋት ሲያቅተው የፀረ ሽብርተኛ አዋጁን በመለጠጥና ሕገ መንግሰታዊ መብቶችን በሚጋፋ መንገድ በስፋት በመንቀሳቀስ የወጣቱን አመጽና ተቃውሞን ለማርገብ በማለም ሰብአዊ መብቶችን የሚጥሱ ተግባራትን ከመፈጸም አልታቀበም፡፡ እልፍ ብሎም አመጹንና ተቃውሞውን ያረገበ መስሎት የአስቸኳይ አዋጅን ካንዴም ሁለቴ በማወጅ የኃይል እርምጃውን አጠናክሮ ለመቀጠል ሲኳትን ታይቷል፡፡ በስተመጨረሻውን ግን አካሄዱና አገዛዙ ስሕተት ያለበት መሆኑን ተገንዝቦ

በድርጅቱ ቋንቋ ጥልቅ ተሐድሶ አድርጊያለሁ! ሁሉም ጥፋት የአመራርና የኔ ጥፋት ነው! የሚል ንስሐ መሰል እምነት በይፋ አውጆ ሲያበቃ በእስር ያሉትን የፖለቲካና የሰብአዊ መብት እስረኞችን እንደሚፈታ፡ የዲሞክራሲ ምሕዳሩን እንደሚያሰፋ፡ ከኤርትራ ጋር የቆየውን ፍጥጫ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እንደሚንቀሳቀስ፡ ለወጣቶች በሚጠቅም መልኩ የስራ ፈጠራ ሂደቱን እንደሚያጠናክር፡ ወዘተ በሚሉ ጉዳዮች ላይ ተጠናክሮ እንደሚሰራ በመግለጽ ለመንቀሳቀስ መወሰኑን ገልጾ አመራሩንም ከአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ወደ ዶ/ር ዓብይ አሕመድ ማሸጋገሩን ገልጾ ከመጋቢት 07/2010 ዓ.ም በኃላም ቢሆን አገሪቱን መምራት ቀጥሏል፡፡

የተጠያቂነት ወሰን

ኢሕአዴግ በቁንጮው የአመራር ለውጥ ያድርግ እንጂ በውስጡ ጤናማ እንዳልነበር ከጅምሩ በአካሄዱና በመሪው መግለጫዎች ያስታውቅበት ነበር፡፡ ከጅምሩ በድርጅቱ ውስጥ በነበረው አለመግባባት ምክንያት ለውጥን የሚፈልግ በቲም ለማ መገርሳ የሚመራ ቡድንና በሌላም በኩል ለውጥን በማይፈልግ የቀድሞው አመራር መካከል ውስጣዊ ትግል ይካሄድ እንደነበርና በስተመጨረሻውም የለውጥ ኃይሉ? አሸንፎ እንደወጣና ሁሉም የተከናወኑት ድርጊቶች ማለትም የእስረኞች መፈታት፡ የተቃዋሚዎች ከውጭ እንዲገቡ መፍቀድ፡ የሚድያው ምሕዳር መስፋት፡ ከኤርትራ ጋር የተፈጸመው አዲስ ግንኙነት ወዘተ ሊፈጸሙ የቻሉት በለውጥ ኃይሉ ውስጣዊ ትግል እንደሆነ ተደርጎ አዲስ ትርክት እንዲነገርና ተቀባይነት እንዲያገኝ የፖለቲካ ፈጠራ ተሰርቷል፡፡ ይህም በመሆኑ የኦሔደድና የብአዴን አንዳንድ አመራሮች የለውጡ ሃወርያት እንደሆኑ፡ የደኢሕዴን አንዳንድ አመራሮች ደግሞ የለውጡ ደጋፊዎች አንደሆኑ ተደርገው የፖለቲካ ስእል የተበጀ ሲሆን የለውጡ ሁነኛው ተቃዋሚ ደግሞ የህወሓት አመራሮች እንደሆኑ ተደርገው ተፈርጇል፡፡ የዚህ ዓይነት የፖለቲካ ቁማር ደግሞ በህወሓት በኩል ለውጥ እንዲደረግ የወሰንነው ሁላችንም አራት የኢሕአዴግ እህት ድርጅቶች ነን እንጂ በተወሰኑ ድርጅቶች ብቻ ለውጥ እንዲመጣ ተደርጓል የሚለው አባባል የፈጠራ የፖለቲካ ትርክት እንጂ እውነትነት የለውም! ይህ ዓይነት አካሄድና ትርክት በኢሕአዴግ ውስጥ ክፍፍልን የሚፈጥርና የፖለቲካ ክህደትን የሚያመላክት ነው የሚል አቋም በመያዝ ሲቃወሙት ከርሟል፡፡

በኦሔዴድና በብአዴን ማለትም ባሁኖቹ አዴፓና አዴፓ በኩል ግን የህወሓትን አቋም ባለመቀበል አሁንም የለውጥ ኃይሎቹ እኛ ነን! የሚለውን ትርክት በሚቆጣጠሩዋቸው ሚዲያዎችና በነኢሳትም ጭምር ሲስተጋቡ ከርሟል፡፡ ይህም በመሆኑ በኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች መካከል መግባባት ሊፈጠር ባለመቻሉ ምክንያት የተለያዩ አገራዊና ሕዝባዊ ችግሮች ሲፈጠሩ በአፈታታቸውና በአመራራቸው ዘንድ አንድ ወጥ የሆነ መርሐ ግብር ለመያዝ ባለመቻሉና መንግስትን በመምራት ላይ ያለው ኢሕአዴግ በውስጡ መናበብ ሊፈጠር ባለመቻሉ ምክንያት በአገሪቱ ውስጥ ማሕበራዊ፡ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውሶች ሲከሰቱ ከርሟል፡

አሁንም በመከሰት ላይ ናቸው፡፡ በመሆኑም ባሁኑ ወቅት ከ3 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ይገኛሉ፡ ኢኮኖሚው እያሽቆለቆለ ይገኛል፡ የፖለቲካ አካሄዱ ቅጥ አምባሩ ጠፍቷል፡ ከኤርትራ ጋር የተጀመረው ግንኙነትም ወዴት እንደሚያመራ አልለየለትም፡ ወዘተ፡፡

የኢሕአዴግ የፖለቲካ ልዩነት እየሰፋ እንዲመጣ ያደረገው አንዱ መገለጫው ደግሞ ልዩነቱ የለውጥ ኃይሎች ነን የሚሉትና በዶ/ር ዓብይ አሕመድ የሚመሩት ወገኖች ያለፈው 27 ዓመታት የጨለማ ጊዜ ነበር የሚልና በእውነታ ላይ ያልተመሰረተ አቋም ይዘው ብቅ ማለታቸው ሲሆን የዚህ ጨለማ የሚሉት ጊዜ ኃላፊቱን የሚወስደው ህወሓት ነው! በሚል ትርክት ፖለቲካውን ማጦዛቸውና የፖለቲካ ድራማ ለመስራት መንቀሳቀሳቸው ነው፡፡ የብአዴን/አዴፓ አመራሮች የአማራ ክልል ባለፉት 27 ዓመታት በህወሓት ተላላኪዎች ነበር የሚመራው በሚል ትርክት የቀድሞ አመራሮቹን በማባረርና በማሰር በመንቀሳቀስ ላይ ሲገኙ፡ የኦሕዴድ/አዴፓ አመራሮች ደግሞ የቀድሞዎቹን አመራሮች ጠራርገው በማውጣት በኦሮሞ ከልል ለወጣቱ ስራ ያልተፈጠረው በህወሓት አመራር ምክንያት ነው፡ በኦሮሚያ እስከ 30 ሺሕ ሰዎች የታሰሩት በህወሓት አማካይነት ነው፡ ስለሆነም የለውጥ ኃይሎች ሆነን ታግለንልሃል፤ ወዘተ በሚል ትርክት ሕዝቡንና ወጣቱን ሲመግቡት ከርሟል፡፡ የራሱ ትርክት መፍጠር ያልቻለው የደኢሕዴን አመራር ግን ባድር ባይነት ለስልጣኑና ለጥቅሙ ሲል ከለውጥ ኃይል ነን ባዮች ጋር ሲሰለፍ ከርሟል፡፡

የለውጥ ኃይል ነኝ ባዩ ቡድን ትርክቱን ከመሬት ላይ ለማውረድ እንዲመቸው በመመኘት ጨለማ ብሎ ለሰየመው ጊዜ ተጠያቂን ለመሰየም ከፍተኛ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ከርሟል፡፡ በመጀመሪያ የለውጡ መሪ ዶ/ር ዓብይ አሕመድ በሰኔ ወር 2010 ዓ.ም ፓርላማ ውስጥ ተገኝተው ያገሪቱ ፖሊስ ከጣቢያ ጀምሮ እስከ ፌዴራል ድረስ ሰውን ያስርና ይገርፍ ስለነበር አሸባሪ ነው! ብለው የፈረጁት ሲሆን ከዚሁ ጋር በተያያዘም የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅን ሲያስፈጽሙ የነበሩት አካላትና ሰራተኞችም ምንም ጥናት ባልተደረገበትና ባልተገራ የፖለቲካ አገላለጽ አሸባሪዎች እንደሆኑ ተርኳል፡፡ ከዚያ በመቀጠልም በቅድሚያ የወሰዱት እርምጃ የፌዴራል ፖሊስ፡ የመረጃና ደህንነትና የኢንሳ ኃላፊዎችንና ሰራተኞችን ስለድርጊታቸው ምንም ማጣራት ሳይካሄድ ወደ እስር መወርወር ነበር፡፡

የዶ/ር ዓብይ አሕመድ መንግስት የብሄራዊ የፀረ ሽብርተኝነት አስተባባሪ ኮሚቴ አባል አካላት የነበሩትን የፌዴራል ፖሊስ፡ የመረጃና ደህንነትና የፍትሕ ሚኒስቴርን ተጠያቂ ለማድረግ ሲንቀሳቀሱም ሚዛናዊ ትኩረትና አፈጻጸምን መሰረት አድርገው ሳይሆን የጨለማው ጊዜ ተጠያቂው ህወሓት ነው የሚለውን ትርክት እንደመነሻነት በመያዝ ባብዛኛው ወደ እስር ቤት እንዲወረወሩ የተደረጉት የትግራይ ተወላጆችና የህወሓት ደጋፊዎች የሆኑትን በመለየት ነው፡፡ በመሆኑም ባሁኑ ወቅት በመከናወን ላይ ባለው የፍርድ ሂደት የጨለማው ጊዜ ተጠያቂዎች ተደርገው ክስ እየቀረበባቸው የሚገኙት ሰራተኞች እነዚህ በብሄር ማንነታቸው በተለዩት የትግራይ ተወላጆች ላይ ነው፡፡ ለዚሁም እንደ አንድ መቋጫ እስራት ተደርጎ እንዲፈጸም

እየተፈለገ ያለው ሰው ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርነው የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ኃላፊ የነበረው አቶ ጌታቸው አሰፋ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

በመሰረቱ በኦሮሚያ፡ በአማራ፡ በደቡብ፤ በሶማሊ ወዘተ ክልሎች ከፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ ጋር በተያያዘ አግባብ ያልሆነ እስራት ተፈጽሞ ከሆነ ተጠያቂ መሆን የሚችለው በክልል ደረጃ የክልሉ አስተዳደርና ፖሊስ፡ በፌዴራል ደረጃ የብሄራዊ የፀረ ሽብርተኝነት አስተባባሪ ኮሚቴ አካላትና አባላት ናቸው ሊሆኑ የሚችሉት፡፡ ከዚህ ውጭ ህወሓት ነው በኦሮሚያ፡ በአማራ፡ በደቡብና በሶማሊ ወዘተ ሲያስር የነበረው የሚለው ትርክት ግን የውሃ ቋጠሮ ሊኖረው አይችልም፡፡

የዶ/ር ዓብይ አሕመድ መንግስት ቅንጣት ታክል ትክክለኛ ፍርድ የመስጠት ፍላጎትና አቋም ቢኖረው ኖሮ ግን አቶ ጌታቸው አሰፋን ብቻ ለይቶ ለማሰር አደን ውስጥ ከሚገባ በወቅቱ የፌዴራል ፖሊስ ኃላፊዎች የነበሩትን እነዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁን፡ እነ አቶ አሰፋ ባዩን፡ ከፍትሕ ሚኒስቴር በወቅቱ ኃላፊዎች የነበሩት እነ አቶ ጌታቸው አምባዬን፡ እነ አቶ ብርሃን ኃይሉን፡ በወቅቱ የፍትሕ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር የነበሩትንና አሁን ጠቅላይ ዓቃቢ ሕግ የሆኑትን አቶ ብርሃኑ ፀጋዬንም እንደ አቶ ጌታቸው አሰፋ ሁሉ ተጠያቂዎች ናቸው ብሎ ክስ ማቅረብ በተገባው ነበር፡፡ ነገር ግን የነዶ/ር ዓብይ አሕመድ አካሄድ ፍትሕን የማረጋገጥና የማስፈን ጉዳይ ሳይሆን የብቀላና የፖለቲካ ቁማር የመጫወት ጉዳይ ስለሆነ ነገር ዓለሙ ሁሉ ፍየል ወዲያ ቅዝምዝም ወዲህ! ሆኖ ይታያል፡፡

የተጠያቂነት ጉዳይ በትክክል ይነሳ ቢባል ከፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ ጋር በተያያዘ ተጠያቂ መሆን ያለባቸው አካላት ከስልጣን ደረጃቸው ጋር ተያይዞ ሲመዘን በተዋረድ ቅደም ተከተል የሚከተሉት አከላትና ባለስልጣናት መሆን ነበረባቸው፡፡

1.   አዋጁን ያወጣው የተወካዮች ምክር ቤትና 547 አባላቱ፡

2.   ለአፈጻጸሙ ኃላፊነቱን ወስዶ የተንቀሳቀሰው የሚኒስትሮች ምክር ቤትና አባላቱ፡

3.   የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ፡

4.   የወቅቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ አዲሱ ለገሰ ወይም አቶ ደመቀ መኮንን፡

5.   የብሄራዊ የፀረ ሽብርተኝነት አስተባባሪ ከሚቴ አባላትና ኃላፊዎች የነበሩት፡

5.1.     እነ አቶ ጌታቸው አሰፋ ከመረጃና ደህንነት ኤጄነሲ፡

5.2.እነ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ፡ አቶ አሰፋ ባዩ፡ ከፌዴራል ፖሊስ፡

5.3.እነ አቶ ብርሃን ኃይሉ፡ አቶ ጌታቸው አምባዬ፡ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ፡ ከፍትሕ ሚኒስቴር፡

6. ከላይ በቁጥር 5 በተጠቀሱት መስሪያ ቤቶች ስር ሲሰሩ የነበሩት የዳይሬክተሮችና የመምሪያ

ኃላፊዎችና የተዋረድ አካላት የስራ ኃላፊዎች፡

7.   የቁጥር 5 ፈጻሚ ሰራተኞች፡፡

ምክረ ሐሳብ

የዶ/ር ዓብይ አሕመድ መንግስት ከላይ ከተጠቀሰው የፍርድና የፍትሕ ሂደት ውስጥ እጁን በንጽሕና ለማውጣት ከፈለገ መስራት ያለበት በሰዎች ሰብአዊ መብት ላይ ሆን ብለው ጉዳት ያደረሱትን በመለየት የፍርድ ሂደቱን ማስቀጠል አንድ ጉዳይ ሆኖ በጥርጣሬ ብቻ ለእስር የዳረጋቸውን የፌዴራል ፖሊስ ኃላፊዎችንና አባላትን፡ የመረጃ ደህንነት ኃላፊዎችንና አባላትን፡ የክልሎች የፖሊስና የፀጥታ አባላትን ባስቸካይ ከእስር ቤት ሊለቃቸው ይገባል፡፡ ለምን ቢባል ከላይ በዝርዝር በስልጣን ተዋረድ ደረጃ ተጠያቂ ሊሆኑ ይችሉ የነበሩትን አካላትና አባላትን ለመክሰስ የማይቻል መሆኑ ግልጽ ስለሆነና ሁሉም አካላትና አባላት ባንድ አቋምና አንደበት ይቅርታ እንጠይቃለን! ተብለው መታለፍ ስላለባቸውና ላሞች ባልዋሉበት ኩበት መልቀም አይቻልምና!

ቸር ይግጠመን!

 


Back to Front Page