Back to Front Page

የመደመር ቀለም አብዮትና መዘዙ፡ ክፍል ሁለት

የመደመር ቀለም አብዮትና መዘዙ፡

በትግራይ ህዝብ ላይ ያነጣጠረ እንደገና አዲስ የቀለም አብዮት እየተሸረበ ነው!

 

ክፍል ሁለት

ዑስማን ሙለዓለም ከሐራ ገበያ

መስከረም 2012 ዓ/ም

 

 

የቀለም አብዮት ሙከራዎችና ውጤቱ በኢትዮጵያ

የቅድመ ቀለም አብዮት ሁኔታ

በአገራችን የፋሽስት ደርግ ስርዓት በኢትዮጵያ ህዝቦች ትግልና መስዋእትነት በ1983 ግንቦት 20 ተገረሰሰ፡፡ ከሽግግሩ ወቅት ጀምሮም የመረጋጋት፣ የሰላም፣ የዴሞክራሲና የተስፋ ብርሃን መታየት ጀመረ። ያኔ ደርግ በአስገዳጅነት የመሰረተው ሰራዊት ወደ ሚልዮን የሚጠጋ ነበር። እዚህ ላይ በግልፅና በማያሻማ መልኩ መገለፅ ያለበት ጉዳይ አለ፡፡ የደርግ ርዝራዦች በውዴታ ያላሰለፉትን፣ የህዝብን ጥያቄ ለመጨፍለቅ መሳርያ አድርገው የተጠቀሙበትንና ስልጣናቸው ለማራዘሚያ የሚዋጋ የግዳጅ ሰራዊትን የደርግ ሰራዊት አትበሉ ይላሉ፡፡ ነገር ግን በምን መለከያ የኢትዮጵያ ሰራዊት እንበለው ቢባሉ ብቁ መልስ የላቸውም። ሐውዜን ላይ በገበያ ቀንና በጠራራ ፀሓይ ህዝብን በአውሮፕላን ቦምብ የሚደበድብ የደርግን ሰራዊት ከማለት ውጭ የኢትዮጵያ ህዝብ ሰራዊት ነበር ብሎ ለሐውዜን ኢትዮጵያዊ ማሳመን እንዴት ይቻላል? ለኔ በፍፁም አይቻልም ነው፡፡

 

ድህረ ደርግ የኢትዮጵያ ሽግግር መንግስት የመራው ኢህአዴግ ጠላቱን እና ወዳጅን በደንብ ለይቶ ያውቅ ነበር፡፡ ደርግ በሐይል ከወላጆቻቸውና ከቤተሰቦቻቸው ቀምቶና አስገድዶ ወታደር ያደርጋቸውን እንደ ጠላቱ ያየበት ሁኔታ አልነበረም፡፡ ኢህአዴግ ወታደሮቹ እንደ ዜጎች ብቻ ሳይሆን እንደ ወዳጅ የህዝብ አካል በመውሰድ ወደ ሲቪልነት የሚቀየሩበትና መልሰው ኑሯቸውን የሚመሰርቱበት ዓላማ ይዞ ነበር የተንቀሳቀሰው፡፡ ይህንን ስራ የሚመራ መስርያ ቤት አደራጅቶ የተሃድሶ ስልጠና በመስጠት ወታደሮቹ በአጭር ጊዜ ራሳቸውን እንዲያቋቁሙ ማድረጉ በታሪክ የሚወሳ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች አገሮችም ጥሩ ልምድና ተሞክሮ ሆኖ አገልግሏል።

 

ኢህአዴግ ከደርግ በኃላ የደርግን ፋሽስት መንግስት ያሸነፍኩት ወይም የአንበሳው ድርሻ ሚና የነበረኝ እኔ ነኝ ብሎ ስልጣን ለብቻየ አላለም፡፡ ደርግን በተለየ ዓላማ ቢሆንም አብሮት እንደ ተዋጋው የኢሳያሱ ሻዕብያ/የበኃላው ህግደፍ ስልጣንን ያለ ህዝቡ ምርጫ ብቻየ ልቆጣጠር አላለም። ኢህአዴግ ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በመሆን አገሪትዋ በቻርተር በጋራ የሚያስተዳደሩበት ሁኔታ ፈጠረ። በህዝቡ ፍቃድ ላይ የተመሰረተ መንግስት ለመገንባት ደግሞ በወቅቱ በቻርተር አገሪቷን ሲያስተዳድሩ የነበሩት ድርጅቶች በጋራ የህገ መንግስት አርቃቂ ኮሚሽን አቋቋሙ። አቶ ክፍሌ ወዳጆም ኮሚሽኑን እንዲመሩ ተደረገ፡፡ አቶ ክፍሌ ኒውዮርክ ሆነው ደርግን ሲቃወሙ የነበሩ አገር ወዳድ ሙሁር ነበሩ። ኮሚሽኑም አንባቢና ዕድሜ ጠገቡ አቶ ክፍሌ እየመሩት ዘመናዊና ወቅታዊ፣ የኢትዮጵያ ሁኔታ መሰረት ያደርገና አለም አቅፍ ሕግጋትን ያከበረና የሚያኮራ የህገ መንግስት ማርቀቅ ስራ ሰራ። ህገ መንግስቱ ልሂቃን አወጡት ተብሎ ይፅደቅ አልተባለም። በገጠርም በከተማም ህዝቦች በየአካባቢው ጥልቅ ውይይትና ክርክር አደረጉ። በመጨረሻም ህዝቦቹ ተወካዮቻቸው በመላክ (ህገ መንግስቱ ሲፀድቅ ከኦሮሚያ ክልል ከባሌ ገጠር አካባቢ የመጡ ሙስሊም ሽማግሌ አባት በደስታ ሲዘሉ በተደጋጋሚ በቴሌቭዥን ተቀርፀው የሚታዩት ዓይነቶች ሳይቀሩ ተሳትፈው) ያፀደቁት ህገ መንግስት ፀደቀ።

 

ምርጫም በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ተካሂዶ የተመረጠ መንግስት የሚያስተዳድር አካል በህዝቦች ፍቃድ በፌደራልም በክልሎችም ተመሰረተ። ህዝቦች ለመጀመርያ ጊዜ ራሳቸውን በወኪሎቻቸውና በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መተዳደር ጀመሩ። ዲሞክራሲ በተግባር ተጀመረ። የመደራጀት መብት፣ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትና የመፃፍ መብት በህዝብ ትግል ተረጋገጠ። ጋዜጦችና መፅሔቶች እንደአሸን ፈሉ። ኢትዮጵያ ዴሞክራሲ እየተጠቀሙ ዴሞክራሲ የለም ብለው መናገር፣ መፃፍና በአደባባይ መቃወም የሚቻልበት አገር ሆነች። የፋሽስትን ደርግ ታሪክ በአወንታ ለማቅረብ ጭምር የሚፈቅድ ስርዓት ተፈጠረ። ጀርመናዊያን እሰከአሁን ድረስ የፋሽስት ሂትለር ናዚ ፓርቲ አባላትን የመደራጀት መብት አግደዋል። የናዚን የሂትለርን ስርዓት ማወደስ ጀርመኖች ከልክለዋል። ይሁን እንጂ አንድን ትውልድ ሙሉ የጨፈጨፈው የኮ/ል መንግስቱ ኢሰፓ ፓርቲ አባላትና የፋሽስት ደርግን ታሪክና የጨካኙ መሪ ታሪክ ማወደስ መደራጀት መብት የማይገድብ ዴሞክራሲ ኢትዮጵያ ላይ በህገ መንግስቱ እውን ሆነ። የኢሠፓ አባላት የነበሩ እነ ሃይሉ ሻውል፣ ሃይሉ አርአያ፣ ኢንጅነር ግዛቸውና፣ ደበበ እሸቱና መቶ አለቃ ሲሳይ አገኔ ተቃዋሚ ድርጅት ፈጥረው እንዳሻቸው የፈለጉትን ሃሳብ እየገለፁ ተደራጅተው በምርጫ ተወዳደሩ። የመሰላቸውን ተቃወሙ። መብት ያጎናፀፋቸውን ህገ መንግስት ሁሉ መተቸትና መቃወም ቻሉ።

 

ነግር ግን ምንም እንደማይባሉ ሲያቁ መብታቸውን ባለጉበት፡፡ከህግ ውጭ ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጭ በህገ መንግስቱ የተከለከለውን በተግባር መጣስ ጀመሩ። በህግ ሲጠየቁ ጋዜጠኛ/ፖለቲከኛ ታሰረና ተጠየቀ ማለት ጀመሩ። በምርጫ ትተው በሁከት ከህዝቡ ድምፅ ውጭ ስልጣን እየተመኙ በህግም ከህግ ውጭም ካልተጫወትን በሚል ተንቀሳቀሱ። የተጀመረውን ሰላም፣ መረጋጋት፣ ዲሞክራሲ፣ ልማትና ዕድገት ለማንቋሸሽ ህግና ህገወጥነት እያጣቀሱ መሄዱን መረጡ።

 

በዚህ ወቅት አክራሪው የኒዮ ሌበራል ሐይል የኢትዮጵያን መንግስት የፖሊሲ ነፃነትና በራስ መተማመን (በሌላ አጠራር ለጌቶች ምክርና ትዕዛዝ ሳትቀንስ መቀበል ላይ የማይተጋው) በህዝብ የተመረጠው የኢህአዴግ መንግስት አልዋጥ ይላቸው ጀመር። አክራሪ ኒዮ ሌበራልስቶቹ እሱ ሲፈቅድ የሚተባበረን ሲቃወም ደግሞ ድህነታችን ይዘን ክብራችንና ሉዓላውነታችን እንመርጣለን የሚለውን ኢህአዴግ ማንበርከክ ወይም መጣል የሚል ግብ ይዘው ሙከራዎች ማድረግ ጀመሩ። አክራሪዎቹ ኒዮ ሌበራሎች ኢህአዴግን መንቻካ የሚል ስም አውጥተውለት ነበር፡፡ የሰራቸው በጎ ተግባራትም የማያሞጉሱት በዚህ ቅሬታቸው እንደሆነም ይታወቃል፡፡

 

ይህም ሆኖ የኢትዮጵያ መንግስት አክራሪ ካልሆኑት ሌበራል የምዕራብ አገራት መንግስታት አመራር በመተባበር ከልብ የሚሰራቸው ስራዎች ነበሩ፡፡ ለምሳሌ በትምህርት፣ በጤና፣ በድህነት ቅነሳ፣ በዲሞክራሲ፣ በፀጥታና ድህንነት ስራዎችና ሌሎች በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች በመንግስታቱ ምስጋና እየተቸረው ነበረ። የሚያበረታታ ድጋፍም ይደረግለት ነበር። በኢትዮጵያ መንግስት በወቅቱ የነበረ የውስጥ ስራ ስኬታማ መሆኑ ተያይዞ የውጭ ስራውም ስኬታማ በመኖሩ ትብብሩ ወደ ላቀ ደረጃ ደርሶ ነበር። በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ የሁሉም የምዕራብ አገሮች መሪዎች ኢትዮጵያን የሚጎቡኝበት ሁኔታ ተፈጠረ። የምስራቁ ዓለም መሪዎቹም በተመሳሳይ የሚጎበኟት አገር ኢትዮጵያ ሆነች። በመሆኑም አክራሪዎቹ ኒዮ ሊበራሎች የተመቻቸ ሁኔታ ሳያገኙ ቀሩ። ሙከራቸውን ግን አላቋረጡም ነበር።

 

የ1997 ምርጫ ወቅት ያልተሳካና ስም ያልወጣለት የቀለም አብዮት ሙከራ

ብዙ ጊዜ የቀለም አብዮት ሲካሄድ ወይም ከተካሄደ በኃላ ስም ይወጣላቸዋል። በአገራችን ኢትዮጵያ የ1997 ዓ/ም የቀለም አብዮት ሙከራ መጠርያ የቀለምም ይሁን የወቅት ወይም በሌላ መንገድ ስም አልወጣለትም።

 

ሙከራው የተደረገውም የከሸፈውም ምክንያት በህዝብ ተመርጦ ሲያስተዳድር በቆየው ኢህአዴግ ውስጣዊ ሁኔታ ጋር የተያያዘ ነው። ሙከራው የተደረገው በኢህአዴግ ውስጥ በነበረው ድክመት ምክንያት ምቹ ሁኔታ በመፈጠሩ ነበር። ሙከራውም የከሸፈውም ኢህአዴግ ድክመትም ቢኖረውም ለማረምም ዝግጁነትና ብቃትም ስለነበረው ነበር፡፡ በውቅቱ የውስጥ ችግሩን በራሱ ፈቶ ህዝቡን ለማገልገል ቁርጠኛም ስለነበረና ህብረተሰባዊ መሰረቱም ጠንካራ ስለነበረ ተንገዳገዶ ትምህርት ወሰደበት እንጂ ሊወድቅ አልቻለም።

 

የያኔው የቀለም አብዮት በአዲስ አበባና በአማራ ክልል ከተሞች ካልሆነ በስተቀር ከዛ ያለፈ ስፋት አልነበረውም። ሆኖም ግን ዘረኛና የኢንተርሃሞይ ባህሪ የነበራቸው መፈክሮችን አንግቦ የመንግስት ስልጣንን ህገ መንግስታዊ ባልሆነ ነውጥና ግርግር ፈጥሮ ለመቆጣጠር ወይም ለመካፈል ዓላማ ያደረገ ነበር፡፡ ለዚህም የወጣቶች ሞት አቅዶና አስልቶ፡፡ ይህን ያህል ወጣቶች አስገድለን ስልጣን በሐይል ቀምተን እንይዛለን የሚል ፍልስፍናና ዕቅድ የነበረው ያልተሳካ ቀለም አብዮት ነበር። የቀለም አብዮቱ ባለቤቶች ይህን ወደ አገራችን የላኩት አብዮት (exported revolution) ቢከሽፍባቸውም አክራሪ ኒዮ ሌበራሊስቶቹና ተላላኪዎቻቸውም ትምህርት ያገኙበትና በቀጣይ ለሚሰሩት ቀለም አብዮት ዕቅድ ልምድ የገበዩበት ሙከራ ነበር።

 

የ2007 - 2010 ዓ/ም የመደመር ቀለም አብዮት

ኢህአዴግ ከ1997 ዓ/ም የቀለም አብዮት ሙከራ ከፈፃሚዎቹ በላይ ውስጡን ፈትሾ ትምህርትና ልምድ አግኝቶ ነበር፡፡ ለተፈጠረው የውስጥ ችግር መፍትሔው ውስጣዊ ጥንካሬውን መጠበቅ እንዳለበት ተገንዝቦ ነበር፡፡ የህዝብ ወገንተኝነቱን ማጠናከር፣ ለህዝብ የገባውን ቃል ማክበርና ህዝብን እያዳመጠ የህዝብን ጥያቄና ፍላጎት መመለስና ሟሟላት እንዳለበት ተረዳ፡፡ መሰረታዊ መፍትሔውም ፈጣን ዕድገት ማምጣትና ድህነትን በከፍተኛ ደረጃ መቀነስና ብሎም ማጥፋት መሆኑን ተገንዝቦ በመስራቱ በተከታታይ ተዓምራዊ የሆነ ለውጥ ማስመዝገብ የቻለበት ሁኔታ ተፈጠረ። ኢህአዴግም በህዝብ ዘንድ ተቀባይነቱ በከፍተኛ ደረጃ ጨመረ።

 

ለቀለም አብዮት የማይመች ሁኔታ ተፈጥሮ አገራዊ ምርጫዎች ሰላማዊ፣ ነፃና ፍትሓዊ በሆነ መንገድ መፈፀም ተቻለ። ተቃዋሚዎች በ1997 ዓ/ም ምርጫ ተመርጠው ሲያበቁ ለመረጣቸው ህዝብ ክብር ስላልነበራቸውና ከሁኔታው ጋር መሄድ ስላልቻሉ ፓርላማ አንገባም አሉ፡፡ ይህ በማለታቸው ቀጥለው በነበሩ ምርጫዎች ሊመርጣቸው የሚፈልግ የህብረተሰብ ክፍልም ሊያምናቸው ባለመቻሉ የፈለጉትን ድምፅ ሳያገኙ ቀሩ። እንዴት መቶ በመቶ ኢህአዴግ አሸነፈ ብለው ከመጮህ ውጭ የራሳቸውን ጉድለት ማየት ተሳናቸው። ከኢህአዴግ ውጭ በሶማሊ፣ በአፋር፣ በሀረሬ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ እና በጋምቤላ ያሉ ፓርትዎች ያሸነፉትንም ጨምረው ኢህአዴግ መቶ ፐርሰንት አሸነፈ ብለው እስከ 2007 ዓ/ም ሲወቅሱና ሲያለቃቁስበት ቆዩ። በተቀራኒው ደሞ ኢህአዴግ በምርጫ ብቻ ሳይሆን በልማት በዕድገትም ድል ላይ ድል እየተጉናፀፈ ሁለገብ ፈጣን ለውጥ እያስመዘገበ ቀጠለ።

 

ድል ሲበዛ እርካታ የሚባል አደገኛ በሽታ በኢህአዴግ ውስጥ ተፈጠረ፡፡ ከፍተኛ አመራሩ ከህዝባዊ መስመሩ እየወጣ ሄደ፡፡ ስልጣንን ለህዝብ ማገልገያነት መጠቀም እየተወ የራሱ የግል ፍላጎት መጠቀሚያ አድርጎ የሚያስብ አስተሳሰብ በአመራሩ ውስጥ እያደገ መጣ። ይህን አዝማሚያ ለመታገል የተደረጉ ሙከራዎች አዝማሚያውና እርካታው እየተደጋገፉ የውስጥ ትግሉን ሙከራ አደናቀፉት። የውስጥ ትግል ሙከራዎቹ በተደጋጋሚ ከሸፉ። ኢህአዴግ በውስጡ የነበረውን በሽታ ፈጥኖ ለማከም በማቅማማቱና ጊዜ በመውሰዱ ለቀለም አብዮት የተመቻቻ ሁኔታ ፈጠረ። የአክራሪ ኒዮ ሊበራሎቹ የቀለም አብዮት ዕቅድ እስከ 2012 ዓ/ም የኢህአዴግን የመተካካትንም ፕሮግራም ግምት አስገብቶ የወጣ ዕቅድ የነበረ ቢሆንም በውስጥ በሽታው የተዳከመዉ ኢህአዴግ ቀድሞ ፍርክስክሱ ወጣ፡፡ ቀድሞ የቀለም አብዮት ዕቅድ መፈፀም ጀመረ።

 

ኢህአዴግ በስልጣን ጥመኞችና ለውጭ ሐይሎች ባደሩ የራሱ መስለው በውስጥ በነበሩ የውስጥ የቀለም አብየቶኞች ፍርክስክሱ አወጡት፡፡ በፓርቲ ውስጥ በህቡእ በተቀናጀና በውጭም በህዝብ ስም በተደራጁና በተዘጋጁ የቀለም አብየተኞችም ጭምር የህዝቡና የወጣቱን እውነተኛ ጥያቄና ትግል ጠልፈውና ዓላማውን አዛብተው የራሱን ህጋዊ የተመረጠ መንግስት በቀለም አብዮተኞቹ እንዲነጠቅ የተመቻቸ ሁኔታ ፈጠሩ። በተጨማሪም ከፓርቲው ውጭ የአክራሪው ኒዮ ሊበራል ቅጥረኞችና የሶሽል ሚድያ ቀለም አብዮተኞች እነ ጁሓር፣ ስዩም ተሾመና ሌሎችንም በስራቸው አደራጅተው ተንቀሳቅሰዋል፡፡ የግብፅ መከላከያ በኢትዮጵያ ላይ ያዘጋጀውን ቢግ ዳታና አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ ቴክኖሎጂ (BD and IA) አቅም ተጠቅመው የውሸት ዜናቸውን (fake news) የሌላቸውን አቅም ፈጥሮ በከፍተኛ ደረጃ በማባዛት በሚስኪን ህዝቦች ላይ የውሸት ተስፋና ጉጉት ፈጠሩ፡፡ በሁለንታዊና በፈጣን ለውጥ ዓለምን ያስደነቀ ስኬት ያረጋገጠውን በአብዮታዊ ዲሞክራሲ የተመራውን ግዙፉን ኢህአዴግ በራሱ በሽታ እየከሳ በመምጣቱም በቀላሉ ማንገዳገድ ቻሉ። ጊዜ በማይሰጥ ሁኔታ አጣደፉት። ኢህአዴግ በዋናነት በራሱ የእርካታ ተህዋስ የፓለቲካ አተት ያዘው፡፡

 

የመደመር ቀለም አብዮተኞቹ ትልቁ ስትራተጂ ለሁሉም ነገር ተጠያቂው ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍሎ ደርግን የተፋለመውና ህገ መንግስታዊ ስርዓት እውን እንዲሆን ከሌሎች ህዝቦች ጎን ተሰልፎ የታገለውን የትግራይ ህዝብና መሪው ድርጅቱ ህወሓት አደረጉ፡፡ ህወሓት በወቅቱ 2010ዓ/ም ለሳላሳ አምስት ቀናት ስብሰባ አድርጎ ራሱን ፈትሾ ከበሽታው ለመዳን ውስጣዊ ትግል በማድረግ ለመታረም ዝግጁ ሆነ። በሌላ በኩል ደግሞ ይህን በጥልቀት ተሃድሶ ራሱን ለመለወጥ ዝግጁ የሆነውን ህወሓት ላይ ያነጣጠረ ዘመቻ ለማድረግ የራሱ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ኦሮማራ የተባለ የጥፋት ቅንጅት ፈጥረውና ተደምረው ማጥቃት ጀመሩ። ይህ ዘረኛና ፀረ አብዮታዊ ዲሞክራሲ መስመር የሆነ የጥፋት ስትራተጂ ዓላማ ያደረገው ልማታዊውን የኢህአዴግን መንግስት ገርስሶ መጣልና አሻንጉሊት ተላላኪ መንግስት መፍጠር ነው። ይህም ጥልቅ ተሃድሶ በማካሄዱ ምክንያትና ቀድሞ መዳን የሚችለውን ህወሓትን አስቀድሞ ለመምታት ነው የኦሮማራ የስትራተጂው እምብርት።

 

ስትራተጂውን ለማሳካት አክራሪው ኒዮ ሊበራል ሐይል አክራሪ ዲያስፖራና አገርቤት ያሉትን ቅጥረኞች ብቻ አይደለም የተጠቀመው። ግብፆች፣ ኤርትራና በኃላም ሌሎች የአረብ አገሮችም ኃይል ተጠቅመዋል። መጨረሻውም በተዳከመውና አንድነት ባልነበረው ጥልቅ ተሃድሶ አደርጋለሁ ብሎ ሳያደርግ በቆየው ኢህአዴግ ምክርቤት ስብሰባ በኦሮማራ አደረጃጀትና በገንዘብና ቃል ተገብቶላቸው በተሰበኩ ተሰብሳቢዎች የምርጫ ድራማ ተደረገ። የሸፍጥ ምርጫ በታቀደው መሰረት በውስጠ ፓርቲ መፈንቅለ መንግስት ተካሂዶ ኮ/ል አብይ ተመረጡ። ወዲያውኑ በለሊቱ ጥቁሩ ፕሮፖጋንዳ ስራም ተጀመረ።

 

በመቀጠልም የመደመር ቀለም ሪፎርም/አብዮት በፌደራል ደረጃ ስልጣን በብቃት ለመቆጣጠር ዝርዝር ዕቅድ ተሰጥቶት በሊስቱ መሰረት ከህግ ውጭም ውሳኔ እየተወሰነ የቀለም አብየቱ እንዳይቀለበስ ፈጣን የሆኑ እርምጃዎች ተወሰዱ። ብዙ ሰዎች አብይ በራሱ ጭንቅላት እርምጃዎቹን የፈፀማቸው ይመስላቸዋል። እንዲመስላቸውም የግብፁ ቢግ ዳታና አርቲፊሻል እንተሊጀንስ ቴክኖሎጂ (BD and IA) ከፍተኛ ሚናውን ተጫውቷል። አብይም ጥሩ ፈፃሚ ባይሆንም አድርግ የተባለውን በተዋጣለት መንገድ ይተውነዋል። የተዋጣለት ቀለም አብዮተኛ አይደለ? አብይ ፊቱንም በሜክአፕ ቀለም አስውቦና በአለባበስ ሽክ ብሎ ትልቅ ለውጥ ያደረገ ያስመስለዋል።

 

የትላንት ታሪክን ጠባሳ የነበረም ያልነበረም ብቻ አጋግሎ በማቅረብ እሱ መሲሕ መጥቶ እንደፈታው ይመፃደቃል። የራሱ ስህተትም የኔ አይደለም የትናንት ቁርሾ ነው ብሎ ያላክካል። ቦንብ ከመቶ ሜትር በላይ ርቀት ባለው ስፍራ ተወርውሮ እኔን የለውጥ ሃዋርያ ለመግደል ተሞከረ ብሎ ያለቃቅሳል። ራሱ የፈጠረው ድራማ ነው ተብሎም ይታማል። በሚያሰለች ሁኔታ ይደጋግመዋል። ነገር ግን በኢትዮጵያ ህዝብ ልብ ውስጥ የሰፈረው ተወዳጁ እንጂነር ስመኘው በጠራራ ፀሓይ ተገድሎ እንኳን ሊደጋግመው ራስ ወዳዱ ጠቅላይ ሚኒስተር ተብዬ ምንም ሃዜኔታ አላሳየም። እሱ ግን አንዴ የመግደል ሙከራ ተደረገብኝ አንዴ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ተደረገብኝ ብሎ ያዙኝ ልቀቁኝ ይላል። እውነት እንነጋገር ከተባለ አንድ ሰው ቦምብ ቢወረውር ከሳላሳ ሜትር በላይ አርቆ መወርወር አይችልም። ከዛም ጉዳት የሚያደርሰው በሜትርና በሁለት ሜትር ራድያስ ውስጥ እንጂ እንደሚሳይል እየተምዘገዘ ክብር ትሪቡን ድረስ ሄዶ የቀለም አብዮተኛ መሪን አይገድልም ወይም አይስትም። ወታደር ነኝ የሚሉት መሪ ዩኒፎርም ብቻ መልበስ ብቻውን ወታደር ያሰኛል እንዴ? ያስብላል፡፡ የሆሊውድ ፊልም ተዋናይ እንኳን ዩኒፎርም ብቻ ለብሶ አይተውንም። ትንሽ ወታደራዊ ዕውቀት እንዲኖረው ይደረጋል እንጂ። ታድያ በምን ተዓምር ነው በዛ ርቀት የመግደል ሙከራ ተደረገብኝ የሚሉት? ሳይጣራ ከመቅፅበት የደመደሙት? ለኢንጅነር ስመኘው አገዳደል በዛው ፍጥነት ለምን ድምዳሚያቸውን አልገለፁልንም ታድያ? በውሸት የተገኘ ስልጣን በውሸት ዕድሜ ለመግዛት ነው።

 

የቀለም አብዮት ዕቅድና ስራ በሦስት ምዕራፍ ይከፈላል። ቅድመ አብዮት፣ በአብዮቱ ወቅትና ድህረ አብዮት ምዕራፋት አሉት።

 

በኢትዮጵያ የመደመር ቀለም አብዮት ሁለቱ ምዕራፋች ተፈፅመዋል።ኮ/ል አብይ ሁለቱም ምዕራፎች በድል ተወጥተዋቸዋል። ሦስተኛ ምዕራፍ የድህረ መደመር ቀለም አብየቱ ምእራፍ ኮ/ል አብይ ምን እያሉና እያደረጉ ነው? አብይ ስልጣን ከያዙ በኃላ ልገደል ነበር አሉ፡፡ መፈንቅለ መንግስት በአብንና በባልደራስና ከባህርዳር ተጠነሰሰብኝ አሉ፡፡ የዳውድ ኢብሳን ኦነግንም ይከሳሉ። ከዚህ ሁሉ ጀርባ ደግሞ ለውጡን ያልተቀበለው የትግራይ ህዝብና ህወሓት ተጠያቂ ያደርጋሉ። ሚድያዎችን በብር አፍነው የትላንት ሌባና ሰብኣዊ ጥሰት ተጠያቂ፣ አሁኑም የራሳቸው ዓቅም ማነስ ጭምርና ፀረ ህዝብ ውሳኔ በመወሰን የሚፈጠሩትን ችግሮች ሁሉንም ህወሓትና የትግራይ ህዝብ ላይ ያላክካሉ። ይከሳሉ። የትግራይ ተወላጆች ብቻ በመሆናቸው ሰዎች ያስራሉ። ይባስ ብሎም ከትግራይ ተወላጆች ጋር ሰርታቹሃል ተብለው ያለምንም ጥፋትና ማስረጃ ሰዎች ያስራሉ። ፍርድ ቤት ማስረጃ የላችሁም ዋስትና ይሰጣቸውና ውጭ ሁነው ይከራከሩ ያላቸውን የፖለቲካ እስረኞች የፍርድ ቤትን ስልጣን ተጋፍተው እስሩን ያስረዝማሉ። በረከትንና ታደሰ ጥንቅሹን ውቃቤያቸው የኮ/ል አብይ መንግስት መሪነትን አልወደደውም ብለው በኦሮማራ ኔትዎርክ ዘብጥያ ያወርዳሉ። ታድያ ይህ ድንቄም ለውጥ አያሰኝም።

 

በአገር ውስጥ ከሶስት ሚልዮን በላይ ህዝብ በማፈናቀል ዓለምንም ሶርያንም ያስናቅን እንዲንሆን ያደረገን፤ ህገ መንግስታዊ ያልሆነ በኢትዮጵያ ህዝቦች ምክርቤት ያልፀደቀ አስቸኻይ ጊዜ አዋጅ በኦሮሚያ፣ በሶማሊያ፣ በአማራ፣ በቤንሻንጉልና በቅርቡም በደቡብ ህዝቦች ክልሎች ያወጀለን፤ የአንድነት መንፈስ የጠፋበት፣ የሰላም ሁኔታ የሌለበት፣ ስጋትና ጥርጣሬ የሰፈነበትና ተስፋ የጨለመበት ህዝብና አገር እንድንሆን ያደረገንና ሌሎችም የቀለም አብዮቱ ቱሩፋት እንድንቋደስ ያደረገን የቀለም አብዮት መሪ የአብይ አመራር ውጤት አይደለምን?

 

በጠራራ ፀሓይ ባህርዳር ላይ የህዝብ ተመራጮች የሆኑ የክልል መሪዎችን ከስልጣኔ ልታወርዱኝ እየወሰናቹህ ነው ብሎ በመስርያ ቤታቸው የሚረሽን ጋጠወጥ ያለበት አገር ፈጠሩ። በዛኑ ቀን በአዲስ አበባም የመከላከያ ኤታማዦር ሹም ከወዳጃቸው ጀነራል ጋር በቀላሉ ተገድለው ስንት የጀግንነት ታሪክ ያሳለፉ ከፍተኛ መኮነኖች አገሪቱ እንድታጣ ሆነ። አብይ የአዞ እንባ አነባ። ምንም ሳያጣራ መፈንቅለ መንግስት አለ። ምርመራ ግን የለም። እንሆ እንጂነር ስመኘው መቶ ቀረ። እነ ዶ/ር አምባቸው እና አነ ጀነራል ሰዓረም ሞተው ሊቀሩ ነው? ቤተሰብና ወዳጅ ከማልቀስ ውጭ ምንም ማድረግ አልቻለም፡፡አሁንም እየተረሱ ነው ማለት ነው?

 

አብይ አህመድ ከግድያው ንፁህ እንዳልሆኑ አሁንም ስማቸው ይነሳል፡፡ ተወዳጁ ስመኘው አስገድለውታል እንደሚባሉት ሁሉ አሁንም አየታሙ ነው። ኮነሬሉ ለምርመራው ሳይሆን የሚጨነቁት ለራሳቸው ስልጣን ነው። ነገር ግን ቢያንስ በቀጥታ ግድያው ላይ ተሳትፎ ባያደርጉም ከተጠያቂነት አያመልጡም። ሁኔታው የአስተዳደራቸው ጉድለት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው።አየር መንገዳችን ቴሌኮሚኒከሽን ምድር ባቡር ወዘተ ሊቸበችቡት ሲሯራጡ እያየን ነው።ኢህአዴግን አፈራርሰው ከጨረሱ በኃላ አሁን ደግሞ ውህደት ሊፈፅም ነው ብለው ብቻቸውን ወስነው እየተጣደፉ ነው።ይህ መጣደፍ ደግሞ በኢኮኖሚም በአመራርም ለከፍተኛ ውድቀት የሚዳርገን ነው።

 

በአጠቃላይ በአገራችን እያጋጠሙ ያሉ አስከፊ ክስተቶች የጋጠወጡ መሪ ኮ/ል አብይ አህመድ አመራር ውድቀት ውጤቶች ናቸው። ስልጣኔን ብቻ ብሎ የሙጥኝ የሚል መሪ የስራ ውጤት ከልማት ይልቅ ጥፋት፣ ከሰላም ይልቅ ሁከት፣ ከተስፋ ይልቅ ስጋት ላይ የምንኖርበት ሁኔታ ተፈጥሮ አገራችን ኢትዮጵያ በፍጥነት ወደ መበታተን መፍረስ አደጋ እየተቃረበች ነው።

Videos From Around The World

 

አገራችን ኢትዮጵያ ልንታደጋት የምንችለዉም ሁላችንም ነን፡፡ በቅርቡ አገር ወዳዶች እንዴት አገራችን እናድናት ብለው በመቀሌ በህወሓት ተነሳሽነት የመጀመርያ ስብሰባቸውን አድርገዋል። ይሁን እንጂ በመደመር ቀለም አብዮተኞቹ ይህ ዓይነት ስብሰባ በበጎ አልታየም። እንደ መዳፈርም ተወስዷል። ህወሓትና የትግራይ ህዝብ የመደመር ቀለም አብዮቱን አለመቀበሉ ምክንያት አድርገው ውስጥ ውስጡ ሴራዎች ሲጠነሰሱበት ቢቆይም አልበገር ብሎ እየታገለ ይገኛል፡፡ አሁን በቅርቡ ያደረገውን ተነሳሽነትም በቀለም አብዮተኞቹ ጉዳዩን አሳሳቢ አድርጎታል።

 

የስልጣን ጉዳይ የሞት ሽረት ጉዳይ ሁነባቸዋል። አክራሪ ኒዮ ሊበራሎችም የነደፉት የቀለም አብዮት በተሟላ ውጤታማ እንዳልሆነ ቆይተው ቢሆንም ደርሰውበታል። በትግራይ ህዝብና በህወሓት መካከል ይፈጠራል ብለው የገመቱት ልዩነትና መቃቃር ሳይፈጠር በተቃራኒው ጠንካራ አንድነትና መግባባት በተለየም በአካባቢው ሰላምና መረጋጋት መስፈኑ ያልጠበቁት ነበር። አሁን እንደገና እያሳሳብዋቸው ያሉት ሁለት ነገሮች ናቸው። አንደኛ የኮ/ል አብይ መንግስት የቀለም አብዮት መክሸፍና ውደቀት ነው። ሁለተኛውና በነሱ ዓይን አደገኛው የህወሓትና የሌሎች አገር ወዳድ ድርጅቶችና ሰዎች በመተባበር አገሪቱን አድነው ያለውን ህገመንግስትና ፌደራሊዝም እንዳይታደጉትና ህገመንግስቱ ማሻሻል ቢያስፈልግም በራሳቸውና በህዝቡ ፍላጎት እንጂ በውጭ ሐይሎች አይሆንም ብለው እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ነው።ይህንም ለመቀልበስ ብሎም አብይ አህመድና የመደመር ቀለም አብዮቱን ለማዳን አክራሪ ኒዮ ለበራሎቹ አሁንም አልተኙም።

 

ከፍል 3 ይቀጥላል

 


Back to Front Page