Back to Front Page

የመደመር ቀለም አብዮትና መዘዙ፡ክፍል ሦስት

የመደመር ቀለም አብዮትና መዘዙ፡

በትግራይ ህዝብ ላይ ያነጣጠረ እንደገና አዲስ የቀለም አብዮት እየተሸረበ ነው!

 

ክፍል ሦስት

ዑስማን ሙለዓለም ከሐራ ገበያ

መስከረም 2012 ዓ/ም

 

ለአንዴና ለመጨረሻ የቀለም አብዮት ሙከራ

በኢትዮጵያ በተካሄደው የቀለም አብዮትየአገር ውስጥም የውጭም ሁሉም ሐይሎች የተሳካና አስተማማኝ የስርዓት ለውጥ (regime change) ተረጋግጧል ብለው ተማምነው እንደነበረ ይታወቃል። በሁሉም የሚድያ አውታሮቻቸው አስረግጠው የገለፁት ይህንን ነበር። ኢሳያስ አፈወርቂ ከአስመራ game over ሲል፣ እነ ደመቀ መኮነንና ገዱ ከባህርዳር የጨለማ ዘመን አከተመ ብለው ሲያውጁ፣ አብይ አህመድ ከአዲስ አበባ የቀን ጅቦች ሲል ሁሉም የቀለም አብዮቶኞች ደስታና ፈንጠዝያ አስኩሯቸው ነበር። ህወሓት ላይመለስ ጨፍልቀነዋል አሉ። ከአሁን በኃላ ዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት፣ የብሄር ብሄረሰቦች መብት፣ ፌደራሊዝም፣ አብዮታዊ ልማታዊ ዲሞክራሲ፣ . . . ቅብርጥሴ ቅብርጥስጥሴ ብሎ ነገር የለም አሉ። ለሁሉም ነገር ለውጥ ላይ ነን፣ ሽግግር ላይ ነን ተባለ። ከየት ወዴት መሆኑ የማይታወቅ ጉዞ ለውጥ ተብሎ ተለፈፈ።

 

ነፃ ሚድያ የተባሉትም ይህን ቅኝት ብቻ ይዘው ተረባረቡ። Ltv፣ EBC፣ ዋልታ፣ ፋና፣ ናሁ፣ OBN፣ OMN እና ኢሣት በትግራይ ህዝብ፣ በህወሓትና እንዲሁም የትግራይ ህዝብና ድርጅት ዓላማ ደግፈው የቆሙት የሌሎች ህዝቦች አባላትም ሳይቀሩ ስም እየጠሩ ስም የማጥፋት ዘመቻቸውን አፋፋሙ። ጥሩ ስም ያስመዘገቡ በህዝባዊነታቸው በኢትዮጵያ ህዝቦች የሚከበሩና የሚታመኑ ተቃማትን እንዲፈርሱ በጥቁር ፕሮፖጋንዳ ዘመቱባቸው። በድህንነት፣ በፌደራል ፖሊስ ብሎም በመከላከያ ሰራዊት ላይ ምላሳቸውን ዘልዝለው ማስረጃ የሌለው ውሸት ደረደሩ።

 

Videos From Around The World

የመደመር ቀለም አብዮተኞች ለውጭ መንግስታት እነዚህን መስራያ ቤቶች ገብተው ያሻቸውን እንዲያደርጉ በሩን ከፍተው እንዲገቡ ፈቀዱላቸው። የአገራችን ሉዕላዊነት በደንበር ሳይሆን በአገሪቱ እንብርት ውስጥ ተጣሰ። ለኢትዮጵያ አገራቸው ቀን ከለሊት ሲሰሩ የነበሩ የነዚህ ተቀማት አመራሮችና አባላት በሽብርተኞች፣ በአክራሪዎችና በውጭ አገር ሰላዮች ጥቆማ እየተደረገባቸው ለእስር ተዳረጉ። እንደነ ኢንጅነር ስመኘው፣ ጀነራል ሰዓረ፣ ጀነራል ገዛኢ፣ አቶ አምባቸው፣ አቶ እዘዝ፣ አቶ ምግባሩና ሌሎች የመንግስት አባላት፣ መኮንኖችና ወታዳሮች ደግሞ እየገደሉና እያስገደሉ እኛ አላየንም ብለው መልሰው ምርመራ ላይ ነን ይሉናል የነውጡ መሪዎች።

 

ለውጡ እየዋለ እያደረ ወደ ዋናው ባህሪው ወደ ነውጥነት ነው የተሸጋገረው፡፡ በሁሉም አካባቢ ሰላም ጠፍቶ ግጭት፣ ህውከት፣ ግርግር፣ ሞት፣ በሚልዮኖች መፈናቀል እና ከቦታ ቦታ መዘዋወር የማይቻልበት አገር ተፈጥሮ በኮማንድ ፖስት መተዳደር ከጀመርን ወራቶች እየተቀጠሩ ናቸው፡፡ ይህ አስቸካይ ጊዜ አዋጅ ህገ መንግስታዊ ያልሆነ በፓርላማ፣ በሚኒስተሮች ምክርቤት፣ ይሁን በኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚም የማይታወቅና ይሁንታ ያላገኘ ከጠቅላይ ሚኒስተሩም በደብዳቤም ያልተገለፀ በስልክና በስብሰባ ቀጭን የቃል ትዕዛዝ ተግባራዊ እየሆነ ያለ ነው። ይሁን እንጂ ይህ ህገወጥ አካሄድም ያሰገኘው ፋየዳ የለም፡፡ ህዝቡ ስለ ራሱ፣ ስለ አገር ድህንነትና ስለ ሰላም በቅድሚያ የሚጨነቅበት አዲስና ቅድሚያ የሚሰጠው ሁኔታ ላይ ይገኛል። አገር ልትፈርስ ገደል ጫፍ የደረሰችበት ሁኔታ ላይ ሁኖ ነገ ምን ሊፈጠር እንደሚችልና ወዴት እየተጓዝን እንደሆነ ማንም መገመት የማይቻልበት ሁኔታ ላይ እንገኛለን።

 

በሌላ በኩል የመደመር ቀለም አብዮት ዋና ዒላማ የነበረው የትግራይ ህዝብና መሪ ድርጅቱ በቀለም አብዮቱ ጎርፍ ለመጠራረግ ቢፈለግም አልተሳካም። ከስም ማጥፋት ጀምሮ እስከ የማፈናቀል፣ የማሰርና የመግደል ጥቃት ደርሶበታል። አዲስ ትርክት ፈጥረው ጥቁር ቀለም እየቀቡ ሌላው ወንድም ህዝብ በትግራይ ህዝብና በመሪ ድርጅቱ የነበረው ፍቅርና ክብር ለመፋቅ ባለ በሌለ አቅማቸው ሰርተዋል። የነበረው አስተዳደር በህወሓት የበላይነት ይመራ እንደነበር፡፡ የኢትዮጵያን ህዝብ ሀብት ዘርፈው ወደ ትግራይ እንደወሰዱ። ሰብኣዊ ጥሰት በሌላው ህዝብ መፈፀማቸው። ፌደራሊዝም የተባለ ዘረኛ ስርዓት ፈጥረው የኢትዮጵያን አንድነት ማዳከማቸው። ሲጀመር የአማራ ህዝብ ጠላት ብለው ፈርጀው ወደ ትጥቅ ትግል ወጡ ብለውና ብዙ ሌሎች ልበወለድ የስም ማጥፋት ዘመቻ ሲያደርጉ ያለመታከት በአንድ አካባቢ በሰፈረ ህዝብ ፋሽስት ደርግ ለመገርሰስ ከፍተኛ መስዋእትነት መክፈል ብቻ ሳይሆን በምንም መመዘኛ ያልተመጣጠነ ሰብኣዊና ሀብት ኪሳራ የደረሰበትን የትግራይ ህዝብና ትግሉን በከፍተኛ ጀግንነት የመራ ድርጅትን ህወሓት ላይ ሲያነጣጥሩ ቆይቷል፣ እስካሁን ድረስም እየቀጠሉበት ነው።

 

አሁን ደግሞ ቢቀጠቅጡት መሞት ያልቻለው ህዝብና መሪ ድርጅቱ ህወሓት ለአንዴና ለመጨረሻ ለመምታት አዲስ ሴራ እየተሸረበ ነው። የመደመር ቀለም አብዮት በከፊል ደረጃ በአገር ደረጃ ቢሳካም በሰሜን የአገሪቱ ክፍል በሚፈለገውና በታሰበው መንገድ አልተሳካም ብለው በቅርቡ ገምግመዋል። የመደመር ቀለም አብዮት ቀያሶቹ አክራሪው ኒዮሌበራል ሐይሎች ይህ ግምገማ ቀድመው ቢደርሱም፣ በአገር ውስጥ አስፈፃሚ ያደረጉት አብይ አህመድ ግዴላችሁም እሰራላቸዋለሁ፣ እናሳያቹሃለን ጠብቁን ብሎና ኢሳያስ አፈወርቅም game over ብለው አሳስቷቸው ነበር። ይሁን እንጂ እቅዱ ባለመሳካቱ ምክንያት እንደ አዲስ ህወሓትን በመምታት ያታጋዩ ህዝብ ቅስም ለመስበር አዲስ ዕቅድ አውጥተው ዝግጅታቸውን ጀማምረዋል። በሌላ በኩል ተዳክሟል የተባለው ህወሓት ጭራሽ ተጠናክሮ የህዝብ ከፍተኛ ድጋፍ አግኝቶ በተለየ መንገድ በአካባቢው ሰላምና መረጋጋት ማረጋገጥ መቻሉና ብሎም ለሌሎች ህዝቦች ተስፋና ደጀን ሆኖ ማገልገል መጀመሩ ክፉኛ አስደንግጧቸው የቀለም አብዮት በትግራይ ደረጃ ለመፈፀም በሚልዮኖች ዶላር መድበው እንቅስቃሴ ጀምረዋል።

 

የመደመር ቀለም አብዮቱ መሪዎች ማን ናቸው?

ከውጭ ሃይሎች ዋናው የአክራሪ ኒዮ ሊበራሎች የሚመሩት የግብፅና ኤርትራ መንግስታትም ይገኙበታል። ከአገር ውስጥ ደግሞ ተላላኪዎቻቸው የሆኑት የመደመር ቀለም አብዮት መሪው አብይ አህመድና የግንቦት ሰባት/አዜማ እና የትግራይ ባንዳዎች ናቸው።

 

ዓላማው ምንድነው ነው?

ህወሓትን በማስወገድ የትግራይ ህዝብን በማንበርከክ አብዮታዊ ዲሞክራሲን በሐይል መደምሰስ ነው። በትግራይ ክልል ህዝብ ድምፅ ስልጣን ላይ የወጣውን የህወሓት ድርጅት ከስልጣን ማውረድ ነው። በአጭሩ በክልሉ የአስተዳደር ለውጥ (Regime change) በማካሄድ የቀለም አብዮት የተለመደ ዓላማ ማሳካት ነው።

 

ይህን ዓላማ በምን ስትራተጂና ታክቲክ ሊፈፅሙ አቅደዋል?

ዋናው ስትራተጂ ሰላም የሰፈነበትና የተረጋጋው የትግራይ ክልልን ማንኛውም ግርግር በመፍጠር የፈደራል መንግስት ጣልቃ ለመግባት የሚያስችል የተመቻቸ ሁኔታ ለመፍጠር መንቀሳቀስ ነው። ይህን ስትራተጂ ብዙ ታክቲኮችን በመፈፀም ለማጠናከር እንዲያስችሏቸው ስልቶቻቸውን ቀይሰዋል። ባንዳዎችን በማደራጀትና ትልቅ በጀት መድበው ትግራይ ባለው ነፃ እንቅስቃሴ ተጠቅመው በትግራይ የሚታዩ አስተዳደራዊ ችግሮች ለቅመው እንዲታረሙ ሳይሆን በህዝብና በክልሉ መንግስት መካከል ልዩነት ሰፍቶ ግርግር እንዲፈጠር ማመቻቸት ነው።

 

ሌላው ስትራተጂ በኢትዮጵያና በኤርትራ የድንበር አካባቢ ያለውን የመሬት ይገባኛል ጥያቄ አመላለስ ጉዳይ የትግራይ ህዝብን ስሜት በሚጎዳ መንገድ መፍታት ነው፡፡ በዚህም ህዝቡ በህወሓት ላይ ያለው አመኔታና ፍቅር እንዲሸረሸርና ብሎም ተቃውሞ ተነስቶ የራሱን መንግስት እንዲያፈርስና ስልጣን በተላላኪዎች እንዲገባና የክልሉ ህዝብ እስካሁን የከፈለውን መስዋእትነት ዋጋ የሌለው አድርጎ ለማንበርከክ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ነው።

 

በኤርትራ መንግስትና በኢትዮጵያ መንግስት መካከል ለህዝብ ግልፅና ይፋ ያልሆነው የሰላም ስምምነት መፈረሙ ይታወቃል። ይህን ስምምነት በመጠቀም በሁለቱ ህዝብ መካከል የናፍቆት ግንኙነት ተፈጥሮ ቆይቷል። የትግራይ ክልላዊ መንግስትም ሁለቱ ህዝቦች ያለምንም ዕንቅፋት እንዲገናኙ ከልብ በመነጨ ህዝባዊነትና የሰላም ፍላጎት በግልፅ በአደባባይ አውጆ በተግባርም ተንቀሳቅሷል። በዚህም በሁለቱ ህዝቦች መካከል በማንኛውም የትግራይ አካባቢ እንደፈለጉት እንዲንቀሳቀሱ አስችሏል። የአቶ ኢሳያስ አፈወርቅ መንግስት ይህን በሁለቱ አገሮች ህዝብ መካከል የተጀመረው ግንኙነት በቅን ልቦና ባለማየታቸው ማደናቀፍ ጀመሩ። የዛላንበሳንና ሰነዓፌን መሰመር ዘጉ። ራማ ዓድኻላን መስመር ዘጉ። ህዝቦች ሲደሰቱ አይወዱም እንዴ እስኪባሉ ድረስ ያለ መግለጫ ዘጋጉት። አንደገና የሁመራ ተሰኔ መስመር ከፈቱ ተብሎ ሁለቱ መሪዎች ህዝቡን እንደገና አስጨፈሩ። ተዘግተው የነበሩትም እንደገና ተከፈቱ። በሁለቱም መሪዎች እስካሁን ለመክፈት ካልተፈለገው የባድመ ባረንቱ መስመር ውጭ ሁሉም ተከፍቶ እንቅስቃሴ ተጀመረ። ተፈጥሮ የነበረው ስጋትና ተስፋ መቁረጥ እንደገና ታድሶ ነበር።

 

ብዙ ሳይቆይ ደግሞ የማይገመቱት ኢሳያስ አፈወርቅ በድንገት ሁሉንም ዘጋግተው ጭራሽ ሰራዊታቸውን በማዘጋጀት የውግያ ልምምድ ውስጥ ገቡ። ምሽግ ማስተካከልና ከምሽግ ውጭ ሊያጠቃ የሚችል ሐይል ማደራጀት ተያያዙት። ሰራዊት ሰብሰባ ላይ ሰላም ስምምነት ተደርጎ እያለ እንዴት ለጦርነት ተዘጋጁ ትሉናላቹ? ብሎ ተቃውሞ ሲያሰማ፣ ወታደር ናቹሁ የተባላቹሁትን መፈፀም ነው፡፡ እንዴት መሬታችን አሁንም በወያኔ ቁጥጥር ስር ሆኖ ለምን እንዘጋጀለን እንዴት ትላላቹህ ብለው መልሰው የወቀሱበት ሁኔታ ላይ እንገኛለን።

 

በትግራይ ላይ የቀለም አብዮቱ እንዲካሄድ ተስማምተዋል፡፡ ይህንን ስትራተጂ ለመተግበር የኤርትራ መንግስት ከአብይ መንግስት በመሆን በህወሓትና በትግራይ ህዝብ ላይ ጦርነት ለመክፈት እየሸረቡ ነው። ይህ ደግሞ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በማዳከምና በቀጭን ትዕዛዝ ምሽግ ልቀቁ ተብለው የኤርትራ መንግስት ጦር በቀላሉ ምሽጉን አልፈው እንዲገቡ ሊያደርግ ይችላል። ይህ ግምት ራሳቸው ኢሳያስ አፈወርቅ ካሉት የሚነሳ ነው፡፡ እንደሳቸው አባባል ከፌደራል መንግስት ችግር የለም ችግር ያለው ከወያኔ ነው ብለው ደጋግመው የገለፁት ጉዳይ በማየት ግምቱ ሚዛኑን ከፍ ያደርገዋል። ይህን በመፈፀም ትግራይን ማዳከምና ህዝቡን በመከፋፈል ህወሓትን ለአንዴና ለመጨረሻ መምታትና ፍላጎታቸውን በመደመር ቀለም አብዮት መፈፀም ነው።

 

ሌላው ሶስተኛው ስትራተጂ ሚድያን በመጠቀም መርዝ መርጨት ነው። ሚድያ አስተባብሮና እስካሁን የፈፀሙትን ዘመቻ አጠናክረውና በአዲስ ቅኝት ዘረኛና አደገኛ ፀረ ህዝብ ጥቁር ፕሮፖጋንዳቸውን በመሸፋፈን የትግራይ ህዝብ አዛኝ መስለው ባንዳዎችን እየተጠቀሙ በተከፈላቸው መጠን ይተጋሉ። መደበኛውንና ሶሻል ሚድያውን ውጤታማ ለማድረግ የውጭ ሃይሎችንም ቴክኖሎጂ ተጠቅመው ይንቀሳቀሳሉ። በውሸት ተመስርተው የሐሰት ዜና ደጋግመው በማቅረብ በህዝቡ የተወደዱ መሪዎቹ ላይ ጥላሸት በመቀባት ይደሰኩራሉ። በድህረ ገፆች ስም ያጠፋሉ። በአጋጣሚ የሚከሰቱ ችግሮች አጉልተው በማስጮህ ለሰላምና ለመፍትሔ ሳይሆን እንደ ሌሎች የኢትዮጵያ ክልልች ትግራይም ሁከት ያላትና ግርግር የበዛባት በማድረግ የእንስሳዋ እኔ ከሞትኩኝ ስትራተጂ ለመከተል ምንም ግድ የላቸውም። ካልተሳካ ማበላሸትም አንዱ ስትራተጂያዊ ዓላማቸው ነው።

 

ማጠቃለያ

የትግራይ ህዝብ ተዘጋጅቶ ይህን በሱ ስም እየተዘጋጀ ያለውን የቀለም አብዮት በተለመደው የትግል ቆራጥነቱ እንደሚያከሽፈው ሳይታለም የተፈታ ነው። ማሸነፍ የሚችለው ደግሞ ብቃት ያለው ዝግጅትና የጠላቶቹ መሰሪ ባህርያትና ዝርዝር ስትራተጂና ታክቲክን አውቆ በንቃት ሲታገል ነው። ይህ ደግሞ ያለ መሪ ድርጅት አመራር የሚሳካ ትግል የለም።

 

የመደመር ቀለም አብዮት ካልተቀለበሰ የመጨረሻው ጦስ አገር መበተን ነው። በሊብያ፣ በየመንና በሶርያ ያየነው የቀለም አብዮት ውጤት በአገራችን ኢትዮጵያ እንዲደርስ መፍቀድ ነው፡፡ ስለዚህ አሁን እየተሸረበ ያለውን ሴራ በግልፅ ውይይት በማድረግና ህዝቡን በማስተባበርና በግዜ የለም መንፈስ ማዘጋጀትና የኢትዮጵያ ህዝቦችን በጎኑ አሰልፎ በመመከት ህወሓት እንደሁሌም በብቃት ሊመራ ይገባዋል። እንደገና እንደ ባለፉት ሦስት ዓመታት በቸልነት ወይም በብልጣብልጦች መታለል የለበትም። NEVER AGAIN ብሎ መነሳት አለበት። ህወሓት።

 

ሰማእታት ለዘላዓለም ክቡር ናቸው!

 

እናሸንፋለን!

 


Back to Front Page