Back to Front Page

አልደራደርም የሚል የህዝብ መሪ አምባገነን ብቻ ነው ።

አልደራደርም የሚል የህዝብ መሪ አምባገነን ብቻ ነው ።

በልኡል ገብረመድህን (ከአሜሪካ )

4.4.2019

 

ታሪክ የጋራ ነው ። ምክያቱም በዳይና ተበዳይ በታሪክ ተቃርኖ ተነፃፃሪ ይዘት አላቸው ። ተበዳይ ባይኖር በዳይ ቦታ አይኖረውም ነበር ። ሰው ለዘመናት ከኖረበት ፣ ከሰፈረበት ቦታ ሲፈናቀል ፣ አፈናቃይ ጉልበተኛ ሐይል አለ ማለት ። ሰው ሲታሰር ፣ አሳሪ አለ ማለት ነው ። ሰው ሲገደል ፣ ገዳይ አካል ማለት ነው ። ጥፋት ካለ ልማት ነበር ማለት ነው ። በመሆኑም ሰው የሚሰራቸው ምድራዊ ክስተቶች ፊት ሆነ አሁን ፣ እንዲሁም ወደፊት በታሪክ ይመዘገባል ። ታሪክ በራሱ ሰው ሰራሽ በመሆኑ በቀላሉ ታሪክ በሚያዛቡ (በሚሰርቁ) ግብታውያን የክስተቱ አቅጣጫ ሊለወጥ ፣ ሊቀየር ፣ አልያም ሊጠፋ ይችላል ። ታሪክ የጊዜና የክሰተቶች ውጤት በመሆኑ በውጤቱ ላይ ተቀራራቢ መግባባት እንዲኖር ይመከራል ። ምክንያቱም ታሪክ የማህበረሰብ የጊዜ ክንውን በመሆኑ ምን ፣ የትና በማን እንደተፈፀመ ተቀራራቢ አረዳድና አተያይ ከሌላ ቅድመ ታሪክ አልነበረም ማለት ነው ። የሰው አኗኗር ከታሪክ ጋር ነው ። የሰው ልጅ ብቸኛ ሐብቱ ታሪክ ብቻ ነው ። ምድር ላይ ለታሪክ የማይመች ህዝብ የለም ። እንዴት ቢባል ታሪክ ሰሪው ህዝብ በመሆኑ በታሪክ ክሰተት የማያልፍ ህዝብ የለም ። ሰለሆነም ታሪክ መዘከር ፣ መተንተን ፣ መጠበቅ ፣ መበልጸግ ይኖርበታል ። በሐይል ሚዛን አተያይም ታሪክ ሚዛናዊ ነው ። ለአብነት ያህል ፦ በወታደራዊ ውጊያ በተለያዩ ምክንያቶች አሸናፊ እና ተሸናፊ ይኖራል ። በታሪክ ምዘና ሁለቱም በተቃርኖ ተነፃፃሪ ናቸው ። በመሆኑም ታሪክ የአሸናፊ እና ተሸናፊ ሚዛኑ የተጠበቀ ይሆናል ። ለምን ከተባለ የክስተቱ ሒደት የጋራ በመሆኑ በጋራ አምኖ መቀበል አማራጭ የሌለው ሐቅ ነው ።

Videos From Around The World

በኢትዮጵያ የደፈጣ (ግልጽነት ) የሌለው የፖለቲካ ሴራ አንዱ ምክንያት ማህበረሰብ በታሪክ ላይ ያለው የተሳሳተ አረዳድ ነው ። የጣሊያን ወራሪ አድዋ ላይ በኢትዮጵያ ህዝብ ተጋድሎ መሸነፉ ጣልያኖች አልካዱም ። የአድዋ ጦርነት ሲነሳ በሒደቱ ሆነ በፍፃሜው ላይ ጠንካራ ስምምነት አይታይም ። ምክንያቱም የአድዋ ጦርነት ላይ ቅድመ ጦርነት ሆነ ድህረ ጦርነት የላቀ ሚናና ተፅዕኖ የነበራቸው ጀግኖች ታሪክ ላይ ተገቢውን ቦታ አላገኙም ። ታሪክ ፀሐፍያን ማህበራዊ ሆነ ታሪካዊ ክስተቶች በተገቢው ሁናቴ ሰንዶ ለትውልድ የማስተላለፍ የታሪክ ግዴታ እንዳላቸው ቢታመንም የታሪክ አሰናነድ ላይ ጉድለቶች በመኖራቸው ቀጣይነት ባለው የማህበረሰብ ውስጣዊ ግጭቶች መንስኤ ይሆናል ። አፄ ሚኒሊክ አማራ እንጂ ኢትዮጵያዊ አልነበሩም የሚል ታሪክ የሚፅፍ የታሪክ ፀሐፊ ለህዝብ የሚበጅ አይደለም ። ታሪክ እውነተኛ ክሰተት ላይ ያልቆመ ከሆነ የማህበረሰብ ጠንቅ ከመሆኑም በላይ ለማስረጃነት አያገለግልም ። የነበሩ ጉድለቶች ለማረም ሆነ በቀጣይ ጉድለቶች እንዳይደገሙ ለማድረግ በታሪኩ ክሰተት ላይ መተማመን ይጠይቃል ። ታሪክ ለድርድር የሚቀርብ አጀንዳ ሊሆን አይችልም ። የታሪክ መረጃ በታሪክ ክሰተት የመረጃ ቅንብር የሚሰነድ የማህበረሰብ ሁለንተናዊ ሒደት የሚያሰረዳ ሰነድ በመሆኑ በሰነዱ ላይ መደራደር አይቻልም። የታሪክ ሰነድ መነሻና መድረሻ ይታወቃል ። ምክንያቱም ታሪክ የማህበረሰብ ክንዋኔ ማሳያ መነፅር ነው ።

በኢትዮጵያ የመንግስትነት ቦታ የሚይዙ መሪዎች የገዢነት ድባብ የተላበሱ በመሆናቸው የፖለቲካ ድርድር ወይም ከሰጥቶ መቀበል መርህ የራቁ በመሆናቸው የህዝብ ጉዳዮች በሆኑ አጀንዳዎች ላይ አንዳራደርም ሲሉ ይሰማል ። ለእኔ እሰከሚረዳኝ ለፖለቲካ ድርድር የማይቀርብ ጉዳይ ያለ አይመስለኝም ። በዚህ ሀያ አንደኛ ምዕተ አመት ምዕራባውያን ሐይማኖት ላይ እንካን ድርድር በሚያደርጉበት ዘመን ኢትዮጵያ ላይ የህዝብ ጥያቄና ፍላጎት ከሆነ በህገ መንግስት ሆነ በመሬት ፖሊስ ሆነ በፌዴራል ሰርአት አወቃቀር ላይ መደራደር የማይቻልበት ምን አሳማኝ ምክንያት ሊኖር ይችላል ?። የኢትዮጵያ ፌደራል አወቃቀር ለዜጎች መፈናቀል ምክንያት ከሆነ ቀይ መሰመር ማስመሩ ለምን አስፈለገ ?። የአሁኑ የኢትዮጵያ ህገ መንግስት ለኢትዮጵያ ህዝብ ደህንነትና አንድነት መናድ ምክንያት ከሆነ ለምን ህገ መንግሥቱ አትንኩ ይባላል ?። የኢትዮጵያ ህገ መንግስት የህዝብና የአገር ህግ ከሆነ እንዲቀየርም ሆነ እንዲሻሻል ለህዝብ መቅረብ ይገበዋል ። ህዝብ በስፋትና በጥልቀት ጊዜ ወሰዶ እንዲመክርበት የህገ መንግስት ጥናት እና ምርምር ኮምሽን ገለልተኛ ሆኖ እንዲቋቋም ያሰፈልጋል ። በጉዳዩ ላይ ህዝብ የማወያየት ስራ መጀመር ይኖርበታል ።

በኢትዮጵያ የመንግስት ሰልጣን ታሪክ የድርድር መርህ አልባ በሆኑ ማህበረሰብ ጉጂ ተግባራት ላይ ሲርመሰመስና ሲርመጠመጥ ማየቱ የተለመደ ነው ። የመልካም አሰተዳደር ችግር በድርድር ሳይሆን በህግ ልዕልና የሚፈታ ጉዳይ ነው ። ህግና ህገመንግስት እንዲከበር የህግ እርምት እንጂ የፖለቲካ ድርድር አያስፈልገውም ። የሰው ልጅ ቁልቁል ተሰቅሎ ሲገደል የታየው ኢትዮጵያ ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ነው ። ቁልቁል ስቃዮችም የኦሮሞ ወጣቶች ነበሩ ። ትዕዛዝ ሰጪና አስፈፃሚ የኦሮሞ ተወላጆች ነበሩ ። ጉዳዩ ሲፈፀም ከመንግሥት ወገን ለጉዳዩ ውግዘት አልተሰጠውም ነበር ። መንግስት ህግን መሠረት አድርጎ የዜጎች ደህንነትና ሰላም የማስጠበቅ ግዴታ አለበት ። ዜጎች ላይ የህልውና ጥቃት የሚፈፅሙ ህግ አልባ ሰዎች ላይ ግልጽና ህጋዊ እርምጃ የማይወስድ ከሆነ ህግ አልባነት መስፋፋቱ የማይቀር እውነታ ነው ። በገለልተኛ ተቋም የሚመራ የህግ አፈፃፀምና አሰራር መከተል የዜጎች የህልውና ጉዳይ ነው ። መንግስት ህግን ያላገናዘበ አሰራር ከተከተለ የዜጎች ደህንነት አደጋ ላይ መሆኑ ግልፅ ነው ። ሰው በህግ ካልመራ ተግባሩ ከእንስሳት ያነሰ ይሆናል ። የመንግስት አስፈላጊነት ለህዝብ ጥቅም እንጂ የመንግስት ሹማምንት ኑሮ ለማደላደል አይደለም ። መሬት የዜጎች ተፈጥሯዊ ይዞታ በመሆኑ መንግስት የመሬት ግብር መሰብሰብ እንጂ መሬት ሺያጭና ልዋጭ እጁ ማስገባት አልነበረበትም ። በኢትዮጵያ የመንግስት ከፈተኛ የገቢ ምንጭ መሬት በመሆኑ የመልካም አሰተዳደር ችግር እንዲሰፋፋ ምክንያት ሆነዋል ። የመንግስት ሀላፊዎች መሬት በህገ ወጥ በመሸጥ የሚያገኙት ገንዘብ በወር በመንግሥት ሰራተኝነት ከሚያገኙት በብዙ እጥፍ የበለጠ ነው ። በኢትዮጵያ ድሐ ህዝብ እንጂ ድሐ ባለስልጣን ለመኖሩ እርግጠኛ መሆን አይቻልም ። በልማት ምክንያት ሰው ከመሬቱ እያፈናቀሉ የመሬት ንግድ ገበያ ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ የመንግስት ሀላፊዎች ህዝብ ለሚያነሳቸው የመብትና የጥቅም ጥያቄዎች ባንዳ አሰያሉ ከማስፈራራት ውጭ ለተገቢው የህዝብ ጥያቄ ተገቢ ምላሽና መፍትሄ መሰጠት ላይ ውጣውረድ አለ።

ለህዝብ በቀጥታ ተደራሽ ያልሆነ የመንግስት አሰተዳደር የግልፅነትና ተጠያቂነት ችግሮች ይኖሩታል ። የችግሩ መንስኤ ደግሞ መንግስት በዲስኩር ላይ የተንጠለጠለ መርህና ህግ አልባ ህዝባዊ ሆነ አገራዊ ምልከታ ሲኖር ነው ። መንግሥት ብሎ ሲያበቃ ይህን ፣ ያን አላልኩም ፣ አልሰማሁም ካለ የግልፅነትና የተጠያቂነት ችግር አለ ማለት ነው ። በኢትዮጵያ ስህተት ፈፅሞ ህዝብ የሚከዳ መሪ እንጂ ስህተቱን የሚያምንና ለዛም የሚፀፀት መሪ አልታየም ። ለዚህ አብይ ምክንያት ደግሞ መንግስት ከህዝብ ፍላጎት የራቀ መሆኑን ያመላክታል ። አንድም ዜጋ ቢሆን አለአግባብ የመብት ሆነ የጥቅም ጥሰት ሲፈፀምበት መንግስት የማይከታተል ከሆነ ህዝብ በመንግሥት ላይ ያለው አመኔታ ይቀንሳል ። የዜጎች መብትና ተጠቃሚነት በድርድር ሳይሆን በህግ ልዕልና ይፈታል ።

አሁን ኢትዮጵያን እያስተዳደረ ያለ የኢህአዴግ ጥምረት የፖለቲካ ድርጅት ህልውና ከጊዜ ጊዜ እንደ ቅቤ እየተናጠ ይገኛል ። የሰጥቶ መቀበል የፖለቲካ መርህ የሌለው ድርጅት የሚቀጥለው አመት ተደምረን ሐያ ዘጠኝ የስልጣን አመታት በህይወት ቆይተዋል። የኢህአዴግ ድርጅት ምንም እንካን ዕድሜ ጠገብ ቢሆንም በድርጅቱ ውሰጥ ይሁን ከድርጅቱ ውጭ መሬት የሚነካ የበሰለ የፖለቲካ ውይይትና ድርድር ልምዱ እምብዛም ከመሆኑም በላይ የሴራ ፖለቲካ የሚያራምድ ደንቃራ የፖለቲካ ድርጅት ሆኖ ቆይተዋል። የኢህአዴግ የፖለቲካ ድርጅት በራሱ ውስጣዊ ችግሮች ተጠልፎ የወደቀ ሲሆን ሌላው ፍርድ ቤት የማያውቃቸው የግል እስርቤቶች የነበሩት ድርጅት ሆኖ በታሪክ ይጠቀሳል ። በኢትዮጵያ በዘመነ ኢህአዴግ ሁለት እስርቤቶች ነበሩ ። የመንግስት እስርቤቶች እና የግል እስርቤቶች ። ግለሰቦች ከህግ በላይ ሆኖ እንደ ሸቀጥ ንግድ ድብቅ የግል እስርቤት ከፍቶ በሽብርተኛ ሰም ዜጎች ያሰቃዩ ነበር ። ይህ እንግዲ በኢትዮጵያ ታሪክ የግል እስርቤት የነበረው መንግስት የኢህአዴግ መንግስት መሆኑ ታሪክ ይመዘግበዋል። የኢህአዴግ ስርአትና መንግስት ልዩነት የላቸውም ። በኢህአዴግ ዘመነ መንግስት የመንግስት ሥራና የፖርቲ ሥራ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታ ሆኖ አሁን ያለበት ሁኔታ ደርሰዋል ።

የአዲስ አበባ ባለቤትነት ጉዳይ የኢትዮጵያ ህልውና ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የኢህአዴግም የህልውና ማክተሚያ ደውል ነው ። በአንድ አገር የሚኖር ህዝብ ልዩ ጥቅም ወዘተ እያለ ሲዘባርቅ የከረመ የኢህአዴግ ሰርአት ግንቦት 20, 1983 .ም በድል አዲስ አበባ እንደገባ በግንቦት ወር 2012 .ም አዲስ አበባ ላይ የቀብር ሰነ ስርአቱ በደመቀ ሁኔታ በህዝብ ምርጫ ይቀበራል ። የአዲስ አበባ ጉዳይ የአዲስ አበባ ነዋሪ ጉዳይ ብቻ አይደለም ። የአዲስ አበባ ጉዳይ የሁሉም የኢትዮጵያ ህዝቦች የጋራ ጉዳይና ጉዳት ነው ። የኢትዮጵያ አገር አቀፍ የፖለቲካ ፖርቲዎች የምርጫ ውድድር ተራዘመ አልተራዘመ የአዲስ አበባ ባለቤትነትና ልዩ ጥቅም የሚያቀነቅን የፖለቲካ ፖርቲ በህዝብ ነፃ ምርጫ ይደፈቃል። የኢትዮጵያ ህዝብ ቀጣይ ዋና የምርጫ አጀንዳ አዲስ አበባን ከቅርምት ማዳን ሲሆን ሥራ አጥነት እንዲሁም የህግ የበላይነት የቀጣዩ አገር አቀፍ የስልጣን ወድድር ወሳኝ ጉዳዮች ናቸው ። አሁን የኢትዮጵያ ፖለቲካ መልክ ይዘዋል ። የፖለቲካ ሀይል አሰላለፍ በሦስት (3) አማራጭ መንገዶች ላይ የቆመ ነው ። (1) የብሔርተኝነት የፖለቲካ አሰላለፍ ፣ (2) የፌዴራል አወቃቀር ሰርአት የፖለቲካ አሰላለፍ ፣ (3) የአንድነት ሐይል የፖለቲካ አሰላለፍ ሲሆኑ በአንድነት ሐይልና በፌዴራል ሐይል የተራራቀ ልዩነት የላቸውም ። የ

ኢትዮጵያ ውስጥ ዘረኝነት ከሚገባው በላይ ፈርጥመዋል። ነገሩ አፈር በዱቄት ይሰቃል ሆነና አንዱ ህዝብ ሌላውን ክልሌ ፣ ከአገሬ ፣ ከሰፈሬ ውጣልኝ ሲል ይሰማል ። ያፈናቀለ ህዝብ ደግሞ ራሱ በሌላ ህዝብ ይፈናቀላል ። ይህ እንደ ህዝብና አገር አስነዋሪና አሳፋሪ ነው ። ቀደም ሲል ድህነት የኢትዮጵያ መለያ ምልክት ነበር ።አሁን ደግሞ የድህነት ማጣፈጫ ክፋትና ብልግና ተጨመረበት። የኢትዮጵያ ህዝብ ሰክኖ ማሰብ የሚገባ ጉዳይ አለ ። ይህም ለመጪው ትውልድ እውቀት ፣ አንድነትና ፍቅር እንጂ ዘረኝነት ማውረስ የለበትም ። ህፃናት አገራዊ ራዕይ እንጂ ጎሳዊ አመለካከት እንዲያዳብሩ ማስተማር ተገቢነት የለውም ብቻ ሳይሆን ለአገር ግንባታና እድገት አይጠቅምም ። አገርና ህዝብ የሚያስተዳድሩ መሪዎች የህዝብና የአገር ትሰሰራዊ እድገትና መረጋጋት ላይ ከማተኮር ይልቅ በዜማና ግጥም ባስገኙት የሥራ ውጤት ሳይሆን ብሔር ተኮር አጉል ውደሳ ሲሹ ማየት የተለመደ ሆነዋል ። ለህፃናት ግጥምና ዜማ ተደርሶ እየተሰጠ መሪ እንዲያወድሱ ማድረግ የአምባገነን መሪ ማሳያ ከመሆን የዘለለ ውጤት የለውም ። ለአብነት : አንደኛ አመት የለውጥ ጉዞ ለመዳሰስ በሚሊኒየም አደራሽ በተካሔደው ህዝባዊ ሰብሰባ የአቶ ለማ መገርሳና የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሰም በግጥምና ዜማ የኦሮሞ ልጆች እየተባሉ ሲወደሱ በፌሽታ ሲወራጩ ማየቴ ግርምት አሳድሮብኛል ። ይህ ብሔር ተኮር ውዳሴ ጠቀሜታው አልታየኝም ። በድርጊቱም አዝኛለሁ ። ማንም በማታውቀው ህፃን ልጅ የኪነጥበብ ለዛ አላብሶ ምርጥ የኦሮሞ መሪዎች እየተባለ ማቆለማመጥ ምን የሚሉት የስልጣኔ ዘመን ነው ። የአገር ህዝብ በተሰባሰቡበት ቦታ ሰለ ኦሮሞ መሪ መደስኮር ምን ማለት ነው ። ካልተሳሰትኩ በቀር ዶክተር አብይ የኦሮሞ ተወላጅ አይደሉም ያለ ህዝብ ያለ አይመስለኝም ። ታድያ ዶክተር አብይ ለምን ይህን ያህል ውዳሴ አስፈለጋቸው ?። የኢትዮጵያ ኪነጥበብ ባለሞያዎች ለመሪዎች ያልተገባ ውዳሴ ማበርከት የኪነጥበብ ውድቀትና ዝቅጠት ያሳይ እንደሆነ እንጂ መሪ ማቆለማመጥ የኪነጥበብ ሞያ አይመስለኝም ። ሰለሆነም ቢታሰብበት መልካም ነው እላለሁ ። በኢትዮጵያ ውስጥ መሪዎች ምን ሰርቶ ይወደሳሉ ?። የኢትዮጵያ ኪነጥበብ ባለሞያዎች መሪዎች በዘፈንና ግጥም የፖለቲካ መሪዎች ለማወደሰ በቂ ጊዜ ያላቸው አይመስለኝም ። ትርፍ ጊዜ ካላቸው ለወገን የሚተርፍ ተግባር ላይ ቢያውሉት ተመራጭ ነበር ። ኪነጥበብ የፖለቲካ መሪ ለማወደሰ ጊዜ ካላት ኪነጥበብ በመቃብር ጫፍ ላይ መሆኗ መገንዘብ ያሰፈልጋል ። የኢትዮጵያ ኪነጥበብ ባለሞያዎች ደጋግሞ እንዲያስቡበት የሚያስፈልገው ጉዳይ መንግስት ወይም የፖለቲካ መሪ በማወደሰ የኪነጥበብ ዘርፉን ማቆራቆዝ እንደሌለባቸው ይሆናል ። መልካም የሠሩ መሪዎች በታሪክ ማህደር ቢታወሱ እንጂ ተገቢነት በሌለው የኪነጥበብ ጫጫታ አይመስለኝም ።

አዲስ አበባ ከተማ ባለቤት የኦሮሞ ህዝብ ነው ለሚል መሪ ፣ የጋራ መኖሪያ ቤት የእጣ እድለኛ ዜጎች ቤታቸው እንዳይገቡ የሚከለክል መሪ ፣ በብራዩ አና ለገጣፎ የሚኖሩ ዜጎች የሚያፈናቅል መሪ ፣ የአዲስ አበባ ባልደራስ ምክርቤት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳይሰጥ የሚያግድ መሪ ፣ ወቀሳና ኩናኔ እንጂ ውደሳ የሚገባው አይመስለኝም ። ውሰጤ በሰብሻለሁ ካለው የኢህአዴግ ፖለቲካ ድርጅት የተገኙ ዶክተር አብይ ለውጡን በሚገባ እየመሩት አይደለም የሚሉ በርካታ ትችቶች በመደመጥ ላይ ሲሆኑ እንደምክንያት የአመራር ብቃትና ግልፅነት ችግሮች እንደሆኑ ይገመታል ። የዶክተር አብይ አሰተዳደር የአዲስ አበባ ነዋሪ ያልሆኑ ዜጎች የቀበሌ መታወቂያ ያለአግባብ ሲያሰራጭ መቆየቱ የተደረሰበት ሲሆን ድርጊቱ እጅግ መወገዝ ያለበት ነው ። የሚቀጥለው የአዲስ አበባ ከተማ ምርጫ ታሳቢ ተደርጐ የአዲስ አበባ ነዋሪነት የመታወቂያ እደላ በስፋት በየክፍለ ከተሞች ሲሰጥ ቆይተዋል። ይህ ህገወጥ አሰራር በኢንጂነር ታከለ ኦማ ከንቲባነት የሚመራ የአዲስ አበባ ከተማ ህዝብ በዶክተር አብይ አመራር ላይ እምነት አጥተዋል ።

በፌዴራል ስርአቱ ላይ አንደራደርም ሲል የቆየ የኦቦ ለማ መገርሳ አመራር ባህሪው ቀይሮ እመኑኝ ኢትዮጵያ ሱሴ ነው በማለት ህዝቡን ለመደለል መሞከር የፖለቲካ የአመራር ብቃት ማነሰ አይነተኛ ምክንያት ነው ። ኦቦ ለማ መገርሳ ሆኑ ዶክተር አብይ አህመድ መርህ አልባ መሪዎች ለመሆናቸው በርካታ ምክንያቶች እየታዩ ነው ። ግብፆች አባይ ታሪካዊ ንብረታችን ነው ሲሉን ኦቦ ለማ መገርሳ እና ዶክተር አብይ አህመድ ደግሞ ውስጣዊ ግዛት ለማስፋፋት አዲስ አበባ ከተማ የኦሮሞ ታሪካዊ ግዛታቸን ነው ይሉናል ። ይህ እጅግ አስገራሚ ጉዳይ ነው ። ራሱ በራሱ የሚጣረስ ሀሳብ በመናገር ላይ ያሉ ኦቦ ለማ እና ዶክተር አብይ የአመራር ክህሎታቸው አበሳ ውሰጥ እየከተታቸው እንደሆነ በውል የተገነዘቡት አይመስለኝም ። የኦሮሞ ብሔር ተኮር የፖለቲካ ድርጅቶች አዲስ አበባ ከተማ ላይ የህዝብ ድምፅ ለማግኘት የሚያበቃ ቁመና የላቸውም ። አሁን የአዲስ አበባ ጉዳይ በዶክተር አብይ ሆነ በኦቦ ኢንጂነር ታከለ ኦማ አመራር ሥር አይደለም ። የአዲስ አበባ ጉዳይ በባልደራሰ ምክርቤት ሥር ሆኖ እስከሚቀጥለው አገር አቀፍ ምርጫ ይቀጥላል ። ዶክተር አብይ ሆኑ ኦቦ ታከለ በአዲ አበባ ከተማ ላይ ምንም ህጋዊ ሰልጣን የላቸውም ። የባልደራሰ ምክርቤት በህዝብ የተመረጠ ህጋዊ አካል ነው ። People of Addis Abeba have spoken unequivocally and handed power to Council of public trust board lead by activist and journalist Eskider Nega. በዚህ ጉዳይ ላይ የዶክተር አብይ አሰተዳደር የሐይል እርምጃ ከመውሰድ መቆጠብና ጉዳዩን በድርድርና በውይይት መከታተል ይበጃል የሚል እምነት አለኝ ። ነገር ግን የዶክተር አብይ አሰተዳደር በአዲስ አበባ ከተማ ባልደራሶች ላይ የሐይል እርምጃና አፈና ቢውሰድ የዶክተር አብይ የስልጣን ዘመን በአጭሩ ይቀጫል ። ዶክተር አብይም አፋኝ መሪ ለመሆን በር ይከፍታል ። የኢትዮጵያ ሡሤ ቃልም አብሮ ይቀበራል ። ህግ ወጥ ተግባራ እየፈፀሙ ኢትዮጵያ ሱሰ ነው ማለት ፈፅሞ አይሰራም ።

ከምንም ይሻላል እና ዶክተር አብይ በአንድ አመቱ የለውጥ ሒደት ባልተሳኩ ጉዳዮች ላይ ለህዝብ ይቅርታ መጠየቃቸው ተገቢነት አለው ። ሆኖም ዶክተር አብይ መሥራት እየቻሉ ያልሠሯቸው በርካታ ጉዳዮች ነበሩ ፣ አሉም ። አንድ የህግ ልዕልና በቅጡ ተግባር ላይ አልዋለም ። በየክልሉ ያሉ በሰብዓዊ መብትና ሙስና የተጠረጠሩ ባለስልጣናት ለፍርድ አልቀረቡም ። የዜጎች መፈናቀል እና ህገ አልባነት መስፈን ፣ የስልጣን አሿሿም ችግሮች ፣ እንዲሁም የህግ ልዕልነት ለማስፈፀም የአቅም ውስንነትና ግልፅነት ችግሮች ነበሩ ፣ አሉ ። የዶክተር አብይ የአመቱ ስኬቶች ስንቃኝ የፖለቲካ እስረኞች መፈታት ፣ የሴቶች ከፍተኛ የስልጣን ተሳትፎ መጨመር ፣ የዲሞክራሲ መስፋት ፣ የምርጫ ቦርድ በገለልተኛ አካል እንዲመራ ማድረግ ፣ የፍትህ ተቋማት እንዲጠናከሩ መጣር ፣ ከጎረቤት የኤርትራ ህዝብ ጋር የሰላም ስምምነት ማድረግ በበጎች ከሚጠቀሱ ጉዳዮች ውስጥ ናቸው ። ሆኖም በአንድ አመት ውስጥ በዶክተር አብይ አህመድ የተከናወኑ መልካም ጅምሮች ተቋማዊ መልክ ገና አልያዙም ። ሌላው ችግር የዶክተር አብይ ለውጥ ከላይ ተንሳፍፎ ያለ መሆኑ ነው ። አሁን በየክልሉ የመልካም አሰተዳደር ፣ የዲሞክራሲ ፣ የፍትህ ፣ የስርአት አልበኝነት ፣ የመሬት ወረራ ፣ የኢኮኖሚ ፣ የሰላምና መረጋጋት ችግሮች አሉ ። ለውጡ ሰር ሥር አልሰደደም። የተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች በሁሉም የአገሪቱ ቦታዎች ተዘዋውሮ ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ለማድረግ አይችሉም ። ህገ አልበኝነት በሁሉም ክልሎች ተስፋፍቷል ። የየክልል መሪዎች የአፈና መረብ ዘርግተዋል ። አፈና እየተስፋፋ ይገኛል ። የህዝብ መፈናቀልና የምግብ እጥረት እየተስተዋለ ይገኛል ። የመጠላለፍና የደባ ፖለቲካ አሁንም እንደሰጋት ይታያል ። ዜጎች በአገራቸው ማስፈራራትና ዛቻ ከመንግሥት ሆነ ከኦሮሞና አማራ ወጣቶች (ቄሮ +ፋኖ) ይደርስባቸዋል ። ገጀራ ፣ ሜንጫና አጠና ዜጎች ለማሸበር የቄሮዎች አስነዋሪ ተግባር የዶክተር አብይ አሰተዳደር ተግባሩ ህገወጥ መሆኑ እየታወቀ ሊያወግዘው አልቻለም ። የፋኖ ወጣቶች ክላሽ አንግቦ ጎደና ላይ ሲወጡ ከመንግሥት ማስጠንቀቂያ ሆነ ውግዘት አልደረሳቸውም ። መንግስት ህገወጥ እንቅስቃሴዎች የመግታት ግዴታ ቢኖርበትም የአፈፃፀም ችግሮች በስፋት አሉት ።

 

Back to Front Page