Back to Front Page

የነ ለማ-ገዱ ሹመት፣ "ባልተልተቀደሰ ጋብቻ የኦሮ-ማራ ጥገኛ ገዢ መደብ" መፈጠር ያሳያል

የነ ለማ-ገዱ ሹመት፣ "ባልተልተቀደሰ ጋብቻ የኦሮ-ማራ ጥገኛ ገዢ መደብ" መፈጠር ያሳያል

ከህዳሴ ኢትዮጵያ

ሚያዝያ 12፣ 2011 ዓ.ም.

ኢትዮጵያ ለውጥ የሚያስፈልግባት አገር መሆንዋ የማይስማማ ማንም የለም ቢባል ማጋነን ኣይሆንም፡፡ ምክንያቱ የኢህአዴግ ተቃዋሚ ብቻ ሳይሆን ኢህአዴግ ራሱ እንደ ገዢ ፓርቲ ላለፉት 27 ዓመታት ከፍተኛ ውጤት አስመዝግቤአለሁ ብሎ የሚያምን ቢሆንም፤ የተመዘገበው ውጤት ማስቀጠል የሚቻለው ከተለመደው ኣካሄድ ውጭ አገራዊና ዓለማዊ ሁኔታ ያገናዘበ ለውጥ ሲደረግ ብቻ ነው ብሎ ያምናል፡፡ ህወሓትም ሌሎች እህት ድርጅቶችም በዚህ ላይ ልዩነት የላቸውም፡፡ ስለዚ የገዢው ፓርቲ ተቋዋሚዎችም ደጋፊዎችም ለውጥ መኖር ሁሉም ይፈልጉታል፡፡ ኢህአዴግ እንደ ኢህአዴግ ለውጥ የሚፈልግ ቢሆንም ልዩነቱ ግን በለውጡ ይዘት እና ሂደት ነው፡፡ ኣንዱ ለውጡ በጥልቅ ተሃድሶ ባስቀመጣቸው አቅጣጫዎች መሄድ አለበት ሲል፣ በስልጣን ላይ ያለው ደግሞ ኢህአዴግ የገነባው ስርዓት ፈርሶ በሌላ መተካት ኣለበት የሚል ነው፡፡

እነዚህ ሃይሎች ሁለቱም ከኢህአዴግ የወጡ ሲሆኑ፣ አንዱ ወይም ህወሓት የሚያራምደው አመለካከት አብዮታዊ ዴሞክራሲ ተጠናክሮ፣ ታድሶ መቀጠል ኣለበት፡፡ ኢትዮጵያ ያለ ኣብዮታዊ ዴሞክራሲ ትፈራርሳለች ሲል፤ በቲም ለማ-ገዱ የሚመራው ኣካል ደግሞ ኣብዮታዊ ዴሞክራሲ ኣብቅቶለታል ስለዚ ሌላ አጥንተን እስክናመጣ ድረስ በትእግስት ጠብቁን ጊዜ ስጡን፣ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ግን አበቃለት ይላል፡፡ ለዚህም ነው በ11ኛው የኢህአዴግ ጉባኤ የብአዴን ተወካዮች አልተሳካላቸውም እንጂ፣ አብዮታዊ ዴሞክራሲን ቀብረው ለመመለስ ነበር ታጥቀው የመጡት፡፡

Videos From Around The World

በሰከነ አእምሮ ከተከታተልነው፣ የነለማ-ገዱ ቡድን ስልጣን ከያዘበት ቀን ጀምሮ በየቀኑ የሚወስዳቸው እርምጃዎች ያልተጠኑና ስሜታዊነትን የተጠናወታቸው እርምጃዎች ሆኖው ዓላማቸው ደግሞ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ አሻራ ማጥፋት ነው፡፡ ህወሓት እና የትግራይ ህዝብ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ስር ተጠልለው በተነፃፃሪ ለረጅም ጊዜ የታገሉና ከፍተኛ መስዋእትነት የከፈሉ ድርጅት እና ህዝብ በመሆናቸው አብዮታዊ ዴሞክራሲ ሲሸረሸርም ቀድመው የነቁ እነሱ ብቻ ነበር፡፡ ለነዚህ ም ነው ህወሓት እና የትግራይ ከፍተኛ የለውጥ ፍላጎት ቢኖራቸውም የነለማ-ገዱ ቲም የሚወስዳቸው እርምጃዎች ገና ከጅምሩ ተቋውሞቻቸውን ሲያሰሙ የነበረው፡፡ ይሁንና ከቡዱኑ የተሰጣቸው ምላሽ ግን ፀረ ለውጥ፣ የቀን ጅቦች የሚል ስያሜ ነበር፡፡

ኢህአዴግ እንደ ኢህኣዴግ መቆም የሚችል በኣብዮታዊ ዴሞክራሲ ብቻ ነው፡፡ ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ ውጭ 4ቱ የኢህአዴግ እህት ድርጅቶች አንድ ሊሆኑ እና ሊስማሙ ኣይችሉም፡፡ የኢህኣዴግ ኣባል ድርጅቶች ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ እስከወጡ ድረስ የሚኖራቸው ግንኝነት በመርህ ላይ የተመሰረተ ሊሆን ኣይችልም፡፡ ለዚህም ነው  አሁን እያየነው ያለው የአዴፓ እና የኦዴፓ ግንኝነት የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው በሚል ጊዝያዊ ዕርቅ እንጂ ዘለቄታዊ ሊሆን ኣይችልም የሚባለው፡፡ በመሆኑም ኣብዮታዊ ዴሞክራሲ የሚነካ ኣንድ ኣጀንዳ ሲፈጠር እርስ በርሳቸው ሲፋጁ ማየት የተለመደ ሆኖዋል፡፡ ለምሳሌ የአዲስ አበባ ጉዳይ ሲነሳ እየተነታረኩ ያሉት አዴፓና ኦዴፓ ናቸው፤ በአማራ ክልል የኦሮሚያ ልዩ ዞን ጉዳይ ሲነሳ ህዝቡ እያፋጁት ያሉት ኦዴፓ እና አዴፓ ናቸው፡፡ ስለዚህ ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ ውጭ የሚደረግ ማንኛውም ግንኙነት የተንኮል፣ የድብቅ ሴራ እና የመጠላለፍ ከመሆን ውጭ ሌላ ሊሆን ኣይችልም፡፡

አብዮታዊ ዴሞክራሲ ማንኛውም ህዝብ እንደ ህዝብ እኩል መብት አለበት፣ እኩል መደመጥ ኣለበት፣ እኩል መሳተፍ አለበት ይላል፤ ቲም ለማ ግን ይህን በመጣስ በህዝብ ብዛት መሆን አለበት ይላል፡፡ ብዙ ህዝብ ያለበት እና ጥቂት ህዝብ ያለበት እኩል መብት ሊኖረው አይገባም ስለዚ በዚች አገር ወሳኙ ብዙ ህዝብ ያለበት ነው ስለዚህ አማራ እና ኦሮሞ ከተስማሙ የሌሎች ህዝቦች ጉዳይ ኢምንት ነው ይላሉ፡፡ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ እምነት አማራ እና ኦሮሞ መቸም ተጣልቶ አያቅም፣ አንድ ህዝብ ከሌላ ህዝብ የሚያጣላ ነገር የለውም ለወደፊትም የሚያጣላቸው ነገር አይኖርም፡፡ እየተጣሉ የነበሩ ከህዝቦች አብራክ የወጡ ጥገኞች ብቻ ናቸው፡፡ እነዚህ ጥገኞች ከአሁን በፊትም ነበሩ፤ አሁንም አሉ፤ ወደፊትም ይኖራሉ፡፡ ነገር ግን እነዚህ ጥገኞች ስልጣን ከያዙ ኢትዮጵያ ወደኋላ መንሸራተትዋ ኣይቀርም፡፡ እነዚህ ጥገኞች በስልጣን በኖሩባቸው ባለፉት ዘመናት ለስልጣን ማቆያ ይጠቀሙበት የነበረው ስልት ማጋጨት፣ መለያየት፣ መብቶችን መርገጥ ነበር፡፡ እነዚህ ሀይሎች ከስልጣን ተወግደው እኩልነት በተረጋገጠበት 27 ዓመታት ደግሞ ሰላም፣ መረጋጋት እና ልማት ሰፍኖ ነበር፡፡ አሁን ተመልሶ ጥገኛ ሀይል ስልጣን ሲቆጣጠረው ኢትዮጵያ ወደኋላ መጓዝ ጀመረች፡፡ ይህ ጥገኛ ሃይል ህዝብ ከህዝብ ለመለያየት እየተጠቀመበት ያለ ስልት ኦሮ-ማራ የሚል ነው፡፡ በተግባር ግን የኦሮ-ማራ ስልት አማራና ኦሮሞ ሲያጋጭ እንጂ ሲጠቅም አልታየም፡፡ በአሁኑ ሰዓት በጣም የከፋው ህዝብ ኦሮሞ እና አማራ ነው፡፡ በስልጣን ላይ ያለው ሀይል በስሙ እየነገደ ከሌሎች ህዝቦች እያጋጨው ይገኛል፡፡ የኦሮሞ ወጣት የአማራ ወጣት ጥያቄ ከትግራይ ወጣት ከደቡብ ወጣት ከሶማሌ ወጣት ጥያቄ የሚለየው ነገር የለም፡፡ ሁሉም አንድ ነው፡፡ የስራ ፈጠራ ጥያቄ ነው፣ የፍትሀዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ ነው፡፡ ታድያ በስልጣን ላይ ያለው ሀይል ኢትዮጵያን ያክል የብዙ ህዝቦች አገር እየመራ ኦሮ-ማራ የሚል ምን አመጣው፡፡ ኦሮ-ማራ እያለ በአዲስ አበባ ኦሮሞ እና አማራ ማጋጨት ለምን ተፈለገ? በአማራ ክልል የኦሮሞ እና የአማራ ህዝብ በፀጥታ ሀላፊዎች ገፊነት ግጭት መፍጠር ለምን ተፈለገ? ታድያ ኦሮ-ማራ እንዴት ኦሮሞ እና አማራ ይወክላል? ገዢዎች ማንም ህዝብ ኣይወክሉም፡፡ ነፍጠኛው ሚኒሊክ የአማራ ህዝብን አይወክልም ነበር፣ አሁንም ኦሮ-ማራ የኦሮሞም የአማራም ህዝብ አይወክልም፡፡ ኦሮ-ማራ በ21ኛው ክፍለዘመን ባልተቀደሰ ጋብቻ የተፈጠረ አዲስ የጥገኞች ገዢ መደብ ነው፡፡

በአብዮታዊ ዴሞክራሲ እምነት ህዝብን እንደ ህዝብ ለያይቶ ማየት ከተጀመረ፣ አንድን ህዝብ ከሌላው ህዝብ ማበላለጥ ከተጀመረ፣ በቃ ዴሞክራሲ አበቃለት ማለት ነው፡፡ ወደ ገዢ መደብ ተቀየረ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ኦሮ-ማራ ማለት ገዢ መደብ ማለት ነው፡፡ በኦሮሞ እና በአማራ ህዝብ ለመነገድ የተፈበረከ ስልት ነው፡፡ ለአንድ ህዝብ ፀረ ዴሞክራሲ የሆነ ለሌላ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ሊሆን አይችልም፡፡ ፀረ ዴሞክራሲያዊነት ባህሪ ከተያዘ ገደብ የለውም ዙሮ ዙሮ መለያ ባህሪው ፀረ ዴሞክራሲያዊ ከመሆን አይድንም፡፡ ስለዚ የቲም-ለማ ወይም የኦሮ-ማራ አመለካከት ለማንም ኣይበጅም፤ እንኳን ለኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች ይቅር፣ እወክለዋሎ ለሚሉት ለአማራም ለኦሮሞም ኣይበጅም፡፡ የሌሎች ህዝቦች መብት መከበር እንዲሁም የሌሎች ህዝቦች እኩል ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት መረጋገጥ፣ የአማራ እና የኦሮሞ ህዝብ ጥቅም አይነካም፡፡ በታሪካችንም በሳይንሳዊ ትንታኔም ቢሆን፣ የአንድን ህዝብ መብት የረገጠ፣ ተሳትፎ የገደበ ሃይል በባህሪው ፀረዴሞክራሲ በመሆኑ፣ የማንም ህዝብ መብትና ጥቅም ማረጋገጥ አይችልም፡፡ ኢትዮጵያ የጥቂት ፈላጭ ቆራጭ ሰዎች አገር ትመስል ቲም ለማ ከመርህ ውጭ በህዝብ ሃብት እና ስልጣን እንደፈለገው ሲፈነጭ ይታያል፡፡

የኢትዮጵያ ልዩ እና ነባራዊ ሁኔታ ሲታይ አንዱ ብዙሀነት ነው፡፡ ይህ ቡዝሀነት ደግሞ በጥንቃቄ ካልተያዘ በጣም አደገኛ ነው፡፡ ብዙሀነታችን በዴሞክራሲያዊና ፍትሃዊ አገባብ ካላስተናገድነው አደገኛ ነው፡፡ ጊዜ ባመጣው ዕድል በ21ኛው ክፍለዘመን አስተሳሰብ አንድ ሚልዮን የማይሞላ ህዝብ ያላት ጁቡቲ እና ከመቶ ሚልዮን በላይ ህዝብ ያላቸው ናይጀርያ፣ ኢትዮጵያና ግብፅ በአፍሪካ አንድነት ድርጅት እኩል መብት አላቸው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ግን መራራ ትግል አልፎ ከባድ መስዋእትነት ከፍሉ በኢትዮጵያ ከአንድ ሚልዮን በታች የዜጎች ብዛት ያላቸው ብሄሮች እና በአስር ሚልዮን የሚቆጠር ዜጋ ያላቸው ብሄሮች እኩል የመደመጥ መብት አረጋግጠው ለ27 ዓመት በሰላም፣ በመቻቻል በፍቅር ለመኖር በቅቷል፡፡

አሁን የነቲም-ለማ ዱድን በብቸኝነት ስልጣን ከተቆጣጠረ ቦኋላ ግን አንዱን ህዝብ ከሌላው ህዝብ ማበላለጥ በመጀመሩ፣ አንዱን ህዝብ ሌላውን ህዝብ በድሏል ማለት በመጀመሩ፣ እንዲሁም በስልጣን ላይ ያለው አካል አንዱን ታማኝ ሌላው የማይታመን ተደርጎ መወሰድ በመጀመሩ በምንወዳት አገራችን ሰላም እና መረጋጋት ታጥቶ፣ የዜጎች መፈናቀል ሰማይ ነክቶ፣ የዜጎች እንቅስቃሴ ተገድቦ፣  የመበታተን ደመና አንዣብቦብናል፡፡ ከ60% በላይ የኢትዮጵያ ህዝብ አብራክ ነው የወጣነው ስለዚ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የኢትዮጵያ ህዝብ እኛን መስማት አለበት የሚለው ቲም-ለማ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ መርህ በመጣስ፣ በኢህአዴግ ውስጥ ህቡእ ቡዱን (ቲም-ለማ የሚባል) ተቋቁሞኢህአዴግ ባበጀው የስልጣን መወጣጫ መሳለል ተጠቅሞ የስልጣን ኮርቻው ከተቆጣጠረ ቦሃላ ኢህአዴግ የገነባውን መንግስታዊ ስርዓት ማፈራረስ መጀመሩ አገራችን ኢትዮጵያ በህልውናዋ ከፍተኛ አደጋ ተጋርጦባት ትገኛለች፡፡

ይህ አደጋ ገና ከጅምሩ የተገነዘበው የህወሓት አመራር ለኢትዮጵያ ህዝብ የማስጠንቀቂያ ደወል ወይም ብጫ መብራት ሲያሳይ፣ ቲም-ለማ ግን በቀላሉ ስልጣን በመቆጣጠሩ በደስታ ሰክሮ ማስጠንቀቂያው እንደ-ቁብ አልቆጠረውም፡፡ ይባስ ብሎ ማፌዝ እና ማስፈራራት ነበር የተያያዘው፡፡ ቲም-ለማ ይህን የህወሓት ማስጠንቀቂያ እንደ ፀረ ለውጥ አድርጎ በመውሰድ ሲሳለቅበት ታይቷል፡፡ ቲም ለማ አሁን ከስካሩ እና ከሱሱ መንቃት የጀመረ ይመስል ከአንድ አመት ቦኋላ ኢትዮጵያ በመፈራረስ ላይ እንዳለች፣ ከቁጥጥር ውጭ እየሄደች እንዳለች የተገነዘበ ይመስል በየጊዜው አዳዲስ የስልጣን ሹምሽር ሲያደርግ ይታያል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ቲም-ለማ ኢትዮጵያን መምራት እንደማይችል ማንኛውም ዜጋ በደንብ ተገንዝቦታል፡፡ በስሜት ሲደግፉት የነበሩም ሳይቀር ማፈግፈግ ጀምሯል፡፡ ሌላ ቀርቶ የለውጡ መሪዎች ከሚባሉት ጥቂት ግለሰቦች አንዱ ወይም የውጭ ጉዳይ ሚኒስተር የነበሩት ዶክተር ወርቅነህ በዚህ ቀውጢ ሰዓት አገራቸውን ትተው፤ የለውጡ/ነውጡን ቡዱን ትተው የተሻለ ጥቅም እና ምቾት ይገኝበታል ብለው ባሰቡት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተቀጣሪ ሆኑ፡፡

በነዚህ ስግብግብ የስልጣን ጥመኞች ምክንያት ኢትዮጵያ ወደ ማይቀለበስ ከፍተኛ ችግር ውስጥ እየገባች መሆኑ የሚያሳየው ሌላ መገለጫ ቲሙ የሚያስተዳድረው ክልል ማረጋጋት ያለመቻሉ እና በቲሙ የሚመሩ ኣመራሮች እርስ በርሳቸው መተማመን ጠፍቶ፣ መጠላለፍ ነግሶ በየሳምንቱ አዲስ አጀንዳ፣ አዲስ ንትርክ እና እልቂት እያስተናገዱ ይገኛሉ፡፡ አንዴ በአዲስ አበባና ዙሪያው ሌላ ጊዜ በአማራ ክልል የኦሮሚያ ዞን ውስጥ የአዴፓ እና የኦዴፓ አመራሮች የብሄር እና የድንበር ግጭት እየሎኮሱ ለዘመናት ኣብሮ ተከባብሮ ይኖር የነበረ ህዝብ እያፋጁት ይገኛሉ፡፡

የኢትዮጵያ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ያሳሰበው ይመስል ቲም ለማ በለውጡ/ነውጡ እንቅስቃሴ የአንበሳ ድርሻ የነበራቸው የኦሮሚያ እና የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድሮች ከክልላቸው በማንሳት ለዶ/ር አብይ አሕመድ እንዲደግፉ በሚኒስተርነት እንዲሾሙ ተደርጓል፡፡ ከአንድ ዓመት ቦሃላ የኢትዮጵያ ሁኔታ መገንዘብ መቻሉ አንድ ነገር ሆኖ፤ አሁን ቲሙ ያልተገነዘበው ነገር ግን የችግሩ መፍትሄ ላይ ነው፡፡ ቲሙ ካለው የስልጣን ጥማት የተነሳ ስልጣን ካለህ ሁሉም ነገር ታደርጋለህ የሚል ኣመለካከት ስላለው የፌደራል ስልጣን በመቆጣጠር አገርን መምራት ወደፈለከው መውሰድ ይቻላል በሚል ይመስላል የክልል ርእሰመስተዳድሮች ወደ ፌደራል ያመጣቸው፡፡ የኢህአዴግ መሳልል ተጠቅሞ ወደ ስልጣን የመጣው ይህ ጥገኛ ቡድን የፌደራል ስርዓቱ ህልውና ችግር ውስጥ መግባቱን እንጂ የህልውናው ምሶሶ ምን እንደሆነ አልተገነዘበም፡፡

የችግሩ መፍትሄ ለመረዳት የግድ እንደገና አንድ ዓመት መጠበቅ አለብን እንዴ? የኢትዮጵያ ህዝብ አንድ ዓመት ይጠብቀናል ብለው ያስባሉን?

ኢህአዴግ የፈጠረው ፌደራላዊ ስርዓት የህልውናው ምሶሶ ክልሎች ናቸው፡፡ አሁን ስልጣን የተቆጣጠረው ጥገኛው ቲም ወደ ስልጣን የመጣውም በነዚህ ክልሎች አማካኝነት ነው፡፡ ታድያ ለምን ክልል ሳታረጋጋ፣ የክልል ህዝብ ህገመንግስታዊ መብት ማስጠበቅ ሳትችል፣ በየክልሉ የህግ የበላይነት ማስከበር ያቃተው አመራር እንዴት በፌደራል ስልጣን ሆኖ አገርን መምራት ይችላል?

አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የኣማራ ክልል ሰላም ማረጋጋት ያልቻሉ፣ በአማራ ክልል ያሉ 4 ወይም 5 ብሄር ብሄረሰቦች እርስ በርሳቸው እንዲጋጩ ሲያስተባብሩ እና ሲመሩ የነበሩ፣ ለዘመናት አብሮ ይኖር የነበረ የአማራ እና የትግራይ ህዝቦች በድንበር ምክንያት ለማጋጨት አስመላሽ ኮሚቴዎች ሲያቋቁሙ እና ሽፍቶችን ሲያበረታቱ የነበሩ አመራር እንዴት የ80 ብሄር ብሄረሰብ አገር ኢዮጵያን ማረጋጋት ላይ ያግዛሉ ተብሎ ይጠበቃል?

አቶ ለማ መገርሳ ቢሆኑስ፤ በክልላቸው ሰላም እና መረጋጋት ማስጠበቅ አቅቷቸው ችግሩ በሽምግልና ለጊዜው ጋብ ባለበት ወቅት፣ በክልሉ ያሉ የተለያዩ ብሄር ተወላጆች ጥቃት ሲደርስባቸው መከላከል ወይም ማረጋጋት ያልቻሉ፣ ሌላ ቀርቶ በአዴፓ እና በኦዴፓ ኣመራሮች የሚፈጠረውን ችግር መፍታት ኣቅቷቸው የህዝብ ዕልቂት ሲያስተናግዱ የነበረ በምን ስሌት ነው በፌደራል ስልጣን ጨብጠው ኢትዮጵያን ሊያረጋጉ የሚችሉት?

እነዚህ ጥያቄዎች የጠየቅኩት ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ አመለካከት ነው፡፡

ኢትዮጵያ ጠንካራ አገር እንድትሆን ከተፈለገ ጠንካራ ክልሎች ሲኖሩ ነው፡፡ ሰላም እና መረጋጋት የሰፈነበት የህዝቦች መተማመን ያለበት፣ የህግ የበላይነት የተረጋገጠበት፣ የዜጎች በሰላም ወጥቶ በሰላም መግባት ዋስትና ያለበት ሲሆን ነው ጠንካራ አገር ጠንካራ መንግስት መኖር የሚችለው፡፡ በርካታ የአገራችን አከባቢዎች በመንጋ ፖለቲካ በሚመሩበት ሁኔታ፣ ሰላማዊ የንግድ እና የስራ እንቅስቃሴ ባልተረጋገጠበት ሁኔታ እንዴት አገርን መምራት ይቻላል?

ቲም ለማ በትክክል የበለፀገች እና ጠንካራ አገር መፍጠር የሚፈልግ ከሆነ ከታች ነው መጀመር ያለበት፡፡ ከክልል ነው መጀመር ያለበት፡፡ ጠንካራ ክልል ካለ ጠንካራ አገር ይኖራል፡፡ የፌደራል መንግስት ጠንካራ አገር ለመፍጠር የግድ ከክልል በጋራ መስራት ኣለበት፡፡ በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ችግር፣ ህዝብ እያማረረበት ያለ ችግር መፈታት ካለበት በታች በክልል ነው፡፡ ስለዚ ጠንካራ አመራር መመደብ ካስፈለገ በክልል ነው፡፡ ነገር ግን ጠንካራ ስለሆኑ፣ የለውጥ መሪ ስለሆኑ ወደ ፌደራል መምጣት አለባቸው ተብለው ቀውስ ካለበት ክልል አስነስቶ ወደ ፌደራል ማምጣት ከችግር ማፈግፈግ እንጂ ለውጡን ወደፊት መውሰድ አይደለም፡፡ አሁን በአገራችን ያለው ችግር ብቸኛው ፈውስ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ብቻ ነው፡፡ ተወደደም ተጠላም ከዚህ ውጭ መንገዱ የመፈራረስ መንገድ ነው፡፡

 

 

ከህዳሴ ኢትዮጵያ

ሚያዝያ 12፣ 2011 ዓ.ም.

hidaseethiopia@yahoo.com ወይም hidaseethiopiaa@gmail.com

 

 

Back to Front Page