Back to Front Page

“የለውጡ” አስመጪ፣ ባለቤትና ጎረቤት ማን ነው?

“የለውጡ” አስመጪ፣ ባለቤትና ጎረቤት ማን ነው?

ሰላምወርቅ ሁላገር

ጥቅምት 22/2012 ዓ/ም

አዲስ አበባ

 

ውድ አንባብያን በቅርቡ እኛ ማን ነን? ምንድነን? በሚል ካቀረብኩት አንድ ፅሁፍ ውጭ ለብዙ ግዜ መጥፋቴ እውነት ነው። እኔ ከሦስት አመታት ተኩል በፊት ጀምሮ ስጽፍ ለሙገሳ፣ ለታዋቂነት ወይም ለተደናቂነት አልነበረም። ለእውነተኛ ለውጥ ማገዝ የሚችል ከሆነ የጥርሻየ ልወጣ በሚል ነበር። ይሁን እና ሃሳቤን የተጋሩኝ የመኖራቸው ያክል “ያንተ ጭንቀት መጠኑ ያለፈ ነው” ከሚል ጀምሮ “ክፉ ሟርተኛና ብርሃን የማይታየው ጨለምተኛ” አድርገው በመሳል ከሌላ አጀንዳ ጋር አያይዘው ለማየት የሞከሩም ነበሩ። እናም አሁን እየሆነ ያለው ነገር ሳይ ምንስ ብል ምን እጨምራለሁ የሚል ስሜት ስለነበረኝ ነው።

ዛሬም ቢሆን በዚህ አገር ያልተደረገና ያልተነገረ ስለሌለ አዲስ ነገር ይዠ አልመጣሁም። እየተደረጉና እየተባሉ ያሉ ጉዳዮች እንደተለመደው ከእናንተ ጋር ስነጋገርበት ለኔ ቀለል ስለሚለኝ ነው። ለማጣቀሻ ይሆነኝ ዘንድ ከዚህ ቀደም ከፃፍኳቸው መጣጥፎች አንዳንድ ሃሳቦች ስለምጠቅስ ከዚህ ቀደም ያነበባችሁት ሰዎች ቅር እንደማትሰኙብኝ ተስፋ በማድረግ ነው። የተለመደው ገንቢም ይሁን ሌላ ማናቸውም አስተያየታችሁ እጠብቃለሁ። አመሰግናለሁ። 

ለውጥ አለ ወይስ የለም? ለውጡ ማን አመጣው? እንዴት መጣ? ለምን መጣ? ከየት መጣ? የሚለው ለማየት ለውጥ ማለት ምን ማለት ነው የሚል ይቅደም። ምናልባት በጥሬ ትርጉሙ ከተወሰደ ለውጥ ማለት አንድን ቁስ ወይም ነገር ወይም ሃሳብ(አስተሳሰብ) በቅርፅና በይዘት ወይም በአንዱ መቀየርን ያመላክታል።ስለዚህ ለውጥ እወንታዊ ወይም አሉታዊ በሆነ መልኩ መቀየርን ያመለክታል። እኛ ለለውጥ ስንጮህ የነበርነው ለየትኛው የውጥ መሆኑ ስለሚታወቅ ወደ መዘርዘር አልገባም።

ኢህአዴግ በጅምር ደረጃ የታዩ የዴሞክራሲ ወጋገን ለማጨለም ሲጀምር፣ ስር የሰደደውና የማይፈወስ የሚመስል የመልካም አስተዳደር ችግሮች ከመጥፎ ወደ ከፋ ሁኔታ ሲደርሱና የልማት እንቅስቃሴውም ወደኃላ መመለስ ሲጀምር ሁሉም በብዙ መንገድ ለውጥ ጠይቋል ለለውጥም ታግሏል። በኢህአዴግ ውስጥ ስልጣንን እንደ አንድ የኑሮ መንገድ ካዩት የተወሰኑ ባለስልጣናት ውጭ በአንዳንድ የኢህአዴግ አመራርም ጭምር ለውጥ ያስፈልጋል ያሉ ጥቂቶች አልነበሩም። እኔ በበኩሌም አባል ድርጅቶችን በተናጠል እንዲሁም እንደ ኢህአዴግ በጋራ ያላቸው መሰረታዊ ችግር ያለ ምህረት በዝርዝር በመግለፅ ምክረ ሃሳብም ጭምር በማካተት ህዝቡ ለውጥ እየፈለገ እንዳለና ለውጡ ከራሱ ከኢህአዴግ ቢመጣ ለቀጣይነታችን የተሻለ እንደሚሆን በሁሉም መጣጥፎቼ ገልጫለሁ።ሌላውም ልክ ይሁን አይሁን ልክ ነው ብሎ ባመነበት መንገድ ትግል አካሂዷል።

ዋናው ነገር ለውጡ የጮህንለትን ምክንያትና አላማ አሳክቶልናል ወይ? የሚለው ነው። በብዙዎቻችን እምነት ለውጥ ያስፈልጋል ያልነው 27 አመት በጨለማ ውስጥ ስለነበርን ከሚል የሚነሳ አልነበረም። በቀድሞ ኢህአዴግ ኢትዮጵያ በታሪኳ አይታው የማታውቀው እወንታዊ ለውጥ አይታለች የሚል የያኔው አቋሜ በኃላ  ይበልጠ ጠንክሮ እንደሆነ እንጂ አልቀነሰም። “ከለውጡ” በኃላ በባህርዳር “ምክንያታዊ ወጣቶች መድረክ” በሚል የተዘጋጀ የክልሉ ወጣቶች መድረክ አንድ ምክንያታዊ የአማራ ወጣት እንደገለፀው “የህዝቦቻችን ጥያቄዎች የተመለሱት 1983 ላይ ነው። በህዝቦች ትግል። ትግሉ አብዛኛው ህዝብ የሚያስማማ ውድና ውብ የሆነ ህገ- መንግስት አመጣ። በዚሁ መሰረት አንፃራዊ የሆነ ዴሞክራሲ፣ አንፃራዊ የሆነ ሰላም፣ አንፃራዊ የሆነ ኢኮኖሚያዊና የማህበራዊ እድገት አመጣ። ከጨለማ የመውጣት ጉዛችን የተጀመረው ከ1983 ጀምሮ ነው እንጂ አብይ ስለመጣ አይደለም።የምክንያታዊነት ወጣቶች መድረክ ስለሆነ ያገኘናቸው ለውጦች እውቅና ሰጥተን የጎደሉንንና ቅሬታ የሚፈጥሩብንን መጠየቅ ይገባናል” ብሏል። እኔም ከዚህ ወጣት ጋር ሙሉ በሙሉ እስማማለሁ። ከ1983 ወዲህ አገራችን በኢህአዴግ መንግስት በታሪኳ ያላየችው ለውጥ አስመዘግባለች የሚል እምነቴን  በ2008 ዓ/ም የካቲት ወር ኢህአዴግ ከቸልሲ ምን ይማራል በሚለው ፅሁፌ የኢህአዴግን ፈርጀ ብዙ ችግሮች ከገለፅኩ በኃላ ይሁን እንጂ ኢህአዴግ ከነበርነው የጨለማ ዘመን ለማላቀቅ የከወናቸው ተግባራት እንዲህ ገልጨው ነበር፤

--------በኃይለስላሴ ዘመንና በደርግ በ1977 ዓ/ም በአገራችን ድርቅ መከሰቱ ይታወሳል። በአንዱ የድርቅ ወቅት ብቻ እስከ አንድ ሚልዮን ህዝብ ማለቁ የውጭ ሚድያዎች ጭምር ገልፀዉታል። የተጋነነ ሊሆን ይችላል ካልን እንኳን እስከ ግማሽ ሚልዮን ብለን እንውሰድና አደጋው ምን ያክል አሰቃቂ እንደነበር እናያለን። በእነዚህ ግዚያቶች ህዝቡን የሚታደግ ፖሊሲ ቀርፆ መንቀሳቀስ የሚችል ኃላፊነት የሚሰማው መንግስት ስላልነበረን  እልቂቱን ለመቀነስ መሞከር ይቅርና ንጉሱ የንግስና ብዓላቸውን እንዲሁም ደርግ ደግሞ የኢትዮጵያ ሰራተኞች ፓርቲ (ኢሰፓ) ምስረታ በዓሉን የሚያከብሩበት ግዜ ስለነበር እነዚህ በረሃብ በቆዳ የተሸፈነ አጥንት የያዙ ዜጎች የበዓላቱ ገፅታ እንዳያበላሹ ከከተሞች ተለቅመው ወደ ሌላ ቦታ እንዲወሰዱ የተደረገበት ሁኔታ ነበር።

በዘመነ ኢህአዴግ ከደርግ ግዜ የባሰ የሚባል የድርቅ አደጋ አጋጥሞን ነበር። ለዚያውም የህዝብ ቁጥራችን ከ30% በላይ በጨመረበት ግዜ። ኢህአዴግ በተወሰነ እርዳታና በራስ አቅም ችግሩን መፍታት ችሎ እንደነበረ ብቻ ሳይሆን ያን ያክል ከባድ ድርቅ አጋጥሞን እንደነበረ እንኳን ማስታወስ በሚሳነን ደረጃ ችግሩ ፈቶታል። ይላል ፅሁፉ። (ከፅሁፉ ከተለያየ ቦታ የተወሰዱ ስለሆነ የአረፍተ ነገሮች ቅደም ተከተል ማስተካከያ ተደርጎበታል።) ቀጥሎም

ኢህአዴግ ለዝች አገር የሠራው መልካም ነገር በማን ዘመነ መንግስት ነው የተሠራው ? ያለፉት የአገራችን ሥርአቶች እንተውና አሁን ማን የምትባል የአፍሪካ አገር ነች በዚህ አጭር አመታት ብቻ ይህንን ያክል ርዝመት ያለው የባቡር መንገድ በመገንባት የህዝብ ችግር ለመፍታት የሠራች፣ ማን አገር ናት ባጭር ግዜ ይህንን ያክል ህዝብ ከድህነት ማውጣት የቻለች፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ቤቶች እየሰራች ለህዝብ በብድር ያከፋፈለች፣ ሥራ አጥ በተበራከተበት አለም ራሷ አደራጅታ ብድር ሰጥታ ሥራ ያስያዘች፣ማን የሚሏት አገር ናት ከፍተኛ በጀት መድባ ያገር ውስጥ ባለሃብትን ያበረታታች ? ማን ናት በዚህ አጭር ግዜ ብቻ ይህን ያክል የገጠርና የከተማ ህዝብ ኤሌትሪክ በማስፋፋት ህዝቡ ከጨለማ ያላቀቀች፣ የስልክ መገናኛ አገልግሎት እንዲያገኝ ያደረገች፣ ያሁሉ ሺዎች /ሜትር መንገድ በመሥራት በገጠርና በከተማ የነበረ ልዩነት ያጠበበች፣  የገጠሩ ህዝብ ሊያገኘው ይቅር ሊያስበው እንኳን የማይችለውን በአጭር ግዜ ይህንን ያክል የትምህርት፣የጤናና የንጹህ ውሃ አቅርቦትና የስልክ አገልግሎት እንዲዳረስ ያደረገች አገር ማን ናትበሚል ገልጨው ነበር። አሁንም ይህንን ጥያቄ እኔጋ አለ።

 

ኢትዮጵያ በንጉሶቹ ግዜ በንጉስና ንጉሳውያን እንዲሁም ለስርአቱ አገልጋዮች ብቻ እንደ ማንኛውም እቃ እንደ ግል ንብረታቸው ሲገለገሉባት ቆይቷል። በደርግ ግዜም ቢሆን አገሪቱ ሙሉ በሙሉ ወደ እርስ በርስ ጦርነት መግባቷ ተከትሎ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ቁልቁል ከዜሮ በታች ሆኖ “ቆራጡ መሪያችን” ለጦር መሳርያ ግዢ የተበደረውን እዳ አስቀምጦልን፣ በእጁ የነበረውን ገንዘብ በሄሊኮፍተር ጭኖ ነበር እንደ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ “ለአገሪቱ ሰላምና ለውጥ የራሱ አስተዋፅኦ ለማድረግ” ወደ ዙምባብዌ የኮበለለው። እናም ኢትዮጵያ ከዚህ ተነስታ ነው እንግዲህ ብዙዎቻችን ማወቅ ባንፈልግም በተፈጥሮ ተገደንም ቢሆን ወደ ምናውቀው ለውጥ ተሸጋግራ የነበረችው።

 

በሰላምና መረጋጋት በኩል ኢትዮጵያ በ1983 ዓ/ም በአይነቱ አዲስ ወደ ሆነ ሁኔታ እየገባች ነበረች። በወቅቱ በመቶ ሺዎች የሚገመት የደርግ ሰራዊት ከነ ትጥቁ፣ ከነ ቂሙና ቁጭቱ በአገሪቱ ተበትነዋል፣ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ብሔር ተኮር አደረጃጀት በመያዝ አንዳንዶቹ የመገንጠልን አላማ አንግበው የሚንቀሳቀሱ ከነዚህም ውስጥ ከደርግ ጋር ብቻም ሳይሆን ከኢህአዴግም ጭምር የሚዋጉ ሃይሎች በነበሩበት፣ እንደ ኢህአፓና ኢዲህ ያሉ ደግሞ በህብረ ብሔራዊነት ስም ተደራጅተው በተለይ በሱዳን አዋሳኝ ቋራና አንዳንደ የአርማጭሆ አከባቢዎች ቀዳሚ አጀንዳቸው ደርግ ሳይሆን ኢህአዴግ አድርገው በሚንቀሳቀሱበት፣ ከተወሰነ የሰሜኑ ክፍል በስተቀር ህዝቡ ኢህአዴግ ማለት ማነው ?  ምንድነው ? ካለማወቅ ባለፈ ጥቂቶች ኢህአዴግ የሰዎች ስብስብ እንደሆነ እንኳን የሚጠራጠርበት ሁኔታ ውስጥ ነበርን።

 

ወቅቱ አለማዊ ፖለቲካዊ ሁኔታው ኢህአዴግ እከተለዋለሁ ሲለው ከነበረ ርእዮተ አለም በተፃራሪ የተቀየረበት ሁኔታ እና ከተማን የማስተዳደር ልምድ የለውም ብለን በምናፌዝበት ሁኔታ ላይ ሆኖ በተደጋጋሚ እንደተገለፀው ብዙ ሰው ኢትዮጵያ ዩጎዝላቭያ እንደምትሆን ከመተንበይ አልፎ እርግጠኛ በሆነበት ሁኔታ ነው እንግዲህ  ኢህአዴግ የአገሪቱ የደህንነት ስጋት ምንጮች በመለየት፣ በመተንተን፣ ቅደም ተከተል በማስቀመጥ፣ እድሉ በተገኘ አጋጣሚ ከህዝቡ ጋር ውይይት በማድረግ ይህንን ወደ እቅድ በመቀየር አገር የማረጋጋት ስራ በተሳካ ሁኔታ አረጋግጦ አገሪቱ በሁለት እግሯ እንድትቆም በማድረግ አሁን በአለም አቀፍ ሰላም የማስከበር ስራ ስሟ ከፍ ብሎ እየተጠራች የምትገኘው አገር ያስረከበን።

 

በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ በአለም አቀፍ ዲፕሎማሲና በሌሎች መስኮችም ቢሆን ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሚባል እመርታ ያሳየች በዘመነ ኢህአዴግ ቀደም ሲል እየዘቀጡ ያሉ የአፍሪካ አገራት ከተባሉት የመጨረሻዎቹ መካከል ከኃላ ከአንድ እስከ ሦስት ቦታዋን ለዘመናት አስጠብቃ የቆየችው ኢትዮጵያ ዛሬ አለም ከፍተኛ ብቻ ሳይሆን ፈጣንና ተከታታይም እድገት እያስመዘገቡ ናቸው ብላ ስማቸው ከምትጠራቸው አገሮች ውስጥ አንድ ብላ አምስትን ሳታልፍ ኢትዮጵያ የሚል ስም ትጠራለች። ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊ ያሉትን ማመን አልችልም አልፈልግምም ለምትሉኝ ወገኖቼም ለእናንተ የምትሆን አጭር ማሳያ አለችኝ። ይህንን ሊንክ ተጫኑ ተመልከቱትና እንነጋገርበት። https://youtu.be/Cv6ZJlh8BuU   Yes they did it !!!

 

ከዚህ ቀደም በነበሩ ፅሁፎቼ ይህንን የአገራችን ሁሉን አቀፍ እድገት የሁላችን አስተዋፅኦ ያለው ነው በሚል ስከራከር ቆይቻለሁ። በአሁኑ ወቅት አብዛኛው ፖለቲከኛ፣ ሚድያና ህዝብ የህወሃት መንግስት እያለ በሚጠራው መንግስት የመጣ ለውጥ ነው። አዎ “ሙሰኛው”፣ “ዘራፊው”፣ “ገዳዩ፣ ገንጣዩና አስገንጣዩ” የምንለው የህወሃት መንግስት ያመጣው ለውጥ ነው። እኔም እስከአሁን ጉዳዩ አገራዊ ለማድረግ የሁላችን ለውጥ! እያልኩ ስላደነቆርኳቹ ይቅርታ እየጠየቅኩኝ ከዚህ በኃላ ያንን ዘመን የህወሃት መራሹ መንግስት እያልኩ እጠራዋለሁ።

Videos From Around The World

 

ፈልጌ ያነሳሁት ቢሆንም እንደወጉ “ነገርን ነገር ያነሳዋል” ብየ በዚሁ እንደለመድኩት ወደ ትግራይ ህዝብ የሚመለከት ጉዳይ ልግባ።ታስታውሱ እንደሆነ በሁሉም ፅሁፎቼ ይህንን ጉዳይ ሳልነካ ያለፍኩበት ግዜ የለም። በሁለት ምክንያት ነው። አንዱ የአገሪቱ የብተና አጀንዳ ማስፈፀምያና ማጠንጠኛ እየሆነ በመቀጠሉ ሲሆን ሌላው ግን ሰው ሁኜ የሰው አስተሳሰብ እና አቋም ያለኝ መሆኑ የማረጋግጥበት ጉዳይ ስለሆነም ነው። እናም የማምንበትንና ፍትሃዊ የምለው አቋም በግልፅ ማቅረብ በመቻሌ ኩራት ይሰማኛል።ከዚህ ቀደም ኢህአዴግና መጭው የአካል ጉዳተኝነት አዝማምያ በሚል ባቀረብኩት ፅሁፍ የትግራይ ህዝብን ባለውለታችን እያለ ለምንና ከመቸ ጀምሮ ይህንን የህዝቡ ውለታ በጭቃ በመለወስ ወንጀለኛ ለማድረግ ሆን ተብሎ ሲሰራበት እንደቆየ በመጥቀስ እንዲህ በሚል ስሜቴን ለመግለፅ ሞክሬ ነበር፤

 

----------የትግራይ ህዝብ በሌላው ህዝብ ዘንድ እንደ ጠላት እንዲታይና ይህንን አስተሳሰብ በሁሉም እንዲሰርፅ ለማድረግ በብተና ኃይሎች በየትምህርት ቤቶች፣ መስራቤቶች፣ የእምነት ተቋም፣ ካፌዎች፣ እድሮች፣ አዝማሪ ቤቶች፣ ታክሲና ባስ መጠበቅያ ቦታዎች፣ በተለያዩ የኮሜዲ፣ የግጥምና ስነ ፅሁፍ በመሳሰሉ የኪነ ጥበብ ውጤቶችና በቤተሰብ ደረጃ ታቅዶ የተሰራበት ሲሆን በታሪካችን ለመጀመርያ ግዜ ባገኘነው ሃሳብን በነጻ የመግለጽ ዴሞክሪያሳዊ መብት ተጠቅመው በብዙ ጋዜጦችና መጻህፍት ሳይቀር ፀረ-ትግራይ ህዝብ ብዙ ነግረውናል። በሚል ገልጨው ነበር እውነትም ነው።

 

እነዚህ ኃይሎች ይህንን በማድረግ ለማሳካት የፈለጉት ነገር በከፊል ለማሳካት ከቻሉም በኃላ አሁንም ከዚህ ህዝብ ትክሻ ለመውረድ አለመፈለጋቸው በአንድ በኩል እንዲህ ካላሉ “ታድያ ማንን አሸንፈን በድል አድራጊነት አዲስ አበባ ገባን” ይበሉ ብየ አስብና ግን ደግሞ አሁንም ከመጀመርያው በባሰ ሁኔታ ከተቻለ ከምድረ ገፅ ለማጥፋትም ጭምር ያለመ የተደራጀና የተቀናጀ ስራ እየተሰራ መሆኑን ሳስብ ማንም ሰው ከሚያስበው በላይ ሌላ ምክንያትና አጀንዳ እንዳለ ያረጋግጣል። እውነት ነው በቁጥሩ አነስተኛ ቢሆንም ለዝች አገር በዋለው ውለታ ትልቅ የሆነውን የትግራይ ህዝብ ከሌላ ህዝብ በተለየ ካለፈው ጥቃት በባሰ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቱ እየተረገጠ ይገኛል።

 

በህዝቡ እየደረሱ ያሉ ጥቃቶችና የመብት ጥሰቶች የሚጀምሩት ከመርህ አልባውና  “ለህገ-መንግስቱ ታማኝ በመሆን የአገሪቱን ህዝብ በእኩልነት ላገለግል ቃል እገባለሁ” ያለውንና ቃሉን ለማጠፍ ብዙ ቀናት ካላስፈለጉት  ከጠ/ሚኒስትሩ ነው። ጠ/ሚንስትሩ ስራ ሲጀምር ኢትዮጵያ ያለ ትግራይ ምንም ናት “መኪና ያለ ሞተር” በሚል ገልፆ ህዝቡን ያሞገሰ መሪ በጥቂት ቀናት ልዩነት “የቀን ጅብ” በሚል ከሌላው ህዝብ የመነጠል ስራ መስራት ጀመረ። በሰኔ 16ቱ ቦምብ ጥቃት ወቅት እድሜ ልካቸው ታግለው ለስልጣን ያበቁትን፣ ከድርጅታዊ አሰራሮች ባፈነገጠ መልኩ በአሻጥር አሸነፈ ሲባል ባይዋጥላቸውም ለሰላም ብለው ሚጉ፣ ታንኩና ሚሳይሉ አስረክበውት ከሄዱ በኃላ  በጥቃቱ ወቅት እንኳንስ ስለ ጥቃት ፈፃሚ አካል ለማውቅ ቀርቶ  ተጎጅዎች ከመስቀል አደባባይ እንኳን ሳይነሱ ባለችው ደቂቃ “የእጅ ቦምብ ይዘው ጥቃቱን የፈፀሙ የተሸነፉ ናቸው” የሚል የግብዝነት መግለጫ በመስጠቱ በወቅቱ ሌላው ህዝብ ለሱ በነበረው ከስካር የማይተናነስ ስሜታዊ ድጋፍ ተገፋፍቶ በትግራይ ህዝብ ላይ ጥቃት እንዲጀምር ለማነሳሳት ሞክረዋል።

 

በሰብአዊ መብት ጥሰትና በሙስና ሰበብ በሱ ትእዛዝ እንዲታሩ የተደረጉ የትግራይ ተወላጆች ጉዳይ ከአንድ አጀንዳ በላይ የያዘ ሲሆን ሁሉም ተመርጠው የታሰሩ  ናቸው። በመሃል እንዲገቡ የተደረጉት ጥቂት የሌላ ብሔር አባላት ለምን በዚህ ሽፋን ታሰሩ ያልን እንደሆነ የየራሳቸው ምክንያት ነበራቸው። አንዳንዶቹ አሁን ከመጣዉ አዲሱ አመራር ጋር በነበራቸው ትውውቅና ግንኙነት በግል ጉዳይ ቂም ቋጥረው በመቆየት ግዜ አግኝተው ለመበቀልና አንዳንዶቹ ለህገ-መንግስታዊ ስርአቱ በነበራቸው ጠንካራ አቋም ምክንያትና በነበራቸው የስራ ድርሻ ምክንያት እነዚህ “የለውጥ መሪዎች ነን” ባዮች በተለያየ ወንጀል እጃቸው ያስገቡ መሆናቸው ስለሚያውቁ ራሳቸው ለመከላከል ካልሆነ በስተቀር ብዙዎቹ ከሰብአዊ መብት ጥሰት መፈፀም ጋር በተያያዘ ምንም የስራ ሃላፊነት፣ የስራ መደብና ስልጣን ያልነበራቸው መሆኑ ከክስ ፋይላቸው መረዳት ችያለሁ።

 

እርግጥ ነው በኔ እምነት ከታሰሩ ውስጥ በሙስና መጠየቅ ያለባቸው ከሁለት የማይበልጡ ሰዎች አሉ። ሆን ተብሎ ችግሩን ከተራራ ለማግዘፍ የተሰራ ስራ ትተን ከነዚህ ወስጥ ሜቴክ አንዱ ነው። እርምጃው አገራዊ ጥቅምንና አገራዊ ደህንነትን ለማስጠበቅ የተሰራ ቢሆን ከዚህ በብዙ ከፍታ የሚበልጥ የሙስና ችግር ሌሎቹ ጋር እንደነበረና እንዳለ እኔ በመንግስት ቤት እሰራ በነበርኩበት ግዜ ከነበረኝ ትስስር እንደ አንድ የህግ ባለሞያ እንደተረዳሁትና ከኔ በላይ ደግሞ ፀረ-ሙስና ኮሚሽን በተለይ የህግ ክፍሉ፣ ብርሃኑ ፀጋዮ ጠቅላይ አቃቢ ህጉ፣ የቀድሞ ጠ/ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝና አብይ አህመድ በሚገባ የሚያውቁት ጉዳይ ነው። በፌደራል ተቋማት ደረጃ፣ በክልሎች ደረጃ እንዲሁም በግል ከመንግስት ሃላፊዎችና ነጋዴዎች ደረጃ የትግራይ ተወላጆች የመኖራቸው ያህል ብቻ ሳይሆን ከዛ በአስገራሚ ሁኔታ ከፍ ባለ ሁኔታ ያለው ችግር የሌሎች ብሔር ተወላጆች እንደሆኑ ብዙዎቻችን እናውቃለን። እኔም ከዚህ በፊት እንደ ECX, METEC፣ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን፣ ቴሌ የመሳሰሉ ተቋማትና የኦሮምያ ተዘዋዋሪ ፈንድ ምን እንደተደረገ በመጥቀስ ችግር ያለባቸው ስለመሆኑ በመነሻነት ስገልፅላቹ አገርን እንጂ ብሔርን አስቤ አልነበረም። ቢሆን ኖሮ በብሔር ሂሳብ ብዙዎቹን ባላነሳሁ ነበር። ግዜው የጥፋት ግዜ ሆነና ሙስና ጠብቆ ጠብቆ ለትግራይ ህዝብ የመብት ጥሰት ማስፈፀምያ መሳርያ ሆኖ ተገኘ።

 

ከሙስናው በላይ የሚገርመው ግን የሰብአዊ መብት ጥሰት በሚል ስለታሰሩ የትግራይ ተወላጆች ጉዳይ ነው።ይህንን ሳነሳ የተፈፀመ የሰብአዊ መብት ጥሰት አልነበረም ለማለት እንደማይሆን የከዚህ በፊት ፅሁፎቼ ያረጋግጣሉ። ይሁንና በማህበራዊና በመንግስት ሚድያዎች በተደጋጋሚ በተገለፀው ደረጃ  የሰብአዊ መብት ጥሰት ከነበረ ይህንን የሚያደረገው በማእከላዊና ሌሎች ፖሊስ ጣብያዎች መሆኑ የታወቀ ነገር ነው። በሌሎች የፖሊስ ጣብያዎች ጉዳይ ለግዜው አቆይተን በማእከላዊ “ሆነ” ያሉንን ብቻ ወስደን ብናይ ማእከላዊ የፌደራል ፓሊስ አካል ነው። የሚታዘዘውም በፌደራል ፖሊስ ነው። መርማሪዎቹም ከሁሉም ብሔር አባላትና የፌደራል ፖሊስ ናቸው። ችግሮች ተከሰቱ በተባለበት ምርጫ 1997 ግዜና በኃላ የፌደራል ፖሊስ የሚመራው በወርቅነህ ገበዮህ፣ በኃላ “ለውጥ” መጣ እስከሚባለውም ግዜ ድረስ ተቋሙን የሚመራው የሌላ ብሔር ተወላጅ ፣ ማእከላዊ እስከ ለውጡ የመሩት መስፍንና ረታ ተስፋዮ የተባሉ የኦሮሞ ተወላጆች፣ በተለይ ረታ ከመርማሪ ጀምሮ እስከ ኃላፊነት በቁጥር አንድ ስሙ የሚነሳ ሆኖ ሳለ መስፍንን በሹመት ረታን ደግሞ ከመንግስት በተፃፈለት  የትብብር ደብዳቤ ከነ ሙሉ ቤተሰቡ ቪዛ እንዲሰጠው ተደርጎ አውሮፓ ባለበት ሁኔታ ጌታቸውንና እሱ የሚመራው ተቋምን ወንጀለኛ ብሎ ማሰርንና ለማሰር የማሰብ ምክንያት መደመርን ጨምሮ በሁሉም የሒሳብ ስሌቶች መልስ ልታገኝበት አትችልም።

 

በደርግ ዘመን ማእከላዊ የትግራይና የመላ አገሪቱ ህዝቦች በሰው ፍጡር ላይ ይደረጋል ተብሎ ለማሰብ በማይቻልበት ሁኔታ የግፍ ግፍ ይፈፀምበት የነበረ የገሃነም ቦታ ሆኖ የቆየና ለታሰረ የቤተሰብ አባል ስንቅ ለማቀበል ብሎ የሄደ ሰው ሳይቀር በሰላም እንደሚመለስ እርግጠኛ የማይሆንበት ቦታ ሆኖ ሳለ እድሜ ለመሪያችን አብይና አማካሪዎቹ ለሆኑት የደርግ አባላት ይሆንና ሆን ተብሎ ታቅዶና በከፍተኛ ደረጃ አመራር እየተሰጠበት በሰሩልን ዶክሜንተሪ አሁን ሁሉም ሰው ደርግን ረስቶ ማእከላዊ ሲነሳ ማስታወሻነቱ ለህዋሃትና ለትግራይ ተወላጆች እንዲሆን በበቂ ሁኔታ ተሰርቶበታል። በዚህ መንግስት በራሱ ደራሲ፣ ተዋናይ፣ ዳይሪክተርና የክብር ስፖንሰር በመሆን በሰራው ድራማ ሌላው ህዝብ በትግራይ ህዝብ እንዲነሳ ተሞክረዋል። ያሳደረው ጠባሳም ቀላል እንዳልሆነ በየመንገዱ ከምንሰማቸው ነገሮች መረዳት ይቻላል።     

 

ፍቅርና መደመር አቀንቃኙ ጠ/ሚኒስትር በቅርቡ ወሎ ደሴ ላይ ከህዝቡ ጋር በነበረው ቆይታ  ህዝቡ በተለይ አንድ አባት በቅኔ ሳይሆን በግልፅ ለጠየቁት ጥያቄ መልስ ሲሰጥ “አባቴ በቦሩ ሜዳ ላይ የተፈፀመ ጭፍጨፋ ረሱት እንዴ” በሚል ስሜት ቀስቃሽ በሆነ መልኩ የአጼ ዮሃንስ ታሪክ በማጠልሸት የትግራዋይ ጨፈጨፋቹ እንዴት ታሪክ ረስታቹ ዝም ትላላቹ የሚል የፍጅት ጥሪ አቅርቦ ነበር። ዳሩ ህዝቡ ኢትዮጵያዊ ነውና ጉዳዩ ከቁብ ቆጥሮ በወንድሙ ላይ አልተነሳም።

 

ይህንን ጉዳይ ከልማትም ከአገር ደህንነትም በላይ የአብይ መንግስት ቀዳሚ አጀንዳ መሆኑ የተረዱ የግልና  የመንግስት ሚድያዎችም ጭምር ህዝቡ እንደ ጠላት ህዝብ በመቁጠር በህዝቡ ላይ የሚደርሱ በደሎች አለመዘገብ ብቻ አይደለም ያልፈፀመውን ፈፀመው ብለው ለመዘገብ በምድርም በሰማይም ይመጣብናል ብለው የሚፈሩት ነገር እንደሌለ አይተናል ሰምተናል።

 

ዛሬ የትግራይ ተወላጅ በመሆኑ ብቻ መገደሉ አይደለም፣ ከሌላ የአገሪቱ ህዝቦች እንዳይገናኝ መንገድ በመዝጋት መውጭያ መግብያ እንዲያጣ መደረጉ ብቻ አይደለም በሌሎች ክልሎች የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆችና በፌደራል መንግስት ተቋማት የሚሰሩ የትግራይ ተወላጆች ዛሬ እንደ ሰው ስህተት እንዳይሰሩ ወይም እንዳይናገሩ ይጨነቃሉ፣ ከዛ በላይ ግን ሰው በመሆናቸው የሰሩት ስህተት የትግራይ ተወላጅ በመሆናቸው  እንደሰሩት እንዳይቆጠርባቸው እንቅልፍ አጥተው ያድራሉ። ሲያወሩ ስህተት እንዳይናገሩ አፋቸው ይሎጉማሉ።

 

ዛሬ ከክልሉ ውጭ ያሉ የትግራይ ተወላጆች ትርፍ ዋጋ ከፍለው በገነቧት አገር በጥቂት የብሔሩ ተወለጆች እየተሳበበ “የቀን ጅብ” ተብለው ገንዘባቸውና ንብረታቸው እንዳይወረስ ብቻ ሳይሆን በዚሁ ሰበብ ህይወታቸው እንዳያጡ ይሰጋሉ። ብዙዎቹ ድሃ የነበሩበት ዘመን መናፈቅ ጀምረዋል። ዛሬ የትግራይ ተወላጆች ከክልላቸው ውጭ በየትኛውም የአገሪቱ አካባቢዎች ችግር የፈጠረ ወይም ህግ የተላለፈ ሰው ስለመኖሩ ዜና ሲሰሙ በመጀመርያ ዜናው ውሸት እንዲሆን ይፀልያሉ፣ ዜናው እውነት ከሆነ በችግሩ እንደ ማንኛውም ሰው የትግራይ ተወላጅ ወይም ትግርኛ የሚመስል ስም እንዳይኖር ይፀልያሉ። ለምን ቢባል በዚሁ ሰበብ እነሱ ጋር የሚመጣ ችግር ያሰጋቸዋል ያስጨንቃቸዋልና ነው። ለምን አይጨነቁ?

 

በአገሪቱ በሁሉም አካባቢዎች በየቀኑ በሚባል ደረጃ የጦር መሳርያና ህገ-ወጥ ገንዘብ ተያዘ እየተባለ አመት ሙሉ ሲዘገብ እናስታውሳለን። እንዳውም በበርካታ ህዝብ ዘንድ “ሰዎች ስማቸውና ምስላቸው የማይገለፅበት የወንጀል ዜና እየተበራከተ ነው ስለዚህ ዜናዎቹ ውሸት ናቸው” እስከመባል ተደርሶ የነበረ ሲሆን በቅርቡ በቶጎ ውጫሌ በህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር ተያዘ የተባለ ሰው ሙሉ የትግርኛ ስሙና መታወቅያውም ጭምር በመንግስት ሚድያዎች መቅረቡ ምን ማለት ይመስልሃል? እንኳንስ ህግ ለተላለፈ ቀርቶ ባለቤትነቱ የመከላከያ የሆነ ህጋዊ የጦር መሳርያ  በመተማ ሲያዝ ንብረቱ የመከላከያ መሆኑ ተረጋግጦ እያለ የሾፌሮቹ ስም ትግርኛ ስለሆነ ብቻ ስማቸው እየተጠራ ከመንግስት ሚድያ እስከ ማህበራዊ መገናኛ መነጋገርያ እንዲሆን የተደረገው ለምን ይመስልሃል? ንብረቱ ከተያዘ በኃላ ለዝያውም የመከላከያ የጦር መሳርያ ሆኖ ሳለ መከላከያ ድምፁን አጥፍቶ ዝም ያለውና  ከቀናት በኃላ አለሁ ማለቱስ ለምን ይመስልሃል?     

 

ከዚሁ ጋር የተያያዘ በቅርቡ ከመንግስታዊና የግል ሚድያዎች፣ ፖለቲከኞች፣ አክቲቪስቶችና ከአንዳንድ የሶሻል ሚድያ ተጠቃሚዎች የሆኑ፣ የተፃፊና የተነገሩ ጥቂት ነገሮች ብቻ ሳይና ካለፉት ሁኔታዎች እያገናዘብኩ ስመለከት ይህ ህዝብ ምን አድርግ እያልነው እንደሆነ ይጨንቀኛል። ብዙዎቻችን አይተናቸዋል ብየ አስባለሁ። ያመለጣቸው ስለሚኖሩ አንዳንዶቹ ባነሳቸው ይጠቅማል ብየ አሰብኩኝ እና እንዲህ ጠቀስኳቸው።

 

ከወራት በፊት በአንድ የአፍሪካ አገር የብስክሌት ውድድር ነበር። ኢትዮጵያ ወክለው የሄዱ ተወዳዳሪዎች ከፍተኛና ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ውድድር ተገኝቶ የማያውቅ ዉጤት አስመዘገቡ። አገር ወክለው ያሸነፉት የትግራይ ተወላጅ በመሆናቸው ብቻ በቂ የሚድያ ሽፋን ሳያገኙ ቀሩ። ሌላው አንዳርጋቸው ፅጌ በቅርቡ ባሳተመው ራሱን በራሱ ያጋለጠበትና የስብእና መጓደሉ ያሳየበት መፅሐፉና የመፅሃፉን ምርቃት ተከትሎ በነበሩ መድረኮች “አማራ የሚባል ህዝብ የለም። ከህዝቡ በፊት ቋንቋው ነው የተፈጠረው እሱም ለወታደሮች መግባብያ ተብሎ የተፈጠረ ቋንቋ ነው” ካለ በኃላ ከብዙ የክልሉ ተወላጆች የተነሳበትን ተቃውሞ ለማካካስ ብሎ ከዚህ በፊት ከኢሳት ጋር በነበረው ቃለ-መጠይቅ በኢህአፓ ወቅት ካጋጠመው ነገርና የትግራይ ህዝብ ካደረገለት እንክብካቤ በመነሳት አሁን ደርሶ እንባው መቆጣጠር ተቸግሮ እያለቀሰና ጋዜጠኛው እያባበለ ያቀረበውን የምስጋና ትያትር በወራት ልዩነት ውስጥ አሁን በመስከረም ወር አውሮፓ በነበረው የህዝብ መድረክ ከሁለት ወር በፊት “የለም” ያለውን ህዝብ ለማሞገስ ብሎ “ትግሬዎች” ብሎ በመጥራት “የዘቀጠ” ህዝብ እንደሆነ  ሊነግረን ደፍሯል።

 

አንዳርጋቸው “ትውልድ አይደናገር፤ እኛም እንናገር” በሰየመው በአዲሱ መፅሐፉ “በአድዋ ጦርነት ዘምተው የተሰዉ የሃረር ሞስሊሞች ሳይቀበሩ ቀርተው የአሞራ ሲሳይ ሲሆኑ  የጣልያን ወታደር ግን ተለቅመው ተቀብረዋል” ይላል። ይህ የሆነው ደግሞ በወቅቱ በነበሩ የትግራይ ገዢ ጋር ለማያያዝ ሞክረዋል።እዚህ ላይ እንድናየው የፈለግኩት ስለ ታሪኩ እውነት ውሸትነት አይደለም። ጉዳዩ ያለው ይህንን የውሸት ታሪክ ለምን አሁን ለመፃፍ ተፈለገ? ለምን ከሞስሊምም ከሃረረም ጋር ለማያያዝ ተፈለገ ወዘተ እያሉ ራሱ የቻለ መፅሐፍ መፃፍና ማውራት ቢቻልም ሰውየው አንዳርጋቸው መሆኑ ራሱ መልስ ስለሆነ ብዙ ማለት አያስፈልግም።

 

ሌላው ከአንድ የስራ ባልደራባየ የተረዳሁት በተባበሩት አረብ ኢሜሬቶች ባለው አንድ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተመድቦ የሚሰራ ጓደኛው እንደነገረው አንዳንድ ኢንቨስተሮች ወደ ኤምባሲ ሄደው “ትግራይ የተሻለ ሰላምና የአስተዳደር ስርአት አለ ስለሰማን እዛ ኢንቨስት ለማድረግ ሁኔታዎች አመቻቹልን” ብለው ሲጠይቋቸው “ወደ ትግራይ መሄድ አደጋ እንዳለው በመንገርና ለአንዳንዶቹም አብይና የኤርትራ መንግስት በትግራይ ጦርነት ስለሚያካሂዱ አስተማማኝ አይደለም” ብለው ሃሳባቸው እንዲቀይሩ ማድረጋቸው እንደ ድል ቆጥሮ እንዳወራው ነግሮኛል። ይህ ሁኔታ እኔ በአገር ቤት ካጋጠመኝ ጋር አያይዠ ሳየው እውነት ሆኖ አግኝቸዋለሁ። በርካታ አስጎብኚ ድርጅቶች ቱሪስቶች ወደ ትግራይ እንዳይሄዱ በሰበብ አስባብ እንደሚያስቀሯቸው ስለማውቅ ነው።

 

የዚህ ህዝብ መከራው ብዛቱ ያስገረመኝና አሁንም አሁንም ሃጢአቱ ምን እንደ ሆነ የምጠይቀው የትግራይን ህዝብ መሪር ሃዘን ውስጥ ካስገባውና እንደ ጀነራል ሰዓረ ያሉ ውድ ልጆቹ ባሳጠው፣ ሁኔታዉን ተከትሎ የትግራይ ህዝብ የተለመደው ትእግስቱ ባያሳይ ኖሮ በዚህ አገር ይፈጠር የነበረ ችግር ከፍተኛ ይሆን እንደነበር እየታወቀ፣ ጠ/ሚኒስትሩም ይህንን ስለሚያውቅ ስጋት ገብቶት በወቅቱ ማታ በሰጠው መግለጫ “ምን እናግዛቹ ብላቹ ለጠየቃችሁን ጎረቤት አገራት ለግዜው ምንም የለም ግን ጠብቁን” በሚል ህዋሃት ችግር እፈጥራለሁ ካልሽ ሻዕብያን እጠራለሁ የሚል መግለጫ ለመስጠት በተገደደበት የሰኔ 15 ጥቃት እንኳን ሳይቀር የትግራይ ህዝብ ተጠያቂ ለማድረግ የተደመጡ ዘገባዎችና የተራመዱ ሃሳቦች ስሰማ እጅግ እጅግ የሚዘገንኑና እንኳን እነሱ ሆነህ እንደ ማንኛውም ዜጋም በዚህ ህዝብ ላይ እየወረደ ያለው ኢ-ሰብአዊ ተግባር ያንገሸግኝሃል።

 

በወቅቱ ከነበሩ ዘገባዎች መካከል ይህንን የሽብር ስራ ለመስራት ሰው ሲመለምል እና ስያስተባብር የነበረ የመ/አለቃ መአርግ ያለው የትግራይ ተወላጅ እንደሆነ ተዘገበ። እንግዲህ ይታያቹ ተግባሩ የፈፀሙት እነ ጀነራል አሳምነው ፅጌ፣ ጀነራል ተፈራ፣ እነ ኮነሬል አለበል አማረ እንደሆኑ እየታወቀና እነዚህ ሰዎች ለትግራይ ህዝብ የነበራቸው ጥላቻ ከፍተኛ ሆኖ እያለ አንድ የትግራይ ተወላጅ መ/አለቃ ለነ ጀነራል አሳምነው መለመለ እና መሪዎቻችን ገደለ ይሉሃል።

 

የመመረቅያ ፅሑፉ በትግራይ ህዝብ ጥላቻ ተሞርኩዞ የፃፈ የሚመስለው ዶ/ር ሲሳይ መንግስቴ “የሰኔ 15ቱ ጥቃት የፈፀመው ልዩ ኃይል ነው ተብለዋል። የሁሉም ልዩ ኃይል የደምብ ልብስ ደግሞ አልመዳ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ስለሚሰራ ጥቃቱ የፈፀመው የአማራ ልዩ ሃይል ልብስ ለብሶ የትግራይ ልዩ ኃይል ላለመሆኑ ምን ማረጋገጫ አለ” ብሎ የውሸት ጥያቄ በመጠየቅ ለትግራይ ያለው ጥላቻ እና ለአማራ ክልል የፀጥታ አካላት ያለው ንቀት በአንድ ላይ ገልፀዋል።ሌሎች ደግሞ የጀነራል ሰዓረ ባለቤት ሳትቀር በግድያው ተጠርጣሪ ለማድረግ እኮ ተደጋጋሚ ዘገባ ሰርተዋል። ከዚህ ጋር በተያያዘ በብዙ ጉዳይ በብዙ ቦታ ዋስትና የከለከሉ ዳኞች ብዙ ሆነው ሳለ በግድያው ተጠርጥረው በአዲስ አበባ ለታሰሩ የአብን አባላትና ጋዜጠኞች ዋስትና የከለከለ ዳኛ የትግራይ ተወላጅ መሆኑ ለማሳየት ከችሎቱ በላይ ስሙ ተደጋግሞ ሲጠራም ሰምተናል።

 

የመቀሌ 70 እንደርታ የእግር ኳስ ተጫዋቾች ወልድያ በሄዱበትና አንድ ደጋፊያቸው ገብረው የተመለሱ ግዜ ቧ- ኖዎች( በቧያለው አስተሳሰብ የሚመሩ ፋኖዎች) በባነር ፅፈው የተቀበልዋቸው ፅሁፍ “ወደ ኢትዮጵያ እንኳን በሰላም መጣቹ” ይላል። በቅርብ ግዜ ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሩዋንዳ ጋር በመቀሌ በነበረው ጨዋታ ውጤት ማጣቱን ተከትሎ ወሎ ፕረስ በተባለ የፌስቡክ አካውንት ላይ ተፅፎ ያነበብኩት “ብሔራዊ ቡድናችን ከሜዳውና ከደጋፊው ውጭ መጫወቱ ዋጋ አስከፍሎታል” ይላል።

 

የአሸንድየና የአሸንዳ ብዓላትና የሚድያ አዘጋገብ፣ የመንግስት ሚድያ ሆን ብሎ የመስቀል ብአል በተለያየ ቦታ መከበሩ ለመግለፅ መቀሌን ጨምሮ ሌሎች የትግራይ ከተሞችን በአማራ ክልል በማካተት መዘርዘር፣ በቅርቡ በህዋሃትና አዴፓ መካከል በነበረ እንካ ስላንትያ የሁለቱም መግለጫዎች በመንግስትና በግል ሚድያዎች እንዲሁም በሚገርም ሁኔታ በEPRDF OFFICIAL የፌስ ቡክ ገፅ ላይ ሳይቀር የተዘገበበት አግባብና የተሰጠው ትንታኔ በሙሉ አይተህ ዞር ስትል ከኃላህ የህዝቡ ፅናት ታያለህ።

 

በዚህ ፅሁፍ ህዋሃት መግባት በነበረበት ቦታ ስሙን ጠርቸ አላስገባሁትም። ያላስገባሁት ምክንያት አንዳንዶቹ እንደሚሉት ህዋሀትና የትግራይ ህዝብ አንድ ነው በሚል አይደለም። ለህዋሃት ከለላ ለመስጠትም አይደለም። እስከአሁን እንደተረዳሁት በእያንዳንዱ ጉዳይ ህዋሃት የሚያነሱት ህዝቡን በቀጥታ ማጥቃት ስለማይችሉ ህዋሃትን የሚጠሩት ለእኩይ ምግባራቸው ሽፋን (ከለላ) ለማግኘት እንደሆነ ግልፅ በመሆኑ ነው። ህዝቡ የውስጥና የውጭ ጠላቶቹን ተደራጅተው ሊያጠፉት ሲፈልጉ እንደ እገሌ ብለህ ለመጥቀስ በሚያስቸግር ደረጃ ብዙ ጀግኖች እያፈራ ግን እንደ አንድ ሰው የአስተሳሰብ አንድነት በመፍጠር አላሳልፍ ብሎ ያስቸገራቸውን ህዝብ ከስረ መሰረቱ ለማጥፋት በማሰብ እንደሆነ ስለተረዳሁ ነው። በሁሉም ሞክረው ሞክረው አልሳካ እንዳላቸው የገባኝና በጣሙን ያሳቀኝ ነገር “ህዋሀት የአረና አባል ንብረት የሆኑ 16 ፍየሎች አሰረች” ብለው አብዛኛዎቹ የመንግስትና የግል ሚድያዎች እየተቀባበሉ ሲዘግቡ የዋሉ እለት ነው። ይገርማል! ስለ እውነት ግን በዚህ ህዝብ አንድነትና ልባምነት እኔም እንደዚህ “ቀናሁ” ያለው ሰው https://youtu.be/feKkrcXdamQ ቀናሁ።

 

አንዳንዴ በአንዳንድ የትግራይ ተወላጆች “በቃን ብለው” መገንጠልን እንደ አማራጭ አንስተው ሲፅፉና  ሳይና ሲናገሩ ስሰማ ታድያ እነዚህ ሰዎች ምን ያርጉ ? እንዴት ይኑሩ? ከማን ጋር ይኑሩ? እላለሁ። እንዳውም እስከአሁን በዚህ ሁኔታ መቆየታቸው ተበድለዋል እልና በኃላ ደግሞ ተጋሩ እኮ ኢትዮጵያ የተከራዩዋት ቤት አይደለችም ከአከራይ ጋር እሰጣ ገባ ውስጥ ገብተው ጥለዋት የሚሄዱ። ኢትዮጵያን የሰራት ሳይሆን የተሰራችው በትግራዋይ መሆኑ ሳስብ ደግሞ የተከራየና ከ------- መጣ የሚባለው ሳይወጣ እሱ የት ይሄዳል። ከፈለጉ እነሱ ይሂዱ እላለሁ። 

 

እንግዲህ “ለውጥ” በትግራይና በትግራይ ህዝብ እንዲህ ባለ ሁኔታ እየቀጠለ ነው። በኛስ? በእናንተስ? የለውጥ ነገር እንዴት እያረጋቹ ነው? ከላይ ያነሳነው የትኛው ለውጥ? የሚል ጥያቄ እዚህ ይነሳል። እናም ሰላምዋና ሉአላዊነቷ የተጠበቀ፣ ከጀመረችው የልማት ጎዳና ወደተሻለ ብልፅግና፣ በህዝቦቿ መካከል የቆየና ያለ የባህል፣ የሃይማኖችና የማንነት ልዩነቶችን በማክበርና በመከባበር ላይ ተመስርቶ ልዩነታችን እንደ ውበታችን የምናይበት፣ የህዝቦች አንድነትን፣ ሰናይ የሆነ የአስተዳደር ዘይቤ ያላትንና የተጀመረው የዴሞክራሲ ጭላንጭል የሚፈነጥቅባት አገር እንድትሆን ነበር ህዝቦቿ የጠየቁትና የታገሉለት ለውጥ። እህሳ? ብላቹ እንደጠየቃችሁኝ ወስጄ ትንሽ ልበል።

 

ከሁሉ በፊት የመለወጥ ፍላጎትና እንቅስቃሴ የሚጀምረው እንኳንስ ከገዱና ለማ ቀርቶ ከጁሃርና ከታማኝ፣ ከቄሮና ፋኖ፣ ከብርሃኑ ነጋና ከመሳሰሉ የንጋት ፎካሪና የሌለ ድል አብሳሪ እንዳልሆነ በሚገባ ሊሰመርበት የሚገባ ጉዳይ ነው። ከደርግ ውድቀት በፊት ጀምሮ ጥያቄው እንዳልተመለሰለት በማሰብ ሲንቀሳቀሱ ከነበሩ የተለያዩ ቡድኖች ጀምሮ በተለያየ ግዜ በተለያየ ምክንያትና አጋጣሚ እየተነሳ ለውጥ የሚፈልግና ለውጥ ለማምጣት በግልም በተደራጀም ትግል ለማድረግ ማህበራዊ መሰረቴ ለሚለው የህብረተሰብ ክፍል ሲያደራጅና ሲንቀሰቅስ የቆየ ብዙ ነው። በኔ እምነት ባለ ኳልኩሌተሩና ባለ ሮድማፕ ሰነዱ የማጠቃለያ ሒሳብ የሰሩ ለዝያውም የተሳሳተ ሒሳብ የሰሩና ሪፖርት ያዘጋጁ ናቸው ባይ ነኝ። 

 

የህዝቡ የለውጥ ፍላጎትና እንቅስቃሴ ይህንን ይምሰል እንጂ በህዝቡ የለውጡ እንቅስቃሴ  ባህር ውስጥ ገብተው ሲያምቦጫርቁ የነበሩ ግን በርካታ የሚመለከታቸውም የማይመለከታቸው፣  የኢትዮጵያ እድገት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ጥቅማችን ይነካል ወይም ይጎዳናል ብለው ያሰቡ የተለያዩ የቅርብና የሩቅ የውጭ ኃይሎች እንዲሁም ሌላ አላማ ለማስፈፀም የጥፋት መልእክተኛ የሆኑ የዚችው አገር ልጆችም ጭምር እንደነበሩ በኔ የቀደሙ ፅሁፎችና ከኔ በተሻለ ደግሞ በሌሎች በስፋት ይገለፅ የነበረ ጉዳይ ነው።

 

ምእራባውያን በመለስ ግዜ ሞክረው ያላሳኩዋቸው ጫናዎች መለስ ካለፈ በኃላ በዚሁ አጋጣሚ መንግስትን አስገድዶ ወደ ፍላጎታቸው ለማስገባትና በሪፎርም ስም መንግስት ለማፍረስ ያደረጉት እንቅስቃሴ አንዱ የዚህ ማሳያ  ተደርጎ የሚወሰድ ነው። በኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች የአመፅ እንቅስቃሴው በተጠናከረበት ሁኔታ የአሜሪካና የአውሮፓ ህብረት አምባሳደሮች በየኤምባሲዎቻቸው ምን እያደረጉ እንደነበሩ ከ”ለውጡ” በኃላ  በጣም በአጭር ግዜ ብስለት በጎደላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎቻችን አመራሮች አማካኝነት እነሱ ባልፈለጉት ግዜና መንገድ ለአደባባይ አብቅተውታል።

ዶናልድ ያማማቶ ይህንን “የአደፍርስ” (ከተመስገን ደሳለኝ የተዋስኩት ቃል ነው) ስራ ለመስራት የነበረው የእንቅልፍ ግዜ ትንሽ እንደነበር አይተናል። አብይ በኢትዮጵያዊነት ስምና ዜማ አራት ኪሎ ገብቶ ኢትዮጵያዊነት በተገነባበት ወንበር መቀመጥ በጀመረ  በቀናት ልዩነት የFBI እና የCIA ሰዎች በአዲስ አበባ ሚኒሊክ ቤተ መንግስት ውስጥ ኮማንድ ፖስት ለማቋቋም ግዜ ማባከን አልፈለጉም። “የኢኮኖሚ” በሚልም በርካታ አሜሪካውያንና የአሜሪካ የብተና አጀንዳ ያነገቡ ትውልደ ኢትዮጵያውያን በገፍ ገብተው መሸጉ። ከነዚህ መካከል ከወያኔ ጋር የማይታረቅ ቅራኔ ያላቸው የደርግ ባለስልጣናት ተጠቃሽ ናቸው። አንዳንዶቹ ከአማካሪነት አልፈው የውሳኔ አመንጭነት ደረጃ ያገኙም ነበሩ። ከእነዚህ መካከል ካሳ ከበደንና ዳዊት ወልደጊዮርጊስን መጥቀስ ያስፈልግ ይሆናል።ይህ ኃይል በግልና በቡድን የየራሱ አላማ አንግቦ ገብቷል።የደርጉ ኃይልም እንዲሁ ሌላ ተጨማሪ የራሱ ግብ ይዞ ገብቷል።

ይህ በተደጋጋሚ ሊዩ-ሊበራል እያልን መጥራት የለመድነው ኃይል ጥቅሙን በተሟላ አኳሃን ለማረጋገጥ የፖለቲካና የፀጥታ መዋቅሩ በመቆጣጠር የአገሪቱ ኢኮኖሚ በራሱ ፖሊሲና እቅድ እንዲመራ ለማድረግ ግዜ ማባከን እንደሌለበት ወስኗል። ምክንያቱም የምእራቡ አለም ከኢህአዴግ ጋር ሲያናቁሩት ከነበሩ ጉዳዮች መካከል አንዱና ዋነኛው አገሪቱ ስለምትከተለው የኢኮኖሚ ፖሊሲና አተገባበሩ ዙርያ እንደነበረ ሁላችን የምናውቀው ጉዳይ ነው። ስለሆነም አደረጉት እና በነሐሴ ወር መጀመርያ ላይ “ኢትዮጵያ በአይነቱ የመጀመርያ የሆነው አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አደረገች የሚል” ዜና ከኢትዮጵያ መገናኛ አውታሮች እንድንሰማው ተደረገ። “አገር በቀሉ” የኢኮኖሚ ማሻሻያ መደረጉ ሲነገረን ባለቤቶች ሆነው ዜናው ላይ በኩራት የቀረቡ ሰዎች እነማን እንደነበሩ አስታወሳቹ ? በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር አቶ ማይክል እና ፕሮፌሰር ሪካርዶ ሁስማን ናቸው። Mint press news March 2019 የዜና ማእከል ባወጣው ዘገባ መሰረት ፕሮፌሰሩ በአለም ዋነኛው የኒዮ-ሊበራል የኢኮኖሚ አለቃ ሆኖ አለምን በማደህየት የሃብታሞች መፈንጫ እንድትሆን የሚሰራ ሰው ሆኖ በአሁኑ ወቅት በቀለም አብዮት እያፈረሷት ባለችው ቬንዙዌላ ላይ እየሰራ ያለውን ስራ ገልፆልናል።በኛ አክቲቪስቶችም ስለ ሰውየው ሲነገር ስለሰማሁና ስላነበብኩ ከዚህ በላይ መዘርዘር አልታየኝም። በነገራችን ላይ የቀለም አብዮት መደመር ህዝበኝነት በሚል አርእስት ለእናንተ ባቀረብኩት ፅሑፍ የሚከተለውን ማለቴን አስታውሳለሁ፤ ከዚህ በፊት ያነበባችሁት ማለፍ ትችላላቹ።

--------የቀለም አብዮት ከቀዝቃዛ ጦርነት ማብቃት በኃላ እየተተሰፋፋና እየታወቀ የመጣ ቢሆንም ከዛ በፊትም የተሞካከረ ጦርነት (Act of War) ነው። ሲጀምሩት ግጭት አልባው ጦርነትና የመንግስት ለውጥ ማከናወኛ መንገድ ተብሎ የሚታወቅ የነበረ ቢሆንም ከግዜ በኃላ ግን ሰልፈኛው ከሚጠቀመው ኃይል ባለፈ አብዮቱን የሚመሩት አካላት ራሳቸው የግድያ ቡድን በመመልመል፣ በማሰልጠንና ለዚህ የተመረጠ መሳርያ በማስታጠቅ ከመንግስት በኩልም ከሰልፈኞቹ በኩልም ታዋቂ ሰዎች እንዲገደሉ በማድርግ መንግስትም በተገደለበት ባለስልጣን ተናዶ የአፀፋ እርምጃ እንዲወስድ ሰልፈኞቹም የተገደለባቸው ታዋቂ ሰው መንግስት እንደገደለው በማመን ሁለቱም በስሜታዊነት ወደ አፀፋዊ እርምጃ ገብተው አብዮቱ ወደኃላ እንዳይመለስ የሚያደርግ ስልት ተግባራዊ እያደረጉት ይገኛሉ።ይህንን የገለፅኩት በመስቀል አደባባይ በዶክተር አብይ የድጋፍ ሰልፍ የተፈፀመ የቦምብ ጥቃት አስመልክቶ ሃሳባቹና ግምታቹ ለማስቀየስ ሳይሆን በተጨባጭ በጆርጂያና ዩክሬን የነበሩ የቀለም አብዮት ታሪኮች ያረጋገጡት እውነተኛ ታሪክ ስለሆነ ነው።

 

በአሜሪካ ይህንን የሰው አገር መንግስት በማፍረስ አገር የመበተን ስራ የሚያከናውኑ በርካታ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች[NGOs]ስም በማቋቋምና በቢልዮን ዶላሮች ካፒታል በመመደብ የሚከናወን ተግባር ነው። ከእነዚህ መካከል United states agency for international development(USAID),National democratic institution ,Center for strategic and international study ,Freedom house ,National endowment for democracy, Albert Einstein institute እና ሌሎች የመሳሰሉ ተቋማት በማቋቋም በመረጃ፣ በአደረጃጀት፣ በገንዘብ፣ በእውቀት፣ በስልጠና፣ በቴክኒክ፣ በፕሮፖጋንዳና በመሳሰሉ ጉዳዮች በሽፋንና በግልፅ ከቁጥቋጦ ጀምሮ እስከ አውድማ ምርት መከወን ድረስ የሚመሩ ናቸው። ይህንን የበለጠ ለመረዳት የሚጠቅም ከሆነ Thierry Meyssan የተባለ የግሎባል ጥናት ፀኃፊ The CIA,NGOs and color revolution በሚል ፅሑፉ ያገኘሁትን አንድ ምስልም አጋርቻቹ ነበር። በፌስቡክ ፎቶ አልበሜ አለ ማየት ትችላላቹ።

በዚህ መንገድ በአለማችን በጣም ብዙ በዛፍ፣ በፍራፍሬ፣ በሃረግና በተለያዩ የአትክልት ቀለማት የተሰየሙ የተሳኩና ያልተሳኩ የቀለም አብዮቶች አካሂደዋል። የተወሰኑት ለመጥቀስ ያክል ፖርቹጋል 1974፣ፊሊፒንስ 1986፣ችኮዝላቫክያ1989 ዮጎዝላቭያ2000፣ ጆርጅያ 2003፣ ዩኩሬን2004፣ኢራቅ ፣ክይርጅይኪስታን፣ሊባኖስ፣ኩዌትና ኢትዮጵያ፣ ቤላሩስ፣ ማይናማር፣ኢራን ፣ቱኒዝያ፣ግብፅ፣ሶርያ በመሳሰሉና በሌሎች አገራት ተግባራዊ ሊያደርጉ ተንቀሳቅሰው በአንዳንዶቹ ሲሳካላቸው በሌሎቹ አልተሳካላቸውም ወይም ወደ ሁለተኛ የቀለም አብዮት ለመሸጋገር ተገደዋል።

በዚህ ዘመን እንኳንስ በኃያላን መንግስታት ደረጃ ይቅርና ግለሰቦች እንኳን አለምን በበጎ የመቀየርም ሆነ የማተራመስ አቅም ያላቸው መሆኑ በተለያየ አጋጣሚ አይተናል።ለዛሬ ከተነሳሁበት አላማ አንፃር አገሮችን በማፍረስ እኩይ ተግባር ተጠምደው ዝና ለማግኘት ከሞከሩ ውስጥ አንድ ሰው አይተን የአለም የፖለቲካ ጨዋታ ምን ያክል አስቀያሚና እንደ አገራችን ያሉ ያላደጉ አገሮች በግለሰቦች ኪስ ውስጥ እየኖሩ እንደሆነ ያሳየናል የሚል እምነት አለኝ።ከዚህ አኳያ ማሳያ ለማቅረበ እንደ ጆርጅ ሶሮስ የሚያክል ማግኘት አልቻልኩም።

ሰውየው ጆርጅ ሶሮስ ይባላል ሰኔ ወር 1930 በሃንጋሪ የተወለደ አሜሪካዊ ዜግነት ያለው ሰው ነው።እሱና አባቱ ከናዚ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ስማቸው ትተን በተለያየ የህይወት ምዕራፍ አልፎ በቢዝነሱ አለም ከተሳካላቸው የአሜሪካ ቢሊየነሮች አንዱ ነው።ሰውየው የሊበራሊዝም ደጋፊ በመሆኑ ርእዮተ አለሙን ከመደገፍና የቢዝነስ አለሙን ሞኖፖል ለማድረግ ከሞመከር ባሻገር አገርን በማፍረስ ህዝብ ያለ አገርና ያለ ህግ በማስቀረት ከሚዝናኑና ከሚረኩ ሰዎች ዋነኛው ነው። እንደ Truthwiki.com ዘገባ በሰይጣናዊ ስራው ከሚታማበት አንዱ ዶክተር ቶማስ ፍሬድን ከተባለ ሰው ጋር በመሆን በምዕራብ አፍሪካ የኢቦላ ቫይረስ ያስፋፋ ሰው እንደሆነ ተዘግበዋል።

ጆርጅ ሶሮስ አለምን ለማተራመስ “open society foundation” የተባለ መንግስታዊ ያልሆነ  ድርጅት በማቋቋምና በበጎ አድራጎት ስም በ70 አገሮች ቢሮ በመክፈት እንዲሁም  ለሌሎች ተቋማት ጭምር እስከ 18 ቢሊዮን ዶላር በማፍሰስ በተለያዩ አህጉሮች በነበሩ የቀለም አብዮቶችና የኢኮኖሚ ቀውሶች ጀርባ ያለ ሰው ሆኖ እናገኘዋለን።በ1993 በእንግሊዝ ባንክ ሲስተም ውስጥ ገብቶ የፓውንድ አቅም በከፍተኛ ደረጃ እንዲዳከም በማድረግ በእንግሊዝ ማህበራዊ ቀውስ የፈጠረ፣ በ1997-1998 በኤስያ በነበረ የኢኮነሚ ቀውስ እጁ በማስገባት በማለዥያ፣ ታይላድና ሆንግ ኮንግ ከፍተኛ ችግር እንዲፈጠር ያደረገ ሰው ነው።

በአለማችን ከነበሩ የቀለም አብዮቶች ውስጥ በሰርብያ፤ጆርጂያና በግብፅ በተካሄዱ አብዮቶች በከፍተኛ ደረጃ የተሳተፈበት ተግባር ሲሆን በቱርክ እስላሚስት ቡድን በማቋቋም ድርሻው ከፍተኛ ነበር የሚሉም አይቻለሁ። ሌላው ለብዙዎቻችን እንግዳ ይሆናል ያልኩት በአሜሪካ በራሷስ የቀለም አብዮት ተካሂዶ ያውቃል ወይ የሚለው ሲሆን መልሱ አዎ ነው።ሶሮስ ከቡሽ በኃላ የአሜሪካ ፖለቲካ ለመዘወር ተንቀሳቅሰዋል።ኦባማ እንዲመረጡ በማድረግና የኃላው የሂላሪ ክሊንተን ምርጫ ከ23 ሚሊዮን ዶላር በላይ በመመደብ ክሊንተን እንዲያሸንፉ ጥረት ያደረገና ሌላ የምስራቅ ቀለም አብዮት አሸንፎ ብዙዎች ባልጠበቁት ሁኔታ ዶላንድ ትራምፕ ሲመረጡ በአሜሪካ በአጭር ግዜ የተቀጣጠለው “ሐምራዊ አብዮት” የተሰየመው የቀለም አብዮት ታውጆ ከ10 ትላልቅ ከተሞች በላይ በሰልፈኞች የተጠለቀለቀው የቀለም አብዮቱ ባለቤት አቶ ጆርጅ ሶሮስ ነው። በሚል ከተለያየ ቦታ የቃረምኩትን በዚህ መልኩ ገልጨው ነበር።

ይህንን ሁኔታ ከኛ አገር ሁኔታ ጋር ያለው መመሳሰልና በአገራችን እየተካሄደ በነበረ የቀለም አብዮት ከነበረኝ ጥቂት መረጃ ጋር አያይዠ ለመዘርዘር ሞክሬም ነበር። በወቅቱ አንዳንድ አንባብያን በኢ-ሜይል አድራሻዮ “ተቃውሞ ሁሉ እንዴት የቀለም አብዮት ይባላል” የሚል ገንቢ ጥያቄ እንዳነሳቹሁልኝ አስታውሳለሁ። እውነት ነው ተቃውሞ ሁሉ የቀለም አብዮት አይደለም። የቀለም አብዮት ከሌላው ተቃውሞ የሚለይባቸው መለያ ባህሪያት መኖራቸው ግን እሙን ነው። እስኪ ይህንን ዜና ያልሰማቹ ካላቹ ላካፍላቹና ሌላው በአገሪቱ እየሆነ ስላለው ጠቅላላ ሁኔታ ጋር በማያያዝ አይታቹ ፍርዱ ለናንተ በመተው ቀጣይ የሚሆነው አብረን እንይ ። ጆርጅ ሶሮስ ለቀለም አብዮት ማስፈፀምያ ካቋቋማቸው ድርጅቶች አንዱ “open society foundation” ነው። እ.አ.አ october 15 2019 ድርጅቱ በራሱ ድረ-ገፅ Soros Economic Development Fund Joins Ethiopia Investment Fund በሚል አርእስት ባወጣው ዘገባ የሚከተለው ገልፆልናል፤ The Open Society Foundations are investing $10 million in the Cepheus Capital Growth Fund focused on supporting business development in Ethiopia, as part of its broader commitment to support Ethiopia’s democratic and economic development. ይላል። በሌላ በኩል አንድ በአሜሪካ የሚገኝ አገርኛ ጉዳዮች የሚዘግብ ሚድያ ጆርጅ ሶሮስ በ “open society foundation” በኩል ለኢሳት ቴሌቪዥን ሊሰጥ የነበረ 5 ሚልዮን ዶላር በተመለከተ ከአብይ አህመድ፣ አበበ ገላውና አንዳርጋቸው ፅጌ ጋር እንደሚያያዝና በአውሮፓ የተለያዩ ግልፅ ያልሆኑ ውይይቶት ከተካሄዱ በኃላ በኢሳት በተፈጠረ ውዝግብና ተያያዥ ጉዳዮች የገንዘቡ ስጦታ መታገዱን  አንድ ዘገባ አቅርቧል።

ሌላው ባለ አጀንዳና በህዝቡ የለውጥ ባህር ውስጥ ዋናተኛ የሆነው የኤርትራ መንግስት ሲሆን በግልፅና በስውር ኢትዮጵያን የማፍረስ አጀንዳ የኤርትራ የቅድምያ ቅድምያ አድርጎ የወሰደና የአገሪቱ ትኩረት፣ ሃብትና አመራር በሙሉ በዚህ አጀንዳ እንዲጠመድ በማድረግ “ኢትዮጵያን በማዳከምና በማፍረስ የኤርትራ ሉአላዊነት ይረጋገጣል” በሚል የተሳሳተ የውጭ ፖለሲ መሰረት ከሁሉም የኢትዮጵያ ኃይሎች የኤርትራ ህልውና ከሚቃወሙም ጭምር ስልታዊ ጉድኝት በመፍጠር እናሳካዋለን ያሉትን ለማሳካት አብይን በሰላይነት መልምሎ ፀረ-ኢትዮጵያ በሚደረግ እንቅስቃሴ ለ6 አመታት እስከማሰራት መሄዳቸው አንዳርጋቸው ፅጌ በካናዳ ባደረገው ንግግር ከሰማነው አስገራሚ ነገር ጀምሮ ብዙ ነገር እያደረጉ እንደነበሩና እንዳሉ ሁላችንም እየተረዳነው መጥተናል።

ሻዕብያ “ለውጥ” የሚባለውን ተከትሎ ለሁሉም ኤርትራ ለነበሩ ተቃዋሚ ኃይሎች አስቀድሞ ግዳጅ በመስጠት ወደ አትዮጵያ አስገብቷል። ራሱም “ማታ ነው ድሌ” በትግርኛ እየዘፈነ አዲስ አበባ ተገኝቷል። የኤርትራ መንግስት ከማንኛውም የኢትዮጵያ ኃይል ጋር ስትራቴጂክ ወዳጅነት መፍጠር አይፈልግም። ከአብይ መንግስትም ጭምር። “በኢትዮጵያ በየግዜው ከሚፈጠር ሁኔታና ኃይል ጋር መሯሯጥ ሳይሆን ኢትዮጵያን በዘላቂነት በማፍረስ በማንኛውም ግዜና ሁኔታ ከኢትዮጵያ በኩል ሊመጣ የሚችለውን ስጋት በዘላቂነት በማስወገድ ነው ኤርትራ እንደ ሉአላዊ አገር መቀጠል፣ መበልፀግና የቀጠናው የበላይነት መቆጣጠር የምትችለው።” የሚል ግልፅ ያለ አቋም ነው ያለው ።

ታድያ የኢትዮጵያ መንግስትም ሆነ ህዝብ በብዙ አስርት ሺዎች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ወጣቶች በመገበር አይቀጡ ቅጣት ቀጥቶ ወደ መቃብር ያስገባውን ኃይል በአብይ በ “ሰላም” ስም ሬሳውን ከመቃብር አውጥቶ አሸናፊው በተሸናፊው እግር ላይ በመውደቅ “ኢትዮጵያ እንደፈለግክ አድርጋት” ብሎ አገርን መስጠት በየትኛው የሃይማኖት እምነት ፅድቅ፣ በየትኛውም ዲፕሎማሲና የፖለቲካ አስተምሀሮ ድንቅ ሊሆን አይችልም።  ኢትዮጵያ በሻዕብያ ብቻ ሳይሆን በአህጉር ደረጃ የገነባችው ተፅእኖ ፈጣሪነትና በህዝቡም ሆነ በወታደሩ የነበረው የአሸናፊነት ታሪክና ስነልቦና ለኢሳያስ በማስረከቡ ምክንያት ሻዕብያ በኢትዮጵያ ከያዛቸው እቅዶች ካሰበው በብዙ ፍጥነት መከወን መቻሉን እያየን ነው።

ሌላው የራሱ አጀንዳ ቀርፆ ሲንቀሳቀስ የቆየና አሁንም በከፍተኛ የሞት ሽረት እየተንቀሳቀሰ መሆኑ የሚነገረው የግብፅ መንግስት ነው። በተለያዩ አጋጣሚዎች ከአብይ መንግስት በፊትም ጀምሮ በኢንቨስትመንት፣ በኤምባሲውና በአፍሪካ ህብረት ሽፋን ብዙ ስራ እየከወነ መቆየቱ እርግጥ ሆኖ አብይ በካይሮ የፈፀመው መሃላ ተከትሎ በወርቅነህ በኩል የተፈረመው ሰነድ ከቀደመው የተደራዳሪነት የበላይነታችን አንፃር ችግር እንደነበረበት ከመገለፁ ባለፈ በመረጃ የሚደገፍ ምንም የሰማሁት የተጨበጠ ነገር ሳይኖረኝ በይሆናል አልዘባርቅም። አንድ ነገር ግን ማለት የሚቻለው ከለውጡ በፊት በግብፅ ባለስልጣናት በኩል ኢትዮጵያ ላይ ምን ከማን ጋር እየሰሩ እንደሆነ  በሚድያ ከሰማናው ነገር የተለየ እየሆነ እንዳልሆነ ሁላችንም ምስክር መሆን የምንችል ይመስለኛል። ኢንጅነር ስመኘው ግን---

ሌሎች የአረብ አገሮችም በኛ የለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ ተዋንያን ሆነው መክረማቸው በደማቁ ያየነው ነው። በተለይ ሳውዲና የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች የጋራም የተናጠልም አጀንዳ ይዘው በቅኝ ግዛት ያልተገዛችውን አገሬን በዶላር በመግዛት ብሔራዊ ጥቅማችን የሚሉት ለማሳካት ደፋ ቀና እያሉ ናቸው። የእነዚህ ተስፋፊነት ያላስደሰታቸው ኳታርና ቱርክም መንግስት በሩ በከፈተላቸው መጠን በግልፅ እንዲሁመ መግቢያ በሩ በጠበባቸው ግዜ በህቡእ ተከብራ በኖረችው አገራችን በመቆመር ላይ መሆናቸው ሌላ ቦታ ሳትሄዱ የገልፍ አገሮችና የመካከለኛ ምስራቅ የሚድያ ዘገባዎችና ትንታኔዎች መከታተል ብቻ በቂ  ነው።

ሌላው ባለ አጀንዳ “ድሉ የኔ ብቻ ” ብሎ ወደ አገር የገባው የኦሮሞ ፅንፈኛ ኃይሎች እንቅስቃሴ ሲሆን እነዚህ ኃይሎች ሌላው ቀርቶ በአንድ ፓርቲ ስም አራትና ከዛ በላይ ኃይሎች ይኑሩ እንጂ ከግለሰቦች በስተቀር የሁሉም አቋም አንድ ነው። “ኢትዮጵያ የምንመራትና ወደፈለግነው የመዘወር እድሉ ካገኘን ኢትዮጵያዊ ነን። ይህ ካልሆነ እኛ አገር ነን” የሚለው ነው።ይህ አመለካከት ከኢትዮጵያ ሱሴ ጀምሮ ለአብዛኛው የኦህዴድ አመራሮችንም የሚገልፅ አስተሳሰብ ነው። ይህንን ለማሳካት በውጭ ለበርካታ አመታት በስደት የነበሩ ተቃዋሚዎችና ምሁራን በቆዩባቸው ግዚያቶች ከሚኖሩባቸው አገራት በየሚኖሩባቸው መንግስታት መዋቅር ውስጥ መልካም ግንኙነት በመፍጠር አንዳንድ ባለስልጣናትንና ተፅእኖ ፈጣሪ ሰዎችን ከጎናቸው ለማሰለፍና የዲፕሎማሲ ጫና ለመፍጠር በቻሉት መጠን ተንቀሳቅሰዋል። በዚህ ረገድ ከአውሮፓ በጀርመንና በኖርዌይ እንዲሁም በአንዳንድ የአሜሪካ የሴኔትና የኮንግረንስ አባላት ያገኙት እድል ቀላል አይደለም።

በእነዚህ መንደርደርያነት ድሮም ጠንካራ ወዳልነበረውና አብዛኛው አመራሩ በዚህ አመለካከት የተሰለበ የኦህዴድ/ኦዴፓ ፓርቲ  ውስጥ የውጭው ኃይል  ሰተት ብሎ ለመግባት አስቸጋሪ አልነበረም። ቀሪው ስራ የሚሆነው የዚህ የጥፋት ሃይል አባላት መሆናቸው የሚያረጋግጥ የግል ማህደር ሞልቶ መታወቅያ መስጠት ብቻ ነበር።  የድርጅቱ ህግና ደምብ ከሚፈቅደው ውጪ “የአመራር ለውጥ አደረግኩ” ብሎ ሊቀመንበሩንና ምክትሏን በማባረር ለማ መገርሳንና ወርቅነህን መተካታቸውን በነገረን ግዜ ኦህ!dead? በሚል አጭር ፅሁፍ በፌስቡክ ግድግዳዮ ላይ መለጠፌን አስታውሳለሁ። አሁንም አለ። በዛን ወቅት የተካሄደው ስብሰባ የአገር ብተና ሃይሉ የኦህዴድ ድርጅቱን ከነ ስያሜው ጋር ሙሉ በሙሉ መረከቡን ለመግለፅ ነበር። ስራውን የተከናወነበት መንገድ በጀብደኛ ስሜቱ ጁሃር ራሱ ከነገረን ውጭ ያሬድ ጥበቡ በቅርቡ በመፅሐፉ ምርቃት ምክንያት በአሜሪካ ተዘጋጅቶ በነበረ የውይይት መድረክ በግልፅ አስቀምጦታል። እናም የኦሮሞ ኃይል ወደ አንድ በማሰባሰብ በእጃችን የገባውን ስልጣን እንዴት ወደ ኦሮሞ ጥቅም በመቀየር በኢትዮጵያዊነት የራሳችን አዲስ ታሪክ እንስራ በዚህ የማይሳካልን ከሆነ የተፈጠረው ሁኔታ ተጠቅመን እንዴት ኦሮምያ የምትባል አገር እንመስርት የሚል አጀንዳ ይዘው ጉዞ ጀምረዋል፣ እየተጓዙም ይገኛሉ፣ እኛም  ዝም ብለን እነሱ ወደመሩን መጓዙን ቀጥለናል።

በዚህ ውስጥ አብይ መነሳቱ ግድ ይላል። በኔ እይታ የአብይ ጉዳይ ከኦሮሞ ፖለቲካና ከኦህዴድ ብቻ አያይዞ ማየት ትክክል አይሆንም። አብይ ከኦሮምያ፣ ከኦህዴድ፣ ከኢህአዴግ፣ ከኢዜማና ከኢትዮጵያም ውጭ ከራሱ ለራሱ የሚያገለግል “ፍልስፍና” ባለቤት የሆነ ሰው ነው። የፍልስፍናው መነሻ ታሪክም ሆነ የመጨረሻ መዳረሻ ስልጣንና የስልጣን እድሜ ማራዛም ነው። ኢትዮጵያዊነት፣ ኦሮሞነት፣ ኦህዴድነትም ሆነ ኢህአዴግነት እንዲሁም መጭው የብልፅግና ፓርቲ ሁሉም ራሳቸው የቻሉ ግቦች ሳይሆኑ ቀደም ሲል ለገለፅኩት የግል የስልጣን፣ የግል ስብእና፣ የግል ታሪክ በማግዘፍ ረገድ በሚኖራቸው ድርሻ ይወሰዳሉ መጣል ባለባቸው ቦታ ላይ ይጣላሉ። ከኢትዮጵያዊነት ወይም ኦሮሞነት በላይ ይህንን ግብ የሚያሳኩ ኤርትራ፣ ኢሳያስ፣ ግብፅ፣ አሜሪካ ወይም ሳውዲ ከሆኑ ፍቅር፣ መደመርና መሻገር ከነሱ ጋር ይሆናል ማለት ነው።

አብይ ለአገር መሪነት ብቻ ሳይሆን ለፖለቲካ ጨቅላነቱም በተግባር ያሳየን ቢሆንም በቅርቡ አቶ ዮሃንስ ቧያለው የተባለ የአዴፓ ም/ሊቀመንበርና አክቲቪስት "በፖለቲካ ፕላን A, ፕላን B, ማለት ትክክል አይደለም የፖለቲካ አሻጥር ነው" ብሎ እንዳሳቀን አይነት አይደለም። አብይ ሲጀምር ፕላን A ከማንኛውም ሃይል ጋር ተዛምዶም ይሁን ተጋምዶ ኢትዮጵያን ለረጅም ግዜ መግዛት፣ ፕላን B ይህንን ካልተሳካ ከጁሃርም ከሌላው በላይ የኦሮሞ አክራሪ ብሔርተኛ ሆኖ ኦሮሞን ገንጥሎ ህዝብን ለረጅም ግዜ መግዛት መቻል፣ ፕላን C ሁሉም የሚበላሹ ከሆነ ባለቤቱ ወደ አራት ኪሎ ስትመጣ ዘግታው የሚጣችው  የአሜሪካ መንግስት የሰጣት ቤትና ንብረት ስለማይመጥነው ቃል በተገባለት መሰረት ለአገልግሎቱና ለክብሩ ወደሚመጥን ቤትና ህይወት  ደህና እደሩ ብሎ ወደ "ስኳርት" አገሩ  መብረር ጠረጴዛው ላይ አስቀምጦ ነው።

ይህንን ደረጃ በደረጃ ለመጓዝ እየሞከረ ነው። ችግሩ ግን Plan A ሆኖ Plan B እንደማይሳካ ገና ከወዲሁ እያየው ነው። ስለሆነም ተስፋው በውጭ ሃይሉ ላይ ያደረገ ይመስላል። በመዋቅር ውስጥ ቦታ ስጠን ከሚል ጀምሮ ግደልልን፣ እሰርልንና መሬት ስጠንን አልፈው አሁን አገር ስጠን ደርሰዋል።መገለጫዎቹ ሁላችንም እያየናቸው ስለሆን መዘርዘር ባያስፈልግም ሁሉንም ያለመታከት እያከናወነው ይገኛል። እኛም ያንን ሁሉ ሰንደቋ ይዘን የምናለቅስላትና የምንዘምርላት አገር በጠራራ ፀሐይ በአንድ ሰው እየተሸጠች በስምምነቱ የአይን እማኝ ሆነን እያፈራረምናቸው እንገኛለኝ።

ከዚህ ጋር በተያያዘ አብይ ለምን የተለያየ ሽልማት አሸናፊ ሊሆን ቻለ? በተለይ እንዴትና ለምን የኖቬል ሽልማት አሸነፈ? ብለህ ከጠየቅከኝ አገር ሲፈርስ፣ ይህንን ሁሉ ህዝብ ሲጨፈጨፍ፣ ይህ ሁሉ ህዝብና ጋዜጠኛ ሲታሰር ለምን እንደለመዱት የተቃውሞ መግለጫ አላወጡም በሚል ጥያቄ መልስ እሰጥሃለሁ። ኢትዮጵያ በታሪኳ በጣም ብዙ መከራ ያየች አገር ብትሆንም እንደ አሁን ከጫፍ ጫፍ እንዲህ ያለ መከፋፈልና የመፍረስ አፋፍ ደርሳ አታውቅም። ስለሆነም ይህንን ስራ ላከናወነላቸው መሪና ኢትዮጵያ በታሪክ ለመጀመርያ ግዜ የሰላም የኖቤል ተሸላሚ ሆኑ። ብዙም አትገረም አብዝተህ ብቻ እልልልልል በል የአገርህ "መሪ" አይደል።

ይህንን በብዙ አገር ለብዙ ሰዎች ለብዙ ምክንያት ያደረጉት እንደሆነ ደግሞ ታሪክ ዘግቦታል። በዚህ ጉዳይ በርካታ የአገራችን ተንታኞችና አክቲቪስቶች ብዙ ምሳሌዎች አንስተው ሲገልፁ ሰምቻለሁ። እኔ ለጉዳዩ መነሻ እንዲሆነን አንድ ምሳሌ ብቻ ላንሳ። የግብፁ መሓመድ ኤልባራዳይ ለግብፅ ቀለም አብዮች ማከናወኛና ቀጥሎ የአገሪቱ መሪ በመሆን ምዕራባውያንን እንዲያገለግሉ የታጩ ግዜ  IAEA(አለማቀፍ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ) ተጠሪ ሆነው ይሰሩ ነበር። በወቅቱ ምስላቸው አግዝፎ ለመቆየትና ለማዘጋጀት ሲባል እሳቸውና የሚመሩች ድርጅት የ2005 የሰላም ኖቤል ሽልማት እንዲያሸንፉ ተደረገ።  በምን ምክንያት ተሸለሙ ካላቹ "የኒኩሌር ሃይል ለወታደራዊ አገልግሎት እንዳይውልና ለሰላማዊ አገልግሎት እንዲውል ባደረጉት አስተዋፅኦ" ይላል። ወቅቱ ሸላሚዎቹን ጨምሮ ሁሉም ሃያላን አገሮች የተባሉ ይህንን የጦር መሳርያ አሁን ካለው በበለጠ ለማዘመን እየሰሩ ባሉበት ሁኔታ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ኢራን ከአሜሪካና ከእስራኤል በኒኩሌር ጦር መሳርያ ጉዳይ መካረር ውስጥ የገቡበት፣ ባኪስታን ያመረተችው የኒኩሌር ጦር መሳርያ በአሸባሪዎች እጅ ይገባና አለም ትሸበራለች የሚል ስጋት በጨመረበት ሁኔታ ላይ መሆኑ እንግዲህ ሽልማቱ የተበረከተው።

እርግጥ ነው ሌላ እውነትም አለ። አሜሪካ በ UN የፀጥታው ምክር ቤት በኩል ኢራን በሯ ለአቶሞክ ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ ክፍት እንድታደርግ በተፅእኖ እያስወሰነች ኤልባራዳይን በተደጋጋሚ ኢራን ውስጥ አይደለም ለአሜሪካ ለዜጋው የማይፈቀድ ቦታ ገብተው በርብረዋል። የኢራንን ከፍተኛ የኒኩሌር መረጃ መሰብሰብና ለአሜሪካ መስጠት ችለዋል። በዚህ ረገድም ሰውየው ላበረከተላቸው አስተዋፅኦ ይህንን ሽልማት አይበዛበትም። ለኛ ደግሞ ይህን ሽልማት በማን? ለማን? ለምን? እንደሚሰጥ ግልፅ ያደርግልናል።

በቅርቡ ከትግራይ አክቲቪስቶች ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም አሉት ተብሎ ተፅፎ ያነበብኩት ቢሉትም ባይሉትም ገላጭ ስለሆነ እዚህ ልጠቀምበት፤ “አንድ በጎችን በተደጋጋሚ በቀበሮ የሚያስበላ እረኛ ተሸለመ ካሉህ በርግጠኝነት ሸላሚው ቀበሮ ነው” ይላል። እውነት ነው የብተና ሃይሉ አገር እንዲበትን  ግዳጅ ለሰጠው ሰው ግዳጁ መፈፀሙ ሲረጋገጥ እንዴት አይሸልሙት? እንዳውም የአሜሪካዋ ጥያቄ አቅራቢዋ ማህሌት አበራ እንደነገረችን "አብይ የጥበብ አድናቂ" ስለሆነ የኦስካሩም ሽልማት ለሱ ይገባዋል ይሉናል ብየ እየተጠባበቅኩ እገኛለሁ። በዚህ አጋጣሚ ያኔ ደስታችን በደምብ ለመግለፅ እንድንችል አዲስ ፓርኮች ሚሊኒዮም አዳራሽን አሁን ካለበት ሰፋ አድርጋቹ እንደገና ብትሰሩት እላለሁ ።

ወደ ጀመርነው እንመለስ ሌላው ባለ አጀንዳ "የለውጡ ባለቤት ነኝ" ብሎ የገባው የአሃዳዊ ኃይሉ ነው። ይህ ሃይል ሲፈጠር ጀምሮ ከኦሮሞ አክራሪ ሃይሉ እሳትና ጭድ ሆኖ የተፈጠረ ቢሆንም በውስጡ ያሉ መሰረታዊ ግጭቶችና ከአክራሪ ብሔርተኛው በተለይ ከኦሮሞ ብሔርተኞች ጋር ያለውን መሰረታዊ ቅራኔ በተካነበት የማስመሰል ባህሪው እፍን አድርጎ በመያዝ የድሉ ባለቤት ሆኖ “----ታጋይ ድል አርጎ ሲገባ” እየዘመረ ከትግል ከአሜሪካ ወደ አዲስ አበባ በአውሮፕላን የገባው ሃይል ነው።  ከቡድን በተጨማሪ “በግል ክብር ይሰጠኝ” እያለ እየተንጠባጠበ በመግባት የአቀባበል ብዓላትን ከትግል ቆይታው በላይ እንዲረዝም ያደረገ ነው። እነዚህ ኃይሎች ሁሉም ማለት በሚቻል መልኩ አማራ የሚባል ብሔር የለም ባዮችና ኦሮሞና ትግራይ ጠል ሲሆኑ ሌላውን ህዝብ የቁጥር መሟያ አድርገው የሚያስቡ ናቸው። አብዛኛዎቹ የሌላ አገር ዜግነት የያዙ ወይም እየተጠባበቁ የሚገኙ በመሆናቸው ባሉበት አከባቢ ሰልፈ እንዲበዛና እነሱም ከፊት መስመር ለመሰለፍና ለመጮህ የሚሯሯጡ ጭሆታቸው ከፍ የሚያደርጉት ለየሚገኙበት አገር ኢሚግሬሽን ቢሮ ለማሰማት ነበር።   

እንግድያውስ  ኢትዮጵያ እንግዳ ተቀባይ በመሆኗ ባሳለፍነው አንድ አመት ተኩል እነዚህን ሁሉ እንግዶች ተቀብላ ያስፈለጋቸው ነገር ባስፈለጋቸው መጠን እያቀረበች አሁን ባለንበት ሁኔታ አለን እላቹዋለሁ። ብዙ የጨፈርንበት ለውጥና የለውጡ ኃይል ወዴት ሊወስደን እንደፈለገ እንኳን ሳይነግረን አገሪቱ የአንድ መንገደኛ ሰው ያክል እንኳን እቅድና የአቅጣጫ መጠቆምያ ኮምፓስ ሳይኖራት አሜሪካ ሲስባት ወደ አሜሪካ፣ አረብ በዶላር ሲጎታት ወደ አረብ፣ አውሮፓ እኔ ነኝ ሲል ወደነሱ ሌላው ቀርቶ ኢሳያስ እንኳን ግማሽ አካሉ መቃብር ላይ ሆኖ በቀጭን ገመድ ሲስባት ወደ ሰሜን አቅጣጫ የምትጎተት እንዲሁም በውስጧ የተሳፈሩ ህዝቦች እርስ በርስ ሲጓተቱ ለመገልበጥ የምትወዛወዝ አገር ይዘን ነው እየተንፏቀቅን እንዳለን ያለነው።     

“ለውጥ” መጣ የተባለ ሰሞን ከህወሃቶችና ሌሎች ጥቂት ግለሰቦች በስተቀር ኢህአዴጉና ተቃዋሚው፣ ፀረ-ሰላሙ፣ አሸባሪው፣ ሌባውና ፖሊሱ፣ የመንግስት ሰራተኛውና የጎዳና ተዳዳሪው፣ አክቲቪስቱ፣ ተማሪው፣ መምህሩ፣ ሞስሊሙ፣ ክርስትያኑ እንዲሁም ሚድያዎች በሙሉ ሊባል በሚችል መልኩ በፀሐይ ላይ ፀሐይ የወጣለት ይመስል ሜዳው አልበቃ ብሎት ሲጨፍርና ሲዘል ነበር።ምንድነው? ምን ተገኘ? ስትለው ሁሉም አንድ ቃል ይደጋግማል።U(መደመር) በርካታ የእስልምና እምነት ተከታይም የመስቀል ቅርፅ በእጁ ይዞ መስቀል ያለበት T-shirt ለብሰዋል ይታያል። አንተስ? ስትለው መልሱ ያው አንድ ነው መደመር።

በወቅቱ ሂደቱና መጪው ነገር ብዙም እንደማያምር ብረዳም በግዜው ለሁሉም ተመሳሳይም ተቃራኒም ኃይሎች በእኩል በደስታ የሚያሰክር አንዳች ያላወቅኩት መለኮታዊ ነገር እንዳለ ራሴን እስከ መጠየቅ ደርሸ ነበር። እዚህ ላይ ከማንም በላይ ታሪክ ሊዘክራት የሚገባ ማህሌት አበራ የተባለች አብይ አሜሪካ በገባበት ግዜ በአዳራሹ ቀርባ ስለ መደመር በግጥም ያቀረበች የአቋም ሰውን ያለማስታወስ ግን እጅግ ከባድ ነው።በዛን የስካር ወቅት፣ በዛ የእብደት ዘመን በግጥም መልክ ያቀረበችው በጣም ገላጭ ነገር ይደንቅሃል፣ መካሪ የለም እንጂ ምነው አንዳርጋቸው ፅጌ ምንም ለማይጨበጥ መፅሐፍ ሁለት አመት ተጨንቆ 664 ገፅ ከሚፅፍና ለህትመት ያን ሁሉ ብር ከሚያወጣ እንደሷ አንድ ገፅ ባልሞላ ግጥም እውነት እውነቱ ተናግሮ ተኝቶ ባደረ ያስብላል። ለነገሩ እሱ አማካሪ ስለሆነ መካሪ አያስፈልገውም።

የመደመር ትሩፋቶች የተወሰኑትን በመጠቃቀስ ነገሩ ብናየው አይከፋም። ለመጀመር ያክል ቀደም ሲል በሽብር ወንጀል የተፈረደባቸውና የፖለቲካ እስረኞችን መፍታት በሚለው የኢህአዴግ ድርጅታዊ ውሳኔና ውሳኔውን ወደ ተግባር ለማሸጋገር የተደረገ ጥረት በበጎ ጎኑ መታየት የሚገባው ነው። በዚህ ውሳኔ ተጠቃሚ የሆኑ ዜጎች ብዛት ስትመለከት ልንደግፈውና ልናመሰግነው የሚገባ ጉዳይ ነው የሚል ስሜት አለኝ። ከዚህ ጋር ተያይዞ ግን የድርጅቱን ውሳኔ በማስታከክ በየትኛውም አለምና ሁኔታ ሊደገፍ የማይችል ጉዳይም ተፈፅሟል።

በአገር ክህደት፣ በሽብርተኝነት፣ በሰው ንብረትና ህይወት ማጥፋት ተጠያቂ የሆኑ ግለሰቦችን እንዲሁም በሙስና ወንጀል የተፈረደባቸውን አንጋግተህ የምትፈታበት ሁኔታ ለአገርም ሆነ ለተበዳይ ወገን በፍፁም አሳማኝ ምክንያት ማቅረብ አትችልም። የህግ የበላይነት የሚፃረር፣ ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች ፍትህ የማግኘት መብታቸው የሚጋፋና አገርንም ወደ አደጋ የሚከት እንደሆነ ምርምር አይጠይቅም። በተጨባጭ የሆነውም ይህንኑ ነው። ብዙ ሰው ይቅርታውን በመቀበል ከጥፋቱ ተፀፅቶ ከህይወት ጋር እየታገለ ያለ ቢሆንም በዛው ልክ ደግሞ ከነበረው በባሰ እንደ ቀደመው ተግባሩ አገርን ለማፍረስ ተንቀሳቅሷል።

እዚህ ላይ ህወሃት መራሹ ኢህአዴግ  ብዙዎቹ መካከል በርካታዎቹን መታሰር የነበረባቸው ሰዎች ለአገር ጥቅም፣ ለህዝብ ሰላምና ደህንነት ሲል አስሯቸው እንደነበረ  አሁን ከብርሃን በላይ ደምቆ ታይቷል። ያኔ እንኳን “የለውጥ”  ሰሞን ሰዎቹ ስለትግላቸው ግዝፈት ሊነግሩን በማሰብ የፈፀሙትን ወንጀል በታጋይነት ኩራት ዘክዝከው አልነገሩንም? የነገሩን በሙሉ በወቅቱ የነበረው ህግ ጥሰት አልነበረም? ታድያ ህግ የማስከበር ሃላፊነት የነበረበት መንግስት ህግ ማስከበር አልነበረበትም? ብለን እንድንጠይቅ፣ መንግስት ያኔ ይህንን ባያደርግስ ኖሮ? ካልክ  ሶርያና ሊብያ መጥራት አያስፈልግህም ኢትዮጵያ እየሆነ ያለው በቂ ማሳያ ስለሆነ።

በነገራችን ላይ እነ አሳምነው ፅጌና ተፈራ ማሞ መጀመርያ የታሰሩ ግዜ ብዙዎቻችን በወቅቱ በታሰሩበት የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ሳንስማማ “አማራ በመሆናቸው ብቻ በግፍ ታሰሩ” ብለን መጮሃችን እንስታውሳለን። እኔም በወቅቱ ቅሬታ ፈጥሮብኝ እንደነበር አልሸሽጋቹም። ታድያ በቅርቡ የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አበረ አዳሙ “ከድል” በኃላ በኢሳትና በቅርቡ ከአባይ ሚድያ ጋር በነበረው ቆይታ እነ አሳምነውና ተፈራ ከሁለቱም ወገን በተፈጠረ ስህተት መፈንቅለ መንግስቱ መክሸፉንና እነሱ ለእስር ቢዳረጉም የመፈንቅለ መንግስቱ ስዊዲን አገር ሆኖ ያቀነባብር እንደነበርና አንዳርጋቸውም በጉዳዩ ተሳታፊ እንደነበር በመግለፅ ከዘረዘረ በኃላ ዝርዝሩን በዚህ ሚድያ መዘርዘር አያስፈልግም ብሏል። አያይዞም አሁን ያለው መንግስት በዚህ የሚከሰን አይሆንም ብሎ እንደያምን ምህረትም እንደተደረገላቸው የማፌዝ ሳቅ በመሳቅ ይገልፀዋል።  

 መልሱን  እዚህ ቃለ መጠይቅ https://youtu.be/37QXubdHsEo ከ22ኛ ደቂቃ በኃላ ታገኙታላችሁ።

አበረ አዳሙ ታድያ አሁን አንተ መንግስት ከሆንክ በኃላ የፖሊስ ኮሚሽነር ሆነህ አሳምነውን ለምን ገደልክ እነ ተፈራና አለበልስ ለምን አሰርክ ሲባል በጣም በብስጭት በለውጥ ምክንያት ከእስር እንዲፈቱና ሹመትም እንዲያገኙ ያደረገን የለውጥ ኃይልና የለውጥ መሪዎቻችን ጨፍጭፈው ስለገደሉና የመፈንቅለ መንግስት ሙኩራ ማድረጋቸው በሚል ይግልፅልሃል። እዚህ ውስጥ ወያኔ አንዳርጋቸውን፣ ተፈራን፣ አሳምነውን ማሰሩና አለበልን መፈለጉ ለምን እንደሆነ ግልፅ ሆነ፣ አሁን ያለው የብተና መንግስት የእስረኞች ይፈቱ የኢህአዴግ ድርጅታዊ ውሳኔ አስታክኮ አብይ ማን እና ማንን መፍታቱ፣ በመፍታቱ ያመጣው ጣጣ ካሰየን በኃላ አንዳርጋቸው የሰኔ 15ቱ ጥቃት እንደሚፈፀም ስም ዝርዝርቸውም ጭምር ለአብይ ሰጥቸው ነበር ብሎ መናገሩን የሰማን ሰዎች አንዳርጋቸው የኤርትራና የምዕራባውያን መልእክተኛ ሆኖ ሲሰራ ለአብይም መልምሎ 6 አመት ሙሉ ለግንቦት 7 እና ለኤርትራ ይሰራ እንደነበር ራሱ የነገረንን ብንደማምረው ምን አይነት ስእል ሰጠን? “የለውጥ ኃይሉ” ማን እንደሆነስ ገባን? የደህንነትና የፖሊስ አባላቱ በሰብአዊ መብት ጥሰት ስም መታሰራቸውስ ለምን እንደሆነ አሁን ገና ጠየቅን? እኔ እንጃ ? ከገባን ጥሩ 

በሌላ በኩል ግን አሁንም የለውጥ ሃይል ነኝ ባይ እስረኞችን ፈታሁ በሚል ሊመፃደቅብን የሚችል ሊኖር አይችልም። ለምን ቢባል አሁን ገና ለገና ችግር ሊፈጥር ይችላል፣ ዝም አይልም እየተባለ ብቻ እንኳን የታሰረና እየታሰረ ያለው ስታይ ከነበረው የከፋ ሁኔታ መምጣቱን ይታይሃል። ከጋዜጠኞችና ከሚድያ ነፃነት ጋር በተያያዘ በእስር ላይ ከነበሩ ጋዜጠኞች በለውጡ ከተፈቱት ቁጥር ብያንስ በሁለት ሰው እንደሚበልጥ ስንቶቻችን እንደምናውቅ እርግጠኛ አይደለሁም። እኛ ጋዜጠኞች ታረሱም ተፈቱም ብለን የምንጮህላቸው በውጭ አጀንዳ የሚንቀሳቀሱ በመሆናቸው የውጭ ሚዲያ ሽፋን የሚሰጣቸውን ጥቂት ሰዎችን ነው። እስክንድርና ተመስገን በምን ሁኔታ እንዳሉና ለምን እንዳልታሰሩም ሁላችን ይገባናል። ስለ መለስ የግል ስብእናና ቤተሰቡ በውሸት የሚፅፉ ብዙ ጋዜጦችን በአገራችን ሲታተሙም ሲሸጡም እናውቃለን። ዛሬ “የተጠለፈው አብዮት” የሚል አብይን የሚተች መፅሃፍ ሳትፅፉ አልቀራቹም። እናንተን ነው የምንጠረጥረው በሚል የታሰሩ ሰዎችና ይባስ ብሎ አሳታሚውና አከፋፈላቹ ተብለው የታሰሩ የመፅሃፍ አዘዋዋሪዎች ቁጥር እየጨመረ ይገኛል።

“ግዜው የዴሞክራሲ፣ ይፍቅርና የመደመር ስለሆነ ማንኛውም ሃሳብ የሚያራምዱ ሚድያዎች እንዲያብቡ እንሰራለን” የተባልነው ከለውጡ የመጀመርያው ቀን ጀምሮ ነው። ቀጥሎ በህዋሃት ዘመን ያልበረ ስራ ተሰራ። እንደ ENN ቴሌቪዥን፣ ዛሚ ሬድዮ ለውጡን ተከትለው በምን ሁኔታ እንዳሉ ግልፅ ነው። የምን ልታዘዝ ሾው፣ በአሃዱ ሬድዮ ይቀርብ የነበረ የእነ ሽመልስ አበራ ፕሮግራም ለምን እንዲታገድ ተደረገ ? በቅርቡ ዋዜማ ሬድዮ እንደዘገበው ደግሞ ፋና ብሮድካስት በለውጡ ምክንያት ፈተና እንደገጠመው አንድ ዘገባ አስደምጦናል። 

ከሰላም አንፃር የለውጥ ትሩፋት ወደ መዘርዘር አልገባም ምክንያቱም ምን ለማን ልናገር? ምክንያቱም ችግሩ ወደ ሁሉም ዜጋ በር አንኳኩቶ ገብተዋልና ነው። የሌላው ትተን እስኪ መንግስት ከቀሸበው በኃላ በራሱ የሰጠን ሪፖርት ብቻ ወስደን ብናይ እንኳን 2011 ዓ/ም ብቻ ከ1200 በላይ ዜጎች መገደላቸውና ከዛ በላይ መቁሰላቸው ገልፆልናል ።አስቡት እንግዲህ ሞት በረከሰበት ዘመን ላይ ስለሆንና በአማራና በኦሮምያ ክልሎች በብዙ ቦታ የታችኛው የመንግስት መዋቅር በፈረሰበት ሁኔታ በየገጠር ቀበሌው የሞተውን ህዝብ አይጨምርም ማለት ነው። ከዚህ ውጭ ያለው ዋናው ጉዳይ ግን አብዛኛው ህዝብ ራሱ ባይሞትም የደህንነት ስነ ልቦናው ተገድለዋል። ሰላም አይሰማውም፣ነፃነት የለውም፣ ደህንነቱ ከመንግስት እንደማያገኘው በመተማመን ራሱ ለመከላከል ያለው አማራጭ እየተጠቀመ ይገኛል። እኔ አሁን የምሰራበት መስሪያቤት በሰራው አጭር የዳሰሳ ጥናት መሰረት በህገ ወጥ መንገድ እየተዘዋወረ ካለ የጦር መሳርያ ውስጥ በርካታው የግሉ ደህንነት ከመንግስት አይገኝም ብሎ ተስፋ የቀረጠበትን ደህንነቱን በራሱ ለመጠበቅ በማሰብ እየተደረገ ያለ እንደሆነ ነው።

እንዳው ግን በሞቴ እስኪ እውነት እንነጋገር በወያኔ ዘመን  ከጎንደር መተማ በወታደራዊ አጀባ ይክሄድ ነበርን? በክልሉ የክልሉ ባለስልጣናት እንዳይገቡ የሚከለከሉበት ቀበሌ ኖሮ ያውቃልን? የአዲስ አበባ መቀሌ መንገድ እንደ ድሮ አትዮ- ኤርትራ ድንበር ሆኖ ያውቃልን? ከአዲስ አበባ ሃረር በፈለጉት ግዜ ተነስቶ መሄድ ይቻላልን? ከአዲስ አበባ ሃዋሳ ሰው የእለት የመዝናኛ ቦታው ነበር ዛሬስ? ከክልል ክልል፣ በክልል ውስጥ ከወረዳ ወረዳ አስተዳዳሪዎች በነፃነት ያለ አጃቢ እየተንቀሳቀሱ ነውን? ኦዲፒ/ኦህዴድ ምዕራብ ወለጋና ቀሌም ወለጋ ሁለት ዞን ሙሉና የተወሰነ የቦረና አከባቢ እያስተዳደረ ነውን? ኦህዴድ እንደ 2011 ካድሬዎቹና ፖሊሶቹ ተገድለውበት ያውቃሉ ? ኦህዴድ ተበሳጭቶ በወለጋ ህዝብ የውግያ ሄሊኮፕተር ልኮ ህዝብ እንደ ደበደበው ወያኔ በህዝብ ላይ ህይንን አድርጎ ያውቃልን? እንዳው ግን ደቡብ እንደ ክልል በሰላም ችግር ምክንያት ሙሉ በሙሉ በወታደራዊ አገዛዝ ወድቃ ታውቃለች? ወዳጄ ሃረር የሚባል ክልል በአሁኑ ስአት በህይወት ስለመኖሩ የምታውቀው ነገር አለ? በወያኔ ግዜ ድሬዳዋ በእንዲህ ያለ የሰላም ሁኔታ ነበር የምታውቃት? እያሉ እያሉ ብዙ ማለት ይቻላል አጀንዳው ግን እሱ አይደለም። እናስ ጓዴ ሰላም “በዘመነ ለውጥ” እንዴት ነው? አንድ የፌስ ቡክ ጓደኛየ ይህንን እና የሚቃጠሉ መኪኖችን እያሳየ እንዲህ ብሎ ፃፈ፤ “አንዲት እብድ ቤቴ ብላ በጎማ፣በእንጨትና ጨርቅ ወዘተ እንደነገሩ አድርጋ ያቆመችው ቤቷን በእሳት አቃጠለችና ቤቱ በእሳት ሲምቦገቦግ አይታ እሰይ አሁን በራልኝ” አለች የሚል የአባቶቻችን አባባል የገለፀበት ጉዳይ የአገሬ ሁኔታ እያየሁ ያስገርመኛልም። አንደ የመጨረሻ ጥያቄ ከተፈቀደልኝ ትግራይ ለምን ከዚህ የተለየ ሁኔታ ውስጥ መኖር ቻለች? ለዚያውም እኛ አናስተኛሽ እያልናት?  ራስክን ጠይቅ?

ከኢኮኖሚ አንፃር ያለው የለውጡ ትሩፋትና ምስቅልቅል አሁን በቀጥታ እየተሰማን ካለው ክብደት በላይ መሆኑ እየቆየን እናየዋለን።ሁኔታው ከምናስበው በላይ መሆኑ አይቀርም። መለስ በ1983 ደርግ ትቶልን የሄደዉ ባዶ ካዝና ነው በሚል በወቅቱ ለነበረው ሁኔታ የገለፀበት ሁኔታ አብይ የሁሉም መሪ  ስራ መጀመርያ ቃል መስሎት ይህችን ቃል ሲጠራት ሰማን ። በለውጥ ግዜ ምንስ ቢባል ምን ችግር አለው ብየ ባልፈው ይሻላል። አቶ አያልቅበት(ጠቅላያችን) “የመደመር ፍልስፍና” በኦሮምያ አከባቢና በአንዳንድ ኦህዴድ አባላትም ጭምር ተቀባይነት እያጣ መምጣቱን ሲያሳስባቸው ቆይቶ  በቅርቡ በኦሮምኛ ባደረጉት ቃለ ምልልስ “እንደ መንግስቱ ሃይለማርያምና መለስ ሪእዮተአለም ከውጭ ማስመጣት  ለአገር እንዳልበጀ ስለተገነዘብኩኝ “የመደመር ፍልስፍና” ከገዳ አንድ አካል በመውሰድ አገሪኛ ቅርፅ በማስያዝ ለአገር መፍትሔ ማምጣት ነው” ብለው ፈገግ እንዳደረጉን ሁሉ ለአገርኛ የኢኮኖሚ ችግር አገርኛ መፍትሄ በማጥናት እያጋጠመና እየተባባሰ ያለው የኢኮኖሚ ቀውስ አማካይ የዋጋ ግሽበቱ ወደ 20% እየተጠጋ በመሆኑ ይህንን ለመቋቋም የግድቡ ግንባታ በማዘግየት አምና ከነበረበት ከ2% በላይ እንዳያድግ ማድረግና መሰረታዊ የምግብ ፍጆታ የዋጋ ንረት ለመከላከል ደግሞ ቤተመንግስት ውስጥ ቃርያ፣ጎመንና ኮረሪማ ሳይቀር መትከል የመሳሰሉ ናቸው። 

ለውጡ ከዲፕሎማሲ አንፃር ያየሰው ሽመልስ የተባለ ጋዜጠኛ በቅርቡ ያቀረበው ትንተና እንዳለ ወስጄ በአብይ ዘመን ያለው የዴፕሎማሲ ውድቀት የሚጀምራው ባለ ሞያዎች የዲፕሎማሲ ቋንቋ የሚሉት በአካል፣ በምልክት፣ በሰላምታና በአቀራረብ ካለው ችግር ይጀምራል። አብይ ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያ ህዝብን ወክሎ ለሚያገኛቸው የሌሎች አገር መሪዎች  እናቷ ፈልጋ እንዳጣች ጥጃ እየዞረች ከአገኘቻት ላም እግር መሃከል ሽጉጥ የማለት እንዲሁም ደስ ብሏት የሆነ ነገር እንፈለገች ኮረዳ አስሬ የፍቅረኛዋን ጀርባ እንደምትነካ ሲያረገው በተደጋጋሚ እያየን ነው። የሌላው ጉዳይ ብዙ የተባለ ነው።

ሲጠቃለል ለውጡ ይህንን የሚመስል ከሆነ ለውጡ ማን አመጣው የሚለው መልስ ለመስጠት ነገሩ ቀላል ይሆና። የለውጡ ፍላጎትና ለውጥ እንዲመጣ በየራሱ መንገድ የታገለው ህዝቡ ሁሉ ስለሆነ እውነተኛ ለውጥ ቢመጣ ኖሮ የለውጡ ባለቤትና ጎረቤት ብሎ ነገር የለም።ሁሉም የለውጡ አምጪም ተጠቃሚም ይሆን ነበር። ዳሩ ግን የህዝቡ ትግልና የለውጥ ፍላጎት ገና በጧቱ ነው ውሃ የበላው። አሁን ያለው የአገር ብተና ለውጥ በተመለከተ በአክራሪ ብሔርተኛውና በአሃዳዊው ኃይል መካከል ያለው የለውጡ የኔ ነው መቀራመት ረጋ ብለው አስበው የየድርሻቸው ቢወስዱ። ሁለቱም አንድ እውነት አላቸው አሁን ያለው የጥፋት ለውጥ አስመጪም አከፋፋይም  ሁለቱም ናቸው።

  እወቁልኝ፦

     በዚህ ፅሑፍ ሁሉም ዓይነት ማህበራዊ ሚድያ፣ የአገር ወስጥና የውጭ ሚድያዎችን በዋቢነት ተጠቅሜለሁ።

     ለማንኛውም አስተያየ አድራሻየ  በE-mail---- agerawiguday.et@gmail.com

 

Back to Front Page