Back to Front Page

መቀጣትና መወገድ ያለበት የኢህአዴግ ሰርአት እንጂ ታጋይ ጌታቸው አሰፋ አይደለም ።

መቀጣትና መወገድ  ያለበት የኢህአዴግ ሰርአት እንጂ ታጋይ ጌታቸው አሰፋ አይደለም

ልኡል   ገብረመድህን (ከአሜሪካ ) 5.19.2019

    የ46 አመቱ ታጋይ ክንፈ ገብረመድህን ግድያ ( 13 May 2001) በኋላ የኢትዮጵያ ደህንነት ድርጀት በዋና ሀላፊነት ሲመሩት የቆዩ ታጋይ ጌታቸው አሰፋ ከሀላፊነታቸው በጡረታ ከተነሱ ድፍን አንድ አመት ሆነ ። ታጋይ ጌታቸው አሰፋ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ትዕዛዝ ከሀላፊነታቸው የተነሱት በሰኔ ወር 2018 ነበር ። በኢህአዴግ ሰርአትና ስልጣን ውስጥ የመጠንና የይዘት ልዩነት ካልሆነ በአንድ ሆነ በሌላ ወንጀል ያለፈፀመ ባለስልጣን ለመኖሩ እርግጥ መሆን አይቻልም ። በመሆኑም ታጋይ ጌታቸው አሰፋ የህግ ጥሰት ፈፅሞ ሊሆንም ይችላል ። ሆኖም ይህ ሰው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒሰትር አልነበረም ። ካልነበረ ደግሞ የቅድሚያ ቅድሚያ መጠየቅ የነበረበት አገርና ህዝብ ለማስተዳደር ሀላፊነት የተሰጠው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው ። በተዋረድም የኢትዮጵያ ርዕስ ብሔር ነው ። በመቀጠልም የኢትዮጵያ ህዝብ ተወካዮች ምክርቤት መሆን ነበረበት ።

Videos From Around The World

   የኢህአዴግ ሰርአት በሥልጣን የቆየው የዲሞክራሲ መርህ ተከትሎ ሳይሆን ህግ እየጣሰ ፣ የዜጎች መብት በቀጥታ ሆነ በተዘዋዋሪ እየረገጠ ፣ የተፎካካሪ ፖለቲካ ድርጅት አባሎች እያሰረ ፣ የሰብዓዊ መብት ታጋዮች አፍ እየሸበበ ፣ እንዲሁም  ነፃ ማህበራዊ መገናኛ እያፈነ ነበር ። የኢህአዴግ የፖለቲካ መርህ እና ተግባር ፍፁም የመጣጣም ችግር ነበረባቸው ። ስርአቱ በህግ ልዕልና የሚመራ አልነበረም ። የህግ ልዕልና በሌለበት አገር ህጋዊ ፍትህ አይኖርም ። የሚኖረው ጨቋኝ ህግ ነው ። ነፃ የፍህት ተቋም ባልነበረበት አገር ወንጀል ፈፃሚዎች በህግ ለመጠየቅ የህግ መፋለስ ይኖራል ። ማን ትክክለኛ ፍርድ እንደሚያገኝ በውል ሊታወቅ አይችልም ። ሁሉም የቻለው ወንጀል ፈፅሞ በየመንደሩ በመሸገበት በአሁኑ ወቀት የተወሰኑ ወንጀለኞች በወረንጦ እየነቀሱ ተጠያቂ ማድረግ ተገቢም አዋጪም አይደለም ። የኢህአዴግ ስርአት ባለስልጣናት በሰብሰናል እያሉ በስልጣን ላይ እንዲቀጥሉ መደረጉ ታላቅ ስህተት ነበር ። የበሰበሰ ሥርዓት እንዴት አገርና ህዝብ ያስተዳድር እንደነበር ለማሰብ አሰቸጋሪ ነው ። ሥርዓት ከበሰበሰ መጣል እንጂ በስልጣን እንዲቀጥል መፍቀዱ የሥርዓቱ ችግር ሳይሆን የህዝብ ችግር ነበር ።

    የኢህአዴግ ሥርዓት የዲሞክራሲና የግልፅነት ችግሮች ያሉበት ሥርዓት በመሆኑ ለተፈፀመው የወንጀል ሒሳብ በጋራ ማወራረድ እንጂ በተናጠል በወንጀል ተጠያቂ ማድረግ ከህግ አንፃር ፍትሀዊ አይሆንም ። ያለፈው ወንጀል ለመመርመር ገለልተኛ የወንጀል አጣሪ ኮምሽን ማቋቋም የተሻለ የህግ አሰራር ያመጣል ። ወንጀል ፈፃሚዎች ተጠያቂ መሆን አለባቸው ።ነገር ግን የተጠያቂነት አሰራር ታማኝነት እንዲኖረው ከመንግሥት ውጭ በገለልተኛ የፍትህ አካል መመርመርና መጣራት አለበት ። በዚህ መንገድና ሁኔታ የወንጀል ማጣራት ተግባር ካልተከናወነ የወንጀል ሒደቱ የተወሳሰበ ይሆናል ። የወንጀል ማጣራትና ተፈፃሚ ማድረግ የዘር ድጋፍ የሚያስፈልገው አይደለም ። ወንጀል በፖለቲካ መርህም ማገድ ሆነ ማስቆም አይቻልም ። ሆኖም አሁን በኢትዮጵያ የመንግስት ወንጀለኛ ለማጣራት ሆነ በህግ ለመጠየቅ አሰቸጋሪ እየሆነ መጥተዋል ። ህዝብ ወንጀለኛ አሳልፌ አልሰጥም እስከማለት ደርሰዋል ። ይህ የስርአቱ ችግር ያስከተለው ማህበራዊ የፍትህ ቀውስ ነው ።

    በኢህአዴግ ሰርአት የተፈፀመ ወንጀል ጥቅል እርምጃ መወሰድ አለበት ። በተናጠል የሚወሰዱ የወንጀል እርምጃዎች የኢትዮጵያ ህዝብ የፍትህ ፍላጎትና መብት የሚያሟሉ አይሆኑም ። በጡረታ የተሰናበተ ታጋይ ጌታቸው አሰፋ በማሰር የሚገኝ በቂ ፍትህ አይኖርም ። ታጋይ ጌታቸው አሰፋ ወንጀለኛ ቢሆን ኑሮ ለምን በጡረታ ተሰናበተ ብሎ የሚጠይቁ በርካታ ሰዎች አሉ ። ለጥያቄዎቻቸው አጥጋቢ መልስ ያለ አይመስለኝም ። የእኔ ጥያቄም በመሆኑ እኔም ለጥያቄው መልስ ፈላጊ ነኝ ። በክብር በጡረታ የተሰናበተ ሰው ወንጀል ፈፅመሐል ብሎ መጠየቅ ክልክል ባይሆንም ፍትሐዊነቱ ግን አጠራጣሪ ነው ። የታጋይ ጌታቸው አሰፋ ጉዳይ የፖለቲካ ጉዳይ ይመስለኛል ። መፍትሔውም የፖለቲካ ውሳኔ መሆን አለበት ። ታጋይ ጌታቸው ወንጀለኛ ከሆነ የበላይ አለቆችም ወንጀሎች መሆናቸው አይቀርም ። በመሆኑም የወንጀሉ ውስብስብነት ለመቅረፍ የሚረዳ አሰራር የፖለቲካ ውሳኔ መሰጠት ብቸኛ አማራጭ ይመስለኛል ። የኢትዮጵያ ህዝብ በኢትዮጵያ እየተፈፀመ ያለ የፍርድ ሆነ የፍትህ አሰጣጥ ሒደት ሆነ ትግበራ ላይ የተሟላ እምነት የለውም ። የህግና የፍትህ አሰራር በህግ ማዕቀፍና ድንጋጌ መሠረት ያደረገ ሳይሆን በዘር አድላዊ አሰራር የሚፈፀም ነው ። በመሆኑም የፍትህ ታአማኝነት ላይ ጥርጣሬ አሳድሯል ።

    የኢትዮጵያ ድህንነት ድርጅት ሀላፊ ነበር ታጋይ ጌታቸው አሰፋ በማሰር የሚለወጥ ጉዳይ የለም ። መሠረታዊ የፍትሕ ማሰፈኛ መንገድ ተደርጎ የሚወሰደው ከዘር የፀዳ የፍትሕ ተቋም ሲኖር ብቻ ነው ። የኢትዮጵያ ፍትሕ ተቋማት በዘር ፖለቲካ መስፈሪያ የሚሰሩ እንጂ በገለልተኛ የህግ ባለሞያዎች የሚመሩ አይደለም ። ይህ አሳፋሪና ኋለ ቀር አሰራር ነው ። ዘር መሠረት ያደረገ የፍርድ አፈፃፀም በቅርብ ጊዜ ሞያዊ ተቋም እንደሚሆን እገምታለሁ ። ህዝብ በፍርድና ፍትህ ተሳትፎና እምነት ከሌለው የህግ ተፈፃሚነት ፍትሐዊነት ይጎድለዋል ። በመሆኑም በኢህአዴግ ሰርአት ውስጥ ለተፈፀሙት ሁሉም ወንጀለኞች ሀላፊነት የሚወሰደው ራሱ ድርጅቱ መሆን አለበት ። ሰለሆነም የኢህአዴግ ድርጅት በህግ መጠየቅ አለበት ። የኢትዮጵያ ህዝብ ፍትህ ማግኘት አለበት ። የኢህአዴግ የፖለቲካ ድርጅት በይቅርታ መታለፍ ያለበት መስሎ አይታየኝም ። ወንጀለኞች የተፈፀሙት በኢህአዴግ የፖለቲካ ድርጅት ክልል ውስጥ በመሆናቸው ድርጅቱ ሀላፊነት መውሰድ ተገቢ ይመስለኛል ። የታጋይ ጌታቸው አሰፋ ጉዳይም በዚህ ማዕቀፍ ሥር መታየት አለበት እንጂ በተናጠል ግለሰቦች በመቅጣት የሚለወጥ አልያም የሚመጣ የፍትህ ልዕልና የለም ።

   

   

 

Back to Front Page