Back to Front Page

ዘር ከሰውነት በላይ ሲውል ክፍል አንድ

ዘር ከሰውነት በላይ ሲውል

 

ክፍል አንድ

 

በዳንኤል ብ. ተክሉ

danielekfta74@gmail.com

ቶሮንቶ ካናዳ

12-13-19

 

እግዚአብሄር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ፣ ከዚያም ሌሎች ነገሮችን፣ ከዚያም አዳምን ብሎም ሄዋንን ወዘተ እያለ የሚያትተው የዘፍጥረት ትረካ ላይ ተመስርቼ ለፈጣሪ ስራ በዋጋው ቀዳሚው ሰው እንደሆነ ሲገባኝ ያቺ የኔዋ ኢትዮጵያ ታዲያ ለምንድነው ከሰው በፊት ዘርን ለማስቀደም የፈለገቺው በማለት ሳስብ ልቤ በሃዘን ይሰበራል።

በመጀመሪያ እኔ ተወልጄ ባደግኩበት አዲስ አበባ ልጆች ሆነን ከሁሉም ልጆች ጋር አብረን እንጫወታለ፣ አብረን እንማራለን አስፈላጊ ሲሆንም እንጋጫለን። የግጭታችን ምንጭ በምንም መልኩ ከልጅነት ስህተቶች ውጭ ዘር የሚባል ነገር ሊነሳ የማይችል ክስተት ነበረ።

በዝምድና በሰፈር ልጅነት፣ በቅርርብ ወዘተ ሰዎች አድሏዊ ቢሆኑና ላንዱ ቢወግኑ ምንም ማለት አይደለም፡ ደግሞም የተፈጥሮ ህግ ባይሆንም ስር የሰደደ ሰውኛ ባህሪይ ነው። መጥፎ የሚሆነው አሁን ባገራችን እንዳለው ሁሉም ነገር ከዘር ጋር በማያያዝ ማለቂያ ወደሌለው ግጭትና ሁከት መግባት ነው።

Videos From Around The World

የትኛው ሰይጣን እንዳመጣውና በየትኛው ዘመን የሁሉም ሰው አዕምሮ እንደተቆጣጠረ ለማወቅ ሰፊ ጥናት የሚጠይቅ ቢሆንም ከልሂቆቹና ለጥቅም ከሚሮጡት ፖለቲከኞች ባልተናነሰ መልኩ ባሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያውያን በዘር አስተሳሰብ ተበክለናል ቢባል የተጋነነ አይሆንም።

አንድ አስተሳሰብ ከመነሻው ተመርምሮና በህገ ልቦናም ሆነ በተጻፈ ህግ ትክክል አለመሆኑን በመገንዘብ አፋጣኝ እርምት ሲወሰድበት ባጭሩ ቀጭጮና ተከታይ አጥቶ ሊከስም ይችላል። አንድ የተንሻፈፈ አስተሳሰብ ህዝብን ወደ ብርሃን ይመራሉ ተብለው ተስፋ ከተጣለባቸው መሪዎችና ልሂቃን ሲመጣ ግን ማን ደፍሮ ሊሞግተውና ሊያስቆመው ይችላል? የሃገራችን በዘር ላይ የተመሰረተ እንከንም እንደዚሁ ከመሪዎችና ከልሂቃን ልቦና የሚመነጭና የሚፈስ ስለሆነ ሃገራችን ልትወጣው ወደማትችል አዘቅት ይዟት እየገባ መሆኑን ለማመን የፖለቲካ ተንታኝ መሆንን አይጠይቅም።

አሁን በሃገራችን ሁሉም ሰው በሰውነቱ ሳይሆን በዘሩ እንዲያስብ የሚገደድበት አደገኛ ሁኔታ ተፈጥሯል። ዘረኝነት ከአንድ ጥቅል መለያ የሚነሳና በዚያው የሚያበቃ ቢሆን ኖሮ መልካም ነበር። ይሁን እንጂ ዘረኝነት ሰይጣናዊና ስጋዊ አመለካከት ላይ የተመሰረተ ስለሆነ ለተነሳው ጥያቄ መልስ ቢሰጥ እንኳ እፎይ ብሎ በደረሰበት የሚያበቃ ጉዳይ አይደለም። ይህንን አባባል በምሳሌ ለማስረዳት የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ በጣም አመቺ ነው። ለምሳሌ የትግራይ ህዝብ የማንነት ጥያቄ ትግራይን ነጻ በማውጣት የሚያበቃ ቢሆን ኖሮ ይህንኑ ካለመመለስ ጋር ተያይዞ ሊደርስ ከሚችል አደጋ አንጻር ሲታይ መልካም ነበር። ይሁን እንጂ በትግራይ ውስጥም ሌሎች እንደ የራያ፣ የወልቃይት፣ የኢሮብ እንዲሁም የእንደርታና የኩናማ ጥያቄዎች መነሳታቸው የማይቀር ነው። የኦሮሞ ጉዳይ ሲነሳ፣ የቦረናው፣ የሸዋን ኦሮሞ እንደ አማራ የሚያይበት፣ የወለጋው ኦሮሞ የሃረሩን እንከን የሚያወጣበት ወዘተ አስተሳሰቦች ሞልተዋል። የአማራውም ሆነ የሌላው ከዚህ የተለየ ነገር የለውም። ወሎ ሲፋቅ ኦሮሞ ነው ከሚሉ ጥቂት አማሮች ባሻገር በጎንደርና በጎጃም መካከል እንኳ ምን ያህል ሰፊ የአመለካከትና የአስተሳሰብ ልዩነት እንዳለ የሚያውቀው ያውቀዋል።

ከላይ በምሳሌ ያቀረብኩት በየትኛውም ዘረኛ ህዝብ ላይ ሊፈጠር የሚችል ክስተት እንጂ የኛ ህዝብ ላይ ብቻ የሚፈጠር አይደለም። ዘረኝነት እጅግ በጣም ጠባብ ከሆነና ለዓለም ያለንን ዕይታ በማበላሸት ህሊናችንን የሚገዛ የተፈጥሮ ህግን የሚጣረስ አስተሳሰብ ስለሆነ መቅረትና ሰውን በሰውነቱ በመመዘን ላይ ብቻ የተመሰረተ ስርዓትና አስተሳሰብ ለማንገስ ዘረኝነትን ካለማባበል በቀጥታ ልንታገለው የሚገባ የዚህ ዘመን እርግማን ነው።

ዓለማችን አሁን እንዳለንበት ያሉ በርካታ የርግማን አስተሳሰቦችን አሳልፋለች ወደፊትም የሽረት ሽረት ህግን ተከትሎ ብዙ ፈተናዎች እንደሚጋረጡብን የታወቀ ነው። ቀደም ሲል ኮሎኒያሊዝምና የመንግስታት ፉክክር ለሚሊዮኖች ህይወት መጥፋት ምክንያት ሆኖ በኋላ ዓለም ተጸይፎ እንስኪያወግዘው ድረስ እጅግ በጣም ከፍተኛ የሆነ ኪሳራ አድርሶብናል። በመቀጠል ሁለተኛ የዓለም ጦርነትን ተከትሎ በጀርመን የተነሳው ጠባብነትና ዘረኝነት መልካም የሆኑና ምንም ጥፋት ያልሰሩ ከስድስት ሚሊዮን በላይ የአይሁድ እምነት ተከታዮችን አሳጥቶናል። በመቀጠል በካርል ማርክስና በደቀ መዝሙሩ ፍሬድሪክ ኤንግልስ እንዲሁም በቭላድሚር ኢሊች ሌኒን አማካኝነት የተነሳው የኮሙኒዝም አስተሳሰብ ዓለምን ለሁለት ከፍሎ እንደጠላት እርስ በርስ ሲያዋጋንና ሲያስተላልቀን ቆይቶ በኋላ በታላቋ ሶቪየት ህብረት መፍረስ ምክንያት ከምድረ ገጽ እንዳልነበረ ሆኖ ጠፋ። ታሪክ ሰሪ ሰፊው ህዝብ ነው የሚለው አባባል እንዳለ ሆኖ አንዳንዴ የግለሰቦች ሚናም ታላቅ ነገር በማምጣት በኩል የማይናቅ አስተዋጾኦ አለው። የኮሙኒስት ፓርቲው ይሁንታ ቢኖረውም ባይኖረውም የወቅቱ የሶቪየት ህብረት ፕረዚደንት ሚኻኤል ጎርቫቼቭ በግላቸው ኮሙኒዝምን ለመናድ የመጀመሪያውን እርምጃ በመራመድ በኩል የማይናቅ ተግባር ፈጽመዋል።

በመቀጠልም በመካከለኛው ምስራቅና በባልካን ሃገሮች የታየው ዘር፣ ሃይማኖትና የፖለቲካ አስተሳሰብ ላይ የተመሰረተ መከፋፈል ሃገራትን በታትኗል፣ ንጹሃንን ለሞት፣ ለስደትና ለችግር ዳርጓል። በሩዋንዳና በኮንጎ የደረሰው የዘር ጭፍጨፋም እንደዚሁ የቅርብ ቀን ትዝታችን ነው። የሚያሳዝነው ግን እኛ ኢትዮጵያውያን ከሌሎች ስህተት ለመማር አለመቻላችን ነው። ከነሱ ውድቀት ብንማር ኖሮ አሁን ሃገራችንን ወደተሻለ መንገድ ከመውሰድ ይልቅ በዘረኝነት ላይ ተመስርተን እርስ በርሳችን አንተላለቅም ነበር።

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አሕመድ ወደ ስልጣን ሲመጡ የተናገሩትና በተለይም የሳቸው የቅርብ ሰው ይባሉ የነበሩት አቶ ለማ መገርሳ በባህር ዳር ያደረጉት ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው የሚለው ንግግር ስሰማ በልቤ ውስጥ ከፍተኛ ደስታና ተስፋ ተፈጥሮ ነበር። ይሁን እንጂ እኚህ ጠቅላይ ሚኒስትርና አሁን የመከላከያ ሚኒትር የሆኑት አቶ ለማ መገርሳ በአማርኛና በኦሮምኛ ሲያወሩ የተለያየ መልዕክት ያለው ንግግር እንደሚያሰሙ ሳውቅ ደግሞ ተስፋ ቆርጫለሁ። በጨፌ ኦሮሚያ ኦሮሞ ለሆኑ ሰዎች ብቻ ስለ ኦሮሞ ህዝብ ታላቅነትና ስለሌሎች ህዝቦች በደለኝነት እያወሩ በአማርኛ ሲሆን ግን ርካሽ ተወዳጅነትን ለማግኘትና ህዝቡንም ለማዘናጋት የማይጨበጥና የማይዳሰስ ተስፋ እየሰጡ ሃገራችንን ወደ ጨለማ እየመሯት እንደሆነ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ የሚገነዘበው ይመስለኛል።

የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር በውጭ ሃገርና በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ በኢትዮጵያ ፍጹም ሰላምና ዲሞክራሲ ያለ ለማስለሰል እያደረጉት ያለ የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ ጊዜው ደርሶ እንስኪጋለጥ ድረስ በርካታ የውጭ መንግስታትን ጭምር በማሳሳት ላይ ይገኛል። ይህ ከታሪክ አንጻር ሲታይ የሚገርም አይደለም። ሁልጊዚ ህዝበኛ መሪዎች ወደ ስልጣን ሲመጡ የሌለ ታሪክና ተስፋን የሚያጭር ንግግር በመናገር ህዝቡ ላጭር ጊዜ ቢያስፈነድቁትም ከጊዜ በኋላ ግን የራሳቸውን የስልጣን መዋቅር በማስተካከል ህዝቡ ላይ ከፍተኛ በደል እንደሚፈጽሙ ከነሳዳም ሁሴን፣ ከነፊደል ካስትሮ፣ ከነሙዓመር ቓዛፊ፣ ከነ ሁስኒ ሙባረክ ከነ አውጉስቶ ፒኖቼ ወዘተ መማር ይቻላል። የአሁኑ የዶክተር ዓቢይ አሕመድ ድለላም ስልጣናቸውን ካመቻቹ በኋላ ምን እንደሚሆን አብረን የምናየው ይሆናል። እንኳንስ በተመቻቸ ሁኔታ ላይ ደርሰው አሁንም ምን እያደረጉ እንዳለ የኢትዮጵያ ህዝብ ያውቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለህዝብ ክብር የሌላቸውና የህግን የበላይነት የማያከብሩ መሆናቸው ባለፉት አንድ ዓመት ተኩል ውስጥ በጥሩ ሁኔታ ታዝበናል። እሳቸውና ቡድናቸውን ወደ ስልጣን ለማምጣት በኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶችና የውጭ ሃይሎች ይደገፋሉ ተብለው የሚታሙት ቄሮና ፋኖ የተባሉ ቡድኖች እሳቸው ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ሰላማዊ ሰዎችን እያስፈራሩ፣ እየዘረፉ፣ ሴቶችን እየደፈሩና እየገደሉ ሃገራችን መንግስት የሌላት እስክትመስል ድረስ በጎሳ ግጭትና በቀላሉ መቆጣጠር በሚቻሉ ግጭቶች ሳቢያ ከሶስት ሚሊዮን በላይ ዜጎች ከቀያቸው ተፈናቅለው በየበረሃው ሲበተኑ ዓቢይ አሕመድ ችግሩ መኖሩን ለማመን እንኳ አልፈለጉም። ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕና ሌሎች ሃገር በቀል የዜና ማዕከሎች ችግሩን ለዓለም ህዝብ ግልጽ እስከሚያደርጉት ድረስ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በየቦታው እየዞሩ ፎቶ ሲነሱና ስልጣናቸውን ሲያደላድሉ ይውላሉ። በጌዶኦ ብሄረሰቦች ላይ በኦሮሞ ጉጂዎች እንዲሁም በትግራይና ሌሎች ብሄሮች ተወላጆች ላይ የተፈጸመው የዘር ጭፍጨፋ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንኳንስ በህግ ሊቆታጠሩት በማንኛውም ሚዲያ ቀርበው ድርጊቱን ለማውገዝና ለመተቸት እንኳ ፍላጎት የላቸውም። ትናንሽ ህጻናት ሳይቀሩ አንገታቸው በቢላዋ እየታረዱ የሞቱበት ሁኔታ ዓለም እንዳያውቀው ከመሸፋፈን በስተቀር አጥፊን ወደ ህግ የማቅረብ ፍላጎትም ሆነ እንቅስቃሴ አልታየባቸውም። ምክንያቱም እሳቸው የማህበረሰብ መሰረቴ ነው የሚሉት የኦሮሞ ተወላጅ የሆነ ሰው ወንጀልም ቢፈጽም ሊጠይቁትና ሊወቅሱት አይፈልጉም። ምክንያቱም ይህንን ሲያደርጉ አልታዩም።

በቡራዩ እሳቸው ከተቀመጡበት የአራት ኪሎ ቤተመንግስት ሃያ ኪሎ ሜትር እንኳ ባልሞላ ርቀት ላይ የኦሮሞ ቄሮዎች በሰላማዊ ህዝብ ላይ በዘር ላይ የተመረተ ጭፍጨፋ ሲያካሄዱ ዶክተር ዓቢይ ምንም ያሉት ነገር የለም። በሻሸመኔ ሰላማዊ መንገደኛ ወጣት በቂሮዎች ተደብድቦና ተገድሎ በኤሌትክትሪክ ፖል ላይ ቁልቁል ሲሰቀል የመንግስት ፖሊስ ሳይቀር ቆሞ እንደ ድራማ ሲመለከት የሚያሳይ የቪዲዮ ፉቴጅ በመላው ኢንተርኔት ተለቆ በህዝቡ ላይ ከፍተኛ ሃዘንና ቁጣ ቢፈጥርም ዶክተር ዓቢይ ግን ስልጣናቸውን ለማመቻቸት ብቻ ላይ ታች ከመኳተን ውጭ አንዳችም የፈጸሙት ነገር የለም።

ባጠቃላይ በሃገራችን በሰሜን፣ በምስራቅ በምዕራብና በደቡብ ምንም የተረጋጋ ሁኔታ ሳይኖር በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ዓመጽና የዘር ግጭት ነግሶ ተማሪዎች ለትምህርት ከክልላቸው ውጭ ወደ ሌላ ክልል መሄድ ሲፈሩ ዶክተር ዓቢይ ግን ካለምንም ሃፍረት በዓለም መድረክ ላይ ቀርበው ኖቬል ሲሸለሙ በማየቴ የሳቸው አስመሳይነት ብቻ ሳይሆን የሸላሚዎቹ ግብዝነትም በማየቴ ከፍተኛ ሃዘን ተሰምቶኛል። ሽልማት ለሃገራችን ቢሆንም በሃሰተኛ አመክንዮ ላይ ተመስርቶ የሚሰጥ ሽልማት ግን ሊያኮራንም ሆነ ሊያስደስተን አይችልም። ማንም ሰው ከአዲስ አበባ ወደ ደብረዘይት እንኳ በሰላም ለመሄድ የማይችልበት ስርዓት አልበኝነት ያነገሰን ሰው የኖቬል የሰላም ሽልማት ተሸላሚ ብሎ ማቅረብ በራሱ ነገ ሸላሚዎቹን ለከፍተኛ ሃፍረት የሚያጋልጥ ተግባር እንደሆነ ይታያል። ለነገሩ ኖቬል በግልሰቦች መልካም ፈቃድ የሚሰጥ ውስጡ ፖለቲካዊ ይዞታ ያለው የሃሰት ሽልማት እንደሆነ በተለያዩ ጊዜያት ታይቷል። ለምሳሌ በ1939 ዓ/ም ኤሪክ ብራንት የተባሉ የስዊድን ፓርላማ አባል ጨፍጫፊውና የዓለማችን ጨካኝ መሪ የነበረውን አዶልፍ ሂትለርን የሰላም ኖቬል ተሸላሚ እጩ አድርገው አቅርበዉት ነበር። በ1935 ቤኒቶ ሙሶሊኒ እንዲሁም በቅርቡ የበርማዋ አንግ ሳን ሱኪም እንደዚሁ የዚህ ሸላሚ ድርጅት ደካማነትን ያሳያል።

አሁን ኢትዮጵያ በጥሩ ሁኔታ ላይ ያለች የሚመስላቸው በርካታ የውጭ ሃገር ዜጎች አሉ። ምክንያቱም ዓቢይ አሕመድና ደጋፊዎቻቸው የሆኑ በርካታ የዓረብ ሃገር መሪዎች የሃሰት ፕሮፖጋንዳ በመንዛት ግዚያዊ የኢንፎርሜሽን የበላይነትን ይዘዋል።

ሰላም እንሰንብት

ቀጣዩ በክፍል ሁለት እንመለስበታለን

 

Back to Front Page