Back to Front Page

በዘር የተደራጁ ፓርቲዎች እጣ ፋንታ አክቲቪስት መሆን ነው

(ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)

ሰሞኑን በሀገራችን የፖለቲካ ምህዳር ላይ ጎላ ብለው ካየናቸው ጉዳዮች አንዱ ኋላቀር የፖለቲካ ባህላችን የወለዳቸው ነባር ፓርቲዎች እንደየ ርዕዮተ-ዓለማቸው እየተሰባሰቡ መሆኑን ነው፡፡ የዚች የጽሁፌ ትኩረትም በዚሁ ዙሪያ የሚያጠነጥን ይሆናል፡፡ በቅድሚያ በዚህ መጣጥፍ የተካተቱትን ዋና ዋና ጉዳዮች ላስተዋውቅ፡፡ ከምርጫ ቦርድ በተገኘ መረጃ መሰረት በሀገራችን 108 ገደማ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሉ፡፡ ለመሆኑ ፖለቲካና ፓርቲ ማለት ምን ማለት ነው? ይህን ያህል ፓርቲ የተደራጀበት ምክንያት ምንድነው? አስፈላጊስ ነው? የፓርቲዎች ማህበራዊ መሰረት ምንድነው? የሌሎች ሀገሮች የምርጫ ድምፅ መነሻ (electoral threshold) ምን ይመስላል? ለምን ይጠቅማል? በሀገራችን የፓርቲ ፖለቲካ መቼ ተጀመረ? ለሚሉት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ጥረት ይደረጋል፡፡

Videos From Around The World

እንደ መንደርደሪያ

የሰው ልጆች ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተሳትፎ ከማድረጋቸው አስቀድሞ ለመኖር ሦስት ነገሮች ሊሟሉላቸው እንደሚገባ ይታመናል፡፡ እነዚህም ሦስት ነገሮች ምግብ፣ አልባሳትና መጠለያ ናቸው፡፡ በፖለቲካ ድርጅት ስር ተሰባስቦ መብትና ጥቅምን ለማስጠበቅ መታገልም ይሁን ሌሎች ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ተግባራትን ማከናወን፤ ከላይ የተጠቀሱት ሦስት መሰረታዊ ፍላጎቶች ነፀብራቆች መሆናቸውን በመስኩ ምርምር ያካሄዱ ምሁራን ያስረዳሉ፡፡ አበው እዬዬም ሲዳላ ነው እንዲሉ፤ የሰው ልጅ ካልጎረሰና ካልለበሰ እንኳን ቁም ነገር ሊሰራ እዬዬ ብሎ ማልቀስም አይቻለውም፡፡

ፖለቲከኞቻችን በቀን ሦስት ጊዜ ጠግበን እንድንበላ ቢመኙልንም ምኞቱ ሳይሳካ 27 ዓመታት አለፉ፡፡ አማርጠን መልበስ አልታደልንም፡፡ የወፍን ያህል ለጎናችን ማሳረፊያ የሚሆን ጎጆ አልቀለስንም፡፡ ዳቦ አሮብን፣ እራፊ ጨርቅ ቸግሮን፣ በረንዳ አዳሪነት እጣፈንታችን የሆንን ዜጎች ቁጥር ጥቂት የሚሰኝ አይደለም፡፡ እናም ይህንን ጉድለታችንን እናሟላላችኋለን የሚሉ ፖለቲከኞቻችን በምርጫ ወቅት ድምጻችንን ስለሚፈልጉት እንደ ደላው ሰው የፖለቲካ ተሳትፎ ማድረጋችንና አውራ ፓርቲ መምረጣችን ይስተዋላል፡፡ እንደ ዜጋ ውሳኔ ስንሰጥ ይታያል፡፡ በበኩሌ፤ እንዲህ ያለው ተሳትፎአችን በደመ-ነፍስ የምናደርገው እንጂ አስበን፣ አውጥተንና አውርደን የምናከናውነው መስሎ አይታየኝም፡፡ እንኳን ተራው ሕዝብ በርካታዎቹ ፖለቲከኞቻችን ጭምር ምን እያደረጉ እንደሆነ በቅጡ የተገነዘቡት አይመስለኝም፡፡ ያም በመሆኑ ፈረሱን ከጋሪው ማስቀደም ብቻ ሳይሆን፤ ጋሪውን እየጎተቱ፣ ፈረሱን እየሳቡ ሲባዝኑ ይስተዋላሉ፡፡ ባለፉት ዓመታት ማህበራዊ መሰረቱን ለይቶ ያላስቀመጠ ፓርቲ በምርጫ ለመወዳደር አደባባይ መውጣቱ ይህንን እውነት ግልጽ አድርጎ የሚያሳይ ይመስለኛል፡፡

እዚህ ላይ ለመሆኑ ማህበራዊ መሰረት ማለት ምን ማለት ነው? የሚል ጥያቄ ይነሳ ይሆናል፡፡ ለዚህ ጥያቄ ምላሽ ይሆን ዘንድ ከዚህ ቀደም የጣፍኳትን ሃሳብ መልሼ ልድገማት! ስለ የፖለቲካ ፓርቲዎች ማህበራዊ መሰረት (Social Base) ምንነት ከመግለጼ በፊት ግን ስለ ፖለቲካና ስለ ፓርቲዎች በአጭሩ ጠቅሼ ማለፍን መረጥኩ - እሱን ላስቀድም!

የፖለቲካና የፓርቲ ትርጉም

ፖለቲካ የሚለው ቃል ፖለቲከስ (Politicus) ከሚለው የላቲን ቃል የተገኘ ሲሆን፤ ፖለቲከስ የሚለው ቃል ደግሞ ፖሊስ (Polis) ከሚለው የግሪክ ቃል የተገኘ መሆኑን ዕድሜ ጠገብ ሰነዶች ያስረዳሉ፡፡ ፖሊስ የሚለው ቃል ትርጉም ደግሞ ራሱን የቻለ ማህበረሰብ፣ ራሱን የሚያስተዳድር ከተማ ወይም አገር ማለት ነው ይላሉ ቀደምት የፖለቲካ ሣይንስ ልሒቃን፡፡

አንዳንዶች ደግሞ ፖለቲካ ማለት የመንግስትና የህዝብ የግንኙነት ሂደት ነው ይላሉ፡፡ ፖለቲካ ማለት ሰዎች በእለት ተእለት እንቅስቃሴአቸው የሚያከናውኗቸውን ተግባራት ለመምራትና ለማስተዳደር ስልጣንን መሰረት በማድረግ (በግድም በውድም እንዲፈጸም) የሚሰጥ ውሳኔ ነው የሚሉ አስተያየት ሰጪዎችም አሉ፡፡ ከላይ የተጠቀሱት ሃሳቦች ያን ያህል የሰፋ ልዩነት ያላቸው አይመስለኝም፡፡ በአንድ የፖለቲካ ስርዓት ውስጥ አገር፣ ሕዝብ፣ መንግስትና የመወሰን ስልጣን መኖራቸው የግድ ነው፡፡ እዚህ ላይ መነሳት የሚገባው ጥያቄ የመወሰን ስልጣን የት፣ በማን ቁጥጥር ስር ነው ያለው? የሚለው ነው፡፡

የመወሰን ስልጣን በእያንዳንዱ ዜጋ እጅ ተበታትኖ ነው የሚገኘው፡፡ ይህ የተበታተነ የመወሰን ስልጣን ተሰባስቦ አንድ ቦታ ላይ ካልተቀመጠ በየእለቱ የሚከናወኑ ሀገራዊ የጋራ ጉዳዮችን ለመፈጸምም ሆነ ለማስፈጸም አስቸጋሪ ነው፡፡ የሀገሪቱ ዜጎች በየእለቱ እየተሰባሰቡ በእያንዳንዱ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ውሳኔ ይስጡ ቢባል የማይቻል ነገር ነው፡፡ (አንዳንድ የፌስቡክ ሊቃውንት የሚፈልጉት ግን እንዲህ እንዲደረግ ነው፡፡ ዶ/ር ዓብይ የሚናገራትን ቃል ጭምር እነሱን እንዲያስፈቅድ የሚፈልጉ አክቲቪስቶች ጥቂት አይደሉም) መንግስት የሚባለው አካል በሕዝብ ተመርጦ የእለት ከእለት ሥራዎችን እንዲያከናውን የሚደረገው በያንዳንዱ ጉዳይ ላይ በህዝብ ስም ውሳኔ እንዲወስን ነው፡፡ በሕዝብ ተመርጦ በሀገርና በሕዝብ ላይ የመወሰን መንግስታዊ ስልጣንን ለማግኘት ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያስፈልጋሉ፡፡

ፓርቲ የሚለው ቃል ፓርት (Part) ከሚለው የእንግሊዝኛ ቃል የተገኘ ሲሆን፤ ትርጉሙም የተወሰነው፣ ከፊሉ፣ ጥቂቱ፣ የህብረተሰብ ክፍል ተመሳሳይ ዓላማ ለማራመድ የሚሰባሰብበት የፖለቲካ ማህበር ነው በዚህ ትርጉም መሰረት፤ ፓርቲ የሚቋቋመው የአባላቱንና የደጋፊዎቹን ብቻ ሳይሆን፤ በዋናነት የተወሰኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መብትና ጥቅሞችን ለማስጠበቅ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ይህም መብትና ጥቅም የሚጠበቀው ፓርቲው የብዙሃኑን ይሁንታ አግኝቶ ስልጣን ሲይዝና በስልጣኑም አማካይነት ፖሊሲዎችን፣ ሕጎችንና ደንቦችን አውጥቶ ሥራ ላይ ሲያውል ነው፡፡

የፓርቲዎች ማህበራዊ መሰረት

አንድ ፓርቲ የሚቋቋምበት መሰረታዊ ዓላማ ይኖረዋል፡፡ በዚያ ዓላማውም መሰረት መብትና ጥቅማችሁን አስጠብቅላችኋለሁ ለሚላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ወገንተኛ ነው፡፡ ይህም በመሆኑ አንድ ፓርቲ በአንድ ሀገር ላሉ ዜጎች ሁሉ በእኩልና በተመሳሳይ ደረጃ መብትና ጥቅማቸውን ሊያስጠብቅ አይችልም፡፡ ስያሜውም የሚያመለክተው ለተወሰኑት የህብረተሰብ ክፍሎች ጥብቅ የሚቆምና፣ ውግንና ያለው መሆኑን ነው፡፡ ለምሣሌ፡- የወዛደሩ ፓርቲ በዋናነት ለወዛደሩ መብትና ጥቅም የቆመ ነው፡፡ የቡርዧው ፓርቲ የታላላቅ ከበርቴዎችን ጥቅም አስጠባቂ ነው፣ ወዘተረፈ፡፡

የአንድ ፓርቲ ማህበራዊ መሰረትም በዋናነት በማወጣቸው ፖሊሲዎች መብትና ጥቅማችሁን አስጠብቅላችኋለሁ የሚላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ናቸው፡፡ እነዚህም የህብረተሰብ ክፍሎች ለዚያ ፓርቲ አባል በመሆን፣ የገንዘብ መዋጮና የቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ፣ በስብሰባዎች ላይ በመገኘትና በማስተባበር፣ በምርጫ ወቅት ቅስቀሳ በማድረግ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋሉ፡፡ እዚህ ላይ መታወቅ የሚገባው ነገር፣ አንድ ፓርቲ የተወሰኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ጥቅም ያስጠብቃል፣ ውግንና አለው፣ ማለት እግረ መንገዱን የሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችን ጥቅሞች ሊጫን ይችላል ማለት ነው፡፡

አባባሌን በምሣሌ ላስረዳ፡፡ የፕሬዝዳንት ኦባማ ዴሞክራቲክ ፓርቲ ስልጣን የያዘው በባለሃብቶች ላይ ከፍ ያለ ግብርና ታክስ በመጣልና ገንዘብ በመሰብሰብ ለዝቅተኛው ብዙሃን ህብረተሰብ የሚጠቅም የትምህርትና የጤና ፖሊሲ አወጣለሁ በማለቱ ነው፡፡ ኦባማ እንዲህ ያለ ፖሊሲ በመከተላቸው ዝቅተኛውን የህብረተሰብ ክፍል ሲጠቅሙ የአገሪቱ ከበርቴዎች ገቢ ግን በሚጣለው ታክስ ምክንያት ይቀንሳል ማለት ነው፡፡

የእኛን ሀገር ሁኔታ ስናይ፤ ኢህአዴግ ማህበራዊ መሰረቴ የገጠሩ አርሶ አደር ነው ይላል፡፡ የአሁኑን አላውቅም እንጂ እኔ አመራር በነበርኩበት ዘመን ኢዴፓ መካከለኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች፣ ወጣቶችና ሴቶች በማለት ማህበራዊ መሰረቷን ማስቀመጧን አስታውሳለሁ፡፡ አሁን በመቋቋምና በመዋሃድ ላይ ያሉ ፓርቲዎች (እነ ኢዜማ) ማህበራዊ መሰረታቸው የትኛው የህብረተሰብ ክፍል ነው? የሚለውን ጥያቄ እንደ ዘበት ጣል አድርጌ ማለፍ እወዳለሁ፡፡ ምናልባት ወደፊት የምናየው ይሆናል፡፡

የሆነ ሆኖ ማህበራዊ መሰረቱን ለይቶ፣ ያንን የተለየ የማህበረሰብ ክፍል በማሳመን ወደ ምርጫ ካልተገባ በምርጫ ተወዳዳሪ እንጂ አሸናፊ መሆን ይቻልም፡፡ የሀገራችን ተቃዋሚዎች እንዲያሸንፉ ከማስያስችሏቸው ምክንያቶች አንዱ ይሄ ሁኔታ ይመስለኛልና ከወዲሁ ሊያስቡበትና ሊዘጋጁበት ይገባል፡፡

በሀገራችን የፓርቲ ፖለቲካ መቼ ተጀመረ?

በፊውዳሉ የኢትዮጵያ የአስተዳደር ዘመን ፓርቲ የሚለው ጽንሰ ሃሳብ የሚታሰብ አልነበረም፡፡ በዚያ ወቅት የነበሩት ልዑላንና መኳንንቱ የዘር ሀረግን መሰረት ያደረገ የስልጣን ማስተላለፍ ዘዴን ይከተሉ እንደነበር ይታወቃል፡፡ የስልጣን ተቀናቃኝ ይነሳ የነበረውም እዚያው በዙፋኑ ዙሪያ ባሉ ዘመዳሞች መካከል ነበር፡፡ በርግጥ የአካባቢ ገዢዎችም ለማዕከላዊ መንግስት አንገብርም ብለው ያንገራግሩ ነበር፡፡ እሱም በጉልበት ይጨፈለቃል፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ ያነጋገርኩት አንድ የታሪክ ምሁር በአጠቃላይ እስከ ጣሊያን ወረራ ድረስ የፓርቲ ፖለቲካ በኢትዮጵያ የሚታወቅ አልነበረም፡፡ ከጣሊያን መምጣት ጋር የፓርቲ ፖለቲካ ፍንጭ ታይቷል፡፡ በተለይም በኤርትራ በግልጽ የታወቁ ፓርቲዎች ብቅ ብቅ ብለው ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ የኦሮሞን ጥያቄ ያነሱ ማህበራትም ተፈጥረዋል የሚል አስተያየት ሰጥቶኛል፡፡

በአብዮቱ ዋዜማ አካባቢ እነ ኢህአፓና መኢሶን በድብቅም በይፋም የፖለቲካ እንቅስቃሴ ማድረግ መጀመራቸው ይታወቃል፡፡ በአብዮቱ ሂደት በአስተሳብ ላይ የተመሰረቱ ብቻ ሳይሆን ዘርን መሰረት ያደረጉ ነፃ አውጪ ድርጅቶች ጭምር የብሔር ጥያቄን አንግበው መደራጀታቸውም ታይቷል፡፡

ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ሲመጣ በብሔር መደራጀት የህግ ድጋፍና እውቅና ተሰጠው፡፡ በዚህም ምክንያት የብሄር ድርጅቶች እንደ አሸን ፈሉ፡፡ በዚሁ ወቅት ህብረ ብሄራዊ ቅርጽ የያዙ ፓርቲዎች የተደራጁ ቢሆንም ብዙዎቹ ምን ዓይነት ርዕዮተ ዓለም እንደሚከተሉ፣ ማህበራዊ መሰረታቸው ምን እንደሆነ እና ኢህአዴግን ከመክሰስና ከመውቀስ ውጪ ከኢህአዴግ የሚለዩበትን አማራጭ ፖሊሲያቸውን በግልጽ ያስቀመጡበት ሁኔታ አልነበረም፡፡ በዚህ ምክንያት በኢህአዴግ በኩል ተቃዋሚዎች አማራጭ ፖሊሲ የላቸውም የሚል ወቀሳ ደጋግሞ ያቀርብባቸው ነበር፡፡

በርግጥም ባለፉት 26 ዓመታት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ያደርጉት የነበረው ትግል የፖሊሲ ፉክክር ሳይሆን የኢህአዴግን ድክመቶች የማጋለጥ፣ የመንግስትን የአፈጻጸም እጥረቶች የመተቸት፣ የፖለቲካ ምህዳሩ ይስፋ የሚል አቤቱታና ዓባላቶቼ ታሰሩ የሚል ክስ ነበር፡፡ ዶ/ር ዓብይ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ እነዚህ ክሶች ቀርተዋል፡፡ ምህዳሩም ሰፍቷል፡፡ ይህም በመሆኑ ፓርቲዎች ወደ ራሳቸው በማተኮር አደረጃጀታቸውን የመፈተሽ፣ በርዕዮተ ዓለም ማእቀፍ ውስጥ የመሰባሰብና አደረጃጀታቸውን በማስተካከል ሥራ መጠመዳቸው ይስተዋላል፡፡ ባለፈው ሳምንት የተመሰረተው ኢዜማ የተሰኘው ፓርቲም የዚሁ የአዲስ አደረጃጀት ውጤት ነው፡፡

ፓርቲና የህዝብ ቁጥር

በዚህ ወቅት የሀገሪቱ የህዝብ ቁጥር ከመቶ ሚሊዮን በላይ የደረሰ ሲሆን የፓርቲዎቹ ቁጥርም 108 ደርሷል፡፡ በዚህም መሰረት የህዝብና የፓርቲው ምጣኔ (Ratio) አንድ ፓርቲ ለአንድ ሚሊዮን ህዝብ እንደ ማለት ነው፡፡ ጎረቤት ሀገር ኬንያ የህዝቧ ቁጥር 53 ሚሊዮን ሲሆን፤ በኬንያ ያሉ ፓርቲዎች ብዛት ደግሞ 50 ነው፡፡ ይህም ከኢትዮጵያ ጋር ተመሳሳይ የፓርቲና የህዝብ ምጣኔ ያላት መሆኑን ያሳያል፡፡

የፓርቲዎች ቁጥር መብዛት የአስተሳሰብ መበተንን ያሳያል፡፡ የአስተሳሰብ መበተን ደግሞ ለህዝብም ለፓርቲዎችም አይጠቅምም፡፡ በመደራደር ላይ የተመሰረተ የፓርቲ ፖለቲካ ባህል ለሌለው እንደ ኢትዮጵያ ላለ ሀገር የፓርቲዎች መብዛት የተረጋጋ መንግስትን ለመመስረት አያስችልም፡፡ በለይም ፓርላማዊ የፖለቲካ ስርዓት በሚከተሉ ሀገራት ፓርቲዎች በተጣሉ ቁጥር በድርድር የተቋቋመው መንግስት ስለሚበተን የተረጋጋ መንግስት ሊኖር አይችልም፡፡ ጣሊያን በዚህ የታወቀች ናት፡፡ በ50 ዓመታት ከ15 በላይ መንግስት ቀይራለች፡፡ ይሁን እንጂ የጣሊያን ፓርቲዎች የመደራደርና በዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ የመኖር የፖለቲካ ባህልን ያዳበሩ በመሆኑና ፓርቲዎቹም በዘር ሳይሆን በአስተሳሰብ የተደራጁ በመሆኑ የከፋ ችግር አልገጠማቸውም፡፡

የሀገራችን የፓርቲ ማቋቋሚያ አዋጅ ፓርቲዎች በቀላሉ ለመደራጀት እንዲችሉ እድል የሚሰጥ ነው፡፡ 1 ሺህ 500 የድጋፍ ፊርማ ማሰባሰብ የቻሉ ስብስቦች ፓርቲ ማቋቋም ይችላሉ፡፡ ይህ ህግ የመደራጀት መብትን ከመጠበቅና ከማስከበር አኳያ ጠቃሚ ነው ቢባልም፣ በፓርቲዎች ውስጥ አንጃዎች እንዲፈጠሩ ከማድረጉም በላይ በሀገሪቱ ፓርቲዎች እንደ አሸን እንዲፈሉ ምክንያት መሆኑ ይስተዋላል፡፡

በአንድ ፓርቲ ውስጥ ያሉ ሰዎች በሁሉም ጉዳዮች ላይ አንድ ዓይነት አቋምም ሆነ ተመሳሳይ ፍላጎት ሊኖራቸው እንደማይችል ይታመናል፡፡ በዚህም ምክንያት የሃሳብ ልዩነት ሊፈጠር ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜ የውስጥ የሃሳብ ትግል በማድረግ ልዩነትን ማጥበብ ሲቻል (ኢትዮጵያውን እኔ ያልኩት ብቻ መሆን አለበት የሚል ግትር ባህሪ ያለን በመሆኑ) ልዩነት በተፈጠረ ቁጥር ሃሳቡ የተሸነፈበት ወገን አንጃውን ይዞ ይወጣና ካንተ ጋር ምን አጨቃጨቀኝ የራሴን ፓርቲ አቋቁማለሁ ወደሚል አቅጣጫ ይገፋል፡፡ እና መፍትሄው ምንድነው? መፍትሄውማ በምርጫ የተገኘን ድምፅ መሰረት ያደረገ መነሻ ወለል (electoral threshold) ማስቀመጥ ነው፡፡

የምርጫ ድምፅን መሰረት ያደረገ መነሻ (electoral threshold) ምንድነው?

አንዳንድ ሀገሮች እንዲህ ያለውን የፓርቲዎች ልቅ የመደራጀት መንገድ ለመዝጋት የተለያዩ ዘዴዎችን ይከተላሉ፡፡ ለዚህም ትልቁ መሳሪያ ፓርቲዎች በምርጫ ህዝብ የሚሰጣቸውን ድምፅ መሰረት ያደረገ መነሻ ወለል (electoral threshold) አስልተው በጥንካሬ መለኪያነት በመቶኛ ያስቀምጣሉ፡፡ የምጣኔው መቶኛ እንደየሀገሩ የተለያየ ሲሆን የብዙዎቹ ሀገሮች ከ1 10 በመቶ ባለው ውስጥ ነው፡፡

አንዳንድ ምሳሌዎችን እንይ፡፡ በፖላንድ፣ በጀርመንና በኒዊዚላንድ የፕርላማ መቀመጫ ለማግኘት ከመራጩ ህዝብ 5% መነሻ ድምፅ ማግኘት ያስፈልጋል፡፡ በቱርክ 10% ሲሆን በስሎቬኒያ ቀደም 4% ነው፡፡ በኖርዌይ 4% ሲሆን፣ በመላ ሀገሪቱ 12% ድምፅ ያገኘ ፓርቲ በምርጫ ክልል (ወረዳ) ደረጃ ባለ ምክር ቤት መቀመጫ ተካፋይ ይሆናል፡፡ ከአፍሪካ ሩዋንዳና ሞዛምቢክ 5% መነሻ አስቀምጠዋል፡፡

ይህንን ሁኔታ ለማስረዳት የእስራኤልን ሁኔታ ላቅርበው፡፡ የእስራኤል ፓርላማ (ኬነስት) 120 መቀመጫዎች አሉት፡፡ በእስራኤል የምርጫ ወረዳ የሚባል ነገር የለም፡፡ መላ ሀገሪቱ እንደ አንድ የምርጫ ክልል ነው የምትታየው፡፡ እናም ሁሉም ዜጋ ለሚፈልገው ፓርቲ ድምፁን ይሰጣል፡፡ በእስራኤል መነሻ ድምፅ (electoral threshold) 3.25% ነው፡፡ በዚህም መሰረት (በንድፈ ሃሳብ ደረጃ) አንድ ፓርቲ ከመራጩ ህዝብ የአስር በመቶውን (10%) ድምፅ ካገኘ ከመቶ ሃያው መቀመጫ አስራ ሁለቱን ይዛል፡፡ ይሁን እንጂ ሌላ ሊታለፍ የሚገባው መሰናክል አለ፡፡ ይኸውም አንድ ፓርቲ ከአጠቃላዩ መራጭ ከ3.25% ድምፅ በታች ካገኘ በፓርላማ አንድም መቀመጫ አይሰጠውም፡፡ ከመራጩ ህዝብ ከ3.5% ድምፅ ካገኘ ግን አራት መቀመጫ ያገኛል፡፡ እንዲህ ያለው አሰራር ብዙዎቹን ፓርቲዎች የፓርላማ መቀመጫ ስለማያስገኝላቸው በቀጣይ ምርጫ ወይ ከሌላ ፓርቲ ጋር ይዋሃዳሉ ወይ ህዝቡ ሙሉ ለሙሉ ድምፁን ይነፍጋቸውና ይከስማሉ፡፡

በእኛም ሀገር እንዲህ ያለ ገደብና አሰራር ቢኖር በፓርቲዎች መካከል ያለውን የመወያየትና የመደራደር የፖለቲካ ባህልን ያዳብረዋል፡፡ የመቻቻል መንገድን ያጠናክራል፡፡ የፖለቲካ አጀንዳን በቅደም ተከተል የመፍታት አሰራርን ያዳብራል፡፡ ካለበለዚያ የድርድር ፖለቲካ ልምድ የሌለን በመሆኑ ለፓርቲዎች መከፋፈልና ተመሳሳይ ርእዮተ ዓለም የሚያራምዱ ፓርቲዎች በየጊዜው እንዲቀፈቀፉ ምክንያት ይሆናል፡፡

በግርጌ ማስታወሻ መልክ አንድ ጉዳይ አንስቼ ልሰናበት፡፡ የፓርቲዎች ዋነኛና ተቀዳሚ ተግባር በየደረጃው የሚያገለግሉ የሀገር መሪዎችን ማፍራት ነው፡፡ በመሆኑም ሰሞኑን ፓርቲዎች የጀመሩት በርእዮተ ዓለም አቅጣጫ የመሰባሰብ ሁኔታ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡ ፓርቲዎች ጠንካራ ተቋም ሆነው ሲደራጁ ጠንካራ፣ ራዕይ ያላቸው መሪዎችን ማፍራት ይችላሉ፡፡

በኔ እይታ በዚህ ወቅት ያልተመለሰ የብሔር ጥያቄ የለም፡፡ አለ ከተባለም ሀገሪቱ ባላት ህገ መንግስት መሰረት እልባት ማግኘት ይችላል ብየ አስባለሁ፡፡ በመሆኑም በዘመነ ግሎባላይዜሽን በዘር መደራጀት አስፈላጊ አይደለም፡፡ በዘር መደራጀት የዴሞክራሲ ምንጭ ሊሆን ስለማይችል እንዲያውም በህግ መታገድ አለበት የሚል እምነት አለኝ፡፡ በዘር የተደራጁ ፓርቲዎች ለብጥብጥና ለሁከት ምክንያት ከመሆን ውጪ ሀገርና ህዝብ ለመምራት አይመጥኑም፡፡ እንደኔ እንደኔ በዘር የተደራጁ ፓርቲዎች እጣ ፋንታቸው አክቲቪስት መሆን ነው፡፡ ፈርሰው ሀብታቸውን ከሚበትኑ ወደዚያ ቢሸጋገሩ መልካም ነው፡፡ ዴሞክራሲያችን ስር እስኪይዝ ድረስ ከብሔራቸው ጋር ተያይዞ ሊከሰት የሚችልን ችግርም በአክቲቪስትነት ጠንክረው በመስራት ሊመክቱት ይችላሉ ብየ አስባለሁ፡፡

ጸሐፊውን በEmail: ahayder2000@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡


Back to Front Page