Back to Front Page

ከብዕር ወደ ክላሽ ከመሸጋገር ይልቅ የህግ ልዕልና ማስቀደም ይበጃል ።

ብዕር ወደ ክላሽ ከመሸጋገር ይልቅ የህግ ልዕልና ማስቀደም ይበጃል

ልኡል ገብረመድህን (ከአሜሪካ ) 7.4.2019

በኢትዮጵያ ሰኔ 15 ቀን 2011 የፈፀመው ከፍተኛ የመንግስት ሀላፊዎች የመግደል ተግባር መንግስት ስርአተ ፍንቀላ ብሎ የሰየመው በመሆኑ ይሁን አይሁን የበርካታ ኢትዮጵያዊያን መነጋገሪያ ሆኗል መፈንቅለ ሰርአት ሆነም አልሆነም ጉዳዩ በእኔ እምነት የመንግስት ተቋም (ደህንነት ) ድክመት መሆኑ ፈፅሞ አልጠራጠርም መፈንቅለ ስረአት ያህል በእቅድ ሲሰራ የደህንነት መስሪያ ቤት መረጃ አልነበረውም ለማለት አዳጋች ነው እንደ ራሴ እምነት የግድያ ድርጊቱ ከመፈፀሙ አሰቀድሞ መከላከል አልያም ማክሸፍ ይቻል ነበር የሚል ፅኑ እምነት አለኝ የዜጎች ደህንነት የማይከለከል መንግስትና የመንግስት ደህንነት ጥያቄ የሚያስነሳ ጉዳይ ይሆናል

Videos From Around The World

የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሰተዳደር ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር የሻከረ ግኑኝነት እንዲፈጠር እንዲሁም ተደጋጋሚ ማህበራዊና ፖለቲካዊ አለመረጋጋት እንዲከሰቱ አንዱ ምክንያት የመንግሥት ግልፅነት ( Transparency ) መሸርሸር ነው ለፀጥታ መደፍረስ ምክንያት የሆኑ ፀጥታ አደፍራሽ ሀይሎች መንግስት ቢያውቃቸው እንጂ የኢትዮጵያ አያውቅም ። ህዝብ ካላወቀ ደግሞ ከመንግሥት ጋር መተባበር አይችልም ። በመሆኑም ማህበራዊ ችግሮች ከመቀነስ ይልቅ እየተባባሱ የመሄድ አጋጣሚ መፈሩ አይቀርም ። መንግስት ወቅታዊ እንዲሁም በቂ መረጃ ለህዝብ አይሰጥም ። ህዝብ መረጃ የማግኘት መብቱ ሲነፈግ የፀጥታና መረጋጋት ችግር ይስፋፋል ። መንግስት ባለቤት የሌለው አጀንዳ እያናፈሰ የህዝብ ሰላም ያውካል ። በምዕራብ ሆነ በምስራቅ ፣ በሰሜን ሆነ እንዲሁም በደቡብ የአገርና የህዝብ ደህንነት ስጋት ለይቶ ለህዝብ የማሳወቅ የመንግስት ሀላፊነት ነው ። ህዝብ በአገሩ የሚፈፀሙ የፀጥታ ስጋቶች የማወቅ ሙሉ መብት አለው ። ህዝብ ሰለ አገሩ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ይበልጥ ባወቀ ቁጥር ሰላሙን የማስጠበቅ ሀላፊነቱ ይወጣል ።

ጠቅላይ ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ ጀምሮ በለውጥ ሰም የታሰሩ እና የተገደሉ ኢትዮጵያውያን ቁጥር በቀላሉ የሚገመት አይደለም ። በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ከመሬት ይዞታ እንዲሁም የንግድ ስርአትና ዝውውር ጋር በተያያዘ በትግራይ ተወላጆች ላይ የደረሰ እስራትና መንገላታት ተገቢ አልነበረም ። አህያውን ፈርቶ ዳውላው እንደሚባለው መሬት ሲሸጡ ሲለውጡ የነበሩ ባለስልጣናት ተጠያቂ ሳይሆኑ የግለሰቦች ንብረትና ሐብት እንዲታገድ መደረጉ ተገቢ አልነበረም ። በምዕራብ ኢትዮጵያ የመንግስት ሆነ የግል ባንኮች በኦነግ ታጣቂዎች ሲዘረፍ ፣ ንፁሃን ሰዎች ሲገደሉ መንግስት እንዳልሰማ ማለፉ ከትዝብት በላይ ነበር ። ዜጎች በአገራቸው ተፈናቃይ እንዲሆኑ መሆን ከመንግሥት አልባ አገር እንኳን የማይጠበቅ ድርጊት ነበር ። በኮዮፈች የጋራ መኖሪያ ቤቶች የቤት ባለቤት እጣ እድለኞች በጃዋር መሐመድ አማካይነት እደላው እንዲቆም መደረጉ እንዲሁም ጉዳዩ በጠቅላይ ሚኒስትር የዘር የፖለቲካ ድርጅት መደገፉ አሰገራሚም አሳዛኝም ነበር ። ያ ክሰተት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የህዝብ መሪ ለመሆናቸው አጠያያቂ ነበር ። የአማራ እና የትግራይ አገናኝ መንገዶች በስርአት አልባ የመንግስት ሀላፊዎች ሆኑ ግለሰቦች ሲዘጉ የጠቅላይ ሚኒስትር አሰተዳደር ምንም የማስተካከያ እርምጃ ያለመወሰዱ የመንግስት የማስፈፀም አቅም መሽመድመድ የሚያመላክት ነበር ።

ኢትዮጵያ እንደ አገር እንዲሁም የኢትዮጵያ ህዝብ እንደ ህዝብ ከመበልፀግ ይልቅ መደህየት ፣ ከመደጋገፍ ይልቅ መጠላለፍ ፣ ከመከባበር ይልቅ መጠላላት ፣ ከአንድነት ይልቅ መነጣጠል ፣ ከመተሳሰብ ይልቅ ፣ መጎዳዳት እንዲያቆጠቁጥ አንዱ ምክንያት ለሴራ ፖለቲካ ተገዢ መሆን ይመስለኛል ። የፖለቲካ ሰልጣን ለመያዝ መገዳደል ለምን አስፈለገ ? ። ወንድም ወንድሙን አጥፍቶ የመንግስት ስልጣን ለመጨበጥ ማሰቡ በራሱ አብይ ስህተት ነው ። የመንግስት ስልጣን የህዝብ መሆኑ የሚያምኑ ፖለቲከኞች የሴራ ፖለቲካ ስንክሳር ውሰጥ መነከር ኪሳራ ቢሆንም እንጂ ትርፍ አይኖረውም ። የሴራ ፖለቲካ አገር አፍራሽ ፣ ትውልድ ጨራሽ ፣ ህዝብ በታኝ ፣ የአገር ልማት አውዳሚ ፣ የድህነት መነሻ ፣ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግጭት ምክንያት ፣ የኋላቀርነት ማሳያ ምልክት ነው ። በሀሳብ ልዕልና ተከራክሮ ፣ በህዝብ ይሉኝታና ተቀባይነት አግኝቶ የመንግስት ሰልጣን ከመያዝ በጠበንጃ አፈሙዝ ስልጣን ላይ ለመውጣት ማሰብ የዋህነት ብቻ ሳይሆን አገራዊ ወንጀል ነው ። በሴራ ፖለቲካ የመንግስት ሰልጣን የሚጨበጥ መንግስት በህዝብ ፈፅሞ ተቀባይነት የለውም ። የፖለቲካ ስልጣነ የህዝብ አሰተዳደር በመሆኑ የህዝብ ይሉኝታ ያሰፈልጋል ። የሴራ ፖለቲካ መጠንሰሰ የህዝብ ውሳኔ መግታት በመሆኑ በምንም መልኩ ተቀባይነት የለም ። ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም በአማራ ክልል ባህርዳር ከተማ የተፈፀመው በጅምላ የክልሉ ባለስልጣናት የመረሸን ተግባር የተወገዘ ሲሆን መላ የኢትዮጵያ ህዝብ ያስቆጣ አሳዛኝ ድርጊት ነው ። ድርጊቱ በምንም ማሳያ ኪሳራ እንጂ ትርፋማ አልነበረም ። በእኔ አተያይ በባህርዳርና አዲስ አበባ የተፈፀመው የግድያ ወንጀል የመፈንቅለ ሰርአት እንደነበር ስምምነት የለኝም ። የሰኔ 15 ቀን በአማራ ክልል በህዳር ከተማ እንዲሁም የኢትዮጵያ ዋና ከተማ አዲስ አበባ ላይ የተፈፀመው አሳፋሪና አሳዛኝ የሴራ ፖለቲካ ወንጀል በገለልተኛ አጣሪ ኮምሽን መመርመር እና መጣራት አለበት የሚል እምነት አለኝ ።

የጠቅላይ ሚነስትር ዶክተር አብይ አህመድ አስተዳደር የ 2011 የበጀት አመት ዝርዝር የሥራ አፈፃፀም ለኢትዮጵያ ህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ባቀረቡበት ወቅት ወቅታዊ የኢትዮጵያ ጉዳይ ከምክር ቤቱ በጥያቄ መልክ ተነስቶ ነበር ። ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ የመንግስት ትዕግሥት እሰከ አገራዊ አንድነት ድረስ እንደሆነ ነገር ግን የአገር ልዕልና እንዲሁም የህዝብ ደህንነት የሚፃረር ሁሉ አሰፈላጊ መንግሰታዊ እርምጃ ይወሰዳል ሲሉ ተደምጧል ። በክልሎች ከተሞች ሆነ በአዲስ አበባ ከተማ ሰዎች በገፍ እየታሰሩ እንደሆነ የሰማል ይታያል ። በእኔ እምነት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ህግን መሠረት ያደረገ እርምጃ ለመውሰድ ዘግይቷል የሚል እምነት አለኝ ። ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒሰትሩ ጠበንጃ አንግበን እንዋጋለን ሲሉ የኢትዮጵያ ህዝብ ተወካዮች ምክርቤት አባላት ሀሳቡን በጭብጨባ ሲደግፉት ማየቴ በሁሉም ባይሆን ደጋፍ በሰጡ የምክር ቤቱ አባላት ላይ አዝኛለሁ ። ለምንና እንዴት ብሎ ከመጠየቅ ይልቅ ግደል ብሎ ድጋፍ መሰጠት ከምክር ቤት አባላት የሚጠበቅ አልነበረም ። የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ተጠሪነቱ ለኢትዮጵያ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሆኖ ሳለ ምክርቤቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እስኪመስል የወረደ የልጅ ጨዋታ ነበር የታዘብኩት ። መንግስት ህግን መሠረት አድርጎ ወንጀል መከላከል ሲቻል ሀይል እጠቀማለሁ ሲል ማጨብጨብ ለምን አስፈለገ ። የኢትዮጵያ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወንበር መቶ በመቶ በኢህአዴግ የተያዘ ነው ። በመሆኑም የሀሳብ ልዩነት ፍጭት የማይታይበት ደካማ ምክርቤት ነው ። ህዝብ ከህግ ውጭ በሐይል ማስተዳደር ሰላምና መረጋጋት አያመጣም ። ህዝብ ለህግ ካልተገዛ ለሐይል አይገዛም ። በመሆኑም የተረጋጋ አገር ለመፍጠር ህግን መሠረት በማድረግ ወንጀል መከላከል ይቻላል ። ችግሩ የፍትሕ ተቋማት ገለልተኛ ካለመሆን ጋር በተያያዙ የሚፈጠሩ ማህበራዊ ችግሮች ውስብስብ ከመሆናቸውም በላይ ፍትሀዊ የህግ አሰራር እንዳይኖር ምክንያት ይሆናል ። ለህዝብ ታማኝ ያልሆነ መንግስት አገራዊ ችግሮች በቀላሉ መፍታት አይችልም ። የህዝብ ደህንነት የማያስጠብቅ መንግስት በትናንሽ አጀንዳዎች ጊዜ ከማጥፋት ውጭ የህዝብ ፍላጎት አያሟላም ። በመሆኑም መንግስት ህዝብ በማያምንበት ጉዳይ ጊዜ ማባከን የለበትም ። የህዝብ ፍላጎት ሰላምና መረጋጋት መስፈን ነው ። የህዝብ ፍላጎት የመንግስት ፍላጎት ከሆነ ህዝብ የሚጠይቀው መንግስት ማስተካከል አለበት ። የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አስተዳደር የኢትዮጵያ ህዝብ አይንና ጀሮ መሆን ላይ መሸራተት ይታይባቸዋል ። የህዝብ ድምፅ በአግባቡ አይሰማም ፣ አይመዘንም ፣ ተግባር ላይ አይውልም ።

በኢትዮጵያ ከፍተኛ የመንግስት ሀላፊዎች ላይ ለተፈፀሙት ከፍተኛ የግድያ ወንጀሎች የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በቀጥታ ሆነ በሌላ ከተጠያቂነት ውጭ አይሆንም ። ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መሐንዲስ በግፍ መገደል ገና ያልተጣራ ጉዳይ ነው ። የአማራ ክልል አሰተዳደር ከፍተኛ የሥራ ሀላፊዎች የጭካኔ ግድያ ከአማራ ዲሞክራሲ ፖርቲ ካድሬዎች አሰተያየት ውጭ በቂና ገለልተኛ መረጃ አልተገኘም ። የኢትዮጵያ ከፍተኛ የጦር አዛዥ በግፍ መገደል ከገለልተኛ አካል መረጃ ገና አልተገኘም ። በግድያ ሴራ ላይ የመንግስት እጅ ይኑር አይኑር በገለልተኛ የተጣራ መረጃ የለም ። ጉዳዩ በገለልተኛ ካልተጣራ መንግስት በሚሰጠው መረጃ ብቻ ተመሥርቶ ትንታኔ ለመስጠት የሚቻል መስሎ አልታየኝም ። ምክንያት እውነት ከቤተመንግስት ይገኛል ብሎ መጠበቅ የዋህነት ነው ። የኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት የተቀነባበረ ግድያ በተመለከተ የኢትዮጵያ ህዝብ ተወካዮች ምክርቤት የግድያ ሁኔታ የሚያጣራ የምክርቤቱ አባላት ያሉበት ኮምሽን መቋቋም አለበት የኢትዮጵያ ህዝብ እውነቱን የማወቅ የተሟላ መብት አለው የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጀግና መሐንዲስ ኢንጂነር ስመኘው በቀለ እንዴት ራሱን ያጠፋል ? ። የኢትዮጵያ መከላከያ የበላይ ሀላፊ ጀነራል ሰዐረ መኮነን እንዴት በቅርብ ጠባቂው ይገደላል ? ። የአማራ ክልል ርዕስ መስተዳድር ለመግደል ሴራ ሲጠነሰሰ የኢትዮጵያ የደህንነት መሥሪያ ቤት ጉዳዩ እንዴት ሳያውቀው ቀረ ? ።

በኢትዮጵያ የፖለቲካ የሐሳብ ልዩነት ምክንያት መገዳደል ማብቃት ያለበት ጊዜ ይመስለኛል ። የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ባለቤት አልባ አጀንዳዎች እንዲሁም ውጤት አልባ የሴራ የፖለቲካ አካሔድ ማቆም ፍትሀዊነት ነው ። ክብር ነክ የትንኮሳ ንግግር አለፍ ሲልም የዘር ፖለቲካ ማራመድ ማቆም ፍትሐዊነት ነው ። ህዝብ የሚያከብር ፣ለህዝብ ደህንነት ጥብቅና የሚቆም ሀቀኛ የፖለቲካ ድርጅት እንዲያቆጠቁጥ ፣ የዲሞክራሲ መርህ ተኮር የፖለቲካ ሰርአት እንዲያብብ ከተፈለገ በህግ ልዕልና የሚመራ ህዝብና መንግስት መኖሩ የግድ ይሆናል ። መንግስት ህዝብ ገዳይ ፣ ህዝብ ደግሞ መንግስት ገዳይ ከሆነ አገርም ህዝብም አይኖርም ። በመሆኑም ለህግና ሰርአት ልዕልና የቆመ መንግስት ያሰፈልጋል ። ህዝብና መንግስት መናበብና መግባባት ካልቻሉ የችግር መነሻ ይሆናሉ ። አገር በህግ የበላይነት እንጂ በአድርባይ የፖለቲካ ድርጅት ካድሬዎች አይመራም ። የፖለቲካ ድርጅት ካድሬዎች ከህግ በላይ ሆኖ ዜጋ ሲበድሉ እርምጃ የማይወስድ መንግስት ለህዝብ አስተዳደር አይደለም የሞተ እሬሳ ለመቅበርም ብቁ አይደለም ። መንግስት የሚወስዳቸው የእርምት እርምጃዎች ለህዝብ አይገልጽም ። በመሆኑም በኢትዮጵያ ወንጀለኛና ንፁህ መለየት አይቻልም ። አውራ ጎደና የጭነት መኪና አስቁሞ የሚዘርፉ የተደራጁ ስርአት አልባ ሰዎች መንግስት ተከታትሎ ለህግ ማቅረብ ሥራው ነው ። ሰላምና መረጋጋት ማስፈን ተቀዳሚ የመንግስት ሰራ ነው ። ልማት ማፋጠን ፣ የአገር አንድነት ማስጠበቅ ፣ የህዝብ ድህነት ማስከበር ፣ ሥራ አጥነት መቀነስ ፣ ሁሉም አይነት ወንጀሎች አሰቀድሞ መከላከል መንግስት ከህዝብ የተቀበለው ሀላፊነት ነው ።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አሰተዳደር በበርካታ ችግሮች የተከበበ ቢሆንም የችግሮች መፍትሔ ደግሞ ራሱ መንግስት ነው ። ያለአግባብ በአዲ አበባ ከተማ የታሰሩ በርካታ የትግራይ ተወላጆች በአስቸኳይ መፈታት አለባቸው ። የአማራ ህዝብ እና የትግራይ ህዝብ በጠላትነት እንዲተያይ ጥላቻ የሚሰብኩ የኢህአዴግ ካድሬዎች ከድርጊታቸው መታቀብ የግድ ይላቸዋል ። የአማራ አሰና የትግራይ ህዝብ ወንድም ህዝብ እንጂ የቆየ ቅራኔም ሆነ ቂም በቀል ያልተላበሰ ህዝብ ነው ። የሁለቱም ህዝብ የፖለቲካ ካድሬዎች ህዝብ የሚያቀራርብ ተግባራት ከመፈፀም ይልቅ አሉባልታ ላይ ተሰማርቶ ይታያል ። ይህ አስነዋሪ ድርጊት እንዲቆም ይፈለጋል ። በውይይት እንጂ በጉልበት የሚፈታ ጉዳይ የለም ። የአማራ ክልል ሆነ የትግራይ ክልል አመራሮች እየፈፀሙት ያለ የተሳሳተ የፖለቲካ ቁማር ተገቢነት የለውም ። መሬት የሰው ህይወት አይተካም ። የሐይል አሰራር ማንንም አያስተምርም ፣ ምንንም አያሰወግድም ። ትርፉ ትርምስና መተላለቅ ብቻ ነው ። ችግሮች ከጥላቻ በራቀ መንፈስ ለመፍታት መትጋት የአንድ መሪ ብልህነት ነው ። በቅርቡ የአማራ ክልል ምክርቤት ያስተላለፈው አስቸኳይ ውሳኔ በሚገባ የተሞከረበት ሳይሆን ከስሜታዊነት የመነጨ ውሳኔ ይመስለኛል ። የትግራይ ልዩ ሐይል ከአማራ አዋሳኝ ቦታዎች እንዲለቅ የሚል ሲሆን መቀሌ የመሸገው አጥፊ ሐይል ብሎ መፈረጅ አግባብነት የለውም ። በአንድ አገር እየኖሩ ፣ በአንድ አይነት ቋንቋ እየተግባቡ ፣ እንደ ባላንጣ መተያየት አግባብነት የለውም ። መስክን ያሰፈልጋል ። ከክብር ነክ የጥላቻ ንግግሮች መቆጠብ ያሰፈልጋል ። መቀሌ የመሸገው ሐይል ለኢትዮጵያ አንድነት ችግር መስሎ አይታየኝም ። ምክንያቱም ሁሉም ኢትዮጵያውያን በመሆናቸው ሁሉም የኢትዮጵያ ዜጋ የሚያስበው መሳብ የሚችሉ ሰዎች ናቸው ። የፖለቲካ ልዩነት ቢኖራቸውም ክፋት የለውም ። ሀሳብን በሐሳብ መሞገት ተፈጥሯዊም ህገ መንግሰታዊም ነው ።

 

Back to Front Page