Back to Front Page

የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ህልውና የሚወሰነው በኢህአዴግ ህልውና ሳይሆን በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ነው

የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ህልውና የሚወሰነው በኢህአዴግ ህልውና ሳይሆን በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ነው

 

ህዳሴ ኢትዮጵያ

መጋቢት 192011 ..

 

አገራችን ኢትዮጵያ ባለፉት 100 ዓመታት የትምክህት አራማጅ የሆኑት የዘውድ እና የደርግ ስርዓቶች የአማራ ህዝብን ጨምሮ መላው የአገራችን ህዝቦች በአስከፊ ጭቆና ቀንበር አስገብቶ ሲያሰቃዩ እንደነበረ ማንም የማይረሳው ሓቅ ነው፡፡ ነገር ግን እነዚህ ጨቋኝ ገዢመደቦች የወጡበት ብሄር አማራ በመሆኑ፡ በሌላው ብሄር የሚጭኑት ቋንቋ፡ ባህል፡ ወግ እና ማንነት የአማራ በመሆኑ ቀላል የማይባለው የአገራችን የህብረተሰብ ክፍል አማራ ማለት ጨቋኝ አድርጎ የሚወስድ ነበር፡፡

በአማራው በኩልም ይህን የገዢነት አስተሳሰብ የወረሰ እሱ ከኢትዮጵያውያን ልዩ እና ቤተኛነት የሚሰማው፡ ከሱ ውጭ ስለ ኢትዮጵያ የሚቆረቆር እንደሌለ፡ እሱ አንደኛ ደረጃ ዜጋ ሌሎች 2ኛ እና 3ኛ ደረጃ ዜጋ እንደሆኑ አድርጎ የሚያስብ አማራ ቀላል ቁጥር አልነበረም፡፡

Videos From Around The World

ይህ በአማራ እና በሌሎች የአገራችን ህዝቦች ውስጥ የነበረ የተደናገረ እና የተሳሳተ አመለካከት፡ አብሮነት እና መቻቻል እንዳይመጣ ከፍተኛ እንቅፋት የነበረ በመሆኑ፡ ይህን የተሳሳተ ግንዛቤ የመለወጥ ጉዳይ ጊዜ የማይሰጥ ጉዳይ ነበር፡፡ በመሆኑም ባለፉት 27 ዓመታት በአገራችን ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ውስጥ ኢህአዴግ በተለይ ህወሓት በአብዮታዊ ዴሞክራሲ መርህ በገዢው መደብ እና ገዢው መደብ የወጣበት ብሄር ያለው ልዩነት እና አንድነት የጠራ ግንዛቤ እንዲኖር ከፍተኛ ትግል አድርጓል፡፡ ትግሉም ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገቡ የሚታወቅ ሲሆን የዚህ ማረጋገጫም ላለፉት 27 ዓመታት በዚህ ጉዳይ ምንም ግጭት ተፈጥሮ አያውቅም ባይባልም ባመዛኙ ሰላም፡ መረጋጋት፡ ልማት፡ መቻቻል፡ እኩልነት የሰፈነበት ዓመታት ነበር፡፡ ይህም አብዮታዊ ዴሞክራሲ ስር እንዲሰድ የረዳ ነበር፡፡

በዚህ ጊዜ ቀላል የማይባሉ ፈተናዎች ማለፍ የግድ ይል ነበር፡፡ በመሆኑም ከአማራው ብሄር ውጭ ያለው ፅንፈኛ ሀይል፣ ገዢዎች እና ጭቁን ህዝቦች አንድላይ በማደባለቅ በጠላትነት በመፈረጅ ግጭቶችን ለመፍጠር ከፍተኛ ጥረት ያደርጉ ስለነበር ግጭቱ ለማስቀረት ወይም አደጋው ለመቀነስ ትልቅ ፈተና ነበር፡፡ በሌላ በኩል የአማራው ፅንፈኛው ሃይል በተለይ ቀላል ቁጥር የማይባል የአማራው ወጣት እና ሙሁር በማሰለፍ የፌደራል ስርዓቱ እንዲቃወም፡ የአሀዳዊ ስርዓት እንዲያቀነቅን፡ ፌደራል ስርዓት የሚደግፍ እንደ ጠላት እና የኢትዮጵያ አንድነት ተፃራሪ ተደርጎ እንዲፈረጅ ከፍተኛ እንቅስቃሴ አድርገዋል፡ ግጭቶችም ፈጥረዋል፡፡

ይሁንና ባለፈው ዓመት የኢህአዴግ ስራአስፈፃሚ እንደገመገመው፤ ኢህአዴግ በውስጡ ፀረ ዴሞክራሲ እየገነገነ በመምጣቱ፣ ውስጠ ትግል እየተቀዛቀዘ በመምጣቱ፣ የኪራይ ሰብሳቢነት እና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እየተባባሱ በመምጣት ኢህአዴግ በስብሷል በጥልቀት መታደስ አለበት ነበር የተባለው፡፡ መበስበስ ሲባል ደግሞ ኢህአዴግ ካስቀመጣቸው እሴቶች፡ መርሆዎች፡ አላማዎች እና ግቦች ወጥቶ መጓዝ መጀመሩ እና ረጅም ርቀት መጓዙ ነው፡፡ ኢህአዴግ ከዚህ የገባበት የመበስበስ አዘቅት እንዲወጣ ወደ ጥልቅ ተሀድሶ ወይም ለውጥ መግባት አለበት የሚል ውሳኔ በመወሰኑ ምክንያት በአገራችን የመንግስት ለውጥ በመበሰሩ ኢህአዴግ አዲስ ሊቀመንበር በድምፅ ብልጫ መርጦ ጠ/ሚ ሾሞዋል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ የኢህአዴግ የለውጥ እንቅስቃሴ እየመራ ያለው ቡድን ኢህአዴግን ከመበስበስ አዘቅት የሚያወጣ ሳይሆን በበለጠ በመበስበስ ጎዳና እንዲ ከንፍ ነው እያደረገ ያለው፡፡

በሌላ አባባል ይህ ቡድን እየተገበረው ያለው የለውጥ እንቅስቃሴ ኢህአዴግን ወደ ቀድመው ቦታው ወይም ወደ ቀድመው እሴቶች፡ መርሆዎች፡ አላማዎች እና ግቦች የሚመልሱ ሳይሆን አነዚህ እሴቶች፡ መርሆዎች፡ አላማዎች እና ግቦች እየጣሱ የኢህአዴግ ደብዛ ማጥፋት እና ራስን በራስ የማጥፋት ተልእኮ በመፈፀም ላይ ነው ያለው፡፡ ለዚህ ነው ኢህአዴግ አሁንም መልኩ እና መሪውን ቀይሮ ፍጥነቱን ጨምሮ በመበስበስ እና በዝቅጠት ጎዳና ላይመለስ ወደ ገደል እየገባ ያለ ድርጅት ነው የምለው፡፡

ይሁን እነጂ ኢህአዴግ ላይመለስ ወደ ገደል ገባ ተሰባበረ በሞት አፋፍ ላይ ያለ ወይም ሞተ የሚባል ቢሆንም ክስተቱ ድርጅቱ እንጂ መስመሩ ወይም አብዮታዊ ዴሞክራሲ ላይመለስ ተሰባበረ ማለት አይደለም፡፡ ኢህአዴግ የሚመራበት ርእዮት "አብዮታዊ ዴሞክራሲ" ህዝቦች ከጭቆና የሚያወጣ፡ ህዝቦች በፍጥነት ከድህነት የሚያወጣ፡ በህዝቦች መካከል ያለው የመብት ልዩነት በማስወገድ እኩልነት የሚያረጋግጥ ወይም ሁሉም ህዝቦች እኩል እንዲታዩ የሚያደርግ ርእዮት ነው፡፡ በአጠቃላይ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ማለት ቡዝሀነት ካላቸው ጭቁን ህዝቦች፡ በድህነት ስር ከሚማቅቁ ህዝቦች ፍላጎት የሚመነጭ እና እነዚህ ፍላጎቶች በተቀላጠፈ ፍጥነት እውን የሚያደርግ መስመር ነው፡፡

ስለዚህ

         ቡዝሀነት ያላቸው ጭቁን ህዝቦች እስካሉ ድረስ፡

         በድህነት ስር የሚማቅቁ ህዝቦች እስካሉ ድረስ፡

         ከጭቆናና ከድህነት በተቻለ ፍጥነት መውጣት የሚፈልጉ ህዝቦች እስካሉ ድረስ

አብዮታዊ ዴሞክራሲ ሊሞት አይችልም፡፡ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ሊሞት የሚችለው የህዝቦች ነባራዊ ሁኔታ ሲቀየር ብቻ ነው፡፡ እነዚህ ነባራዊ ሁኔታዎች እስካሉ ድረስ በኢህአዴግ ወይም ወቅቱ በሚፈጥረው ሌላ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ያብባል፡፡ ይቀጥላል፡፡

አሁን የኢትዮጵያ አገራችን ነባራዊ ሁኔታ ስናይ

1.      የብዙሀነት አገር ሆና የጀመረችው የብዙሀነት ዴሞክራሲ አደጋ ላይ የወደቀበት ሁኔታ፡

2.      የብዙሃን መብት መከበር ለድርድር የማያቀርብ የነቃ ህዝብ ያላት አገር ፡

3.      ቀላል የማይባል ህዝቦቿ (ከጠቅላላው ህዝብ 23%) በድህነት እየማቀቀ የሚኖር ህዝብ፡

4.      ከአስከፊ ድህነት እና ከተመፅዋችነት ለመላቀቅ ከፍተኛ ፍላጎት ያለው ህዝብ፡

5.      ባለፉት 27 ዓመታት በአብዮታዊ ዴሞክራሲ አመራር አለምን ያስደነቀ ውጤት የተመዘገበበት እና ውጤቱን ያጣጣመ ህዝብ፡፡

እላይ የተዘረዘሩት 5 ነባራዊ ሁኔታዎች በአገራችን መኖራቸው አብዮታዊ ዴሞክራሲ የግድ እንዲኖር ይጋብዛሉ፡፡ ኢህአዴግ ባይኖር እንኳን አብዮታዊ ዴሞክራሲ የሚያራምድ ቁርጠኛ ህዝባዊ ሀይል/ድርጅት የግድ ይፈጠራል፡፡ አብዮታዊ ዴሞክራሲ እንኳን አሁን በተግባር ተፈትኖ የተረጋገጠበት ጊዜ በ1960ዎቹም በተስፋ ብቻ ሚልዮኖች አሰልፈዋል፡፡

አሁን ኢህአዴግ በሞት አፋፍ ባለበት ወቅት የአብዮታዊ ዴሞክራሲ አስፈላጊነት ከመቸውም ጊዜ በበለጠ እየተነሳ ይገኛል፡፡ ከሁሉም በላይ የቲም ለማ ወይም የቅጥረኛው የኦሮማራ ቡድን ያስደነገጠው ደግሞ አብዮታዊ ዴሞክራሲ የሚያራምዱ ድርጅቶች በሞቱባቸው ክልሎች የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ጥያቄ መጠየቅ መጀመራቸው ነው፡፡ ለምሳሌ

) በኦሮምያ ክልል፡

ኦህዴድ እንደ ማንኛውም የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች በመበስበስ መንገድ ሲጓዝ የቆየ ቢሆንም ከጥልቅ ተሀድሶ ቦኋላ ህመሙ ፀንቶበታል፡፡ የኦህዴድ መበስበስ የት ደረጃ መድረሱን ለማወቅ በህቡእ የፈጠራቸውን ግንኝነቶችን ማየቱ በቂ ይመስለኛል፡፡ እንደ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ተከታይ ድርጅት ኣብዮታዊ ዴሞክራሲ ለመጣል ከፀረ-አብዮታዊ ዴሞክራሲ ሀይሎች ድብቅ ግንኙነት ማድረጉ ነው፡፡ ዕብደት ምን ያክል ከፍተኛ ደረጃ መድረሱ የሚያሳየው ኦህዴድ የብሄር ጥያቄ ከማይቀበሉ ድርጅቶች መመሳጠር መጀመሩ ነው፡፡ ይህ የበሰበሰ ጥገኛ ድርጅት በሸረበው ሴራ ተሳክቶለት ስልጣን ከተቆጣጠረ ቦኋላ የሚያደርጋቸው የነበሩ ስውር ግንኝነቶች በማን አለብኝነት ለህዝብ ይፋ ሲያደርገው የኦሮሞ ህዝብ በቀጥታ ኦህዴድን በመነጠል ሌላ ድርጅት ማማተር ጀመረ፡፡ ኦሮማራ የሚለው የኢትዮጵያ ህዝቦች የነጠለ ስውር ሴራ ያለው የፀረ ህዝቦች እና ፀረ ብሄር ብሄረሰቦች ቡድን መሆኑ ሲያውቅ የኦሮሞ ህዝብ በትግሉ ያረጋገጠው መብቱ ለመግፈፍ የታቀደ ሴራ እንደሆነ በመረዳት ጥያቄ ማንሳት መጀመሩ፣ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ምንኛ በኦሮሞ ህዝብ ውስጥ እንደገባ ማሳያ ነው፡፡ ኦህዴድ የህዝቡን ጥያቄ ሲያይ፣ በኦሮማራ የተዋዋለውን ውል ወደጎን ትቶ የፌደራል ስርዓት ለድርድር አናቀርብም በሚልበት ጊዜ ነበር በኦሮማራ የተጠለለው የአማራ ፅንፈኛው ቡድን የተደናገጠው፡፡ ኢህአዴግ ይኑር አይኑር ኦህዴድ ይኑር አይኑር አብዮታዊ ዴሞክራሲ በኦሮሞ እንደሚኖር የኦሮሞ ህዝብ አረጋግጧል

/ በአማራ ክልል

በአማራ ክልል የሚገኘው የኢህአዴግ እህት ድርጅት ብአዴንም በመበስበስ ጎዳና ረጅም ርቀት ከተጓዙት አንዱ ነው፡፡ ከጥልቅ ተሃድሶ ቦኋላ ሲታይ ብአዴን በይፋ ስላልወጣ ወይም መሪዎቹ ስላልተናገሩት እንጂ ብአዴን አስቀድሞ የሞተ ግን መሪዎቹ የሞተውን ቆዳ ለብሰው /ዓርሲ/ የኢህአዴግ ወተት ሲጠጣ የነበረ ድርጅት ነው፡፡ አዴፓ የተላላፊው በሽታ አስመጪ ሆኖ ድርጅቱን ገድሎ በመቅበር የብአዴን ቆዳ ለብሶ ኢህአዴግን ሲያምስ ከቆየ ቦኋላ በኢህአዴግ ውስጥ ሆኖ ህቡእ /ኦሮማራ/ ቡድን በመፍጠር ስልጣን ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ ወደ ጥገኛው አመለካከት ካሸጋገሩት ቁንጮዎች አንዱ ነበር፡፡ ይህ የዘቀጠ ድርጅት በኢህአዴግ ምክርቤት ስብሰባ አብዮታዊ ዴሞክራሲ አሽቀንጥሮ ለመጣል ሲሞክር፣ እንደ ጥቂቶቹን አታሎ ኦሮማራ መፍጠር ቀላል ሆኖ አልተገኘም፡፡ የበሰበሱት የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ይህንን በቀጥታ ነበር የተቃወሙት፡፡

አዴፓ ድርጅቱ ነው የበሰበሰው እንጂ አብዮታዊ ዴሞክራሲ እንዳልበሰበሰ ከራሱ ክልል ከኣማራ ክልል በቅርቡ የተከሰተው ነገር ማየት ይቻላል፡፡ እሱም በቅርቡ የባህርዳር ወጣቶች ግንቦት-7 በመቃወም ያደረጉት ሰልፍ ማየት በቂ ነው፡፡ ተቃውሞ ያቀረቡት ወጣቶች "ግንቦት 7 የአማራን ብሔርተኝት የሚያዳክም፣ በኢትዮጵያዊነት ስም አማራን እንዳይደራጅ የሚያሴር፣ ሀገሪቱ በብሔር ፖለቲካ መወጠሯን እያወቀ አማራ ብቻ ስለኢትዮጵያ እንዲያቀነቅን የሚወተውት ፀረ-አማራ ነው" ብለዋል፡፡ ይህ የሚያሳየው አብዮታዊ ዴሞክራሲ በአማራ መቀበሩን ሳይሆን አሀዳዊ ስርዓት በአማራ ክልል በጠና መታመሙ ነበር፡፡

በአጠቃላይ በአሁኑ ጊዜ ኢህአዴግ ወደማይድንበት ደረጃ መድረሱ ለሁሉም ግልፅ ነው ምናልባት በኦሮሚያ ክልል እና በአማራ ክልል ኢህአዴግ ሙሉ በሙሉ ህልውናው አጥቷል ቢባል ማጋነን አይደለም፡፡ ነገር ግን የአብዮታዊ ዴሞክራሲ እርሾው ከነ ሀይሉ ስላለ ለአዴፓ እና ለኦዴፓ ትልቅ ፈተና ሆኖባቸዋል፡፡ በተለይ በኦሮሚያ ክልል የአብዮታዊ ዴሞክራሲ እርሾው ለቲም-ለማ ዥዋዥዌ በማጫወት ላይ ሲሆን በአማራ ክልል ግን ማንም ባልጠበቀው ወጣቱ የአማራነት ማንነት አንስቶ የመደራጀት ጥያቄ ሲያስነሳ የትምክህት ጎራው ከፍተኛ መደናገጥ ገጥሞታል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ኢህአዴግ በሞት አፋፍ ላይ ቢሆንም፣ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ግን በህዝቡ ዘንድ እያበበ ነው፤ ድምፅ አውጥቶ እየተናገረ ነው፡፡ ስለዚ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ህልውና በኢትዮጵያ የሚወሰነው በኢህአዴግ ህልውና ሳይሆን በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ነው፡፡

ህዳሴ ኢትዮጵያ

መጋቢት 192011 ..

አስተያየት ካለ በሚቀጥለው ሊንክ ማድረስ ይቻላል

hidaseethiopia@yahoo.com and/or hidaseethiopiaa@gmail.com

 

 

Back to Front Page