Back to Front Page

የነውጥ መስመር በኢትዮጵያ፡

የነውጥ መስመር በኢትዮጵያ፡

የራእይ አልባ፣የጥፋት አመራር አነሳስ

ፈይሳ ነግሪ 7-23-19

ኢትዮጵያ አገራችን ከደርግ ውድቀት በኋላ ከምዕራቡና ከምስራቁ ዓለም ምህዋር ውጭ በራሷ መንገድ መሽከርከር መጀመሯ የሚታወቅ ነው። ከፖሊሲ ጥገኝነት ወጥታ በራሷ አገራዊ ፖሊሲ መመራት ከጀመረችም ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ተቆጥሯል። ከተመፅዋችነት የምትወጣበትን ሐዲድ በመከተልና በህዝቦችዋ ዓቅም በመተማመን በለኮሰችው የለውጥና የህዳሴ ጉዞ በከፍተኛ ፍጥነት በመገስገስ ላይ የምትገኝ አገር ሆናለች። ከዚህ የተነሳም የአፍሪቃ የለውጥ ተምሳሌት መሆን ብቻ ሳይሆን የአፍሪቃ ያበረ ድምፅ መሪ ወደ መሆን ተሸጋግራ፣ በዓለም ያላት ተሰሚነትና ተቀባይነትም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል።

ይህ አዲሱ የአገራችን ገፅታ ግንባታ እውን የሆነው ኢህአዴግ ወደ መድረክ መንበረ-ስልጣን ብቅ ማለቱን ተከትሎ ነው፡፡የዛሬ አያድርገውና ኢህአዴግ በጣም ጠንካራ ከሚባሉ የዓለማችን ፖለቲካዊ ድርጅቶች አንዱ ነው፡፡ የኢህኣዴግ ጥንካሬም የኢህአዴግ አስኳል ከሆነው ህወሓት የመነጨ እንደሆነ ድፍን አገር ያወቀው ጉዳይ ነው፡፡ ብዙዎቹ ፖለቲከኞች ግን እስከ 1970ዎቹ መጨረሻ ኢህኣዴግን ወደ እንዲህ ዓይነቱ ጥንካሬና ውጤት ያደረሰው ህወሓት በጥልቀት የተገነዘቡበት ሁኔታ አልነበረም፡፡ከ1966ቱ ህዝባዊ ዓመፅ በኋላ በኢትዮጵያ ፖለቲካ የጎላ ቦታና ተሰሚነት የነበራቸውኢህአፓ እና መኢሶን የተባሉቱ ፖርቲዎች ነበሩ ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ከታጣቂዎች ደግሞ ታዋቂየነበሩት የኤርትራዎቹ ሁለቱ ድርጅቶችን [ጀብሃና ሻዕቢያ] መጥቀስ ይቻላል፡፡ በዛን ጊዜ ህወሓት በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ መድረክ ብዙ ቦታ የሚሰጠውና እምብዛም የሚታወቅ አልነበረም፡፡ በወቅቱ ደርግን ሲቃወሙ የነበሩ ኃይሎች ህወሓትን ከቁብ የሚቆጥሩት አልነበሩም፡፡ አንዳንዶቹም ሲበዛ ንቀት ነበራቸው፡፡ ደርግ ራሱ በህወሓት ላይ በጣም ከፍተኛ ንቀት እንደነበረው ከአነጋገሩም ሆነ ከድርጊቱ ይስታውቅ ነበር፡፡ በዛን ወቅት ደርግ ህወሓትን በስሙ ሳይሆን የገጠር፣ የጓሮ ኣይጥ ወዘተ… እያለነበር የሚጠራው፡፡ ፀረญญ‑ህወሓት በአካሄዳቸው የመጀመሪያዎቹ መጠነ‑ሰፊ ዘመቻዎቹም በአብዛኛው መፈክሩ ትግራይን በመዳሰስ ኤርትራን መደምሰስ የሚል እንደምታ ነበረው፡፡

Videos From Around The World

       የኋላኋላ ግን ደርግና የቀኝ እጁ የነበረው የልዕለ ኃያሏ ሶቭየት ሕብረት የስለላ ድርጅት [ከይ.ጂ.ቢ.]በህወሓት የሚመራው የትጥቅ ትግል ለእንቅስቃሴያቸው ትልቁ እንቅፋትና አደጋ መሆኑን ደርሰውበታል፡፡ ከዚህ የተነሳም ሶቭየት ሕብረት ለደርግ ዘመናዊ የጦር መሳርያና ሎጂስቲክስ አቅርቦት በገፍ በማቅረብ፣ የስለላና የውግያ ስልትና ጥበብ ስልጠና በመስጠት፣ በጣም የተራቀቁ የዘመቻ ስምሪቶችን ፕላን በማዘጋጀት ህወሓትን ለማጥፋት እጅግ ብዙ ጥረቶች አድርጋለች፡፡ ከ1970ዎች አጋማሽ ጀምሮ በተለይ በ70ዎቹ መጨረሻ ዓመታት ደርግ በትግራይ ያካሄዳቸው ዘመቻዎች ይህንኑን በግልፅ የሚያሳዩ ነበሩ፡፡ ህወሓት እነዚህ በሶቭየት ሕብረት ከፍተኛ የፖለቲካና ወታደራዊ አመራር የተካሄዱበትን ዘመቻዎች በሚያስገርም ቆራጥነትና የአላማ ፅናት በመመከት፣ ደርግ ከሶቭየት ሕብረት በገፍ የታጠቀውን ዘመናዊ የጦር መሳሪያ በመማረክ ይበልጥ እየፈረጠመ ናበድል እየተራመደ ወደ ስትራተጂያዊ ማጥቃት መሸጋገር ችሏል፡፡ ህወሓት ወደዚህ ከፍታ በደረሰበትና በደርግ ውድቀት ዋዜማ ወቅት ሶቭየት ሕብረት በፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ተመታ መሰነጣጠቅ የጀመረችበት ክስተት ስለተፈጠረ ደርግን ልታግዝ ቀርቶ ራሷን መታደግ ተስኗት የመፈራረስ ፈተና አጋጠማት፡፡ በዚህም የምስራቁ ልዕለ ኃያል ካምፕመናድ ሲጀምር የምእራቡ ዓለም ሙሉ በሙሉ የበላይነቱን ለመያዝ በቃ፡፡

       በሌላ በኩል ልዕለ ኃያሏ ኣሜሪካና ምዕራባውያኑ ሸሪኮቿ የህወሓት ዓላማና ጥንካሬ የማይጥማቸው ቢሆንም ከሶብየት ሕብረት ጋር ተጣብቆ ለስትራተጂያዊ ጥቅማቸው እንቅፋት ነው ብለው ከፈረጁት ደርግ ጋር ሲያነፃፅሩት ለህወሓት ትልቅ ትርጉም ሰጥተው በአጀንዳቸው የያዙት አልነበረም፡፡ በሂደትም ደርግን በማዳከምና በማሸነፍ ስልጣን ይዘው የኛን ዓላማ ያስፈፅማሉ ያልዋቸውን በአብዛኛው የትምክሕት ኃይሎችን በተለያዩ ድጋፎች ሲያጠናክሩ ነበር፡፡ ይህ በእንዲህ እያለ ምዕራባውያኑና የዓረብ አገራት ህወሓትን ኮሚኒስት በሚል ጥርጣሬ የተነሳ ከሌሎች ተቃዋሚ ድርጅቶች የሚደርሳቸውን ኢንፎርሜሽን መሰረት በማድረግ በህወሓት የውጭ ጉዳይ እንቅስቃሴ ላይ ቀላል የማይባል ጫና ሲፈጥሩ እንደነበር ይታወቃል፡፡

ይሁንና በአንድ በኩል ምዕራባውያኑ ተስፋ የጣሉባቸው ተቃዋሚ ኃይሎች በደርግ እየተንኮታኮቱ የመጡበት፣ የኤርትራ ታጣቂ ድርጅቶችም ሳይቀር ብዙ ተስፋ የማይጣልባቸው የሆኑበትና ራሳቸውን ከደርግ ጥቃት ወደ መከላከል የገቡበት ሁኔታ  ሲታይ በሌላ በኩል ደግሞ በዚህ ፍጥነት ያድጋል ተብሎ ያልተገመተውና የተናቀው ህወሓት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበተ ፈርጣማ ሆኖ የወጣበት ሁኔታ ተፈጠረ፡፡ በዚህም በደርግ ላይ ከፍተኛ ጫናና ምት ሊያሳርፍ የሚችል ህወሓት ብቻ እንደሆነ ለሁሉም ግልፅ እየሆነ መጣ፡፡ በዚህ ምክንያት የምዕራቡ ዓለም የህወሓት ዓላማና ጥንካሬ የማይዋጥለት ቢሆንም ቅሉ የመጀመሪያ እንቅፋት አድርጎ ከሚያየው ደርግ አንፃር ሲመዝነው ግን ከህወሓት ጋር ቅራኔ መፍጠር ተመራጭ ሆኖ አላገኘውም፡፡ ለጊዜውም ቢሆን ህወሓትን ችላ ብሎ በማለፍ በደርግ ላይ ትልቅ ጫና እንዲያሳርፍለት ይፈልግ ነበር፡፡ ይህ አጋጣሚ በሁለቱ ልዕለ‑ኃያላን ያለውን ቅራኔ የመጠቀም ስልት ለሚያራምደው ህወሓት በተነፃፃሪ የተመቸ የትግል ሁኔታ እንደፈጠርለት ይታመናል፡፡ ህወሓት በበኩሉ በስልታዊ መድረኩ በቅድሚያ መታየት ያለበት የሶቭየት ሕብረት ጣልቃ ገብነት ነው ብሎ ያስቀመጠ ስለነበር ከምዕራቡ ዓለም ጋር ወደ አላስፈላጊ አታካራ እንዳይገባ በጥንቃቄ ይጓዝ ነበር፡፡ ሁለቱም ኃይሎች [ህወሓትና ምዕራባውያን] ልዩነታቸውን በይደር በማቆየታቸው ለትጥቅ ትግሉ የተመቸ ሁኔታ እየፈጠረ ሄደ፡፡ በሂደትም የሁለቱ ስልታዊ ግብ [ደርግንና የሶቭየት ሕብረት ጣልቃ ገብነትን ማስወገድ]ለማሳካት አስቻለ፡፡

       በአጠቃላይ ሲታይ በትጥቅ ትግሉ ወቅት ምዕራባውያኑ ስለ ህወሓት ምንነትና የአመራር ጥንካሬ ከቅንጭብጭብ ኢንፎርሜሽን በዘለለ የረባ መረጃና እውቀት የነበራቸው አይመስልም፡፡ ከደርግ መደምሰስ በፊት ስለ ህወሓትና አመራሩ ጥልቅ ጥናት እንዳልነበራቸውም ይነገራል፡፡ ህወሓት በዓውደ‑ውግያ የማሸነፍ ዕድል ሊኖረው እንደሆነ እንጂ ድሕረ-ደርግ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ወሳኝ ሚና ይጫወታል፣ አገር በመምራትም ተዋናይ ይሆናል የሚል ግምት የነበራቸው አይመስልም፡፡ የህወሓት ሚና ደርግን በመደምሰስ እንደሚያበቃ አድርገው የሚያስቡ አንደነበሩ በዛን ጊዜ ከነበራቸው አመለካከትና ተግባራዊ እንቅስቃሴ ለመገንዘብ የሚከብድ አይደለም፡፡ የደርግ ውድቀት ሲረጋገጥ በተለመደው የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሴራቸው [በሌሎች አገሮች ተግባራዊ እንዳደረጉት ሁሉ] ህወሓትን ከጨዋታ ውጭ እንደሚያደርጉት እምነት የነበራቸው ይመስላል፡፡ ደርግ ሊወድቅ በተቃረበበትና በወደቀ ማግስት ሲያደርጉት የነበረ እንቅስቃሴ ሲታይም ይህንን የሚያረጋግጥ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ከደርግ ወድቀት ማግስት ኢትዮጰያን ሊያስተዳድር የሚችል አማራጭ ያሉት የግለሰቦች ስብስብ በጥናት ይዘው እንደነበርም ከታማኝ ምንጮች ይነገራል፡፡

የውግያ ጡንቻው ከማሳየት ባለፈታላቋን ሀገረ‑ኢትዮጵያ በብቃት በመምራት የማረጋጋት፣ የፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችንፈር በማስያዝ ውጤት የማስመዝገብ ተልእኮ ብዙም የሚሳካለት አይሆንም ተብሎ በብዙዎቹ ዘንድ የታሰበው ህወሓት በአጭር ጊዜ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ግንባር [ኢህአዴግ] በመመስረት የትጥቅ ትግሉን ለመሰረታዊ አገራዊ የፖለቲካ ስኬት አደረሰው፡፡ግንባሩ ከተመሰረተ አጭር ዕድሜ ያስቆጠረ ቢሆንም በህወሓት ፊታውራሪነት ከዕድሜው በላይ ተፅእኖ ፈጣሪ ለመሆን በቃ፡፡ የካበተ ልምድ አላቸው ከሚባሉት የዓለም የገንዘብ ተቋማት ሳይቀር በሽግግሩ ወቅትና ማግስት ያጋጠሙትን ተግዳሮች በብቃት ለመመከት ያደረገው እንቅስቃሴና እያደረ ያስመዘገበው ውጤት ብዙዎችን ያስደመመ ነበር፡፡ እንደ ዩጎዝላቭያና ሞንሮቪያ ትበታተናለች ተብሎ የተተነበየላት አገር በብቃት አረጋግቶ ማስቀጠል መቻሉ፤ የተሳካ የሽግግር መድረኽ መርቶ፣በሰፊ የህዝብ ተሳትፎ ሕገ-መንግስት ማስፀደቅና በህዝብ ምርጫ የተሰየመ መንግስትን ለማቋቋምና የአገሪቱ ኢኮኖሚ የቁልቁለት ጉዞ በመግታት የእድገት ዜና ለማብሰር መብቃቱ ኢህአዴግ ቀላል ኃይል አለመሆኑን በኃያልያኑ መንግስታት ዘንድ ትልቅ ሓሳብ ጫረ፡፡ ብዙዎች ያልተገነዘቡት የኢህአዴግ የንድፈ-ሓሳብ፣ የፖለቲካና የአመራር ብቃትም ጋሃድ ሊሆን ቻለ፡፡

ግንባሩ የልማታዊ መንግስታትን ተሞክሮ በመቀመር በነደፈው የልማታዊ መንግስት ፖሊሲም በአገሪቱ ታይቶ የማይታወቅ ባለ ሁለት አሃዝ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ለማስመዝገብ ቻለ፡፡ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ ብቻ ሳይሆን የኢኮኖሚ እድገቱ የሀብት ትሩፋት ክፍፍሉም ከማንኛውም አገር የተሻለና ፍትሃዊነት ያለው እንዲሆን የሚያደርግ የፖለሲ አቅጣጫ ተከተለ፡፡ በዚህም ኢህአዴግ ስልጣን ላይ ሲወጣበ 1983 ዓ/ም ከድህንነት ወለል በታች የነበረው ዜጋ 60.5% ሲሆን ይህ አሃዝ በ1993 ዓ/ም ወደ 53.6% በ2008 ዓ/ም ደግሞ ወደ 23.5% ዝቅ ብሏል፡፡ ኢትዮጵያ ፈጣን እድገት በማስመዝገብ ተርታ ላይ ከሚገኙት 10 የዓለም አገራትአንዷ ለመሆን በቅታለች፡፡ በዲፕሎማሲው መስክም ከጊዜ ወደ ጊዜ አበረታች ለውጥ በመታየቱ የአገሪቱ ተሰሚነት በአፍሪቃ ብቻ ሳይሆን በዓለም ደረጃም ከፍ ሊል ችሏል፡፡

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ከሁሉም ዓይነት ጥገኝነት ደረጃ በደረጃ እየተላቀቀች በራሷ መዘውር ብቻ የምትሽከርከር አገር መሆንዋ ለምዕራባውያኑ [ኒዮ‑ሊበራሊስቶች] የሚዋጥላቸው አልሆነም፡፡ ቀደም ሲል የናቁት ኃይል ባልተገመተ ፍጥነት የመጓዝ ዓቅም እያሳየ በመምጣቱ ኒዮญญญญ‑ሊበራሊስቶቹ ፈፅሞ ሊቀበሉት የሚችሉ አልነበረም፡፡ ይህንን ጉዞ የተለያዩ መሰናክሎች በማጥመድ ለማኮላሸትም ሙከራዎች አድርገዋል፡፡ ኢህአዴግ በበኩሉ የእነዚህ መሰናክሎች ባህርይ በሳይንሳዊ መንገድ እያጠና መፍትሄዎችን በማስቀመጥ ሊሻገራቸው ችሏል፡፡ በመሆኑም ኢህአዴግ እነሱ ካሰቡትና ካስቀመጡት በላይ ዓቅም ያለው መሆኑን ሳይወዱ ለመረዳት ተገደዋል፡፡ ከዚህ የተነሳ አንድ ብለው ኢህአዴግ እንዴት ማንበርከክ እንዳለባቸው ለሁለት አስርት ዓመታት በስለላ ድርጅታቸው ሲ.ኣይ.ኤ. አማካኝነት ጥናት ሲያደረጉ ቆይተዋል፡፡ ከጥናታቸው በመነሳትም ኢህአደግን ሊያዳክምና ሊያንበረክክ ይችላል ያሉትን በተለያየ ጊዜያት ሴራ ከማቀነባበር አልቦዘኑም፡፡ በአገር ውስጥ ለዚሁ ሴራቸው የተመቻቸ ሁኔታ ስላልነበራቸው፣ ይህ እስኪመቻች ድረስ በዋነኛነት በኢህአዴግ ላይ ካኮረፈው የዲያስፖራ ማሕበረሰብ ውስጥ ይታዘዘናል ያሉትን ኃይል በመጠቀም ከአገር ቤቱ ፀረ‑ኢህአዴግ እንቅሰቃሴ ጋር በማስተሳሰር ሲሸርቡ ኖረዋል፡፡ በተለያየ ጊዜም ይብዛም ይነስ የቀለም አብዮት ሙከራዎች አድርገዋል፡፡

ኒዮ‑ሊበራሊስቶችና የኢትዮጵያ እድገት ብሄራዊ ጥቅማችንን ይጎዳል ብለው ሁሌም የሚያስቡ አንዳንድ አገራት የኢትዮጵያን ፈጣን እድገት እንቅልፍ ሲነሳቸው ታይቷል፡፡ በዚህ የተነሳም ይህንኑን ለመቀልበስ ያልፈነቀሉት ድንጋይ አልነበረም፡፡ ብዙ ነገር ሞክረው አልሳካ ሲላቸውም ለዚህ እድገት ዋና አንቀሳቃሽ ሞተር የሆነው ኢህአዴግን በማዳከም ሽባ ለማድረግ ቆርጠው ተነሱ፡፡ ለዚህም የመጀመሪያ እርምጃቸው ያደረጉት የኢህኣዴግን ጠንካራ አመራር ማዛባት ነበር፡፡ የኢህአዴግ “የስበት ማእከል’’[1] የሆነውን ህወሓት ላይ ጠንካራና የማያቋርጥ ምት ማሳረፍ ላይ ያለ የሌለ ኃይላቸውን በመጠቀምም ተረባረቡ፡፡ ለዚህ ዓላማቸው ትግበራ የጠንካራውና ታዋቂው መሪ አቶ መለስ ዜናዊ ያልተጠበቀ ህልፈተ‑ህይወት አመቺ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው ይታመናል፡፡ የአቶ መለስ ድንገተኛ ሞት በብዙዎች ዘንድ እንቆቅልሽ የሆነና እስካሁንም ጥያቄዎችን እያጫረ ያለ ክስተት ነው፡፡ የተለያዩ መላምቶች በማስቀመጥ በአሜሪካና የግብፅ የስለላ ድርጅቶች ተቀነባብሮ የተፈፀመ ድርጊት እንደሆነ የሚያምኑ ጥቂቶች አይደሉም፡፡የአሟሟቱ ጉዳይ በዚሁም ይሁን በሌላ ክስተቱ ግን በኢህአዴግ ውስጥ የተለየ ሁኔታ እንዲፈጠር አድርጓል፡፡ ይህ ፍላጎታቸው በመሳካቱ ደግሞ እነዚህ ኒዮ‑ሊበራል የቀለም አብዮቶኞች የተቀረውን የኢህአዴግ ኮር ከጨዋታ ውጭ ለማድረግ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ብዙም ከባድ ሆኖ አልታያቸውም፡፡ስለሆነም ኢህአዴግን በማዳከም የኢትዮጵያን የህዳሴ ጉዞ በሁሉም መስክ ለማሽመድመድ በተለያዩ ጊዜያት ሲሞካክሩት የነበረውን የቀለም አብዮት እቅዳቸው በነውጥ መስመር ይበልጥ በማጠናከር ወደ መረባረብ ገቡ፡፡ ይህ ደግሞ የተሳካላቸው ይመስላል፡፡በመሆኑም፣ አሁን ኢትዮጵያ ከህዳሴው የልማታዊ ዴሞክራሲ ሐዲድ ወጥታ በነውጥ መስመር [shock doctrine] እየተመራች ያለች መሆንዋ ጋሃድ እየሆነ ነው፡፡

አንድን ነገር በተለመደው መንገድ ወደ ተፈላጊው ዓይነት ለማስተካከል አስቸጋሪና አዳጋች በሚሆንበት ጊዜ የነውጥ ሕክምና [shock therapy]የሚባል በሕክምናው ዘርፍ ሲሰራበት ቆይቷል፡፡ በኢኮኖሚውና በፖለቲካውም ወዘተ…ዘርፍ በአንዳንድ ምሁራንና [ሊሂቃን] ፖለቲከኞች ዘንድ እንደ የለውጥ መርህ ለዓመታት ሲንሸራሸርና ሲሰራበት የቆየ ጉዳይ ነው። ይህ ዓይነት መፍትሔ ነባራዊውንና ተፈጥሮኣዊውን ሁኔታ በማናወጥና በማናጋት የሚተገበር ነው። የነውጥ ሕክምና የአሜሪካው ሲ.ኣይ.ኤ.[2]ለእኩይ የስለላ ተግባራቱ፣ ኒዮ‑ሊበራሊስቶች ደግሞ ለኢኮኖሚና ፖለቲካ የበላይነታቸው ሲሉ በከፍተኛ ደረጃ ተጠቅመውበታል፤ ባሰቡት ደረጃ የተሳካላቸው ባይሆንም፡፡ለዚሁ ተግባር ቤተ‑ญሙከራ ተደርጎ የሚወሰደው ሰውና አገር ደግሞ የሚያስከፍለው ጉዳት አደገኛ ከመሆኑም በላይ በተጎጂው ላይየሚተወው ጠባሳ በቃላት ለመግለፅ በጣም አዳጋች ነው። ለነውጥ ሕክምና መሃንዲሶቹ ግን የታካሚው ጉዳይ ጉዳያቸው አይደለም፤ ከዛ የሚያገኙት ውጤትና የሚያግበሰብሱት ትርፍብቻ እንጂ።

አገራችን ኢትዮጵያ የነውጥ ሕክምና ቤተ-ሙከራ መሆን ከጀመረች ሰነባብታለች። ኢትዮጵያን ከተፈጥሮአዊና ነባራዊ መንገዷ አስወጥቶ የነውጥ ሕክምና መሃንዲሶቹ በሚፈልጉት መንገድ ለመምራት ጥረት የተደረገው አሁን ብቻ አይደለም። ለ27 ዓመታት ተደጋጋሚ ሙከራዎች ሲደረጉ ቆይተዋል። እነዚህ ሙከራዎችግን በተለያዩ ጊዜያት፣ በነበረው ጠንካራ የኢህአዴግ አመራር ሊከሽፉ ችለዋል።በዚህ ተስፋ ያልቆረጠው የኒዮ-ሊበራል ኃይል የኢትዮጵያን ከእጁ መውጣትና በከፍተኛ ደረጃ መመንደግ መጀመሯ ይበልጥ እያሳሰበው ስለመጣ የኢህአዴግን ደካማጎን ለዓመታት በመፈተሽና በዚህ ቀዳዳ ሰርጎ በመግባት፣በኢህአዴግ የአመራር አካላት ውስጥ ዝንባሌያቸውን በረቀቀ መንገድ ሲያጠና ከርሟል፡፡ ከነዚህ መካከልምየሱን ተልእኮ በሚገባ ሊያስፈፅሙ የሚችሉ አካላትን በመለየትና በማደራጀት፣በተዘዋዋሪ መንገድ የትግል ስልቶችን በማሰልጠንና በማለማመድ ስራየ ብሎ ተያያዘው።

በዚህ አኳኃን የኒዮ-ሊበራል ተልእኮ ሊያሳካ የሚችል ኃይል መያዙን ካረጋገጠ በኋላየቀለም አብዮት በመለኮስ የኢትዮጵያ የህዳሴ ጉዞን ለመቀልበስ የሚያስችል የዓመፅ እንቅስቃሴ በተመረጡ አካባቢዎች እንደ እሳት ሰደድአስፋፋ። ይህ እንቅስቃሴ ግለቱንጠብቆ እንዲቀጥል ደግሞ ከውጭና ከውስጥ ያደራጀውን የሚዲያ አውታር በሚገባ በማንቀሳቀስ አገሪቱ አይታው ወደ እማታውቀው የፖለቲካ ቀውስ እንድትዝፈቅ አደረገ። ሁኔታዎች በከፍተኛ ሁኔታ በመቀጣጠላቸው አገሪቱ በማያቋርጥ ነውጥ ውስጥ ገባች።ይህ የነውጥ ሁኔታ ኒዮ‑ሊበራሉ ኃይል አገሪቱን በቁጥጥሩ ስር ለማስገባት የነደፈውን ፍኖተ-ካርታ ለመተግበር ምቹ መደላደል ፈጠረለት። በዚህ የተበረታታው የአድህሮት ኃይል ሁሉ ኢትዮጵያ ከዚህ የነውጥ ሕክምና እንዳትወጣም በከፍተኛ ግስጋሴ እየሰራ ይገኛል። በመሆኑም ይህ የነውጥ መስመር በኢትዮጵያ ደረጃ በደረጃ እንዴት እየተተገበረ እንደሆነ ለማሳያ ያህል የሚከተለውን ማስቀመጥይቻላል።

ቀደም ብሎ እንደተገለፀው የኢህአዴግ የአመራር ዓቅም ክፍተት በሚገባ ያጠናው የኒዮ‑ሊበራል ኃይል [የአሜሪካ የስለላ ድርጅት] ከቀደሞው ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ህልፈት በኋላ በከፍተኛ አመራሩይታዩ የነበሩትን አደገኛ አዝማሚያዎች እንዲጠናከሩ የሚያስችል የተዋጣለትስራ እንዲሰራ አድርጓል። በዚህም አቶ መለስ በር ቆልፎ ይዟቸው የነበሩትን የከፍተኛ አመራሩ የግለኝነት አዝማሚያና የጥቅማጥቅም ጥያቄዎችበራቸው መከፈት ሲጀምር ተው ተመለስ የሚል ጠፍቶ አመራሩ ልጓም የሌለው በቅሎ እንዲሆን አድርጎታል። የውጭ ጉዞ የጫጉላ ሽርሽር እስኪመስል ድረስ በሩን ክፍት በመደረጉገሚሱ ዓላማውን ረስቶ ዶላር የሚሰበስብ ነጋዴ የሆነበት፤ገሚሱ ደግሞ የስልጣን ዘመኑን ለማራዘም ዕድል አገኘሁ ብሎ ለቀላሉም ለከባዱም ሕመም ለከፍተኛ ሕክምና ወደ ውጭ አገር እሚሯሯጥበትና ጭራሽኑ በድህነትና በስቃይ ውስጥ ያለውን ህዝብ የረሳበት፤አነስተኛ ቁጥር ያለው ደግሞ በዲያስፖራ ደላላነት ጠቀምያለ ጉርሻ እየተሰጠውና ቃል እየተገባለት የሲ.አይ.ኤ. እና የሌሎች ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች መሳርያ ለመሆን የተመለመለበት ሁኔታ እየተፈጠረ መጣ።

በዚህ ሁኔታ ወደ ኢህአዴግ አመራር ዘልቆ የገባው የኒዮ‑ሊበራል መርዝ በአመራሩ ውስጥ በተራቀቀ መንገድ ስንጥቅ በመፍጠር የስልጣን ሽኩቻ ገዝፎ እንዲወጣ በማድረግ አጧጧፈው፡፡ከዚህ በመነጨ በኢህአዴግም ሆነ በአባል ብሄራዊ ድርጅቶቹ የነበረው የጋራ አመራር [Collective Leadership] ጥንካሬ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየላሸቀ ከፍተኛ አመራሩ መልፈስፈስ ጀመረ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የኢህአዴግ አመራር በተለያዩ ምክንያቶች ስልጣኑን የህዝብ መገልገያ ሳይሆን ለራሱ መጠቀምያ ማድረጉ ተጠናክሮ በርካታ አመራር ወደ ሀብት ማካበት መግባቱ፤ በአገራችን የኪራይ ሰብሳቢነት አደጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋመጥቷል። ሙስና እንደ ሰደድ እሳት መንሰራፋቱን ቀጠለ።ከፍተኛ አመራሩ በአንዱ ይሁን በሌላ መንገድ በሙስናው እጁ ስላለበት [ማኖ በመያዙ] ይህንን ሁኔታ አስመልክቶ መፈክር ከማሰማት በዘለለ ደፍሮና ቆርጦ ሊታገለው አልቻለም።

በዚህ መንገድ ፀረญ-ኢህአዴግ ኃይሎች “ኢህኣዴግን በውስጡ ገብተህ ሽባ ማድረግ’’የሚል እቅዳቸው ተሳካ። በዚህም ኢህአዴግ የሚያገሳግን ደግሞጥርስญ-አልባ አንበሳ ሆኖ ቁጭ አለ።ይህ ከተረጋገጠ በኋላ የኒዮ‑ሊበራሊስቶቹ ቀጣይ ስራኢትዮጵያን በፈለጉት መንገድ ለመዘወር የሚያስችላቸውን ፍኖተ-ካርታ በታማኝነት የሚተገብርላቸው ኃይል ሙሉበሙሉ ስልጣኑን እንዲቆጣጠር ማድረግ ነበር።ይህ ኃይል አስቀድሞ ተጠንቶ የተዘጋጀ ሲሆን እንዴት አድርጎ ወሳኙን ስልጣን ይቆጣጠር የሚለው ጉዳይ ግን መመለስ ነበረበት። ይህም አገሪቱ በነውጥ እንድትታመስ በማድረግ ኢህአዴግ አጣብቂኝ ውስጥ በማስገባት ያዘጋጁትን ኃይል በስመ ለውጥ ወደ መድረክ ማስመጣት ነበር። ለዚህ አመቺ ያልሆነው ነባሩ የኢህአዴግ አመራር ደግሞ ሙሉ በሙሉ ተጠራርጎ ከመድረኩ እንዲወጣ ማድረግ ነበር የዘየዱት። ይህ በውጤት ከተፈፀመ አስቀደመው ያዘጋጁት የለውጥ ኃይል መድረኩን ተቆጣጥሮ ዓላማቸውን እንደሚያሳካም እምነት አሳድረዋል።

ይህ እውን ለማድረግ ነባራዊ ሁኔታውን መጠቀም ወይ ደግሞ የራሳቸው ነባራዊ ሁኔታ አስመስለው መፍጠር [creating reality]ነበረባቸው። ለመሰሪ ዓላማቸው መቀስቀሻ የተጠቀሙበት ነባራዊ ሁኔታም የመልካም አስተዳደርና የስራ አጥነት ችግሮች ሲሆኑ ለዚህ እንደምክንያትና እንደ መነሻ ደግሞ የወያነ፣ የትግራይ የበላይነት አለ የሚል የፈጠራ ነባራዊ ሁኔታ መሳል ነበር። የትግራይ የበላይነት አለ የሚለው የፖለቲካ ዘመቻ የቆየ ቢሆንም አሁን ደግሞ በተፈጠረው አዲስ ሁኔታ ከማንኛውም ጊዜ በላይ ጣራ ነክቷል፡፡ እነዚህ ጉዳዮች በሚዲያና በተለያዩ መንገዶች እንዲቀጣጠሉ በማድረግም የሕግ የበላይነትን የሚጥስ ሁኔታ በመፍጠርና በማበረታታት በአገሪቱ የነውጥ እንቅስቃሴ ለኮሱ፡፡ የነውጥ እንቅስቃሴ'ውን በተሟላ መንገድ ለመተግበር አስቀድመው የእቅድ ተግባሪ ኃይላቸውንና የመንግስትን የመቋቋም ዓቅም ለመፈተሽ የሚያስችሏቸው የሙከራ እንቅስቃሴዎች በተመረጡ አካባቢዎች ማካሄድን ተያያዙት። ይህ የሚያበረታታ ሆኖ ሲያገኙት ደግሞ ግፋ በለው እያሉ ወደ ተሟላ ዓመፅ ገቡ፡፡ይህ ሲሆን አስቀድመው ሽባ ያደረጉት የኢህአዴግ መንግስት የነውጥ እንቅስቃሴውን ለመቆጣጠር ተሳነው። ይህንን ሁኔታ በብቃት ለመቆጣጠር የሚችልና ሲቆጣጠር የነበረው የአገሪቱ የፀጥታና የደህንነት ኃይልም በተለያዩ መንገዶች በማደናቀፍ እንዲገታ ለማድረግ ቻሉ።

በኦሮምያ በተቀሰቀሰው ዓመፅ ሰበብ የውጭ ኃይሎች ያዘጋጁት አዲሱ ጥገኛ ኃይል በክልሉ ስልጣን ለመያዝ ቻለ። ይህ ኃይል ዓመፅን በመጠቀም በኦህዴድ መድረክ ነውጥ በመፍጠር ነባሩን አመራር በዚህ ተደናግጦ ከስልጣን እንዲወርድ አደረገ። በዚህ አኳኋን ሰላማዊና ኢ-ዴሞክራሲያዊ የሆነ የስልጣን ሽግሽግ [መፈንቅል-መንግስት ሊባል ይችላል] ተደረገ። በብአዴን ግን የነበረው ከፍተኛው አመራር ከአዲሱ ተተኪ ተብሎ ወደ መድረክ የመጣና ለነውጥ እንቅስቃሴው ራሱን ያመቻቸ ስለነበር እንደ ኦህዴድ ሌላ ሹምሽር ሳያስፈልገው ነባሮቹንና የነሱ ተከታዮች ናቸው የሚባሉትን አመራሮች “ፀረ-አማራና የህወሓት ተላላኪዎች’’ በማለት ፈርጆ ስማቸውን በማጠልሸት ከየአመራር እርከኑ አንድ በአንድ መጠራረጉን ተያያዘው። አዲሱ ጥገኛ የብአዴን አመራር ቁንጮ ቦታ ይዞ የቆየ በመሆኑ የአመራር መዋቅሩን እሱን በሚመስል መንገድ ዳግም በማደራጀት ወይም በማስፈራራት እየሰለበ ማጠናከርን ስራው ሆነ፡፡ በዚህ ሁኔታ ነባሩ የብአዴን አመራር ራሱ ባሳደጋቸው ውሾች መነከስና መሳደድ ጀመረ።

በኦህዴድ ውስጥ የጠባብ ብሄራዊነት በሽታ በተለይ ከ1997 ዓ/ም ጀምሮ በከፍተኛ ደረጃ ሲብላላ ቆይቶ የኪራይ ሰብሳቢነት አዝመራው በፈጠረለት ለም አፈር ፖለቲካዊ ብክለቱ ጣራ ነክቷል፡፡ በብአዴን ደግሞ አማራ ተገፍተዋል፣ ተዋርደዋል የሚል የሊሂቃን የውስጥና የውጭ ግፊት ተጨምሮበት ከላይ እስከ ታች መዋቅሩ የተንሰራፋው ኪራይ ሰብሳቢነት ድርጅቱን የትምክህት መጫወቻ ሜዳ አድርጎታል፡፡ በሁለቱም ድርጅቶች አብዮታዊ ዴሞክራሲ በጠባብነትና በትምክህት አረሞች ተወሮ መፈናፈኛ አጥቷል፡፡ በኦህዴድና በብአዴን ውስጥ ለውስጥ ሲብላላና በኔትዎርክ መልክ ሲደራጅ የቆየው ኃይል ራሱን እያጠናከረ “ኦሮማራ’’ በሚል ስያሜገሃድ እየሆነ መጣ። እንዲያብሎም “እኛ ብዙሓን ነን፣ በውሑዳን አንገዛም፣ እኛ ነን ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን ያለብን’’ በሚል በኢህአዴግ ታሪክ ያልተለመደ አዲስ መፈክር ይዞ ብቅ በማለት የበላይነት ለመያዝ ጥረት አደረገ።

የደኢህዴን አመራር ቀድመውኑ አብዛኛው በፖለቲካ ትግሉ ያልበሰለ፣ የብሄረሰቡን ታርጋ መያዣ በማድረግ ወደ ስልጣን የተቆናጠጠ ነው፡፡ ባካሄዳቸው ጉባኤዎቹ ሳይቀር ለዚሁ ዓላማ ተብሎ ሚስጢራዊ ምርጫ እንኳ አካሂዶ የማያውቅ ነው የነበረው፡፡ ደኢህዴን ውስጡ ሳይጠና በስልጣን ትርፈ‑ጋራ ተጠፍጥፎ የተፈጠረ ውሁድ ድርጅት ነው፡፡ ስለሆነም ለክፉ ቀን ደራሽ ሊሆን ቀርቶ ራሱንም መታደግ አልቻለም፡፡ከፍተኛ አመራሩ ከፖለቲካዊ ብስለቱ ማነስ ባልተናነሰ በኪራይ ሰብሳቢነት በመበከሉ፣ ሁኔታዎችን በሆዱ ልክ እያሰበ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ ተጨባጭ የፖለቲካ ምስቅልቅሉ በሚገባ ሳይረዳው፣ ሳይወድ ዝም ብሎ ተጓዥ የሆነበት ሁኔታ ተፈጠረ፡፡

የህወሓት አመራርም እንደ ሌሎቹ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች በኪራይ ሰብሳቢነት በሽታ ከተበከለ ቆይቷል፡፡ ይህንን በሽታ ይዞ ለመቀጠል ግን እንደ ሌሎቹ አካባቢዎች ቀላል አልነበረም፡፡ የትግራይ ሕብረተሰብና አብዛኛው ታጋይ ከፖለቲካ ተሞክሮው ሲታይ ይህንን የሚሸከም ትከሻ አልነበረውም፡፡ ስለሆነም ለዚህ የሚሆን አስቻይ ሁኔታ ለመፍጠር ሲል አመራሩ በተከተለው መንገድ ከሌሎቹ የኢህአዴግ ድርጅቶች በባሰ በህወሓት ፀረ‑ዴሞክራሲ ምህዳር ገንግኖ የታየበት ሁኔታ ሊከሰት ችሏል፡፡ ሆኖም በዚህ መቀጠል ስለማይቻል አመራሩ በሁኔታዎች አስገዳጅነት በዳግም ጥልቅ ተሃድሶው ይህንን ለመገምገምና ለማስተንፈስ ሞክሯል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ህወሓት ገራገሩ ግንራሱን ብቻ እያነበበ እኔ “በጥልቀት”ገምግሚያለሁና ሌሎቹ እህት ድርጅቶችም በሂደት ራሳችውን በግምገማ ያጠራሉ ብሎ በተስፋ ሲጠብቅ ጊዜ መሸበት። የድርጅቱ ከፍተኛ አመራር ዝቅጠቱ ከሌሎቹ እህት ድርጅቶች ያልተናነሰ፣ እንደ ነባር አመራር ሲታይ ደግሞ የባሰ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በጥልቀት ችግሬን ገምግሜያለሁ ቢልም [ከሌሎቹ ድርጅቶች ራሱን በማነፃፀር እንጂ አሟልቶ እንዳላጠራ ልብ ይሏል] ሁኔታዎችን በጥልቀት የተረዳ አልነበረም፡፡ በዚህም ህወሓት በኢህአዴግ ግምገማ ወቅት በአፈጮሌዎቹ አመራሮች ክፉኛ ተሸወደ።

ይሁን እንጂ በኢህአዴግ የግምገማ መድረክ ጠንካራ ትግል ያደረገው ህወሓት የሊቀመንበርነት ምርጫ በሚካሄድበት ወቅትም ገንቢ ትግል አድርጓል። በተደረገው ትግል ለግንባሩ ብቃት ያለው ሊቀመንበር ለመምረጥ ያግዝ ዘንድ መመዘኛ ነጥቦች እንዲቀመጡ የግንባሩ ምክር ቤት ተወያይቶ ስምምነት ላይ ደርሷል [አንዱ በገርነቱ፣ሌላው በብልጠቱ ይሏል እንዲህ ነው]። ይሁን እንጂ ከውጭ ሆኖ ለሚታዘብ ሰው ግን መመዘኛው ከብሄራዊ ድርጅቶቹ የአመራር ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ሲታይ እንዴት ሊሰራ እንደሚችል ግራ የሚያጋባ ነበር። “ከዝንጀሮ ቆንጆ ምኑን ይመራርጡ’’ የሆነ ነገርም ነበር። በተጨባጭም መመዘኛው ለብቻ፣ ምርጫው ለብቻ ሆነውውስጥ ለውስጥ በውጭ ኃይሎች የተመለመለው የነውጥ ኃይል አስቀድሞ በዘረጋው ኔትዎርክ አማካኝነት የበላይነቱን ይዞ ወጣ። የምርጫ ተውኔቱ ትራጀዲ አይሉት ኮሜዲ በዚህ አበቃ፡፡ በዛ በእኩለ ሌሊት፣ ምርጫው እንደተጠቃለለ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ለአዲሱ ተመራጭ ሊቀመንበር ከምዕራባውያኑ ኤምባሲዎች የእንኳን ደስ ያለህ መልእክት ከመቅፅበት እንደጎረፈለትም ብዙዎች ይናገራሉ።በህወሓት በኩል ግን[በቁጭት ለስር ነቀል ለውጥ ራሱን ባለማዘጋጀቱ ምክንያት]የነገሮች አቅጣጫ ትክክል አለመሆኑና ግልፅ ያልሆነ ችግር በኢህአዴግ ውስጥ እንዳለ ዘግይቶ የገባው ይመስላል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢህአዴግ ከአጠቃላይ የሁኔታዎች ግምገማ በመነሳት መፍትሔ ያላቸውን አቅጣጫዎች በመንደፍ፣ እነዚህን እንደየሁኔታው በቅደም‑ተከተል ለመተግበር የጋራ ስምምነት ደርሷል። የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ከህዝቡ ጋር በቀጥታ በመወያየት መፍትሔ ማበጀት፣ የወጣቶችን የስራ አጥነትና የተጠቃሚነት ጉዳይ ችግሮች የሚፈታ መርሃ-ግብር መቅረፅ፣ የፖለቲካዊ ምህደሩን በሚገባ ማስፋት፣ በመንግስት አስተዳደር ችግር ለተቃውሞ ወጥተው በተለያየ ምክንያት የታሰሩትን መፍታት [በመንግስት የመልካም አስተዳደር ችግር ምክንያት በተለያየ መንገድ ለእስራት የተደረጉት ዜጎችን ከቀንደኛ ወንጀለኞች በመለየት እንዲፈቱ ማድረግ] ወዘተ… የሚሉት ጉዳዮች በአጠቃላይ ስምምነት የተደረሰባቸውና ግልፅ የሆነ የመተግበርያ አቅጣጫ የተቀመጠላቸው ነበሩ።

አዲሱ ወደ መድረክ የመጣው አመራር ግን እንዚህ ጉዳዮች በተቀመጠላቸው ትክክለኛ መንፈስና አቅጣጫ፣ የሕግ የበላይነትን በሚያረጋግጥ መልኩ፣ ሰላምና መረጋጋት በሚያመጣ አኳኋን ለመፈፀም ዝግጁ አልነበረም፡፡ ዝግጅቱ ሲታይ በተቃራኒው መንገድ ነበር፡፡ዕንቅፋት ይፈጥሩብኛል ብሎ በሌላ ረድፍ የፈረጃቸው ነባር የኢህአዴግ አመራሮችን በተለይ የህወሓትን በሚያንበረክክና በሚያጣጥል መንገድ፣በምእራባውያን የተቀነባበረውን የቀለም አብዮት ዳር በሚያደርስና የነውጥ እንቅስቃሴውን በሚያጠናክር መንገድ ለመተግበር ቆርጦ ተነሳ። ከዚህ በመነጨም፡-

-   በስመ የፖለቲካ ምህዳር ማስፋትና እስረኞችን መፍታት አሉ የተባሉ ወንጀለኞችንና ሽብርተኛ ግለሰቦችን ከእስር ነፃ አደረገ። ይባስ ብሎም ሽብርተኛ የነበረው መንግስት ራሱ ነው በሚል በአደባባይ በይፋ ተናገረ።

-   የትጥቅ ትግል ሲያካሄዱ የነበሩ ድርጅቶች ትጥቃቸው ሙሉ በሙሉ ሳይፈቱና ግልፅነት በጎደለው ድርድር ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡና እንዲንቀሳቀሱ ሁኔታዎችን አመቻቸ።

-   በፖለቲካ ምሕዳር ማስፋት ሰበብ ከሕገ-መንግስቱ ጋር የሚጋጩ ንግግሮችና ተግባራት በአደባባይ እንዲናኙ ተደረገ።ብሄር‑ተኮር ስድቦች፣ በሕገ-መንግስቱና በአዋጅ ዕውቅና ያልተሰጣቸው ባንዴራዎችን ማውለብለብ፣ ሌሎች አፀያፊ ስድቦችና ተግባራት መፈፀም ወዘተ…የእለት ተእለት ክስተቶች መሆን ጀመሩ፡፡

-   ለአመፅና ሕገ-ወጥ ተግባራት ማበረታታት፣ እውቅና መስጠት፣ የትግል ስልት አድርጎ እስከ መውሰድና ማወደስ የደረሰ ተግባር በከፍተኛ አመራሩ ሳይቀር የተለመደ ደጋፊን የማባዣ ዘዴ እየሆነ መጣ።

-   በውስጥና በውጭ ተቃዋሚ ኃይሎች ሲሰራበት የቆየውን በአገሪቱ ለተፈጠሩት ችግሮች የአንድ ድርጅትና የአንድ ብሄር የበላይነት ያመጣቸው አድርጎ የመሳል እንቅስቃሴ አዲሱ አመራርም አጠናክሮ ቀጠለበት፡፡

-   የፌደራል ተቋማት የአንድ ድርጅትና የአንድ ብሄር እንደሆኑ አድርጎ በመሳል በሕብረተሰቡ ዘንድ አመኔታ እንዳይጣልባቸው የሚያደርግ አካሄድ ተጠናክሮ ቀጠለ።

-   አዲሱ አመራር የሕግ የበላይነት ለማረጋገጥ የተዋቀሩ ተቋማትን ሽባ በማድረግ፣ ስልጣኑን አለአግባብ በመጠቀም የተቀመጡ አዋጆችና አሰራሮች ተግባራዊ እንዳይሆኑ ሽፋን በመስጠት ነውጠኖችን ማበረታታት ተያያዘው፡፡ ሕገ‑ወጦችን በማጀገን ለሕግ የበላይነት የሚንቀሳቀሱትን ማብጠልጠልና በተቃራኒው መወንጀል ስራየ ብሎ ገባበት።

አዲሱ አመራር የአገሪቱ ተቋማት እንዲልፈሰፈሉና የነውጥ እንቅስቃሴው ሃይባይ እንዳይኖረው ፖለቲካዊና መንግስታዊ አሰራሮችን በማሽመድመድ ሁሉም ነገር እሱ በመረጠው መንገድ እንዲጓዝ በከፍተኛ ፍጥነት ተረባረበ። ለዚህድርጊቱ ይቃወመኛል ወይ ደግሞ ዕንቅፋት ይደቅንብኛል ያለውን የቀድሞ አመራር የፖለቲካና የኢኮኖሚ ዓቅም ለማሽመድመድ በረባ ባልረባ ምክንያት ሰበብ በማፈላለግ ማሳሰርና በማስፈራራት ማሳደድ ስራየ ብሎ ተያያዘው። ለዚህ እንዲመቸውም የህዝቡን ስነ‑ልቦና በመስለብ ምልኣተ ህዝቡን በተለይ የተማረውን ክፍል ማደናገሩን አጦፈው። ወጣቱን በስሜት መንዳት ቀጠለበት። የህዝቡን ስስ ብልቶች በመነካካት አገሪቱን እንደፈለገ መዘወር ጀመረ።

በኦሮሚያና አማራ ክልሎች በፈጠረው የኦሮማራ ኔትዎርክ አመራሩን አስተማማኝ ደጋፊነው በማለት ፈርጆ፤ የደቡብ ክልልን ግን ለነውጥ ኃይሉ አስተማማኝ ደጋፊ ሊሆን የማይችልና በማንኛውም ወቅት ዞሮ ዞሮ ከህወሓት ጎን ሊሰለፍ ይችላል የሚል ግምት በመያዝ ይመስላል ክልሉን ቶሎ ብሎ ማዛባት የመጀመሪያ እርምጃው ሆነ፡፡ በዚህም ወደ ክልሉ የነውጥ ኃይሎች በማስረግ ትርምስ በመፍጠር የነበረው ነባር አመራር እንዲቀየር ግፊት አደረገ። በዚህ ግርግር የተጀመረው እንቅስቃሴ ደግሞ የደቡብ ክልል ብትንትኑ እንዲወጣና በአከባቢው አዲስ ነባራዊ ሁኔታ እንዲፈጠር አስችሏል። በዚህ የተነሳ ደኢህዴን እንኳንስ ሌሎች ሊያግዝና ሊደግፍ ቀርቶ ራሱንም ለማቆየት የተቸገረበትና አሁን አሁን ደግሞ ለነውጡ ቁጥር ከማብዛት ባለፈ ከጨዋታ ውጭ የሆነበት ሁኔታ በግልፅ ይታያል። በደቡብ ክልል የሚገኙ ብሄረሰቦች ከሌሎች የታጠቁ ኃይሎች የሚሰነዘረባቸውን ጥቃት መቋቋም ተስኗቸው ክልሉ የተፈናቃይ ብዛት በገፍ የሚታይበት ሆኗል።

ደቡብ ክልል የማተራመስ እቅዱን ካሳካ በኋላ ከዚህ በመቀጠል አዲሱ አመራር ትኩረቱን ወደ የአጋር ድርጅት ክልሎች በማዞር እነዚህ ክልሎች ደረጃ ብደረጃ በማሽመድመድ ለነውጥ ኃይሉ ዕንቅፋት የማይሆኑበት ሁኔታ መፍጠር ነበር።በዚህ መሰረት በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ትንኮሳውን በመጀመር፣ ይህንን ትንኮሳ ተጠቅሞ ቤተክርስትያናትን የሚያቃጥልና ሰዎችን የሚገድል ቡድን አደራጅቶ ዘግናኝ ሁኔታ እንዲፈጠር ለማድረግ ቻለ። ይህ ሁኔታ በሚዲያ እንዲቀጣጠል በማድረግ የሶማሌ ክልል አመራርን ከሌላው የክርስትና አማኝ የበዛበት አካባቢ በመነጠል ኃይል በተቀላቀላበት መንገድና በግፊት የአመራር ሹምሽር እንዲካሄድና ታማኝ የተባሉ አመራሮች ወደ መድረክ እንዲመጡ አደረገ። በሌሎቹ የአጋር ድርጅቶች ክልሎች ደግሞ በቀላል ግፊትና ተደጋጋሚ ማስጠንቀቅያ የነበሩት ነባር አመራሮች የለውጡ ደጋፊ ናቸው በተባሉት እንዲቀየሩ ተደርጓል። በአጠቃላይ ሲታይ አሁን ሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች ከትግራይ በስተቀር የሕግ የበላይነት ሊያስጠብቅ የሚችል አመራርና ብቃት ያለው ተቋም የሌላቸው የተሽመደመዱ ሆነዋል። በዚህም አዲሱ አመራር የፈለገውን የነውጥ እንቅስቃሴ ለማካሄድና ለማስቀጠል ይችል ዘንድ የተመቻቹ ሆነዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በአንፃሩ ደግሞ ከአጋር ክልሎች የባሰ ችግርና ስርዓት አልበኝነት የታየባቸው፣ የከፍተኛ አመራሩ ሳይቀር ግፋበለው እያለ ሕገ-ወጥነትን በሚያጠናክርባቸው ክልሎች [አማራናኦሮሚያ]አመራሩ እንኳንና እርምጃ ሊወሰድበት ቀርቶ በትንሹም ቢሆን ሊወገዝ አልተሞከረም። ይባስ ብሎም አመራሩ እርስበርሱ የለውጥ ሐዋርያ እየተባባለ ሲወዳደስ ታይቷል፡፡ ለምን ቢባል የነውጥ እንቅስቃሴውን በተፈለገው መንገድና ፍጥነት እየመራ ስለሆነ። ነውጡን ሊቃወሙ ይችላሉ፣ ዞሮዞሮ ወደ ነበረው ትክክለኛ ሕገ-መንግስታዊ ስርዓት ሊያዘነብሉ ይችላሉ የተባሉት ብሄረሰቦችና ህዝቦች ልክ የዘር ማጥፋት ዘመቻ በሚመስልመልኩ እየተቀጠቀጡ እያለ የፊደራል መንግስቱ ሆነ የሁለቱ ክልል መንግስታት ምንም ትንፍሽ አላሉም። ይባስ ብሎም ሁኔታውን እንደ ተራ ግርግር ወስደው ከማጣጣል በዘለለ የሶስተኛ ወገን [ያው የፈረደበት ወያነ]እጅ እንዳለበት በማስመስል ህዝቡን ለማደናገር ያልሸረቡት ነገር የለም።

የአዲስ አበባን ጉዳይ ለመመለስ የሚያስችል ሕግ ብሕገ-መንግስቱ ተቀምጦ እያለ አጀንዳውን ከማንም በላይ በማጦዝና በአዲስ አበባ አዋሳኝ አከባቢዎች ሁከትና ግርግር በመፍጠር፣ በስመ ሕገ-ወጥ ይዞታና አረንጓዴ ልማት በሚል ሆን ተብሎ ሰዎችን በማፈናቀል የተለየ ነባራዊ ሁኔታ ለመፍጠር ርብርብ ተደርጓል። በተለያዩ የአገሪቱ መንደሮች እየታዩ ያሉ የእሳት ቃጠሎዎችም በርካታዎቹ ሆን ተብሎ የተለየ ነባራዊ ሁኔታ ለማመቻቸት የተቀነባበሩ እንደሆኑ ገሃድ እየሆነ መጥቷል፡፡ ከፌዴራል መንግስት ጀምሮ ከሞላ ጎደል በሁሉም ክልሎች የሕግ የበላይነት ተንዶ ስርአት አልበኝነት በመንገሱ ተጠያቂነት የሚባል ነገር ደብዛው ጠፍቷል፡፡ በመሆኑም በየደረጃው ባለው ቢሮክራሲ ለተሰገሰጉት ሙሰኞችና የውጭ ደላሎቻቸው እንዲሁም በየአካባቢው እንደ አሸን ለፈሉት የመንደር ጎረምሶች እንዳሻቸው እንዲፈነጥዙ ጊዜው ምቹ ሆኖላቸዋል፡፡ በሕብረተሰቡ ላይ ግን በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ የደህንነት ስጋት አንዣቧል፡፡

ህዝቡን የሚያስቆጡ የተለያዩ እርምጃዎች ሲወስዱ፣ ከዚህ የመነጨ ብዙ ጥፋትና ውድመት ሲደርስ ጣቶች ወደ ጠቅላይሚኒስትሩ እንዳይቀሰሩና ነውጡ ይዞት የተነሳውን ተልእኮ በአጭሩ እንዳይቀለበስ በማሰብ ድራማዎች በተደጋጋሚ ሲሰሩ ታይቷል፡፡ ለእነዚህ የጥፋት ድርጊቶች እቅድ እርሳቸው ባሉበት ተነድፎ ፈፃሚ ከተዘጋጀ በኋላ ሰውየው ወደ ውጭ አገር በሚወጡበት ወቅት ድርጊቶቹ እንዲፈፀሙ ተደርገዋል። ወደ አገር ቤት ሲመለሱ ጥያቄ መነሳቱ አይቀርምና ድራማው ይቀጥላል፡፡ አልሰማሁም ነበር፣ እኔ አልወሰንኩም የማለት አባዜ በተደጋጋሚ ተስቶውሎባቸዋል። ይሁን እንጂ ነገሩ ሆን ተብሎ ታቅዶ የተፈፀመ መሆኑ የሚያሳየው ድርጊቱን ለመቀልበስ ፍላጎትና ተነሳሽነት የሌላቸው መሆኑ ነው። ድርጊቱ በእሳቸው ይሁንታ እንደተፈፀመና በደረሰው ጉዳት ምንም ነገር እንደማይሰማቸው ከፊታቸውና ከቃል አቀባዮቻቸው አንደበት ያሳብቅባቸዋል።

ከዚህ በተጨማሪ በአገራችን እየታየ ያለው ሌላው ክፋት የመንግስት መዋቅር ሆን ተብሎ እንዲዳከም መደረጉ ነው። ይህ የተፈፀመው ግን እንደወረደ ሳይሆን በዘዴ [systematic] ነበር። ለዚህ ጥሩ ሽፋን የሆነው የሴቶች ተሳትፎና የወጣት አመራር ወደ መድረክ ማምጣት የሚል እሳቤ ነው። ይህ ላይላዩን ሲታይ ጥሩ ለውጥ የሚመስለው በተጨባጭ ግን ቢሮክራሲውን ከነበረው የባሰ እንዲዳከም አድርጎታል። ይህ ደግሞ የነውጥ አመራሩ በማንኛውም ተቋም ተገዳዳሪ ኃይል ሳይኖረው ያሻውን ለማድረግና የነውጥ እንቅስቃሴውን ለማስቀጠል እንዲያስችለው የሰራው ነው። ከፌደራል በተጨማሪ በክልሎችም በተለያዩ ወንጀሎች ተከሰውና ተፈርዶባቸው እስርቤት የቆዩ የአገር ክህደት ወንጀል የፈፀሙቱ ሳይቀር፣ ብስርዓቱ የቆየ ስር-ሰደድ [chronic] ቅሬታ ያላቸው በቅርቡ የተፈቱ ሰዎች የክልል አመራሮች ተደርገው የተሾሙበት[ይባስ ብሎም በፀጥታ መዋቅር ውስጥ የተመደቡበት]ሁኔታ ታይቷል። ይህ ድርጊት ደግሞ ለለውጥ ሳይሆን ለነውጥ የተመቸ ሁኔታ ሊፈጥር ችሏል።

አዲሱ አመራር በፈጠረው ምስቅልቅልና ሆን ብሎ በፈጠረው ስርዓት አልበኝነት የኮንትሮባንድ ንግድ ከመቼውም ጊዜ በላይ ተጣጥፏል። ከዚህ አልፎም የተለያዩ ዓይነት የጦር መሳርያዎችና ጥይቶች [በይፋ ፈቃድ የተሰጠ ይመስል] በገፍ ወደ አገሪቱ የተለያዩ አከባቢዎች ገብተዋል። በአማራ ክልል ደግሞ የጦር መሳርያዎች ገበያ ልክ እንደ እህል ገበያ ደርቶ ለዓመታት ቆይቷል። የአማራ ክልል አንዳንድ አመራሮችም ይህንን ሁኔታ ሲያበረታቱ ቆይተዋል። በሌላ በኩል መንግስት ስፖንሰር ያደረገው እስኪመስል ድረስ በርካታ የመንግስትና የግል ባንኮች በጠራራ ፀሓይ ተዘርፈዋል፡፡

አዲሱ አመራር በፖለቲካ ረገድ የነውጡ እንቅስቃሴን ወደ አንድ ደረጃ አድርሶታል፡፡ አሁን የቀረው የልማታዊ መንግስቱን የኢኮኖሚ ዓቅም በመስበር የነውጥ መስመሩን ሙሉ በሙሉ ማሳካት ይሆናል። በዚህም በኢኮኖሚ ሴክተሩ የነውጥ መስመሩን የሚያሳካ የተሟላ እርምጃ ለመወሰድ እንዲመቸው ደረጃ በደረጃ የተለያዩ ስራዎችን በመስራት ላይ ይገኛል። ስርዓት አልበኝነትን በማበረታታት በኢኮኖሚ ተቋማት ላይ ጉዳት እንዲደርስ ማድረግ፣ ጉዳት ከደረሰ በኋላ ደግሞ በዝምታ ማለፍ ይታያል። መንገዶች እየተዘጉና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴው እየተዳከመ እያዩ ምንም መፍትሔ አለማድረግና በዝምታ መመልከት የተለመደ ተግባር ሆኗል። ኢኮኖሚው ሄዶ ሄዶ መናጋቱና ተንገራግጮ መቆሙ ስለማይቀር የነውጡ አመራር ቀደም ብሎ ይፋ ያደረግውንና ሁኔታዎች እስከሚመቻቹለት ድረስ በይደር የያዘውን ትላልቅ የአገሪቱ የመንግስት የልማት ድርጅቶችወደ ግሉ ሴክተር በማዛወር ስም የልማታዊ መንግስት ኢኮኖሚ ሙሉ በሙሉ ለማሽመድመድ በመጠባበቅ ላይ ነው። የዓለም ገንዘብ ድርጅትም ይህንኑ በመረዳት በአዲስ አበባ መሽጎ ትላልቆቹን የኢትዮጵያ የልማት ድርጅቶች ለማሻሻጥ አሰፍስፎ ይገኛል፡፡ የጠቅላይ ሚንስትሩ አማካሪዎች በዓለም ባንክና መሰል ዓለም አቀፍ ተቋማት ሲሰሩ የነበሩ በመሆናቸው [በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የኒዮ‑ሊበራልና የሲ.አይ.ኤ. ጉዳይ አስፈፃሚ መሆናቸው የማይቀር ነው] ምእራባውያኑ ጥቅማቸውን ለማስፈፀም ቀላል ይሆንላቸዋል፡፡ ኢኮኖሚው ተሸመድምዶ አገሪቱ ወደ ከፍተኛ ቀውስ ከገባች በኋላ ለምን እንዲህ ተደረገ ብሎ የሚጠይቅ ይሁን የሚሞግት ብዙ ሰው ስለማይኖር፣ በዚህ ጊዜ አመራሩ የፈለገውን የኢኮኖሚ እርምጃ ለመውሰድ የሚቸገር አይሆንም።

እንዲህ በተመሳቃቀለ ሁኔታ ሰዎች በሰከነ አእምሮና በተለመደው መንገድ ለማሰብና ነገሮችን ለማየት እንዲሚችገሩ የታወቀ ነው። እንዲህ ባለ መያዣና መጨበጫ በሌለው ሁኔታ ነገሮች መስመር በማስያዝ ተጠያቂነት ለማረጋገጥ እጅጉን አስቸጋሪ ያደርገዋል። ስለሆነም እንዲህ ግራ በተጋባ አገር ነውጠኖች የፈለጉትን ለመወሰንና ለማስፈፀም ዕድል ይከፍትላቸዋል። ነገሮች ወጥንቅጣቸው በወጡበት ሁኔታ ሰው የሚጎዳውን ውሳኔ ሳይቀርነገ መፍትሄ ያመጣ ይሆናል በሚል እንዲቀበለው ይገደዳል። የጨነቀው እርጉዝ ያገባል እንዲሉ፣ አማራጭ ያጣ የሆነውንነገር እንደሚመርጥ ሁሉ አሁን እየታየ ያለውም ይህንኑ የሚያረጋግጥ ነው። በእንደዚህ ሁኔታ ምክንያታዊነት፣ እሴት የሚባል ነገር ቦታ አያገኝም።

በነውጥ ይሁን በሌላ መንገድ ነባራዊ ሁኔታው አንዴ ከተቀየረ ዳግም ቀድሞ ወደ ነበረበት ለመመለስ ፍፁም አዳጋች ይሆናል፣በቃ ተለወጧልና። ከዚህ በኋላ ለአዲስ ነባራዊ ሁኔታ የሚሆን ወይ የሚስማማ ሌላ መፍትሔና አቅጣጫ ነው ወደ ማፈላለግ የሚገባው። አንዴ በተሟላ መንገድ ከተቀየረና ከፈራረሰ ጥገና ብሎ ነገር የለም፣ እንደ አዲስ መስራት እንጂ። ለዚህ ስለሚያመቸው ነው አዲሱ አመራርም በአገሪቱ ሁሉም ነገር እየተናደ እያለ አይቶ እንዳላየ፣ ሰምቶ እንዳልሰማ በዝምታ ማለፉን የመረጠው። ሄዶ ሄዶ ደግሞ ጊዜው ሲደርስ በፈራረሰው ምትክ ሌላ ስርዓት ለመገንባት መሯሯጡ አይቀሬ ነው። ይህ እንደሚያደርግም ፍንጭ እየሰጠ ነው። የ2012 አገራዊና ክልላዊ ምርጫ ሆን ተብሎ ዝግጅቱን በማጓተትና ምክንያቶችን በመደርደር ለሌላ ጊዜ ለማስተላለፍ እየተሸረበ ያለው ተንኮል የዚሁ አንዱ ማሳያ ነው፡፡

አዲሱ አመራር የነውጥ መስመር ተከታይና አስፈፃሚ መሆኑ እስካሁን ሲተገብራቸው የቆየና እየቀጠሉ ያሉ ተግባራት ቁልጭ አድርገው ያሳያሉ። የየትም አገር መንግስት ዴሞክራሲያዊ  ይሁን ኢ-ዴሞክራሲያዊ ዋናው ስራው የአገሪቱን ሕግ በማስጠበቅ በአገሪቱ የተረጋጋ ስርዓት እንዲኖር ማድረግ ነው። በአገራት ግርግር የሚፈጠረው በተቀናቃኞች መሃል በሚደረግ ሽኩቻ እንጂ መንግስት የራሱን ስርዓት ወደ ህውከትና ብጥብጥ አያስገባም፡፡ለተቃዋሚ ኃይሎች የሰላም ጥሪ በማድረግ ወደ አገር ቤት አስገብቶ ሲያበቃ ራሱ ግርግር የሚፈጥር መንግስት ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም። መለስ ብለን የኢትዮጵያ ታሪክ ስንቃኝም ያለፉት መንግስታት ደርግን ጨምሮ ስርአት አልበኝነት ሲቆጣጠሩ እንጂ ሲያበረታቱ አልታየም፡፡ ኢህአዴግም እንኳንና ስልጣን ይዞ በትጥቅ ትግል ወቅትም ቢሆን ለስርአት አልበኝነት ቦታ አልነበረውም፡፡ ስርአት አልበኞችን የሚያሳድድ ድርጅት ነው የነበረው፡፡ስለዚህ ለምንድነው ይህ አዲስ አመራር [የለውጥ ኃይል ነኝ ባይ] የተለየ ሆኖ የሚገኝው? የሚልጥያቄ አንስተን ወደ መፈተሽ ስንገባ ሁኔታው የበለጠ ግልፅ ይሆንልናል።

አዲሱ አመራር አገሪቱን “በመደመር እሳቤ’’ አረጋግቼ ከጥፋት አድናታለሁ ብሎ ስብከት አይሉት መፈክር ይዞ ቢነሳም ዋናው ግቡ ነባሩን አመራር አሸንፎ ስልጣኑን መቆጠጣር እንጂ ይህ የሚባል ፖለቲካዊ ራእይ አልነበረውም፡፡ ይህንን ስግብግብ ጥማቱን በሚገባ የተረዱት ከኋላ ሆነው የሚዘውሩትና የሚገፉት ኢትዮጵያን ማዳከም ዓላማቸው ያደረጉ የውጭ ኃይሎች ናቸው፡፡ ከዚህ በመነሳት በለኮሰው በመንጋ የሚነዳ፣ ራእይና መርህ አልባ እንቅስቃሴ አገሪቱ ከድጡወደ ማጡ ገብታለች። በአስቸˆይ ጊዜ አዋጅ ፈርመያዝ ጀምሮ የነበረው የአገሪቱ ሰላም አዲሱ አመራር ሆን ብሎ አዋጁን በማንሳት ግጭቶች እንዲበራከቱ አድርጓል። ይህም ለስልጣን ያበቃው የነውጥ ኃይል እጁና እግሩ በሕግ ታስሮ ወደ ማኩረፍ ከገባ ገና ያልተደላደለው አዲሱ አመራር አደጋ ላይ እንደሆነ ገብቶታል፡፡ በአንድ በኩል ለራሱ ሲል ሁሉም ነገር ለመቆጣጠር ይፈልጋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሊያሳካ የፈለገውን የውጭ ኃይሎች ተልእኮ እንዳይከሸፍበት የተጠቀመበትን የነውጥ ኃይል ድጋፍ ይፈልጋል፡፡ በዚህ ምክንያት ራእይ አልባው አመራር አጣብቂኝ ውስጥ ስለገባ አንዱን ለመምረጥ ተገደደ። ስለሆነም አንዳንዶቹ ከቁጥጥሩ ውጭ በመሆናቸው ቢከፋም ቅሉ ነውጠኞችን መደገፉንግን መረጠ፡፡በዚህም ቱባ ቱባ የመንግስት ባለስልጣናት ሳይቀሩ የነውጥ ኃይሉን እያሞካሹ ግፋ በለው ሲሉት በተደጋጋሚ ተደምጠዋል።

ራእይ አልባው አመራር የመንግስት መዋቅርን ሽባ ለማድረግና ርካሽ ተወዳጅነት ለማግኘት ሲል መንግስት አሸባሪ ነበር በማለት ራሱን የዴሞክራሲ ሐዋርያ ለማድረግ ቢሞክርም ቅሉ በተገላብጦሽ ግን ራሱ በከፋ መልኩ አሸባሪ ሆኖ ተገኝቷል። ምናልባት ያለፈው አመራር ግለሰቦችን ወይ ቡድኖችን ሊያሸብር ይችል ይሆናል። የአሁኑ አዲስ አመራር ግን ብሄር ብሄረሰቦችንና ህዝቦችን በጀሌዎቹ አማካኝነት በማሸበር ላይ የሚገኝ ነው። ማሸበርብቻም ሳይሆን አገሪቱ ከዚህ በፊት አይታው በማታወቀው የእርስ በርስ ግጭቶች እንድትዘፈቅ በማድረግ በሺዎች የሚቆጠሩ ንፁሃን ዜጎች ህይወታቸው በአሰቃቂ ሁኔታ የተቀጠፈበት፣ ከ3 ሚልዮን በላይ ዜጎች ደግሞከቀያቸው የተፈናቀሉበት ሁኔታ አስተናግዳለች። ይባስ ብሎም አዲሱ አመራር ይህ ሁኔታ በዓይኑ እያየ እንዳላየ የሚያልፍበት፣ እየሰማ እንዳልሰማ የሆነበት፣ በለውጡ ተደምረናል ባዮቹ የአገሪቱ ሚዲያዎች የህዝቡን ሰቆቃ እንዳይዘግቡ በራቸው የቆለፉበትና በተፃራሪው ደግሞ የነውጡ እሳት አቀጣጣይ የሆኑበት ሁኔታ በግልፅ ታይቷል።

በሌላ በኩል ደግሞ ለነውጡ ስኬት ሲባል የኢትዮጵያ ህዝቦች የጋራ እሴቶችና አመለካከቶች ለመሸርሸር ያልተሞከረና ያልተሰራ ነገር የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም። የኢትዮጵያ ህዝብን የሚያስተስሩት የጋራ ተቋማት አንድ በአንድ ለማፍረስና ኢትዮጵያዊ ስሜቱን ለማዳከም ሰፊ ጥራት ተደርጓል። የዚህ አንድ ማሳያ የህዳሴውን ግድብ ዋና ስራ አስከያጅ አርበኛው ኢንጅነር ስመኘው በቀለን በእጅ አዙር መንገድ ማስገደል ሳይበቃ፣ ግድቡ ለፖለቲካ ፍጆታ ተብሎ እንደተጠነሰሰና የቴክኒክ ችግር እንዳለበት በማስመስል የተሳሳተ መረጃ በመንዛት በጋራ መንፈስና በወኔ ተነሳስቶ የነበረውን የኢትዮጵያ ህዝብ ሞራሉ እንዲነካ ተደርጓል። ሌሎች በጋራ ሊያስተሳስሩት የሚችሉ የመሰረተ-ልማት ተቋማትም የማይረባ ምክንያት እየተፈለገ እየተስተጓጎሉ ይገኛሉ።

በኢትዮጵያውነትና በአንድነት ስም የሚዘምረው፣ መደመር በሚል የተምታታ እሳቤ የተሰባሰበው የነውጥ ኃይል በዚሁ ከመነገድ ባለፈ የኢትዮጵያውነትና የአንድነት ስሜት ይቅርና ሽታውም የሌለው ነው፡፡ ይህ ኃይል በፈጠረው የተዛባ ሁኔታ ኢትዮጵያውነትንና የአገር አንድነትን ከማንም ጊዜ በላይ ከባድ አደጋ ተጋርጦበት ይገኛል፡፡ ባለፉት አሃዳዊ መንግስታት እንኳ አገርን በሚያዋርድ ደረጃ ያልነበረው የውጭ ኃይላት ጣልቃ ገብነት አሁን ግን ጣልቃ ገብነቱ በሚያሳፍር ሁኔታ እንደጠራ ሰማይ ኮለል ብሎ ይታያል፡፡ አፄ ሚኒሊክ እንኳ ኤርትራንና ጅቡቲን ለሽያጭ ከማቅረባቸው ውጭ መላው ኢትዮጵያን ለባእዳን አሳልፈው አልሰጡም ነበር፡፡ እንደዚህ ዓይነቱ አጣብቂኝ ሲያጋጥምም ከቤተ‑መንግስታቸው ጀምሮ [የእቴጌ ጣይቱ ብጡልን ታሪክ ያስታውሷል] ተከላካይ ነበር፡፡አፄ ኃይለስላሴም ኤርትራን ወደ ኢትዮጵያ በማስመለስ ለአሜሪካ የጦር ሰፈር ግንባታ ብቻ ነበር የፈቀዱት፡፡ ደርግም ቢሆን የአሜሪካውን ቦታ በሶቭየት ሕብረት ጦር ሰፈር ነው የቀየረው፡፡ የአሁኑ አመራር ግን ከሞላ ጎደል ታላቋ ኢትዮጵያን ለምእራባውያን፣ ለግብፅና ለዓረቦች በችርቻሮ ዋጋ እያቀረባት ይገኛል፡፡

በአቶ መለስ ዜናዊ ህልፈት መላው ዓለም በተለይ የአፍሪቃ አገራት ጥልቅ ሀዘናቸውን ሲገልፁ ወደ ከበሮ ድለቃ የገቡት ግብፆችና የኤርትራ መሪዎች ብቻ ነበሩ፡፡ ግብፆች በነበረው ጠንካራ የኢህአዴግ አመራር በኢትዮጵያ ላይ ለሚያደርጉት ሴራ መፈናፈኛ አጥተው የነበረ ቢሆንም የመለስን ህልፈት የዘመናት ህልማቸውን ለመተግበር እንደ ምቹ አጋጣሚ ቆጥረውታል፡፡ በሂደት ለዚህ የሚመች የኢትዮጵያ አመራር ወደ መድረክ መምጣቱ ደግሞ በደስታ እንዲፈነድቁ አድርጓቸዋል፡፡ የኢንጅነር ስመኘው በቀለን ሞት ቃል በቃል “ታላቁ የህዳሴ ግድብ ሞተ’’ ብለው ነው ደስታቸውን የገለፁት፡፡ በቅርቡ ደግሞ ኢትዮጵያ ከእንግዲህ በኋላ እንኳንና የህዳሴ ግድብ ልታጠናቅቅ ቀርቶ አንድ ላይ ተሰባስባ ዳግም ለመነሳት ዓቅም የላትም፣ ብትሞክርም ብዙ አመታት ሊወስድባት ይችላል ብለው በኩራት ተንብየዋል፡፡ ለግብፆች እንዲህ ዓይነቱ የልብልብ እንዲሰማቸው ያደረገውና ለአገራዊ ውርደት የዳረገን ደግሞ ያው ኢትዮጵያ አሁን የፈጠረችው ድውይአመራሩ ነው፡፡

ይህ የጥፋት አመራር በተከተለው የነውጥ እንቅስቃሴ በሕብረተሰቡ ያደረሰው የስነ‑ልቦና ችግር በጣም ከባድ ነው፡፡ ነውጡ ያስከተለው ሞት፣ ውድመት፣ መፈናቀልና የቤተሰቦች መፍረስ ወዘተ… በሕብረተሰቡ አመለካከትና ስነ‑ልቦና ትልቅ ጠባሳ ፈጥሯል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ ወደ ነበረበት ለመመለስ እጅግ አስቸጋሪ ከመሆኑም በላይ ነገሮች ለማስተካከል የሚፈጀው ጊዜም ቀላል አይደለም፡፡ ይህ ጉዳይ ከባድ መሆኑ ጥቂት አብነቶችን በማንሳት ማየት ይቻላል፡፡

ያለፉት ነገስታትና በኋላም ደርግ በህዝቦች መካከል የፈጠሩት ቅራኔ ምን ያህል ዋጋ እንዳስከፈለን እኛ ኢትዮጵያውያን በደንብ የምናውቀው ጉዳይ ነው፡፡ በተለይ በአማራ ህዝብ ዘንድ የፈጠሩት የስነ‑ልቦና ችግር [አማራው ገበሬ የዚህ ክፉኛ ተሸካሚ ባይሆንም]ኢትዮጵያን የተሟላ መረጋጋት እንዳይኖራት ያደረገ ሲሆን በተለይ ለአማራው ደግሞ እስካሁን ድረስ ከባድ ዋጋ እያስከፈለው ይገኛል፡፡ በዚህ በኩል ኢህአዴግም ቢሆን ልማቱን እንጂ ከድሮዎቹ የተረከበውን የስነ‑ልቦና መዛባት ለማስተካከል የሰራው እምብዛም ነው፡፡ በኢህአዴግ ጉያ ተወሽቆ ችግሩን ያባባሰም አልታጣም፡፡

ሌላው አብነት ደግሞ የኤርትራውያን ወንድሞቻችን ጉዳይ ነው፡፡ ኤርትራን ያስተዳደሩት ምዕራባውያን ቅኝ ገዥዎች [በተለይ ኢጣልያ] ኤርትራን ከኢትዮጵያ ነጥለው ለመግዛት ሲሉ የነዙት የፖለቲካ መርዝ በኤርትራውያኑ መካከልና ከአጎራባች ወንድሞቻቸው ጋር በሚኖራቸው ግንኙነት ላይ ደንቃራ ሁናቴ ፈጥሯል፡፡ ይባስ ብሎም ኤርትራውያኑ ድርጅቶች ሳይቀሩ ለጠባብ ድርጅታዊ ጥቅም ሲሉ ይህንን የስነ‑ልቦና በሽታ በማጠናከራችው የተነሳ የኤርትራ ህዝብ [አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ በዚህ ብዙም የሚጠቃ ባይሆንም] እርስ በራሱም ሆነ ከኢትዮጵያውያን ወንድሞቹ ጋር በቀላሉ ለመግባባት ተቸግሯል፡፡ በዚህም ለነፃነቱ ሲል በ30 ዓመታት ትግል ሂደት ከባድ መስዋእትነት የከፈለው የኤርትራ ህዝብ ነፃ ባወጣው አገር ከአብራኩ በወጡ አምባገነኖችና አረመኔ መሪዎች ወደ አዲስ ባርነት ገብቶ እጅግ ዘግናኝ የሆነ ህይወት በመምራት ላይ ይገኛል፡፡

በመሆኑም የጥፋት አመራሩ በቀሰቀሰው ነውጥ በአገራችን እየተፈጠረ ያለው የስነ‑ልቦና ችግር እላይ ከተጠቀሱት አብነቶች የባሰ ዋጋ የሚያስከፍል እንደሆነ እንጂ አያንስም፡፡ በኢትዮጵያ ወደ መድረክ የመጣው የጥፋት አመራር በተከተለው የነውጥ መስመር ምክንያት የኢትዮጵያውያን ወርቃማ እሴቶች የሚባሉት ብሄራዊ አርበኝነት፣ መቻቻል ወዘተ… በአስገራሚና አስደንጋጭ ሁኔታ በመናድ ላይ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ባህላዊና ሃይማኖታዊ እሴቶች ለመሸርሸርና ለማዳከም በውጭ ኃይሎች ለዓመታት ሲሰራበት እንደቆየ ይታወቃል፡፡ አሁን ደግሞ የነውጥ እንቅስቃሴውን ተከተሎ በተፈጠረው አጋጣሚ ተበረታትተው ይበልጥ አጠናክረው ቀጥለውበታል፡፡ ዋና የፖለቲካና የመንግስት ስራው ትቶ በማያገባውም ጭምር እንደ እርጎ ዝንብ ጥልቅ የሚል የአገር ውስጥ ኃይል በማግኘታቸው ጊዜውን በሩጫ እየተጠቀሙበት ነው፡፡ የኢትዮጵያውያን ጠንካራ እሴቶች ለማጥፋት ነባሮቹን ሐይማኖቶች በተለይም ኦርቶዶክስንና እስልምናን ማዛባት የመረጡ ይመስላል፡፡ በአሁኑ ሰዓት በመንግስት ታግዞ በሁለቱ ቤተ እምነቶች የፖለቲካ ሽኩቻ ተጣጧፏል፡፡ መንግስት በቤተ እምነቶቹ አንጋሽ እስከመሆን የደረሰ ተግባር በይፋ ከታየ ሰንበትበት ብሏል፡፡ ይህ በዕርቀ ሰላም ሰበብ የሚደረገው ሕገ መንግስቱን የሚፃረር ድርጊት ሄዶ ሄዶ ከባድ ችግር ሊፈጥር የሚችል ነው፡፡ የነገሮች አዝማሚያም ጥሩ አይደለም፡፡ ብድምር ነገሮች በአጭር ጊዜ በመመሳቀላቸው በኢትዮጵያውያን ዘንድ ከባድ የስነ‑ልቦና ቁስል እየተፈጠረ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ለኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች ህዝቦች እጅግ ከባድ ዋጋ እያስከፈለ ይገኛል፡፡ ይህ ነገር በአስቸኳይ መፍትሔ ካልተበጀለትም ውጤቱ የባሰ ሊሆን ይችላል፡፡

በሌላ በኩል የአፍሪቃውያን የኩራትና የክብር ተምሳሌት የነበረችው ኢትዮጵያ ወደ እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ መግባትዋ ለአፍሪቃውያን ወንድሞቻችን ትልቅ የመንፈስ ስብራት ነው የፈጠረባቸው፡፡ በተለይ ትልቅ ተስፋ የጣሉብን ጎረቤቶቻችን በወቅታዊ ሁኔታችን በጣም አዝነዋል፣ ተስፋም ቆርጠዋል፡፡ ይሁንና እኛ ከችግራችን ወጥተን አብረን እንድናድግ ይፈልጋሉ፣ ተስፋቸውም ገና አልተሟጠጠም፡፡

በአጠቃላይ አዲሱ አመራር የነበረውን ስርዓትሆን ብሎ ለማፍረስና በሌላ ለመተካት ከአይዞህ ባዮቹ ጋር ቆርጦ የተነሳ ስለሆነ ዛሬ ተፀፅቶ ወደ ነበረው ይመለሳል ማለት ራስህን ማሞኘት ይሆናል። የጥፋት አመራሩ በምዕራባውያን ጌቶቹ የተሰጠውን ተልእኮ ዳር ሳያደርስ ይመለሳል ተብሎም አይታሰብም፤ አንዴ ማኖ አስይዘው በቁጥጥራቸው ስር አስገብተውታልና፡፡ይህንን የሚቃወም ሌላ ኃይል ተነስቶ ነገሮችን ወደ ነበሩበት ይመልሳል እንዳይባል ደግሞ በዚህ ብዙ በተመሰቃቀለበትና በተወሳሰበበት ሁኔታ ራሱን አደራጅቶና ዓቅም ፈጥሮ ወደ መፍትሔ የሚያሻግር ተግባር እስኪሚገባ ድረስ ሁኔታዎች ባልተገመተ ፍጥነት እየተቀያየሩ በመጓዝ ላይ ናቸው፡፡ህዝቡና በተለይ የአገራችን ምሁራን የጉዳዩን አሳሳቢነት በጥልቀት ተረድተው አገር ወዳድ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች በቶሎ እንዲጠናከሩ ካላገዙ በስተቀር ይህንን ሁኔታ በተፈለገው ጊዜና አኳኋን ይለወጣል ማለት እጅግ አዳጋች ነው። ለዚህም ነው በአገራችን ብሩህ ተስፋ እየጨለመ ያለው።ይህን ተከትሎ የሚመጣው መዘዝ ደግሞ ለትውልዶች የሚተርፍ ጠባሳ የሚተው በመሆኑ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ቆም ብሎ ነገሮችን ሊያስብ ይገባል፡፡ ይህ የጥፋት አመራር አገሪቱን ይዟት ከመጥፋቱ በፊት ድርጊቱን እንዴት ማቆም ይቻላል የሚለውን ጉዳይ እያንዳንዱ ሰው [በተለይ ምሁሩ]ወቅታዊ አጀንዳው አድርጎ ለመፍትሔ መነሳት አለበት፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያዊ ሆይ የነውጥ ማእበሉ ሳይጠራርግህ በፊት ጠራርገህ ለመጣል ራስህን በብቃት አዘጋጅ፡፡

ቸር እንሰንብት፡፡ 

 

                           ፈጣሪ ኢትዮጵያን ከጥፋት ይታደጋት !!!

 

 [1]“የስበት ማእከል’’ማለት በአንድ አካባቢ የሰፈረ ጦር ዋና ማዘዣና ኮር አመራሩ ያለበት ጣቢያን የሚገልፅ ሲሆን በትጥቅ ትግሉ ወቅት ህወሓት ሲጠቀምበት የነበረ የወታደራዊ ስልት ቋንቋ ነው፡፡

[2]“The Shock Doctrine:The Rise of Disaster Capitalism’’ በሚለው የናኦሚ ክሌን ምርጥ መፅሐፍ ውስጥ ከገፅ 25 ‑ 48 ያለውን በቀላሉ ማየት ይቻላል፡፡


Back to Front Page