Back to Front Page


Share This Article!
Share
ጣና ሃይቅና የትኩረት ችግሩ

ጣና ሃይቅና የትኩረት ችግሩ

ዶር. ዮሃንስ አበራ አየለ 2-13-19

ከሁለት አመት በፊት ትኩረትና እንክብካቤ ርቆት የቆየው ጣና ሃይቅ ድንገት መብረቅ የመታው ይመስል ጩኸትና ዋይታ ነገሰ። በህመም ሲማቅቅ ዞር ብለው ያላዩት ህመምተኛ ሞተ የተባለ ቀን "ካንተ በፊት ይድርገኝ" እያሉ ማላዘን ትዝብት ላይ ይጥላል። በዚህ ጉዳይ ላይ ሳትፅፍ ቆይተህ አሁን መፃፉ ምንድነው ያሰኛል። መልሱ ከዚህ የተሻለ ጊዜ ስላልነበረ ነው የሚል ነው። አሁን ምን ሆነ ስባል "አሁንም እንደበፊቱ ጣና ሃይቅ ስለተረሳ የመናገርያየ ሰአት ደርሷል" ብየ እመልሳለሁ።

በጣና ላይ እምቦጭ ተከሰተ በሚለው የካች አምናው ዜና እንደሌላው ያልተደናገጥኩት ቀደም ብየ ከስድስት አመት በፊት ባህርዳር ዮኒቨርሲቲ ውስጥ በተካሄደ ኮንፈረንስ ላይ አቶ ረዘነ ባቀረቡት ጥናታዊ ፅሁፍ ላይ ስለሰማሁት ነበር። ያኔ ደንግጫለሁ፣ ብዙ የተጋራኝ ሰው ግን አልነበረም። ከዛ ቀደም ብየ በኬንያ በኩል የቪክቶርያ ሃይቅን ወተር ሃያሲን (እምቦጭ) ጉዳት ስላየሁ፣ ቆቃ ሃይቅም ላይ አየው ስለነበር የሚከተለው ችግር ምን እንደሆነ ተገንዝቤ ስለነበር ነው።

Videos From Around The World

እምቦጭ ዝም ብሎ አይከሰትም። ከሃይቅ ተፋሰስ እንክብካቤ ጉድለት የሚመጣና በሃይቁ ላይ ትኩረት የሚያደርግ ተቋማዊ አወቃቀርና ችግር ፈቺ የምርምር ስርአት አለመዘርጋት የሚያባብሰው ነው። የሚያሳዝነው ነገር እንዲህ አይነት ተቋምና የምርምር ስርአት እንዳይኖር አድርገው የቆዩት የክልል ባለስልጣናትና ምሁራን እምቦጭ ጣናን አለበሰው ሲባል መጀመሪያ የታያቸው የአካባቢውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ህይወት ማሰናከሉ ሳይሆን የኦሮሞና የአማራ ፓርቲዎችን ለማጣመር የነበረው የፓለቲካ ፋይዳውን ነበር። "ጣና የኛ፤ ጣና ኬኛ" ተባለ። ይህን ጉደኛ ነገር ዝቅ ብየ ማሳለፍ ነበረብኝ። ይባስ ብሎ ይህን አገራዊ ተፈጥሮ ሃብት ሁሉም እንዲረባረብ ጥሪ እንደ ማድረግ ክልሉ የሰባት የክልሉ ዩኒቨርሲቲዎች ጉዳይ ብቻ አድርጎት አረፈ። ከሁሉም የከፋው ነገር ደግም በኢትዮጵያ የዉሃ ሃብት ላይ በአዋጅ ሙሉ ሃላፊነትና ስልጣን የተሰጠው የዉሃ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት የማይመለከተው መሰለ። ሃይቁን ለሃይል ማመንጫ ሲጠቀም ከጣና ሃይቅ ትራንስፓርት ጋር የነበረው ግብግብ የዘነጋው ይመስላል።

ጣና ሃይቁ፣ ተፋሰሱ ፣ ዋና ዋና ገባር ወንዞቹ 2/3ኛቸው የሚገኙት ጎንደር ውስጥ ነው። ለጣና ሃይቅ ባለቤትነት ስሜት ላይ ግን የጎጃሙ 1/3ኛ ያመዝናል። ጎጃምም ቢሆን ዋናው የህዝቡ አርማ አባይ ስለሆነ ጣና የሚታየው በአባይ ምንጭነቱ ነው። ለዚህም ይመስላል ከጎንደርም ከጎጃምም ጠበቅ ያለ ተቆርቋሪ ያጣው። በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ 17 አመት አስተምሬእለሁ። ሃይቁንና ተፋሰሱን እንደ እጄ መዳፍ በሚገባ አውቀዋለሁ። ከሙያም አንፃር፣ ተወላጅ ባልሆንም አገሬ ነው ብየ ከልብ አምንም ስለነበር የዩኒቨርሲቲውን ባለስልጣናት አስፈቅጄና በጀት ተመድቦልኝ "የጣና ሃይቅ ተፈጥሮ ሃብት ምርምር ማእከል" ብየ የሰየምኩትን ተቋም መሠረትኩ። የዚህ ተቋም አላማ ሴክተራዊ ሳይሆን የተቀናጀ ችግር ፈቺ ምርምር በማካሄድ የክልሉን መንግስት ማማከር ነበር። ከክልሉ የሚጠበቀው ጣና ተኮር የሆነ የተፈጥሮ ሃብት እንክብካቤ ተቋማዊ ስርአት ማዋቀር ነበር። ሰፊ የሆነ አለም፣ አገር፣ ክልል አቀፍ የማስተዋወቅ ዘመቻ ካደረግሁ በኋላ የአለም አቀፉ የሃይቆች ማህበር ትኩረት አገኘሁ። ብዙም ሳይዘገዩ የማህበሩ ፕሬዚዳንት ዶር. ዴቪድ ባርከር ከአሜሪካ ባህር ዳር ድረስ መጥተው የትብብር ስምምነት ተፈራረምን።

የምርምር ማእከሉ ዋና ተስፋ ግን የውጭ ድርጅት አልነበረም። በርግጥ ስለ ሃይቆች እንክብካቤ የምናገኘው ልምድ በቀላሉ የሚታይ አልነበረም። ይህ የቴክኒክ ትብብር እውን ሊሆን የሚችለው ግን ክልሉ ሲተባበር ብቻ ነው። በወቅቱ ይህን ጉዳይ በሚመለከት ለመተባበርም ላለመተባበርም ወሳኝ የመወሰን ስልጣን የነበራቸው ሁለት ሰዎች ነበሩ። አንዱ የክልሉ ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ዮሴፍ ረታ ናቸው፤ ሌላው የክልሉ ግብርና ምርምር ዲሬክተር የነበሩት ዶር. ጌቴ ዘለቀ ነበሩ። ከክልሉ ፕሬዚዳንት ጋር አንድ ጊዜ ብቻ በስብሰባ ላይ ተገናኝተናል። ከግብርና ምርምሩ ዲሬክተር ጋር ግን የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የግብርና ፋካልቲ ምስረታ ኮሚቴ ፀሃፊ ስለነበርኩ በትብብር አብረን እንሰራ ነበር። የጣና ሃይቅ ምርምር ማእከል በሚመለከት ከፍተኛ ድጋፍ አገኛለሁ፣የክልሉ ፕሬዚዳንትንም ያሳምኑልኛል ብየ ተስፋ ያደረግሁት በዶር. ጌቴ ላይ ነበር። የሆነው ግን በተቃራኒው ነበር። ዶር. ጌቴ የክልሉን ፕሬዚዳንት አቶ ዮሴፍ ረታን በማሳመን ለጣና ሃይቅ ምርምር ማእከል ድጋፍ እንዳይሰጡ አደረጓቸው። የዶር. ጌቴ ድርጊት ሙሉ በሙሉ በራስ ወዳድነት ላይ የተመሠረተ ነው። እሳቸው በሚመሩት በክልሉ ግብርና ምርምር ስር የጣና ሃይቅ አሳ ምርምር ማእከል ነበር። ብዙ የምርምር ገንዘብ ድጋፍ የሚጎርፍለት ብቸኛ ማእከል ነበር። የማእከሉ ምርምር ትኩረት ግን በአጠቃላይ የጣና ሃይቅና ተፋሰሱ ተፈጥሮ ሃብት እንክብካቤ ጥናት ላይ ሳይሆን በአሳ ላይ ብቻ ነው። ከአሳውም ተመርጦ "ባርብ" በሚባል የአሳ ዝርያ ላይ ያተኮረ ነበር። እኔ የመሠረትኩት የጣና ሃይቅ ምርምር ማእከል ተገቢ ባልሆነ መንገድ እንደተቀናቃኝ ቆጠሩት። የክልሉ ፕሬዚደንት ይሁንታ ካገኙ በኋላ እኔ የፈጠርኩትን ማእከል ለማፍረስ የመምህራና የዩኒቨርሲቲው ማኔጅመንት ትብብር ማግኘት ጀመሩ። በዛ አላበቃም። በኔ ላይም የማግለል ዘመቻ ተጀመረ። ለስኬታቸው የረዳቸው የአላማቸው ትክክለኛነት ሳይሆን የኔ ተወላጅ አለመሆን ነበር።

ከሁሉም እኔን የገረመኝ የክልሉ ፕሬዚደንት ተግባር ነበር። ስለ ጣና ሃይቅ ምርምር ማእከል አላማ እንዲረዱ ብየ በራሪ ወረቀት (ብሮሸር) በክብር የላክሁላቸው እኔ ነበርኩ። እኔን ጠርቶ ከማነጋገርና ሃቁን ከባለቤቱ አፍ ከመረዳት ይልቅ ለምን ከሌላ ሰው ሰምተው ለውሳኔ እንደቸኮሉ ነው። ጣና ሃይቅ የጋራ ሃብታችን እንጂ የዮሃንስ የግል ንብረት አልነበረም። እኔም በእንክብካቤ እጥረት አሁን የተከሰተው ችግር እንዳይመጣ በመስጋት ነበር እንጂ በግሌ የምጎዳው ነገር አልነበረኝም።

የተፈጠረውን ችግር ለአለም አቀፍ ሃይቆች ማህበር ሪፓርት በማድረግ የመልቀቂያ ደብዳቤ አቅርቤ የፈጠርኩትን ማእከል ሃላፊነት አስረከብኩ። ከዛም በኋላ ወደ አዲስ አበባ ተዛወርኩ። ከትንሽ ቆይታ በኋላ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የመሠረትኩትን የጣና ሃይቅ ማእከል አፍርሶ "የብሉ ናይል ዉሃ ተቋም" የሚባል የምርምር ማእከል በምትኩ አቋቋመ። እግዚአብሄር ያሳያችሁ። ባህር ዳር ውስጥ ያለ ዩኒቨርሲቲ አጠገቡ ያለውን ሃይቅ ችላ ብሎ ጨርሶ የማይመለከተው ስራ ላይ ተሰማራ። በኢትዩጵያ ውስጥ "ብሉ ናይል" የሚባል ወንዝ የለም። ብሉ ናይል የሚገኘው ሱዳን ውስጥ ነው።ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አባይ ነው። ቀለም ይሰጠው ከተባለ አባይ ድፍርስ ቡኒ እንጂ ሰማያዊ አይደለም። ብሉ ናይልን ካርቱም ላይ አይቼዋለሁ። እውነትም ስማያዊ ነው። ሜዳማ ስለሆነ ደለሉ ወደታች ዘቅጦ ስለሚረጋጋ ነው ሰማያዊ የሆነው።  ወንዞቻችንን ለብራም የፈረኝጅ ተመራማሪ እንዲጥም አድርገን የምንሰይማቸው ከሆነ ባሮን ጁባ፣ ተከዘን አትባራ እንበላቸዋ። አላማችን ለብዙ ህዝብ አገልግሎት የሚሰጠውን የተፈጥሮ ሃብት መንከባከክ ከሆነ መቸም በምንም ተአምር የጣና ሃይቅን ማእከል አፍርሰን በናይል ማእከል አንተካውም። እንኳንና ናይል አባይም ቢሆን ለአካባቢው ህዝብ የጣና ሃይቅ ያህል አገልግሎት አይሰጥም። አባይ ለጎጃም ህዝብ የጠቀመው ምንድነው? ለመስኖ አይጠቀምበት፤ ከጥቃት ሲከላከለት የኖረ መከታ በመሆኑ በህዝቡ ዘንድ ሞገስ ከማግኘቱ በስተቀር። በናይል ጉዳይ ላይ መረጃ የሚፈልገው ባመዛኙ በውጭ አገር ያሉ ተቋማት ናቸው። የምርምር ገንዘብ በቀላሉ የሚያገኙትም እነሱ ናቸው። የምርምር ትኩረታችን በገንዘብ አቅርቦት እንጂ በአስፈላጊነት የሚነዳ ካልሆነ ለምርምር ትልቅ ተግባራዊ ውድቀት ለምሁራንም ትልቅ የህሊና ገደል ነው። "እንዳያማህ ጥራው ፣ እንዳይበላ ግፋው" ሆነና በባህርዳር ዩኒቨርሲቲው የብሉ ናይል ተቋም ውስጥ ጣና ሃይቅ "የናይል ንኡስ ተፋሰስ" ተብሎ እንዲዳበል ተደርጓል። ወይ መቸገር!!

ይህን ስል በጣና ሃይቅና ተፋሰስ ላይ ምርምር አይደረግም ማለት አይደለም። ምርምሩ ግን የተቀናጀና ችግር ፈቺ ሳይሆን ተበጣጠሰና የተደጋገመ ነው። አብዛኝው ምርምር ለማስትሬትና ዶክትሬት ዲግሪ መመረቅያ፣ በጆርናል ላይ አሳትሞ የደረጃ እድገት ለማግኛ፣ ለኮንሳልታንሲ ስራ፣ ለፕሮጀክቶች፣ ወዘተ ነው። የስኮላር ጉግል መፈለጊያ ላይ "ጣና ሃይቅ ተፋሰስ" ብሎ በማስገባት የሚገኘው ውጤት የተጠቀሱትን (ሳይቴሽንስ) ሳይጨምር ወደ 400 የምርምር ውጤቶችን ያሳያል። ይህ ሁሉ ግን በስነ ውሃ፣ በደለልና መሬት መሸርሸር፣ በአሳና ምግቡ፣ በመሬት አጠቃቀም፣ በዳርቻ ላይ እርጥብ መሬቶች፣ በሌሎችም የተደጋገሙ ምርምሮች ተካሂደዋል። ሆኖም ግን ጣና ሃይቅ የሚያስፈልገው ምርምር መኪና ሆኖ የቀረበውን እንጂ ስፔር ፓርት ሱቅ ውስጥ እንዳለ የመኪና መለዋወጫዎች ክምር ሆኖ አይደለም።

ሃረማያ ሃይቅ የደረቀው ሃረማያ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ባሉ ምሁራን ስለ አደራረቅ ሂደቱ ምርምርና አውደጥናት እየተካሄደ እያለ ነው።  ከደረቀ በኋላም ስለ አሞላሉ ምርምርና አውደጥናት እየተካሄደ እንደሆነ በወሬ ደረጃ ይነገራል። ጣና ሃይቅ በአረም የተሞላው  "በናይል ንኡስ ተፋሰሱ" ላይ ምርምርና አውደጥናት እየተካሄደ እያለ ነው። አሁንም እምቦጭ ከወረረው በኋላ ምርምርና አውደጥናት ቀጥሏል። እምቦጩን በጥንዚዛ! ከእምቦጭ ሳይሆን ከጥንዚዛ አደጋ ተጠንቀቁ!

አባያ ሃይቅ ላይ 2000 ሄክታር እምቦጭ ተከስቷል ተባለ። አሁንም ቄሱም መፅሃፉም ዝም ሆኗል። ከአምስት አመት በኋላ አባያ ሃይቅ  "የእምቦጭ መብረቅ መታው" ተብሎ ደግሞ እንደ ጣና ሃይቅ ዳሱ እስኪፈርስ ድረስ ዋይ ዋይ እንላለን።

 

Back to Front Page