Back to Front Page

የኮ/ል ዓብይ አስገራሚው የሹመት አሰጣጥ፣

የኮ/ል ዓብይ አስገራሚው የሹመት አሰጣጥ፣

አጀንዳ ማስቀየር ወይስ የትልቁ እቅድ አካል ነው?

 

ክፍል አንድ

 

ዑስማን ሙሉዓለም 7-6-19

 

ይህ የመረጃ መጣጥፍ ሁለት ክፍል አለው፡፡ በክፍል አንድ አዲሱ ኤታማዦር ማን ናቸው? አዲሱ የድህንነት ሹምስ? አዲሱ የልዩ ሃይል አዛዥስ? በሚሉት ላይ ታማኝ ምንጮች በመጠቀም እንደሚከተለው ተከትባል፡፡ መልካም ንባብ!  ለአስተያየትና ተጨማሪ መረጃ ለመላክ osman.mulualem@yahoo.com ይጠቀሙ፡፡ 

 

አዲሱ ኤታማዦር ሹም ጄነራል አደም ማን ናቸው?

ጄነራል አደም ነባር የብአዴን ታጋይ የነበሩ ናቸው። በብአዴን ውስጥ የታምራት ላይኔ ሬድዮ ኦፕሬተር ሆነው ካገለገሉ በኃላ የድርጅቱ ሠራዊት ምልክት መምርያ ኃላፊ ሆነው ሰርተዋል። ፋሽስት ደርግ ከተገረሰሰ በኃላ የኢትዮጵያ አየር ሐይል እንደ አዲስ ሲመሰረት ለአብራሪነት ዕጩ ሆነው በተዋጊ ሄሊኮፕተር አብራሪነት ሰልጥነው ከተመረቁት የመጀመሪያ ሰልጣኞች አንዱ ነበሩ። ከስልጠናው በኃላ የሄሊኮፕተር ስካድሮን/ክንፉ አስተባባሪ በመሆን መርተዋል። በኢሳያስ መንግስት ወራራ ወቅትም በተዋጊ ሄሊኮፕተር ሰራዊቱን የተኮስ ድጋፍ በመስጠት በጅግንነት ተዋግተዋል።

 

Videos From Around The World

ለማሰታወስ ያክል የኢትዮጵያ አየር ሐይል በአዲስ መልክ ከተዋቀረ በኃላ   ሲመሩ የነበሩት ጄነራሎች በቅድመ ተከተል አበበ ጆቤ፣ ሃይለ ጥላሁን፣ አለምሸት ደግፌ፣ ሞላ፣ በመጨረሻ ደግሞ ጄነራል አደም ነበሩ። የጄነራል አደም መምጣት በብቃት ሳይሆን መከላከያ ውስጥ በወቅቱ ተፈጥሮ በነበረው የአመራር ክፍፍል ጄነራል ሳሞራ ሌፊተናንት ጄነራል ሞላ ሃይለማሪምንን ለማግለል ያደረጉት ሹም ሽር እንደነበር ነው የሚታወቀው። በወቅቱ ኤታማዦር ሹሙ በግለቂም ጄነራል ሰዓረን ዝቅ አድርገው መደበው ጄነራል አበባው ታደሰን፣ ጄነራል ገዛኢ አበራንና ጄነራል ባጫን ከነሙሉ ብቃታቸው በጡረታ አገለሉቸው። በተቃራኒው ደግሞ ብቃት የሌላቸውን ጄነራል አደምን የማይመጥናቸው ሓላፊነት አሸከሟቸው። አየር ሐይሉ በጄነራል አደም ወቅት በከፍተኛ ደረጃ የተዳከመበትና ብዙ ብቃት የነበራቸው የአየር ሐይሉ አባላት  ወደ ጠላት እየከዱ የሄዱበትና ውጭ ሲሄዱ ደግሞ የሚቀሩበት ሁኔታ ነበር። ይህ ሁኔታ ጄነራል አደም ብቻ የሚጠየቁበት ሳይሆን በዋናነት የያኔው ኤታማዦር ሹም ጄነራል ሳሞራ የኑስ ሊጠየቁበት የሚገባ ነበር። እንደመረጃ ምንጮቻችን ከሆነ ከዚያን ግዜ በኃላ የአገሪቱ መከላከያ አመራር  ውስጡ እየታመሰ ቆይቷል።

 

ጠቅላይ ሚኒስተር ሀይለማርያም በስልጣናቸው የመጨረሻ ዘመን መመዘኛው ግልፅ ያልሆነ የሙሉ ጄነራልነት መዓርግ ለአራት ከፍተኛ መኮነኖች ሰጡ። ለጄነራል ሰዓረ መኮነን፣ ለጄነራል አብርሃ ወልደማርያም፣ ለጄነራል ብርሃኑ ጁላና ለጄነራል አደም፡፡ ምንጮቻችን እንዲሚሉት በወቅቱ ትችት ተስጥቶት የነበረው ጉዳይ የጄነራል አደም መዓርግ መጨመር ነበር። ብቃታቸውና ጠቅላላ የስራ አፈፃፀማቸው ደካማ እያለ እንዴት የማዕርግ ዕድገት ያገኛሉ በሚል። ጄነራል ሰዓረና ጄነራል ብርሃኑ ጁላ ምክትል ኤታማዦር ሲሆኑ ጄነራል አደም በነበሩበት አየር ሐይል ቀጠሉ። ሆኖም ግን በምደባው ደስተኛ እንዳልነበሩ ነው የሚገለፀው።

 

የኮ/ል ዓብይ ወደ ስልጣን መምጣት ተከትሎ በመከላከያ የኤታማዦር ሹምና   በደህንነት መስርያቤትም ዳይርክተር ለውጥ ሲደረግ ጄነራል አደም የደህንነት መስሪያቤት ሐላፊ ሆነው ተሾሙ። ይህ ስልጣን ያገኙት ደመቀ መኮንን የኢህአዴግ ሊቀመንበርና ቀጣይ ጠቅላይ ሚኒስተር ሆነው እንዲመረጡ ቀን ተለሊት ሲንቀሳቀሱ ስለነበረና ምንም እንካን የምረጥዋቸው እንቅስቃስያቸው ባይሳካም ለዚህ ስራቸው የብአዴኑ ሊቀመንበር ውለታ እንደዋሉላቸው ይነገራል።  እዚህ ላይ ያኔ  አጋጥሞ ነበር  የተባለው ክስተት እንዲህ ነው በወቅቱ ደመቀ መኮንን በኦሮሞ ፖለቲኮኞች በተለይ ደግሞ ኦህዴድ ውስጥ ተሰሚነት አላቸውና ቀስቅሳቸው ብሎ ጄነራል አደምን ጄነራል ባጫ ጋር  ይልከዋል። ጄነራል ባጫም ኦሮሞው ኮ/ል ዓብይ እንዲመረጥ ይንቀሳቀሱ ስለነበር በጄነራል አደም ድፍረት ተናዶው እንዲህ አሉዋቸው አሉ። ጄነራል አደም ያለአቅምህ የተሸከምከውና ትክሻህ ላይ የተጫኑቡህ ኮከቦች መጀመርያ አይመጥኑኝም ብለህ ጣላቸው። እንዴት ስትደፍር ነው እኔን ደመቀ መኮንን እንምረጥ የምትለኝ? በምን አቅሙ ነው የሚመራው? ከማለት አልፎው ጥፋ ከፊቴ እንዳልዋቸው  ይነገራል። ይሁን እንጂ በግርግር የአገሪቱ ቁልፍ ቦታ ላይ ዳይርክተር ሆኖው ተሾሙ ።

 

በስራቸው ደግሞ ሁለት የኦህዴድና የደኢህዴድ ማእከላይ ኮሚቴና የኢህአዴግ ምክር ቤት አባላት ተሾሙ። በአደባባይ የፓርቲ አመራር በደህንነት መስሪያቤቱ ከአሁን በኃላ አይኖርም ብለው የድሮውን ደህንነት መስሪያቤት የወቀሱት ጄነራል እስከ በጥቃት አደጋ የሞቱትን ኤታማዦር ሹሙ ጄነራል ሰዓረን ተክተው እስኪቀየሩ ድረስ መስሪያቤቱን ከፓርቲ አመራር ሳያፀዱ ቆይተዋል። ለነገሩ እንኳን ሊያፀዱ በደህንነት መስሪያቤቱ ምንም ስልጣን እንዳልነበራቸው ነው የሚነገረው፡፡ ከሳቸው ይልቅ ምክትላቸው የኦህዴዱ ማእከላይ ኮሚቴ አባል ደምመላሽ ነበር የሚፈራውና ስልጣኑን የተቆጣጠረው።

 

እነዚህ ሰዎች የደህንነት መስርያ ቤቱንም ምንም መረጃ መሰብሰብ የማይችልና ደካማ አደረጉት። አገሪቱ በሰላም እጦት ስትታመስ ምንም የመፍትሔ አስተዋፅኦ የማያደርግ መስሪያቤት ሆነ። የውጭ ሐይሎች የአገራችን ሉዓላዊነት እንደፈለጉ የሚደፈሩበት ሁኔታ ተፈጠረ። የኢንጅነር ስመኛው አገዳደል ሳይጣራ ቀረ። የኢሳያስ ሰላዮች እነ ኮ/ል ፍፁም አዲስ አበባ እየኖሩ ያሻቸውን ሲያደርጉ፣ ኤርትራውያን ዲያስፖራ ሲገድሉና ተጠልፈው ሲወስዱ የሚጠይቃቸው የለም። በቅርቡ ደግሞ በሽብርተኘነት ተፈርዶባቸው በስመ ምህረት የተለቀቁ እነ አሳምነው በሚስጥር ሲያቅዱ ቆይተው በከፍተኛ የክልል ባለስልጣኖችንና ጄነራሎችን ግድያ ሲፈፅሙ መስሪያቤቱ ምንም የሚያውቀው አልነበረም። ወይም ደግሞ ቢያውቅም ግድያው አላከሸፈም። ጄነራል አደም በመስሪያቤቱ ቆይታቸው በስራም ሳይቀናቸው፣ ከምክትላቸው የስልጣን ሽኩቻና ከላይም ተሰሚነት በማጣታቸው ደስተኛ አልነበሩም ይባላል። በተፈፀመው የደህንነት ቀውስ መጠየቅ ሲገባቸው አሁን ደግሞ ኤታማዦር ሆነው ተሾሙ። አሁን ተገላገሉ ነው የሚባለው ወይስ ሌላ ጣጣ ውስጥ ገቡ፡፡ አይታወቅም ብቻ ከደምመላሽ ምክትላቸው ሹክቻና ንትርክ ግን ነፃ ወጡ።

 

አዲሱ የድህንነት ሹም አቶ ደምመላሽ ገብረሚካኤል ማን ናቸው?

የኦህዴድ የበላይ አመራርና ካድሬ ሆነው በኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን በተለያዩ ሐላፊነት ያገለገሉ ናቸው። በኃላም ወደ ፌደራል ፖሊስ ተዛውረው በመምርያ ሐላፊነት ሰርተዋል። በኦህዴድ የለማ ቲም/ቡዱን የበላይነት ባገኘበት ወቅት አቶ ደምመላሽ ወደ ኦሮሚያ ክልል ተዛውረው የፀጥታ ዘርፉን እንዲመሩ ተሸሞው ነበር። በዚህ ወቅት የለማ ቲም የኦሮሞ ጥቅም ተጎድቶ ቆይቷል በሚል ከሁሉም የሚያዋስኑት ክልሎች ግጭት ሲፈጥር አቶ ደምመላሽ ቅድመ ግንባር አስፈፃሚ ነበሩ። ከሶማሊ ክልል ጋር ግጭት በተፈጠረ ወቅት የዘመቻ ሐላፊ ሆነው ልዩ ሐይላቸውና ሚሊሻው አሰማርተው ለብዙ ሰው ሞትና መቁሰል ምክንያት የሆነውን ጦርነት ከነ ለማና ዓብይ በመሆን መርተዋል። ከሁለቱም ክልሎች ወደ ሚልዮን የሚጠጋ ህዝብ ተፈናቅሎ ችግር ላይ እንዲወድቅ ያደረጉና ግፍ የፈፀሙ ሰው ናቸው። በኃላም በአወዳይና በገለምሶ በሶማሊዎች ላይ ጆኖሳይድ የፈፀሙ ሰው ናቸው። በተለይም የገለምሶው እሳቸው ሲመሩት በነበረው ፖሊስ ጣብያ እስር ቤት የነበሩ ሰዎች ሶማሊ በመሆናቸው ብቻ ሴቶች ከህፃናት ልጆቻቸው ሳይቀሩ ስልሳ የሚደርሱ ሰዎችን ረሽነው ገድለው በአንድ ጉድጋድ ቆፍረው እንዲቀበሩ ያደረጉ ሰው ናቸው። በወቅቱ የጆኖሳይድ ድርጊቱ ተጣርቶ የፍርድቤት መያዣ ትዕዛዝ ወጥቶባቸው የነበረ ቢሆንም እሳቸውና ሌሎች በጉዳዩ ተጠያቂ የሆኑት በነለማ፣ ዓብይ ተባባሪነትና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ወርቅነህ ገበየሁ አማካይነት ወደ ደቡብ ኮርያ ወጥተው እንዲቆዩ ተደርጎ የለማ ቲም በፌደራል መንግስት የበላይነት ሲያገኝ የተመለሱ ናቸው።

 

ኮ/ል ዓብይ ስልጣን ከያዙ በኃላ አቶ ደምመላሽ የጄነራል አደም ምክትል ሆነው ተሾሙ። በኦህዴድ ጉባኤም ማእከላይ ኮሚቴ ሆነው ለመጀመርያ ጊዜ ተመረጡ። ደምመላሽ በለፈው አመት ምክትል ዳይርክተር ቢሆኑም ከጄነራል አደም በላይ  በሁሉም የሚፈሩና ተሰሚነት የነበራቸው እሳቸው ነበሩ። በመጀመሪያ ደረጃ ዋና ስራቸው ያደረጉትም በመስሪያቤቱ ለበርካታ አመታት ለአገራቸው በቅንነት አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩና ከፍተኛ ሙያ ያላቸውን ሰራተኞች በቂም በቀል ማጥቃት፣ የውሸት ወንጀል ፈጥሮ ማሰር፣ ማባረር እና በምትኩ በግልፅ ችሎታ ይኑራቸው አይኑራቸው ያልታወቁ ሰዎች ኦሮሞዎች በመሆናቸው ብቻ ቁልፍ ቦታ ላይ መመደብ ነበር። በዋና የመስሪያቤቱ ተልእኮና ግዳጅ መፈፀም ያልቀናቸው ቢሆንም የመስሪያቤቱ ገፅታ በማበላሸትና አባላቱ ላይ በተለይም በትግራይ ተወላጆች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት በመፈፀም ትልቅ ሚና ተጫውተዋል። ቀንቷቸዋልም። ጄነራል አደም በመኖራቸው እንደፈለጉት መረን ለቀው ያሻቸውን እንዳይፈፅሙ በመጠኑም ቢሆን ተገድበው የነበሩት አዲሱ ሹም ብቻቸው ስልጣን ሲይዙ ምን እንደሚያደርጉ መገመት ይቻላል።  

 

የአዲስ ምድብ አዲስ ተሿሚ የምድር ጦር አዛዥ ሌፊተናንት ጄነራል ሞላ ሃይለማርያም ማን ናቸው?

ጄነራል ሞላ የህወሓት ነባር ታጋይ የነበሩና በትግሉ ወቅት በተለያዩ የሰራዊት ደረጃ ሐላፊ ሆነው የታገሉና ደርግ ሲደመሰስ የክ/ጦር ኮሚሳር የነበሩ ናቸው። በኃላም የሐውዜን ክፍለጦር አዛዥ ሆነው ነበር። ከለጋ ወጣትነት ዕድሚያቸው ጀምረው ፀረ ፋሽስቱ ደርግ በተደረገ ጦርነት በብዙ ውጊያዎች ተዋግተዋል አዋግተዋል።

 

ከደርግ መገርሰስ በኃላ የአየር ሐይል እንደገና ለማዋቀር በተደረገ እንቅስቃሴም ተመልምለው በነበራቸው ዝጉጁነትና ብቃት የተዋጊ አውሮፕላን ትምህርት/ስልጠና ወስደው የራሽያ ስሪት የነበሩትን ሁሉንም ሚግ አውሮፕላኖችን ማብረር ችለዋል። በኃላም ሱከይ ሃያ ሰባት የተባሉ ዘመናዊ የራሽያ ሚግ አውሮፕላኖች ሲገዙ እሳቸው ሰልጥነው ሲያበሩ ነበር። የኢሳያስ መንግስት በኢትዮጵያ ወረራ በፈፀመበት ወቅት ጄነራል ሞላ በተዋጊ አውሮፕላን ተዋግተዋል። ለእግረኛ ሰራዊታችን የተኩስ ድጋፍ በማድረግ አየር ሐይላችን ያደረገው ጀብድ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል።

 

ጄነራል ሞላ እስከ በጄነራል አደም እስከሚተኩ ድረስ በአየር ሐይል በተለያዩ የሐላፊነት ደረጀና በምክትል አዛዥነት ሲያገለግሉ ቆይተዋል። ጄነራል  አለምሸት ከአየር ሐይል አዛዥነት እንደተነሱ የተኩዋቸው ጄነራል ሞላ ነበሩ። ጄነራል  ሞላ የተዋጊ አውሮፕላን አብራሪ የነበሩ በመሆናቸው የአየር ሐይል አዛዥ ሆነው መሾማቸው በአየር ሐይሉ አባላት ክብርና ተቀባይነት አገኙ። መጀመርያ አካባቢ አየር ሐይሉን ያነቃቁት ቢሆንም ከጄነራል ሳሞራ ጋር ስምምነት ስላልነበራቸው ስራቸውን በአግባቡ ለመስራት አልቻሉም። አልታገዝኩም በሚል ሰበብ ደካማ የስራ እንቅስቃሴ ያደርጉ እንደነበር ይገለፃል። በኃላም ያለመስማማቱ ወደ ጥቃት ተሸጋግሮ  ከኃላፍነታቸው ተነስተው ያለስራ እንዲቀመጡ ተደረገ። ቀይቶ ደግሞ ወደ የተባበሩት መንግስታት ተልእኮ ተሰጥቶቸው በደቡብ ሱዳን ሰርተዋል። ይህ ተልእኮ እሳቸውን ለማግለል የተደረገ ምደባ ነበር። የተሰጣቸው ተልእኮ ፈፅመው እንደተመለሱ የሚመደቡበት ቦታ ተፈልጎ በመከላከያ ሚንስትሩ (በአቶ ስራጅ) ስር ሆነው የጥናትና ምርምር ስራ እንዲሰሩ ተመደቡ። ጄነራል ሳሞራ ሊያይዋቸውም ጭምር አይፈልጉም ነበርና።  በተጨማሪም በማናቸውም መለክያ ከእሳቸው በታች የነበሩት የሙሉ ጄነራልነት መዓረግ ሲያገኙ እሳቸውን ሆን ተብሎ በነበሩበት እንዲቆዩ ተወሰነባቸው። ያኔ ሌፊተናንት ጄነራሉ  ተበድለዋል ብሎም የቆመላቸው ሰው አልነበረም ይባላል።

 

ኮ/ል ዓብይ ስልጣን ሲይዙ ይህን ሁሉ ስለሚያውቁ ማረም ሲገባቸው ለራሳቸው ዓላማ ተጠቀሙበት። ስልጣን እንደያዙ ጄነራል ሳሞራ እያለም ጄነራል ሞላን እያስጠሩ ጥናት እንዲያደርጉላቸውና ምክረሃሳብ እንዲያቀርቡ ያዝዋቸው ነበር። በዛውም ተበድለህ ቆይተሃል። እኔ ግን ደረስኩልህ አሉዋቸው። ጄ/ል ሳሞራን በጥበብ ከሸኝዋቸውም በኃላም ጄነራል ሞላ የኮ/ል ዓብይ የቅርብ ሰው ሆነው ቀጠሉ። በዚህም በአብዛኛው የሰራዊት አባል ይታማሉ። በተለይም የልዩ ሐይል አዛዥ ተደርገው ሲሾሙ ትልቅ ትዝብት ላይ ወደቁ። አሁን ደግሞ ለሳቸው ተብሎ በወጣ አዲስ አደረጃጀት (አደረጃጀቱና መዋቕሩ ሳይታወጅ) አዛዡ ተብለው ጄነራል  ሞላ ተሾሙ።

 

ብክፍል ሁለት ለምን እነዚህ ተሾሙ? አንድምታውስ ምንድነው? የሚለውን አቀርባለሁ። ቸር ሰንብቱ።

 

ዑስማን ሙሉዓለም

ከሓራ ገበያ

 

Back to Front Page